Monday, September 7, 2015

ብዙ ተስፋ


ተስፋ የሚለው ቃል ሲጠራ በራሱ ተስፋ ይለመልማል። ልብ በሐሤት ይሞላል። የሰው እግር በድል የሚራመደው ልቡ በተስፋ ሲሞላ ነው። ተስፋ ከሌለ እግር ሽባ ይሆናል። ተስፋ ግን ሽባውን እግር የሚያረታ፥ ከተጠበቀው በላይ የሚያራምድ ነው። ተስፋ ያጣ ሰው ምንም ሳይሆን ብዙ የሆነ ይመስለዋል። ገና ቀን ሳለ ሌሊት መስሎት ይተክዛል። ትጥቁና ስንቁ እያለ ጦርነቱን በሽንፈት /በበቃኝ/ ይደመድማል። ተስፋ መዳረሻ ነው። ከምሳ ሰዓት በኋላ እስከ እራት ያለው ጊዜ ረጅም ነው። ሠርክ ላይ ትንሽ ምግብ ይቀመሳል። ያ መክሰስ ወይም መዳረሻ ነው። ተስፋም እንዲሁ ነው። እግዚአብሔር ያሰበልን ነገር ላይ ለመድረስ መዳረሻ /መቈያ/ ነው።

ተስፋ በመጀመሪያ በፅንሰቱ ኋላም በልደቱ ደስ ያሰኛል። ተስፋ ያደረጉት ነገር ሲፈጸም ልብ ሙሉ ይሆናል፤ መኖርም ምክንያታዊ ይመስላል። እግዚአብሔር የተስፋ አምላክ፥ የተስፋ መሠረት፥ የተስፋ ፍጻሜ ነው። እግዚአብሔር ተስፋን የሚሰጠው ከራሱ የፍቅርና የቸርነት ባሕርይ በመነሣት ነው። ይህ ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል።
1.    ተስፋን የሰጠን በራሱ ፈቃድ ስለ ሆነ ለመፈጸም አይቸገርም።
2.   የተስፋ መነሻ ፍቅር ነው፤ ፍቅር ሲኖረን ቸሮች ብቻ ሳይሆን ባለተስፋም እንሆናለን።

ተስፋን በሚመለከት የሰው ልጅ አመለካከት ከዚህ ተቃራኒ ይመስላል። ይኸውም፡- ሰው ተስፋ የሚሰጠው በስሜት፥ በጉባኤ ሞቅታ ሊሆን ይችላል፤ ሲረጋጋና አጢኖ ሲያስበው ይቆማል። እግዚአብሔር ግን በመጥራቱና በመስጠቱ የማይጸጸት አምላክ ነው። የሰው ልጅ ብዙ ጊዜ ከጥላቻና ከመሰልቸት ጋር ስለሚሆን ተስፋ ማድረግና ተስፋ መስጠት ያቅተዋል። እግዚአብሔር ግን ሳይለወጥና ሳይናወጥ ፍቅር ሆኖ ይኖራል። የእግዚአብሔር ተስፋ ጨቅጫቃ ልጆችን ማባረሪያ አይደለም፤ የፍቅሩ መግለጫ ነው።

የእግዚአብሔር ቃል ትንቢትን፥ ተግሣጽን ብቻ ሳይሆን ተስፋንም የተሞላ ነው። ተስፋ የቃሉ አካል ነው። ተስፋ ክርስቲያኖች የሚራመዱበት ኀይል ነው። የእስትንፋስን ያህል ሊቋረጥ የማይገባው የመጀመሪያው ነገር ቢኖር ተስፋ ነው። ተስፋ ከሌለ ማቀድ፥ ማገልገል፥ … ሊኖር አይችልም፤ ወደ ትልቅ ፈተና ውስጥ የምንገባው ተስፋችን የተነቃነቀ ቀን ነው።

ስለ ተስፋ ይህን ያህል ያልነው ከትንቢተ ሐጌ ምዕራፍ 1፥9 ላይ፥ “እናንተ ብዙ ነገርን ተስፋ አደረጋችሁ፥ እነሆም፥ ጥቂት ሆነ፤” የሚለውን ቃል ለማንሣት ነው፤ ሰዎች ተስፋ ይሰጡናል። የሰዎች ተስፋ ግን ርግጠኛነት የሌለው፥ ሊሆንም ላይሆንም የሚችል እንጥልጥል በረከት ነው። እንዲህ መሆኑንም በጥርጣሬ እንጂ በልበ ሙሉነት አንይዘውም። የእግዚአብሔር ተስፋ ግን ርግጥና ጽኑ ነው። እግዚአብሔር ተስፋ ከሰጠን የሆነ ያህል ነው፤ ርግጠኛም ነው። በራሳችንም ብዙ ተስፋ እናደርጋለን። ከፖለቲካው ዙረት፥ ከአባቶች ጉባኤ፥ ከክርስቲያኖች አንድነት፥ ከአገልጋዮች መቀራረብ፥ ከትዳር ጓደኛችን፥ ከልጆቻችን፥ ከጀመርነው ዕቅድ፥ … የምንጠብቀው ነገር አለ። እግዚአብሔር ግን ለእነዚያ ከምርኮ ተመላሾች፥ “እናንተ ብዙ ነገርን ተስፋ አደረጋችሁ፤ እነሆም ጥቂት ሆነ” አላቸው (ሐጌ 1፥9)።

ብዙ ተስፋ አድርጎ ጥቂት እንኳ አለማግኘት የጨነገፈ ምኞት ነው። እግዚአብሔር ለምን እንዲህ አለ? በቃሉ ውስጥ “በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን?” ተብሎ ተጽፏል (ሐጌ 1፥)። የተሸለሙ ቤቶች መሥራት፥ ስለ ተሻለ ኑሮ ማሰብ፥ እግዚአብሔርን አያስከፋውም። ነገር ግን ሁሉም ነገር ውብ የሚሆነው በጊዜው ነው። ጊዜው የእግዚአብሔር ቤት የፈረሰበት፥ ቅጥሩ የወደቀበት፥ መሥዋዕት የማይቀርብበት፥ ንጹሕ አምልኮ የሌለበት ነበር። በዚህ ጊዜ በተሸለሙ ቤቶች ውስጥ መኖር፥ ስለ ጌጠኛ ዕቃዎች ማሰብ ተገቢ አይደለም። በዚህ ሁኔታ ብዙ ተስፋ ማድረግ፥ ምርቱን ዕፍኝ የማይሞላ ያደርገዋል።

በየአብያተ ክርስቲያናቱ ያለው የልማት ዕቅድ ድንቅ ነው። ስለ ትልልቅ ተቋማት ማሰብ፥ ጫና በሚያሳድር የተፈሪነት ቦታ መቀመጥ፥ የክርስቲያን መሪዎች ጥማት እየሆነ መጥቷል። ክርስቲያኖችም እኛ ቦታውን ብንይዘው ምድሪቱ ትባረካለች በማለት ሥጋዊ ዝግጅታቸውን እያጧጧፉት ነው። የእግዚአብሔር ቤት ግን ፈርሷል። ንጹሕ አምልኮት፥ እግዚአብሔርን የሚያከብር መሥዋዕት ጠፍቷል። ሕዝቡ ቅር እንዳይለው የልማዱ ዝማሬና ቅዳሴ ይቀርብለታል እንጂ በንስሓና በይቅርታ መቅረብ አልቻልንም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙ ተስፋዎችና ዕቅዶች በዝተዋል። እግዚአብሔር ከሌለበት ዕቅድ ሁሉ ከንቱ መሆኑን ግን አላስተዋልንም። የቤተ ክርስቲያን ግርማዋ ቅድስና እንጂ ሥጋዊ ሥልጣን አይደለም። የሚያስፈልገንም ምድራዊ በረከት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ይሁንታ ነው። - “ብዙ ተስፋ”

በጮራ መጽሔት ቍጥር 44 ላይ የቀረበ

1 comment: