Wednesday, October 16, 2019

ከዓለመ መጻሕፍት


ሃይማኖተ አበው ቀደምት

“ሃይማኖተ አበው ቀደምት” የተሰኘውና በቁም ጽሑፍ ተዘጋጅቶ የተባዛው መጽሐፍ፣ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (ኪ.ወ.ክ.) ጽፈውት ለአቶ ደስታ ተክለ ወልድ በዐደራ የሰጡትና በዶ/ር ብርሃኑ አበበ አማካይነት ምዕራብ ጀርመን ፍራንክፈርት በሚገኘው በፍሬቤንዩስ ድርጅት የታተመ መኾኑን በመጽሐፉ ላይ ደስታ ተክለ ወልድ የሰጡት መግለጫ ያስረዳል። መጽሐፉ ምንም እንኳ በቤተ ክህነት ዐማርኛ በመምህራን ቋንቋ የተጻፈ መኾኑን ስለሚገልጥ፣ አንዳንድ ታሪኮችና ጸሎቶችም በግእዝ በመቅረባቸው በቀላሉ ለመረዳት አስቸጋሪ ቢኾንም፣ ከ15 የሚበልጥ ብዙ ዐይነት ምዕላድ በማየትና በመመልከት፣ በማስተዋልና በመመርመር፣ በማነጻጸርም የተዘጋጀ በመኾኑ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ሥራ ነው። 

በውስጡም የሦስቱን ማለትም የተዋሕዶን፣ የካራንና የቅባትን ባህላተ ትምህርት ምንነት ይዟል። በዘመናቸው የትምህርት ሕጸጽና የሃይማኖት ጕድለት፣ መከራና ስደት፣ ጠብና ክርክር ከዚሁ ጋር ተያይዞ በባህለ ሃይማኖት ልዩነት ምክንያት ምላስና ዐንገት እስከ መቍረጥ የደረሰ አሳዛኝ ቅጣት የፈጸሙ ነገሥታትና የኢትዮጵያ ግብጻውያን ጳጳሳት ታሪክም የተካተተበት መኾኑን መጽሐፉ ይገልጣል።

    
ጥልቅና ሰፊ ነገረ መለኮታዊ ትንታኔ የተሰጠበት አዕማደ ምስጢርም በጥያቄና ምላሽ መንገድ ቀርቧል። የተዋሕዶ ባህለ ትምህርት ትክክለኛነት፣ የካራና የቅባት ባህለ ትምህርት ስሕተትነትም ተገልጦበታል። በአጠቃላይ በምስጢረ ሥላሴና በምስጢረ ሥጋዌ ላይ ከፍ ያለና ጠለቅ ያለ ነገረ መለኮታዊ ሐሳብ የተብራራበት መጽሐፍ በመኾኑ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለሚታዩት ሦስቱ ባህላትና (ተዋሕዶ፣ ካራ እና ቅባት)፣ የትምህርታቸው ይዘት ምን እንደሚመስል ለማወቅም ኾነ በመስኩ ለሚደረግ ጥናትና ምርምር ከፍ ያለ አስተዋፅኦ አለው። እስካኹንም ስለ ሦስቱ ባህላት ለመጥቀስ በምንጭነት የሚያገለግል አንዱ ሰነድ ኾኗል። ከላይ በተገለጡት አርእስትና በሌሎችም ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ የተገጠሙ ግጥሞችም ተካተውበታል። በመጽሐፉ ከተነሡ ሐሳቦች አንዳንዶቹን ቀጥሎ ለመጠቃቀስ እንሞክራለን።

ተዋሕዶ ቅባትና ካራ
ነገረ ክርስቶስን አስመልክቶ ከዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሦስት ቡድኖች መፈጠራቸው ሲተረክ እንሰማለን። እነዚህም ቡድኖች፦ ጸጋ (ተዋሕዶ)፣ ቅብዐትና ካራ በመባል ይታወቃሉ። ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ በኋላ የቤተ ክህነቱን ሥልጣን የያዘው ካራ ተብሎ የሚጠራው ቡድን መኾኑ ግልጥ ነው። የኢትዮጵያን ሃይማኖት ካቶሊክ ለማድረግ የተንቀሳቀሱትና በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ለብዙዎች ዕልቂት ምክንያት የኾኑትን ኢየሱሳውያንን፣ በተለይም አልፎንስን ዐፄ ፋሲል ይህ ሁሉ ደም የፈሰሰው በናንተ ምክንያት ነውና ከነተከታዮችህ ከአገሬ ውጡልኝ አላቸው፡፡ እርሱም ከመውጣቱ በፊት በድብቅ የጸጋን ባህለ ትምህርት ለቈረንጭ መናፍቅ ተክለ ሃይማኖት (ዘሸዋ)፣ የቅብዐትን ባህለ ትምህርት ደግሞ ለኤዎስጣቴዎስ ዘሳንኳ ጊዮርጊስ (ጐጃም) እንዳስተማረና በኢትዮጵያ ሁለት እሾኽ ተክዬባታለሁ ብሎ እንደ ተናገረ ይተረካል፡፡

ትረካው በካሮች በኩል የተሰናዳ መኾኑን ለማወቅ ብዙ ምርምር አይጠይቅም። በአብዛኛው ስለ ጸጋና ቅብዐት እየተነገረና እንደ ታሪክ እንዲወሰድ እየተደረገ የመጣው ይኸው በካሮች በኩል እየተነገረ የመጣው ትረካ ነው፡፡ እንዲህ የተደረገውም የካራ ባህለ ትምህርት አገር በቀልና ጥንታዊ፣ የጸጋና የቅብዐት ባህላተ ትምህርት ደግሞ ከካቶሊኮች የተወረሰና በኋላ የመጣ ለማስመሰል ነው፡፡ እስካኹንም ብዙዎች እየተቀባበሉ የተረኩት ይህ ትረካ ታሪክ ኾኖ መቀጠሉን ማስተዋል ይቻላል።

ኪ.ወ.ክ. ግን፣ የሣልስ ሰላማ ቅድም አያት የሚሉትን ሉተራዊውን መዐልም ጴጥሮስን ደብረ ሊባኖሶች እንደነአባ አልፎንስ ካገር እንዲያስወጣላቸው ለዐፄ ፋሲል ነግረው ከአገር እንዲወጣ ባደረጉት ጊዜ፣ እርሱ “እኔ ብነቀል በመካከላችኹ የዘራኹት እሾኽ እንደኔ መነቀል አይችልም፤ ሲወጋችሁና ሲያደክማችሁ ሲያቈስላችሁ ይኖራል እንጂ” ብሎ መናገሩን ጽፈዋል። እሾኽ የተባሉትም ቅባትና ካራ መኾናቸውን ዝቅ ብለው አብራርተዋል።

በዚህ ዘመን የተደረገውን ክርክር አስመልክቶም በኹለቱም ወገን የቀረበው ትረካ ልዩነት ይታይበታል። በካሮች በኩል አልፎንሱ ከዕጨጌ በትረ ጊዮርጊስ ጋር እንደ ተከራከረና እንደ ተረታ በመጨረሻም አልፎንሱ በጓደኞቻቸው ላይ ያደረሰው ግፍ አናዷቸው ስለ ነበር በጥፊ እንደ መቱትና በዚህ ምክንያት አንድ የጎንደር ሊቅ፦           “ረከብናሁ ለበትር ዘያደክማ ለሮሜ
         ጽሩበ በንባብ ወቅሩጸ በትርጓሜ”
በማለት እንደ ተቀኘ ይተርካሉ።

በተዋሕዶዎቹ በኩል ደግሞ፣ “የባሕርይ ልጅነት አለውና በሰውነቱ የጸጋ ልጅ መባል አይስማማውም” ላሉት [ለቅባቶች] የደብረ ሊባኖስ ሊቃውንት እነዕጨጌ በትሩ እንዲህ ሲሉ መልሰዋል። ‘ሀብተ መንፈስ ቅዱስ መዠመሪያ ዳግማይ አዳም ክርስቶስን ርሱን ባለቤቱን ቀዳሜ ጸጋ (ጸጋን በመቀበል የመጀመሪያ)፣ ምሉአ ጸጋ (ጸጋን የተመላ)፣ መንበረ ጸጋ (የጸጋ መንበር) የተባለውን ሥግው ቃልን በሥጋነቱ በሥግውነቱ፥ ዮም ወለድኩከ (ዛሬ ወለድሁህ) ወልደ አብ (የአብ ልጅ) በኵረ አብ (የአብ በኵር) ካላሰኘች፥ እኛን ወንድሞቹን ተከታዮቹን ውሉድ (ልጆች) ማሰኘት አትችልምና ነገራችሁ እወና አልቦ (አዎንና የለም/አይደለም) ነው።’” ብለው የቄርሎስን ምስክርነት ያመጣሉ። ቄርሎስ “‘ወተሠርዐ ወልደ እግዚአብሔር በኀይል ቅብዐ መንፈስ ቅዱስ። እመሰ ኰሰይነ ልደቶ እንተ ከማነ በመኑ ተመሲለነ ንከውን ውሉደ እግዚአብሔር በመንፈስ። - በቅብዐ መንፈስ ቅዱስ በኀይል የእግዚአብሔር ልጅ ተባለ። [ይህን] እንደ እኛ የኾነበትን ልደቱን ከካድነው በየትኛው ልደት መስለነው በመንፈስ የእግዚአብሔር ልጆች እንባላለን’ ይላልና ልጅነቱን እመኑለት፤ በኵረ ልደት (በጸጋ በመወለድ የመጀመሪያ) በሉት። ወይም በጭራሽ እንደ ካሮች አልተቀባም ጸጋ አልተቀበለም በሉት።” አክለውም “ዋሕድ (አንድ) የሚያሰኘው የባሕርይ ልደቱ በኵር የሚያሰኘውን የጸጋ ልደቱን ካስነቀፈው፥ እንኪያስ በዚህ አንጻር አምላክነቱም ሰው መባሉን ጸጋ መቀበሉን መሲሕነቱን ያስነቅፋል።” የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።

በቅባቶቹ በኩል በሰውነቱ የጸጋ ልጅ ማለት የንስጥሮስ ነው ላሉትም፣ ንስጥሮስ አካላዊ ቃል ከሴት በተወለደው ዐደረ እንጂ ፈጽሞ ሥጋ አልኾነም (ኢሥግው በፍጹም ትሥጉት፤ አላ ኀዳሪ በወልደ ብእሲት) አለ እንጂ “ሰው ከመኾን፥ ከሰውነት ሥራ፥ ከመቀባት፥ ጸጋ ከመቀበል መቼ አገባውና በሰውነቱ ይለው ኖሯል?” ሲሉ ተከራክረዋል። ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርት ከአርዮስ ትምህርት ጋርም ለማመሳሰል የተሞከረውን ፈጽሞ እንደማይመሳሰል ከማብራራታቸው የተነሣ ነበር ባለቅኔው ከላይ የተጠቀሰውን ቅኔ በማቅረብ ያወደሳቸው። (በቅኔው ንባብ ላይ የቃላት ልዩነትም ይታያል። ኪ.ወ.ክ. ያሰፈሩት፦
“ወረከብናሁ ለበትር ዘይጌሥጻ ለሮሜ፤
ጽሩበ በንባብ ወቅሩጸ በትርጓሜ” ነው የሚለው። ትርጕሙም፦ ሮምን የሚገሥጻት በንባብ የለዘበ፣ በትርጓሜም የተቀረጸ በትርን (ዕጨጌ በትሩን አገኘነ የሚል ነው።)  
እንግዲህ ቅኔ የቀረበላቸው የደብረ ሊባኖሱ ዕጨጌ በትሩ የካራ ወገን እንደ ኾኑ ተደርጎ የቀረበው ትረካ በኪ.ወ.ክ. በኩል የጸጋ (የተዋሕዶ) ወገን መኾናቸውን ነው የሚያመለክተው።
                
እንደርሳቸው ትረካ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ከመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ከከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ ጀምሮ በግብጹ ፓትርያርክ በአባ ቆዝሞስ ዘመን (919 ዓ.ም.) እስከ መጣው ጳጳስ አባ ጴጥሮስ ድረስ ኦርቶዶክስ ብቻ ነበረ። በእርሱ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ተልኮ የነበረውን እውነተኛ ጳጳስ ጴጥሮስን፣ ሚናስ እንድራኦስ ወይም እንድራኦስ ፊቅጦር የተባሉ ኹለት ሐሰተኞችና የአውጣኪ ባህለ ትምህርት ተከታዮች በሐሰት ጳጳሳት ነን ብለው ጴጥሮስን እንዲሻር በማድረግ ኢትዮጵያን በሐሰትና በስሕተት ትምህርት እንደ በከሏትና የተዋሕዶን እውነተኛ ትምህርት አንድ አካል አንድ ልጅ ወልድ ዋሕድ ብሎ አንድ ሠሪ አንድ ገባሪ (አድራጊ) አምላክ ወሰብእ (አምላክና ሰው) በማለት ፈንታ፣ ተዐቅቦን (የቃልና ሥጋን ከመደበላለቅና ከመለያየት መጠባበቅን) አፍርሰው አራት ዐይነት ስሕተት ኢትዮጵያ ላይ እንደ ዘሩ ተናግረዋል። እነርሱም፦
(1) አንድ ባሕርይ ማለት
(2) አንድ ግብር ማለት
(3) በሰውነቱ አምላክ ማለት፣ እና
(4) በዓለ ልደትን በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ 28 ማክበር፣
እነዚህ አራቱ ስሕተት ያን ጊዜ ተዘርቶ የበቀለ የነሱ ክርዳድ ነው ይላሉ።
 
ጥንታዊው የኦርቶዶክስ ትምህርት ለመለወጡና የካራና ቅብዐት ባህለ ትምህርት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ይልቁንም በነገሠ በ15ኛው ዓመት ገና ኢየሱሳውያን ሳይመጡ ለመፈጠሩ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች እነዚሁ ከግብጽ የመጡ አውጣኪያውያን የኾኑ ጳጳሳት መኾናቸውንም በኢትዮጵያ የግብጽ ጳጳሳት ታሪክ ውስጥ ዋቢዎችን በመጥቀስ በሰፊው አስረድተዋል።

ምስጢረ ተዋሕዶ
“ተዋሕዶ” የተባለው ቃል በብዙዎች አእምሮ የሚከሥተው የኹለት ወይም ከዚያ በላይ የኾኑ ነገሮችን መቀላቀል ወይም መደባለቅ ነው። አምላክ ሰው የኾነው በተዋሕዶ ምስጢር ነው ሲባል ግን ተዋሕዶው መቀላቀል የሌለበትና በተዐቅቦ (በመጠባበቅ) የተከናወነ መኾኑ መታወቅ አለበት። ተዋሕዶው መደባለቅም መለያየትም የሌለበት መኾኑን ለማመልከት መጠበቂያ የኾኑ ቍልፍ ቃላትን (ያለ መለየት ያለ መደባለቅ፣ ...) መጠቀምም የተለመደ ነው። ተዋሕዶ ምስጢር የተሰኘውም ቅሉ ከዚህ የተነሣ ነው።

ኪ.ወ.ክ. የኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትን ዐዋጅ መሠረት አድርገው ምስጢረ ተዋሕዶን በስፋትና በጥልቀት አብራርተዋል፤ ስለ ተዋሕዶ ምንነት ሲናገሩ፣ “ተዋሕዶ አድልዎና ጽነት (ጠማምነት) የሌለባት በመንፈስ ቅዱስ እጅ የተያዘች አምላካዊት ሚዛን ናትና እንደ ዳኛ የወል (የጋራ) እንደ ምሰሶ የመካከል ኹና ለቃልም ለሥጋም ለኹለቱ ኹሉ በትክክል ትነገራለች። ካለማድላቷም የተነሣ ባዕል (ባለጠጋ) ቃልን በሥጋ ርስት በሥጋ ባሕርይ ነድየ (ደኸየ) ተትሕተ (ዝቅ አለ) ሐጸ እመላእክት (ከመላእክት አነሰ) ብእሲ (ሰው) ወልደ ብእሲት (ከሴት የተወለደ) ፍጡር ግቡር (ሥጋው የተፈጠረ) ኅቡረ ህላዌ ምስሌነ (ከእኛ ጋር በባሕርይ አንድ የኾነ) አሰኝታ፤ ነዳይ (ድኻ) ሥጋን ደግሞ በባሕርዩ አጽንታ ቱሳሔ (መደባለቅ) ውላጤ (መለወጥ) ሳታስነካ በቃል ርስትና በቃል ባሕርይ ከብረ (ከበረ) ተለዐለ (ከፍ ከፍ አለ) ኀየሰ እመላእክት ወረሰ ስመ ዘየዐቢ እምአስማቲሆሙ (ከመላእክት ይልቅ ከፍ ከፍ አለ፤ ከእነርሱ የሚበልጥ ስምንም ወረሰ) አምላክ ወልደ አምላክ ኅቡረ ህላዌ ምስለ አብ (ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ የኾነ አምላክ የአምላክ ልጅ) ታሰኛለች።” ይላሉ።

“ዳግመኛም [ቃልና ሥጋን] ከማገናዘቧ የተነሣ የአምላክነት ክብር በተዋሕዶ ለሥጋ እንዲነገር፥ የሰውነትም ክብር በቅባት ለቃል ይነገራል። የተዋሕዶና የተዐቅቦ ነገር የተሰብአና (ሰው የመኾንና) የተቀብዐ (የመቀባት) ምስጢር ያምላክነትና የሰውነት ግብር እንዲህ ልዩ ልዩ ስለ ኾነ ምንም በየስልቱ ቢነገር የዚህ ኹሉ ባለቤት አንድ አካል ኹኖ የሚሠራው የስምና የግብር ጠቅላዩ አንቀጽ ተቀባዩ (ባለቤት/Subject) ሥግው ቃል ብቻ ነው። ለሥጋ ግን ማድረጊያነት እንጂ ያድራጊነት አንቀጽ የለውም። ይኸውም “ቃል ሥጋ ኮነ… ሞተ በሥጋ … ” በሚለው ይታወቃል።  “ሥጋ ኾነ” እና “በሥጋ ሞተ” የተባለው “ቃል” ነው። በዚህ ኹነት ውስጥ አድራጊውና ዃኙ ቃል ሲኾን፣ ማድረጊያው ደግሞ ሥጋ ነው ማለት ነው።

ይህን አዘዋውረው ቃልን በሰውነቱ አምላክ፣ በሰውነቱ የአብ የባሕርይ ልጅ፣ በሰውነቱ የባሕርይ አምላክ ከአብ ጋር የተካከለ የሚሉት ካራና ቅባት መኾናቸውን ይናገራሉ። እነርሱ ቃልን በሰውነቱ አምላክ የአብ የባሕርይ ልጅ፣ የባሕርይ አምላክ ከአብ ጋር የተካከለ የሚሉት ከኾነ፣ በአምላክነቱም ሰው፣ የማርያም ልጅ፣ ከአብ የሚበልጥ ይበሉት፤ አካኼዳቸው እንዲህ እንዲሉ ያስገድዳልና። ነገር ግን በአምላክነቱ ሰው እንደማይባል ኹሉ በሰውነቱም አምላክ አይባልም። “ማርያምን ዘምስለ ወልዳ አምላክ[1] (ከልጇ ጋር አምላክ ናት) ካላሉ [በቀር]፥ በሰውነቱ አምላክ ወልደ አምላክ ማለት የስሕተት ስሕተት ነው።” ይላሉ። ትክክለኛው አገላለጥ “እስመ ውእቱ አምላክ በመለኮቱ ወሰብእ በትስብእቱ - እርሱ በመለኮቱ አምላክ በሰውነቱ ደግሞ ሰው ነው” የሚለው ነው (ሃይማኖተ አበው ገጽ 332)።
      
ከላይ እንደ ተመለከትነው ሥጋ ኾነ የተባለው ቃል ነው እንጂ ሥጋም ቃል ኾነ አልተባለም። ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ላይ የቆመ መኾኑ ግልጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሥጋ እንደ ኾነ ይናገራልና አንዱ ሥግው ቃል (ሥጋ የኾነው ቃል) ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው። ተዋሕዶም በሊቃውንት ዐዋጅ መሠረት “ቃልና ሥጋን አንድ አካል አንድ ልጅ ወልድ ዋሕድ ታሰኛለች እንጂ፥ ባሕርያትንና ግብራትን ቀላቅላ ደባልቃ አንድ ባሕርይ አንድ ግብር አታሰኝም፤ ተዐቅቦ ይከለክላታል።” በማለት አንድ አካል በኾነው ሥግው ቃል ኹለት ባሕርያት በተዐቅቦ መኖራቸውን ይናገራሉ። ከዚህ በተቃራኒ አንድ ባሕርይ ማለት በምስጢረ ተዋሕዶ የሚያስከትለውን ተፋልሶ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፤ “በተለየ አካሉ በተለየ ስሙ የኛን ባሕርይ ነሥቶ ከኀጢአት በቀር እንደኛ ፍጹም ሰው ለኾነው ለዚህ ላንዱ አካል ላንዱ ልጅ በተዐቅቦ ኹለት ባሕርያት ከሌሉት በአንዲት ባሕርይ ብቻ ኹለት ሥራ መሥራት፥ ኢመዋቲና መዋቲ (የማይሞትና ሟች)፥ ግዙፍና ረቂቅ መኾን፥ የአብ ልጅ የማርያም ልጅ፥ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መባል አይቻልምና በግድ እንዳውጣኪ ሥጋ ወደ ቃል ባሕርይ ተለወጠ ተቀላቀለ ያሰኛል።” አንድ ባሕርይ ማለት መቀላቀልን እንጂ ሌላን ነገር እንደማያሳይም በሚከተሉት ኹለት ስንኞች ገልጠዋል፦
“አንድ ባሕርይ ብሎ ቱሳሔ (መቀላቀል) የለም
ተፈትፍቷል ብሎ አልተቈረሰም”

ቃልና ሥጋ በተዋሕዶ አንድ አካል በተዐቅቦ ኹለት ባሕርያት መኾናቸውን ለማስረዳት በሥጋና በነፍስ፣ (በመንፈስም ቢሉ) የቆመውን የሰውን ኹለንተና ምሳሌ አድርገው ያቀርባሉ፤ “የነፍስ ባሕርይ ወደ ሥጋ ባሕርይ ወደ ግዘፍ ሳይሳብ የሥጋም ባሕርይ ወደ ነፍስ ባሕርይ ወደ ርቀት (“ቀ” ጠብቆ ይነበብ) ሳይሳብ ነፍስና ሥጋ ተውሕደው ፩ አካል ፩ ህላዌ ሰው ይገኛል።” በሥጋና በነፍስ ተዋሕዶ የቆመው ሰው አንድ እንጂ ኹለት እንዳይባል፣ ለሥግው ቃልም በተዐቅቦ ኹለት ባሕርያት ስላሉት አንድ አካል እንጂ የግድ ኹለት አካላት ሊኖሩት ይገባል አያሰኝም።

ስለ አካልና ባሕርይ ኹኔታ “አካል ያለ ባሕርይ ብቻውን አይቆምም፤ ባሕርይም ያለ አካል አይፈጸምም።” በማለት ሲያስረዱ፣ በሌላ ክፍል ደግሞ “ከባሕርይ ለሚገኝ ባሕርያዊ ሥራ ሠሪው አካል ሲኾን መሣሪያው ደግሞ ባሕርይ ነው። አካል ሠሪ እንደሚባል ባሕርይ ደግሞ ሠሪ አይባልም። ማጭድ ማጨጃ እንጂ ዐጫጅ እንዳይባል … የሥራ ባለቤት ወትሮ አካል ነው።” ይላሉ።

ይህን ባለመገንዘብ ባሕርይን ቀላቅለው አንድ ባሕርይ የሚሉት ወገኖች መሠረታዊ ችግር የተዋሕዶን ዐዋጅ አለማስተዋልና የአንዳንድ ቍልፍ ቃላትን አገባብና ትርጓሜ አለመለየት ነው ይላሉ። ለምሳሌ ጠባይዕ የተሰኘው ቃል እንደየዐውዱ፦ ባሕርይ፣ አካል፣ መልክ፣ ቁመት ተብሎ ይፈታል። ይህን ባለመረዳት ብዙዎች ከባሕርይ ጋር ብቻ አያይዘው ይተረጕሙታል፤ “ያፌታውያን እነዲልማን እንኳ ሳይቀሩ ያውጣኪን አሠር (ፍለጋ) ተከትለው ጠባይዕን በቦታው ኹሉ ባሕርይ ብቻ እንጂ አካል አይሉትም።” ይህም የተሳሳተ አፈታት አንድ አካል ተብሎ መተርጐም የነበረበትን ንባብ አንድ ባሕርይ በማሰኘት ከትክክለኛው ትርጓሜ ጋር አልገጥም ብሏል፤ “ካለመግጠሙም የተነሣ ተለያይታለች ከኒሳ (ቤተ ክርስቲያን)” ብለው የቃላትን ትርጕም በተገቢው መንገድ አለመፍታት ያስከተለውን ችግር አመልክተዋል። ይህን ኹኔታ ለመግለጥ በግእዙ በጥቅም ላይ የዋሉት በተለይ “ባሕርይ”፣ “ህላዌ” እና “ጠባይዕ” የተሰኙት ቃላት እንደየዐውዱ አካልንም ባሕርይንም የሚያመለክቱ እንጂ ባሕርይ ተብለው ብቻ የሚፈቱ አይደለም በማለት አስረጂዎችን ያቀርባሉ።

ቀጥሎ በተጠቀሰው የሃይማኖተ አበው ክፍል “ባሕርይ” ተብሎ የተተረጐመው ቃል “ህላዌ” የሚለው ቃል መኾኑን ልብ ይሏል፦ “ወኢተወለጠ ህላዌ ቃል ኀበ ህላዌ ትስብእት ወህላዌ ትስብእት ኀበ ህላዌ ቃል ዳእሙ ይሄልዉ ፪ቱ ህላውያት በበህላዌሆሙ እንበለ ውላጤ። - የቃል ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ወደ መኾን የሥጋ ባሕርይም የቃል ባሕርይን ወደ መኾን አልተለወጠም፤ ኹለቱ ባሕርያት ያለመለዋወጥ ያለመቀላቀል ጸንተው ይኖራሉ እንጂ።” (ሃይማኖተ አበው ገጽ 147)።

ኪ.ወ.ክ. ምስጢረ ተዋሕዶ ይህ ኾኖ ሳለና ይህን ባህለ ትምህርት የሚከተለው ወገን ስሙ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኾኖ ሳለና መባልም ሲገባው፣ ስሙ ይህን ባህለ ትምህርት በማይከተሉና በተቃራኒው በቆሙ ክፍሎች መነጠቁን በሚከተሉት ስንኞች ገልጠዋል። 
“የዛሬ ዘመን ልጅ አባቱን አያውቅ
በቄርሎስ ፈንታ አውጣኪን ናፈቅ
ተዋሕዶ ሳይኾን ስሙ ሃይማኖቱ
ኦርቶዶክስም ሳይኾን ባህሉና ትምርቱ
ሰርቆና ቀምቶ የሰው ስም በከንቱ
ሰው ኹሉ አለስሙ ምነው መጠራቱ”

ስለ ኬልቄዶን ጉባኤ
በኬልቄዶን ጉባኤ የተወሰነው ውሳኔ በዋናነት አንዱን ክርስቶስን ከኹለት የሚከፍልና በክርስቶስ ያሉት ኹለት ባሕርያት  የየራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ፤ መለኮት የመለኮትን ሥራ ይሠራል፣ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ይሠራል የሚል እንደ ኾነ ይታወቃል።

ኪ.ወ.ክ. በተዋሕዶ ባህለ ትምህርት መሠረት ሥግው ቃልን “አንድ አካል አንድ ሠሪ፣ ኹለት ባሕርያት በተዐቅቦ” ሲሉ፣ አንዳንዶች “ኹለት ባሕርያት” የሚለውን ጫፍ ይዘውና ተዐቅቦን ገድፈው፣ እርሳቸው እንዲህ የሚሉት የኬልቄዶንን ጉባኤ ውሳኔ በመቀበል የሚመስላቸው አይጠፉ ይኾናል። ነገር ግን የኬልቄዶኑ ኹለት ባሕርይ እርሳቸው ከሚሉት ፈጽሞ የተለየና የራቀ መኾኑን ያብራራሉ። በኬልቄዶን ጉባኤ ላይ በኤፌሶን ጉባኤ ከተወሰነው የተዋሕዶ ትምህርት ያፈነገጠውን የልዮንን ደብዳቤ ባለመቀበሉ ውግዘትና ስደት የታወጀበት ዲዮስቆሮስ እንኳ፣ በሥግው ቃል ኹለት ባሕርያት በተዐቅቦ መኖራቸውን እንደሚያምንና ከተዋሕዶ በኋላ የሥግው ቃልን አካል ወደ ኹለት የሚከፍለውን ሐሳብ ግን እንደ ተቃወመ፣ በጋግራ ሳለ ለበርጢር በላከው መልእክት ውስጥ መስክሯል ይላሉ፤ እንዲህ በማለት፦ “እመሰ ሰብአ ማኅበረ ኬልቄዶን ይትአመኑ እግዚአብሔር ቃል ሐመ በሥጋ ወአኮ በመለኮት ወንሕነኒ ነኀብር ምስሌሆሙ በዝንቱ። ወአመ ይብሉ ክልኤቱ ህላውያት (ህላዌን በአንቀጸ ተዋሕዶ ኹለት ቢሉ) ወከፈልዎ ለወልድ ዋሕድ ኀበ ክልኤቱ አካላት (ህላውያትን አካላት ብሎ ተረጐመ)።”
ትርጕም፦ “የኬልቄዶን ማኅበር ወገኖች እግዚአብሔር ቃል በመለኮት ያይደለ በሥጋ እንደ ታመመ ካመኑ እኛም በዚህ ነገር ከነሱ ጋር እንተባበራለን፤ ኹለት ህላውያት ካሉ ግን (ህላዌን በአንቀጸ ተዋሕዶ ኹለት ቢሉ) አንድ ወልድንም ወደ ኹለት አካላት ከከፈሉት ኹለትም ካደረጉት ግን በዚህ ከእነርሱ ጋር አንተባበርም።”[2] እዚህ ላይ ህላዌ[3] እንደ ተነገረበት አገባብ አካል ተብሎ እንደሚፈታ አስረድተዋል። ይኹን እንጂ ህላዌን እንደየተነገረበት ዐውድና ስልት መተርጐም ሲገባ፣ እርሱ አካል ብሎ የፈታውን ወደ ዐማርኛ የመለሱት ለውጠው ባሕርይ ብለው ተርጕመውት በሃይማኖተ አበው ውስጥ እናነባለን።[4] እርሳቸው ግን በቅንፍ ዲዮስቆሮስ ስለ ባሕርይ ሳይኾን ስለ አካላት እየተናገረ መኾኑን በዐውዱ መሠረት አብራርተዋል። በሚከተሉት ስንኞችም ሐሳባቸውን አጠናክረዋል።

“ሥራው መሣሪያው ኹለት ቢባል - አንድ ብቻ ነው ሠሪው አካል።
ባንድ አካል በረት ወስኖት አጕራ (የብረት መዝጊያ) - ሊኖር አይችልም ኹለት ሠሪ አውራ፤
ሠሪም አካል ነው አካልም ሠሪ - መሣሪያው ግና ኹለት ባሕሪ
ኹለት ሠሪና ኹለት ባሕርይ - ልዩ እንደ ኾነ አጥርተህ እይ።”

“በሥግው ቃል ውስጥ የየራሳቸውን ሥራ የሚሠሩ ኹለት ባሕርያት ማለትም የአምላክነት ባሕርይና የሰውነት ባሕርይ” አሉ ከሚለው የንስጥሮስ ኑፋቄ ለመሸሽ ሲሉ አንድ ባሕርይ ወደሚለው የአውጣኪ ኑፋቄ የገቡት ክፍሎች ስሕተት ሲታይ ከድጡ ወደ ማጡ ነው። ይህን ኑፋቄም ሲሞግቱ በግጥም እንዲህ ብለዋል፤ 
“አንድ ባሕርይ ብሎ ሥላሴን - አንድ አካል ማለት እንዳይኾን
አንድ አካል ብሎ ወልድንም - አንድ ባሕርይ ማለት አይኾንም፤
አምላክና ሰው ሥግው ቃል - እንዴት አንድ ባሕርይ ይባላል?
አንድ ባሕርይ የሚል ሰባኪ - ያውጣኪ ልጅ ነው ያውጣኪ፤
የባሕርይ ግብሩስ ልደት - ክልኤቱ ሲባል በእውነት
ማነው የሚለው አንድ ግብር - ካውጣኪ ልጅ በቀር።”

የኬልቄዶኑ ጉባኤ የንስጥሮስን አሠረ ፍኖት (ፈለግ) ተከትሎ በአንዱ በክርስቶስ የየራሳቸውን ሥራ የሚሠሩ ኹለት አካላትና ኹለት ባሕርያት እንዳሉና በዚሁ መሠረት ቃል የቃልን፣ ሥጋም የሥጋን ሥራ እንደሚሠራ የሚናገርና አንዱን ክርስቶስ ከኹለት የሚከፍል የተወገዘ ትምህርት በመኾኑ አለቃ ከሊቃውንቱ ብዙ ምስክሮችን እየጠቀሱ ይነቅፉታል። ለዚህ አስረጂ አድርገው የጠቀሱት የወልደ ኬፋ መወድስ ቅኔ አንዱ ነው፤ እንዲህ ይላል፦
“በዘሞተ ወልድ ወበዘኢሞተ
ክልኤቲ አንስት ለእመ አንሥኣ ቅሥተ
ወእመ ለፍትሕ ሖራ እለ ሰሎሞን አብያተ
ሰሎሞን ይቤ ይግበራ ክልኤተ
ወልደ ዘኢሞተ
ከመ በዝንቱ ያጠይቅ ጽድቀ ወሐሰተ።
አብሰ ወማርያም እንዘ ኢይትናገሩ ምንተ
ወነገረ ቅሥት ኢያንሥኡ በዘሞተ ወኢሞተ
እስመ እምንእስከ ልዮን መፍቀሬ ነገር አንተ፤
ከፈልከ ኀበ ክልኤ ሥግወ መለኮተ።”

ትርጕም፦ “በሞተውና ባልሞተው ልጅ
ኹለቱ ሴቶች ክርክር ባነሡ ጊዜ
ያልሞተውን ልጅ ሰሎሞን ከኹለት ይክፈሉት አለ። (1ነገ. 3፥16-28)
በዚህ እውነትና ሐሰቱን እንደሚያጠይቅ
አብና ማርያም ምንም ሳይናገሩ
በሞተውና ባልሞተው ልጅም የክርክር ነገርን ሳያነሡ
ልዮን ከታናሽነትህ ጀምሮ ነገር ወዳድ ነህና
ሥጋ የኾነውን መለኮት ከኹለት ከፈልኸው።”

ይቀጥላል


[1] ካሮች እንዲህ ነበር የሚያምኑት በቦሩ ሜዳ ጉባኤ ላይ ግን ማርያምን “ዘምስለ ወልዳ አምልኮ ወስግደት - ከልጇ ጋር አምልኮትና ስግደት ይገባታል” የሚለው ትክክል ባለመኾኑ ተወግዟል። ይህም በተዋሕዶዎች (ሦስት ልደት) ጥያቄ የተገኘ ውጤት ነው። 

[2] ሃይማኖተ አበው ቀደምት ገጽ 171፤ ሃይማኖተ አበው ዘብንያሚ ገጽ 369-370።

[3]ህላዌ አስተጋባኢ (ሰብሳቢ) ስም ስለ ኾነ እንደ ጠባይዕ ለአካል በሚመችበት አካል፤ ለባሕርይ በሚመችበት ባሕርይ ይባላል። ባማርኛ ሌላ ስም ታጥቶለት እንጂ በአካልና በባሕርይ መካከል ሌላ የተለየ ማእከላዊ ስም ያስፈልገው ነበር። (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ 1948፣ ገጽ 371)። ስለዚህ በዚህ ክፍል “ህላዌ” አካል ኾኖ ነው የገባው ማለት ነው።

[4] ሃይማኖተ አበው ዘብንያሚ ገጽ 370።


No comments:

Post a Comment