Sunday, January 15, 2023

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

READPDF

(ሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 39፥ በአለቃ ነቅዐ ጥበብ ዐምድ ውስጥ የቀረበው ትረካ ማጠንጠኛ የነበረው ሐሳብ “ያለ ወላዲተ አምላክ አማላጅነት ዓለም አይድንም” የሚለው ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ነበር። ከሰሞኑ ይህን ጥቅስ አስመልክቶ መምህር ያረጋል አበጋዝ፥ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያልኾነ ወፍዘራሽ ትምህርት መኾኑን ገልጦ ሲናገር ከማኅበራዊ ሚዲያ አድምጠናል። የስሕተት ትምህርቱ በርሱም ዘንድ ስሕተትነቱ በመገለጡ፥ እውነት ፍሬ ማፍራቱን እንድንረዳና ጌታን እንድናመሰግን ምክንያት ኾኖኗል። ከዛሬ 13 ዓመት በፊት የወጣውን ዘለግ ያለ ጽሑፍ እንድታነብቡት ጋብዘናል።)

ትረካ

በቅርቡ ወደ ርእሰ ሕይወት መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የጕዞ መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ለብዙ ዓመታት በተከፈለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ከተለያዩ የስሕተት ትምህርቶችና ከመናፍስት አሠራሮች ነጻ የወጣና ምንም ያልተቀላቀለበት ንጹሕ ወንጌል የሚሰበክበት፣ ያልተቀያየጠ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት ደብር ነው፡፡ ደብሩን የሚያውቁት በዚያ ያሉ ወንድሞችንና እኅቶችን ለመጐብኘትና ከእነርሱ ጋር መንፈሳዊ ነገርን ለመከፋፈል÷ ዝናውን የሰሙት ደግሞ የተባለው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የጕዞው እድምተኞች ሆነዋል፡፡

አለቃ ነቅዐ ጥበብና ከደቀ መዛሙርቶቻቸው ጥቂቶች÷ እንዲሁም ወደ ስፍራው ለመሄድ የተዘጋጁ ሌሎች ወገኖችም ማልደው በስፍራው ተገኝተዋል፡፡ ወደሚጓዙበት አውቶቡስ ከገቡ በኋላ ጕዞ ከመጀመሩ በፊት÷ ቀሲስ ፍሬ ጽድቅ ጕዟቸውን ለታመነው ፈጣሪ ለእግዚአብሔር በጸሎት ዐደራ ሰጡና ጕዞው ቀጠለ፡፡