Tuesday, December 3, 2013

መሠረተ እምነት

ኢየሱስ ክርስቶስ ዐዲስ ኪዳን መካከለኛ
በጮራ ቊጥር 40 ላይ፡-
·        ኢየሱስ አሁን ጠበቃ ነው ወይስ ዳኛ?
·        1ዮሐ. 2፥1-2 ስለ ማን ይናገራል?
·        የኢየሱስ ጠበቃነት በምድራዊ ጥብቅና ይመዘናልን?
·        ኢየሱስ በአብ ቀኝ መቀመጡ መካከለኛነቱን አስቀርቶታልን?
·        ቅዱሳን መካከለኞች አይደሉምን?  
በሚሉ ዐምስት ንኡሳን አርእስት ሥር የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል ማስረጃዎችን በማቅረብ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በዚህ ዕትም ደግሞ የዕብራውያንን መልእክት መሠረት በማድረግ የክርስቶስን መካከለኛነት እንመለከታለን። በቅድሚያ ግን ለዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ለሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላና ምሳሌ ስለ ሆኑት የብሉይ ኪዳን መካከለኞች ስለ ነበሩት ሊቃነ ካህናት መሠረታውያን ነገሮችን እንዳስሳለን። ከዚህ በፊት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 23 በስፋት መጻፉን ለአንባብያን መጠቈም እንወዳለን።

የካህናት ሹመትና አገልግሎት በብሉይ ኪዳን
የዕብራውያን መልእክት “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤” (ዕብ. 5፥1) በማለት፥ ስለ ሊቀ ካህናት ማንነት፣ ሊያሟላ ስለሚገባው መስፈርትና ስለሚሰጠው አገልግሎት የሚናገር ቃል እናነባለን። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ሊቀ ካህናት ሆኖ የሚሾመው፡-
·        ከሰው ተመርጦ መሆኑን፣
·        ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ መሆኑን እና
·        ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ላይ ስለ ሰው የሚሾም መሆኑን
እንገነዘባለን። ጥቅሱ ስለ ብሉይ ኪዳን ካህናት ማንነት፣ ስለሚሾሙበት ምክንያትና ስለሚወክሉት ወገን ይናገራል ማለት ነው። “ከሰው ተመርጦ” የሚለው፥ ሊቀ ካህናት የሚሆነው የመላእክት ወገን ሳይሆን የሰው ወገን መሆኑን ሲያስረዳ፥ መራጩም አካል ሌላ [እግዚአብሔር] እንጂ ካህኑ ራሱን በራሱ ሊመርጥ ወይም ሊሾም እንደማይችል ያመለክታል። “እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም” (ቊጥር 4)።


ሊቀ ካህናት የሚሾምበት ምክንያት ደግሞ አንድ ነው፤ “ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ”። ይህም ስለ ኀጢአተኛው ሰው የሚቀርብ የኀጢአት ማስተስረያ ነው።

ሊቀ ካህናት የሚሾመው “ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ላይ ስለ ሰው” ነው የሚለውም ሌላው ሊታወቅ የሚገባው ነጥብ ነው። ሊቀ ካህናቱ የእግዚአብሔር የብቻው ገንዘብ በሆነው ኀጢአትን የማስተስረይ ተግባር ላይ የሰው ወኪል ሆኖ የሰውን ጉዳይ ለእግዚአብሔር አቅራቢ መሆኑን ይጠቊማል።

በነዚህ መስፈርቶች መሠረት የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት፥ ከሰዎች መካከል በእግዚአብሔር ተመርጦ ስለ ሰዎች የኀጢአትን መሥዋዕትና መባን ለማቅረብ ቢሾምም፥ ማንነቱ፣ ክህነቱ፣ መሥዋዕቱና መቅደሱ ፍጹማን አልነበሩም፤ ብዙ ጕድለቶች ነበሩባቸው።

·        ማንነቱ
ከላይ እንደ ተገለጸው በብሉይ ኪዳን ለሊቀ ካህናትነት የሚያበቃው አንደኛው መስፈርት ሰው መሆን ነው ቢባልም፥ ይህ መስፈርት በራሱ ከሰዎች መካከል ተመርጦ ለሚሾመው የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ፍጹምነትን ያጐናጽፈዋል ማለት አይደለም። እንዲያውም “ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና” (ዕብ. 7፥28) በማለት ሊቀ ካህናት ሆነው ይሾሙ የነበሩት የአሮን ወገኖች ኀጢአተኞች መሆናቸውን ያስረዳል። የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኀጢአተኛ መሆኑ፥ የሌላውን ኀጢአተኛ ሰው ድካም እንዲረዳና ለኀጢአተኛው ሰው በመራራት የመካከለኛነቱን ተግባር በተገቢው መንገድ እንዲያከናውን ያደርገዋል (ዕብ. 5፥2)።

የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ዕሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻ) በመሆኑ እንደ ማንኛውም ሰው ብዙ ጕድለቶች ነበሩበት። ሰው ሁሉ ኀጢአተኛ ነው፤ ከሰዎች መካከል የተመረጠው ሊቀ ካህናትም ኀጢአተኛ ነውና፥ ስለ ሕዝቡ ኀጢአት መሥዋዕትን ከማቅረቡ በፊት ስለ ራሱ ኀጢአት መሥዋዕትን ማቅረብ ይጠበቅበት ነበር (ዘሌ. 9፥7-8፤ 16፥6፡11፤ ዕብ. 5፥2-3፤ 7፥27፤ 9፥7)።
 
·        ክህነቱ
የብሉይ ኪዳን ክህነት ከሌዊ ነገድ ለሆነው ለአሮን ቤት የተሰጠ በመሆኑ ከሌላ ነገድ የሆነ ሰው ሊያገኘው የማይችለው ሹመት ነበር። በዘር ላይ መመሥረቱ ግን ከላይ እንደ ተመለከትነው፥ ድካም ላለበት ለካህኑ የተለየ ማንነትን አያጐናጽፈውም።

ካህን የሚሆነው ሰው ብቻ ሳይሆን ክህነቱ ራሱ ፍጹም እንዳልነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። የክህነቱን ጕድለቶች ከሚያሳዩት ነጥቦች መካከል አንዱ፥ ክህነቱ ያለ መሐላ እንዲሁ የተሰጠ ክህነት መሆኑ ነው (ዘፀ. 28፥1፤ ዕብ. 7፥20)፤ ይህም፥ ክህነቱ ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ ላለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።

ሌላው የብሉይ ኪዳን ክህነት ጕድለት በእድሜ የተገደበ መሆኑ ነው። ካህኑ በእድሜ የተገደበ እንደ መሆኑ፥ ከ25 ዓመት ጀምሮ እስከ 50 ዓመት ድረስ ያገለግልና 50 ዓመት ሲሞላው አገልግሎቱን ይተው ነበር (ዘኍ. 4፥24-26፤ 8፥24-26)፤ ክህነቱ የዕድሜ ገደብ የተጣለበት ስለ ነበረ ከ25 ዓመት በታች የሆነው ካህን ለአገልግሎት የማይበቃ፥ ከ50 ዓመት በላይ የሆነው ካህን ደግሞ ከአገልግሎት በጡረታ የሚገለል ነበረ ማለት ነው። የዕብራውያኑ ጸሓፊ ደግሞ የብሉይ ኪዳን ካህናት ክህነታቸው በሞት የተገደበ መሆኑን ጽፏል፤ የዚህም ውጤት አንዱ ካህን ሌላውን እየተካ የካህናቱን ቊጥር ብዙ አድርጎታል (ዕብ. 7፥23)።

እነዚህና ሌሎቹም ጕድለቶቹ ተደምረው በዚህ ክህነት ፍጹም አገልግሎትና ድኅነት አልተገኘም (ዕብ. 7፥11)፤ ምክንያቱም ካህናቱ ያገለገሉት ለሰማያዊው ነገር ጥላና ምሳሌ የሆነውን አገልግሎት ነውና (ዕብ. 8፥5)።
   
·        መሥዋዕቱ
ስለ ኀጢአት መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ የሚሾመው ሊቀ ካህናት የሚያቀርበው መባና መሥዋዕት የግድ ያስፈልገዋል (ዕብ. 5፥1፤ 8፥3)። የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ለኀጢአተኛው ሰው ያቀርብ የነበረው መባና መሥዋዕት ኀጢአትን ከቶ ሊያስወግዱና ኀጢአተኛውን ሰው ፍጹም ሊያደርጉት የማይችሉ ነበሩ፤ እንዲህ ማድረግ ቢችሉ ኖሮ ግን ሊቀ ካህናቱ አንድ ጊዜ ብቻ ማቅረብ በበቃው፥ የኀጢአተኛው ሰው ኅሊናም በነጻ ነበር፤ ነገር ግን እንዲህ ማድረግ አልተቻላቸውም (ዕብ. 10፥1-4)።

ስለ ኀጢአት ይቀርቡ የነበሩት መባና መሥዋዕት ብዙና ልዩ ልዩ ዐይነት መሆናቸው፣ በተደጋጋሚ መቅረባቸውና ለሚመጣው አማናዊ መሥዋዕት ጥላና ምሳሌ ሆነው መሰጠታቸው መሥዋዕቶቹ ፍጹማን እንዳልነበሩ ያመለክታሉ (ዕብ. 10፥1-11)።

·        ቤተ መቅደሱ
የብሉይ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት አገልግሎቱን ይፈጽም የነበረው በቤተ መቅደስ ነው። ይህች ቤተ መቅደስ ምድራዊት፣ በሰው እጅ የተሠራችና ለእውነተኛዪቱና ለሰማያዊቱ መቅደስ ምሳሌ ነበረች (ዕብ. 9፥1፡6-7፡24)። ሊቀ ካህናቱ በዚህች ምድራዊት መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው የመጀመሪያ ክፍል ለማገልገል ዘወትር ይገባ የነበረ ሲሆን፥ ወደ ውስጠኛዋ ክፍል የሚገባው ግን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር (9፥6-7)።

የክርስቶስ መካከለኛነት በዕብራውያን መልእክት
የዕብራውያን መልእክት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት በስፋትና በጥልቀት ይናገራል። መልእክቱ በዋናነት ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ከመላእክት፣ ከሙሴ፣ ከአሮንና በአጠቃላይም ከብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት የሚበልጥ ብቸኛው መካከለኛና ሊቀ ካህናት መሆኑን ይመሰክራል። ብልጫውም ከማንነቱ የሚመነጭ ነው። እርሱ ፍጹም ሰው ሆኖ ቢገለጥም ፍጹም አምላክ ነው። በዚህ ማንነቱ አምላክንም ሰውንም መወከሉ ደግሞ ታላቁና ብቸኛው የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ አድርጎታል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የሆነው ስለ ሊቀ ካህናት አመራረጥ በወጣው መስፈርት መሠረት መሆኑን የዕብራውያኑ ጸሓፊ በንጽጽር ያስረዳል።
·        ፍጹም አምላክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውም ነው፤ ስለዚህ ሊቀ ካህናት “ከሰው ተመርጦ” ይሾማል የሚለውን መስፈርት እርሱ አሟልቷል ማለት ነው።
·        ሊቀ ካህናት የሆነውም ራሱን በራሱ ሾሞ አይደለም፤ ነገር ግን “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው” አባቱ እንደ ሆነና “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ” የሚል ቃል አስቀድሞ እንደ ተነገረለት በመጥቀስ፥ የሾመው እግዚአብሔር መሆኑን ያስረዳልና (ዕብ. 5፥5-6)፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሐላ ጋር (ዕብ. 7፥20-21) በእግዚአብሔር የተሾመ ሊቀ ካህናት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
·        ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት የሆነበት ዋና ምክንያትም፥ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ የሕዝብን ኀጢአት ለማስተስረይ ነው (2፥17)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ለተገነዘበ ክርስቲያን ይህን መረዳት አስቸጋሪ አይሆንም። የሚያስቸግረው ወገን ቢኖር፥ ለመናገር ያህል ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ፥ ፍጹም ሰው ነው ብሎ የሚናገር፥ በተግባር ግን የአምላክነቱን ክብር ይቀንሳል በሚል ሥጋት የሰውነቱን ግብር የሚክድ ውስጠ አውጣኬያዊ[1] ብቻ ነው።

በዚሁ የዕብራውያን መልእክት ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑ በስፋት ተጽፏል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት የሚበልጥ የእግዚአብሔር ልጅና ታላቅ ሊቀ ካህናት መሆኑ በተነገረበት ክፍል፥ “ስለ ልጁ ግን፡- አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ” (ዕብ. 1፥8-9) በሚለው ቃል ውስጥ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክም ሰውም መሆኑን በሚገልጹ ቃላት ማንነቱ ተብራርቷል። “አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤” በሚለው ዐረፍተ ነገር ውስጥ “አምላክ ሆይ” በሚል ባለቤት የቀረበው የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ይግልጻል፤ “እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ” በሚለው ዐረፍተ ነገር ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ “አምላክ” ተብሎ መጠራቱና ተቀባ መባሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን ያስረዳል፤ ምክንያቱም ቃል ለተወሐደው ሥጋ እግዚአብሔር አምላኩ ነው። እግዚአብሔር አብ ለአንዱ ለኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ አባቱ በሰውነቱ ደግሞ አምላኩ ነው ማለት ነው።

ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር አብን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ሲሉ የሚጠሩትም በዚሁ መሠረት መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል (1ቆሮ. 1፥3፤ ኤፌ. 1፥3፡17፤ 1ጴጥ. 1፥3)። ይህ አገላለጽ የማይስማማቸው ወገኖች ግን “የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” ብቻ በማለት እግዚአብሔር አብ ለኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ አባቱ መሆኑን ብቻ ተቀብለው፥ በሰውነቱ አምላኩ መሆኑን ያስተባብላሉ፤ ባያስተውሉት ነው እንጂ ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆኑን መካድ ነው። ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አብን አባቴና አምላኬ ብሎ መጥራቱን ሊፍቁት አይችሉም፤ ግእዙም “… አዐርግ ኀበ አቡየ ወአቡክሙ ኀበ አምላኪየ ወአምላክክሙ፤ -   ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ …” ይልባቸዋልና (ዮሐ. 20፥17)።   

ከጥንት አበው አንዱ የሆነው ዮሐንስ አፈ ወርቅ የኤፌሶንን መልእክት በተረጐመበት ድርሳኑ የኤፌሶን መልእክት ምዕራፍ 1 ቊጥር 17ን ማለትም “የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ” የሚለውን ቃል ሲተረጕም፥ አብን አምላኩ ለክርስቶስ (የክርስቶስ አምላክ) ያለው በሰውነቱ ነው፤ ወይም ወልድ ፍጹም ሰው መሆኑን ሲያስረዳ ነው እንጂ  ወልድ በአምላክነቱ ከአብ ያንሳል ማለቱ አይደለም ሲል አብራርቷል። አክሎም፥ ጌታ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት “ለደቀ መዛሙርቱ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ …” ያለው፥ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ብቻ እንዳይመስላቸውና ሰው የሆነ ፍጹም አምላክ መሆኑን እንዲገነዘቡ ስለ ሆነ፥ አስቀድሞ “አባቴ” ቀጥሎ ደግሞ “አምላኬ” አለ በማለት ማንነቱን ገልጿል (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 68፣ ክፍል 19፣ ቊጥር 10-14)።

ይሁን እንጂ በዚሁ የሃይማኖተ አበው ክፍል የግእዙ ንባብ “ወእዜከረክሙ በጸሎትየ ከመ አምላኩ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ አበ ስብሐት የሀብክሙ መንፈሰ ጥበብ።” ያለውንና ዐማርኛው “የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ የጥበብን መንፈስ እንዲሰጣችሁ በጸሎቴ አስባችኋለሁ” ሊል የሚገባውን፥ ያለንባቡና ያለምስጢሩ “የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” (ቊጥር 10) ብለው ተርጕመዉታል። ይህም ሰው መሆኑን ማስተባበል ካልሆነ በቀር ለአምላክነቱ ጥብቅና መቆም ሊሆን በፍጹም አይችልም።  

እነዚህ ወገኖች ክርስቶስ ሰው መሆኑን በተግባር መካዳቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ነው የሚለውን እውነት በንግግር ብቻ እንዲጠቅሱትና  አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕትና ምልጃ ዛሬም የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ የሆነበትን ግብሩን እንዲክዱት አድርጓቸዋል ማለት ይቻላል። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ነው ስንል፥ ሰው መሆኑንና መካከለኛችን የሆነውም በሰውነቱ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። የእርሱ ክህነት ያስፈለገበትንና ከቀደሙት ካህናት የበለጠበትን ምክንያት የዕብራውያን መልእክት በሚያስተምረን መሠረት አንዳንድ ነጥቦችን ቀጥሎ እንመለከታለን።

የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት
የዕብራውያን መልእክት የሚጀምረው እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ሲናገር እንደ ነበረና በዚህ ዘመን መጨረሻ ግን የተናገረው በልጁ በኩል እንደ ሆነ በማስረዳት ነው (ዕብ. 1፥2)። እግዚአብሔር በዚህ ዘመን የተናገረው በአንድ መንገድ በልጁ በኩል መሆኑ መካከለኛው እርሱ ብቻ መሆኑን ያመለክታል። የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት ሲገልጽም እርሱ የእግዚአብሔር የክብሩ ነጸብራቅና የባሕርዩ ምሳሌም ነው ይላል። ይህም የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያመለክት አገላለጽ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ትክክለኛ ወካይና ገላጭ መሆኑን ያስረዳል።
ሌሎች የሐዲስ ኪዳን ክፍሎችም ይህን ያረጋግጣሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ፥ “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” (ዮሐ. 1፥18) በማለት መስክሯል። አይሁድ ስለ ማንነቱ በትክክል እንዲነግራቸው ጌታን በጠየቁት ጊዜ፥ “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐ. 10፥30) ሲል መልሷል። ፊልጶስ ላቀረበለት “አብን አሳየንና ይበቃናል” ለሚለው ጥያቄ ጌታ ሲመልስ፥ “ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፡- አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ” (ዮሐ. 14፥8-9) በማለት አምላክነቱን ገልጧል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ በነገር ሁሉ የተፈተነ ሊቀ ካህናት ቢሆንም፥ ኀጢአትን ግን ፈጽሞ ያልሠራ ንጹሕ መካከለኛ ነው፤ በነገር ሁሉ የተፈተነ መሆኑ፥ መካከለኛ ለሚሆንላቸው ሰዎች በድካማቸው እንዲራራላቸው ያደርገዋል (ዕብ. 4፥15)። የዕብራውያኑ ጸሓፊ ስለ እርሱ ሲመሰክር፥ “ቅዱስና ያለ ተንኰል፥ ነውርም የሌለበት፥ ከኀጢአተኞች የተለየ” (ዕብ. 7፥26) ነው ይላል። እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ድካም ስለሌለበትና ንጹሕ ስለ ሆነ፥ ስለ ራሱ መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም (ዕብ. 7፥27)።
በክህነቱ ይበልጣል
ካህን ወይም አገልጋይ የሌለበት ሃይማኖት አለ ማለት አይቻልም። በተለያዩ ሃይማኖቶች ተጠልሎ የሚገኝ ሰው ሁሉ መካከለኛ የሚሆነውን ካህን የሚፈልገው፥ ኀጢአተኛ ስለ ሆነና ወደ አምላኩ ለመቅረብ በራሱ ድፍረት ስለሌለው ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ እንደ ተናገሩት፥ መካከለኛ ፈላጊ የሆነው ሁሉም ሰው፥ በየሚገኝበት ሃይማኖት ውስጥ ሳያውቀው እየፈለገው ያለው ታላቁን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው ማለት ነው። የእርሱን ብልጫ የተረዳው የዕብራውያኑ ጸሓፊ፥ “እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል” ብሏል (ዕብ. 7፥26)።

የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት እንደ ሌዊ ክህነት ከዚያ ነገድ በመወለድ የተገኘ አይደለም፤ እርሱ ጌታችን የተወለደው ከይሁዳ ነገድ ነው፤ ይህ ነገድ ደግሞ ለክህነት አልተመረጠም (ዕብ. 7፥14)። በሌዊ ክህነት ፍጹምነት ስላልተገኘ ከእርሱ የበለጠ ሊቀ ካህናት አስፈልጓል። ለዚህም ነው ጸሓፊው፥ “በዚያ [በሌዊ] ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ወደ ፊት ስለ ምን ያስፈልጋል?” (ቊጥር 11) በማለት የሚጠይቀው። የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት ከሌዊ ክህነት የተለየና የተሻለ፥ የመልከ ጼዴቅን ክህነትም የመሰለ መሆኑን እንረዳለን።

የመልከ ጼዴቅ ክህነት ለኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት መገለጫ ከሆነባቸው ነጥቦች መካከል ዋናው፥ የክህነቱ ጥንትና ፍጻሜ አለመታወቁ፥ ወይም ክህነቱ ዘላለማዊ መሆኑ ነው። ይህም ለእግዚአብሔር ልጅ ክህነት ምሳሌ እንዲሆን ነው (ዕብ. 7፥3፡16)። በርግጥም የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት እንደ ሌዊ ክህነት በእድሜ የተገደበና በሞት የሚሻር ሳይሆን፥ ተተኪ የማያስፈልገውና ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር ክህነት ነው። “አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት ለዘላለም ካህን ነህ” (5፥6፤ 7፥17፡20) የተባለውም ለዚህ ነው። እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት ዘላለማዊ መሆኑን በመሐላ አረጋግጧልና (ዕብ. 7፥21-22)፥ ክህነቱ እንደ ሌዊ ክህነት አንድ ቀን ያልፋል፤ ወይም ይቀራል የሚል ሥጋት ከቶ የለበትም። እርሱ እንደ ብሉይ ኪዳን ካህናትም ስለማይሞትና ለዘላለም ስለሚኖር ክህነቱ አይሻርም፤ ወይም አይለወጥም (7፥23-25)። ታዲያ በዘላለማዊነትና በማይሻር ክህነት ከመሐላ ጋር መካከለኛ የሆነውን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ማን ሊተካው ይችላል?  

በመሥዋዕቱ ይበልጣል
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሊቀ ካህናትነቱ ያቀረበው መሥዋዕት የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ካቀረቧቸው መሥዋዕቶች፥ በዐይነት፣ በብዛትና በብቃት እጅግ የተለየና የሚበልጥ ነው። እነርሱ ያቀርቡ የነበረው ለኀጢአተኛው ሰው በዕሴት ሊመጥን የማይችል የእንስሳ መሥዋዕትን ነበር (ማር. 8፥37፤ ዕብ. 10፥4)። መሥዋዕቱም ሥጋን እንጂ ኅሊናን ከኀጢአት ፈጽሞ ሊያነጻ አልቻለም ነበር (ዕብ. 9፥9-10፡13፤ 10፥1-4)። መሥዋዕቶቹ በየዕለቱና በየዓመቱ እየተደጋገሙ ይቀርቡ ነበር፤ ይህም መሥዋዕቶቹ ፍጹምነት ይጐድላቸው እንደ ነበረና ኀጢአትን ፈጽሞ ማንጻት እንደማይችሉ ያመለክታል፤ ፍጹማን ቢሆኑ ኖሮ ግን አንድ ጊዜ ማቅረቡ በበቃቸው ነበር (9፥27፤ 10፥1-3፡11)። እግዚአብሔርም በዚያ መሥዋዕት ደስ እንዳልተሰኘና በክርስቶስ የተወደደ መሥዋዕት ግን እንደረካ ቃሉ ይመስክራል (10፥5-10፤ ኤፌ. 5፥2)

ኢየሱስ ክርስቶስ በሊቀ ካህናትነቱ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው ራሱን ነው። ሊቀ ካህናቱ እርሱ፥ መሥዋዕቱም እርሱ ሆነ ማለት ነው። እርሱ ስለ ሰዎች የሞተው ሰው ሆኖ ነውና፥ መሥዋዕትነቱ የሰዎችን የኀጢአት ዕዳ ለማወራረድ በዕሴት ተመጣጣኝ ሆኗል። የእርሱ መሥዋዕት የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች መፈጸም ያልቻሉትን ኀጢአትን ማስወገድና መሻር ችሏል (ዕብ. 9፥26፤ ዮሐ. 1፥29፤ 1ዮሐ. 3፥5)። በመሆኑም በእርሱ መሥዋዕት ዘላለማዊ ስርየትና ፍጹምነት ስለ ተገኘ፥ በመሥዋዕቱ የተሸፈኑትን ሰዎች “ኀጢአታቸውንና በደላቸውን ደግሜ አላስብም” ብሏል (ዕብ. 10፥14-17)።

እርሱ ነውር የሌለበት ፍጹም መሥዋዕት በመሆኑ፥ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ያስፈለገው አንድ ጊዜ ብቻ ነው (ዕብ. 7፥27፤ 9፥26-28፤ 10፥12-18)። አንድ ጊዜ ያቀረበው መሥዋዕትም ለኀጢአት ሁሉ ማስተስረያነት የሚበቃና ለሁል ጊዜ የሚያገለግል መሥዋዕት በመሆኑ ሌላ መሥዋዕት አላስፈለገም (10፥18፡27፤ 1ዮሐ. 2፥2)። ስለዚህ ኀጢአተኞች ሁሉ ንስሓ እየገቡና በክርስቶስ አዳኝነት እያመኑ፥ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት ስርየተ ኀጢአትን ይቀበላሉ። በዚሁ መሥዋዕት ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ኅብረትም እያደሱ ይኖራሉ።       

ቤተ መቅደሱ ሰማያዊ ነው
የዐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የመካከለኛነት አገልግሎቱ፥ የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ባገለገሉባት ምድራዊት መቅደስ ውስጥ የተከናወነ አይደለም። እርሷ በሰማይ ባለችው ቤተ መቅደስ ምሳሌ በሰው እጅ የተሠራች የዚህ ዓለም መቅደስ እንደ መሆኗ ክብሯ ዝቅተኛ ነው (ዕብ. 8፥5፤ 9፥1፡24)። ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ የገባባት መቅደስ ከምድራዊቷ መቅደስ የምትበልጥና የምትሻል፥ በሰው እጅ ያልተሠራችና በእግዚአብሔር የተተከለች ናት፤ እርሱም የዚህች መቅደስ አገልጋይ ነው (ዕብ. 8፥2፤ 9፥11፡24)። ወደዚህች መቅደስ በገዛ ደሙ ከሁሉ ቀዳሚ ሆኖ የገባው የዘላለምን ቤዛነት አስገኝቶ ነው። ፍጹም የሆነውንና ኀጢአትን ማስወገድ የቻለውን መሥዋዕት ስላቀረበም ሥራው ተጠናቋልና፥ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት ቆሞ አላገለገለም፤ ከገባ በኋላም ተመልሶ አልወጣም፤ በዚያው ተቀመጠ እንጂ (ዕብ. 1፥3፤ 6፥19-20፤ 8፥1፤ 10፥11-13፤ 12፥2)።  

ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊቱ መቅደስ አሁን ምን ይሠራል?
ሊቀ ካህናታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለችው “የመቅደስና የእውነተኛዪቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤” (ዕብ. 8፥2)። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት፥ ኢየሱስ ወደ ሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ለምን ገባ? በዚያ የሚያገለግለው አገልግሎት እንደ ምን ያለ ነው? የሚያገለግለውስ ስለ ማን ነው? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እንድንጠይቅ ያደርገናል። ምላሾቹን ከዚሁ ከዕብራውያን መልእክት እንመረምራለን።
እግዚአብሔር፥  ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ የዐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት አድርጎ በመሐላ ሾሞታል (7፥28)። እርሱም ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃ ሕያውና ዘላለማዊ መሥዋዕት አድርጎ ራሱን ከሠዋ በኋላ፥ በገዛ ደሙ ወደ ሰማያዊቱ መቅደስ ገብቶ በዚያ አለ። በዚያ የሚገኝበትን ምክንያት ሐዋርያው ሲያብራራ፥ “በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ” ነው ይላል (ዕብ. 9፥24፡28)። ኢየሱስ በእርሱ በኩል ለሚመጣው ኀጢአተኛ ሰው መሞቱንና ዕዳውን የከፈለለት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሆኖ ይታይለታል ማለት ነው። አንድ ጊዜ ያቀረበው ምልጃና መሥዋዕት ለዘላለም የሚያገለግል በመሆኑ፥ በእርሱ በኩል አምነው የሚመጡትን በዚያው ምልጃ ያስታርቃቸዋል፤ በዚያው መሥዋዕት ስርየተ ኀጢአትን ይሰጣቸዋል። “እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው” (ዕብ. 5፥7-10)። ልብ እንበል! ኢየሱስ ሊቀ ካህናት ሆኖ በዚያ ያለው ለሚታዘዙለት ማለትም፥ ቃሉ በሚለው መሠረት የሰዎችን የኀጢአት ዕዳ የከፈለው አዳኝ እርሱ ብቻ መሆኑን አምነውና በኀጢአታቸው ተናዘው በእርሱ ቤዛነት በኩል ለሚመጡት የመዳናቸው ምክንያት (ምክንያተ ድኂን)ሆኖ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ተሠውቷል፤ ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃ ፍጹም መሥዋዕትንም አቅርቧል፤ አንድ በሽተኛ በሽታውን ዐውቆ መድኀኒቱን እስካልወሰደ ድረስ በሽታውን ስላወቀና መድኀኒቱም በየመድኀኒት ቤቱ ስለሚገኝ ብቻ ይድናል ማለት እንዳልሆነ ሁሉ፥ ጌታ ይህን የማዳን ሥራ ስለ ሠራ ዓለም ሁሉ ይድናል ማለት አይደለም። ቅዱስ ቃሉ እንደሚለው፥ መዳን የሚፈልግ ሁሉ በሰማያት ያለፈው ሊቀ ካህናት ታላቁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊኖረው የግድ ነው። “ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም” (1ዮሐ. 5፥12) ተብሎ ተጽፏልና። እርሱም ከኀጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ ሰው የተፈተነ ስለ ሆነ፥ የሰውን ድካም ተገንዝቦ የሚራራ ሊቀ ካህናት ነውና፥ ምሕረትን ለመቀበልና በሚያስፈልገው ጊዜ የሚረዳውን ጸጋ ለማግኘት ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት መቅረብ አለበት (ዕብ. 4፥14-16)።
ኢየሱስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ መሆኑ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ተደጋግሞ ተጠቅሷል (8፥6፤ 9፥15፤ 12፥24)። መካከለኛ የሆነውም “የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ” ነው (9፥15)። ታዲያ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ማስተባበልና መካከለኞቹ መላእክት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ናቸው ማለት ለምን አስፈለገ? እንዲህ የሚያምኑና የሚያስተምሩ ሰዎች፥ በተደጋጋሚ እርሱን ዛሬ መካከለኛ ማድረግ ከአምላክነቱ ክብር ዝቅ ማድረግ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፤ ነገር ግን ይህ ለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ከመቅናት የተነሣ የሚነገር መስሎ ቢታይም፥ ዋናው ምክንያታቸው ግን እነርሱ በፈቃዳቸው የሰየሟቸውን “መካከለኞች” የት እናድርጋቸው በሚል በሥርዋጽ ማስገባትና እርሱን ከመካከለኛቱ ስፍራ ማንሣት ነው።
ሊቀ ካህናት ሆኖ የሚሾመው ሰው መሆን እንዳለበት በስፋት ተመልክተናል። ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅም፥ “ወኢያንሥአ ለነ ሊቀ ካህናት እመላአክት ወኢእምኀይላት እለ እሙንቱ ይቀውሙ ዐውደ መንበሩ - … ዙፋኑን ከበው ከሚቆሙ ከመላእክት ከኀይላትም ወገን ሊቀ ካህናት አልሾመልንም” (ሃይማኖተ አበው ገጽ 222) በማለት መላእክት ሊቀ ካህናት ሆነው እንዳልተሾሙልን መስክሯል። ጻድቃንና ሰማዕታት መካከለኞች ይሁኑ ካልንም ተመልሰን ወደ ብሉይ ኪዳን መካከለኞች አሠራር መመለሳችን ነው። ጻድቃን ሰማዕታት እንደ ብሉይ ኪዳን ያለ ክህነት አይቀበሉ እንጂ፥ ሰው በመሆናቸው ከብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት በምንም አይሻሉም። እንደ እነዚያ እነዚህም የግድ መካከለኞች (ሊቃነ ካህናት) ይሁን ብንል እንኳ፥ መካከለኛነታቸው በሞት የሚሻር ነበር የሚሆነው፤ “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው” የሚለውን መስፈርት ዐልፈው የሚሄዱበት ማንነት የላቸውምና። እርሱ ጌታችን ግን “ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” (ዕብ. 7፥23-25) እንደ ተባለው፥ ሕያው ጌታ መካለኛነታቸው በሞት ለተገደበው ሊቃነ ካህናት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታት ጭምር አስታራቂና መካከለኛ ሆኗል።
ይቀጥላል
በጮራ ቍጥር 41 ላይ የቀረበ


[1][1] አውጣኬ መለኮት ሥጋን ዋጠው መጠጠው በማለት የኢየሱስ ትስብእት ወደ አምላክነት ተለውጧል የሚለውን ኑፋቄ ያስተማረ መናፍቅ ነው። 

3 comments: