እውን ኢየሱስ (ሎቱ ስብሐት) “ሰይጥኗልን?”
መግቢያ
በየዘመኑ ኑፋቄንና ልዩ ወንጌልን የሚያስተምሩ ሰዎች በዋናነት ሐሳባቸው የሚያጠነጥነው የእውነተኛው ወንጌል ማእክል በኾነው
በክርስቶስና በማዳን ሥራው ላይ ነው። ከክርስቶስና ከመስቀሉ ሥራ ላይ ዐይንን ማንሣት በቤተ ክርስቲያን፣ በአገር፣ በትውልድ፣ በቤተ
ሰብ … ላይ የሚያመጣውን ድንዛዜ ዲያብሎስ በትክክል ያውቃል። ስለዚህ በየዘመናቱ ተመሳሳይ ክሕደቶችን ዘመን ቀመስ በማድረግና ከሰዎች
ፍላጎት ጋር በማስተሳሰር፣ ይዘታቸውን በመለዋወጥና ሰፋ በማድረግ ሲያመጣ እናስተውላለን።
የስሕተቶቹ መልካቸውና ምንጫቸው ከኹለት አቅጣጫ ሊታይ ይችላል፤ የመጀመሪያው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጽሐፍ ቅዱስ
የሚናገረውን በትክክል ካለማጥናት ሲኾን፣ ኹለተኛው ደግሞ ሰውን ማእከል ያደረገውና የተዛባው የስሕተት ትምህርታቸው፣ የጌታችን የኢየሱስ
ክርስቶስን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ኾኖ ስለሚገኝ፣ ይህ እርሱን ያለመውደድ ውጤት ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ስለዚህም ስሕተታቸውን
ስንቃወምና ኹለተኛውን ሐሳብ ለማፍረስ ስንሠራ፣ የዋሃንንና ባለማስተዋል የሳቱትን በርኅራኄ ለመመለስና ለማቅናት ደግሞ የፊተኛውን
ሐሳብ እንይዛለን።
ዛሬ በኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከሚታመሱባቸው የስሕተት ትምህርቶች መካከል “የእምነት እንቅስቃሴ” አንዱ
ነው። ይህ የስሕተት ትምህርት በ1980ዎቹ ብቅ ብሎ በጊዜው ብዙ ትርምስ ፈጥሮ፣ በኋላ ላይ ከስሞ እንደ ነበር የሚታወስ ነው።
ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ግን እንደ ገና በማንሠራራት ወደ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ተመልሶ ቤተ ክርስቲያንን እያወከ ይገኛል።