Thursday, November 17, 2011

መቅደሱ ሊሠራ የጠላት ፉከራ

Read pdf 
ኀሙስ፣ ኅዳር 7/ 2004
ከጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊ ጥር 41


የእግዚአብሔር ሕዝብ ውድቀት የሚጀምረው የእግዚአብሔርን ዐሳብ ከማገልገል ሲወጣ ነው። እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ የፈጠረን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነት ያዳነንም ለፈቃዱ እንድንገዛ ነው። ስለዚህ ክብራችንም ሆነ ውድቀታችን ለእርሱ በመገዛታችንና ባለመገዛታችን ይወሰናል።

የእግዚአብሔርን ሥራ መሥራት እንዲህ በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም። ሥራው የሚጠይቀው የራሱ መስፈርቶች አሉት፤ በራሱ በእግዚአብሔር መጠራት፣ የአገልግሎት ጸጋ እና የተሰጠ ማንነት ያስፈልጋሉ። ከነዚህ መስፈርቶች ውስጥ ሁለቱ ከእግዚአብሔር ሲሆኑ፥ ሦስተኛው ግን የተጠራው አካል ድርሻ ነው። እግዚአብሔርም በዘመናት የሚሠራው በዚህ መንገድ ነው። የሥራው ባለቤት፣ ሠራዒው እንዲሁም መከናወንን የሚሰጠው ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም፥ በሥራው ውስጥ እንድንሳተፍና የክብሩ ተካፋይ እንድንሆን ይፈልጋል። 

መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ጥሪ፣ በተሰጣቸው የአገልግሎት ጸጋና ራሳቸውንም በመስጠት የእርሱን አሳብ ስላገለገሉ ሰዎች ይነግረናል። ከእነዚህም መካከል ከሰባ ዓመት የባቢሎን ምርኮ በኋላ ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ የተጠሩት ወገኖች ይገኙበታል። እነዚህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የእግዚአብሔር ጥሪ ሲደርሳቸው፥ ራሳቸውን በመስጠት ለሥራው ተሰልፈው ነበር፤ ቃሉም፥ “የይሁዳና የብንያም የአባቶችም ቤቶች አለቆችም ካህናቱም ሌዋውያኑም በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ” ይላል (ዕዝ. 1፥5)።

እነዚህን ወገኖች ለእግዚአብሔር ቤት ሥራ ያነሣሣቸው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ይህም የእርሱን ሥራ ለመሥራት ጥሪ ያስፈልጋል የተባለውን እውነት ያረጋግጣል። ከዚህ ሌላ ጥሪው ሲደርሳቸው በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ውስጥ እያንዳንዳቸው ድርሻ ነበራቸው። ይህም ለአገልግሎት ጸጋ እንደሚያስፈልግ ይጠቊማል። እነርሱም ለሥራውም የተሰጡ ነበሩ።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ሥራው ያለተግዳሮትና ያለጠላት ተቃውሞ የተሠራ አልነበረም። የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ሲሠራ ጠላት ዝም ብሎ አያይም። ሥራውን ማስቆም ባይችል እንኳ ለማዘግየት የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማል፤ ጠላታችን የተሸነፈ እንጂ የሞተ አይደለምና።

ለመቅደሱ ሥራ በዋነኛነት የተጠሩት የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፣ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፣ ካህኑ ዕዝራና ሌሎችም ለዚህ ሥራ የተጠሩ ነበሩ፡፡ አምላካዊ ጥሪ የደረሳቸውና የተስፋ ቃል የተሰጣቸው እነዚህ ወገኖች የፈረሰውን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ሲነሡና ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ ቤተ መቅደሱ እንዳይሠራ ጠላት በገዢዎቹና በጊዜው በነበሩ ወገኖች አማካይነት መቃወም ጀመረ። የጠላት ፉከራና ዛቻ ግን የመቅደሱን ሥራ አላስተጓጐለውም፡፡ ጠላት ስም በማጥፋት ዘመቻ ታጥቆ በመነሣት ለነገሥታቱ ደብዳቤ በማጻፍ፥ የቅጥሩ መሠራት የቤተ መቅደሱ መታነጽ ችግር እንደሚፈጥር ቢወተውትም፥ የእግዚአብሔር ዐሳብ አይከለከልምና፥ የገዢዎቹ ውትወታ የነገሥታቱን ልብ ሊማርክ አልቻለም። እንዲያውም ነገሥታቱ መቅደሱ እንዲሠራ ብቻ ሳይሆን ለሥራው አስፈላጊውን ሁሉ ከመዝገባቸው አውጥተው በመስጠት እንዲተባበሩ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር (ዕዝ. 1፥1-4፤ 6፥6-12 ፤ 7፥20-22) የአባቶቻችን አምላክ ይባረክ!!

በዘመናችንም የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ጥሪው ሲደርሰንና ሥራው ሲሠራ የጠላት ተግዳሮትና ፉከራ ይኖራል። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ዐሳብ ስለማይከለከል ሥራውን ለማስተጓጐል፥ ሠራተኞቹንም ለመቃወም ጠላት ቢሰለፍም የተጀመረው ታላቅ ሥራ ግን አይቆምም፤ ይፈጸማል።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ችግር ዛሬ የጀመረ ሳይሆን፥ በርካታ ምእት ዓመታትን ያስቈጠረ ነው። በተለይ ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ግን እጅግ የከፋ ቀውስ ውስጥ እንደ ገባች ከማንም የተሰወረ አይደለም። “ወርቃማው ዘመን” እየተባለ የሚነገርለት ይህ ዘመን ስያሜውን ያገኘው ሥነ ጽሑፍ የተስፋፋበት ዘመን መሆኑን ለመግለጥ ይሁን እንጂ፥ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቷ ይበልጥ እየተንሸራተተች ወደ ዐፄው ልብ ወለድ ድርሰቶች ጭልጥ ብላ የገባችበት ዘመን ነበር። ብዙ የጥንቆላና የአስማት እንዲሁም የሐሰት ትምህርትን የያዙ መጻሕፍት የተፈበረኩበት ዘመንም ነበር።

እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች በሕዝቡ ልብና መንፈስ ውስጥ ነግሠው ለታላቅ መንፈሳዊ ውድቀት ያበቁትና ለከንቱ አምልኮ የዳረጉት ሲሆን፥ መጻሕፍቱም ብዙ ትውልድን መማረክ ችለዋል። በዚህ ሁሉ ግን እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ከምትገኝበት መንፈሳዊ ቀውስ ለማውጣት በየጊዜው የራሱን ሰዎች እያስነሣ ሲሠራ፥ የጠላት ተግዳሮት እንደ ነበረና የእግዚአብሔር ባሪያዎችም በዚህ ውስጥ ዐሳቡን አገልግለው እንዳለፉ ይታወቃል።

ዛሬም የአባቶቻቸውን ፈለግ በመከተል እውነትን የሚቃወሙና የእግዚአብሔርን አገልጋዮች በማሳደድ ቤተ ክርስቲያን ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቷ እንዳትለመስና የወንጌል እውነት እንዳይገለጥ፥ ሕዝቡም በሐሰትና በተረት እንደ ተተበተበ እንዲኖር ለማድረግ የሚተጉ አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሕዝብ በሐሰት ትምህርት፣ በጥንቆላ በአስማት እንደ ታሰረ አይኖርም። “ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ” የሚል የሥልጣን ቃል ከሰማይ ወጥቷልና! ጠላት ቢከፋውም፥ ፉከራ ቢያበዛም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጎበኝት ዘመን መጥቷል።

በእግዚአብሔር ጥሪ ለዚህ ታላቅ ሥራ የተሰለፋችሁ ወገኖች ሆይ! እጆቻችሁን አበርቱ! የጠላትን ፉከራ ሳይሆን፥ የጠራችሁን ጌታ ድምፅ በመስማትና ራሳችሁን በመስጠት ሥራችሁን ፈጽሙ። ከጨለማ በኋላ ጨለማ አይጠበቅም፤ ብርሃን እንጂ። ቃሉም “ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም” ይላል (ኢሳ. 9፥1)።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

4 comments:

  1. It's good to see you .

    ReplyDelete
  2. gud to hear, but i couldn't find your magazine

    ReplyDelete
  3. i didn't read it but the picture is impresive

    ReplyDelete