Monday, May 22, 2017

የዘመን ምስክር



 READ PDF
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዘኵሎን አድያማተ ትግራይ (1887 - 1983 ..)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተከሥተውና በርካታ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተው ካለፉ ታላላቅና ስመ ጥር አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ተጠቃሽ ናቸው። እኒህ አባት በእምነታቸው የጸኑ፣ በመልካም ሥራቸው የተመሰከረላቸው፣ በትምህርታቸው ብሉያትንና ሐዲሳትን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን በሚገባ የተረዱ፣ በስብከታቸው፣ በተደማጭነታቸው የሚታወቁ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ላመኑበት እውነት ብቻቸውንም ቢኾን የሚቆሙ፣ በፈሊጥና በጥበበ ቃል የማይረሳና ጠንካራ መልእክት ማስተላለፍ የቻሉ፣ ማንንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ የተረዱትን እውነት በሚገባ በመስበክ የኖሩ መምህር ወመገሥጽ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልትሻሻልና ትውልዱን ልትታደግ የምትችለው በትምህርት ብቻ መኾኑን ያመኑ፣ አምነውም በትምህርት ላይ ብዙ የሠሩ ታላቅ አባት ነበሩ። የሕይወት ታሪካቸውና ሕያው ሥራዎቻቸው እነሆ፣  


ልደት እድገት እና ትምህርት
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ከቄስ ገብረ ኢየሱስ ፈቃዱና ከወ/ሮ (በኋላ እማሆይ) ወለተ ኢየሱስ ምሕረተ አብ ሐምሌ 12 ቀን 1887 ዓ.ም. ኤርትራ ውስጥ በአካለ ጕዛይ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ኩርባርያ በተባለ አጥቢያ ተወለዱ። በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሲጠመቁም ገብረ መስቀል ተባሉ። በዚህ ስመ ክርስትና ጳጳስ እስከ ሆኑ ድረስ ተጠርተዉበታል። ወላጆቻቸው የወለዷቸው በስእለት ስለ ነበር፣ በተወለዱ በሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜያቸው በአካባቢያቸው ወደሚገኝ የአቡነ ብፁዕ አምላክ ሥላሴ ገዳም ወስደው ለማኅበረ መነኮሳቱ ሰጧቸው። ማኅበረ መነኮሳቱም ወላጆቻቸው በእምነታቸው መሠረት የገቡትን ቃል መፈጸማቸውን በማድነቅና በማመስገን፣ እስከ ስድስት ዓመት ድረስ እዚያው በቤታቸው እንዲያሳድጓቸው በመምከር አሰናበቷቸው። ስድስት ዓመት ሲሞላቸውም አምጥተው አስረከቧቸውና ከንባብ ትምህርት እስከ ግብረ ዲቁና ያለውን ተምረው በዘጠኝ ዓመታቸው የዲቁና ማዕርግ ተቀበሉ።