Monday, January 14, 2019

ዕቅበተ እምነት


"መድሎተ ጽደቅ" በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን

ክፍል አራት

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዕትሞችመድሎተ ጽድቅለተሰኘው መጽሐፍ ምላሽ ስንሰጥ መቈየታችን ይታወሳል። በዚህ ዕትምም ካለፈው ለቀጠለውና በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ጽሑፍ ላይ ለተሰነዘረው መሠረተ ቢስ ትችት ምላሽ መስጠታችንን እንቀጥላለን።

በዚህ ዕትም መድሎተ ጽድቅገጽ 42 ላይ የሚገኘውና በተራ ቍጥር 1.3.3. ላይ፣ከእምነት ይልቅ በስሜት ሕዋሳት (በማየት፣ በመስማት፣ …) ላይ መመሥረትበሚለው ንኡስ ርእስ ሥር ለተጠቀሱት እንዲሁም “1.1.4 ተገቢ ያልኾኑ አባባሎችንና ጸያፍ አገላለጾችን መጠቀምበሚለው ንኡስ ርእስ ሥር ለቀረበው ሐሳብ ከዚህ እንደሚከተለው ምላሽ እንሰጣለን፦

በመጀመሪያው ንኡስ ርእስ ሥር መድሎተ ጽድቅጸሓፊ ለመተቸት የተጣጣረው፣አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታ በምድር የሚደረገውን ኹሉ ያውቃል ማለት የሚታመን ቀርቶ የማይመስል ነው።” (ጮራ . 38 ገጽ 17) የሚለውን ሐሳብ ነው። 

በተደጋጋሚ ለመግለጥ እንደ ሞከርነው፣ የጸሓፊው አንዱና መሠረታዊው ችግር፣ እኛን ለመተቸት ሲል ብቻ ከየጽሑፎቻችን ቈርጦ ያወጣቸው ጥቅሶች፣ ከተጻፉበት ዐውድ ተነጥለው የተወሰዱ፣ እኛ በጻፍንበት መንገድ ያልተተረጐሙና እርሱ በእኛ ላይ ለማራማድ ለሚፈልገው ዐላማ እንዳሻው እየጠመዘዘ የተጠቀመባቸው መኾኑ ነው። እንዲህ ሲያደርግም፣ ቀደም ብሎ እርሱ የተስማማበትን አንዳንድ እውነት መልሶ እስከ ማፍረስ ይደርስና፣ በምላሻችን የተስማማ የመሰለው ለጊዜው እንጂ ለዘለቄታው እንዳልኾነ፣ ለአፉ እንጂ ከልቡ እንዳይደለ በጽሑፉ ውስጥ ይታያል።

ለምሳሌ ባለፈው የጮራ መጽሔት ዕትም ላይ፣ በዚሁ ዐምድ ሥርየተቀበረ መክሊትበተሰኘው መጽሐፍ ላይ ለቀረበው ፈጣሪንና ፍጡራንን አመሳስሎ የማየትና የመገንዘብ ዝንባሌ፣ መድሎተ ጽድቅጸሓፊ ምላሽ ሲሰጥ እንዲህ ብሎ ነበር፦በኹሉ ስፍራ መገኘት (ምሉዕ በኵለሄነት) እና ኹሉን ዐዋቂነት (ማእምረ ኵሉ መኾን) የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቦች ብቻ መኾናቸው የታወቀ ነው። ስለዚህ ቅድስት ቤተ ርስቲያን ፈጣሪና ፍጡርን አሳምራ ለይታ የምታውቅ ናት እንጂፍጡራንን ከፈጣሪ እኩል ማድረግና ማስተካከልየሚለው አይመለከታትም።” (መድሎተ ጽድቅ ገጽ 38 ይመለከቷል)

ዐለፍ ብሎ ግን፣ (ምላሽ እየሰጠን በምንገኝበት በዚህ ነጥብ ላይ) ያንበኹሉ ስፍራ መገኘት (ምሉዕ በኵለሄነት) እና ኹሉን ዐዋቂነት (ማእምረ ኵሉ መኾን) የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቦች ብቻ መኾናቸው የታወቀ ነው።ያለውን እውነት በመቃረን ቆሟል። ምክንያቱም እኛ ላነሣነውና ከዚህ እውነት ጋር ለሚስማማው ሐሳብ ሌላ መልክ ሰጥቶ የተቸው፣አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታ በምድር የሚደረገውን ኹሉ ያውቃል ማለት የሚታመን ቀርቶ የማይመስል ነው።የሚለውን የጮራን ምላሽ ነውና። ለዚህ ግልጽ መልእክትም፣ከእምነት ይልቅ በስሜት ሕዋሳት (በማየት፣ በመስማት…) ላይ መመሥረትየሚል ከጮራ ሐሳብ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ፣ የእኛ እምነት ያልኾነንና እኛ ላይ ሊለጥፍ የፈለገውን የራሱን ሐሳብ ንኡስ ርእስ አድርጎ አቅርቧል።

ለመኾኑ ጸሓፊው፣አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታ በምድር የሚደረገውን ኹሉ ያውቃልብሎ ያምናል ወይስ አያምንም? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ምላሹን በተመለከተ በሐተታው ውስጥ መገንዘብ የሚቻለው አብርሃም በምድር ላይ የሚደረገውን ኹሉ በዐጸደ ነፍስ ኾኖ ያውቃል የሚል ነው። እንዲያ ባይኾንማ ኖሮ፣ ቀደም ሲል የቅዱሳንን የዕውቀት ልክ በገለጠበት ዐቋሙ መጽናት ይገባው ነበር። እርሱ ግን ከዚያ ዐቋሙ በመንሸራተት ጉዳዩን በሌላ መንገድ ለማቅረብ የወደደው፣ ቅዱሳን በዐጸደ ነፍስ ኾነው ኹሉን ያውቃሉ ከሚለው የስሕተት ትምህርት ስላልተላቀቀና ልባዊ ዐቋሙ በመኾኑ ነው።
  
እርሱ አለአግባብ ለመተቸት የጠቀሰው ንባብ የተወሰደው፣ በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 38 ገጽ 17 ላይኦርቶዶክስ መልስ አላትበሚል ርእስ መጽሐፍ ጽፎ የስሕተት ትምህርት ላራመደው ለዲ/ ዳንኤል ክብረት ከተሰጠው ምላሽ ውስጥ ነው። / ዳንኤል በመጽሐፉ ካነሣቸውና በጮራ ምላሽ ከተሰጠባቸው ነጥቦች መካከል አንዱ፣በዐጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን በምድር ላይ የሚደረገውን የሚያውቁበት ጸጋ አላቸውበማለት የሚጀምረውና በተለይ ስለ አብርሃም ከጻፈው፣አብርሃም ከብዙ ዓመታት በኋላ የተነሣውን ባዕለ ጸጋውን ዐውቆታል።እንደዚሁም ሙሴንና ነቢያትንም ዐውቋቸዋል በማለት ቅዱሳን በዐጸደ ነፍስ ኾነው በምድር የሚሠራውን እንደሚያውቁ አስመስሎ ለጻፈው የተሰጠ ምላሽ ነው።

ጮራ በሰጠችው ምላሽ ውስጥ መከራከሪያዋ የነበረው፣ አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ኾኖ በምድር ላይ የሚደረገውን አያውቅም የሚል ነበር። / ዳንኤል፣ አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ኾኖ በምድር ላይ የሚደረገውን ማወቁን ያሳይልኛል ብሎ የጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሉቃ. 1619-31 ነው። ይህ ክፍል ለማስተማር የቀረበ ምሳሌያዊ እንጂ ታሪካዊ መሠረት ያለው እንዳልኾነ ግን ይታወቃል። ከዚህ አንጻር አብርሃም፦ ድኻው አልዓዛርና ባለጸጋው በምድር ይኖሩ የነበረውን ኑሮ ማወቁ፣ እንዲሁም ሙሴንና ነቢያትን መጥቀሱ ለማስተማሪያነት የቀረበ ምሳሌ እንጂ በትክክል የተፈጸመ ታሪክ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ስለዚህ ይህን ክፍል አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታ ኹሉን ዐዋቂ ነው ለማለት መጥቀስ በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ያለውን ባሕርያዊ ልዩነት ፈጽሞ ካለማወቅ የሚነጭ ነው።
  
አብርሃም ካንቀላፋ ከብዙ ዓመታት በኋላና በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታ፣ የአብርሃም ዘር የኾኑት ሕዝበ እስራኤል፣አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።” (ኢሳ. 6316) ሲሉ የሰጡት ምስክርነት፣ በዐጸደ ነፍስ ያለውን የአብርሃምን ማንነትና የዕውቀት ልክ የሚያሳይ ነው። ይህን ዐልፎ በመኼድ አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ኾኖ በምድር የሚሠራውን ያውቃል የሚለው የዲ/ ዳንኤል ሐሳብ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ከመኾኑም በላይ፣የሚታመን ቀርቶ የማይመስል ነው።ምክንያቱም አብርሃም ፍጡር እንደ መኾኑ፣ በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታም ቢኾን፣ በቦታ የተወሰነና ኹሉን የማያውቅ ነውና።

የሚታመን ቀርቶ የማይመስል ነው።በማለት የገለጥነውን የዲ/ ዳንኤልን ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ፣ መድሎተ ጽድቅጸሓፊ ግን፣ከእምነት ይልቅ በስሜት ሕዋሳት (በማየት፣ በመስማት፣ … ) ላይ መመሥረትነው የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ይህም እውነትን ላለመቀበልና የነገሩን ውል ለማጥፋት ሲል ኾነ ብሎ የፈጠረው እንጂ የእኛ ዐቋም እንዳልኾነ ይጠፋዋል ብለን አናምንም። እኛ ለማለት የፈለግነው፣ ሐሳቡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የሌለውና ሊታመን የማይችል ነው እንጂ፣ ይህ በስሜት ሕዋሳት ካልተረጋገጠ ሊታመን አይችልም የሚል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት በተሳሳተ ትምህርት ወይም በሌለ ነገር ላይ የሚመሠረት ሳይኾን፣ የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት የሚነሣ ነው (ሮሜ 1017) ስለዚህ የቃሉ አንዳች ድጋፍ የሌለውንና በተቃራኒ የቆመውን የሰው ሐሳብ ማፍረስ እንጂ መቀበል የለብንም። ታዲያ ይህ ዐቋም እንዴት ኾኖ ቢታሰብ ነው ለእምነት ቦታ እንዳልሰጠንና ለማመን በስሜት ሕዋሳት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለን እንደ ጻፍን የሚያስቈጥረው?

ሌላውመድሎተ ጽድቅሊተቸው የተነሣው ሐሳብጌታችን ስለ አብርሃም ሲናገር አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤትን አደረገ፤ አየም፤ ደስም አለው ብሏል (ዮሐ. 856) ጌታችን በተወለደ ጊዜ አብርሃም በአካለ ሥጋ አልነበረም፤ ታዲያ እንዴት አድርጎ አይቶ ደስ አለው? በዐጸደ ነፍስ ኾኖ ስላወቀ ነው እንጂ ስለ ተባለው፣ ጌታ ስለ አብርሃም የተናገረው ይህ ቃል አብርሃም ከሞተ በኋላ በዐጸደ ነፍስ ሳለ የተከናወነና ከጌታ ልደት ጋር የተያያዘ ስለ መኾኑ የሚጠቍም ፍንጭ በጥቅሱ ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም። . . . ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ አብርሃም ከሞተ በኋላ ሳይኾን በዐጸደ ነፍስ ሳለ የተከናወነን ድርጊት የሚገልጽ መኾኑን በቃሉ መሠረት ማስረዳት ይቀላል።” (ጮራ . 38 ገጽ 17) የሚለው ነው።

በዚህ ጥቅስ ውስጥመድሎተ ጽድቅሐሰትን እውነት   ለማድረግ (ሐሰት መቼም እውነት ላይኾን) ሲጣጣር፣ ከጮራ መጽሔት የጠቀሰውን ይህን ክፍል፣ ለእርሱ እንዲስማማውና የአንድ ሐረግ ለውጥ በማድረግ ጭምር ከጮራ የወሰደውን ጥቅስ አዛብቶ እንደ ጠቀሰው ተረጋግጧል። የተለወጠው ሐረግ የሚገኘው ከመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ላይ ነው። የጮራ ጽሑፍ “… ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ አብርሃም ከሞተ በኋላ ሳይኾን በዐጸደ ሥጋ ሳለ የተከናወነን ድርጊት የሚገልጽ መኾኑን በቃሉ መሠረት ማስረዳት ይቀላል።የሚል ሲኾን፣ እርሱ ግንበዐጸደ ሥጋየሚለውንበዐጸደ ነፍስብሎ ነው ለውጦ የጻፈው። በተሳሳተ መንገድ እንደ ጠቀሰውም አረፍተ ነገሩ በማስተዋል ሲነበብ ይታወቃል። ይህን ያደረገው ለምን ይኾን? በስሕተት ነው? ወይስ የለወጠው ሐረግ እርሱ ለሚያቀነቅነው የተሳሳተ ሐሳብ ይበልጥ እንዲረዳው ለማመቻቸት ብሎ?

/ ዳንኤል፣ጌታችን ስለ አብርሃም ሲናገር አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤትን አደረገ፤ አየም፤ ደስም አለው” (ዮሐ. 856) የሚለውን ጥቅስ እተረጕማለሁ ሲል እንደ ልማዱ ስሕተት ላይ መውደቁ አልቀረም። ምክንያቱም እንደ እርሱ ትርጓሜ አብርሃም ቀኑን ያየውና የተደሰተው በዐጸደ ነፍስ ኾኖ ነው። ለምን ቢባል? የሰጠው ምክንያትጌታ በተወለደ ጊዜ አብርሃም በአካለ ሥጋ አልነበረም።የሚል ነው። በዚህ ክፍል አብርሃም ያየው ዘንድ ሐሤት ያደረገውና ያየው የጌታ ቀን የቱ ነው? አየ የተባለውስ መቼ ነው? የሚሉትን ጥቅሱ አያብራራም። ይህን ክፍል ማራመድ ለምንፈልገው የራሳችን ሐሳብ በግድ ደጋፊ አድርገን መጥቀስ የለብንም። ከዚህ ይለቅ ከሌሎች ተያያዥ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር በማዛመድ ለመረዳት መሞከሩ ይበልጥ ይረዳል።

ስለዚህ እንደ እርሱ በድፍረት ቀኑ ልደቱ ነው፤ ያየውም በዐጸደ ነፍስ ኾኖ ነው ከማለት ይልቅ፣ ትሑት ኾኖ ቃሉን በመመርመር፣ጥቅሱ አብርሃም ከሞተ በኋላ ሳይኾን በዐጸደ ሥጋ ሳለ የተከናወነን ድርጊት የሚገልጽ መኾኑን በቃሉ መሠረት ማስረዳት ይቀላል።ምክንያቱም ስለ አብርሃምና እርሱን ስለ መሰሉ የእምነት ዐርበኞች በተጻፈበት የዕብራውያን መልእክት ውስጥእነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲኾኑ ታመኑ።” (ዕብ. 1113) ይላል። በዚህ ውስጥ አብርሃምምአየየተባለው እርሱ በኖረበት የአበው ዘመን ኾኖ በሩቁ እንጂ፣ በዐጸደ ነፍስ ወደ ኹሉን ዐዋቂነት ተሸጋግሮ በቀጥታ አይደለም።
  
መድሎተ ጽድቅጸሓፊ ግን አብርሃም ቀኑን ያይ ዘንድ ሐሤት ያደረገውና አይቶ ደስ የተሰኘው እንዴት እና መቼ እንደ ኾነ ለማስረዳት ከመሞከር ይልቅ፣ እኛ ለማመን ነገሮች ቀላል በኾነ መንገድ መቅረብ አለባቸው ብለን እንደምናምንና ለማመን የሚያስቸግሩ ነገሮችን በእምነት እንደማንቀበል አስመስሎ ብዙ ዐትቷል። ይህ በባዶ ሜዳ ወረቀት የፈጀበት ሐተታው የእርሱ ሐሳብ እንጂ የእኛ ዐቋም እንዳልኾነ እርሱም ያውቀዋል፤ ጽሑፎቻችንም ይመሰክራሉ። ታዲያ ማደናገር ለምን አስፈለገ?

ለመኾኑ ጸሓፊው ለዲ/ ዳንኤል ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ የሰጠነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ፣ በሌላ ምላሽ ከማፍረስ ይልቅ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነትን ወደሚቃረኑ የአመለካከት ዘርፎች እኛን በግድ ጐትቶ መጨመር ለምን ፈለገ? መልሱ ቀላል ነው። በዲ/ ዳንኤል የተሳሳተ ጽሑፍ ላይ የቀረበውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሻችንን ማስተባበል የሚችልበት እውነት ስለሌለው ነው።

እምነት የተመሠረተው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ነው። በቃሉ ውስጥ ያልተገለጠውንና ከቃሉ ጋር የሚቃረነውን አመለካከት ወደ ቃሉ መጨመር ትክክለኛውን እምነት መበረዝ ወይም ማዛባት ይኾናል።አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም፤ ደስም አለው።የሚለው የጌታ ቃል ያለአንዳች ጥርጥር በእምነት የምንቀበለው እውነት ነው። ስሕተት ነው ያልነው ቃሉን ሳይኾን፣ በዲ/ ዳንኤል የተሰጠውንና ወደ ስሕተት ትምህርት የመራውን ትርጕም ነው። ቃሉን እርሱ ባቀረበው መንገድ መቀበል ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር መጋጨት ይኾናል፤ ከዚያ ይልቅ የቃሉን ፍቺ በትሕትና ለማስተዋል ቃሉን ማጥናት ወደ ቃሉ ምስጢር ያደርሳል።
        
/ ዳንኤል ያደረገው ምንድነው? በቃሉ ውስጥ ያልተጠቀሰንና እርግጠኛ ያልኾነን፣ እንዲሁም ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ የኾነን ነገር ትክክለኛ አስመስሎ አቀረበ። ይህም የእርሱ ሐሳብ እንጂ ከጥቅሱ የተገኘ አይደለም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውጪ የኾነ የስሕተት ትምህርትም ነው። ትምህርቱ ተቀባይነትን ያጣው በዚህ መለኪያ ተመዝኖ እንጂ፣ ለማስረዳትም ኾነ ለመረዳት ከባድ ወይም ቀላል ኾኖ ስለ ተገኘ አይደለም።

”1.1.4 ተገቢ ያልኾኑ አባባሎችንና ጸያፍ አገላለጾችን መጠቀምበሚለው ንኡስ ርእስ ሥርመድሎተ ጽድቅጮራን የተቸው ከዮሴፍ ጋር በተያያዘ ስለ ቀረበው ሐሳብ ነው።

ዮሴፍ 17 ዓመት ወጣት በነበረ ጊዜ የአባቱን መንጋዎች ለማሰማራት ከባላና ከዘለፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር ይኼድ ነበር። ማታ ማታ ወደ ቤት ሲመለሱ ዮሴፍ ወንድሞቹ ያደረጉትን መጥፎ ነገር ኹሉ ለአባቱ ይናገር ነበር። ዮሴፍ ምንም እንኳ ያደገ ሰው ቢኾንም በሰው ላይ ማሳበቅናን ገና አልተወም ነበር። ... ከቤተ ሰቡ እንደ ማዕድን የተቈፈረው ዮሴፍ እነሆ ከመጠን በላይ ስለ ራሱ የሚያስብ፣ ትዕቢተኛና ስለ ሌሎች ሰዎች ጥፋት የሚያወራ ወጣት ነበረ።” (ጮራ . 21 ገጽ 19-20)

Ìይህ ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ አስተዋይና የዋኅ ከነበረው፣ ረድኤተ እግዚአብሔር ያደረበት ስለ መኾኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን ከዮሴፍ ታሪክ ተቃራኒ የኾነ የዮሴፍን መልካምነት ጥላሸት ለመቀባት ሲባል የተፈጠረ እንግዳ ድርሰት ነው።” (መድሎተ ጽድቅ ገጽ 44)

ባደግሁበት ደብር፣ ከዕለታት በአንዱ ቀን አንዱ ሰባኪ በዐውደ ምሕረት ላይ የጌታን እግር ሽቱ የቀባችው (ማርያም እንተ እፍረት - ሽቱ የቀባችው ማርያም) ኀጢአተኛ መኾኗን ይናገር ነበር። እንደሚታወቀው የጌታን እግር ሽቱ የቀባችው ሴት በዮሐንስ ወንጌል ላይ ስሟ (ማርያም ተብሎ) ተጠቅሷል (ዮሐ. 123) በሌሎቹ ወንጌላት ግን ስሟ ሳይጠቀስ፣ በተለይ በሉቃስ ወንጌል ኀጢአተኛ ሴት ተብላለች (737-38) ሰባኪውም ይህን ጠቅሶ ነበር የተናገረው። ይህን የሰሙና በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሊቅ የተሰኙ አንድ አባት፣ ከዐውደ ምሕረት ውጪ እንዲህ ተባለ እኮ ተብሎ ሲነገራቸው፣እንዴ! ማርያም እንተ ዕፍረት እኮ ድንግል ናት፤ ኀጢአተኛ አይደለችምበማለት ትምህርቱን ተቃወሙ። በሌላ ጊዜ እንዲህ ማለታቸውን የሰሙና በደብሩ የነበሩ ሌላው የሐዲስ ኪዳን መምህር ግን፣አይ! እርሳቸው ደግሞ አበዙት፤ ቅዱሳን አይሳሳቱም ሊሉ ነው እንዴ?” ሲሉ መለሱ።

መድሎተ ጽድቅጸሓፊም በጽሑፍ ያሰፈረው ተመሳሳይ ነገር ነው። የቅዱሳን ብርቱ ጐን ብቻ እንጂ ድካማቸው ሊወሳ አይገባም፤ ወይም ቅዱሳን ፍጹማን ናቸው እንጂ ምንም ስሕተት የለባቸውም እያለ ነው። ቅዱሳን የተባሉ ሰዎችን ምንም ስሕተት የለሽ እና እንከን አልባ አድርገው የሚያቀርቡት ግን ልቦለድ የኾኑት ገድላትና ድርሳናት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቅዱሳን የተባሉት፣ ሰዎች ስለ ኾኑ ብርቱ ጐናቸው ብቻ ሳይኾን ደካማ ጐናቸውም ተጽፏል። በመጽሐፈ ኢዮብ ላይ፣ እንኳ ሰዎችን መላእክቱንም ስንፍና ይከሳቸዋል ይላል (418)

ይኹን እንጂ መድሎተ ጽድቅጸሓፊ፣ይህ ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ አስተዋይና የዋኅ ከነበረው፣ ረድኤተ እግዚአብሔር ያደረበት ስለ መኾኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን ከዮሴፍ ታሪክ ተቃራኒ የኾነ የዮሴፍን መልካምነት ጥላሸት ለመቀባት ሲባል የተፈጠረ እንግዳ ድርሰት ነው።በማለት ዮሴፍን ከልጅነቱ ጀምሮ እንከን አልባ በማድረግ ለማቅረብና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ የጠቀሰው ደካማ ጐን በቃሉ ውስጥ እንዳልተጻፈ አድርጎ፣ እኛን ፀረ ቅዱሳን ለማስመሰል ሞክሯል።

ለመኾኑዮሴፍም [የወንድሞቹን] የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ።” (ዘፍ. 372) የሚለውን የዮሴፍን ማንነት ከቶ አላነበበውም ይኾን? ይህስ በሌላ አነጋገር ሰብቅ አይደለምን? ራስን ከፍ ማድረግና ሌላውን ጥፋተኛ አድርጎ ማቅረብስ አይኾንምን? ይህም የኾነው ገና በልጅነቱ ነበር። እርሱ ግን ይህን የመጀመሪያውን የዮሴፍን የልጅነት ጠባይ ባለማስተዋል ዮሴፍከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ አስተዋይና የዋኅእንደ ነበረ በድፍረት ጽፏል።

በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 21 ላይየቤተ ሰብ አመሠራረትና አመራርበተሰኘው ዐምድዮሴፍና ቤተ ሰቦቹበሚል ርእስ ስለ ዮሴፍ በተጻፈው ላይ፣ መድሎተ ጽድቅጸሓፊ የሰነዘረው ትችት እጅግ አሳፋሪና ያልታደለ አእምሮ ውጤት ነው።
 
ጮራ በዚያ ጽሑፍ ውስጥ የዮሴፍን የቀድሞ ሕይወትና እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መከራ ውስጥ በማሳለፍ ዮሴፍን እንዴት ሠርቶ እንዳወጣው በሚገባ ዳስሳለች። ዮሴፍ እንደ ወርቅ ተፈትኖ ከመውጣቱ በፊት የነበረው ጠባይና ተፈትኖ ከወጣ በኋላ ያለው ጠባይ እጅግ የተለያዩ መኾናቸውም በጽሑፉ ውስጥ በስፋት ተመልክቷል። አንባብያን ጮራ ቊጥር 21 በማንበብ ይህን ማረጋገጥ ይችላሉ። እርሱ ግን ስለ ዮሴፍ የቀድሞ ማንነትና ጠባይ የተጻፈውን ብቻ ቈርጦ በመውሰድ፣ ተገቢ ያልኾነና ጸያፍ አገላለጥን እንደ ተጠቀምን አስመስሎ አቅርቧል።

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ኹኔታ ሲናገር፣ዮሴፍም [የወንድሞቹን] የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ።” (ዘፍ. 372) ይላል። በጮራ ላይዮሴፍ 17 ዓመት ወጣት በነበረ ጊዜ የአባቱን መንጋዎች ለማሰማራት ከባላና ከዘለፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር ይሄድ ነበር። ማታ ማታ ወደ ቤት ሲመለሱ ዮሴፍ ወንድሞቹ ያደረጉትን መጥፎ ነገር ኹሉ ለአባቱ ይናገር ነበር። ዮሴፍ ምንም እንኳ ያደገ ሰው ቢኾንም በሰው ላይ ማሳበቅናን ገና አልተወም ነበር። . . . ከቤተ ሰቡ እንደ ማዕድን የተቈፈረው ዮሴፍ እነሆ ከመጠን በላይ ስለ ራሱ የሚያስብ፣ ትዕቢተኛና ስለ ሌሎች ሰዎች ጥፋት የሚያወራ ወጣት ነበረ።ተብሎ የተገለጠውም ይኸው ነው። ከዚህ ቀጥሎ ያለውናመድሎተ ጽድቅጽሑፋችንን ሚዛን ለማሳጣት ሲል ሊጠቅሰው ያልወደደው ዐረፍተ ነገር እንዲህ ይላል፤የእግዚአብሔር እጅ ግን በዮሴፍ ላይ ነበረ። መልካም ዕቅዱን እንዲፈጽም እግዚአብሔር ይህን ጥሬ ዕቃ ወስዶ እንዴት እንደ ለወጠው በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን።” (ገጽ 20) እንደ ተባለውም በቀጣዮቹ አንቀጾች ዮሴፍ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን በመከራ ነጥሮ እንዴት እንደ ወጣ በሰፊው ያብራራል።

እግዚአብሔር ዮሴፍን ሠርቶ በማውጣት የእርሱ ዐላማ የሚፈጸምበት ምርጥ ዕቃው ለማድረግ በመጀመሪያ በወንድሞቹ አማካይነት ተሸጦ ወደ ግብጽ እንዲወርድ አደረገ። ከዚያ በጲጥፋራ ሚስት ምክንያት ያለ ስሙ ስም ተሰጥቶት ወደ ወኅኒ ወረደ። ስለ ዮሴፍ ይህን ኹኔታ ጮራ ስትገልጥ፣ጥሩ ስሙና ንጹሕ አኗኗሩ ኹሉ ተበላሽቶ ነበር። እግዚአብሔር የዮሴፍን ጠባይ በልዩ ልዩ ዐይነት የመከራ እሳት በማንጠር ላይ መኾኑን እናያለን።” (ገጽ 20) ብላለች። ዐለፍ ብላምዮሴፍ እንደ ባሪያ በተሸጠበት ወቅት 17 ዓመት ወጣት ነበረ። ወደ ፈርዖን ሲጠራ ደግሞ ዕድሜው 30 ዓመት ያኽል ነበረ። 13 ዓመት ውስጥ መለኮታዊ አንጥረኛው እግዚአብሔር የፈጸመው ሥራ አኹን በልዩ ልዩ የዮሴፍ ተመክሮ እንደ ወርቅ ሲያንጸባርቅ ልናይ እንችላለን።” (ገጽ 21)

በመቀጠልም ዮሴፍ በመከራ ውስጥ ዐልፎና እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ተሠርቶ ከወጣ በኋላ፣ዮሴፍ ምንም እንኳ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኾን፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ የአባቱን ሥልጣን ተቀበለ።ትላለች። በመጨረሻም ሕዝበ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ፣ የእርሱንም ዐጥንት ይዘው እንዲወጡ ማዘዙ የሚያሳየው፣በእርጅናውም ቢኾን፣ በእምነት መንገድ በመራመድ ላይ እንደ ነበረ ነው።በማለት ጮራ የቀድሞው ስለ ራሱ ልዩ አመለካከት የነበረውና ስለ ወንድሞቹ ክፉ ወሬ በማምጣት ሰባቂ የነበረው ዮሴፍ፣ ተሠርቶና ተለውጦ እጅግ ትሑትና እግዚአብሔር ለዐላማው ሲል በልዩ ልዩ መንገድ ሠርቶ ያወጣው ሰው መኾኑን በንግግሩም በተግባሩም አስመስከሯል ብላለች። ይህ ኹሉመድሎተ ጽድቅበጠቀሰው ጮራ ቊጥር 21 ከገጽ 19-22 በስፋት የተዘረዘረ ቢኾንም፣ እርሱ ግን ስለ ቀድሞ ማንነቱ የተጠቀሰውን ዋና ነገር ደካማ ጐኑን ትቶ ዮሴፍን በልጅነቱ እንከን አልባ አድርጎ በማቅረብ፣ ጮራን አለአግባብ ለማሳጣት ሞክሯል። ይህ ግን የትም አያደርስም፤ አንባቢው ጮራን አግኝቶ ቢያነብ የሚያረጋግጠው ሐቅ ነውና። እውነትን በቅንነትና በታማኝነት መመስከር ሲገባ፣ ኅሊናን፣ እግዚአብሔርን፣ ሰውንም ዐልፎ በሐሰት ምስክርነት መቆም ትዝብት ላይ ይጥላል። ለመኾኑ በዚህ ማነው የሚከብረው? ማንስ ነው የሚጠቀመው? በሐሰት ምስክርነትስ እውነተኛ መኾን ይቻላል ወይ?

ስለ ዮሴፍ ደካማ ጐን ከተነገረው ስንጠቅስ ዐላማችን መድሎተ ጽድቅጸሓፊ እንዳለው፣የዮሴፍን መልካምነት ጥላሸት ለመቀባትብለን እንዳልኾነ ከእርሱ በቀር ጽሑፉን ያነበበ የትኛውም አንባቢ ይረዳል ብለን እናምናለን። ጽሑፉ የቀረበው በዮሴፍ ሕይወት ውስጥ የተከናወነውን ነጥሮ መውጣትና የቀድሞውን ደካማ ማንነት ወደ ተለወጠ ዐዲስ ማንነት እግዚአብሔር እንዴት መለወጥ እንደሚችል ማሳየት ነው። ሰው ኹሉ ኀጢአተኛ ነው። ሰው ኹሉ በብዙ ድካም የተሞላ ደካማ ፍጥረት ነው። ይህን የሰው ድካም መለወጥ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ ሰው እንደ ዮሴፍ በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሲገባ ተለውጦ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ኾኖ ይሠራል።
     
በዚህ ኹሉ ውስጥ ተሰውሮ ያለው የጸሓፊው አመለካከት ራሱን የቅዱሳን ወዳጅ እኛን ደግሞ የቅዱሳን ጠላት አድርጎ የማቅረብ ነገር ነው። ይኹን እንጂ የቅዱሳንን ታሪክ በከፊል ሳይኾን በሙሉ፣ ጠንካራውን ብቻ ሳይኾን ደካማውንም ለትምህርታችን እንዲኾን መዘገብ ተገቢ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም ቅዱሳንን እንከን አልባ አድርጎ ማቅረብ ሐሰተኛ እንጂ የቅዱሳን ወዳጅ አያሰኝም።


2 comments:

  1. Wow, awesome weblog layout! How lengthy have you ever been running a blog for?
    you made blogging glance easy. The full glance of your website is excellent, as smartly as the content!

    ReplyDelete
  2. Yes! Finally someone writes about 500mg viagra.

    ReplyDelete