Tuesday, January 1, 2019

ርእሰ አንቀጽ



ወሰላም በምድር - በምድር ሰላም

በኢየሩሳሌም የነገሠው የነቢዩ የዳዊት ልጅ ጠቢቡ ሰሎምን በመጽሐፈ መክብብ ውስጥ ለኹሉም ነገር ጊዜ እንዳለው በርካታ ክሥተቶችን በመጥቀስ ይናገራል። ለመወለድ፣ ለመትከል የተተከለውን ለመንቀል፣ ለመግደል ለመፈወስ፣ ለማፍረስ ለመሥራት፣ ለማልቀስ ለመሣቅ፣ ዋይ ለማለት ለመዝፈን፣ ድንጋይን ለመጣል ድንጋይን ለመሰብሰብ፣ ለመተቃቀፍ ከመተቃቀፍ ለመራቅ፣ ለመፈለግ ለማጥፋት፣ ለመጠበቅ ለመጣል፣ ለመቅደድ ለመስፋት፣ ዝም ለማለት ለመናገር፣ ለመውደድ ለመጥላት፣ ለጦርነት ለሰላም ጊዜ አለው በማለት ጠቢቡ ጊዜ በምሕዋሩ ውስጥ ልዩ ልዩ የሚቃረኑ ነገሮችን እንደሚያመላልስ ያስረዳል። በዚህ ሂደት ውስጥ የኹኔታዎች መለዋወጥ በጊዜ ቀመር የታቀበ ነው። ከዚህ ልውውጥ በስተ ጀርባም ነገሮችን የሚቈጣጠረው መጋቤ ኵሉ ወመሴስየ ኵሉ (ኹሉን የሚመግብና ደስ የሚያሰኝ)፣ ጊዜያትን የሚያመላልስና የሚያለዋውጥ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ ክብር ለእርሱ ይሁን!

ለኹሉ ጊዜ አለው እንደ ተባለው፣ በለውጥ ኺደት ላይ የምትገኘው አገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ያልተጠበቁና ያልታሰቡ ለውጦች ጊዜያቸውን ጠብቀው እየተከሠቱባት ትገኛለች። ስለዚህ ወቅቱ አገራችን ለውጡን ተከትሎ በተከሠቱ ኹኔታዎች ለለውጥ ተስፋ የተሰነቀችበት ብቻ ሳይኾን በለውጡ ሂደት ሰላሟ የደፈረሰበትም ጊዜ ነው። እየመጣ ያለውን ለውጥ ተከትሎ በብዙ ቦታዎች የሰላም መደፍረስና ሥጋት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ በተወለዱበት፣ ባደጉበትና ንብረት ባፈሩበት ስፍራ አገሬ ብሎ የመኖር ዋስትና ማጣት፣ በሕግ ሳይኾን በመንጋ ኢፍትሓዊ ፍትሕ የሚሰጥበትና በርካታ አሳዛኝና አስከፊ ኹኔታዎች እየታዩ ነው። ከዚህ ቀደም የኾነውን ኹሉ ወደ ቦታው መመለስ አይቻልም፤ ወደ ፊት የባሰ ችግር እንዳይከሠትና እየታየ ያለው የተስፋ ጭላንጭል እንዳይጨልም ለመሥራት ግን ዕድሉ አለ።

ከዚህ አንጻር አኹን የምንገኝበት ጊዜ የቂምና የበቀል ሳይኾን፣ የምሕረትና የይቅርታ ጊዜ መኾን አለበት። የመጠላላትና የመራራቅ ሳይኾን፣ የመፈቃቀርና የመቀራረብ ጊዜ መኾን አለበት። የመበደልና የመጣላት ሳይኾን፣ የመካስና የመታረቅ ጊዜ መኾን አለበት። የመለያየትና የመከፋፈል ሳይኾን፣ የአንድነትና የመተባበር ጊዜ መኾን አለበት። ስለዚህ በእግዚአብሔር አርኣያና አምሳል የተፈጠርን ኹላችንም በሰብኣዊ ተፈጥሮአችን እኩል ነንና የምንገኝበት ይህ ጊዜ በሚጠይቀው መልካምና በጎ ሕይወት ለመገለጥ የየድርሻችንን መወጣት አለብን።

በዚህ ወሳኝ ጊዜ አገራችን የሚያለያዩ ሳይኾን አንድ የሚያደርጉ፣ የሚያጣሉ ሳይኾን የሚያስታርቁ፣ የሚያራርቁ ሳይኾኑ የሚያቀራርቡ ሰዎች ያስፈልጓታል። በልዩ ልዩ መንገድ ሕዝብ የሚከታተላቸውና ሕዝቡን እየመሩ ያሉ ልዩ ልዩ ሚዲያዎችም ተሰሚነታቸውን ለክፉ ሳይኾን ለበጎ፣ ለማለያየት ሳይኾን ለማስማማት፣ ለማጋጨት ሳይኾን ችግሮችን ለመፍታት፣ ለጊዜያዊና ከራስ ለማያልፍ ጥቅማ ጥቅም ሳይኾን ዘላቂ ለኾነና ለትውልድ ለሚተርፍ፣ አገርንም እንደ አገር ለማቈየት ለሚረዳ ዐላማ በማዋል ተገቢ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።

ሰላም በቅዱሳት መጻሕፍት ይትበሃል ሲገለጽ፦ ኹለንተናዊ ደኅንነትን፣ ዕረፍትን፣ ስምምነትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ኅብረትን፣ ዕርቅና ብልጽግናን፣ ውጫዊና ውስጣዊ ደኅንነትን ኹሉ ያጠቃልላል። ሰላም እንዲመጣ ሰላምን በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ በቅድሚያ ሀልዎተ እግዚአብሔር መታወቅና መታመን አለበት። ሰዎችም በእግዚአብሔር ዙሪያ መሰብሰብና መነጋገር አለባቸው። ፈሪሀ እግዚአብሔር በሌለበት ስለ ሰላም ማውራት ከመንጫጫት ያልተለየ ወሬ ብቻ ይኾናል። የሰላም ሰው ትልቁ ሥራው በሰው ልጆች መካከል ደም እንዳይፈስ መከለከል ነው። አቢግያ ዳዊትን ወደ ደም አትግባ አንተ የእግዚአብሔርን ጦርነት የምትዋጋ ነህና ስትለው፣ ለሰላም ከሰጠችው ዋጋ የተነሣ “ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ።” በማለት ለሰላም ጥሪዋ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል (1ሳሙ. 25፥32-33)። ጊዜው ስለ ሰላም የሚናገር ብቻ ሳይኾን ሰላምን ለመቀበል የተዘጋጀ ሰውም የሚፈለግበት ጊዜ ነው።

እንዲህ ሲባል በምድራችን ለሚስተዋለው ችግርና የሰላም ዕጦት ፍጹም የኾነው መፍትሔ የሚገኘው ከምድር ነው ማለት አይደለም፤ እውነተኛ ሰላም ከሚሰጥ የሰላም አለቃ ከኾነው ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው እንጂ። እርሱ መድኀኒታችን የሚሰጠን ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው ዐይነት አይደለም (ዮሐ. 14፥27)። ምድራችን ግን ይህን የሰላም አለቃ ብዙ ጊዜ ገፍታዋለች። ለሰላሟ የሚኾነውን ሳታውቅ ከዐይኖቿም ተሰውሮባት ኖራለች (ሉቃ. 19፥42)።

የሚገርመው ከዓለምም ዐልፎ የሰላም መልእክተኞች በተባሉት አብያተ ክርስቲያናት (ምእመናን) ዘንድ እንኳ ሰላም ደፍርሶ፣ ፍትሕ ተዛብቶና ዕርቅ ተገፍትሮ ይታያል። ቤተ ክርስቲያን የማያሠልስ ተግባሯ ወንጌልን ማብሠር፣ መታወቂያዋም በፍቅር መመላለስ መሆን ሲገባው፣ ከዚህ በተቃራኒው የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ፣ አለመታዘዝ፣ ጥላቻ፣ ዐመፅ፣ ዝርፊያ፣ ርኵሰት፣ በዘር በቋንቋና በቡድን መለያየትና የመሳሰለው ኹሉ ተገቢ ተግባሯን እንዳትወጣና በትክክለኛ ማንነቷ እንዳትገለጥ ትልቅ መሰናክል ኾነውባታል።


ጌታ በተወለደባት ሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እረኞች በመልአኩ በኩል የተነገረው የመሲሑ መወለድ ለሕዝቡ ኹሉ የሚኾን ታላቅ ደስታ የምሥራች ነው። ከዚህ የተነሣ ከአብሣሪው መልአክ ጋር የነበሩት የሰማይ መላእክት ባቀረቡት ምስጋና ውስጥ የመሲሑ መወለድ በምድር ላይ ሰላምና ለሰውም ኹሉ በጎ ፈቃድ እንዲሆን የሚናገር ነው። በእርግጥም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ (በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛ) ሆኖ፣ ዐማኑኤልም ተብሎ ዘላለማዊ ዕርቅ በማድረግ  የሰውን ዘር በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቋል።

በመወለዱ ሰላም እንደ ተሰበከ ኹሉ (ሉቃ. 2፥14)፣ በመስቀሉ ደም ሰላምን አድርጓል (ቈላ. 1፥19-20)። በእርሱም ወደ እግዚአብሔር በማቅረብ ሰላማችን ኾኖ እስራኤልና አሕዛብ ተብለው የተለያዩትን አንድ አድርጓል (ኤፌ. 2፥14-15)። ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ አይሁድን ፈርተው በዝግ ቤት ሳሉ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ተገኝቶ “ሰላም ለእናንተ ይኹን” (ዮሐ. 20፥19፡21፡26) በማለት በትንሣኤው ፍጹም ሰላም መኾኑን አብሥሯል።

ይህን ሰላም ለማግኘት ከሰላሙ አለቃ ጋር መተዋወቅና እርሱን በእምነት መቀበል ያስፈልጋል። ይህ ከእርሱ የሚገኘው ሰላም ዓለም እሰጠዋለሁ ከሚለው ሰላም የተለየና በምንም ኹኔታ የማይደፈርስ ሰላም ነው። ይህ ሰላም በሰማያዊው ክብር እንጂ በምድራዊው ባለጠግነት የተመካ አይደለም። የሰው ልጅ በሚያልፍባቸው አስቸጋሪ ኹኔታዎች ውስጥም ቢኾን ይህ ሰላም አይደፈርስም። የእውነተኛው ሰላም ልክ እስከዚህ ድረስ የላቀ ነው።

ሰላም ባለበት ጽድቅ፣ ደስታ፣ ፍትሕ፣ መተናነጽ፣ አንድነትና የነገ ተስፋ አሉ። ለኹሉ ጊዜ አለው ስንል የሰላም ባለቤት የሆነውን መድኀኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዘን ስለ ሰላም ማወጅና በየዕለቱ አኹን ጊዜው የሰላም መሆኑን መመስከርና መናገር (ማውራት) አለብን ማለታችን ነው።


1 comment: