Sunday, September 7, 2014

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

ትረካ፡- ከነቅዐ ጥበብ

በቅርቡ ወደ ርእሰ ሕይወት መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የጕዞ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ለብዙ ዓመታት በተከፈለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ከተለያዩ የስሕተት ትምህርቶችና ከመናፍስት አሠራሮች ነጻ የወጣና ምንም ያልተቀላቀለበት ንጹሕ ወንጌል የሚሰበክበት፣ ያልተቀያየጠ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት ደብር ነው፡፡ ደብሩን የሚያውቁት በዚያ ያሉ ወንድሞችንና እኅቶችን ለመጐብኘትና ከእነርሱ ጋር መንፈሳዊ ነገርን ለመከፋፈል÷ ዝናውን የሰሙት ደግሞ የተባለው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የጕዞው እድምተኞች ሆነዋል፡፡
  
አለቃ ነቅዐ ጥበብና ከደቀ መዛሙርቶቻቸው ጥቂቶች÷ እንዲሁም ወደ ስፍራው ለመሄድ የተዘጋጁ ሌሎች ወገኖችም ማልደው በስፍራው ተገኝተዋል፡፡ ወደሚጓዙበት አውቶቡስ ከገቡ በኋላ ጕዞ ከመጀመሩ በፊት÷ ቀሲስ ፍሬ ጽድቅ ጕዟቸውን ለታመነው ፈጣሪ ለእግዚአብሔር በጸሎት ዐደራ ሰጡና ጕዞው ቀጠለ፡፡