Monday, January 23, 2012

መሠረተ እምነት

Read PDF
ካለፈው የቀጠለ
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 2 ላይ የቀረበ
ማስረጃ 2

በኦሪት ዘፍጥረት 1፥26 “ኤሎሂም (አማልክት) በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ሰውን እንፍጠር አለ፤” ተብሏል፡፡ ተናጋሪው በአንድ አካል “ኤል” ራሱን አልገለጸም፡፡ የብዙ ቊጥር መግለጫ በሆነው ስም “ኤሎሂም (አማልክት)” ራሱን የገለጸው ይሆዋ ነው፡፡

“እንፍጠር” የሚለውም ውሳኔ ብዛትን ከሚያመለክተው የአረፍተ ነገሩ ባለቤት ከሆነው “ኤሎሂም” (አማልክት) ጋር ይስማማል፡፡ ሆኖም “ኤሎሂም” (አማልክት) እንፍጠር በማለት ያሳለፉትን ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስ ለኛ ሲያስተላልፍ በአንድ ይሆዋነት የሚታወቁ አካላት መኖራቸውን ለማስረዳት በመፈለጉ እንፍጠር አሉ ሳይል “እንፍጠር አለ” ይለናል፡፡ አገላለጹ ሚዛናዊ ልብ ላለው ሰው ብዛትንና አንድነትን ሊያስተምር ይችላል፡፡

Wednesday, January 18, 2012

መሠረተ እምነት

Read Pdf
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩ ምእምናን ሲጽፍ እንዲህ አለ፡- “ስለዚህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጎችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች ናችሁ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡ በሐዋርያትና በነቢያትም መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑም ራስ የሆነው ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሕንጻው በሙሉ በእርሱ ተገጣጥሞ የጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ያድጋል፡፡ እናንተም እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚያድርበት ሕንጻ ለመሆን በክርስቶስ ትታነጻላችሁ፤” (ኤፌ. 219-22)፡፡

ለአንድ ምእመን የማእዘኑ ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ በሆነበት፥ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ በሚያስተማምን ሁኔታ ጸንቶ መቆሙን ከሌሎች ምእመናን ጋር በመገጣጠም ለሕንጻው እድገትና ውበት አስተዋጽኦ ማድረጉን መርምሮ ከማረጋገጥና በዚህም እግዚአብሔርን ከማመስገን የሚበልጥበት ምንም ነገር እንደማይኖር የታመነ ነው፡፡

Sunday, January 15, 2012

በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

    Read PDF
በጮራ ቊጥር 2 ላይ የቀረበ

/ካለፈው የቀጠለ/

በዚህ ርእስ የሚቀርበው ታሪክ ከጥንት ጀምሮ እየተለዋወጠ እስከ እኛ ዘመን የደረሰውን የሀገራችንን የዳር ድንበር ክልል፥ የመንግሥቷን ዐይነትና አወቃቀር በየዘመኑ በመንግሥቷ የታቀፉትን ልዩ ልዩ ነገዶች ስማቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ አምልኮታቸውን ወዘተርፈ በመጠኑም ቢሆን መያዝ በተገባው ነበር፡፡ ዳሩ ግን በአንድ በኵል ከርእሱና ከዐላማው ላለመውጣት፥ በሌላው በኩልም በሙያው ብዙ የደከሙትን ተመራማሪዎች ድርሻ ላለመሻማት ሲባል በርእሱና በዐላማው መወሰን የሚሻል ሆኗል፡፡

          ሊቀር የማይገባው ነጥብ ቢኖር “ኢትዮጵያ” ስለሚለው ስያሜ ዐጭር መግለጫ የማቅረቡ ጕዳይ እንደ ሆነ ይታመናል፡፡
ለኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ የሚያገለግሉ ምንጮች ናቸው በመባል በባለታሪኮች ከሞላ ጐደል የሚታመንባቸው፡-

Thursday, January 5, 2012

“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ . . . ማን ያድነኛል?” (ሮሜ 7፥24)፡፡

Read PDF
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 2 ላይ የቀረበ)

ካለፈው የቀጠለ

መዳንን አጥብቀው የሚሹ በሽተኞች መሆናቸውን የተረዱና የጤና ስንኩልነታቸው ያስከተለባቸው ጕዳትና ውርደት ከልብ የተሰማቸው ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ በብዙ ድካም ያገኙትን መድኀኒት በሚገባ ሊጠቀሙበት ሙሉ ፈቃደኞች  ይሆናሉ (ሉቃ. 5፥31፤ ሐ.ሥ. 16፥30)፡፡ በዚህ ትይዩ እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ያዘጋጀውን መድኀኒት በምስጋና እንቀበለው ዘንድ በቅድሚያ የበሽታችንን ምንነትና ያደረሰብንን ገናም የሚያደርስብንን አስከፊ ውጤት በጥልቀት ልናጠናው ይገባል፡፡

የእግዚብሔር ቊጣና ምክንያት

በኀጢአተኝነትና በዐመፃ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ እንደሚገለጥ በማስታወቅ ሐዋርያው ጳውሎስ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ለሰው ዘር ሁሉ ያስተላልፋል (ሮሜ 118-31)፡፡ ሐዋርያው “ኀጢአተኛነት” ሲል ኀጢአተኛ የሆነውን ሰብኣዊ ባሕርይ ያመለክታል፡፡ እንዲሁም “ዐመፃ” ሲል ኀጢአተኛ ሰው በኀጢአተኛ ባሕርዩ የሚያፈራውን የኀጢአት ፍሬ ይገልጻል፡፡ በዚህ አገላለጽ መሠረት ሰው በሁለት መንገድ ኀጢአት እንደ ተቈጠረበት መረዳት ተችሏል፡፡ ይህም ማለት ኀጢአተኛነትና ኀጢአት ነው፡፡ ሰውን ኀጢአተኛ ባሰኘው ኀጢአተኛ ባሕርዩና ከኀጢአተኛ ባሕርዩ የተነሣ ሰው በሠራው ኀጢአት ላይ መለኮታዊ ቊጣ ሊገለጽ ተገባ፡፡