Saturday, December 10, 2011

“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ . . . ማን ያድነኛል?”

Read PDF 
“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ  . . . ማን ያድነኛል?” ሮሜ 7፥24

ሰው ተፈጥሮ ካመፀበት፥ ተፈጥሮን መቈጣጠር ካቀተው ብዙ መቶ ዓመታት ዐልፈዋል፡፡ የምድር ፍጥረት ሁሉ ለእርሱ ተፈጥሮለት የነበረና ሁሉን ለመቈጣጠርና ለመግዛት በተፈጥሮ ባሕርዩ ባለመብት ተደርጎ የክብርን አክሊል በመቀዳጀት የተሾመ ሰው (ዘፍ. 1፥28፤ መዝ. 8፥3-8) በአሁኑ ጊዜ ሲታይ ከብዙ አቅጣጫዎች ጥቃት የሚደርሰበትና አደጋን የሚፈራ ድንጉጥ ፍጡር ሆኗል (ኢዮ. 7፥1-31)፡፡
በቀላሉ አገላለጽ የፀሓይ ዋዕይ ያጠቃዋልና መጠለያን ይሻል፡፡ በተቃራኒው ሁኔታ ቊር ቢያኮራምተው ሙቀትን ይፈልጋል፡፡ በእሾኽና በእንቅፋት በቀላሉ ስለሚጐዳ ጫማን ለማዘጋጀት ይገደዳል (ዘፍ. 3፥18፤ ኢሳ. 25፥4-5)፡፡

እንዲሁም በማኅበራዊ ኑሮው እድገት ውስጥ የሰላም ተጻራሪ ኀይሎች ተፈጥረውበታል፡፡ እነርሱንም ለመከላከል እንዲያመቸው በመሰባሰብ በሰፈር፥ በቀበሌ፥ በወረዳ፥ በአውራጃ፥ በብሔር  . . .  እየተደራጀ ከጐበዝ አለቃ ጀምሮ በየደረጃው እስከ መንግሥት ድረስ ያለውን ልዩ ልዩ ድርጅት ቢያቋቁም ያው ያቋቋመው ድርጅት ከቁጥጥሩ ውጪ በመሆን የተገላቢጦሽ አጥቂው ሆኖ የተገኘበት የጊዜ ዝርዝር የታሪክን ገጽ አጣብቧል (መሳ. 9፥14-15)፡፡
ሰው የሚጠቃበትና “እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” የሚያሰኘው ክስተት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይመስልም፡፡ የተፀነሰው ሁሉ በጤና አይወለድም፤ ከተወለዱትም ሕፃናት መካከል የማያድጉት ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡ ፅንሱንም ሆነ የተወለዱትን በየደረጃው የሚቀጭ፥ ሆነ ብሎ ራሱን ለአጥቂነት ያዘጋጀ የሰው ጠላት ምን እንደ ሆነ ማወቅና መድኀኒቱንም ማግኘት ሁላችንንም የሚያጓጓ ነው፡፡
ሌላውንም የክበብ ጠረፍ ብንቃኝ ሰው ሙሉ በሙሉ የድካሙ ውጤት ተጠቃሚ አልሆነም፤ የዘራው በሙሉ አይበቅልም፡፡ ዘሩን ከማሳ የሚለቅምበት ጠላት አለው፡፡ በስብሶ የሚቀር ዘር አለ፤ ከበቀለም በኋላ ዐረምና ተባይ የሚያመክነው፥ በበረዶና በዝናም የሚጨፈጨፈው፥ በውርጭ የሚያረው፥ በሐሩር የሚቃጠለውና ለፍሬ የማይበቃው አቤት ብዛቱ!!
የሰው ልጅ ለግል ምቾቱና ለማኅበራዊ ጠቀሜታው የሠራቸው ሕንጻዎች፥ ፋብሪካዎች፥ መርከቦች፥ የኀይል ማመንጫና የመስኖ ግድቦች . . . በነውጥ፥ በእሳተ ገሞራ፥ በአውሎ ነፋስ፥ በውሃ ማዕበል . . . ሲፈራርሱበት በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ “ከዚህ ሁሉ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” እያለ ነው፡፡ በአራዊት እንኳ የሚጠቃው ሰው የፍጥረት ገዥነቱን ሥልጣን የተነጠቀ በመሆኑ በፍጥረታትና በተፈጥሮ ክሥተቶች የሚጠቃ አሳዛኝ ምስኪን ሆኖአል ማለት ተችሏል፡፡
ፍጥረታትንና የተፈጥሮ ክሥተቶችን ለራሱ ጥቅም ሊያውል ባይችልም ከፍተኛ የመቈጣጠር እና የማዘዝ ፍላጎቱን ከግብ ለማድረስ ጥረት ማድረጉን አላስታጐለም፡፡ ሆኖም ሰው ራሱን እንኳ የማዘዝና የመቈጣጠር ዐቅም የለውም፡፡ ሊሆን የሚመኘውን የመሆን፥ ሊያደርግ የሚገባውንም የማድረግ ችሎታና ብቃት እንደሌለው ታውቋል፡፡ ለማስረጃ፥ ክፉ ምን እንደ ሆነ የሚገነዘብበት የተፈጥሮ ዕውቀት እያለው፥ እንዲሁም ክፉ የመሆንና ክፋትን የመሥራት ውጤት ጐጂ መሆኑን እየተረዳ ሳለ ክፉ ከመሆን ክፋትንም ከማድረግ አልታቀበም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ሰው ክፉ የሆነውን የሚያውቀው ክፉ ከሆነ ወይም ክፋትን ካደረገ በኋላ አይደለም፡፡ ራሱ ክፉ ከመሆኑ በፊት ክፋትንም ገና ከማድረጉ አስቀድሞ በተፈጥሮ ባገኘው ባሕርያዊ ዕውቀቱ ክፉ ምን እንደ ሆነና የውጤቱንም ጐጂነት በሐሳብ ደረጃ እያለ ያውቀዋል፡፡ በዚህም የማወቅ ችሎታው ክፉ የሆነውን ሁሉ አስቀድሞ በባሕርዩ በኋላም በውጤቱ ይጠላዋል፡፡
ዳሩ ግን በማወቅና በመጥላት ብቻ ከመወሰን በቀር የሚጠላውን ክፉውን ከመሆን፥ ክፋትንም ከማድረግ ለመታቀብ ራሱን ማዘዝ ለሰው የሚቻለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ ከዚህም ማስረጃ በመነሣት በሰው ውስጥ ዙፋኑን በመዘርጋትና የበላይነትን በመያዝ የሰውን ነጻነት የቀማና ራሱን የሰው አዛዥ ያደረገ ክፉ መንፈስ (የኀጢአት ባሕርይ) እንዳለ ይታወቃል፡፡ እንዲሆን የማይፈልገውን እንዲሆን፥ የሚጠላውንም እንዲሠራ የሚያስገድደው ይህ ረቂቅ ጠላት እንደ ሆነ ግልጽ ነው (ሮሜ 7፥15-24)፡፡
ታሪክን የመጻፍና ለትውልድ የማስተላለፍ ዋናው ዐላማ የሚጐዳውን ላለመሥራት ካለፈው ትውልድ በመማር ሕይወታዊ ጒዞን በመልካም ዐቅድ ለመምራት እንዲችል ነበር፡፡ ታዲያ ዘመናትን አቋርጦ እየተዋለደ ካለንበት ዘመን የደረሰው የሰው ልጅ ምንም ታሪክን ቢማር ያለፈው ትውልድ የሠራውን ክፋት በዕጥፍ ከመሥራት በቀር ራሱን ማዳን አልቻለም፡፡
የመጀመሪያውን የዓለም ጦርነት ያስነሣ የሰው ልጅ የጦርነትን አስከፊ ውጤት ከታሪክ ይረዳል፡፡ የመጀመሪያውን የዓለም ጦርነት ያስነሣና የተካፈለ ሰው ከዚያ አስቀድሞ ከተጻፈ የጦርነት ታሪክ የጦርነትን ጐጂነት በሚገባ ያወቀ ነበረ፡፡ ሆኖም እያወቀ ካስነሣው የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ያን ያህል የተጐዳ ሆኖ እያለ በብዙ ዕጥፍ ጐጂ የሆነውን የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ከ22 ዓመታት በኋላ ማስነሣቱ ያሳዝናል፤ ያስገርማልም፡፡ ማሳዘኑ ጐጂ የሆነውን እያወቀ ለመተው ችሎታ ማጣቱ ሲሆን፥ ሁለቱንም ጦርነቶች ያው  ትውልድ መካፈሉ ሲጤን ደግሞ ያስገርማል፡፡ ስለ ሆነም ሰው “የምጠላውን ክፉውን እንድሆንና እንድሠራ ከሚያስገድደኝ ክፉ ገዥ ማን ያድነኛል?” የማለቱ ተገቢነት የሚያከራክር አይደለም፡፡
የሚጠላውን ክፉውን ላለማድረግ መልካሙን ብቻ ለመፈጸም መብት ያጣ ሰው ሊታዘንለት የሚገባ የምስኪኖች ምስኪን ሆኖአል ማለት አይደለምን? ከዚህም ለመዳን ወይም ነጻ ለመውጣት ምን ማድረግ ይገባኛል? ከማለት ሌላ ለሰው ምን አማራጭ ይኖረዋል?
የሰው ምስኪንነት መቼ በዚህ ያልቅና! ሳይወድ ባደረገው ክፋትና ሳይወድ ባላደረገው መልካም ነገር ምክንያት የሚቀጣበት ፍርድ ይጠብቀዋል (1ዮሐ. 3፥4-10፤ ያዕ. 4፥17)፡፡
ከሁሉ የባሰ አስፈሪና የማይቀር የመጨረሻ ዕድሉ ይህ ፍርድ ስለ ሆነ ሰውን እጅግ አሳዛኝ ምስኪን ያደርገዋል፡፡ እስከዚህ ደረጃ የደረሰውን ምስኪንነት ካመጣበት ወድቀት በራሱ ጥረት ለመዳን ከቶ አልተሳካለትም፡፡ የሚያድነው መለኮታዊ ረድኤት እንዲደርስለት ልባዊ ጩኸት ያሰማ ዘንድ ተገቢ ይሆናል፡፡ እንዲህ በማድረጉም “ባለቤት ካልጮኸ ጐረቤት አይረዳም” እንደሚባለው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰውና፤ ሰው ነጻነቱን ከቀማው ክፉ ረቂቅ ጠላት፥ ይህ ጠላት ካሠራው ኀጢአት፥ ኀጢአትም ካመጣበት ፍርድ የሚድንበት መንገድ ራሱ ፍቅር በሆነ አምላክ ተዘጋጅቶለታል፡፡
“… ጐስቋላ ሰው ነኝ ማን ያድነኛል?” በሚል ርእስ የመዳን ትምህርት በተከታታይ በዚህ መጽሔት ይቀርብ ዘንድ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ይኸው ነው፡፡

የሰውነቱንም ክፍሎች የሚያጠቁ የበሽታ ዐይነቶች ብዙ ናቸውና “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቅ” እንደ ተባለ ለመዳን በቅድሚያ ይጠነቀቃል፡ ይህም ሳይሳካ ቢቀርና ቢታመም ከበሽታው ለመዳን መድኀኒት ይሻል፤ ይታከማል (ኢሳ. 38፥1-21)፡፡ የሚጐዱትን በሽታዎች ለመከላከልና ለመፈወስ ባዘጋጃቸውና በሚጠቀምባቸው መድኀኒቶች እንኳ ያልታሰበ ሌላ ጒዳት እየደረሰበት መቸገሩ ታውቋል፡፡

1 comment:

  1. በርቱ! እግዚአብሔር ይርዳችሁ፡፡

    ReplyDelete