Friday, March 22, 2013

ጋብቻ



በማስተዋል ዐብራችሁ ኑሩ

የይሥሐቅን የጋብቻ ሁኔታ ለማየትና ከዚህ ጋብቻ ልንማረው የሚገባንን ትምህርት ለመገንዘብ በቅድሚያ ይሥሐቅ ጠንካራ ሥነ ምግባርና እምነት ከነበረው ከአብርሃም የተወለደ ልጅ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ይሥሐቅ የተወለደው አብራሃም በሸመገለበት ጊዜና እምነቱ በከፍተኛ ደረጃ ከተፈተነ በኋላ ነው፡፡ “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይሥሐቅን ይዘህ … ሂድ” ይህ ቃል አብርሃም አንድ ልጁን ይሥሐቅን በመሥዋዕትነት እንዲያቀርብ እግዚአብሔር ለአብርሃም የተናገረው እጅግ ፈታኝ የሆነ ቃል ነው፡፡

ይኸውም አብርሃም ለይሥሐቅ የነበረውን የተለየ ፍቅር እግዚአብሔር ራሱ ያውቀው ስለ ነበረ የመሥዋዕትነቱ ጥሪ የቀረበው አባትና ልጅ የነበራቸው ጥልቅ ፍቅር ከግምት ውስጥ ገብቶ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ የይሥሐቅን ሕይወት በሚመለከት ከተመዘገቡት ሁለት ጠቃሚ ታሪካዊ ድርጊቶች ውስጥ በተለይ በእግዚአብሔር ፈቃድና በአብርሃም አነሣሽነት መሥዋዕት ለመሆን ወደ መሠዊያው ቦታ ያለምንም ተቃውሞ መሄድ መቻሉና የሚያገባትን ሚስት ፍልጎ በማግኘቱ ረገድ የታየው ሁኔታ ይሥሐቅም በበኩሉ ለአባቱ ለአብርሃም እጅግ ታማኝና ታዛዥ እንደ ነበረ ያሳያል፡፡

Saturday, March 16, 2013

መሠረተ እምነት


ካለፈው የቀጠለ
ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው?

ኢ ክርስቲያን ከሆኑ ወይም ስንዴን መስለው ያሳስቱ ዘንድ በስንዴ ዕርሻ ውስጥ እንደ ተዘራ እንክርዳድ ዐይነት የእምነታቸው ሥርና መሠረት አረማዊነት ሆኖ ሳለ ጠላት ወደ ክርስትና አስርጎ ከአስገባቸው ክርስትና መሰል ባህለ ሃይማኖትን ከያዙ ግለ ሰቦች ወይም ቡድኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት ለመማር መሞከር የብርሃንን ድምቀት እንዲነግሩን ወይም የቀለም ዐይነቶችን እንዲለዩልን ዓይነ ስውራንን እንደ መጋበዝ ይቈጠራል፡፡

ይልቁንም ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋና በመንፈስ ዐይን ካዩት፥ ሞቱን ሞተው ሕይወቱን ከኖሩት ቅዱሳን ምስክርነት የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት መማር ተገቢና ብቸኛም መንገድ ይሆናል፡፡

Sunday, March 10, 2013

መሠረተ እምነት


ከነቅዐ ጥበብ
               ካለፈው የቀጠለ

ስለ እግዚአብሔር ወልድ በባሕርይ ፍጹምነትና በህላዌ (አኗኗር) ዘላለማዊነት ጸንቶ ያለው ይሆዋ በመለኮት አሐድነት ላይ በተመሠረተ፥ በህልውናና በኩነት በተሰናሰለ ሦስትነት ራሱን እንደ ገለጸ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ ከሥላሴም እያንዳንዱ ህልው (ኗሪ) ለየራሱ እኔ የማለት መብት ያለውና በምልዐተ ህልውና የሚኖር እንደ ሆነ እኔነቱንም የሚያሳቅውበት ህላዌ ኹነታውና (ኩነቱና) ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ተረጋግጦ መሰበኩ አሌ የማይባል በእምነት በተዘረጋ እንደ መንፈስ የሚዳሰስና የሚጨበጥ እውነት ነው፡፡ ስለ ሆነም በዚህና በተከታታይ ዕትሞች፥ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ በመባል ከሚመሰገኑት ሥላሴ በራሱ እኔ የማለት መብት ስላለው ስለ እግዚአብሔር ወልድ ተከታታይ ትምህርት ይቀርባል፡፡

መግቢያ
ክርስትና ከተሰበከበት ጊዜ ጀምሮ እንክርዳድን በመዝራት ንጹሕ የሆነውን የትምህርተ ክርስትናን ስንዴ ጥራት ለማበላሸት በማቀድ በጠላት የተደረገው ሙከራ ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል (ማቴ. 13፥24-30)፡፡ ጠላት እንክርዳድን በስንዴ መካከል የመዝራቱ ዐላማ ምን እንደ ሆነ የክርስቶስ ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) ከተረዳችውና በጥንቃቄ ከተከታተለችው ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ የጠላት አፈ ሙዝ ምን ጊዜም ከክርስትና ትምህርት በተለይ ጌታ እግዚአብሔር ወልድንና ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በሚመለከት ዶክትሪን ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሰዎች የኀጢአታቸውን ስርየት በመቀበል ከኵነኔ የሚድኑት እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ በሰው ቦታ ተተክቶ የሰውን ኀጢአት በመሸከሙና በመቀጣቱ ነው፡፡ ስለ ሆነም ጌታ የተቀበለው ቅጣት ለኔ ስለ እኔ ነው በማለት የታመኑበት ብቻ እንደሚድኑ የተረጋገጠ ሆኗል (ዮሐ. 3፥14-18)፡፡ ይህን የወንጌል ማእከላዊ ምስክርነት በፍጥረታዊ ሰው ልብ ውስጥ በማስገባት መለኮታዊውንም ብርሃን በመፈንጠቅ ይታመኑበት ዘንድ የሚረዳቸው ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው (1ቆሮ. 2፥10-13)፡፡ የአባባሉን እውነትነት የምንቀበል ከሆነ ይዋጀው ዘንድ ቤዛው ሆኖ የሞተለትን ኢየሱስ ክርስቶስንና እንዲያምን የሚረዳውን መንፈስ ቅዱስን የሰደበ፥ የናቀ፥ ያቀለለ፥ ሰው በምን መንገድ ሊድን ይችላል? እንደዚህ ያለው ሰው መውጪያ ወደሌለው ዐዘቅት ውስጥ ወድቆ በጭንቅላቱ የቆመ ሰውን ይመስላል (ማቴ. 12፥31-32)፡፡ ሰይጣን የራሱን ያህል ብቻ ሰው እግዚአብሔርን በማወቅ እንዲወሰን ቸል ቢልም፥ ሰው ከሰይጣን ተለይቶ ለእግዘአብሔር የሚሆንበትን የመዳኛውን መንገድ ሊዘጋበት ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ስመ ክርስትና ካላቸው ወገኖችም እንደዚህ ያሉ የክርስትናን ታሪካዊ ነገር ብቻ እንዲያምኑ ሰይጣን የለቀቃቸው ሰዎች መገኘታቸው ቢያስደንቅም የመኖራቸው ጕዳይ ግን ርግጠኛ መሆኑ አያከራክርም፡፡

Friday, March 8, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት
ከሁሉን መርምር
በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ በብሉይ ኪዳን መጨረሻ ከገጽ 721-1037 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች የማይገኙ መጻሕፍት በመጨመራቸው፥ ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ያውቃሉን? “ተጨማሪ (ዲዮትሮካኖኒካል) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት” በሚል የክፍል መጠሪያ የተጨመሩት መጻሕፍት 18 ናቸው፡፡

በውሳኔ የተጨመሩት መጻሕፍት የሚገኙበት ጥራዝ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲቈጠር እነርሱ የሌሉበት ጥራዝ ግን “ጐደሎ መጽሐፍ ቅዱስ” ተብሎ ሲጠራ ተሰምቷል፡፡