Sunday, April 26, 2020

ዕቅበተ እምነት


መድሎተ ጽድቅ በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን
ክፍል ዐምስት
“መድሎተ ጽድቅ” ለተሰኘውና እንደ ስሙ ኾኖ ላልተገኘው መጽሐፍ ባለፉት አራት ተከታታይ ዕትሞች ምላሽ እየሰጠን መቈየታችን ይታወቃል። በዚህ ዕትምም ምላሽ መስጠታችንን እንቀጥላለን። መጽሐፉ ባሰፈረው ቅደም ተከተል መሠረት የዚህ ዕትም ምላሽ በዋናነት በእኛ ጽሑፎች ላይ ለቀረበው ትችት የተሰጠ ምላሽ ሳይኾን፣ አጠቃላይ ነገር ላይ በማተኰር ጸሓፊው መርሕ ብሎ ላሰፈረው፣ ከመጥቀስ ባለፈ እርሱ ግን ለማይመራበት ጽሑፍ ምላሽ እንሰጣለን።
በ“መድሎተ ጽድቅ” ገጽ 46 ላይ «1.2 መኃትወ ታሪክ ዘመናፍቃን» በሚለው ዐቢይ ርእስ ሥር በሚገኘው «1.2.1.1 ሃይማኖት ምንድነው?» በሚለው ንኡስ ርእስ ሥር ስለ ሃይማኖት ምንነት በቀረበው ሐተታ ውስጥ የተነሡ አንዳንድ ነጥቦችን እንመለከታለን። በመጀመሪያ የምንመለከተው፣ “እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጠ እኛ ደግሞ ተቀበልን። የሰው ልጅ ሃይማኖትን ይቀበላል እንጂ ሃይማኖትን ሊሠራ ወይም ሊያሻሽል አይችልም። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት’ በማለት የገለጸው ይህን ነው። ዮሐ. 17፥8 እንዲሁም ‘ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው’ ያለው ለዚህ ነው። ስሙንም ማንነቱንም ሊገባን በሚችለው መጠን የገለጠልን ራሱ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሃይማኖት የሰው ልጅ በምርምር የደረሰበት አይደለም። ዮሐ. 17፥6።

«ሃይማኖት አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነው። … (ይሁ. 3) ምግብናው እንደየዘመኑ ይለያያል፤ ይዘቱ ግን ያው አንድ ነው። … በዘመነ ኦሪት፣ በዘመነ ብሉይ፣ በዘመነ ወንጌል የምግብናው ኹኔታ እንደየዘመኑ ሰዎች የመረዳት ዐቅምና ኹኔታ ቢለያይም ይዘቱ (ጭብጡ) ግን ያው አንድ ነው። … ስለዚህ ሃይማኖት የተሰጠው አንድ ጊዜ ያውም ፈጽሞ (ያለመቀናነስና ያለ ቀረኝ) ስለ ኾነ፥ ተሐድሶ ወይም ለውጥ አያስፈልገውም ማለት ነው። ሃይማኖትን ይቀበሉታል፥ ይጠብቁታል ያወርሱታል እንጂ ላድሰው ላሻሽለው አይባልም። እግዚአብሔር የሰጣት አባቶቻችን ከእርሱ ተቀብለው ኖረውባት ለእኛ ያወረሱን ሃይማኖት ፍጽምትና አንድ ጊዜ የተሰጠች ናት ብልየት እርጅና የለባትም።
«ሃይማኖት ከእግዚአብሔር የተቀበልነው እንደ መኾኑ መጠን የሰዎች ድርሻ አምኖ መቀበልና በዚያ በመጠቀም የዘለዓለም ሕይወትን መውረስ ብቻ ነው። ይህም ማለት በዚህ ዓለም ያለ ማንም ግለሰብም ኾነ አካል እግዚአብሔር በሰጠው እውነት (ሃይማኖት) ላይ የመጨመርም ኾነ የመቀነስ ሥልጣን የለውም ማለት ነው። ሲኖዶሳት እንኳ የሚያደርጉት ሃይማኖትን ለማጽናት አስፈላጊ የኾኑ ውሳኔዎችን መወሰንና ቀኖናትን መቀነን እንጂ በሃይማኖት ላይ መጨመርም ኾነ መቀነስ አላደረጉም፤ ሊያደርጉም አይችሉም።   
ይህ ስለ ሃይማኖት (እምነት) የቀረበው ሐተታ በአብዛኛው በመርሕ ደረጃ ትክክል ነው። ዋናው ነገር ጸሓፊው በዚህ መርሕ ይመራል ወይ? የሚለው ነው። እስካኹን እንዳየነው ግን እርሱ ይህን መርሕ ከላይ በቀረበው መልክ የሚጠቅስ እንጂ በዚህ መርሕ የሚመራ አለመኾኑ ግልጽ ነው። መመራት አለመመራቱ ወደፊት በሚቀርቡ ምላሾች ውስጥም እየታየ ይኼዳል። ከዚህ ቀደም ለመግለጥ እንደ ሞከርነው ግን እርሱ በአብዛኛው ውሸትን እውነት ለማድረግ የሚታገል፣ እውነትን ደግሞ ለመቀበል የሚቸገርና ለውሸት ሲል እውነትን እስከ መሠዋት የሚደርስ መኾኑን መታዘብ ችለናል።
በሌላም በኩል ጸሓፊው ይህን መርሕ ያስቀመጠው እርሱ ስለሚመራበት ብቻ ሳይኾን እኛ ይህን መርሕ እንደማንቀበልና እንደማናከብር፣ ወይም ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን እምነት እናሻሽለው፣ እናድሰው እንደምንል አድርጎ በሐሰት ለመወንጀል ነው። ማንም እንደሚያውቀው እኛ ከእግዚአብሔር በተሰጠንና በተቀበልነው እውነት ላይ አንጨምር፤ ከእርሱም ላይ አንቀንስ፤ እንዲህ የማድረግ መብት አልተሰጠንም የሚል ጠንካራ የኾነ ክርስቲያናዊ ዐቋም አለን። ከዚህ በተቃራኒ ኼደን ከኾነ ግን ጸሓፊው ያን በማቅረብ መተቸት በቻለ ነበር። እርሱ ትክክለኛውን መርሕ ለመጥቀስ ያኽል ይጥቀስ እንጂ፣ ያጠለቀው የመርሕ ጭንብል ሲወልቅ የሚገኘው እውነታ በእግዚአብሔር እውነት ላይ ሰዎች የጨመሩት ለምን ይቀነስ ይባላል? ከእግዚአብሔር እውነት ላይም ሰዎች የቀነሱት ለምን ወደ ስፍራው ይመለስ ይባላል? የሚል ነው። 
የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊም በዚህ የጸሐፍት ፈሪሳውያን መንገድ ኼዶ ሌላውን ሲተች፣ እርሱ በየትኛው ቦታ ላይ እንደ ቆመ ያስተዋለ አይመስልም። አንድ ሰው ወይም ቤተ እምነት አንድን ትክክለኛ መርሕ ስለ ተናገረ ወይም ስለ ጠቀሰና እኔ እንደዚህ ነኝ ስላለ ብቻ ግን ትክክለኛ ነው ማለት አይደለም። በዚያ መርሕ መሠረት የሚያምነው እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የተመሠረተ መኾኑ፣ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የማይቃረን መኾኑ በተግባር መታየትና መረጋገጥ አለበት። ለማንኛውም መርሕ በመጥቀስ እውነተኛ መኾን ባይገኝም፣ ከዚህ ቀደም ይህን መርሕ የጣሱ ትችቶቹን እንደ ተመለከትን ኹሉ፣ ሌሎቹንም ትችቶቹን በቦታቸው ስንደርስ ጸሓፊው ይህን መርሕ መጠበቅ አለመጠበቁን እየፈተሽን የእግዚአብሔርን ሃይማኖት እያጸናን እንኼዳለን።
ጸሓፊው ሃይማኖታችን “እግዚአብሔር የሰጣት አባቶቻችን ከእርሱ ተቀብለው ኖረውባት ለእኛ ያወረሱን ሃይማኖት ፍጽምትና አንድ ጊዜ የተሰጠች ናት ብልየት እርጅና የለባትም።” ሲል ጽፏል። በየትኛውም ሃይማኖት የሚኖርና እንዲህ የማይል ማንም አይገኝም። እንዲህ ብሎ መናገር ቀላል ቢኾንም፣ የሃይማኖቱ ዶግማና ቀኖና በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመረመሩ ግን እግዚአብሔር የሰጠው ብቻ ሳይኾን ሰዎች የሠሩትና በየጊዜው የጨመሩት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስም የቀነሱት ትምህርት ይገኛል። ስለዚህ በሃይማኖት ውስጥ ያለውን ነገር ኹሉ እግዚአብሔር ነው የሰጠው፤ አባቶቻችንም ከእግዚአብሔር ተቀብለው ነው ለእኛ ያስተላለፉልን ብሎ መደምደም አይቻልም። እግዚአብሔር ያልሰጠውና ያልተናገረው ስንት ነገር በእግዚአብሔር ስም እንደ ተሰጠና እንደ ተነገረ ተደርጎ በብዙ አዋልድ መጻሕፍት ውስጥ እንደ ቀረበ ይታወቃል። ይህም ታዲያ ከእግዚአብሔር ለአባቶች የተሰጠና ከአባቶችም ለትውልድ የተላለፈ ውርስ ነው ተብሎ ብልየት (እርጅና) የለበትም የሚሰኝ አይደለም።             
ተሐድሶና መሻሻል የሚያስፈለገው እዚህ ላይ ነው። ተሐድሶ የሚያስፈልገው የእግዚአብሔርን እውነት ከሰዎች ሐሳብና ፍልስፍና ለመለየትና ለመጠበቅ ነው እንጂ የእግዚአብሔርን እውነት ለማሻሻልና ለማረም አይደለም። የተሐድሶ እንቅስቃሴ ጥያቄም የእግዚአብሔር እውነት ያለምንም ማሻሻያ ይጠበቅ፤ የእግዚአብሔር እውነት መስሎ የተቀመጠ፣ ወይም በየዘመኑ የተጨመረ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርትና ሐሳብ ደግሞ እንደየኹኔታው የሚታረመው ይታረም፤ የሚወገደው ይወገድ የሚል ነው። 
እንደ ተባለው ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሃይማኖት ምንም ዐይነት ተሐዶሶና ማሻሻያ አያስፈልገውም፤ እንዳለ ተጠብቆ መቈየትና ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ አለበት። ከእግዚአብሔር ያልተሰጠ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሲመዘን ደግሞ እግዚአብሔር ከሰጠው እውነት ጋር የሚጋጭ ዶግማና ቀኖና ግን ዕድሜ ጠገብ ቢኾንም እንኳ፣ ስሕተት እንጂ እውነት ሊኾን አይችልምና እንደ አስፈላጊነቱ መታደስ ወይም መወገድ አለበት እንጂ “ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሃይማኖት” በሚል ስም በመጠራት መጽናት አይገባውም።
ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሃይማኖት ወይም እምነት ያለ ተሐድሶ የሚኖር ነውና ተጠብቆ መኖር አለበት። ይኹን እንጂ በዚህ እውነት ላይ ከተጨመረ ወይም ከዚህ እውነት ላይ ከተቀነስ የእግዚአብሔር ሃይማኖት ተጠብቋል ማለት አይቻልም። በዚህ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ተሐድሶ በማድረግ፣ ማለትም የተጨመረውን ነገር በመቀነስ የተቀነሰውን እውነት ወደ ስፍራው በመመለስ የእግዚአብሔር እውነት እንዲጠበቅ ማድረግ ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት መጠበቅ የተሐድሶ ሥራ ነውና።                  
በዚህ መንገድ ተሐድሶ ማድረግ ዛሬ አልተጀመረም፤ በእግዚአብሔር እውነት ላይ ሰዎች ሲጨምሩና ሲቀንሱ በኖሩባቸው ዘመናት ኹሉ ተሐድሶ ሲደረግ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስም ይህን በግልጽ ይመሰክራል። ለምሳሌ የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በመጀመሪያ ከተቀበሉት የክርስቶስ ወንጌል ወደ ልዩ ወንጌል ፈጥነው በገቡ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዝም አላለም፤ “በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንኾን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አኹን ኹለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይኹን።” (ገላ. 1፥6-8) በማለት ወደ እውነተኛው ወንጌል ዘወር እንዲሉ መልእክቱን ጽፎላቸዋል። “ልዩ ወንጌል” ሲል የጠራው ክርስቶስን ትቶ በክርስቶስ ፍጻሜ ያገኘውን የሙሴን ሕግ መጠበቅና በዚያ በኩል ጽድቅን ለማግኘት መፈለግን እንደ ኾነ ከመልእክቱ ይዘት እንረዳለን። እግዚአብሔር በሰጣቸው እምነት ላይ የጨመሩትን ይህን “ልዩ ወንጌል” ትተው ወደ ተቀበሉት “የክርስቶስ ወንጌል” ዘወር እንዲሉ በአጽንዖት አሳሰባቸው።       
ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ሃይማኖት ወይም እምነት ምንድነው?
“እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጠ፤ እኛ ደግሞ ተቀበልን።” ሲል የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ እንደ ገለጠው፣ ከእግዚአብሔር ለሰዎች የተሰጠው ሃይማኖት ወይም እምነት ምንድነው? የሃይማኖት ወይም እምነት ትርጕም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እየተለወጠ የኼደ መኾኑ ይታወቃል። ይሁዳ በመልእክቱ፣ “ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።” (ቍጥር 3) ሲል በገለጠው ቃል ውስጥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠ ሃይማኖት በእግዚአብሔር፣ በሀልዎቱ፣ በአድኅኖት ሥራው፣ በመግቦቱና በመሳሰለው የእርሱ በኾነው ማንነቱና ግብሩ ማመን፣ መደገፍና መመካት ነው። ከዚህ አንጻር ለቅዱሳን የተሰጠውን ሃይማኖት ለመረዳት “ይህ ሃይማኖት የቱ ነው?” ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ “ይህ ሃይማኖት ምንድነው?” ብሎ መጠየቅ ትክክለኛና ተገቢ፣ ወደ እውነቱም የሚያደርስ ጥያቄ ነው።
በዕብራውያን መልእክት ውስጥ በመጀመሪያ የተመሠረተው የእምነት መሠረት፦
·         ከሞተ ሥራ ንስሓ
·         በእግዚአብሔር እምነት፥
·         ስለ ጥምቀቶችና
·         እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ
·         ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው (ዕብ. 6፥1-2) ተብሏል።
በዚህ ውስጥ የምናገኘውና ከሞተ ሥራ ንስሓ መግባትን ተከትሎ የተጠቀሰው “በእግዚአብሔር እምነት” ነው። ሌሎቹም ትምህርቶች ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙ እንጂ ከእግዚአብሔር ውጪ ወደ ሌላ አካል ወይም ፍጡራን የሚተላለፉና በመታመን ረገድ እነርሱን የሚያሳትፉ አይደሉም። ስለዚህ ሃይማኖት ወይም እምነት ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ የሚያገናኝ፣ እግዚአብሔር ብቻ የሚመሰገንበት፣ እግዚአብሔር ብቻ የሚወደስበት፣ እግዚአብሔር ብቻ  የሚመለክበት እውነት መኾኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ቅዱስ ሳዊርያኖስ ዘሀገረ ገብልህ “ሃይማኖት እንተ እም ኀበ አብ ተወጥነት፥ ኀበ ወልድ ታበጽሕ፥ ኀበ መንፈስ ቅዱስ ትትፌጸም። - ከአብ የተጀመረች ሃይማኖት ወደ ወልድ ታደርሳለች፤ በመንፈስ ቅዱስም ትፈጸማለች።” ብሏል። ይህም የሚያሳየው ሃይማኖት “በአብ ተጀምራ፣ እወልድ ዘንድ አድርሳ፣ በመንፈስ ቅዱስ በመፈጸምዋ ከአንዱ ከእግዚአብሔር ወጥታ ለሌላ የማትተርፍ መኾንዋን ነው።” (ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ ገጽ 23፡24)።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው “ሃይማኖት ቅድስት” የሚለውን የፈቱት “ምስጢረ ሥላሴ” እና “ምስጢረ ሥጋዌ” ብለው ነው። ይህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ማመንን እንዲሁም ሥግው ቃል በኾነው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ያመለክታል። ቅድስት ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ወጥታ ለሌላ የማትተርፍ የእግዚአብሔር የብቻው ገንዘብ ናት። “ቅድስት ሃይማኖት” የሚለውን ሐረግ የወሰዱትም ከይሁዳ መልእክት ቍጥር 20 ላይ “ወአንትሙሰ አኀዊነ ሕንጹ ርእሰክሙ በሃይማኖት ቅድስት…” ከሚለው የግእዙ ንባብ ላይ ነው፤ ዐማርኛው እንዲህ ይላል፦ “እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።” (ኪወክ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 369)።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ሃይማኖታችን ወይም እምነታችን ራሱ እግዚአብሔር ነው። በነቢዩ በኤርምያስ አፍ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን፥ ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ፥ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደረቅ ስፍራ ይቀመጣል። በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውሃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይኾናል።” (ኤር. 7፥5-8)።
ይህ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ እንደሚያሳየው ሰው ማመን ያለበት እግዚአብሔርን፣ መታመንም ያለበት በእግዚአብሔር ብቻ ነው እንጂ በሌላው እንደ እርሱ ባለው ፍጡር አይደለም። በፍጡር የሚታመን ከኾነ ግን ያ ሰው ልቡን ከእግዚአብሔር መመለሱ ነው፤ በዚህም ምክንያት ርጉም ይኾናል። በእግዚአብሔር የሚታመን እምነቱም እግዚአብሔር የኾነ ሰው ግን፣ የተባረከ ነው፤ ብዙ በረከቶችም ያገኙታል። ስለዚህ እምነት ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ የሚያገናኝ እንጂ ወደ ሌላ ፍጡር የሚተላለፍ ወይም በምስጋና፣ በውዳሴ፣ በአምልኮት ፈጣሪንና ፍጡራንን (ኹለቱንም) የሚያጫፍር (የሚያያይዝ) አይደለም። 
ሐዋርያው ጴጥሮስም ከከንቱ ኖሯችን የተዋጀነው በክቡር የክርስቶስ ደም መኾኑንና ይህም ዓለም ሳይፈጠር የታወቀ መኾኑን ጠቅሶ፣ አኹን ግን እምነታችንና ተስፋችን በእግዚአብሔር ይኾን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምናምን ስለ እኛ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ ይላል። (1ጴጥ. 1፥18-21)። በዚህ ውስጥ እምነታችን በእግዚአብሔር በመኾኑ ላይ ትኵረትና አጽንኦት ተሰጥቷል። 
በመጽሐፈ ምሳሌም፣ “እምነትህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ለአንተ ዛሬ እነሆ አስታወቅሁህ።” (ምሳ. 22፥19) ተብሎ ተጽፏል።
ደራሲም ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሃይማኖቴ ነህ ብሏል፤ (“ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖትየ ወንጌል” እንዲል መልክአ ኢየሱስ)።
ሃይማኖት በ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ እይታ
የመድሎተ ጽድቅ ጸሓፊም በመጀመሪያ ሃይማኖትን ሲያብራራ “ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠው መግለጥ ነው። ሃይማኖት የሰው ልጅ ሊቀበለው በሚችለው መጠን እግዚአብሔር ስለ ራሱ ማንነት የገለጠው እውነታ ነው። ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ያሳየበትና ወደ እርሱ ታደርሰን ዘንድ የሰጠን መንገድ ናት።” በማለት ትክክለኛውን የሃይማኖት ፍቺ ያቀረበ ሲኾን፣ “እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጠ፤ እኛ ደግሞ ተቀበልን።” ሲልም ሃይማኖትን ሰጪ እግዚአብሔር፣ ተቀባዮቹ ደግሞ ሰዎች መኾናቸውን የገለጸው ትክክል ነው። ይኹን እንጂ በሌሎቹ የመጽሐፉ ክፍሎች በዚህ ክፍል ያስቀመጠውን ይህን ብያኔና መርሕ ተከትሎና ጠብቆ አለመኼዱና ሰው ሠራሽ ትምህርቶችንና ሐሳቦችን ከእግዚአብሔር የተሰጡ አስመስሎ በሃይማኖት ውስጥ እንዲታዩ ማድረጉ በግልጽ ይስተዋላል። ይህንም ከዚህ ቀደም በተከታታይ ምላሽ በሰጠንባቸው ነጥቦች ውስጥ ማሳየታችንን ከጮራ ቍጥር 47 ጀምሮ የቀረቡትን ምላሾች በመመልከት አንባቢ ማገናዘብ ይችላል። ወደፊትም በቀጣዮቹ ዕትሞቻችን በመጽሐፉ ለቀረቡ ትችቶች በሚሰጠው ምላሽ ውስጥ፣ ስለ ሃይማኖት ትክክለኛውን ፍቺና ማብራሪያ የሰጠው የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ በተግባር ግን ከእግዚአብሔር ሃይማኖት ውጪ ላለና ከእርሱ ጋር ለሚጋጭ የሰው ትምህርት በሃይማኖት ውስጥ ቦታ ለማስገኘት መጽሐፍ ቅዱስን አለዐውዱ በመጥቀስና በተፋልሶ የተሞላ ማብራሪያ በመስጠት ብዙ መድከሙን እንመለከታለን።          
በተግባር ሲታይ በእርሱ ዘንድ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ብቻ የሚወሰን አይደለም። በአንድ በኩል “እግዚአብሔር የሰጣት አባቶቻችን ከእርሱ ተቀብለው ኖረውባት ለእኛ ያወረሱን ሃይማኖት ፍጽምትና አንድ ጊዜ የተሰጠች ናት ብልየት እርጅና የለባትም።” የሚለውን ይዘን “አባቶቻችን ከእርሱ ተቀብለው ኖረውባት ለእኛ ያወረሱን ሃይማኖት” በሚለው ሐረግ ውስጥ እርሱ የሃይማኖቱ መጻሕፍት ብሎ ቦታ ከሚሰጣቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ የኾነውን ተኣምረ ማርያምን እንመልከት። ወደ ኋላ ተመልሰን፣ “መቅደስ የገቡ መናፍቃን” የተሰኘው መጽሐፍ ተኣምረ ማርያምን አስመልክቶ ላቀረበው ተሐድሶኣዊ ሐሳብ “መድሎተ ጽድቅ” በገጽ 38 በተራ ቍጥር 4 ላይ “‘ተኣምረ ማርያምን ከወንጌል አብልጣ ታየዋለች’ ማለታቸው” በሚል ንኡስ ርእስ የሰነዘረውን ትችት እንደ ምሳሌ እንመልከት። “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ ምንም ሊነጻጸርና ሊወዳደር በማይችል መልኩ አክብራና አልቃ የምታምነው መጽሐፍ ቅዱስን ነው። ከዚህ ባሻገር ግን ሌሎች መንፈሳዊ መጻሕፍትን እንደ አግባብነታቸው ታከብራቸዋለች፤ ትጠቀምባቸዋለችም። ከእነዚህ መካ[ከ]ል አንዱ የእመቤታችንን ተኣምር የያዘው ተኣምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ ነው። ኾኖም ተኣምረ ማርያም ከወንጌል በላይ ይከበራል ማለት ሐሰት ነው።” ብሏል።
ወረድ ብሎም “እኛ ይህን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እምነት እየገለጽን ያለነው፣ ወደፊትም በጉዳዩ የምንገልጸውና ምስክር የምንጠቅሰው ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ትምህርት ስለኾነ እናንተም ከእነዚህ ምስክር አለን የምትሉ ከኾነ ማቅረብ እንጂ … ለግል ጸሎትና ለታሪክ እንዲሁም ይህን ለመሳሰለው ተግባር ያሉትን ነገሮች በመጥቀስ አይደለም።” ሲል እርስ በርሱ የሚጣረስ ሐሳብ አስፍሯል።
በቅድሚያ ጸሓፊው ለመጽሐፍ ቅዱስ የሰጠው ስፍራ ትክክልና የሚደነቅ ነው። ሌሎቹን መጻሕፍት ግን “እንደ አግባብነታቸው ታከብራቸዋለች፤ ትጠቀምባቸዋለችም” ነው ያለው። ይህም በራሱ ችግር ላይኖረው ይችላል። ለዚህ ምሳሌ አደርጎ የጠቀሰውን የተኣምረ ማርያምን ነገር ያነሣውም ተኣምረ ማርያም ከወንጌል በላይ እየተከበረ ነው የሚለውን በዐይን የሚታይ ጕዳይ ሐሰት ነው ብሎ ለማስተባበል ነው። ሲያስተባብልም “ተኣምረ ማርያም ከወንጌል በላይ ይከበራል ማለት ሐሰት ነው።” በማለት ብቻ ነው እንጂ ለማስተባበያው ያቀረበው ማሳያ የለም። በኢኦተቤ ተኣምረ ማርያም ያለውን ቦታ ላስተዋለ ግን፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ማስተባበያ ሐሰት ኾኖ ይገኛል።
ተኣምረ ማርያምን ከስሙ ጀምሮ ስንመለከት አግባብነት የለውም። በክርስትና ትምህርት ውስጥ “ተኣምር” የእግዚአብሔር ብቻ ሥራ ነው (መዝ. 71/72፥18፤ 135/136፥4)። ከእግዚአብሔር ውጪ እገሌ ተኣምር ሠራ የሚለው አነጋገርም ልማዳዊ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ክርስቲያናዊ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በእጁ ድንቅና ተኣምር የኾነለት ሰው፣ በአንድም ስፍራ እኔ ይህን አደረግሁ የሚል፤ በሌላውም የእግዚአብሔር ወገን እርሱ ተኣምር ሠራ ተብሎ የተነገረለትን ሰው አናገኝም፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተኣምር ሠሪ እግዚአብሔር ብቻ መኾኑን ያውቃልና። ደግሞም በቅዱሳኑ ዐድሮ ተኣምር ቢሠራ የተኣምሩ ባለቤት እግዚአብሔር እንጂ እግዚአብሔር የተጠቀመበት ፍጡር አለመኾኑን ጠንቅቆ ይገነዘባልና ክብሩን ለተኣምሩ ባለቤት ለእግዚአብሔር ብቻ ይሰጣል እንጂ፣ ቀንሶ ቀናንሶ ለተጠቀመበት መሣሪያ ለፍጡር አያጋራም። ባለማወቅ ክብሩን እናጋራችሁ የሚሉ ቢነሡ እንኳ ቅዱሳን አይቀበሏቸውም (ሐ.ሥ. 3፥11-12፤ 14፥9-18)። ሌሎች ግን ያልተገባቸውን ክብር ሰዎች ሲሰጧቸው በተቀበሉና ለክብር ባለቤት ለእግዚአብሔር ክብርን ባልሰጡ ጊዜ ተቀሥፈዋል (ሐ.ሥ. 12፥20-23)።
ቅዱሳኑ ሳይኾኑ “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው” (መዝ. 68፥35)። ስለዚህ ተኣምረ እግዚአብሔር ብቻ እንጂ ተኣምረ ማርያምም ኾነ በሌሎች ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ስም የሚጠራ ተኣምረ እገሌ ወእገሊት የሚባል ነገር በክርስትና ውስጥ ከቶ የለም። ከዚህ አንጻር ተኣምረ ማርያም አግባብነት ባለው መንገድ ሳይኾን ከአግባብ ውጪ በጥቅም ላይ እንደ ዋለ መረዳት ይቻላል። በዚህ መንገድ የፈጣሪ ሥራና ክብር ለፍጡር መዛወሩን ስንረዳ፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ “ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ያሳየበትና ወደ እርሱ ታደርሰን ዘንድ የሰጠን መንገድ ናት።” ያለውን ይዘን፣ እርሱ አለሁበት በሚለው ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውን “ተኣምረ ማርያም” የተባለውን ስያሜ ስንፈትሽ እንኳ፣ ተኣምር እግዚአብሔር የሚታይበት መኾኑ ይቀርና ማርያም የምትታይበት ኾኗል፤ የተኣምሩ ባለቤትም እግዚአብሔር ሳይኾን ማርያም ኾናለች። በዚህም ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ወጥታ ለሌላ የተረፈች በመኾኗ የእግዚአብሔር ብቻ ሃይማኖት መኾኗ በጥያቄ ውስጥ ይወድቃል።    
ጸሓፊው በተኣምረ ማርያም ምክንያት እሳት ወለደች እንደ ተባለችው ላሕም የኾነ ይመስላል። ምክንያቱም በአንድ በኩል እርሱም ኾነ ተኣምረ ማርያም ተቀባይ እንዳያጡ ተኣምረ ማርያምን እንደ አግባብነቱ እንጠቀምበታለን ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ተኣምረ ማርያምን ጠቅሰን እንዳንሞግተው “ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ትምህርት ስለኾነ እናንተም ከእነዚህ ምስክር አለን የምትሉ ከኾነ ማቅረብ እንጂ … ለግል ጸሎትና ለታሪክ እንዲሁም ይህን ለመሳሰለው ተግባር ያሉትን ነገሮች በመጥቀስ አይደለም።” በማለት በሩን ይዘጋል። ተኣምረ ማርያምን ይዞ መከራከርም ሽንፈትን እንጂ ድልን እንደማያስገኝለት ስለ ተረዳ ተኣምረ ማርያምን “ለግል ጸሎትና ለታሪክ እንዲሁም ይህን ለመሳሰለው ተግባር ያሉትን ነገሮች” ካላቸው ውስጥ መድቦታል። የተኣምረ ማርያም ምድብ ስፍራ ይህ ቢኾንም፣ በተግባር የሚታየው ግን እንደ ተባለው የወንጌልን ስፍራ ቀምቶ ነው።
ሌላም ማስረጃ እናቅርብ፤ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ከፍጡራን ባሕርይ ለይቶ ባስቀመጠበትና ባለፈው ዕትም ምላሽ በሰጠንበት ክፍል በኹሉ ስፍራ መገኘት (ምሉዕ በኵለሄነት) እና ኹሉን ዐዋቂነት (ማእምረ ኵሉ መኾን) የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቦች ብቻ መኾናቸው የታወቀ ነው። ስለዚህ ቅድስት ቤተርስቲያን ፈጣሪና ፍጡርን አሳምራ ለይታ የምታውቅ ናት እንጂፍጡራንን ከፈጣሪ እኩል ማድረግና ማስተካከልየሚለው አይመለከታትም።» (መድሎተ ጽድቅ ገጽ 38) ማለቱ ይታወሳል። ይህን ይዘን ባለፈው ዕትም ያላካተትነውንና ወደፊት በቦታው የምንመለስበትን ክፍል እዚህ ላይ ማሳያ አድርገን እናቅርብ።
በጮራ ቍጥር 38 ገጽ 17 ላይ “እንዲህ ያለውን ከአንድ ሰው ዕውቀት ውጪ የተሰወረውን ነገር መግለጥ የእግዚአብሔር ሥራ ነው እንጂ የሰው ነፍስ በራሷ ልትደርስበት የምትችለው ዕውቀት አይደለም። በሌላ በኩል ግን አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ሳለ ከእርሱ በኋላ የመጡትን ዘሮቹን እስራኤላውያንን እንደማያውቃቸው ተጽፏልና (ኢሳ. 63፥16) አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታ በምድር የሚደረገውን ኹሉ ያውቃል ማለት የሚታመን ቀርቶ የማይመስል ነው።” ለሚለው ሐሳብ ባቀረበው ተችት ውስጥ በገጽ 317 “አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።” (ኢሳ. 63፥16)” ለሚለው ጥቅስ የራሱን ማብራሪያ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል።
አብርሃም ባያውቀን ማለት አብርሃም አያውቀንም ማለት ነውን? በምን አገባብ ነው እንዲህ የሚኾነው? እንዲህ አድርጎ የተረጐመውስ ማነው?
“ይህን ቃል ለመረዳት በመጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መልኩ የተገለጹ ሌሎች ነገሮችን እንመልከት።” ይልና በትንቢተ ዳንኤል ሠለስቱ ደቂቅ አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤል የተናገሩትን ይጠቅሳል፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ አሉት።” (3፥16-18)።
“ሠለስቱ ደቂቅ ‘እርሱ ባያድነን’ ማለታቸው ‘እግዚአብሔር አያድነንም’ ማለታቸው ኖሯልን? በእነርሱ አተረጓጐም ከኼድን እነዚያን የእምነት ዐርበኞችና የጨለማ ዘመን ከዋክብት በእግዚአብሔር አዳኝነት የማያምኑ ሊያደርጓቸው ነውን? …
“እንደዚሁም ኹሉ አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ የሚለው ቃል አብርሃምና እስራኤል (ያዕቆብ) ሰዎች እንደ መኾናቸው ልጆቻቸውን ከማሰብና ስለ እነርሱ ከማሳሰብ ቢደክሙም እንኳ እግዚአብሔር ግን የኹሉም ዘለዓለማዊ አባት፣ የማይረሳና የማይተኛ ትጉህ እረኛ ስለ ኾነ መቼም መች የማይረሳቸው መኾኑን የሚያስረዳ አንጻራዊ (ንጽጽራዊ) አገላለጽ እንጂ በግድ ጠምዝዘው የማይለውን ይላል ለማለት እንደ ሞከሩት እንደ መናፍቃኑ ያለ ሐሳብ የሚናገር አይደለም። አብርሃምንማ ወደፊት ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚመጡትን ልጆቹን ኹሉ ‘ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ኾነ ቍጠር አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይኾናል’ በማለት አስቀድሞ አሳይቶት የለምን? (ዘፍ. 15፥5) …
“እስራኤል የተባለ ያዕቆብንም እንዲሁ ከእርሱ ስለሚወጡት ልጆቹ ነግሮታል። ያዕቆብ የነገዶች ኹሉ አባቶች ለኾኑት ለዐሥራ ኹለቱ ልጆቹ ለእያንዳንዳቸው ወደ ፊት በየዘመናት ኹሉ ስለሚኾኑት በምርቃት ዐይነት መልኩ የነገራቸው ልጆቹን ስለማያውቃቸው ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላልና፦ ‘ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፦ በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ። እናንት የያዕቆብ ልጆች ተሰብሰቡ፤ ስሙም፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ። …’ (ዘፍ. 49፥1-28)። ለዚህ ነበር በየዘመናቱ የተነሡት ልጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ሲጸልዩ ‘የአብርሃም፣ የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ’ እያሉ እግዚአብሔርን ይጠሩትና ይጸልዩ የነበረው” (ገጽ 317፡318)።
የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ እውነተኛ መርሕን ለመጥቀስ ያኽል የሚጠቅስ፣ ነገር ግን በዚያ መርሕ መሠረት መመራት የማይችል፣ እንደዚሁም ሐሰትን እውነት ለማድረግ የሚታገል መኾኑን ከዚህ በፊት ለማሳየት ሞክረናል። እዚህም ላይ እነዚሁ ነገሮች ጐልተው ወጥተዋል። ከመርሕ አንጻር የእግዚአብሔር ብቻ ባሕርይ ስለ ኾነው ኹሉን ዐዋቂነትና በኹሉ ስፍራ መገኘት ትክክለኛውን ነገር እንዲህ በማለት መግለጹን ጠቅሰናል፤ በኹሉ ስፍራ መገኘት (ምሉዕ በኵለሄነት) እና ኹሉን ዐዋቂነት (ማእምረ ኵሉ መኾን) የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቦች ብቻ መኾናቸው የታወቀ ነው።” ይኹን እንጂ አብርሃም ባያውቀን ማለት አብርሃም አያውቀንም ማለት ነውን? በምን አገባብ ነው እንዲህ የሚኾነው? እንዲህ አድርጎ የተረጐመውስ ማነው?” በማለት አብርሃም ይህን “የእግዚአብሔር ብቻ” ያለውን የኹሉን ዐዋቂነት ባሕርይ እንደሚጋራ አስመስሎ ጽፏል። ለመኾኑ “አብርሃም ባያውቀን” የሚለው አብርሃም ያውቀናል ተብሎ የሚተረጐመውስ በምን አግባብ ነው? እንዲህ ብሎ እንዲህ ብሎ የተረጐመውስ ማነው? ብለን ጥያቄውን መልሰን ለእርሱ እናቀርባለን።
ይህን ያስረዳልኛል ብሎ ለንጽጽር የጠቀሰው “እርሱ ባያድነን” የሚለውን የሠለስቱ ደቂቅን የእምነት ቃል ነው። “ባያውቀን” እና “ባያድነን” የተሰኙት ቃላት በቅርጽ ተመሳሳይ ናቸው፤ በተነገሩበት ዐውድና በዐውዱ መሠረት በሚሰጡት ፍቺ፣ እንዲሁም ቃላቱ በተነገሩላቸው ፍጡራንና ፈጣሪ መካከል የተለያዩ ናቸው። እንደ ተባለው ሠለስቱ ደቂቅ “እርሱ ባያድነን” አማልክትህን እንደማናመልክ፣ ላቆምኸውም ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ ማለታቸው፣ እግዚአብሔር አያድነንም ማለታቸው ሳይኾን፣ በሚነድደው እሳት ተቃጥለን እንሞት ዘንድ ቢወሰንም እንኳ ለአምላካችን ታምነን እንሞታለን እንጂ የአንተን አማልክት አናመልክም፤ አንሰግድላቸውምም ማለታቸው ነው። አምላካቸው እግዚአብሔር የሚያድን አምላክ መኾኑንማ አስቀድመው “የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥” ሲሉ በአጽንዖት ገልጠዋል። ስለዚህ “ባያድነን” የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን አዳኝነት ለመሻር የገባ ቃል አለ መኾኑ ግልጽ ነው።
ለአብርሃምና ለያዕቆብ የተነገሩት “ባያውቀን” እና “ባይገነዘበን” የሚሉት ቃላት ግን በቅርጽ “ባያድነን” ከሚለውና ለአምላክ ከተነገረው ቃል ጋር ቢመሳሰሉም፣ በዕውቀትና በመገንዘብ ውሱናን የኾኑት አብርሃምና ያዕቆብ በኢሳይያስ ዘመን እንዲህ ያሏቸውን ዘሮቻቸውን ያውቃሉ፤ ይገነዘባሉም የሚያሰኝ አይደለም። እንዴትስ ያውቃሉ? የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ለእነዚህ ቃላት የሰጠው ትርጕም እንደ ፎከረው ማወቃቸውን የሚያስረዳ ኾኖ አልተገኘም። “አብርሃምና እስራኤል (ያዕቆብ) ሰዎች እንደ መኾናቸው ልጆቻቸውን ከማሰብና ስለ እነርሱ ከማሳሰብ” መድከማቸውን የሚያሳዩ ቃላት ናቸው የሚል ነው። መቼም ያንቀላፉ ቅዱሳን በዕረፍት ውስጥ እንጂ በድካም ውስጥ እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ስለዚህ ከማሰብና ከማሳሰብ መድከማቸውን ያሳያል የተባለው ኹሉን ዐዋቂነታቸውን የማያሳይ ከመኾኑም በላይ ሌላ ጥያቄን የሚፈጥር እንጂ ተገቢ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም።
አንድ መታወቅ ያለበት እውነት አንዱ ስለ ሌላው ሲጸልይ፣ የሚጸለይለት ሰው የሚያውቅበት መንገድ የለም። እንዲያውቅ ካስፈለገ ጸላዩ ሰው ለሚጸልይለት ሰው እንደሚጸልይለት ሊነግረው፣ ወይም ይህን ከሚያውቁ ሌሎች ሰዎች ሊሰማ፣ ወይም እግዚአብሔር እንደሚጸልይለት ሊገልጥለት ይገባል። ከዚህ አንጻር አብርሃምና ያዕቆብ በዐጸደ ነፍስ ኾነው ለትውልዳቸው ማሳሰባቸውን፣ እንዲሁም ከማሳሰብ መድከማቸውን የሚያውቅ ማንም የለም። ባልታወቀ ነገር ላይ እርግጠኛ ኾኖና ያን አስተምህሮ አስመስሎ መናገር ደግሞ ትልቅ ድፍረት ነው። ጸሓፊው  ቃሉ ወደማይለው ወደዚህ ትርጓሜ የገባው የተሳሳተውን አስተምህሮውን በእግዚአብሔር ቃል ከማረም ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል ለተሳሳተው አስተምህሮው መሸፈኛ አድርጎ ለመጠቀም በመታገሉ ነው። ለመኾኑ “ባያውቀን” እና “ባይገነዘበን” የሚሉት ቃላት እንዴት ተደርገው ቢጠመዘዙ ነው “ከማሳሰብ መድከም” የሚል ትርጕም የሚሰጡት?
እንዲህ አድርጎ የቃሉን ቀጥተኛ ትርጕም እርሱ በሚፈልገውና ከኪሱ ባወጣው ትርጕም ቃሉን ለማዛባት ከሞከረ በኋላና መንገዱን የጠረገ ሲመስለው፣ አብርሃምና ያዕቆብ እነርሱ ካንቀላፉ በኋላ የተነሣውን ትውልዳቸውን የሚያውቁ መኾኑን ይናገርልኛል ያለውን “ማስረጃ” እንዲህ በማለት ያቀርባል። “ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚመጡትን ልጆቹን ኹሉ ‘ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ኾነ ቍጠር አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይኾናል’ በማለት አስቀድሞ አሳይ  ቶት የለምን?” (ዘፍ. 15፥5)። ለመኾኑ ይህ ጥቅስ አብርሃም ወደ ፊት የሚነሣውንና ከብዛቱ የተነሣ ሊቈጠር የማይችለውን ዘሩን ኹሉ ያውቃል የሚያሰኝ ነውን? በፍጹም አይደለም። እንዲያውም እግዚአብሔር የአብርሃምን ውሱንነት በሚገልጽ ቃል “ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ኾነ ቍጠር” አለው በማለቱ ይታወቃል። መቍጠር ያልቻለውን ታዲያ እንዴት ያውቃል ይባላል? ለዚህ ነው ቃሉ “አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።” የሚለው (ኢሳ. 63፥16)።     
ያዕቆብንም በተመለከተ እንዲህ ብሏል፤ እርሱ ልጆቹን ወደ ፊት “… ስለሚኾኑት በምርቃት ዐይነት የነገራቸው ልጆቹን ስለማያውቃቸው ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላልና፦ ‘ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፦ በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ።” ያዕቆብ ከአብራኩ የተከፈሉትንና የመረቃቸውን ልጆቹን ማወቁ ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። በኋለኛው ዘመን የሚያገኛቸውን በምርቃት መልክ ብቻ ሳይኾን በትንቢት መልክ መናገሩም በቃሉ ውስጥ የተመዘገበ እውነት ነው (ዘፍ. 49)። እዚያ ላይ የሚነሣ ጥያቄ የለም። ጥያቄው እርሱ ካንቀላፋ በኋላ የሚመጣውን ትውልዱን ያውቃል የሚለው የተሳሳተ ትምህርት ላይ ነው እንጂ። እንደሚታወቀው ያዕቆብ በዚህ ምድር ሳለ የማያውቃቸውና ከዚህ የተነሣ የተታለለባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰከራል። ለመጥቀስ ያኽል፦ ስለ ራሔል ላባን ሰባት ዓመት አገልግሎ ሚስት እንድትኾነው የሰጠው ልያን መኾኑን ግን አላወቀም ነበር (ዘፍ. 29፥25)። ራሔል የአባቷን አማልክት ሰርቃ መደበቋን አላወቀም ነበር (ዘፍ. 31፥32)፣ ሲታገለው ያደረው ሰው ማን እንደ ኾነ አላወቀም ነበርና ስምህ ማነው? ሲል ጠየቀው (ዘፍ. 32፥27)። ይኸው ያዕቆብ ካንቀላፋ በኋላ በቀጣይ ትውልዱ ላይ የሚኾነውንና የሚደረገውን የሚያውቅበት ዕድል የለውም።
በአጠቃላይ ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ወጥቶ በአክብሮት ስም ለፍጡራን የሚተርፍና የሚጋራ ከኾነ ያ ሃይማኖት የእግዚአብሔር ነው፤ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነው ማለት አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ቅዱሳን እንዲኖሩባትና እንዲታነጹባት አንድ ጊዜ የተሰጠችው ሃይማኖት እግዚአብሔር ብቻ የሚታመንባት፣ እርሱ ብቻ የሚመለክባት፣ እርሱ ብቻ የሚከብርባት ናት። ቅዱሳን መላእክትና ሰዎች ይህን ሃይማኖት ተቀብለው እግዚአብሔርን ከማመንና ከማምለክ በቀር፣ በ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ አብርሃምና ያዕቆብ በዐጸደ ነፍስ ከእነርሱ በኋላ የመጣውን ትውልዳቸውን ኹሉ ያውቃሉ እንደ ተባሉት፣ ደረጃ ወጥቶላቸው በአክብሮት ስም እነርሱም የሚታመኑበት፣ የሚመለኩበትና ክብርን የሚወስዱበት ልትኾን ከቶ አትችልም።
በመጨረሻም የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ መልእክቶችን እያዛባ ማቅረብ አንዱ መገለጫው መኾኑን ማሳየት ይገባል። ከላይ ማብራሪያ በሰጠንበትና “ሃይማኖት ምንድነው?” በሚለው ንኡስ ርእስ ሥር መጨረሻ ላይ፣ ከቅዱስ አትናቴዎስ ጽሑፍ በእግርጌ ማስታወሻ በእንግሊዝኛ የጠቀሰውና በጽሑፉ አካል ውስጥ ደግሞ በዐማርኛ ተርጕሞ ያቀረበው ጥቅስ አለ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ የቃል ትርጕም መዛባት ይታያል።
(ከመጽሐፉ ስካን ተደርጎ ይገባል)
እዚህ ላይ እንደሚታየው በእንግሊዝኛው “… Thus the Catholic Church believes …” በሚል የሰፈረው ንባብ “…ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ታምናለች...” በማለት አለንባቡ ተተርጕሟል። “ካቶሊክ” የሚለውን ቃል “ኦርቶዶክስ” ብሎ መተርጐም ግን የመዝገበ ቃላትም ኾነ የታሪክ ድጋፍ የለውም።
“ካቶሊክ” የሚለውን የቤተ ክርስቲያን መገለጫ የኾነ ስም የሮም ቤተ ክርስቲያን የግል መጠሪያዋ ብታደርገውም፣ መጀመሪያ ላይ ቃሉ ጥቅም ላይ የዋለው ቤተ ክርስቲያን በኹሉ ዘንድ ያለች መኾኗን ለማመልከት ነው። የኪዳነ ወለድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት “ኮቶሊክ” (በጽርዕ ካቶሊክ) የሚለውን ቃል የሚፈታው “የቤተ ክሲያን ስም፣ ኵላዊ ዘኵሉ እንተ ላዕለ ኵሉ” በማለት ነው (ገጽ 552)። ቅዱስ አትናቴዎስም ቃሉን የተጠቀመው ይህን የቤተ ክርስቲያን ማንነት መሠረት በማድረግ ነው። እርሱ በኹሉ ዘንድ ያለች ቤተ ክርስቲያንን በሚወክል አገላለጽ ያቀረበውን መልእክት ታዲያ፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ የአትናቴዎስን ሐሳብ በመለወጥና የእርሱን ስመ ሃይማኖት ወደሚገልጠው መጠሪያ ለውጦ በመተርጐም መልእክቱን አዛብቶታል። ጸሓፊው እዚህ ኹሉ ጥፋት ውስጥ የገባው “ካቶሊክ” የሚለውን ስም ላለመጠቀም ወይም ለመሸሽ ሲል እንደ ኾነ ግልጽ ነው። በዚህ ተግባሩም በትርጕም ሥራ ላይ ታማኝነትን አጕድሏል፤ የቅዱስ አትናቴዎስንም መልእክት አዛብቷል። በሃይማኖት ላይ መጨመርም ኾነ መቀነስ አይገባም ሲል ብዙ የለፈፈው የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ራሱ ለግል ዐላማው ሲል የአትናቴዎስን መልእክት በትርጕም ስም አዛብቷል።      
ይቀጥላል!

1 comment: