Sunday, August 16, 2015

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን - ክፍል ሦስት


ካለፈው የቀጠለ -
ዳዊት እስቶክስና የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር
ብንደግፈውም ብንቃወመውም፥ ቢስማማንም ባይስማማንም አንድን የተፈጸመንና የራሱን አሻራ ትቶ ያለፈን እውነተኛ ታሪክ መለወጥ አንችልም። ታሪኩን ለመለወጥና ሌላ መልክ ሰጥተን ለመግለጥ ብንሞክር ግን በታሪክ ተወቃሽ ከመኾን አናመልጥም። እንዲህ ሲባል ግን ታሪክን አዛብቶ ማቅረብና ያን የተዛባ ታሪክ ሰዎች እውነተኛ ታሪክ መስሏቸው ለጊዜውም ቢኾን እንዲቀበሉት ማድረግ አይቻልም ማለት አይደለም። ለምሳሌ፦ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውን የጌታችንን የትንሣኤ የምሥራች፥ ከሞት መነሣቱ ኪሳራ የሚያደርስባቸው መኾኑን የተረዱ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በሌላ የፈጠራ ታሪክ እንደ ተኩትና፥ ‘ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት እንጂ፥ ኢየሱስ ከሙታን ተለይቶ አልተነሣም’ የሚለው የፈጠራ ታሪክ እውነት መስሎ ወንጌላዊው ማቴዎስ ወንጌሉን እስከ ጻፈበት ጊዜ ድረስ እንኳ በአይሁድ ዘንድ ሲወራ እንደሚኖር ጽፏል (ማቴ. 28፥11-15)። ስለ ዴቪድ እስቶክስ ከዚህ ቀደም በማኅበረ ቅዱሳን፥ አኹን ደግሞ በ“መድሎተ ጽድቅ” እየተተረከ ያለው የተዛባ ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም።
ታላቁ ሰው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ስለ ታሪክ አጻጻፍ ያስቀመጡት መርሕ እዚህ ላይ ቢወሳ መልካም ነው። እንዲህ ነበር ያሉት፥
ታሪክን መማር ለኹሉ ሰው ይበጃል፤ … የታሪክ ትምህርት ግን የሚጠቅም የውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲኾን ነው። እውነተኛንም ታሪክ ለመጻፍ ቀላል ነገር አይደለም። የሚከተሉትን ሦስት የእግዚአብሔር ስጥወታዎች ያስፈልጋልና። መጀመሪያ ተመልካች ልቦና፥ የተደረገውን ለማስተዋል፤ ኹለተኛ የማያደላ አእምሮ፥ በተደረገው ለመፍረድ፤ ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ፥ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ። ያገራችን የታሪክ ጻፎች ግን በነዚህ ነገሮች ላይ ኀጢአት ይሠራሉ። በትልቁ ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ። ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጠባሉ። አጻጻፋቸውም ድብልቅልቅ እየኾነ ላንባቢው አይገባም (2002፣ገጽ 1)።
በ“መድሎተ ጽድቅ” ስለ ዳዊት እስቶክስ የተጻፈው በአብዛኛው ይህን መስፈርት ያላሟላ ከመኾኑም በላይ፥ ታሪክን ያላገናዘበ፥ በእውነታው ላይ ያልተመሠረተና ምንጭ የሌለው፥ በጭፍን ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ተራ ስም ማጥፋት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ ቀደም “የገሃነም ደጆች” በሚል ርእስ በስምዐ ጽድቅ ልዩ ዕትም ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ባወጣው ጽሑፍ፥ በተለይ በመጋቢት 1995 ዓ.ም. ዕትሙ የብዙዎችን ስም አክፍቶ በጻፈ ጊዜ፥ እንዲሁም “የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ” በሚል ርእስ በ2003 ዓ.ም. ባሳተመው አነስተኛ መጽሐፍ ላይ፥ የዳዊት እስቶክስን ታሪክ ያቀረበው በዚሁ መንገድ ነው። ዳዊት እስቶክስና ማኅበራቸውን “የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር”ን አገልግሎት በተሳሳተ መንገድ ነው ያቀረቡት። ይህም የሚያሳየው ለዐላማቸው መሳካት ሲሉ የነበረውን ታሪክ ለውጠው በማቅረብ እውነተኛውን ታሪክ እያጠፉና ራሳቸው የፈጠሩትን ዐዲስ ታሪክ አሥርገው እያስገቡ መኾናቸውን ነው።
ዳዊት እስቶክስና “የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያከናወኑት ተግባርና ያበረከቱት አስተዋፅኦ ብዙ ቢኾንም፥ በዚህ ጽሑፍ ግን ለአብነት ያኽል እጅግ ጥቂቱን ለመጠቃቀስ እንሞክራለን። (ለዚህ ምንጫችን በዋናነት፥ “The Most Valuable Thing: The Word at Work in Ethiopia” በተሰኘ መጽሐፋቸው ከሚሲዮናውያቱ አንዷ የነበሩት ዶሪስ ቤንሶን የጻፉት የማኅበሩ የአገልግሎት ታሪክ ነው። በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በትምህርቶቻቸው ከተሳተፉትና በሕይወት ካሉት፥ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥና በሌላም ስፍራ በልዩ ልዩ የሥራ መስክ ላይ ከሚገኙት ከአንዳንዶቹ ያገኘነውን መረጃም በምንጭነት ተጠቅመናል።)

“Bible Church Men’s Society” (BCMS) በእንግሊዝ አገር በሎንደን የተቋቋመ ማኅበር ሲኾን፥ አባላቱ በአብዛኛው ከአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ናቸው። በኢትዮጵያ ተቋቁሞ ይሠራ የነበረው የዚህ ማኅበር ቅርንጫፍ፥ “የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር” በመባል ይታወቅ ነበር። ማኅበሩ በኢትዮጵያ የ”BCMS” ቅርንጫፍ ኾኖ ይሠራ የነበረው በመንግሥት ፈቃድና ድጋፍ ሲኾን፥ በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በቅርብ በመተባበር ነበር። ይልቁንም በጎንደር ከሰሜንና በጌምድር ሀገረ ስብከት፥ በአሥመራ ከኤርትራ ሀገረ ስብከት፥ በመቀሌ ከትግራይ ሀገረ ስብከትና በሸዋ ለመዘዋወር ከሀገረ ስብከቱ ፈቃድና ስምምነት እያገኘ ሲኾን፥ በአዲስ አበባ ከመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጋር ወዳጅና አጋር በመኾን ከፍተኛ የወንጌል አገልግሎት አበርክቷል።

የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ዐላማ ምን ነበር?
የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበርን ያቋቋሙት ሚስዮናውያን ዐላማቸው “መድሎተ ጽድቅ” እንደሚለው በስልት ተጠቅመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ፕሮቴስታንታዊ ማድረግ ፈጽሞ አልነበረም። ማንነቷ እንደ ተጠበቀ መጽሐፍ ቅዱስን በማሠራጨት አገልጋዮቿ ቀሳውስትና ዲያቆናት ስብከተ ወንጌልን እንዲያፋጥኑና ለሕዝባቸው ወንጌልን እንዲያደርሱ ለማድረግ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ የተከናወነውን የቤዛነት ሥራ በመግለጥ፥ የወንጌሉን የምሥራች ለሕዝባቸው ማድረስ እንዲችሉ ከስብከተ ወንጌል ጋር የተገናኘና መሰል ትምህርቶችንና ሥልጠናዎችን በመስጠት ቤተ ክርስቲያኗን መርዳትና መደገፍ ላይ ያተኰረ ነበር። ቀጥሎ የቀረቡትና በጽሑፍ ያሰፈሯቸው የዐላማቸው ነጥቦችና የሠሯቸው ሥራዎች ይህን ይመሰክራሉ። የሚከተሉት “ዘጠኝ ነጥቦች” የማኅበሩ ዐላማዎች ሲኾኑ፥ እነ አልፍሬድ ባክስተን በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎታቸውን በይፋ ከመጀመራቸው በፊት ያስታወቋቸው ናቸው።
1.      ኹሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት መኾን አለባቸው ብለን እንመኛን።
2.     ስለ ኾነም የእኛ እውነተኛ ምኞት ይህቺኑ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መርዳትከክርስቶስ ትእዛዝ ጋር በተገናኘም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ወደሚቻለው የምድሪቱ የጠረፍ አካባቢዎች እንድትሰብክ ማድረግ ነው።
3.     በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሕዝቡ በሚታወቀው ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን የማሠራጨትና የማስተማር ተግባር መጽሐፍ ቅዱስን በማቅረብ እርሷን መርዳት ፍላጎታችን ነው።
4.     በያንዳንዱ መንደር [ሕንጻ] ቤተ ክርስቲያን ይገነባ ዘንድ ፍላጎት አለን።
5.     በዚህ መንገድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ኹኔታ ማደግ ስላለባት፥ እኛ ሕዝቡን በስብከተ ወንጌል እንዲያግዝ እናስተምረዋለን፤ ይህን የምናደርገውም ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያንና ከታሪኳ ጋር በተስማማ ኹኔታ ነው።
6.    የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለመዳን የሚያስፈልጉ ነገሮች ኹሉ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ መኖራቸውን እንደምታምን ኹሉ፥ የእኛም እምነት ይኸው ነው።           
7.     የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኒቅያ የእምነት መግለጫ ዋናው የእምነት አጠቃላይ መግለጫ መኾኑን ታምናለች፤ እኛም እናምናለን።
8.     ክርስቶስ ኹለቱን ምስጢራት ማለትም ጥምቀትንና ቍርባንን እንድንፈጽም አዞናልና አማኞች ኹሉ እነርሱን መፈጸም አለባቸው። ስለዚህ የእኛ ሐሳብ በስብከተ ወንጌል ምክንያት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለሚመለሱት፥ ወይም ለሚጨመሩት ክርስቲያኖች ኹሉ እነዚህን ምስጢራት መፈጸም ያለበት የኦርቶዶክስ ቄስ ሊኾን ይገባል የሚል ነው።
9.    ግእዝ ወንጌልን ለሚሰብኩ ጠቃሚ መርጃ መሣሪያ መኾኑን በመገንዘብ፥ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግእዝ ላለው ጠቀሜታ ዕውቅና እንሰጣለን። ስለዚህ ኹሉም ሰባክያን ግእዝን እንዲያጠኑ ማበረታታት አለብን።
በኋላ ላይ 4ኛውንና 9ኛውን ነጥቦች በአፈጻጸም ረገድ ሊያስቸግሩ ይችላሉ በሚል ሰርዘዋቸዋል (ቤንሶን፣ ገጽ 18፡19)።  
እነዚህ ዐርማዎች “The Most Valuable Thing: The Word at Work in Ethiopia” ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 63 ላይ የተወሰዱ ናቸው

የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር የመጀመሪያውም ኾነ በኋላ የተሻሻለው ዐርማ የማኅበሩን ዐላማ ገላጭ እንደ ነበር መመልከት ይቻላል። ዐርማውን ብቻ እንኳ በማየት፥ የእነ ዳዊት እስቶክስ ዐላማ ኦርቶዶክስን ፕሮቴስታንት ማድረግ ሳይኾን፥ ኦርቶዶክስን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አገልግሎቷን እንድታፋጥንና ወንጌልን ለኢትዮጵያውያን ኹሉ እንድታደርስ መርዳት እንደ ነበር መገንዘብ ይቻላል።
ዳዊት እስቶክስ ከወረራው በኋላ ከአልፍሬድ ባክስተን አመራሩን ተረክበው በማገልገል ላይ ሳሉ፥ የምስጢር አገልግሎት ክፍል ዋና ኀላፊ የኾነ አንድ ጣሊያናዊ፥ የተልእኮአቸውን እንቅስቃሴ ለመመርመር በቀረበና በጠየቃቸው ጊዜ ዳዊት እስቶክስ እንዲህ ነበር ያሉት፤ “እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ነው እንጂ፥ ዐዲስ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመር ዐላማ የለንም።” በዚህ ጊዜ ጣሊያናዊው ዐላማቸውን በመደገፍ ዐይነት ተደንቆ ነበር፤ በመጨረሻም ሰባኪዎቻቸውን እንደሚያምናቸውና ከዚህ በኋላ ጣልቃ እንደማይገባባቸው ለዳዊት እስቶክስ ዋስትና ሰጥቶ ነበር (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 34፡35)።
ይህ ዐላማቸውና ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የነበራቸው ልብ በሚያስተምሯቸው ተማሪዎቻቸው ላይም ይታይ ነበር። ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1950 ሰላሌ ላይ በነበራቸው አገልግሎት ያፈሯቸው ተማሪዎች፥ በከተማው በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነበራቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ከቀሳውስት በኩል ተቃውሞ በገጠማቸውና ከቤተ ክርስቲያን ጠቅለው እንዲወጡ በፍርድ ቤት ቀርበው በተጠየቁ ጊዜ፥ “እኛ ክርስቲያኖች፥ ኢትዮጵያውያን፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት ነን። ማንም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ከመገኘት ሊያግደን አይችልም” ሲሉ ተሟግተው ነበር። ኹኔታው በዳዊት እስቶክስ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ፥ ዐዲስ አበባ ወደሚገኙና ጕዳዩ ወደሚመለከታቸው ሊቀ ጳጳስ ተገልጦ የነበረ ሲኾን፥ እነ ዳዊት እስቶክስ እንደ ተልእኮ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር መሥራት ዐላማቸው መኾኑንና ተማሪዎቹ ከፍቼ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን መባረራቸውን ጠቅሰው፥ “ተማሪዎቹ ከእሑድ አገልግሎት መለየታቸው በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻቸውን እንዳይፈጽሙ ለመከልከል፥ ክርስቲያናዊ ሥርዐተ ቀብር እንዳይፈጸምላቸው ለማድረግ፥ ልጆቻቻውን ጥምቀተ ክርስትና እንዳይወስዱ ለማገድ ነውን?” ሲሉ በመጠየቅ፥ “ቤተ ክርስቲያኗ ሌላ ከእርሷ የተለየ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሠረት ትመርጣለች ወይ?” የሚል ጠንካራ ጥያቄም በማቅረብና ድርድር በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሥልጣናት፥ ቄሶቹ ተማሪዎቹን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመልሷቸው ትእዛዝ በመስጠት በሰላም እንዲቀበሏቸው አድገርዋል (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 77፡78)።
እነ ዳዊት እስቶክስ በኢትዮጵያ በነበራቸው የአገልግሎት ዘመን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ከማገዝና ከማገልገል በቀር፥ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ፕሮቴስታንታዊ ቤተ ክርስቲያንነት ለመለወጥ የተንቀሳቀሱበትም ኾነ፥ ፍቼ ላይ እንደ ገጠማቸው ባለ ተቃውሞ ሰበብነት እንኳ ሌላ ፕሮቴስታንታዊ ቤተ ክርስቲያን የከፈቱበት አጋጣሚ የለም። በስማቸው የተከፈተ አንድም ቤተ ክርስቲያን አናገኝም። ዐላማቸው ኦርቶዶክስን ወደ ፕሮቴስታንትነት መለወጥ ቢኾን ኖሮ፥ በዚያ ዘመን የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳትና የቤተ ክህነት ባለሥልጣናት ዐብረው ለመሥራት ባልተስማሙና ኦርቶዶክሳውያንን እንዲያስተምሩና መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ሌሎች መጻሕፍትን እንዲያሠራጩ ባልፈቀዱም ነበር። ታዲያ “መድሎተ ጽድቅ” ከየት አምጥቶ ነው ዳዊት እስቶክስየኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ፕሮቴስታንት ለማድረግ በስልት ይሠሩ” ከነበሩ ሚስዮናውያን መካከል ናቸው ያለው?

እውነተኛ ወዳጅነት

የኢትዮጵያውያን ወዳጅ የነበሩት ዳዊት እስቶክስ በጣሊያን ወረራ ጊዜ፥ በጦርነቱ ምክንያት ወደ ሶማሊያ (British Somaliland)፥ ጅቡቲ እና ኬንያ በተሰደዱ ኢትዮጵያውያን መካከል ትልቅ የስደተኞች መጠለያ በነበረውና በሰሜን ኬንያ በሚገኘው “Isiolo” በተሰኘው ትልቁ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ለሦስት ዓመታት ዐብረው ያሳለፉ ሲኾን፥ በሺሕዎች የሚቈጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችን አሠራጭተዋል መጽሐፍ ቅዱስንም አስተምረዋል (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 61)


ሚስተር ዳዊት እስቶክሰ
       (ከምስክረ ብርሃን ቍጥር 108፣ ነሐሴ 1964 ዓ.ም. የተወሰደ)

በዚህ የወረራ ወቅት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስና ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ለጠላት መሣሪያ አንኾንም ብለው በፋሺስት በግፍ ሲገደሉ፥ ግብጻዊው የኢትዮጵያ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ግን ሮም ድረስ ሄደው ለሹመታቸው ይካሰሱ ነበር። እኒሁ ግብጸዊ ጳጳስ በችግሩ ዓመታት ሕዝቡን ጥለው ወደ አገራቸው የገቡ ሲሆን፥ ወረራው ካበቃና ጠላት አገር ለቆ ከወጣ በኋላ ግን ተመልሰው ወደ ሥራዬ ልግባ ቢሉ፥ ይህን ድርጊት በመቃወም ኢትዮጵያዊው ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ቀዳማዊ (1988 - 1974 ዓ.ም.) አቡነ ቄርሎስን እስከ ማውገዝ ደርሰው ነበር። ኾኖም በብፁዕ ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ (በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ) ለ2 ዓመት ከ5 ወር እስራትና ግዞት ተፈረደባቸው (ጮራ 2002፣ ገጽ 13)፡፡

እነ ዳዊት እስቶክስ ካከናወኗቸው ተግባራት በጥቂቱ
እነ ዳዊት እስቶክስ በዘመናቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ማንነቷ ሳይለወጥ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ታድሳ ለማየት ከነበራቸው ታላቅ ሸክም የተነሣ፥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር በመቀራረብና በመነጋገር ፈቃድም በማግኘት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እያገለገሉ፥ በተለያየ መንገድ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መታደስ ዕገዛና ድጋፍ ሲያደርጉ እንደ ነበር ይታወቃል። ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል የሚከተሉትን እንጠቅሳለን፡-
1. የመጽሐፍ ቅዱስ ዝግጅት
እ.ኤ.አ. አቈጣጠር በ1962 (1953 ዓ.ም.) የታተመውንና ዛሬ ኹሉም ክርስቲያን የሚጠቀምበትን የዐማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በማዘጋጀቱ ሥራ ከተሳተፉት መካከል ሚስተር ዳዊት እስቶክስ አንዱ ናቸው። በሥራው ላይ ከመጀመሪያው ባይኖሩም፥ በኋላ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ባቀረበላቸው ግብዣ መሠረትበብዙ ጫና ውስጥ ኾነው፥ በጊዜው የፍትሕ ምክትል ሚኒስትር ከነበሩትና በዐማርኛው ላይ ከተመደቡት ከብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ ጋር ሠርተዋል (ቤንሶን፣ ገጽ 94)። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ፥ “ግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርእስ በተዘጋጀው መጽሔት ላይ ስማቸው ባይጠቀስም፥ በ1953ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ላይ የሠሩ “ሦስት የውጭ አገር ሊቃውንት” መኖራቸው ተጠቊሟል ከሦስቱ አንዱ ዳዊት እስቶክስ ነበሩ ማለት ነው (1993፣ 29)።
2.          የሌሎች ክርስቲያናውያት መጻሕፍት ዝግጅትና ሥርጭት
ዳዊት እስቶክስ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ በጐንደር ሳሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የዐምስት መልእክታትን፥ ማለትም የሮሜን፥ የ1ኛ ቆሮንቶስን፥ የኤፌሶንን፥ የዕብራውያንንና የ1ኛ ጴጥሮስን ማብራሪያዎች አዘጋጅተው በማሳተምና በማሠራጨት ብዙዎችን ጠቅመዋል። መጻሕፍቱ አኹንም ድረስ በመሠራጨት ላይ ያሉና ብዙዎች የሚጠቀሙባቸው ናቸው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገት የሚረዱ መጻሕፍትና መጽሔት በማዘጋጀትና የትርጉም ሥራ በማከናወን ረገድም፥ ከ1957 - 196ዐ ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ ለየዕለቱ የሚኾን የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ፥ ከቃለ እግዚአብሔር አንባቢዎች ማኅበር (በኋላ የቅዱሳት መጻሕፍት አንባቢዎች ማኅበር) ጋር በመተባበር አዘጋጅተዋል። አንዱ መጽሐፍ ለሦስት ወራት እንዲያገለግል ኾኖ የተዘጋጀ ሲኾን፥ ለአንድ ዓመት አራት መጻሕፍት፥ በአጠቃላይ ለአራት ዓመት ጥናት 16 ትንንሽ መጻሕፍት ተዘጋጅተዋል። እነዚህ በየዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ወይም ምዕራፍ ለማንበብ የሚመሩ ኾነው፥ ከማብራሪያ ጋር የቀረቡ ናቸው። በመጻሕፍቱ እየተረዳ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብብ ሰው በአራት ዓመት መጽሐፍ ቅዱስን በጥናት መልክ ሙሉ በሙሉ አንብቦ ይጨርሳል ማለት ነው። በሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር የተዘጋጁ ሌሎች አዕማድ መጻሕፍት መኖራቸውም ይታወቃል።

ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም፥ በሰንበት ትምህርት ቤት፥ በክፍል ውስጥና በቤትም ጭምር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያገለግሉ መጻሕፍትን በአስቸኳይ እንፈልጋለን ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፥ ዶሪስ ቤንሶን የተባሉትና ለዚህ ታሪክ ዋና ምንጭ የኾነንን መጽሐፍ ያዘጋጁት ሚስዮናዊት “የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ” የሚል ርእስ የተሰጠውንና ሦስት ቅጾች የኾኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ አንደኛ፥ ኹለተኛና ሦስተኛ መጽሐፍን በስድስት ዓመታት ውስጥ አዘጋጅተዋል። ጽሑፉን ያዘጋጁት በዚህ ረገድ ከሚያግዟቸው ኢትዮጵያውያን ጋር ሲኾን፥ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ከኅትመት በፊት ሦስቱንም መጻሕፍት ተመልክተው በካቴድራሉ ወጪ ታትመው ተሠራጭተዋል። እነዚህ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የድርሰት ክፍል የታተሙትና ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራእየ ዮሐንስ ያሉት መጻሕፍት የያዙትን መልእክት በሙሉ ያካተቱት ሦስቱም መጻሕፍት ገላጭ ሥዕሎች አሉባቸው። መጻሕፍቱ በጊዜው ታላቅ ተቀባይነትን ያተረፉና ወዲያው ዐልቀው ድጋሚ ኅትመት የገቡበት ኹኔታ ነበረ (ቤንሶን፣ ገጽ 118-119)።

በሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር የሚዘጋጅና “ምስክረ ብርሃን” የተሰኘ መጽሔት በየወሩ እየታተመ በማኅበሩ አማካይነት ይሠራጭ ነበር። በዚህ መጽሔት ላይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የተመለከቱ ዜናዎችና መልእክቶችም ይቀርቡ ነበር።

ዳዊት እስቶክስ እ.ኤ.አ በ1970 ጡረታ ሲወጡ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የማስተማሩን ተግባር የተረከቡት ቄስ ኮሊን ማንሰል (ዶሪስ ቤንሶን፣ ገጽ 112) በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ታትመው እየተሠራጩ ያሉትን “የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት”፥ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ”፥ “በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ጋር” በሚል ርእስ በ4 ቅጽ የተዘጋጁትን መጻሕፍት አዘጋጅተዋል። መዝገበ ቃላቱን በእርሳቸው አዘጋጅነት ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጓደኛቸው ጋር ያዘጋጁት ሲኾን፥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱትን ሌሎቹን ዐምስት መጻሕፍት ደግሞ ከባለቤታቸው ከሚስስ ሄዘል ማንሰል ጋር ነው ያዘጋጇቸው። በተጨማሪም “እግዚአብሔር ወልድ”፥ “ከባቢሎን ምርኮ መልስ”፥ “የእግዚአብሔር ጸጋ አሠራር” እና “አስደናቂው ልውውጥ” የተሰኙ አዕማድ መጻሕፍትንም ጽፈዋል። በመጨረሻም ስለ አጠቃላይ ነገረ መለኮት የሚናገሩ “ትምህርተ እግዚአብሔር”፥ “ትምህርተ ክርስቶስ” እና “ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ” የተሰኙ መጻሕፍትን ጽፈዋል (ማንሰል፣ 2003፣ የቄስ ማንሰል ዐጭር የሕይወት ታሪክ)።

መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ክርስቲያናውያት መጻሕፍትን ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በጅምላ በመግዛት በቅናሽና በቀላል ዋጋ በየክፍለ ሀገሩ በተለይ በጎንደር፥ በጎጃም፥ በሸዋ፥ በትግሬ፥ በኤርትራና በሌሎችም ቦታዎች እየዞሩ ይሸጡ ነበር።

3.  የመጻሕፍት መሸጫና የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት
የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ለክርስቲያኖች ከሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ነበር። በአንዳንድ ከተሞች ክርስቲያኖች *በተለይ ወጣቶች( ቅዱሳት መጻሕፍትና ሌሎች መንፈሳውያት መጻሕፍትን ማንበብ የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር ቤተ መጻሕፍት በመክፈት ረድተዋል፤ በዚሁ መሠረት በደብረ ማርቆስ የቅዱስ ማርቆስ ቤተ መጻሕፍት፥ በፍቼና በአሥመራም አብያተ መጻሕፍትን ከፍተው ነበር (ቤንሶን፣ ገጽ 120፡121፡123)።

4. የዕቅበተ እምነት ሥራ ሠርተዋል
በዚያ ዘመን የይሆዋ ምስክሮች ፈቃድ አግኝተው በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርታቸውን በትጋት እያሠራጩ ነበር ከጊዜ በኋላ መንግሥት የውጭ አገር ዜጎች የነበሩ የተልእኮውን አባላት ከአገር አስወጣቸው። ትምህርተ ሥላሴን የማይቀበለውና ክርስቶስን ፍጡር የሚለው ትምህርታቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን አስደንግጧቸው ነበር። ዳዊት እስቶክስም በትምህርቱ የተወናበዱትን ወይም የተጠመዱትን ለመርዳት ትንሽ መጽሐፍ አዘጋጅተው ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ መጽሐፉ ኹለት ጊዜ ታትሟል። በተጨማሪም በዘመኑ ብዙ ምሁራንን እየሳበ ለነበረው ለባሂዝም ትምህርት ዐጸፋዊ ምላሽ የሚሰጥ ትራክት አዘጋጅተው ነበር (ቤንሶን፣ ገጽ 93)። 
               
5. ከኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት ጋር ያከናወኑት አገልግሎት
በዚያ ዘመን በጥቂት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንድ ዐዲስና የሚያበረታታ እድገት መታየት ጀመረ፤ በተለይም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የታወቀ የኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት (Ethiopian Orthodox Mission) እንቅስቃሴ ነበር። በጊዜው ተራማጅ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች፥ እነ ዳዊት እስቶክስ የሚሠሩትን ሥራና በቤተ ክርስቲያኒቱ እያሳደሩ ያለውን በጎ ተጽዕኖ በመመልከትና ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመር ወይም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ሌላ ማንነት ለመለወጥ ዕቅድ እንደሌላቸው በሚገባ ያውቁ ስለ ነበር፥ ዐብረዋቸው እንዲሠሩ የጋበዙበት ኹኔታ አለ። እ.ኤ.አ. በ1964 በጊዜው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ የነበሩት ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም (አኹን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ) ከሚስዮናውያን አንዱ ትምህርት ቤቶች በሚዘጉበት የክረምት ወቅት በሚኖረው የዕረፍት ጊዜ ተማሪዎችን እንዲያስተምሩና በክፍል ውስጥ ተማሪዎች ይገለገሉበት ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ በማቅረብ እንዲረዷቸው ጠይቀዋቸዋል (ቤንሶን፣ ገጽ 111)። ከክረምቱ ውጪ ባለው የትምህርት ወቅትምየኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት ባዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት በየሳምንቱ ቅዳሜ ጠዋት ለተማሪዎች ትምህርት ይሰጡ ነበር። በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተቋቊመው ለነበሩትና ወንዶች ልጆችና ወጣቶች አባላት ለኾኑበት ማኅበረ ሥላሴ እና ሴቶች ልጆችና ወጣቶች አባላት ለነበሩበት ማኅበረ ክርስቶስ ትምህርት ይሰጡ ነበር (ዝኒ ከማሁ)።

በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥር ይካሄድ በነበረው የቅድስት ሥላሴ ፩ኛና ፪ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር እንግሊዛውያን መምህራን የኾኑ ኹለት አባሎቹን  በነጻ ሰጥቶ ሲያስተምሩ ነበር። በመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እንግሊዝኛ፥ ሒሳብ፥ ወዘተ. ያስተምራሉ% በተጨማሪ ሰዓት ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ የስብከት ዘዴ በተለይ ለመነኮሳትና ለዲያቆናት ያስተምሩ ነበር።

እ.ኤ.አ. በ1968 የኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት ለቀሳውስት፥ ለመነኮሳትና ለዲያቆናት ቋሚ ትምህርት በማዘጋጀት መምህራንን እንዲሰጧቸው ሚሲዮናውያኑን ጠይቀው ነበር። በጥያቄው መሠረት በማስተማር ካገለገሉት መካከል ዳዊት እስቶክስ አንዱ ናቸው። በአንድ ወቅት ዳዊት እስቶክስ የዳዊትንና የኦርዮን አሳዛኝ ታሪክ መሠረት አድርገው ሲያስተምሩ ብዙዎች በእንባ ይራጩ እንደ ነበር ጸሓፊዋ ዶሪስ ቤንሶን ጠቅሰዋል (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 112)። በ1970 እ.ኤ.አ. ለሰባክያን ልዩ ትምህርት በኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት ተዘጋጅቶ ነበር። ዐላማውም ሰባክያን ወደየጠቅላይ ግዛቱ ወጥተው እንዲሰብኩ ለማድረግ ነበር። በዚህ ልዩ ትምህርትም ዳዊት እስቶክስ መጽሐፍ ቅዱስንና እንግሊዝኛን በማስተማር ተሳትፈዋል። ከዚያ በተጨማሪ ከእሑድ ጸሎተ ቅዳሴ በኋላ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት ላይ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ይሰጡ ነበር።
በአዲስ አበባ በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ከፍተኛ አገልግሎት ካበረከቱት የማኅበሩ አባላት ዋነኛው ቄስ ኮሊን ማንሰል ነበሩ። “6 ዓመት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት ከ6ኛ - 11ኛ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ በዐማርኛ ቋንቋ አስተምረዋል። በተለያዩ ጊዜያትም በካቴድራሉ ውስጥ በስብከት አገልግለዋል። በተለይ በወጣት ስብሰባዎች እየተገኙ በሰጡት አገልግሎት ኹሉ የታወቁና የተወደዱ መምህር ለመኾን በቅተዋል። እሑድ እሑድ ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ፍላጎቱ ለነበራቸው መነኰሳትና ዲያቆናት መጽሐፍ ቅዱስ አስተምረዋል።” (ማንሰል ፣ የቄስ ማንሰል ዐጭር ሕይወት ታሪክ)። የቤተ ክርስቲያኒቱን ትውፊትና ሥርዐት ሳይነኩና ሳይነቅፉ፥ መጽሐፍ ቅዱስን፥ የስብከት ዘዴን ያስተምሩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከአንዳንድ ተማሪዎች ኾን ተብሎ የፈተና ጥያቄ ሲቀርብላቸው አቅልለው በማየትና የማያስቈጣ መልስ በመስጠት፥ በትዕግሥት ያሳልፉት ነበር። ባለቤታቸው ሚሲስ ሄዘል ማንሰል የማኅበሩ አገልጋይ ነበሩ። ቄስ ኮሊን ማንሰል በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፥ በጎንደር፥ በጎጃም፥ በሸዋ፥ ወዘተ. እየተዛወሩ በማገልገል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ትልቅ ወዳጅነትን አትርፈዋል። ያስገኙት መንፈሳዊ ፍሬም እጅግ ከፍተኛ ነው።
በትምህርቱ ከተሳተፉ አባቶች መካከል አንዱ አባት፥ “ቄስ ኮሊን ማንሰል በማስተማሩ ሂደት አንዳንድ ክፉ ልማዶችን ለማስተው ይጠቀሙበት የነበረው ስልት የተሳካ ነበር” ይላሉ። አንድ ቀን ያደረጉትን በመጥቀስም እንዲህ አሉ፤ “አንድ ቀን በተማሪዎቹ ዘንድ የታዘቡትን ክፉ ልማድ ለማስተው በማሰብ ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ጥቊር ሰሌዳው ላይ ሦስት ባዶ ቦታዎችን ትተው ከመጀመሪያው ባዶ ቦታ አጠገብ ‘ሌባ ነው’፤ ከኹለተኛው አጠገብ ‘ሰነፍ ነው’፤ ከሦስተኛው አጠገብ ደግሞ ‘እንቅልፋም ነው’ የሚሉ ቃላትን ጻፉ። ትምህርቱ ከተጀመረ ከ15 ደቂቃዎች በላይ ካለፉ በኋላ አንድ ተማሪ መጣ። ከዚያ ቄስ ማንሰል በል ቊጥር አንድ አጠገብ በሚገኘው ባዶ ቦታ ላይ ስምህን ጻፍ አሉት። ጻፈ። ሲነበብ ‘እገሌ ሌባ ነው’ ይላል። ከዚያ እርሳቸው ‘አያችሁ አኹን እገሌ ከ15 ደቂቃዎች በላይ ሰርቋል፤ ስለዚህ የቀጠሮ ሰዓትን አለማክበር ጊዜን መስረቅ ነው’ አሉ። ቀጥሎ በመካከል አንዱን ተማሪ ከትምህርቱ ጋር በተያያዘ አንድ ቀላል ጥያቄ ጠየቁት። እርሱም መመለስ አልቻለም፤ ስለዚህ እርሱም በኹለተኛው ባዶ ቦታ ላይ ስሙን እንዲጽፍ አደረጉ። እንደ ገና ጥቂት ቈዩና አንዱ ተማሪ ያንቀላፋ ኖሮ ቀሰቀሱትና ሦስተኛው ላይ ስሙን እንዲጽፍ አደረጉ። ከዚያ በኋላ በተማሪዎቹ መካከል የሚያረፍድም ኾነ ትምህርቱንም በርትቶ የማያጠና፥ በትምህርት ላይ የሚያንቀላፋ አልበረም።”
በዚሁ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥር ራሱን ችሎ ይሠራ የነበረው ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት በየክረምት ወራት በሚያዘጋጃቸው ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርሶች፥ በተለይ በጀንዳ *ጎንደር - ደንቢያ(፥ በአምቦ፥ በአዋሽ እና በመቀሌ በተለያዩ የክረምት ወራት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት በተደረጉ ኮርሶች የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር አባሎች *ቢያንስ ሁለቱ( በመምህርነት እየተመደቡ ከሌሎቹ የሐዋርያዊ ድርጅት መምህራን ጋር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በምስክረ ብርሃን መጽሔት ቍጥር 103፣ ጥቅምት 1964 ዓ.ም. ላይ የወጣው ዜና እንዲህ የሚል ነበር፤
“የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስ (አዲስ አበባ)
“በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እርዳታና በሐዋርያዊ ድርጅት አዘጋጅነት፥ አዋሽ ወንዝ አጠገብ በምትገኘው በደብረ ፀሓይ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውስጥ ከሐምሌ ፲፭ እስከ ነሐሴ ፳፰ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም. ድረስ ለ፴ ተማሪዎች ያኽል የመንፈሳዊ ትምህርት ኮርስ ተሰጥቶአል። ተማሪዎቹ የመጡት ከቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፥ ከመቀሌ፥ ከበጌምድር፥ ከከፋና ከደብረ ማርቆስ ነበር። ለተማሪዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፥ ግእዝ ቋንቋ፥ የስብከት ዘዴና የቅዳሴ ትምህርት ተሰጥቶአቸዋል። አብዛኛውን ትምህርት የሰጡት መምህራን፥ ቄስ ማንሰል፤ ቄስ መክብብና መሪጌታ ሰይፈ ሥላሴ ነበሩ።” (ገጽ 21)።

6. በአዲስ አበባ አንዳንድ አድባራትና ገዳማት ውስጥ የነበራቸው አገልግሎት
በኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት ሲደረግ የነበረውን በመመልከት ሌሎች ጥቂት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ሚስዮናውያኑን ጠይቀው ከአብያተ ክርስቲያኑ ጋር ሠርተዋል። ከእነዚህም መካከል በወቅቱ ሕንጻው እንደ ገና የተሠራው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፣ የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት፣ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ይገኛሉ (ቤንሶን ገጽ 111)። 

ከኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት ሌላ በአዲስ አበባና በአካባቢው ከሚገኙ አድባራትና ገዳማት ጋር በመተባበርም የሰጡት አገልግሎት አለ። ከአራት ኪሎ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ሚስ ጃርቪስ የተባሉ አንዲት አገልጋይ እየተላኩ ሰበታ በሚገኘው ቤተ ደናግል ጠባባት ገዳም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የመደበኛ ትምህርት አገልግሎት ይሰጡ ነበር (ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ፣ የቄስ ማንሰል ዐጭር ሕይወት ታሪክ)። ከእርሳቸው በኋላ እርሳቸውን የተኩትና በሰበታ ያስተምሩ የነበሩት ሚስስ ሄዘል ማንሰል ናቸው (ቤንሶን ገጽ 113)። በማኅበሩ ወንዶች ብቻ ሳይኾኑ ሴቶች ሚስዮናውያትም እንደ ነበሩ ከዚህ መረዳት ይቻላል። ከሚስ ቬራ ጃርቪስ በተጨማሪ  የማኅበሩ አባልና አገልጋይ የምስክረ ብርሃን መጽሔት አዘጋጅ የነበሩት ሚስ ሪና ቴለር፥ ሚሲስ ስፔንሰር የሚባሉና ሌሎችም ሴቶች ነበሩ። እነዚህና ሌሎችም ኹሉ፥ ነቀፋ ያልነበረበት በጎና ታማኝ አገልግሎት አበርክተዋል።

7. በጎንደር የነበራቸው አገልግሎት
በጎንደር ከተማ “ሐዋርያው ጳውሎስ” በሚል ስያሜ በማኅበሩ የተቋቋመ ትልቅ የትምህርት ማእከል ነበር። በዚህ ማእከል የ፩ኛ ደረጃ ትምህርት በነጻ ይሰጥ ነበር% በተጨማሪም ቀሳውስት፥ ዲያቆናትና ወጣቶች፥ የጎንደር ጉባኤ ቤት ደቀ መዛሙርት ጭምር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ የስብከት ዘዴ ይከታተሉበት ነበር። በጎንደር የነበረውን አገልግሎት ይመሩ የነበሩና ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበራቸው፥ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወዳጅ ታላቅ ሰው ሚስተር ዳዊት እስቶክስ ነበሩ። በዘመኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠባቂ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የሚስተር ዳዊት እስቶክስን አገልግሎት በማድነቅ በጀርባው “ቀኃሥ” የሚል የተቀረጸበት የወርቅ የእጅ ሰዓት ሸልመዋቸዋል።
ምንም እንኳ የደርግን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር በማኅበር ደረጃ የነበረው አገልግሎት በ1967 ዓ.ም. ቢቋረጥም፥ ቄስ ማንሰል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በጎንደር በሐዋርያው ጳውሎስ የትምህርት ማእከል ኾነው፥ ከቀድሞው የጎንደር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ጋር በመተባበር፥ በBCMS የበጀት ድጋፍ እስከ 1972 ዓ.ም. ድረስ አገልግሎታቸውን ቀጥለው ነበር (ማንሰል 2003፣ የቄስ ማንሰል ዐጭር የሕይወት ታሪክ)። ይህም የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር በደርግ አላሠራ ባይነት ቢሮው ስለ ተዘጋ ከአገር ለመውጣት ተገደደ እንጂ፥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር የነበረው ወዳጅነትና አጋርነት በጥሩ ኹኔታ ላይ የነበረ መኾኑን ያሳያል። 
8. በመቀሌ የነበራቸው አገልግሎት
እ.ኤ.አ. በ1972 በመቀሌው ከሣቴ ብርሃን ትምህርት ቤት በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ግብዣ እንዲያስተምሩ ከተደረጉት ሦስት እንግሊዛውያን መምህራን ማለትም ከሮጀር ካውሊና ከኮሊን ማንሰል ጋር ዳዊት እስቶክስም አንዱ ነበሩ። በወቅቱ የተሰጠው ትምህርት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ዕውቅና የተሰጠው ሲኾን ፓትርያርኩ ራሳቸውም የአቀባበል ደብዳቤ በመጻፍናመሪዎቹም በጸሎታቸው መልካም ምኞታቸውን በመግለጥ ዕውቅና የተሰጠው ነበር። በጊዜው ትምህርቱን ከወሰዱት መካከል አብዛኞቹ በዕድሜ ከፍ ያሉና የተከበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ነበሩ (ቤንሶን፣ ገጽ 115)። የሊቃውንት ጉባኤ አባል የነበሩት መጋቤ ብሉይ ሠይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ስለ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዘኵሎን አድያማተ ትግራይ” በሰጡት ምስክርነት ላይ እንዲህ ብለዋል፤ “ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ፥ አብያተ ክርስቲያናት በተገቢው መንገድ መቀራረብና አንድነት እንዲኖራቸው ዓለም ዐቀፍ አመለካከት ነበራቸው። በቅዱስ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ትምህርት ቤት ለካህናትና ለወጣቶች ሰሚናር አዘጋጅተው በነበረ ጊዜ መምህራኑ ኢትዮጵያውያንና እንግሊዛውያን ነበሩ። በተለይም ከእንግሊዛውያኑ መምህራን አንዱ ዶ/ር ሮጀር ካውሊ በትምህርት ቤቱ ሥራ ለብዙ ጊዜ ረድተዋቸዋል።” (ያሬድ /ሊቀ ሊቃውንት 1993፣ ገጽ 136)።

ሚስተር ሮጀር ካውሊ ዐማርኛና ግእዝ ቋንቋ በሚገባ አጥንተው በማወቃቸው፥ በዚሁ በግእዝ ቋንቋና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ሰፊ ምርምር አድርገው ጥናታዊ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል። ከጎንደር የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጋር በግእዝ እየተነጋገሩ ስለ ሃይማኖት ምስጢር ይወያዩ ነበር ይባላል። ከላይ እንደ ተጠቀሰው እኒህ ታላቅ ሰው በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ፈቃድና ግብዣ ለጥቂት ዓመታት መቀሌ ተቀምጠው ነበር። ብፁዕነታቸው የከሣቴ ብርሃን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅን ሲያስገነቡ፥ ስለ ወደ ፊት አቅጣጫው በምክር ሲረዱአቸው ቈይተዋል። በ1964 ዓ.ም. ክረምት በሐዋርያዊ ድርጅት አዘጋጅነት በመቀሌ በተደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ዐቢይ ኮርስ፥ ሚስተር ካውሊ የኮርሱ አስተባባሪና መምህር ኾነው በማገልገል የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

9. ዐዳዲስ አማኞችን ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጨምረዋል
የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ከዐላማውና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ካደረገው ስምምነት አንጻር፥ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር የኦርቶዶክስ አማኞችን በቤተ ክርስቲያናቸው እንዲጸኑ ከማድረግ ባሻገር፥ ለሌሎች ወንጌልን በመስበክ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ አባልነት የጨመሩበት ኹኔታ አለ። በኢትዮጵያ *በተለይ በጎንደርና በጎጃም( የሚኖሩትን ቤተ እስራኤል (Jews) ወንጌልን በማስተማርና ክርስትናን እንዲቀበሉ በማድረግ ረገድ የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር አገልግሏል። ከቤተ እስራኤል የኾኑት ወገኖች ከማኅበሩ ልኡካን የክርስትናን ትምህርት ወስደው *ወንጌል ተምረው( በፈቃዳቸው በክርስቶስ ሲያምኑ፥ በአካባቢያቸው ወዳለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ይጠመቁና አባል ይኾኑ ዘንድ፥ ማኅበሩ የነፍስ አባት *መምህረ ንስሓ( እንዲይዙ፥ ትምህርተ ሃይማኖትን (ዶግማ) እንዲያጠኑና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን እንዲማሩ ኹኔታውን ያመቻችላቸው ነበር። በዚያ ጊዜ በማኅበሩ የክርስትና ትምህርት አግኝተው፥ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተጠምቀው የነበሩ በጣም ብዙ የቤተ እስራኤል ሰዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመንነት ጸንተው እምነቱንና ሥርዐቱን ለልጆቻቸው ያስተላለፉት ብዙ ናቸው።
10. የትምህርት ዕድል በመስጠት ያበረከቱት አስተዋፅኦ
የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ በሰጠው አገልግሎት ብዙዎች ተጠቃሚ ኾነዋል። ከእነዚህም በቴኦሎጂ ትምህርት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፥ በስብከት ዘዴ ሥልጠና፥ ወዘተ. በውጭ አገርና በአገር ውስጥ ከፍተኛ የነጻ ትምህርት ዕድል የተሳተፉት ይገኙባቸዋል። በዚህ ከተሳተፉት የታወቁትን ለመጥቀስ ያህል፦
10.1.            በውጭ አገር የነጻ ትምህርት ዕድል (Scholarship) በቴኦሎጂ ያገኙ፡-
·        መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፡- በሐዋርያዊ ድርጅት፣ እንዲሁም በጠቅላይ ቤተ ክህነት በመምሪያ ኀላፊነት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ፣ አኹን የሊቃውንት ጉባኤ አባል። - ወደ እንግሊዝ አገር ተልከው ለ2 ዓመታት ተምረዋል።
·        መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ፦ በሐዋርያዊ ድርጅት ለረጅም ዓመታት፣ ከዚያም በጠቅላይ ቤተ ክህነት በመምሪያ ኀላፊነት ያገለገሉ፣ በኋላም የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ *ሊቀ መንበር( የነበሩና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ። -  ወደ እንግሊዝ አገር ተልከው ለሦስት ዓመት ተምረዋል።
·        ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ፡- በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሰባኬ ወንጌል የነበሩ፥ ወደ ኬንያ ተልከው ለኹለት ዓመት ከተማሩ በኋላ እዚያው በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ ቈይተው፥ ወደ እንግሊዝ አገር ሄዱ% እዚያም አገልግሎታቸውን ቀጥለው ሳሉ$ ወደ አሜሪካ ተሻገሩ። አኹንም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናንን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
·        ቀሲስ ተስፋዬ ረጋሣ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የውስጥ ኦዲት አገልግሎት ኀላፊ፥ በሕንድ አገር ቢብሊካል ቴኦሎጂ ኮሌጅ (Biblical Theology College) የሦስት ዓመት የነጻ ትምህርት ዕድል ተሰጥቶአቸው፥ ለመሄድ የዝግጅት ሂደቱን ካጠናቀቁ በኋላ በሕንድ ኤምባሲ በኩል ቪዛ የማዘግየት ችግር ምክንያት እንዲሄዱ የታቀደበት ዓመት የትምህርት መጀመሪያ ጊዜ ሊያልፍባቸው ችሏል። በቀጣዩ ዓመት እንዲሄዱ ቢፈቀድም፥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመቀጠላቸው ይህን ዕድል ሊጠቀሙበት ሳይችሉ ቀርተዋል።

እነዚህ ሁሉ ከማኅበሩ የውጭ ትምህርት ዕድል ሲሰጣቸው፥ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዐውቆና ፈቅዶ፥ ድጋፍ በመስጠት የመውጫ ቪዛ ጠይቆላቸው የተፈጸመ ነው።
10.2. በአገር ውስጥ ከማኅበሩ አባል መምህራን ትምህርት የተሳተፉ፡-
( በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፦
·    አባ ዘሊባኖስ ፈንታ *አኹን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ኛው ፓትርያርክ( በአሜሪካ አገር ያሉ%
·  አባ ተክለ ማርያም ዐሥራት *አኹን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፥ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ(%
·    አባ ገብረ እግዚአብሔር በየነ *አኹን ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፥ በስዊድን አገር የሚኖሩ(%
·    አባ ተክለ ድንግል ደሴ *በኋላ ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ፥ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ(%
·    አባ ወልደ ገብርኤል *አኹን ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ፥ በካሪቢያን ደሴቶች የጃማይካ፥ የትሪኒዳድና የቶቤጐ ሊቀ ጳጳስ(%
·    መልአከ ምክር ቀሲስ ከፍያለው መራሒ፥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የትምህርተ አበ ነፍስ ክፍል ኀላፊ የነበሩ፥ አኹን ቤተ ክርስቲያኒቱን በመወከል በተለያዩ ድርጅቶች ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የቦርድ ወይም የኮሚቴ አባል ኾነው ያገለግላሉ።
·    ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ ኢሳይያስ ወንድማገኘሁ፥ በሐዋርያዊ ድርጅት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ፥ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እስከ ምክትል የመምሪያ ኀላፊነት ድረስ ያገለገሉ፥ አኹን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰባኬ ወንጌል%
·    ቀሲስ በላይ ተገኝ *ቴኦሎጂያን(፥ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በተለያዩ መምሪያዎች በኀላፊነት ያገለገሉ፥ አኹን የሊቃውንት ጉባኤ አባል%
·    አቶ ለይኩን ብርሃኑ *ቴኦሎጂያን(፥ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በተለያዩ መምሪያዎች በኀላፊነት ያገለገሉ፥ አኹን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ባልደረባ%
·    ቀሲስ ኢሳይያስ ለየህ *ቴኦሎጂያን(፥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትና ቤተ ሰብ ድርጅት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ፥ አኹን ሰባኬ ወንጌል%
·    ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር መኰንን ንዋይ *ዴንቲስትና የፕላስቲክ ሰርጀሪ እስፔሻሊስት(፥ የሚክያስ ከፍተኛ የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ባለቤትና ሥራ መሪ%
·    አቶ ተፈራ በየነ *ሲቪል ኢንጂነር(፥ አኹን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመምሪያ ኀላፊነት ደረጃ የሚኒስትሩ አማካሪ%

( በጎንደር ሐዋርያው ጳውሎስ የትምህርት ማዕከል፡-
·      አባ ጎሐ ጽባሕ *አኹን ብፁዕ አቡነ እንድሪያስ(፥ በወቅቱ የጎንደር ጉባኤ ቤት ደቀ መዝሙር የነበሩ፥ አኹን የደቡብ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ%
·      ሌሎችም በዚያን ጊዜ በጉባኤ ቤቱ የነበሩ የሊቀ ሊቃውንት *የኔታ( መንክር መኰንን ደቀ መዛሙርት%
እነዚህን የታወቁትን ጥቂቶቹን ጠቀስን እንጂ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች በመምህራኑ ይሰጥ የነበረውን መንፈሳዊ ትምህርት ተሳትፈዋል።
የእነ ዳዊት እስቶክስ የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ዐላማ ኦርቶዶክስን ፕሮቴስታንት ማድረግ ቢኾን ኖሮ፥ መጀመሪያውኑ በቤተ ክርስቲያኗ ዕውቅና አግኝተው ይህን ኹሉ ተግባር ባላከናወኑ ነበር። ለእነርሱ የአገልግሎት በር በመክፈት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ዐብረው እንዲሠሩ ያደረጉት፥ በትምህርቶቻቸውም የተሳተፉትና ከላይ ስማቸው የተዘረዘረው ታላላቅ አባቶች እስከ ፓትርያርክነት ድረስ በተለያየ ኀላፊነት ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚመሩና የሚያገለግሉ ነው የኾኑት እንጂ ፕሮቴስታንት አልኾኑም። በዚያ ዘመን የነበረችው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደነ ዳዊት እስቶክስ ያሉ የውጭ አገር መምህራንን አገልግሎት ተመልክታና ደጋፊዎቿ እንጂ ለሌላ ዐላማ ያልተሰለፉ መኾናቸውን ተረድታ ለአገልግሎታቸው ዕውቅና በመስጠት ለውጥ እንዲመጣ ተንቀሳቅሳለች፤ ትልቅ ውጤትም ተመዝግቧል። ይህ ኹሉ ሲኾን ግን አገልግሎታቸውን የሚቃወሙ አንዳንዶች አልነበሩም፤ ዛሬም የሉም ማለት ግን አይደለም። 
ለዚህ ታሪክ ሌላ መልክ ሰጥቶ የእነ ዳዊት እስቶክስንና የማኅበራቸውን ድካምና ውለታ ገደል መጨመር፥ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት በደል ነው። በታሪክም ያስወቅሣል። ስለዚህ “መድሎተ ጽድቅ” ያለ አንዳች ማስረጃ ለዚያ መልካምና በጎ ግንኙነት ሌላ ገጽታ ሊያላብሰው ቢሞክርም እውነታው ግን ከላይ የተገለጠው ነው። ምንም ይባል ምን ይህን ታሪክ መፋቅ አይቻልም።
ዐፄ ኀይለ ሥላሴ መንግሥት በደርግ መንግሥት እስኪተካና ደርግ አላሠራ ብሏቸው በሩን እስኪዘጋባቸው ድረስ ለ40 ዓመታት ያኽል የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበርና አባላቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በማገዝ አገልግለዋል (ቤንሶን፣ ገጽ 138)። ስለ እነርሱና ስለ አገልግሎታቸው፥ ለቤተ ክርስቲያኒቱም ስላደረጉት ድጋፍ ከፍ ያለ አክብሮት አለን! ክብር ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ይኹን።
ወደ ሌላው የተሐድሶ ስልት ተብሎ ወደጠቀሰው ነጥብ ስናልፍ እንዲህ ይላል፤
“3) ሦስተኛው ስልታቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት አስተምህሮ ላይ ያቀረቡትን ነቀፋና ማሳጣት እውነት ለማስመሰል ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ትምህርቶች መካከል ለሐሳባቸው ድጋፍ ይኾኑናል ያሏቸውን የተወሰኑ ነገሮችን ለመጠቃቀስ መሞከር ነው።” (ያረጋል/ዲ/ን 2007፣ 14)
ጸሐፊው ራሱን ትክክለኛ ሌላውን ስሕተተኛ ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱና ዋነኛው፥ ትክክለኛ መርሖችን መጥቀስ፥ በተግባር ግን እነዚያን መርሖች አለ መጠበቅ ነው። ታማኝ የሚያደርገው ግን ትክክለኛ መርሖችን መጥቀስ ሳይኾን፥ በመርሖቹ መሠረት መመራት ነው። በመጽሐፉ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው አንድን መርሕ መጥቀስ፥ ነገር ግን በመርሑ አለመመራት ነው ስንል እንዲሁ ዝም ብለን አይደለም። ለዚህ አንዱ ማሳያ ከየጽሑፎቻችን የተወሰዱ ጥቅሶች የተብራሩበት መንገድ ነው። ጥቅሶቹ ጸሓፊው ለሚያነሣው ሐሳብ ድጋፍ ይኾኑኛል ብሎ በሚፈልገው መንገድ ቀነጫጭቦና ትርጉማቸውን አዛብቶ የጠቀሳቸው ናቸው። በዐውዳቸው ውስጥ ኾነው ሲነበቡ ግን እርሱ እንደ ጠቀሳቸው እንዳልኾኑ ያነበባቸው ሰው ያስተውላል። ስለ ኾነም በዚህ ስልት የሠለጠነው ማን እንደ ኾነ አንባቢው እንዲፈርድ በቀጣዩ ጽሑፍ በምዕራፍ አንድ በ1.1 ላይ “የተሐድሶዎች መነሻዎችና መሠረቶች” በሚለው ርእስ ሥር ላቀረበው ጽሑፍ በምንሰጠው ምላሽ ውስጥ እናመለክታለን።
ይቀጥላል


ዋቢ ጽሑፎች
ማንሰል፣ ኮ. (2003) ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ። ዐዲስ አበባ፣ ንግድ ማተሚያ ድርጅት።
ምስክረ ብርሃን (1964) ጥቅምት። 
                 (1964) ነሐሴ።
ያሬድ ካሳ (ሊቀ ሊቃውንት) (1993) ሕያው ስም። (ማተሚያ ቤቱና ቦታው ያልተጠቀሰ)።
ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ (ነጋድራስ) (2002) ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ሥራዎች። ዐዲስ አበባ፣ አአዩ ማተሚያ ቤት።
ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን (1993) ጥቅምት፡፡
ጮራ (2002) ሐምሌ።

Benson, Doris. The Most Valuable Thing: The Word at work in Ethiopia. n.d.

3 comments:

  1. ምንም ማስተባበያ ብታቀርቡ ማንንም ማታለል አትችሉም እወነታውን አጋለጦችዋል

    ReplyDelete
  2. እስከዛሬ ይህን ታሪክ ሰምተን አናውቅም፣ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ወደኋላ እየሄደች ነው፣ ለዚህ ደግሞ ከሚጠየቁት አካላት መካከል ማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ይሆናል፡፡

    ReplyDelete
    Replies
    1. Are you orthodox Christian? whom do you think you are try to blame mahiber kidusan which is body of our church. whether you believe or not they are the one who protect the church from heretical teaching. the church demand apologists mahibere kidusan is the pioneer among many.

      Delete