Sunday, June 16, 2013

የዘመን ምስክር

በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡


ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ቀዳማዊ የወንጌል እስረኛ (1888 - 1974 ዓ.ም.)
በዘመናት ውስጥ የተፈጸመና ታሪክ የመዘገበው መልካምም ሆነ ክፉ ሥራ ሊረሳ አይችልም፡፡ ለጊዜው እውነት እንደ ሐሰት ይቈጠር$ ሐሰት ደግሞ የእውነትን ስፍራ ይቀማ ይሆናል፡፡ በደካሞች ግምትም እውነት ርቆ ሊቀበርና የሐሰት ዐፈር ሊጫነው ይችላል፡፡ እውነት ግን ለጊዜው እንጂ ተቀብሮ ሊቀር፥ ፈጽሞ ሊሰወርና ሊረሳ አይችልም፡፡ እውነት ሲወጣ ቀድሞ ተሰጥቶት የነበረው ዝቀተኛ ግምት ይለወጣል፡፡ በተቃራኒው ሐሰትም ከተሰቀለበት የክብር ማማ ላይ ይወርዳል፡፡ የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የተጋድሎ ታሪክ ከተቀበረበት መውጣቱና ተገቢውን ስፍራ ማግኘቱ እውነትና እውነተኞች ተቀብረው እንደማይቀሩ ያሳያል፡፡    

የባለ ታሪኩ ማንነት
የተወለደው በ1888 ዓ.ም. በቀድሞው የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት በሐማሴን አውራጃ፣ በላምዛ ሠሓርቲ ወረዳ፣ ዓዲ ቀሺ በተባለው ስፍራ ነው፡፡ ገብረ አብ ይባላል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ክህነት ትምህርቱን ተምሮ ወደ ትግራይ በመሄድ፥ በዓድዋ አውራጃ ዓዲ አቡን ከነበሩት ግብጻዊ ጳጳስ ከአቡነ ቄርሎስ ዲቁና ተቀበለ፡፡ ከዚያ ኤርትራ ውስጥ በሚገኘው አቡነ እንድርያስ ሠፍኣ ገዳም ገብቶ የግእዝን ትምህርት፣ የአበውን ግብረ ገብና ሥርዐተ ገዳምን እየተማረና እያገለገለ ዐምስት ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ መነኰሰ፡፡

አባ ገብረ አብ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ምስጢር ለመረዳት ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ወደዚያው ለመድረስም ቅኔን ከነአገባቡ ተምረዋል፡፡ ፀዋትወ ዜማንና መዝገብ ቅዳሴንም በሚገባ የተማሩ ሲሆን በቅዳሴ መምህርነት ተመርቀዋል፡፡ በ1911 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ ከአቡነ ማቴዎስ የቅስናን ማዕርግ ተቀበሉ፡፡ ወዲያው በቀድሞው የሐረር ጠቅላይ ግዛት የሚገኘውንና በግራኝ ጊዜ የጠፋውን የአሰቦት ደብረ ወገግ ገዳም እንዲያቀኑ ተላኩ፡፡

መጽሐፍ “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” (መዝ. 36(37)፥4) እንደሚል፥ ከእርሳቸው ስምንት ቀን ያህል ቀድመው ወደ ቦታው ከመጡና አለቃ ገብረ መድኅን ከተባሉ የሐዲሳትና የሃይማኖተ አበው መምህር ጋር ተገናኙ፡፡ ይህም ሐዲሳትን ለመማር የነበራቸውን ጽኑ ፋላጎት ለማርካት የተፈጠረ ትልቅ ዕድል በመሆኑ፥ ከእርሳቸው ጉባኤ ሐዲሳትን እየቀጸሉ ጥቂት እንደ ቈዩ፥ በእኒሁ መምህር ምክንያት ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄዱበት በር ተከፈተላቸው፡፡


በኢየሩሳሌም ለ5 ዓመታት የቈዩ ሲሆን፥ የገዳሙ መምህር እንደ ራሴ ሆነው አገልግለዋል፡፡ መምህሩ ባረፉ ጊዜ ሌላ መምህር እስኪሾም ድረስም ገዳሙን አስተዳድረዋል፡፡ በ1916 ዓ.ም. ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን (በኋላ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ) መሳፍንቶቻቸውን አስከትለው ወደ አውሮፓ ለጕብኝት ሄደው በነበረ ጊዜ÷ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ሳለ አባ ገብረ አብ ለመተዋወቅ ዕድል አገኙ፡፡ ለኢየሩሳሌም ሌላ መምህር ከተሾመ በኋላ አባ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደረገና በመጀመሪያ ወደ አሰቦት ደብረ ወገግ ገዳም፣ ቀጥሎም በ1925 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የታእካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም አስተዳዳሪ ሆነው ታላላቅ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ከዚያ በ1931 ዓ.ም. አባ ፊልጶስ ተብለው የሊቀ ጵጵስናን ማዕርግ ተቀበሉ፡፡         

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሾሙበት ጊዜ ፋሽስት ጣሊያን አገራችንን ዳግም የወረረበት ጊዜ በመሆኑ፥ ሀገረ ስብከት ይዘው እንዲያገለግሉ ባለመፈለጉ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስነው ቈይተዋል፡፡ በጄነራል ግራዚያኒ ላይ የተቃጣውን የየካቲት 12ቱን የግድያ ሙከራ ተከትሎ ፋሺስት ወገኖቻችን ከጨፈጨፈ በኋላ፥ ወደ ጣሊያን ታስረው ከተወሰዱት እስረኞች መካከል ብፁዕነታቸው ይገኛሉ፡፡ በዚያም 2 የእስር ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ ከነጻነት በኋላ ግን ተፈትተው ወደ አገራቸው ተመልሰው በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል፡፡

ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር አስተዋፅኦዎች
ቅድመ ጵጵስና በአሰቦት ገዳም በነበሩበት ጊዜ ገዳሙ በሁለንተናዊ መልኩ እንዲስፋፋ ጥረት ከማድረጋቸውም በላይ፥ በአካባቢው አርብቶ አደር ለሆነው ማኅበረሰብ ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡ በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳምም የካህናት ማሠልጠኛ የመሠረቱ ሲሆን፥ ለአሠራር አመቺ ያልነበረውን የገዳሙን አስተዳደር በማቃናትም ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ አድርገዋል፡፡

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በቈዩባቸው ዓመታትም፥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ የሆነውንና ግብጻውያን የይገባናል ጥያቄ አንሥተውና ውዝግብ ተፈጥሮበት የነበረውን የዴር ሡልጣን ገዳምን ጕዳይ፥ በሕግ ፊት ተከራክረው በመርታት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት አረጋግጠዋል፡፡ ከግብጻውያን ጋር የተደረገውን ክርክርና ከጕዳዩ ጋር የተያያዙ ነገሮችን በሚመለከት ጥልቅ ምርምርና ትንተና ያደረጉባቸውን ጠቃሚ ሰነዶች የሆኑ መጻሕፍትን አሳትመዋል፡፡ ከነዚህም መካከል “ኢየሩሳሌምን ዕወቁ”፣ “ዜና ኢትዮጵያ በሀገር ቅድስት ኢየሩሳሌም” እና “ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ቅድስት የሰነድ ማስረጃዎች” የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ጥር 28 ቀን 1980 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም የታሪክ መስተዋት” በሚል ርእስ ለ25ኛ ዓመት መታሰቢያ ባዘጋጀው ልዩ ዕትም ላይ ፎቶ ግራፋቸውን አስደግፎ ባወጣው መግለጫ፥ “ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያን ታሪክ ይዞታ ማስረጃዎች ይዞታችንን በግፍ የወሰዱት፥ በእሳት አቃጥለው ያጠፏቸውም ቢሆን የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ሟቹ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ያሰባሰቧቸው “ኢየሩሳሌምን ዕወቁ” ብለው በጻፉት መጽሔት የመዘገቧቸውን ሰነዶች ስንመለከት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረጋቸው ውለታቸው የሚረሳ አይደለም” ብሏል፡፡  

ብፁዕነታቸው ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በሌሎች ሃይማኖታዊ ጕዳዮች ላይ 16 መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ ከሚጠቀሱት ውስጥ፡- “ትምህርተ ክርስቶስ”፣ “ሃይማኖት በሐዲስ ኪዳን”፣ “ሥነ ምግባራትና ስለ ጾም ማሻሻያ”፣ “ስለ ክብረ በዓላት ማሻሻያ” የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ “እነዚህ ሁሉ እስካሁን ተጠቃሚ አላገኙም” የሚል አስተያየትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በሚለው ሁለተኛ መጽሐፋቸው መጨረሻ ላይ አስፍረዋል፡፡

የለውጥ ሐሳብ
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እንደ መንፈሳዊ አባት ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋም በመንፈሳዊውም በአገራዊውም ጕዳይ ላይ ሁለንተናዊ መሻሻልና ለውጥ እንዲመጣ ጥረት አድርገዋል፡፡ “ወደ ፊት ባለው ዕድሜዬ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በኮፕት ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ከባርነት የማይሻለውን ግንኙነት በማሻሻልና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ቅዱስ ወንጌል እንዲነገርባት ለማገልገል ባለኝ ተስፋ ሕይወቴን ለወንጌል አገልግሎትና ስለ መላው አብያተ ክርስቲያናትም አንድነት አገልግሎት ራሴን ብፅዐት አድርጌአለሁ፤ ፈቃድህ ይሁን” ሲሉ ገና ከመጀመሪያው ለተጠሩበትና ለተሾሙበት ዐላማ ራሳቸውን ለይተዋል፡፡

ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተሾሙና ወደ ኢየሩሳሌም ከሄዱ በኋላ የቤተ ክርስቲያናቸውና የአገራቸው ጕዳይ ያሳስባቸው እንደ ነበረ፥ ከንጉሡ ጋር ከተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች መረዳት ይቻላል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያናቸውን በተመለከተ በወቅቱ ለውጥ ያስፈልገዋል ብለው የተነሡለት አንዱ ጕዳይ፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራትን “ከባርነት ያልተሻለ” ያሉትን ግንኙነት የተመለከተ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቋንቋቸው በማይታወቅ በግብጻውያን ጳጳሳት ስትመራባቸው በነበሩት ዘመናት በመንፈስም ሆነ በሥጋ ከጕዳት በቀር ጥቅም፥ ከኪሳራ በቀር ትርፍ አለ ማግኘቷን በመገንዘብ፥ ኢትዮጵያ “በልማድ ሰንሰለት ታስራ ለማይጠቅሟት ወገኖች (ግብጻውያን) መጠቀሚያና ድጋፍ ሆና በተገዥነት መልክ የምትኖረው እስከ መቼ ነው?” ሲሉ ይጠይቁ ነበር፡፡

ብፁዕነታቸው ግብጻውያን ለዘመናት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ የበላይ ሆነው ሲገዙን የኖሩት አለ አግባብ መሆኑን በተለያዩ ማስረጃዎችና ማጠየቂያዎች ለንጉሡ በጻፏቸው ደብዳቤዎች በጽኑ አስረድተዋል፡፡ ከተለመደውና በፍትሐ ነገሥት “የኢትዮጵያ ሰዎች ከሊቃውንቶቻቸው መካከል ለራሳቸው ጳጳስ አይሹሙ” ተብሎ በሥርዋጽ ከገባው ሰው ሠራሽ ሕግ በመነሣት ብቻ አልተወሰኑም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከሚናገረውና ከሐዋርያት የአገልግሎት ተመክሮ በመነሣትም የግብጾችን የበላይነት ይቃወሙ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያም ቢሆን የተመሠረተችው በግብጾች ሐዋርያነት አይደለም፡፡ አስቀድማ የተቀበለችውን ክርስትና በትምህርት ለማስፋፋት በማሰብ ነው መልእክተኛዋን ወደ ግብጽ ልካ የጳጳስነት ሥልጣን የወሰደችው፡፡ ለነገሩ በእነርሱ ስብከት አምና ቢሆንም እንኳ፥ እነርሱ ሊያደርጉ የሚገባው በሐዋርያነት ሕግ መሠረት ላመኑት ወገኖች ሥልጣኑን ሰጥተው መሄድ እንጂ፥ ከገባን አንወጣም ብለው ያስተማሩትን አገር በርስትነት ይዘው እንዲኖሩ የሚፈቅድ መንፈሳዊ ሕግ የለም ሲሉ ጽፈዋል፡፡ ደግሞም ክርስቲያኖች ሁሉ ወንድማማች በመሆናቸው አንዱ በሌላው ላይ አለ አግባብ እንዲሠለጥንና የበላይ ገዢ እንዲሆን አለ መታዘዙን ከእግዚአብሔር ቃል ጠቅሰው የግብጻውያንን ስሕተት ያሳያሉ፡፡

ይህን ቀንበር ሰብሮ ለመጣል ጽፈው ብቻ አልተቀመጡም፡፡ ጣሊያን አገራችንን ዳግም በወረረባቸው ዓመታት፥ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለወራሪው ጠላት መሣሪያ አልሆንም ብለው በፋሺስት በግፍ ሲገደሉ፥ በዚያ ዘመን የነበሩት ግብጻዊው ጳጳስ አባ ቄርሎስ ግን ሮም ድረስ ሄደው ለሹመታቸው ይካሰሱ ነበር፡፡ በችግሩ ሰዓት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት መከራውን ሲቀበሉ ግብጻዊው ጳጳስ ግን ኢትዮጵያን ለቀው ሄደዋል፡፡ በ1933 ዓ.ም. ነጻነት ሲመለስ ግን እርሳቸውም ተመልሰው ወደ ሥራዬ ልግባ ቢሉ፥ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጥንቱንም ቢሆን ግብጻውያን ጳጳሳት የተሾሙብን አለ አግባብ ነው፤ አሁንም አገር ጥለው ከሄዱ በኋላ ተመልሰው በኢትዮጵያ ላይ ጳጳስ ሊሆኑ አይገባቸውም በማለት ተቃውመው ውግዘት ሁሉ አስተላልፈዋል፡፡ ለዚህ የተሰጣቸው ምላሽ ግን አሳዛኝ ነበረ፡፡ በጊዜው ብፁዕ ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ (በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ) ብፁዕነታቸውን እንደ ወንጀለኛ አድርገው በማሳሰር በአሰበ ተፈሪ ከተማ 2 ዓመት ከ5 ወር ከሰው ተለይተው በግዞት ቈይተዋል፡፡

ይህ እንዴት በጣም የሚያሳዝን ታሪክ ነው! እናት ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሲያታልሏት ለኖሩት ግብጻውያን ክብር እየሰጠች ለገዛ ልጆቿ ክብር መንፈጓ በዚያ ዘመን የኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትን ልብ የሚሰብር ድርጊት ነበር፡፡ በቀደሙት ዘመናት አንዳንድ አታላዮች ጳጳስ ሳይሆኑ ጳጳስ ነን እያሉ ይፈጽሙባት የነበረውን ግፍ አስመልክተው ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አገራቸውን ኢትዮጵያን እንዲህ ሲሉ ይወቅሣሉ፡፡ “ርሷም በጠባይዋ ከልጆቿ ይልቅ ባዕድ የንጀራ ልጅ የምቶድ ወረተኛ ባልቴት ስለ ሆነች፥ ኢትዮጵያን በየዘመኑና በየጊዜው እንደዚህ የመሰለ ልክ የሌለው ሐዘን፣ ጥቃትና ውርደት የሰው መሣቂያነት አግኝቷታል፡፡ መቼም ቢሆን በእንጀራ ልጆቿ በግብጦች ከኀሳር በቀር ክብር አላገኘችም፡፡ የባሕርይ ልጆቿም ታላላቆቹና ብዙዎቹ በመምህር በሞግዚት በቤተ ክርስቲያን ትምርት ያላደጉ ጽልሙታነ ልብ ስለሆኑ፥ ብሩሃነ አልባብ በሊኃነ ንባብ ከሆኑት ከወንድሞቻቸው መርጦ መሾምና በጥቊር ጳጳስ እጅ መባረክ ውርደትና ርግማን መስሏቸው፥ አላስተርጓሚ የማይሰሙትና የማይሰማ ቋንቋውና መልኩ የተለየ የውጭ አገር ጳጳስ አባ ቀዮ በመጣ ቊጥር፥ በሃይማኖት ነገር ጢስ እንደ ገባው ንብ ሲታወኩና ሲታመሱ፥ ሲተራመሱ፥ ሲመሟገቱና ሲፋለሱ፥ ሲካሰሱ ይኖራሉ፡፡” (ሃይማኖተ አበው ቀደምት)

ይህ የብፁዕነታቸውና ከእርሳቸው በፊት የነበሩ የሌሎችም ኢትዮጵያውያን ነገሥትና አበው ተጋድሎ መና ሆኖ አልቀረም፡፡ በ1951 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ ለመሾምና ነጻ ለመውጣት ችላለች፡፡  

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ገዢነት ነጻ ከወጣች በኋላ ለውጥ ፈላጊ ፊታቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ የመለሱ ይመስል ነበር፡፡ ካሁን ቀደም ስናመካኝ የነበረው በግብጻውያን ጳጳሳት፣ በግእዝ መጻሕፍት ነበር፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያውያን ጳጳሳትን በመሾም ራሳችንን ችለናል፤ ብዙ መጻሕፍትም ከግእዝ ወደ ዐማርኛ ተተርጕመዋል፡፡ ይህ ሁሉ ዝግጅት ከተፈጸመ በኋላም ግን በእነዚህ በመጠቀም ሐዲስ ኪዳንን ማስተማር ሲገባ፥ አሁንም የሰውን ገድልና ድርሳን ከመተረት አልወጣንም ሲሉ ለውጡ ገና መሆኑን ይናገሩ ነበር፡፡

መጻሕፍት በግእዝ ቋንቋ ብቻ በነበሩበት ዘመን ሕዝቡ ቋንቋውን ባለማወቁና የሃይማኖቱን ምስጢር የማያውቀው ሕዝብ ብዛት ዐዋቂዎችን እንዳላዋቂ በማስቈጠሩ፥ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ባላዋቂው ሕዝብ አፍ መናፍቃን እየተባሉ ለዕውቀታቸው መግለጫ ጊዜ ሳያገኙለት እንደ ቦሩ ሜዳ ችሎት ታሪክ ምሳሌ፥ ምላሱን አውጣው፣ አካሉን ቊረጠው፥ ይሉናል ሲሉ በፍራትና በመንቀጥቀጥ የሐሳብ ነጻነት ባልነበረበት ዘመን ዕውቀታቸውን ለመግለጽ ሳይችሉ ዕውቀትን እንዳረገዙት ያለፉት የኢትዮጵያ ሊቃውንት እጅግ ያሳዝናሉ፡፡” በሊቃውንት ላይ ይደርስ የነበረውን ነቀፌታና ስደት ጠቅሰው ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቊመዋል፡፡ ዛሬም ይህ ጕዳይ ተስተካክሏል ማለት አያስደፍርም፤ ብዙዎች እየተወገዙ ያሉት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በተከተለ አሠራርና ለማውገዝ ሥልጣን ባለው አካል እንዳልሆነ ይታያልና፡፡ 

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ለጃንሆይ በጻፏቸው ደብዳቤዎች ውስጥ የለውጥ ሐሳባቸውን በተመለከተ ካሰፈሯቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-
“እኔ የምለው በግርማዊነትዎ አስተዋይ መሪነት ተመርጠን ሊቀ ጳጳስ ተብለን የተሾምነው፥ ሰዎች በዘመናቸው የተጠቀሙበትን ተረት እየተረክን ተከናንበን ለመኖር አይደለም፡፡ ግርማዊነትዎ ባስተረጐሟቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባገሩ ቋንቋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት የሆነበትን ሕገ ወንጌልን ልናስተምር ነውና ከንቱ ልማድን ሳይሆን ሐዲስ ኪዳንን እናስተምር፡፡

“የቤተ ክርስቲያናችንንም እርምጃ በሐዲስ ኪዳን በወንጌል ቃል መሠረት ሕዝባችንን ከጊዜው ዕውቀት ጋራ ከመንፈሳዊው ትምህርት በማዛመድ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያናችንን በዘመኑ ዕውቀት በማሻሻል ‘እንዲህ አሉ’ የሚባለውን ልማድ በቅዱስ ወንጌል ትምህርት ዐድሰን ካዲሱ ዘመን ዕውቀት ጋር የሐዲስ ኪዳንን ዕውቀት እናስተምረው፡፡

የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የለውጥ ሐሳብ ጠባብና በራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን የሰው ባህል ያለያያቸው አብያተ ክርስቲያናት አንድ ሊሆኑ ይገባል የሚልም ነበር፡፡ “በሐዲስ ኪዳን ትምህርት ባልተገለጸ በሰው ባህል መጣላቱን ትተን ከሃይማኖት ወንድሞቻችን ከክርስቲያኖች ሁሉም ጋራ ያለንን የእምነት አንድነት በፍቅር ተገናኝተን በሥራ እንግለጸው፤ ዘርና ቋንቋ ቢለየንም የክርስቲያን ሁሉ እምነት በቅዱስ ወንጌል ነውና፥ እንደ ጌታችን ትእዛዝ፥ በፍቅር ተገናኝተን ሐዲስ ኪዳንን በማስተማር የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና የሕዝበ ክርስቲያንም ወንድማማችነት የሚጸናበትን ትምህርት በማስተማር የክርስቲያንን ማገናኛ የሰላምና የፍቅር በር መክፈት ይገባናል፡፡ በተረፈ በወንጌል እምነት አንድ ሆነን በሰው ጠባይ መከፋፈልና አንድነት ማጣት አይገባንም፡፡ አንድነት ለመንፈሳዊና ለሥጋዊም ኀይል ይበጃል እላለሁ” ሲሉ ጽፈዋል፡፡

በኢየሩሳሌም ሳሉ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ጳውሎስ 6ኛ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ባሳዩት የፍቅርና የትሕትና ርምጃ በመመሰጥ፥ “እርሳቸው ያን ያህል ዘመናት ከመመለክ ይቈጠር የነበረውን የሮማን ፓፓዎች ልማድና ለቤተ ክርስቲያን መለያየት ታላቅ ምክንያት የነበረውን ትዕቢትና ኵራትን ባንድ ጊዜ እንዳልነበረ አድርገው፣ የመመለክንም ከንቱ ልማድ ጥሰው፣ ከዙፋን ወርደው ያሳዩት ሐዋርያዊ ትሕትናና የሰው ፍቅር” ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ለጃንሆይ በደብዳቤ ገልጸውላቸው ነበር፡፡ አክለውም “ኢትዮጵያ ባልዋለችበት ፀብና ክርክር (ምናልባትም የኬልቄዶኑን ጉባኤ ሊሆን ይችላል) ውስጥ ገብታ ጠላት የምትሆንበት ከቈየው ልማድ በቀር ሌላ ምክንያት የለም” በማለት፥ ንጉሡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ተሰሚነት ተጠቅመው አብያተ ክርስቲያናትን በማቀራረቡና በማስታረቁ ሂደት ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አሳስበዋቸዋል፡፡

ንጉሡም በጻፉላቸው መልስ ላይ፥ “የልብን ሐሳብ የሚጥሉበት ሰው ማግኘት መንፈስን ማሳረፍ ነው፡፡ ይልቁንም አሁን ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው የነበሩት የካቶሊክ ፓፓ ባደረጉት ሁሉ ማድነቅዎ ጕዳዩ ሁሉ በሰፊው ቢገባዎ ነው፡፡ እኛም በዚሁ አኳኋን ነው የገባን፡፡” በማለት ብፁዕነታቸው ያላቸውን አስተውሎት በመግለጽ አድናቆታቸውን ቸረዋቸዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በዚያ ዘመን በሚስዮናውያን ላይ ይንጸባረቅ የነበረውን ጥላቻ ማሻሻል እንደሚገባ የክርስቶስን ትምህርት ጠቅሰው ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር፤ “ጌታችን እንዳለ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፤ ከእኛ ጋራም ስለማይከተል ከለከልነው ቢሉት፥ የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋራ ነውና አትከልክሉት እንዳለ በቅዱስ ወንጌል ያመነ ክርስቲያን ከሆነ የእኛ ማኅበር አይደለም በማለት ወንጌልን እንዳይነግር (እንዳያስተምር) መቃወም የክርስቶስ ፈቃድ አይሆንምና እንደዚህ ካለው ልማድ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡”
  
ይህን የመሳሰለው የለውጥ ሐሳባቸው ለጊዜው አዎንታዊ ምላሽ ባያገኝም፥ እርሳቸውንም ብዙ ዋጋ ቢያስከፍላቸውም አንዳንዱ ሐሳባቸው ቈይቶም ቢሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከወሰደቻቸው አንዳንድ ርምጃዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይም በአንድ ወንጌል እያመኑ በሰው ሠራሽ ባህል የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እንዲቀራረቡ ለማድረግ የተወጠነው ጥረት ብዙ እክሎች ቢገጥሙትና በተፈለገው ፍጥነት የሚፈለገውን ያህል ለውጥ አምጥቷል ባይባልም÷ እስካሁን ድረስ እንደ ቀጠለ ይታያል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ከሆኑ በኋላ፥ ስለ አብያተ ክርስቲያናት አንድነት በተለያዩ መድረኮች ይናገሩ እንደ ነበር በጽሑፍ የሰፈሩ ንግግሮቻቸው ምስክር ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ በየጊዜው በተለያዩ አገራዊ የጋራ ጕዳዮች ላይ እየተገናኙ በመሪዎች ደረጃ መምከራቸው በራሱ አንድ ርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ብፁዕነታቸው አገራዊ ጕዳዮችን በሚመለከት የተለያዩ የለውጥ ሐሳቦችን ለንጉሡ በደብዳቤ አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በኢየሩሳሌም ሳሉ ያስተውሉት የነበረው የዓለም ሁኔታ ስለ ኢትዮጵያም እንዲያስቡ ያስገድዳቸው ነበር፡፡ “በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢትዮጵያ ኅብረተ ሰብ መካከል የነበረው ያልተስተካከለ አስተዳደር እየታወሰኝ በዓለም ላይ በመሪውና በተመሪው ሕዝብ አለመግባባት የተነሣውን የእርስ በርስ ብጥብጥ ስመለከት በኢትዮጵያችንም እንደማይቀር በጕልሕ ይታየኝ ስለ ነበር፥ ከመሆኑ በፊት ስሜቴን ለግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ” የማስጠንቀቂያ ቃላትን ያዘሉ ደብዳቤዎችን በመጻፍ አሳስብ ነበር ይላሉ፡፡ መፍትሔ ይሆናል ብለው ካቀረቧቸው አስተያየቶች መካከል አንዱ በዓለም ላይ አሉ በተባሉ የሕግ ሊቃውንት የተሰናዳና ለሁሉም የሚበጅ ሕገ መንግሥት ቢዘጋጅ የሚል ነበር፡፡

ከኀይለ ሥላሴ መንግሥት መውደቅ በኋላም በዘመነ ደርግ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት እንዲቆም ደርግንና ሻዕቢያን ለማስታረቅ በተቋቋመው “ዕርቅ አፈላላጊ የሽምግልና ቡድን” ውስጥ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቡድኑ መሪ በመሆን ሁለቱን ወገኖች ለማስታረቅ በረሓው ድረስ ወርደው ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም ከሻዕቢያ በኩል በጎ ምላሽ ባለመገኘቱ የታሰበው ዕርቅ አልተሳካም፡፡ በዚህ ተግባራቸው ከሻዕቢያ በኩል ስድብ ነበር የተረፋቸው፡፡ ከዚያ ተመልሰው ምፅዋ ላይ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሄደው በማልቀስና እንባቸውን ወደ ባሕሩ በመፈንጠቅ÷ “አንተ ባሕር የኢትዮጵያ ልጆች ለአንተ ሲሉ አንገታቸውን ለሰይፍ አልሰጡም? ደማቸውን ከውሃህ አልቀላቀሉም? እነአሉላ እዚህ ድረስ የመጡት ምን ሊሠሩ ኖሯል? እውን አንተ የኢትዮጵያ አይደለህም? ... ” በሚለው ንግግራቸው በዚያ የነበሩትን ሁሉ አስለቅሰዋል፡፡ በስፍራው የነበሩት የ“ነበር” ጸሓፊ ስለ ብፁዕነታቸው የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ የሻዕቢያ መሪዎች ወዳሉበት በረሓ ለመድረስ አይደክማችሁም ወይ ተብለው ሲጠየቁ÷ “‘በዳዴ ሄደንም ቢሆን የሚሉንን መስማት አለብን’ በማለት አቡኑ መልስ ሲሰጡ የመንፈስ ጥንካሬያቸውን አደነቅሁ፡፡ የሰላም ናፍቆት÷ የወገንና የሀገር ፍቅር ስሜት ዕድሜአቸው ከሚፈቅድላቸው በላይ ለመሥዋዕትነት እንዳነሣሣቸው ሳስተውል ራሴን እንድፈትሽ ተገደድሁ፡፡ እኔም ሰላም እፈልጋለሁ፤ እኔም የወገንና የሀገር ፍቅር ስሜት በውስጤ አለ፡፡ ለዚህ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ፡፡ እንደ አቡነ ፊልጶስ ጳጳስ ሆኜ፣ ከሁሉም በላይ መቃብሬ የተማሰ፣ የግናዜ ልጥ የተራሰ ሽማግሌ ሆኜ ግን ያን ያህል መሥዋዕትነት ልከፍል የምነሣ አይመስለኝም” ብለዋል (ነበር ገጽ 156፡164-166)፡፡   

ውግዘት ያመጣው መጽሐፍ
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በተለያየ ጊዜና አጋጣሚ ልዩ ልዩ የለውጥ ሐሳቦችን ሲያራምዱ የነበረ ቢሆንም ዐልፎ ዐልፎ ግዞት እንጂ ውግዘት አልተላለፈባቸውም ነበር፡፡ በ1956 ዓ.ም. ያሳተሙትና “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ” የተሰኘው÷ ስለ ጌታችን ሥጋዌና የተዋሕዶ ምስጢር የሚናገረው መጽሐፍ ግን ውግዘት አስከትሎባቸዋል፡፡ ለውግዘቱ ምክንያት የሆነው ሐሳብ÷ ቃል ሥጋ ሆነ ብሎ የሚያምን ክርስቲያን ሁሉ “በክርስቶስ አካል በተዋሐደ[ሕዶ] ምስጢር ሁለት ባሕርያት÷ ባሕርይ መለኮታዊ፣ ባሕርይ ሰብኣዊ እንዳሉ ማመን ይገባዋል፡፡ የእምነት ምስጢር በፍራቻና በይሉኝታ አይለወጥም” የሚለው ዐቋማቸው እንደ ሆነ ግልጽ ነው፡፡

ጌታ በሥራውም በትምህርቱም ሰውነቱ ከመለኮቱ መለኮቱ ከሰውነቱ አለመለየቱን እያስረዳ÷ በሰው ቃል በመመራት አንድ ነው ሁለት ነው ብሎ ምን ያጣላል? ከእርሱ በላይ ስለ እርሱ ማን ሊናገር ይችላል? ሲሉ ብፁዕነታቸው ይከራከራሉ፡፡ ለአንድ ባሕርይ ባዮችም÷ “ክርስቶስ አንድ ባሕርይ ብቻ ነው ይባል ዘንድ የትኛውን ባሕርይ ትቶ የትኛውን ለመያዝ ነው? የትኛውን አውጥቶ የትኛውን ለማግባት ነው?” ሲሉ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

ይህ ዐቋማቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምታውቀው የጥንት እምነቷ እንጂ እንግዳ ነገር አለመሆኑን ሲሞግቱም እንዲህ ብለዋል፡፡ “በኢየሱስ ክርስቶስ አካል ባሕርይ መለኮታዊ ባሕርይ ሰብኣዊ ሁለቱ ባሕርያት ተዋሕደው የሚኖሩ መሆናቸው ሲነገር ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ወልድ ዋሕድ፣ ወልደ እግዚአብሔር፣ ወልደ እጓለ እመሕያው በማለት መለኮቱ÷ ከትስብእቱ ትስብእቱ ከመለኮቱ እንዳልተለየ የጥንት እምነቷ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡”

ብፁዕነታቸው እንደ ጻፉት በክርስቶስ ባሕርያት ላይ ልዩነትን ያመጣውና በቤተ ክርስቲያን መከፋፈልን የፈጠረው የኬልቆዶን ጉባኤ ነው፡፡ በጉባኤው የተነሡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች÷ አንዱ በሌላው ላይ የበላይ ለመሆን የነበራቸውን ምኞት የሃይማኖት ምስጢር በማስመሰል ቤተ ክርስቲያንን አዛዥና ታዛዥ እንዳሳጧት ይገልጻሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን የመከፋፈል መጥፎ ገጽታ ለመለወጥም÷ በጌታችንና በሐዋርያቱ ትምህርት÷ እንዲሁም በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ባገኙት በሦስቱ ጉባኤዎች (በኒቅያ፣ በቊስጥንጥንያና በኤፌሶን ጉባኤዎች) ውሳኔዎች መሠረት በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ÷ እንዲህ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡ “በክርስቶስ ወንድማማችነትና በክርስቲያናዊ ፍቅር ተገናኝተን ቤተ ክርስቲያን አንድ የምትሆንበትንና ክርስቲያን ሁሉ ሁሉም በክርስቶስ÷ እንደ አንድ ቤተ ሰብ ሆኖ በሃይማኖት የሚዛመድበትንና የሚተሳሰብበትን የፍቅርና የሰላም መገናኛ በር መክፈት ያስፈልገናል፡፡ እንዲህ ካላደረግን ግን እርስ በርሳችን ከመለያየት የተነሣ በክርስቲያናዊ ሰውና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው መለያየት ክርስቲያንን ሁሉ÷ የሚያሳስብ ነውና÷ ሁላችንም በቅንነት ተባብረን ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት በክርስቶስ ፍቅር ባለን ችሎታ ማሰብና ለእውነትም መመስከር ይገባናል፡፡”

እንደዚህ ያለ ይዘትና መልእክት ይዞ የወጣውን መጽሐፍ ተከትሎ በጊዜው የፓትርያርኩ እንደ ራሴ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ መጽሐፉን እንዲያርሙት ለብፁዕነታቸው የነገሯቸው ቢሆንም÷ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የሆነ ትምህርት ስላልሆነ ሊያርሙት እንደማይችሉ ይገልጻሉ፡፡ ከዚያ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ጥቂት ጳጳሳት ተሰብስበው ያስጠሯቸውና የጻፉት መጽሐፍ ከባህላችን ጋር የማይሄድ የካቶሊካውያን ባህል ስለ ሆነ÷ ተሳስቼ ነው የጻፍሁት ብለው እንዲያርሙት ቢነግሯቸው÷ ስሕተት አለው ካሉ እነርሱ መልስ ሊሰጡበት እንደሚችሉ በመንገር እርሳቸው ግን ሊያርሙት እንደማይችሉ በድጋሚ ያረጋግጣሉ፡፡ እነርሱም ቢሆኑ የብፁዕነታቸውን ጽሑፍ ሊያርሙት ወይም ምላሽ ሊሰጡበት አልቻሉም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ሐሳብ እንዴት ሊታረም ይችላል? በማለትም ከሳሾቻቸው እርማት ወይም መልስ መስጠት ያልቻሉበትን ምክንያት ብፁዕነታቸው ያስረዳሉ፡፡ “እውነተኛውን ምስጢሩን ሳይመለከቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሐዲስ ኪዳን ምስጢር ሳይነገረው በግብጾች ባህል መጋረጃ ተሸፍኖ በድንቊርና እንዲኖር በሚያደርጉት ዘዴ” መጽሐፋቸው እንደ ተወገዘም ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ብፁዕነታቸውን የተከተሏቸው እስርና ግዞት ናቸው፡፡

እንዲህ ማድረግ ለመንፈሳውያን መሪዎች  ይገባ ነበር ወይ? እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ሰው ከሚከተለው ሃይማኖት አስተምህሮ ወጥቶ ቢገኝ÷ ከተቻለ አስተምሮ መመለስ ካልተቻለም አውግዞ መለየት እንጂ እስርና ግዞት ይታወጅበት የሚል መንፈሳዊ ሕግ የለም፡፡ በቀደመው ዘመን ግን እንዲህ ይደረግ ነበር፡፡ እስሩና ግዞቱ ሕግን የተከተሉ እንዳልነበሩ ብፁዕነታቸው ይገልጻሉ፡፡ ሕግ ያለ መስሎኝ ወደ ንጉሡ ይግባኝ እላለሁ ብል ሰሚ አላገኘሁም፡፡ እነጳውሎስን የአይሁድ አለቆች ሲከሷቸው ጕዳዩ ይታይ የነበረው በከሳሾቹ በራሳቸው ሳይሆን ዳኝነትን በሚያዩ በሌሎች ገዢዎች ነበር፡፡ የእኔ ጕዳይ ግን በዚህ መንገድ አልነበረም የታየው፡፡ የቤተ ክህነት ሰዎች ራሳቸው ከሳሽ፣ ራሳቸው ፈራጅ ሆነው ከሕግ ውጪ ቀጡኝ ይላሉ፡፡

በመጀመሪያ እንዲታሰሩ ሲደረግ ንጉሡ ከሚኒስትሮቻቸው ጋር በቤተ ክህነት ሳሎን ውስጥ ሆነው የፈረዱባቸው መሆኑን የተገነዘቡት በኋላ ላይ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ግን መጽሐፉ ገና ወደ ኅትመት ከመግባቱ በፊት ለንጉሡ አሳይተው እንዲታተም ፈቅደውላቸው ነበር፡፡ ታዲያ ፊል ለፊት ሳይታዩ ከበስተ ጀርባ ሆነው ለምን እንዲታሰሩና እንዲጋዙ ፈረዱባቸው?   

ስደትና ግዞት
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የወንጌል ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ሕይወቱም የገባቸው አባት ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ወንጌል ዋጋ እንደሚያስከፍል የተገነዘቡና ስለ ተረዱት እውነት የሚመጣውን ማንኛውንም መከራና ችግር ለመቀበል ተምነው የወጡ የወንጌል ዐርበኛ ነበሩ፡፡ በመንፈሳዊም ሆነ በአገራዊ ጕዳዮች ላይ ባነሧቸው የለውጥ ሐሳቦች ምክንያት በተለያየ ጊዜ ስደተኛና ግዞተኛ ሆነዋል፡፡ ቀደም ብሎ እንደ ተጠቀሰው የግብጹን ጳጳስ በመቃወማቸው÷ እንዲሁም “ሰው እንዴት ከመሬት ተፈጥሮ መሬት ይነፈገዋል?” በሚለው መሬት ላራሹ ዐቋማቸው ተግዘዋል፡፡

ብፁዕነታቸው “ባመኑበት የሚጸኑ፣ ለጸኑበት የሚጋደሉ” የተባለላቸው አባት ናቸው፡፡ ይህም በንግግራቸውም ሆነ በሥራቸው የታየ ነው፡፡ ያስወገዛቸውን መጽሐፍ ለማዘጋጀትና ለማሳተም ሲነሡ÷ የሥራ ጓደኞቻቸው ባይገባቸውም እርሳቸው ሊደርስባው የሚችለውን ቀድመው ያወቁ መሆናቸውን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፤ “ይህን መጽሐፍ ስጽፍ ብዙ የቊጣ ማዕበል እንደሚነሣብኝና እንደ እስጢፋኖስም በድንጋይ እስከ መወገርም እንደሚደርስብኝ በማሰቤ÷ ከምስጢሩ ባለቤት ከጌታችን ጋራ በጸሎት ተነጋግሬ የሚደርስብኝን ፈተና ሁሉ የምችልበትን ጽኑ መንፈስና ችሎታ ስጠኝ ብዬ ለክርስቶስ ትስብእት (ሰው መሆን) ለመመስከር ራሴን መሥዋዕት አድርጌ ሕይወቴንም ቢሆን ለመስጠት ቃሌን ሰጥቼ የተነሣሁ መሆኑን አልገባቸውም ነበር፡፡” ይላሉ፡፡

የመጽሐፉን ሐሳብ አስቀድመው ላንዳንድ ሊቃውንት ሲገልጹላቸው በምስጢሩ የተደሰቱ ቢሆንም÷ ሊመጣ የሚችለውን መከራ ሲፈሩ ስላዩ ግን እኔው ብቻዬን እወጣዋለሁ ብለው÷ መጽሐፉ ገና ከማተሚያ ቤት ሳይወጣ ከፓትርያርኩ ጀመረው ለጳጳሳቱ አንድ÷ አንድ ኮፒ ላኩላቸው፡፡ ይህን ያደረጉትም አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉባኤ (በቅዱስ ሲኖዶስ) እንዲጠና በማሰብ ነበር፡፡ ሆኖም ሐሳባቸውን በሚገባ የተገነዘበላቸው ባለ መኖሩ ስደት ተነሣባቸው፡፡ 

በመጀመሪያ የይግባኝ መብት ተነፍገው በፓትርያርኩ ግቢ ውስጥ ጠባብና ቈሻሻ በሆነች ክፍል ውስጥ ለ5 ቀናት ያህል ከሰው እንዳይገናኙ ተደርገው ታስረዋል፡፡ ከዚያ ወደ አርሲ ተግዘው በአሰላ ከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሰው ሳይገናኙ እስረኛ ሆነዋል፡፡ በእስር ላይ እያሉም በጠና ስለ ታመሙ ወደ ናዝሬት ሄደው ሕክምና እንዲከታተሉ ከተደረገ በኋላ÷ የግዞቱ ቦታ እንዲለወጥላቸው በሐኪም ተወስኖ ወደ ጅማ ተልከዋል፡፡

በጅማ ሳሉ ከንጉሡ ጋር ተጻጽፈው አንዳንድ መሻሻሎች የተደረጉላቸው ሲሆን÷ ከቤተ ክህነት በደብዳቤ ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ ሲመጡ ነገሮች ተሻሽለው የሚጠብቋቸው መስሏቸው ነበር፡፡ የሆነው ግን በመጀመሪያ በታሰሩባት ቈሻሻ ክፍል ውስጥ ዳግም መታሰር ነበር፡፡ ለግዞትና ለእስር ምክንያት የሆነውን መጽሐፍ የጻፉት በስሕተት መሆኑን አምነው ይቅርታ መጠየቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ቤተ ክህነቱ አዘጋጅቶ እንዲፈርሙበት ከአንዴም ሦስት ጊዜ ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕነታቸውም ለመፈረም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ዳኝነት እንዲታይላቸው ንጉሡን ቢያስጠይቁ ጃንሆይ “እኛ በዚህ ነገር ዳኝነት ለማየት አንችልም፤ በዚሁ ወረቀት ይፈርሙና አርፈው ይቀመጡ” የሚል መልእክት በልዑል ራስ እምሩና በሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅ ነህ በኩል ስለላኩባቸው÷ ፍትሕ በሌለበት ሁኔታ መፍጨርጨሩ ዋጋ እንደሌለው በመገንዘብ÷ እጃቸው ባልጻፈውና ልባቸው ባላመነበት ወረቀት ላይ ተገደው ፈረሙ፡፡ ልዑል ራስ እምሩም ከጳጳሳቱ ጋር አስታረቋቸው፡፡ ይሁን እንጂ ዕርቁ ሥርዐታዊ እንጂ ልባዊ ስላልነበረ÷ በውጭ አባታችን እየተባሉ ግፉን ተሸክመው እንደ ኖሩና ከቁም እስር እንዳልተላቀቁ ገልጸዋል፡፡

ተደረገ የተባለውን ዕርቅ ተከትሎ ታኅሣሥ 22/1958 ዓ.ም በወጣው በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ 21ኛ ዓመት ቊጥር 4 ላይ እና በዐዲስ ዘመን ጋዜጣ 25ኛ ዓመት ቊጥር 452 ግንቦት 19/1958 ዓ.ም. የወጡት መረጃዎች÷ ብፁዕ አቡ ፊልጶስ ባወጡት መጽሐፍ መሳሳታቸውን እንዳመኑና ይታረም ዘንድ እንደ ተስማሙ የሚያመለክቱ ነበሩ፡፡ ብፁዕነታቸው ግን በቤተ በክህነቱ በተዘጋጀው ወረቀት ላይ ተገደው ከመፈረም በቀር÷ በዚያ ጊዜ “በመሳፍንት ትንፋሽ በሚመራው” ባሉት ሲኖዶስ ፊት ቀርበውና ተጠይቀው የሰጡት አንዳች መልስ እንደሌለ ያረጋግጣሉ፡፡

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን ለዚህ ሁሉ መከራ ያደረሷቸው ንጉሡ መሆናቸውን የተረዱት በኋላ ላይ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በኢየሩሳሌም ሳሉ በጻፉላቸው አንዳንድ ደብዳቤዎች አለ መደሰታቸው ሳይሆን አልቀረም፡፡ በርግጥ የብፁዕነታቸው ማሳሰቢያዎች ደፋሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ሁሉን ሊጠቅም የሚችል ሕገ መንግሥት በዕውቅ የሕግ ሊቃውንት እንዲዘጋጅ ያድርጉ ሲሉ÷ በ1923 ዓ.ም. እና በ1948 ዓ.ም. ንጉሡ ያወጧቸው ሕገጋተ መንግሥት ጕድለቶች እንዳሉባቸው የሚጠቊም ነው፡፡ ንጉሡ በዚህ ቢከፉና ብፁዕነታቸውን በተገለጸው መንገድ እንዲቀጡ ቢያደርጉ ብዙም የሚደንቅ አይደለም፡፡ ማሳሰቢያዎቹ በንጉሡ ዘንድ ተሰሚነትን ቢያገኙ ኖሮ ግን የንጉሡ ፍጻሜ እንዲያ ባልከፋ÷ ኢትዮጵያንም ወደ ተሻለ ሁኔታ ባደረሷት ነበር፡፡ ነገር ግን “ካቀዱት ሳይደርሱ ጊዜ እንዳይቀድምዎ ... ጊዜውን ይቅደሙት” ለሚለው የብፁዕነታቸው ምክር ጆሮ ዳባ ስላሉ እንደ ተባለው ጊዜ ቀደማቸው፡፡

“ይትፌሣሕ ጻድቅ ሶበ ይሬኢ በቀለ - ጻድቅ በቀልን ባየ ጊዜ ደስ ይለዋል” ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. 57(58)÷10)÷ ብፁዕነታቸው በመጨረሻ ላይ መከራ ያደረሱባቸውን÷ “ልብንና ኵላሊትን የሚመረምረው አምላክ በአናጋሪው መንግሥት በተናጋሪው ካህን ላይም የፈጸመውን አምላካዊ ፍርድ በመሬት ላይ ቆሜ እየተመለከትሁ ኰናኒ በጽድቅ ፈታሒ በርትዕ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ሲሉ ጽፈዋል፡፡

ሆኖም በመጀመሪያው ገጽ ላይ “መልእክት የክርስቶስን አዳኝነት ለተቀበለ ክርስቲያን ሰው ሁሉ” በማለት የሚጀምረውንና “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ” የተሰኘውን ሁለተኛ መጽሐፍ የጻፉበት ዋና ምክንያት “ያለፉትን ሰዎች ለመውቀሥ ሳይሆን÷ ተከታዩ ትውልድ እንዲመከርበት ነው” ይላሉ፡፡ በማስከተል “መሓሪ ይቅር ባይ እግዚአብሔር ያለፉትን ይቅር ይበላቸው፤ ተከታዮችንም ይህን የመሰለ ስውር ኀጢአት ከመሥራት ያድናቸው ስል ቅዱስ ይቅርታውን እለምናለሁ” በማለት መጸለያቸውም ለጠላቶቻቸው ያሳዩትን የፍቅር ልብ ሊያሳይ ይችላል፡፡

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ኅዳር 11 ቀን 1974 ዓ.ም. በተወለዱ በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው በብዙ መከራ ወዳገለገሉት ጌታ በክብር ሄደዋል፡፡ ሥርዐተ ቀብራቸውም በኢየሩሳሌም ተፈጽሟል፡፡

እናስተውል!        
ራሱን ያለ ምስክር ያልተወው ቅዱስ እግዚአብሔር÷ በዘመናት ሁሉ ለመንግሥቱ ሥራ የሚቀኑና ስለ ስሙ መሥዋዕትነትን ለመክፈል በነፍሳቸው የሚወራረዱ አገልጋዮች አሉት፡፡  እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ግን ብርቅ ናቸው፤ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ብልጭ ብለው ድርግም የሚሉ፡፡ ታሪካቸውና የሥራቸው ፍሬ ግን መካን አይደለም፡፡ ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ዕጥፍ የሚያፈራና ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡ የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተጋድሎና የአገልግሎት ፍሬ÷ አሁን ላለው ክርስቲያን ትውልድ÷ ወንጌል በነፍሱ የሚወራረድ ቈራጥ ክርስቲያንን እንደሚፈልግና ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልም ያስተምራል፡፡

ቤተ ክርስቲያን አንዲትና የማትከፈል በመጽሐፍ ቅዱስም የምትመራ የክርስቶስ አካል መሆኗ ቢታወቅም በምድር ላይ ተከፋፍላ ትታያለች፡፡ ይህ የጠላት ሐሳብ እንጂ የእግዚአብሔር ሐሳብ ስላልሆነ÷ አሁን ያለችው ቤተ ክርስቲያን ልዩነትን ከማስፋት ይልቅ ልዩነትን በማጥበብና ከራስ ባህል ይልቅ ለእግዚአብሔር ቃል ቅድሚያ በመስጠት÷ ብፁዕነታቸው እንዳሉት÷ “በእምነትና በጥምቀት ከሚመስሉን ከክርስቲያኖች ወንድሞቻችን ጋራ የፍጡር አእምሮ ሊደርስበት በማይቻል በመለኮታዊ ባሕርይ ምርምር መጣላት አይገባም፡፡” ከዚህ ይልቅ በክርስቶስ ትእዛዝ በፍቅር ሆኖ ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋት በጋራና በመረዳዳት መሥራት ክርስቲያንነት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከራሷ ልጆች በየዘመናቱ የሚቀርብላትን የለውጥ ጥሪ ሳትፈትሽና ሳትመረምር ቀድማ ከምትገፋው ይልቅ÷ በልበ ሰፊነት ተቀብላ ብትመረምረውና የተሻለና ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይቃረን ሆኖ ካገኘችው ብትጠቀምበት መልካም ነው፡፡ ብፁዕነታቸው ያቀረቧቸውና ያስተላለፏቸው የለውጥ ጥሪዎች ብዙዎቹ ተፈጻሚ እየሆኑና ተቀባይ እያገኙ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለጥሪው ምላሽ ያልሰጡትም ለጊዜው ቢመስልም ለውጡን አፍነው መያዝ ግን አልቻሉም፡፡ ዛሬም ለውጥን በደፈናው ከመቃወም ይልቅ ተቀብሎና መርምሮ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አስተዋይነት ነው፡፡



ዋቢ መጻሕፍት

መልአከ ሕይወት ይትባረክ እና ገብረ ዮሐንስ (1996) ትምህርተ ቴዎፍሎስ፡፡ አዲስ አበባ፣ (ማተሚያ ቤቱ ያልተገለጸ)፡፡
መርሻ አለኸኝ (ዲያቆን) 1997 ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፡፡ ኢትዮ ጥቁር አባይ ፕሪንተርስ፣ አዲስ አበባ፡፡
አባ ፊልጶስ (ሊቀ ጳጳስ) (1956) እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ፡፡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፡፡
                                (1969) “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ” (2ኛ መጽሐፍ)፡፡ አዲስ አበባ፡፡
ዘነበ ፈለቀ (2002) ነበር፡፡ አዲስ አበባ፣ (ማተሚያ ቤቱ ያልተገለጸ)፡፡
የኢትዮጵያ ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም የታሪክ መስተዋት፡፡ (1980) አዲስ አበባ፣ ንግድ ማተሚያ ቤት፡፡

በጮራ ቍጥር 39 ላይ የቀረበ

1 comment:

  1. ሰውየው የክርስትና ሃይማኖት በሚገባ የገባቸውና ቃሉ የሚናገረውን ትምህርቱንም ለመኖር የተጉ ሰው ነበሩ፡፡ ከቤተ ዘመድ ጠይቄ እንደተረዳኹት ከቤተ ክህነቱ (ከቤተ ትክነቱ/ ከቤተ ምክነቱ) እስር ከወጡ በኋላ እስከ ዕድሜያቸው ፍጻሜ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር አላት የሚባለው ብቸኛው ነገረ ክርስቶስን የተመለከተ ልዩነት እንደሌለ አስረግጠው ይናገሩ ነበር፡፡ ጉባኤ ኬልቄዶን ላይ የቀድሞው የነቅዱስ ቄርሎስ ሃይማኖት ተብራራ እንጂ አዲስ የተረቀቀ ሃይማኖት እንደሌለ አሳምረው ዐውቀውት ነበረ፡፡ ጉባኤው በተካኼደበት በአምስተኛው ክፍለ ዘመን በነበሩ ጳጳሳት መካከል የነበረውን ፍጹም ኢክርስቲያናዊ የኾነ ፖለቲካዊ ሽኩቻና ሽኩቻው የወለደው ሃይማኖትን መጠቀሚያ ያደረገ “እነእገሌ መናፍቃን ናቸው፡፡” የሚል የሐሰት ፕሮፓጋንዳ አንዳች የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እንደለያያት መገንዘብ ችለው ነበር፡፡

    ልክ ዛሬ አሜሪካን ያለውና ኢትዮጵያ ያሉት “ሲኖዶሶች” አንዱ ሌላውን “መናፍቃን ናቸው፤ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አፍራሾች ናቸው!” እያለ እንደሚወጋገዙት መኾኑ ነው፡፡ ኹለቱም በሚያወጧቸው መግለጫዎች ራሳቸውን የሃይማኖቱ ጠበቃ አድርገው ሲያቀርቡ እንጂ እኛ ሥልጣናችን እንዳትነካብን፣ ምቾታችን እንዳትጎድልብን ነው ብለው ተናግረው አያውቁም፡፡ እነርሱ ሲሞቱ የሚቀጥለው ትውልድ ይኽን ፖለቲከኛነታቸውንና የሥልጣን ጥማቸውን ስለማያውቅ መግለጫ እያሉ በሚለቀልቋቸውና በሚለፍፏቸው ጽሑፎች ላይ ተመርኩዞ እውነት የሃይማኖት ልዩነት ያለ ይመስለው ይኾናል፡፡ ብፁዕነታቸው አቡነ ፊልጶስ ግብፆች እነርሱ ከዓለም የክርስቲያን ወገኖች ተገንጥለው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንም ገና በአፍላነት ዕድሜዋ እንደገነጠሏት ይኽም የኢትዮጵያን ክርስትና በጊዜ ኺደት ብስል ከጥሬ የተቀላቀለበት፣ ክርስትና በሚል ስም ክርስቲያናዊ ያልኾኑ ነገሮች የተሠገሠጉበት፣ ክህነትና ጥንቆላ አንድ ላይ ተዳብለው የሚኖሩበት እንዲኾን እንዳደረገው ያስተዋሉ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ እነርሱ በ1973 እ.አ.አ. ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር በነገረ ክርስቶስ ልዩነት እንደሌላቸው በጋራ ባወጡት መግለጫ ሲገልጹ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን “የት ነበርሽ?” ብለው እንኳ ያማከሯት አይመስለኝም፡፡ እነርሱ ዘመኑን አስተውለው የአባቶቻቸውን ስሕተት መርምረው ለመሻሻል ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ እውነቱን የሚያውቁ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ሊቃውንት ግን ዛሬም በፍርኀት ተሸማቅቀው ይኖራሉ፡፡ አቡነ ጳውሎስ እንኳ የሚያውቁትን እውነት መናገር ፈርተው ነበር የኖሩት፡፡ እውነቱ ግን ይኸው ነው፡፡ እስኪ ደግሞ ስለ ሊቁ ዓለማየኹ ሞገስ አስነብቡንና “ኹሉም ኹሉን ይወቅ፡፡”

    ReplyDelete