Sunday, June 25, 2017

የሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበርን የአገልግሎት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ተመረቀ

ከሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ሚስዮናውያት አንዷ በነበሩት ዶሪስ ቤንሰን፣ “The Most Valuable Thing: The Word at Work in Ethiopia” ተብሎ በእንግሊዝኛ የተጻፈውና ወደ ዐማርኛ “ከሁሉ የበለጠ ዋጋ ያለው:- የእግዚአብሔር ቃል በሥራ ላይ በኢትዮጵያ” ተብሎ የተተረጐመው መጽሐፍ በርካታ የአገልግሎቱ የቀድሞ አባላትና ተሳታፊዎች በተገኙበት ሠኔ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት አዳራሽ ተመረቀ።

            በጸሎተ ወንጌል የተከፈተው የምረቃው ሥነ ሥርዐት ዝማሬዎችም የቀረቡበት ሲሆን፣ ቃለ ወንጌልም ተሰብኮበታል። የማኅበሩን አገልግሎት በተለይ ከመጽሐፉ ደራሲት ጋር በተገናኘ ቅኝት ያደረገ ጽሑፍም የመርሐ ግብሩ አካል የነበረ ሲሆን፣ በመጽሐፉ ላይ የተዘጋጀ ዳሰሳዊ ጽሑፍም ቀርቧል። በመጽሐፉ ላይ የታተመው ቀዳሚ ቃልም በንባብ ተሰምቷል። ቀዳሚ ቃሉ አንድ ታሪክ ሳይዛባና እውነተኛነቱ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በተለይ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባትና በሚታወቀው ታሪክ ላይ ሌሎች ሲዋሹ እውነተኛ ምስክር ሆና አለመቅረብ ትልቅ ትዝብት ላይ እንደሚጥላት አስረድቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ታሪክ ላይ የተፈጸመውን ታሪክን አዛብቶ የማቅረብ ክፉ ሥራ ይህ ከእንግሊዝኛ ወደ ዐማርኛ የተመለሰውና ለምረቃ የበቃው መጽሐፍ እንደሚያስተካክለው ተስፋ አድርጓል። አክሎም መጽሐፉን ማስተርጐምና ማሳተም ያስፈለገበትን ምክንያቶች ሲያብራራ፥

“የመጀመሪያው ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ባለውለታ የሆነው የሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር በዘመኑ የሠራው ሥራ አሁን ባለው ትውልድ እንዲታሰብና ቤተ ክርስቲያን ትናንት እንዴት እንደ ነበረችና ዛሬ ደግሞ በምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አንባቢው እንዲያስተውል ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ላይ በሐሰት እየተነገሩ ያሉ የተዛቡ ትረካዎችንና የፈጠራ ታሪኮችን እየሰማ ያለው ትውልድ፣ በስማ በለው እየቀረበለት ያለው የፈጠራ ታሪክ እውነት መስሎት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሄድ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት፣ እውነቱን ከሐሰት እንዲለይ ለማድረግ ይህ መጽሐፍ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ ስለ ታመነበት ነው። ሦስተኛው ምክንያትም፣ የተሐድሶ አገልግሎት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደ ነበረና ይካሄድ የነበረው እንዴት ባለ ሁኔታና መንገድ እንደ ሆነ፣ በተለይ በተሐድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉት ሁሉ እንዲበረታቱበት፣ እንዲማሩበትና የአገልግሎት አቅጣጫቸውን እንዲፈትሹበት ዕድል ለመፍጠር ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ፀረ ወንጌል ቡድኖችም ሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሰጠው አገልግሎት እነርሱ እንደሚሉት ሌላ ዐላማ ያልነበረውና በቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅናና ተቀባይነት ያገኘ እንደ ነበር በማሳየት የተሳሳተ ዐቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት ነው፡፡” ብሏል፡፡ በእርግጥም መጽሐፉን ስለ ሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር እስካሁን በተዛባ መንገድ ሲቀርብ የነበረውን ትረካ ለማቃናትና ትክክለኛውን ታሪክ ለማቅረብ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ከቀዳሚ ቃሉ በተጨማሪ ከመጽሐፉ የተመረጡ አናቅጽ የተነበቡ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
በ1972 የክረምቱ የትምህርት መርሐ ግብር ለስድስት ሳምንታት በመቀሌ ከሣቴ ብርሃን ትምህርት ቤት ተካሄደ፡፡ ዴቪድ ስቶክስ ለጥቂት ወራት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ነበርና ከኮሊንና ከሮጀር እንዲሁም ከሦስት ኢትዮጵያውያን መምህራን ጋር በመርሐ ግብሩ አስተማሩ፡፡ ይህ የትምህርት መርሐ ግብር በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ዕውቅና ተሰጠው፡፡ ፓትርያርኩ ራሳቸው መስማማታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፉ፤ የሚጸልዩ መሆናቸውንም ለመሪዎቹ አረጋገጡላቸው፡፡ ከተማሪዎቹ ብዙዎቹ በዕድሜ የገፉ፣ የተከበሩ የቤተ ክርስቲያን ምሁራን ነበሩ፤ ነገሩም ቀላል አልነበረም፤ በመጨረሻው ግን ብዙ አድናቆት ተቸረው፡፡” (ገጽ 153)።
እንዲሁም “በ1967 ወደ ኢትዮጵያ በተመለስሁ ጊዜ ከአዕማድ መጻሕፍት ሌላውን ለመሥራት ተስፋ አደረግሁ፡፡ ነገር ግን ወዳጃችን ሊቀ ሥልጣናት ዐዲስ ጥያቄ ነበራቸው፡፡ በእሑድ ትምህርት ቤቶችና በትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ እንዲሁም በተጨማሪ በቤቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መጻሕፍት አስፈላጊነት አንገብጋቢ ነበር፡፡ በዐሥራ ዘጠኝኛው ምእ ዓመት በማርቲን ፍላድ የተተረጐመውን በባርት የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በዐማርኛ አንድ ቅጂ በማግኘታቸው ሊቀ ሥልጣናት ተደንቀው ነበር፡፡ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ያለውን ዋናውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የሚያቀርቡ መጻሕፍትን ዐትመው ለማውጣት የሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ይረዳቸዋልን? መጻሕፍቱ ሥዕላዊ ማብራሪያ ይኖራቸዋል፤ በሁለቱ ቀለማትም ይታተማሉ፡፡ እያንዳንዱ መጽሐፍ በዓመቱ ላለ ለእያንዳንዱ ሳምንት አንድ ታሪክ ሆኖ ዐምሳ ሁለት ታሪኮች ይኖሩታል፡፡ ከዐዲስ ኪዳን የሚሰጠው ትምህርት ከጌታ ልደት እስከ ጰንጠቆስጤ ያለውን ጊዜ ይሸፍን ዘንድ፣ እያንዳንዱ መጽሐፍ የብሉይ ኪዳንና የዐዲስ ኪዳን እኩል ቊጥር ይኖረዋል፡፡ እኔ ይህን ሥራ እንድጀምር ተወሰነ፡፡
“የእነዚህን መጻሕፍት ይዘት ማቀድ መሳጭ ተግባር ነበር፤ ሦስት መጻሕፍት ለመጻፍና ለማሳተምም ስድስት ዓመት ገደማ ወሰደ፡፡ በሰፕተምበር በሚጀምረው የኢትዮጵያ ዐዲስ ዓመት የብሉይ ኪዳን ሦስት ወራትን ተከትሎ የዐዲስ ኪዳን ስድስት ወራት፣ በመጨረሻ የብሉይ ኪዳን ተጨማሪ ሦስት ወራት መኖር ነበረባቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት መጻሕፍት ይህን ዕቅድ ተከተሉ፤ ሦስተኛው መጽሐፍ ግን በ“ዮሐንስ ራእይ” ዮሐንስ ስላየው ራእይ ከሚገልጽ መደምደሚያ ጋር ግማሽ ብሉይ ኪዳንንና ግማሽ ዐዲስ ኪዳንን የያዘ ነበር፡፡

        “ርእሱ የተመረጠው በቀላሉ አልነበረም፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ታሪኮቹ እውነት አይደሉም ማለት ነው ብለው በማሰብ “ታሪክ” የሚለውን የዐማርኛ ቃል አሳስተው ይረዱት ነበር፡፡ በመጨረሻ ከአንድ እስከ ሦስት ቊጥር የተሰጣቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ መጻሕፍት እንዲባሉ ወሰንን፡፡” (ገጽ156፡157)
“ከሁሉ የበለጠ ዋጋ ያለው:- የእግዚአብሔር ቃል በሥራ ላይ በኢትዮጵያ” ተብሎ ለተተረጐመው ለዚህ መጽሐፍ መተርጐምና መታተም መነሻ ምክንያት የሆነው “መድሎተ ጽድቅ” በተባለው መጽሐፍ ላይ ስለ ሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር የቀረበው የተዛባ ታሪክ ሲሆን፣ ያን ተከትሎ በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር ፵፯ ላይ በዘመን ምስክር ዐምድ በተሰጠው ምላሽ አሁን ተተርጕሞ የታተመውና የተመረቀው መጽሐፍ ምንጭ ሆኖ መጠቀሱና ያን ተከትሎ ታሪኩ በሙሉ ቢቀርብ የሚኖረው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑ ስለ ታመነበት እንደ ሆነም ታውቋል። መጽሐፉን ያስተረጐመው “የወንጌል አገልግሎት ማኅበራት ኅብረት” ሲሆን መጽሐፉ በቅርቡ በየመጻሕፍት መደብሩ እንደሚሠራጭም ይጠበቃል።        


2 comments:

  1. የት እናግኘው?

    ሕሊና

    ReplyDelete
  2. መጽሐፉ በየመጻሕፍት መደብሩ ለምሳሌ ራእይ መጻሕፍት መደብር፣ ኢማና መጻሕፍት መደብር ...ይገኛል

    ReplyDelete