Monday, August 26, 2013

ርእሰ አንቀጽ



ደጁ ለጌታ ይከፈት


ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ በክቡር ደሙ የዋጃት የብቻው ገንዘቡ ናት። እንደ ተጻፈውም፣ “አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት(ኤፌ. 1፥23) የቤተ ክርስቲያን መሠረት ክርስቶስ ነው፤ ማእከሏም ክርስቶስ ነው፤ ራሷም ክርስቶስ ነው። ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን የሚያሰኛት ቅሉ ክርስቶስን መሠረቷ፣ ማእከሏና ራሷ ማድረጓ ነው፤ ያለ ክርስቶስ ከሆነች ግን “ቤተ ክርስቲያን ነኝ” ማለቷ መንፈሳዊ ትርጕም ያጣል። ብዙ ነገር አለኝ ብትል እንኳ ያለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ባዶ ስብስብ ትሆናለች። ክርስቶስን ኹለንተናዋ ያላደረገች ቤተ ክርስቲያን እንዴት ምስኪን ናት!

በምድር ላይ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን፣ ራሷንና ጌታዋን ክርስቶስን ከውስጧ አስወጥታ በራሷ ነገር ልትሞላና እርሱን በአፍኣ (በደጅ) ልታቆመው ትችላለች። በራእየ ዮሐንስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ይህን ትልቅ ስሕተት ፈጽማ ነበር። ለዚህ ነው ጌታ፣ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” ሲል ለቤተ ክርስቲያኒቱ የክፈችልኝ መልእክት ያስተላለፈው (ራእ. 3፥20)።

የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ጌታዋን ከውስጧ አውጥታ በደጅ እንዲቆም ለምን አደረገች? ለቤተ ክርስቲያኒቱ መልአክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተላለፈው የንስሓ መልእክት ውስጥ እንደ ዘረዘረው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለእኔ ጌታ አያስፈልገኝም ባይ ሳትሆን አልቀረችም። ጌታ ከውስጧ ወጥቶ በደጅ እንዲቆም ያደረገውም ዋና ነገር ይህ እንደ ሆነ መገመት አያስቸግርም። ጌታ እንደ ተመለከታት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ “ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ፤ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም” ባይ ነበረች፤ ይሁን እንጂ፦ ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውር፣ የተራቈተችም መሆንዋን አላወቀችም ነበር (ቍጥር 17)። ባለጠጋ ሳትሆን ባለጠጋ ነኝ፤ ብዙ የጐደላት ነገር እያለ አንዳች አያስፈልገኝም ማለቷና ጌታን በደጅ ማቆሟ የቤተ ክርስቲያኒቱ ውድቀት ከፍ ያለ መሆኑን ያሳያል። አፍቃሪዋ ጌታ ግን ወደ እርሷ ለመግባት በደጅ ቆሞ እያንኳኳ ነበር። ለእርሷ ያልታወቃት ጕስቍልናዋ፣ ምስኪንነቷና ድኽነቷ እንዲወገድና በብልጽግና እንዲተካ “በእሳት የነጠረውን ወርቅ”፣ የለበሰች ሲመስላት ኀፍረቷ እንዳይገለጥ “ነጭ ልብስን”፣ የምታይ ሲመስላት ለታወሩት ዐይኖቿ የምትኳለውን ኵል ከእርሱ እንድትገዛ መክሯታል (ቍጥር 18)። ለቤተ ክርስቲያኒቱ መልአክ “ከእኔ እንድትገዛ እመክርሃለሁ” ነው ያለው፤ ይህም የቤተ ክርስቲያን ችግር የሚፈታውና ጕድለቷ የሚሟላው ከጌታ ዘንድ ብቻ መሆኑን ያሳያል።




እንደ ሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ጌታን ከውስጧ ያወጣችውና በአፍኣ ያቆመችው፣ የእርሱን ስፍራም በሌሎችና በምድራዊ ጕዳዮች ያስያዘች፣ ያለች ሲመስላት የሌለች፣ ባለጠጋ እንደ ሆነች የምታስብ፣ ነገር ግን የተጐሳቈለች፣ ዐይናማ ነኝ ስትል ማየት የተሳናት ቤተ ክርስቲያን መፍትሔዋን ከሌላ ዘንድ ብትፈልግ ችግሯን ማባባስ እንጂ መፍትሔ አታመጣም። መፍትሔው ሳታመነታና ሳትዘገይ “አታስፈልገኝም” ብላ በአፍኣ ያቆመችውን ጌታዋን አሁኑኑ ይቅርታ ጠይቃ ደጇን ከፍታለት ግባ ማለት ይገባታል። በተሰጣት ዕድል ተጠቅማ ደጇን ካልከፈተችለት ግን ፍጻሜዋ የከፋ ይሆናል። “በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን ዐውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ፥ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው” የሚል ብርቱ ማስጠንቀቂያ ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን መሰጠቱን መዘንጋት የለብንም (ቍጥር 15-16)።
  
በማሕልየ መሓልይ ውስጥ እንደምናነበው፣ ውዷ በደጅ ቆሞ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ” ሲላት በጊዜው፣ “እኔ ተኝቻለሁ፤ ልቤ ግን ነቅቷል” የምትለው ሙሽራዪቱ የውዷ ቃል መሆኑን ብታውቅም ተነሥታ ላለመክፈት ምክንያቶቿን በመደርደር፣ “ቀሚሴን አወለቅሁ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ እንዴት አሳድፈዋለሁ?” እያለች ጊዜያቶችን አሳለፈች። ለራሷ ምቾት እንጂ በጠልና በሌሊት ነጠብጣብ ለራሰው ውዷ ቅድሚያ አልሰጠችውም። እርሱም እንዳልከፈተችለት ባየ ጊዜ ማንኳኳቱን ትቶ ፈቀቅ አለ። ዘግይታ ግን ተነሣችና ከፈተችለት፤ ይሁን እንጂ ውዷን አላገኘችውም። ብትጠራውም አልመለሰላትም። እርሱን ፍለጋ በሌሊት ብትወጣም የተረፋት በከተማዪቱ ጠባቂዎች መደብደብ፣ መቍሰልና የዐይነ ርግብ መሸፈኛዋን መነጠቅ ሆነ። ከዚያ የጠፋውን ውዷን የማፈላለጉን ሥራ ቀጠለች (ማሕ. 5፥2-8)። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን በደጅ ቆሞ ለሚያንኳኳው ውዷ ለክርስቶስ ደጇን መክፈት አለባት። ካልከፈተችለት ውዷ ፈቀቅ ሊል ይችላል። ያለእርሱ የምታደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴዋ ሁሉ ከንቱ፣ ምድራዊና እዚሁ ምድር ላይ ቀሪ ነው የሚሆነው።

ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ምክንያት ውዷን ክርስቶስን ከውስጧ አውጥታ በደጅ አቁማዋለች። የራሷን ዝናና ጥንታዊነት ስትተርክ፣ “እኔ ከሁሉ ቀዳሚ ነኝ፤ ሁሉ አለኝ፤ አንዳች አያስፈልግኝም” ስትል፣ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእርሱን ብቸኛ ቤዛነት መስበክ ትታ ሌሎችን ቤዛዎች አድርጋ ስትሰብክ፣ እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ መመሪያዋ ማድረግ ሲገባት፣ እርሱን ቸል ብላ ሌሎች ድርሳናትን መመሪያዋ ስታደርግ፣ በእርሷ ዘንድ ስፍራ ያላገኘው ጌታ ከውስጧ ወጥቷል። በደጅ ቆሞም እንድትከፍትለትና እንዲገባ እያንኳኳ ይገኛል። ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን፣ በማሕልየ መሓልይ ላይ እንደ ተጠቀሰችው ሙሽሪት፣ ለሚያንኳኳው ጌታ ላለመክፈት፦ ጥንታዊነቴ፣ ታሪኬ፣ ትውፊቴ፣ አስተምህሮዬ፣ ሥርዐቴ፣ ባህሌ፣ ልማዴ፣ ወዘተ. እያለች ውዷን ላለማስገባት በደጅ አቁማው እያንገራገረች ትገኛለች። ቤተ ክርስቲያን የእነዚህ ሁሉ ዕሴቶች ባለቤት ብትሆንም፣ ዕሴቶቹን ለጌታ ክብር ካላዋለቻቸውና የእርሱን አዳኝነት ላልሰሙት ለማሰማት ካልተጠቀመችባቸው ጥቅም የላቸውም፤ እዚሁ በምድር ላይ ቀሪዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ጌታ ዛሬም ከውስጧ አውጥታ በደጅ ያቆመችውን ቤተ ክርስቲያን፣ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ፥ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” ሲል የፍቅር ድምፁን እያሰማት ይገኛል (ራእ. 3፥20)።

እኛም የክርስቶስ ሙሽራ የሆንሽ ቤተ ክርስቲያን ሆይ! የክርስቶስ ብቻ እንጂ የሌሎች ልትሆኚ አይገባሽም። በአፍኣ ቆሞ ለሚያንኳኳውና ከአንቺ ጋር እራት ለመብላት ለሚፈልገው ለውድሽ ለክርስቶስ ደጁን ክፈቺለትና ወደ አንቺ ይግባ ማለት እንወዳለን። የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና ደጁን ለጌታ የዘጉበትንም ሁሉ ከዘማሪ ዳዊት ጋር በመተባበር፣ “እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” እንላቸዋለን። “ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው?” ሲሉ ቢጠይቁን መልሳችን ይህ ነው፤ “እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኀያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኀያል። … የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።” ስለዚህ “እናንተ መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” (መዝ. 23/24፥7-10)።

(በጮራ ቍጥር 45 ላይ የቀረበ)


Sunday, August 25, 2013

ማስታወቂያ


ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 45 ለንባብ በቅቷል




*   ርእሰ አንቀጽ
“ደጁ ለጌታ ይከፈት” በሚል ርእስ በቀረበው መልእክት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ከውስጧ አውጥታ በደጅ ያቆመችውንና “ክፈችልኝ” እያለ የሚያነኳኳውን ጌታዋን እንድታስገባው ጥሪ ያስተላልፋል፡፡ እንዲህ በማለት፦
“የክርስቶስ ሙሽራ የሆንሽ ቤተ ክርስቲያን ሆይ! የክርስቶስ ብቻ እንጂ የሌሎች ልትሆኚ አይገባሽም። በአፍኣ ቆሞ ለሚያንኳኳውና ከአንቺ ጋር እራት ለመብላት ለሚፈልገው ለውድሽ ለክርስቶስ ደጁን ክፈቺለትና ወደ አንቺ ይግባ ማለት እንወዳለን። የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና ደጁን ለጌታ የዘጉበትንም ሁሉ ከዘማሪ ዳዊት ጋር በመተባበር፣ ‘እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ’ እንላቸዋለን።”

መሠረተ እምነት
“ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” (2ቆሮ. 5፥16) የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ለስሕተታቸው መሸፈኛነት በተሳሳተ መንገድ እየጠቀሱ፣ የክርስቶስን መካከለኛነት እያስተባብሉና የተዋሕዶን ትምህርት እየበረዙ ላሉ ወገኖች ትምህርተ ተዋሕዶን መሠረት ያደረገ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡

*  የዘመን ምስክር
የዚህ ዕትም የዘመን ምስክር አባ ወልደ ትንሣኤ ግዛው በኋላም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በተሰጣቸው ሀብተ ፈውስ እና ሀብተ ስብከት ለብዙ ምእመናን በረከት ሆነው ማለፋቸው የተዳሰሰበት ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ “እኔ ሰው ሲፈወስ ደስ ይለኛል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የፈውስ ስጦታ እንዲሰጠኝ በልጅነቴ ለምኜው ነበር። እግዚአብሔርም የለመንሁትን ሰጥቶኛል። እኔም በክርስቶስ ኀይል የታመሙትን እፈውሳለሁ፥ ለወደ ፊቱም በዚሁ ሥራዬ ለመቀጠል እፈልጋለሁ” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

 ፍካሬ መጻሕፍት
    “ልጆችዋ ይነሣሉ፥ ምስጋናዋንም ይናገራሉ … መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።” (ምሳ. 31፥28፡29) ለሚለው ጥቅስ ዐውዳዊ ፍቺ ተሰጥቷል፡፡ ጥቅሱ በተሳሳተ አተረጓጐም ለማርያም የተሰጠበትን መንገድ በመፈተሽ ጥቅሱ ለማርያም የተነገረ አለመሆኑን ዋቢዎችን በመጥቀስ ይሞግታል፡፡

*  ታላላቅ መንፈሳውያን ቃላት
ፍቅር የተሰኘውን መንፈሳዊ ቃል የሚያብራራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ቀርቧል፡፡

ሌሎችም ጽሑፎች የተካተቱበትን ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 45ን ገዝተው ቢያነቡ ትልቅ መንፈሳዊ በረከት እንደሚያገኙ ጥርጥር የለንም፡፡

Wednesday, August 21, 2013

የመዳን ትምህርት



ካለፈው የቀጠለ
ድሩም ማጉም ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን ደኅንነት
ሰው እንዴት የራሱ ሊያደርገው ይችላል?

ከላይ እንዳነበብነው ይህ ቀረው የማይባለውን ሰውን የማዳን ሥራ፥ እግዚአብሔር ከፍ ባለ መለኮታዊ ጥበብ ዐቅዶት በነበረው መሠረት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል አጠናቆታል፡፡ ዛሬ ሰውን ለማዳን የሚታቀድም ሆነ የሚደረግ አንድም ነገር አልተተወም፡፡ አሁን የሚቀር ቢኖር በሰው ደረጃ መፈጸም የሚገባው የተፈጸመውን “በእምነት መቀበል” ብቻ ነው፡፡ ከወንጌላውያን አንዱ የሆነው ዮሐንስ የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ የተጠናቀቀውን የሰውን ደኅንነት በወንጌሉ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ በመስጠት ከጻፈ በኋላ የሰው ድርሻም ምን መሆን እንዳለበት ሳይገልጽልን አላለፈም፡፡

ወንጌላዊው፥ መዳንን የሚፈልግ ሰው ወደ ቅድስት ሀገር ይሂድና የታሪክ ቦታዎችን ይጐብኝ፤ ወይም ወርቅ ብር ይክፈልና ይግዛ፤ ወይም ሰባት ዓመት በራሱ ይቁምና ይጸልይ፤ ወይም በአንዱ በረሓ ውስጥ ገብቶ በረኃብና በጥም ራሱን ይግደል፤ ወይም …  አላለም፡፡ እንደዚህማ ባለ መንገድ የሰው ነፍስ ልትድን ብትችል ኖሮ፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ተለዋጭ ሆኖ ይሞት ዘንድ ባላስፈለገ ነበር፡፡ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ያስተማረውን መሠረት በማድረግ ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ ጽፎ ያስተላለፈልን ትምህርት የሚለው እንዲህ ነው፡፡

Friday, August 16, 2013

የመዳን ትምህርት





“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ … ማን ያድነኛል?”
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ (ሮሜ 7፥24-25)

ከናሁ ሠናይ 
ካለፈው የቀጠለ

ሰውን የማዳን ሥራ በጌታችን በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጀምሮ በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተጠናቀቀ ካለፈው ዕትም ያነበብነውን እናስታውሳለን፡፡ ሰውን የማዳን ሥራን ከኀጢአተኛው የሰው ዘር የተወለደ ማንኛውም ሰው ሊያከናውነው አይችል የነበረ መሆኑን፥ በመላክትም እንኳ ሊሠራ የማይችል እንደ ነበረ ካነበብነው ተረድተን እዚህ ደርሰናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው ነፍሱን ለማዳን ቤዛ የመስጠት ግዴታ ያለበትና ያላገኘ መሆኑን ሲያመለክት፥ ሰው ዓለምን ሁሉ ቢገዛ ከሚገዛው ዓለም ሁሉም ለነፍሱ ቤዛ የሚሆንለት ማግኘት ካልቻለ፥ ዓለምን በመግዛቱ ምን ተጠቀመ? አለ፡፡ ዓለም ሁሉ ሲባልም የምናውቀውንና የማናውቀውን ዓለም ሁሉ ቢገዛም፥ ከሚገዛው ዓለም ሁሉም ለነፍሱ ቤዛ የሚሆን ማግኘት ካልቻለ ገሃነመ እሳት መውረድ አልቀረለትምና፥ ሰው ዓለምን ሁሉ የራሱ የማድረጉና ያለማድረጉ ውጤት ነፍሱን በሚመለከት ልዩነት እንደሌለው አመስጥሮ አስረዳ፡፡