Thursday, July 11, 2013

ክርስትና በኢትዮጵያ



የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

ካለፈው የቀጠለ

ሦስተኛ፥ የመሰብሰቢያ ሕንጻ ማሠራቱ

ታላቁ ሐዋርያችን ፍሬምናጦስ በእርሱ ስብከት መነሻ በጌታ ያመኑትን በአንድ መንፈሳዊ ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) አሰባሰበ፡፡ ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ተብላ ለተሠየመችው ማኅበረ ምእመናን አመራር ሰጪ አካል የሆነ ድርጅት አቋቋመ፡፡ ለድርጅቱ ሥራ መንፈሳውያን አገልጋዮችን መርጦ በመሾም ማኅበሩን አጠናከረ፡፡ ይህን ሁሉ እያሟላ ካደራጀ በኋላ ፊቱን የመለሰው ለመሰብሰቢያና ለጽሕፈት ቤት የሚሆን ሕንጻ ወደ ማሠራት ነበር፡፡ ክርስትና ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ከተሰበከባት ከግሪክ የመጣ እንደ መሆኑ መጠን፣ ሕንጻው የት ይሠራ ለሚለው ጥያቄ ፍሬምናጦስ መልስ ነበረው፡፡ ቀደም ብሎ ይሠራበት የነበረውን ትውፊት መሠረት በማድረግ የማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት አስተዳደር ማእከልን በአክሱም መመሥረት ነበረበት፡፡

ስለዚህ ለሚጠፉት ሞኝነት፣ ለሚድኑት ግን የእግዚአብሔር ኀይል የሆነው የክርስቶስ የመስቀሉ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰበከባትና ፍሬ ባፈራባት በመዲናዋ በአክሱም ለማኅበሩ በማእከልነት የሚያገለግለው ሕንጻ እንዲሠራ ተወሰነ፡፡ እንደዚህ ላለው ጕዳይ በምርጫው ብቸኛ ሆኖ የሚቀርበው በአንድ ሀገር ወይም አውራጃ ለመጀመሪያ ጊዜ “መስቀል የተተከለበት ነው” ተብሎ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ታሪካዊ ስፍራ ለወንጌል ሥርጭትና ለምእመናን መንፈሳዊ አስተዳደር ማእከል በመሆን እንዲያገለግል ይደረጋል ማለት ነው፡፡


በፍሬምናጦስ ስብከት ክርስቲያን በሆኑት በታላቁ ነጉሠ ነገሥት በአብርሃ፣ በወንድሙም በአጽብሐ ሙሉ ርዳታ በአክሱም ስለ ተሠራው ሕንጻ ዝዋይ ላይ በተገኘው ታሪከ ነገሥት የተጻፈውን በመጥቀስ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አስተዋፅኦ (ያልታተመ) ላይ የተመዘገበው እንዲህ ይላል፣ “ከመዝ ኑባሬ ሥረታ ለእምነ ጽዮን ገበዘ አክሱም እስከ ዐሠርቱ ወኀምስቱ በእመት ኢረከቡ መሠረታ፤ ወጸፍጸፋ ሰብዐቱ በእመት፣ ወኑኃ እምሥራቅ እስከ ምዕራብ ምእት ዕሥራ ወኀምስቱ በእመት፡፡ እም ደቡብ እስከ ሰሜን ተስዓ ወክልኤቱ በእመት፡፡ ወስፍሓ ኀምሳ ወሠለስቱ በእመት፡፡ ወኑኃ እምድር እስከ ርእሰ ቀመር ሠላሳ ወክልኤቱ በእመት፡፡ አዕማድ ዘንድቅ ሠላሳ፣ ወአዕማድ ዘዕብን ሠላሳ ወክልኤቱ፡፡ ወኵሉ ድሙር ስድሳ ወክልኤቱ፡፡ ማዕፆ ዐቢያን ዘአናቅጽ መንገለ ዓረብ በአፍኣ አርባዕቱ፤ ወዘውስጥ አርባዕቱ፤ ወዘጽርሕ ሠለስቱ፤ ሰሜናዊ አሐዱ፤ ደቡባዊ ዘቤተ ጊዮርጊስ አሐዱ፤ ዘቤተ ዮሐንስ አሐዱ፣ ዘቤተ መዛግብት ክልኤቱ፣ ዘቤተ ማኅበር አሐዱ፣ ዘቤተ ማርያም መግደላዊት አሐዱ፡፡ … ወኵሉ ድሙር ዕሥራ ማዕፆ ዘቄድሮስ አርባዕቱ ምእት ሰብዐ ወአሐዱ መሳክዊሃ፡፡ ምእት ዕሥራ ወሰመንቱ መንኰራኵራቲሃ፡፡ ሰብዐቱ ምእት ቀስተ ደመና፣ ወርእሰ ህባይ ሠላሳ ምእት ወሰመንቱ ምእት ዐሠርቱ ወኀምስቱ፡፡ ወመሥረበ ማይሂ ተሰዓ ወአሐዱ፡፡ በሠለስቱ ምእት አርብዓ ወአርባዕቱ ዓመተ ምሕረት ኮነ ሡራሬሃ፣ ወተፍጻሜታ በተሰዓ ወአሐዱ ዓመተ ምሕረት፡፡ ዓለምሰ ጽላሎት ወሕልም ውእቱ፤ አልቦ ዘይትዌሰክ ዘእንበለ ዘይነትግ፡፡”

ትርጓሜ፡- “የእናታችን ገበዘ አክሱም ጽዮን የአመሠራረቷ ሁኔታ እንደዚህ ነበር፡፡ መሠረትዋን እስከ ዐሥራ አምስት ክንድ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ ደረጃዋ ሰባት ክንድ ነበር፡፡ ርዝማኔዋ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ መቶ ሃያ ዐምስት ክንድ ነበር፡፡ ከደቡብ እስከ ሰሜን ዘጠና ሁለት ክንድ ነበር፡፡ ቁመቱም ከምድር እስከ ቀመሩ ራስ ሠላሳ ሁለት ክንድ ሲሆን፣ ስፋቱ ዐምሳ ሦስት ክንድ  ነበር፡፡ በግንብ የተሠሩ ዐምደ ወርቆች ሠላሳ ነበሩ፡፡ ከድንጋይ ተጠርበው የተዘጋጁ አዕማደ ወርቅ ሠላሳ ሁለት ነበሩ፡፡ ሁሉም በሁሉም ሲደመሩ ስድሳ ሁለት አዕማደ ወርቅ ነበሩ፡፡ የታላላቅ በሮች መዝጊያዎች ከወደ ምዕራብ ወገን ውጭ አራት፣ የውስጥም አራት፣ የአዳራሹ ሦስት፣ በስተ ሰሜን አንድ፣ የደቡባዊ የቤተ ጊዮርጊስ አንድ፣ የቤተ ዮሐንስ አንድ፣ የቤተ መዛግብት (ጽሕፈት ቤትና ግምጃ ቤት) ሁለት፣ የቤተ ማኅበር አንድ፣ የቤተ ማርያም መግደላዊት አንድ፣ በድምሩ ከዋንዛ ዕጨት የተሠሩ መዝጊያዎች ኻያ ናቸው፡፡ መስኮቶች አራት መቶ ስድሳ አንድ ነበሩ፡፡ መቶ ዐሥራ ስምንት መንኰራኩሮች፣ በቀስት የተሠሩ ሰባት መቶ ቀስተ ደመናዎች ነበሩ፡፡ ርእሰ ህባይ (የዝንጀሮ ራስ ቅርጽ ያላቸው) ሦስት  ሺሕ ስምንት መቶ ዐሥራ ዐምስት ነበሩ፡፡ የውሃ መውረጃዎች ዘጠና አንድ ነበሩ፡፡ በ344 ዓ.ም. የሕንጻው መሠረት ተጀምሮ በ391 ዓ.ም. ሥራው ተጨርሷል፡፡ ዓለም ግን ሕልምና ጥላ ነው፡፡ እያደር ከመጕደል በቀር የሚጨምረው የለም” ይላል፡፡

ስለ ሕንጻው አሠራር መግለጫ ሆኖ በተጻፈው በዚህ ታሪክ ላይ ሕንጻው፣ የተለያዩና እየራሳቸው በር ያላቸውን ብዙ የሥራ ክፍሎችን የያዘ እንደ ነበረ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህም ክፍሎች መካከል በጊዮርጊስ፣ በዮሐንስ፣ በመግደላዊት ማርያም ስም የተሠየሙ አዳራሾች እንደ ነበሩ ይተርካል፡፡ ቤተ መዛግብትና ቤተ ማኅበር የተባሉ አዳራሾችም በሕንጻው የነበሩ መሆናቸውን ታሪኩ ይገልጻል፡፡ ይህ ታላቅ ሕንጻ ወደ ኀምሳ ዓመት የሚጠጋ የሥራ ጊዜ ወስዷል፡፡ ሆኖም ሕንጻው በጉዲት ወረራ የወደመ መሆኑ ወደ ፊት በሚያጋጥመን ታሪክ በዝርዝር ይገለጻል፡፡ ዳሩ ግን ይህን ያህል ጊዜ፣ ይህን ያህል ጕልበትና ገንዘብ የፈሰሰበት ሕንጻና ብዙ ድካምን በጠየቀ ጥናት የተቋቋመ ድርጅት በጉዲት ወረራ እንዳልነበረ በመደረጋቸው ተራኪው “አይ ያለም ነገር መጕደል እንጂ መጨመር የለም!!” በማለት በሃይማኖት ወዳድነትና ባገር ፍቅር ስሜት ልባዊ ሐዘኑንና ቍጭቱን ገለጸ፡፡ ሆነ፤ ከዚህ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? በነበረው ላይ እየጨመሩ መጓዝና ማለፍ ቢኖር ምድራችን ምን በመሰለች? ያለፈው ትውልድ ሠርቶ አሳምሮ የተወውን መጭው በላዩ በማከልና ለሚቀጥለው ትውልድ አስተላልፎ በማለፍ ፈንታ አውድሞ ማለፍ ያለፉትን አባቶች ውለታ ማጥፋትና ምቀኝት ሲሆን አደራ በላ መሆንና የተተኪውንም ዕድል ማበላሸት አይደለምን?

አራተኛ፥ መንበሩን በሊቀ ጵጵስና ማሳደጉ

ፍሬምናጦስና ረዳቶቹ ኢትዮጵያውያን አበው ያቋቋሟት፣ በተስተካከለና በሠመረ አመራር ያማከሏትና በተሟላ ድርጅታዊ አሠራር ያዋቀሯት “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” በኢትዮጵያ መዲና በአክሱም ቆማ በሀገር ውስጥ ክርስትና እንድታስፋፋ፣ በማሳደግና በማጠናከር የፈጸሙት ሥራ ብቻውን በታሪክ ሲወደስ የሚኖር የሥራ ውጤት ነው፡፡ ፍሬምናጦስ ግን ከዚህ ወሰን ያለፈ ታላቅ ሥራን በማከታተል አከናውኖ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የተቋቋመችው የእግዚአብሔር መንግሥት በጥራትና በጥንካሬ ታደርገው የነበረ እንቅስቃሴ በሲኖዶስ በተማከሉት ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንዲታወቅላት ያደረገው ጥረት ለፍሬምናጦስ ሠምሮለት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ለፈጸማቸው ተወዳጅ ሥራዎች መግለጫ ይሆኑ ዘንድ፣ በስሙ ላይ ሰላማ እና ከሣቴ ብርሃን ተጨምረዉለት የሚጠራው ፍሬምናጦስ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያቋቋመውን የክርስቲያናዊ ድርጅት ታሪክ በሌሎቹ የዓለም ክፍሎች ከሆነው ዕውቅ ታሪክ ጋር ለማስተያየት እንዲያመች ቀጥሎ የተመለከቱትን ልናጤናቸው ይገባል፡፡ በዚያ ዘመን አካባቢ፦
1. ኢትዮጵያን ያስተዳድር የነበረው ታላቁ ንጉሥ አብርሃ እንዲሁም ተከታዩና ረዳቱ የሆነ ወንድሙ አጽብሐ፣
2.ሰፊውን የሮምን ግዛት አጠቃሎ ይገዛ የነበረው ቄሣር ታላቁ ቈስጠንጢኖስ፣
3.            በእስክንድርያ የሊቀ ጵጵስና መንበር የተቀመጠው እለእስክንድሮስን የተካው በስሙ ላይ ሐዋርያው የሚል ማጐልመሻ የተጨመረለት አትናቴዎስ፣

በየመንበራቸው ሆነው ታሪክ በከፍተኛ ደረጃ የመዘገበላቸውን ሥራዎች በየፊናቸው ይሠሩ ነበር፡፡

በዚያ ዘመን በእስክንድርያ ቄስ የነበረ አርዮስ፣ ወልድ በመለኮቱ ፍጡር ነው ብሎ ያስተማረውን ትምህርት ለመመርመር በቈስጠንጢኖስ ጥሪ የሃይማኖት አባቶች በኒቅያ ተሰብስበው ነበር፡፡ አትናቴዎስን አስከትሎ በጉባኤው የተገኘውና ለተቃራኒው ቡድን አፈ ጉባኤ ሆኖ የተከራከረው እለእስክንድሮስ፣ ከእግዚአብሔር ቃል እየጠቀሰ ያቀረባቸውን ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥቦችና ማስረጃዎች ጉባኤው ከመረመረ በኋላ አርዮስ ከቤተ ክርስቲያን እንዲለይ ወሰነበት፡፡ ጥቂት ቈይቶም አርዮስ ተጸጽቻለሁና ልመለስ በማለት ሲያመለክት፣ ቈስጠንጢኖስ ወደ ሥራው እንዲመለስ እለእስክንድሮስን ለተካው ለአትናቴዎስ የትእዛዝ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ ቈስጠንጢኖስ የሥልጣኑ ክልል ሳይሆን በመንፈሳዊው ጕዳይ ገብቶ ያስተላለፈለትን ትእዛዝ አትናቴዎስ አልቀበልም በማለቱ በልዩ ልዩ ምክንያት እንዲከሰስና እንዲሰደድ ተወሰነበት፡፡ ቈስጠንጢኖስ ሲሞት አትናቴዎስ ወደ መንበሩ እየተመለሰ ለሁለተኛ፣ ለሦስተኛም ጊዜ ከተሰደደ በኋላ እንደ ገና ተመልሶ በመንበረ ሊቀ ጵጵስና ተቀምጦ ነበር ተብሎ ይተረካል፡፡

አትናቴዎስ ከስደት ተመልሶ በመንበሩ ላይ በተቀመጠበት በአንደኛው ጊዜ፣ ፍሬምናጦስ ድጋሚ ሊጐበኘው እንደ ሄደ ይገመታል፡፡ አትናቴዎስ ከስደት እንደ ተመለሰ እግዚአብሔር እንኳ ለመንበርህ አበቃህ ለማለት ወደ እስክንድርያ ሄዶ ሳለ፣ እግረ መንገዱን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የክርስትና መስፋፋት ፍሬምናጦስ በዝርዝር አጫውቶት ይሆናል ይባላል፡፡ አትናቴዎስም ምናልባት ጕዳዩን ቀደም ብሎም ተከታትሎት ሊሆን ስለሚችል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለ ተጽዕኖ ሥራዎችን ለማካሄድ መንገዱ ክፍት ይሆንላት ዘንድ “አንበረ እዴሁ ሊቀ ጳጳሳት ዲበ ርእሰ ፍሬምናጦስ ወጸለየ ጸሎተ ተክሪዝ ዘሢመተ መጥረጶሊስ፡፡ ፍሬምናጦስ መጥሮፖሊታን ይሆን ዘንድ የሚያበቃውን የሹመት ማዕርግ ሊሰጠው ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስ የተክሪዝን ጸሎት አደረሰለት” ተብሎ በመጽሐፈ ምስጢር ተገልጿል፤ አትናቴዎስ ፍሬምናጦስን የታዳጊዋ ቤተ ክርስቲያን ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ሾመው፤ የማዕርግ እድገት ሰጠው ማለት ነው፡፡

ሜጥሮጶሊስ ያንድ ሀገር ዋና ከተማ፤ መዲና ማለት ስለሆነ፣ በመዲናዪቱ መንበሩን ዘርግቶ ሀገራዊት ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተዳድር፣ የሚመራ፣ የሚቈጣጠር መንፈሳዊ አባት ሜትሮፖሊታን (ዓቢይ ጳጳስ ወይም ሊቀ ጳጳሳት) ይባላል፡፡ እንዲህ ከሆነም ሊቀ ጳጳሳት ፍሬምናጦስ መንበሩን በሀገሪቱ መዲና በአክሱም መሥርቶ በኢትዮጵያ በመላዋ እየተስፋፋ የነበረውን በክርስትና ላይ የተመሠረተውን አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመምራት የሚያስችለውን ሁሉ የማደራጀት ሙሉ ሥልጣን አገኘ ማለት ነው፡፡

የሊቀ ጵጵስናው መንበር በአክሱም በመሆኑም ከእርሱ ቀጥሎ የተሾሙት ባለ መንበሮች በዐጭር ሥያሜ “ጳጳሳተ አክሱም” እየተባሉ በተለይ በሀገሪቱ መዲና ስም ቢጠሩም፣ በሹመታቸው የሚያስተዳድሩት የመላዋን ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ባንዳንድ ስፍራም “ሊቀ ጳጳሳት ዘዲበ ርእሰ ሀገረ አበዊነ …” የሚለውን ንዑዳን አባቶች ሲተረጕሙት “በሀገሪቱ መዲና በአክሱም የተሾመ ንዑድ ክቡር የሚሆን አባ ሰላማ …” ይሉና “ርእስ ማለት አክሱም፣ ሀገር ማለት መላዋ ኢትዮጵያ” ብለው ማብራሪያ ይሰጡበታል (ትርጓሜ ቅዳሴ ማርያምን ይመልከቱ)

ዐምስተኛ፥ ለመንበረ ሊቀ ጵጵስናው ዓለም አቀፋዊ እውቅናን ማስገኘቱ

ከሐዋርያት ጀምሮ በመጀመሪዎቹ 300 ዓመታት ውስጥ ዐልፎ ዐልፎ ባንዳንድ ሌሎች ሀገሮች ውስጥ ክርስትና ቢስፋፋም፣ ጐልቶ የታየ ድርጅታዊ ጥንካሬ የነበራቸው አብያተ ክርስቲያናት የተገኙት በሰፊው በተንጣለለው የሮማ የቄሣር መንግሥት ግዛት ውስጥ እንደ ነበረ በታሪክ የታወቀ ነው፡፡ በኒቅያ ከተማ ጉባኤ የተቀመጡት አባቶች በአርዮስ የኑፋቄ ትምህርት ላይ ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን ለማሳደግና ለማስፋፋት አንድነቷንም ለመጠበቅ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በስምምነት አሳለፉ፡፡ ጐልተው ከሚታዩት አስተዳደራዊ ውሳኔዎች መካከል ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ህልውና መጠበቅ የተማከለ ሲኖዶስ መኖሩ አስፈላጊ እንደ ሆነ በማመን፣ በተጠሪነትና በሲኖዶስ አባልነት ሊታወቁ የሚገባቸውን መናብርተ ሊቀ ጵጵስናን መወሰንና ሀገረ ስብከታቸውን ማደላደል የሚሉት ዋናዎቹ ነበሩ፡፡

በሮም የቄሣር መንግሥት ግዛት ውስጥ የነበሩትን በታሪክና በወቅቱ እይታ፣ ተያይዞም በደረሰው ትውፊታዊ አቋማቸው ለማእከላዊ ሲኖዶስ ተጠሪና ቋሚ አባላት ሊሆኑ የተገባቸውን አብያተ ክርስቲያናት በአራት መናብርተ ሊቀ ጵጵስና ማለት፡-

ሀ) በምዕራቡ የሮማ የቄሣር መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በሮማ መንበረ ሊቀ ጵጵስና
ለ) በደቡብ የሮማ የቄሣር መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በእስክንድርያ መንበረ ሊቀ ጵጵስና
ሐ) በሰሜኑ የሮማ የቄሣር መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በኤፌሶን መንበረ ሊቀ ጵጵስና
መ) በምሥራቁ የሮማ የቄሣር መንግሥት ግዛት ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በአንጾኪያ መንበረ ሊቀ ጵጵስና ሥር እንዲጠቃለሉ ሲወሰን፣ ከሮማ የቄሣር ግዛት ውጪ ሆነው በራሳቸው ነጻ መንግሥት ይተዳደሩ በነበሩ ሀገሮች ያሉ አብያተ ክርስቲያናትስ ምን ይሁኑ? የሚለውን ጥያቄ ጉባኤው በአግባቡ ተነጋግሮበት እንደ ነበር ታሪኩን የተከታተሉ ያስረዳሉ፡፡

እንደነዚህ ያሉት አገሮች የማእከላዊው ሲኖዶስ አባልነት ሳይሰጣቸው በሮማ ቄሣር መንግሥት ግዛት ውስጥ ካሉ ከአራቱ መናብርተ ሊቀ ጵጵስና መካከል በአቅራቢያቸው ወይም በአቅጣጫቸው በሚገኝ በአንዱ ሊቀ ጳጳስ ሥር እንዲሠሩ ቢደረግ መናብርተ ሊቀ ጵጵስና ከሮማ ግዛት ሳይወጡ፣ እንደ አራቱ ወንጌላውያን፣ እንደ አርባዕቱ እንስሳ፣ ምድርን ሁሉ ያጠጡ እንደ ነበሩ እንደ አራቱ የገነት ወንዞች የመናብርተ ሊቀ ጵጵስናን ቍጥር በአራት ወስኖ በእነርሱ አባልነት በአንድ ሲኖዶስ ለምትመራ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን በቋሚነት መኖር ዋስትና የሚሰጥ ሆኖ በተገኘ ነበር- እንደ ምኞታቸው፡፡

ዳሩ ግን ከሮማ የቄሣር መንግሥት ግዛት ውጪ በራሳቸው ነጻ መንግሥት ግዛት ውስጥ የተቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናት በአባልነት ባልተገኙበት ሲኖዶስ የተወሰነውን ውሳኔ ሳይቀበሉ ቢቀሩ እንዴት ማስገደድ ይቻላል? በሮማ ቄሣር መንግሥት ግዛት ውስጥ የነበሩት ሊቃነ ጰጳሳት ሳይቀበሉ በቀሩበት ጊዜ ምንም የኋላ ኋላ ሙከራው አልሳካና ውጤቱ አላምር ቢልም ቄሣሮቹ አፈንጋጮቹን በጦር ኀይል በማስገደድ እንዲቀበሉ ለማድረግ ሞክረው ነበር፡፡

የሮማ ቄሣሮችም ከግዛታቸው ውጪ የሆኑትን የራሳቸው ሀገር አቀፍ ሉዓላዊ መንግሥት የነበራቸውን አብያተ ክርስቲያናት በሮም ግዛት የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳት ያሳለፉትን ውሳኔ መቀበል አለባችሁ በማለት ማስገደድና በጦር ኀይልም ያንድን ነጻ ሀገር ሉዓላዊነት መድፈር ስለማይቻል፣ አማራጩ ምን መሆንና መደረግ አለበት? ለሚለው ጥያቄ መልስና መፍትሔ ሆነው የተገኙት ሁለት ዘዴዎች ነበሩ፡፡

1. ከሮም የቄሣር መንግሥት ግዛት ውጪ ክርስትናን የተቀበሉና ራሳቸውን ችለው ቤተ ክርስቲያናቸውን በማስተዳደር ላይ የተገኙት መናብርት ደረጃቸው በአራቱ መናብርተ ሊቀ ጵጵስና እኩል እንዲታወቅ፤

2. በዚህ ሁኔታ የሚታወቁት መናብርተ ሊቀ ጵጵስና በአቅራቢያቸው ካለ ከአራቱ ባንዱ የበላይ ተመልካችነት ሥር እንዲውሉ፤

ይህም ውሳኔ በተሰጠበት ጊዜ በሚያስደንቅ ሁኔታ የጌታ ቃል በሙላት የተስፋፋባቸውና የተጠናከረ አመራር ሰጪ ድርጅት የነበራቸው፡-

ሀ) የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና
ለ) የፋርስ ቤተ ክርስቲያን

መሆናቸው ታውቆ ለእነዚሁ ዕውቅናው ተመዘገበላቸው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተመልካች፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሲሆን፣ ለፋርስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ተመልካች ሆኖ ተመደበ፡፡ በዚህም መሠረት በአንጾኪያና በፋርስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስለ ነበረው ግንኙነት፣ በአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት በአትናቴዎስና በፋርስ (ባግዳድ) ሊቀ ጳጳሳት በእልመፍርያን የተፈጸመውን ትውፊታዊ የስምምነት ውል ከስንክሳር የጥቀምት 9 ቀን ምንባብን መመልከት ይቻላል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም የእስክንድርያንና የኢትዮጵያን አብያተ ክርስቲያናት በሚመለከት የተደረሰበት ስምምነትና ቀኖና እንዲህ በሚል ተገልጿል፡፡

“ዝኩ ኢትዮጵያዊ ዘዝኩር በስመ ሊቃናት ይክበር በስመ ሊቀ ጵጵስና ሊቀ ጳጳሳት ተብሎ የሚጠራው (የሚታወቀው) ይህ ኢትዮጵያዊ ባለ መንበር በሊቀ ጵጵስና ማዕርግና ደረጃ (በአራቱ መናብርተ ሊቀ ጵጵስና ልክ ለማለት ነው) መክበር ይገባዋል፡፡” (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 4)፡፡ እንግዲህ ፍሬምናጦስ በሜትሮጶሊታን ደረጃ መሾሙ ከዚህ የተነሣ ነበር ማለት ይቻላል፡፡


ስድስተኛ፥ የግእዝ ፊደልን ማሻሻሉ

ከደቡብ ዐረብ ከሳባውያን የመጣ ነው የሚባለውና ፍሬምናጦስ እስከ ነበረበት ጊዜ ድረስ የተሠራበት ፊደል አናጋሪ (Vowel) ያልነበረው አሁን “ግእዝ” በሚባለው በመጀመሪያ ፊደል ብቻ እየተጻፈ ይነበብ እንደነበረ በአክሱም አካበቢ በሐውልት ላይ ተጽፈው ወይም ተቀርጸው ከተገኙት ታሪኮች መረዳት እንደሚቻለው ተመራማሪዎች ማስረጃ አቅርበዋል፡፡ ፍሬምናጦስም በኢትዮጵያ ለጀመረው የክርስትና እምነት ማስፋፋት ሥራ ይረዳው ዘንድ ቅዱሳት መጻሕፍትን ወደ ግእዝ ቋንቋ የመመለስን አስፈላጊነት ሲረዳ፣ ግእዝ ብቻ ለሆኑት ፊደሎች አናባቢ አለመኖሩ ግን ግድግዳ ሆኖ ሥራውን የሚገታበት፣ ወይም መሰናክል ሆኖ ዕቅዱ በቶሎ ግቡን እንዳይመታ የሚጐትትበት መሆኑን ዐወቀ፤ ለችግሩም ማስወገጃ መፍትሔውን ፈለገ፡፡

በመፍትሔነቱም ያመነበትን ጥናት በሥራ ላይ አዋለ፡፡ ግእዝ ብቻ ለሆኑት ፊደሎች አናባቢዎችን (Vowels) በማስገባት እያንዳንዱ ግእዝ ፊደል ከራሱ ሌላ ከካዕብ እስከ ሳብዕ ያሉ ስድስት ድምፆች እንዲኖሩት አደረገ፡፡ ለየራሱም የግእዝ ፊደል ተጨማሪ ሆነው እየተጻፉ ድምፅ መለወጥ የሚችሉ እንደ አናባቢ የሚያገለግሉ ቅጥሎችን ፈጠረ፡፡ በአብዛኞቹ ግእዝ ፊደሎች ላይ ከራስጌ፣ ከመኻል፣ ከእግርጌ የሚቀጠሉ ሲሆኑ፣ አንዳንዱን ፊደል ግን ሰባራ፣ ዐንካሳ ሆኖ እንዲጻፍ፣ አንዳንዱንም ራሱን እንዲያዘነብል አደረገ፡፡

ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፤ “ይኸውም ሊታወቅ ከጥንት ከአበው የተገኘ፥ ከውሉድም የተሰናኘ ትርጓሜ ፊደል፥ ያባ ሰላማን ትጋትና ሥራ ሲተርክ፤ ወአምጽአ ለነ ሰላማ ጳጳስ ፊደለ እምሕርክትያኑስ፤ ወሜጦሙ በአሐዱ ልሳን፥ ወእሙንቱ ሰብዐቱ ፊደላት ብሎ ይመሰክራል” ሲሉ ይተርካሉ፡፡ በተጨማሪ ሲያብራሩም በፊደል ማሻሻያ ዘዴው አናባቢንና ፊደልን ለየብቻ በመጻፍ ሌሎች የተጠቀሙበትን ዘዴ በመጠቀም ፈንታ ፊደሉንና አናባቢውን ደባልቆ በመጻፍ ማለት አናባቢ ቅጥሎች በነበሩት ፊደሎች ላይ በመጨመር የተሻሻለ የግእዝ ፊደልን ሰላማ የተባለው ፍሬምናጦስ እንዳዘጋጀልን አለቃ ኪዳነ ወልድ ያትታሉ (መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ገጽ 29)፡፡

እንግዲህ የፊደልን ጕዳይ ያነሣነው በዚህ ርእስ ስለ ፊደል ዝርዝር ታሪክ ለማቅረብ ሳይሆን፣ ዛሬ የምንጠቀምበት የግእዝ ፊደል በፍሬምናጦስ የተባረከ ትጋትና ፈጠራ ተሻሽሎና ታድሶ በሥራ ላይ የዋለ ሳባዊ ፊደል መሆኑን በማስታወስ በፍሬምናጦስ የሥራ ውጤቶች የታሪክ መዝገብ ውስጥ እንደ ገና አስፍሮ ለማለፍ ብቻ ነው፡፡

ሰባተኛ፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን መተርጐሙ

በሙሴ እጅ የተቀረጹትንና እግዚአብሔር በጣቶቹ ዐሠርቱ ቃላትን የጻፈባቸውን ጽላት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ቀዳማዊ ምኒልክ በካህናትና በሌዋውያን አሳጅቦ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቷቸው ነበረ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ክርስትና በፍሬምናጦስ እስከ ተሰበከበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ በብሉይ ኪዳን ሕግ መሠረት በአምልኮተ እግዚአብሔር ነበረች የሚባለው እውነተኛ ታሪክ ቢሆን ኖሮ፣ በዕብራይስጥ የተጻፉ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ለፍሬምናጦስ በደረሱት ነበር፡፡ በተጨማሪም ከአረማዊነት ወደ ይሁዲነት የገቡት ወይም እንዲገቡ የሚጋበዙት ኢትዮጵያውያን ይጠቀሙበት ዘንድ በሳባውያን ፊደልና ቋንቋ (ማለት ባልተሻሻለው ግእዝ ፊደል) የተጻፉ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መካከል ቢያንስ አንዳንድ ክፍሎች እንኳ ቢገኙ ኖሮ በቃል ለሚነገረው ትውፊታዊ ታሪክ ማደጋገፊያ ማስረጃዎች በሆኑ ነበር፡፡

የሕንደኬ ባለሟል የነበረው ትንቢተ ኢሳይያስ በኢትዮጵያ የነበረና በመንገድ ላይ  ሊያነበው ከኢትዮጵያ ይዞት ቢሄድ ነው፤ ወይም ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ እያመጣው የነበረ መሆኑን ይጠቍማል እንዳይባል፣ ሕንደኬ የተባለችው ንግሥት በኑቢያ ኢትዮጵያ እንጂ በሳባ ኢትዮጵያ እንዳልነገሠች የታሪክ ዐዋቂዎች አረጋግጠዋል፡፡ በሌላም በኩል ፍሬምናጦስ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በንግሥት ሕንደኬ ባለሟል የተቋቋመ ቤተ ክርስቲያን አላገኘም፤ ወይም በስብከቱ ያመኑ ናቸው ከተባሉ ቤተ ሰቦች የተወለዱ ክርስቲያኖች አላጋጠሙትም፡፡ ይልቁን በሕንደኬ ባለሟል ስብከት እንደ ተቋቋመች የምትታሰብ ቤተ ክርስቲያን ከ56 እስከ 1100 ዓ.ም. በኑቢያ ኢትዮጵያ እንደ ነበረች በታሪክ ተረጋግጧል፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ብቻ ሳይሆን በግእዝ ተጽፎ የተገኘውን ብሉይ ኪዳን አበጥረውና አንጠርጥረው የመረመሩት ሊቃውንት የግእዙ ብሉይ ኪዳን ከጽርእ፣ ያውም ከ70 ሊቃውንት ትርጉም የተመለሰ እንጂ ከዕብራይስጥ እንዳልተተረጐመ ማስረጃዎችን ከማብራሪያዎች ጋር አቅርበውታል፡፡ ከእነዚህም ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆኑት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ቍጥር ከሌላቸው አዋልድ (አዋልድ እለ አልቦን ኍልቍ) ወገን  ሌላ ምስክር ሳያሻ፣ ራሳቸው መጻሕፍቱ ከየትኛው ቋንቋ እንደ ተተረጐሙ ማስረዳት ይችላሉ ብለዋል፡፡ ለምሳሌም የሀገርና የሰው ስሞች ዕብራይስጡን መሠረት በማድረግ አልተመሰሉም፤ ጽርኡን የሳባ ሊቃናትን ትርጉም እንጂ፡፡ ጽርኡ ብሉይ ኪዳን የዘለላቸውን ግእዙ መዝለሉን፣ ጽርኡ የወረሳቸውን የዕብራይስጥ ቃላት ግእዙም መውረሱን፣ ጽርኡ ለወጥ አድርጎ የተረጐማቸውን ግእዙም የጽርኡን ለውጥ መውረሱን ጠቅሰው የግእዝ ብሉይ ኪዳን ከሰባ ሊቃናት ትርጉም ከጽርእ ለመተርጐሙ ይህ ሁሉ የማያወላዳ ማስረጃ እንደ ሆነ እኒሁ ሊቅ ከሰፊ ሐተታ ጋር አቅርበውታል፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የታሪክ ማበጠር ሂሳቸውን በማስፋፋት፣ የገድለ ቀውስጦስን ጸሓፊዎችና የመጽሐፈ ምስጢር ደራሲ የሆኑትን አባ ጊዮርጊስን መነቀፍ ከሚገባቸው ድርሰቶቻቸው መካከል ምሳሌ አድርገው ሲጠቅሱ፣

1. የብሉይ ከዳን መጻሕፍት በቀጥታ ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ እንደ ተተረጐሙ ለመረዳት የሚፈልግ ሰው በግእዝ የተጻፈውን መጽሐፈ ነገሥትን ቢመለከት፣ አዶናይ፣ ኤሎሄ’፣ ጸባዖት፣ ሲል ያገኘዋል ሲሉ አባ ጊዮርጊስ ባቀረቡት ሐተታ ላይ አለቃ ኪዳነ ወልድ ሂስ አቅርበዋል፡፡ ሲያብራሩም አባ ጊዮርጊስ እንዳሉት ብሉይ ኪዳን ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ የተተረጐመ ከሆነ፣ ጽርኣዊ የቦታና የሰው ስሞችን በግእዝ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ማን አስገባቸው? ዕብራይስጡ ከጽርእ የወረሳቸውና የውርስ ውርስ ወደ ግእዝ ተላለፉ እንዳይሉ ብሉይ ኪዳን መጀመሪያ በዕብራይስጥ ተጽፎ ከኖረ በኋላ፣ ቈይቶ ወደ ጽርእ መተርጐሙ ሊዘነጋ እንደማይገባ አመልክተዋል፡፡ በማያያዝም እነዚህ የዕብራይስጥ ቃላት ወደ ግእዝ ብሉይ ኪዳን ለመግባት ዕድል ያጋጠማቸው የግእዙ ብሉይ ኪዳን መሠረታዊ መዝገብ የሆነው ጽርኡ የሰባ ሊቃውንት ትርጉም ከዕብራይስጥ በተተረጐመበት ጊዜ ስለ ወረሳቸውና እነ ፍሬምናጦስም ከጽርእ ወደ ግእዝ ሲተረጉሙ የዕብራይስጡን ቃል የውርስ ውርስ በመውሰዳቸው እንደ ሆነ አለቃ አስረድተው እውነትን የሚገነባ፣ ሐሰትን ግን ከመሠረቱ የሚያፈራርስ አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡
2. ገድለ ቀውስጦስም ኦሪትና ነቢያት በሰሎሞን ጊዜ ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ እንደ ተመለሱ የተረከውን አለቃ ኪዳነ ወልድ አውስተዋል፡፡ እስራኤላውያን ወደ ባቢሎን በተማረኩ ጊዜ የራሳቸው መጻሕፍት እንደ ጠፋባቸው ይኸው ገድል መግለጹንና በኋላም እስራኤላውያን ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ዘሩባቤል የተባለው መሪያቸው፣ አይዙር የተባለውን ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ለምኖ ከግእዝ ወደ ዕብራይስጥ እንዳስተረጐማቸው መናገሩን አለቃ ኪዳነ ወልድ ጠቅሰው እጅና እግር የሌለውን የገድለ ቀውስጦስን ትረካ በምሬት ነቅፈዉታል፡፡

ወደ እውነተኛው ታሪክም ተመልሰው ፍሬምናጦስና ረዳቶቹ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት፣ የውጪ ሀገር ሰዎችም ተጨምረው ቅዱሳት መጻሕፍትን ከጽርእ ወደ ግእዝ በተሻሻለው ፊደል መተርጐማቸውን አለቃ ተርከው ከስንክሳር የሐምሌ 26ን ምንባብ ዋቢ አድርገዋል፡፡ (መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ገጽ 16-20) የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ግን በካልእ ሰላማ እንደ ገና ከዐረብ ወደ ግእዝ መተርጐማቸውን አለቃ አስረድተዋል፡፡
ለመሆኑ በሰሎሞን ጊዜ ኦሪትስ ይሁን መጻሕፍተ ነቢያት ከየት መጡ? በሰሎሞን ጊዜ ሊኖሩ የሚችሉት ዐምስቱ ብሔረ ኦሪት፣ መጽሐፈ ኢያሱና መጽሐፈ መሳፍንት፣ ምናልባት የተጀመረ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ፣ የተጀመረ መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ፣ መጽሐፈ ሩት፣ ምናልባት መጽሐፈ ኢዮብ፣ የተጀመረ መጽሐፈ መዝሙራት ይሆናሉ፡፡ ከእነዚህ በቀር ሌሎቹ የታሪክ፣ የቅኔ፣ የትንቢተ ነቢያት መጻሕፍት ገና በአምላክ ልብ በፅንስ ደረጃ ነበሩ ከማለት በቀር በዕብራይስጥ እንኳ ባልተጻፉበት ጊዜ ነበሩ ማለት ልብ ወለድ ድርሰት ካልሆነ በቀር ተአማኒነት የሌለው የፈጠራ ወሬ ነው፡፡

ግእዝስ በሰሎሞን ጊዜ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ እስከ መሆን ዳብሮ ነበርን? አናባቢ ሆነው እንዲያገለግሉ ቅጥሎች በተጨመሩለት የግእዝ ፊደል የተጻፈውን የግእዝ ብሉይ ኪዳን በሰሎሞን ጊዜ የተጻፈ ነው ብሎ ሐሰትን ማስተማር በአባ ጊዮርጊስ ድርሰት ላይ ጥቍር ነጥብ የጣለ የታሪክ ሥራ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ደገኛ ሐዋርያ ሆኖ በመጣለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ፍሬምናጦስ የተከናወኑ የሥራ ፍሬ ዘለላዎች ገና እየተንዠረገጉ የሚያድጉ ናቸው፡፡ ሊያጠፏቸው፣ ሊያደርቋቸው፣ ሊዠመግጓቸው የሚያደቡ ተኵላዎችን ዐብረን እንከላከል፡፡ (አሥግሩ ለነ ቄናጽለ ንኡሳነ እለ ያማሰኑ ዐጸደ ወይንነ ማሕ. 2፥16) ፍሬምናጦስ እግዚአብሔር ሥራውን ሁሉ የባረከለት ሐዋርያ ነበር፡፡



በጮራ ቍጥር 7 ላይ የቀረበ

1 comment:

  1. ከየትኛው ክፍል የቀጠለ እንደሆነ ብትነግሩኝ ምክንያቱም ይሄኛው 3ኛ ብሎ ነው የሚጀምረው።

    ReplyDelete