"መድሎተ ጽደቅ" በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን
ክፍል አራት
ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዕትሞች “መድሎተ ጽድቅ” ለተሰኘው መጽሐፍ ምላሽ ስንሰጥ መቈየታችን ይታወሳል። በዚህ ዕትምም ካለፈው ለቀጠለውና በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ጽሑፍ ላይ ለተሰነዘረው መሠረተ ቢስ ትችት ምላሽ መስጠታችንን እንቀጥላለን።
በዚህ ዕትም በ “መድሎተ ጽድቅ” ገጽ 42 ላይ የሚገኘውና በተራ ቍጥር
1.3.3. ላይ፣ “ከእምነት ይልቅ በስሜት ሕዋሳት (በማየት፣ በመስማት፣ …) ላይ መመሥረት” በሚለው ንኡስ ርእስ ሥር ለተጠቀሱት እንዲሁም በ “1.1.4 ተገቢ ያልኾኑ አባባሎችንና ጸያፍ አገላለጾችን መጠቀም” በሚለው ንኡስ ርእስ ሥር ለቀረበው ሐሳብ ከዚህ እንደሚከተለው ምላሽ እንሰጣለን፦
በመጀመሪያው ንኡስ ርእስ ሥር የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ለመተቸት የተጣጣረው፣ “አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታ በምድር የሚደረገውን ኹሉ ያውቃል ማለት የሚታመን ቀርቶ የማይመስል ነው።” (ጮራ ቍ. 38 ገጽ 17) የሚለውን ሐሳብ ነው።