ባለፈው ዕትም ስለ መካከለኛነቱ
ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን፥ በተግባርም እየጸለየ፣ እየለመነና እየማለደ ያሳየውን፥ በዝርዝር ተመልክተናል። አብም፣
ወልድም፣ መንፈስ ቅዱስም ይማልዳሉ የሚል ንባብ በመጽሐፍ ቅዱስ አለና፥ ሦስቱም ይማልዳሉ ከተባለ ወደ ማን ነው የሚማልዱት? በሚል
አንዳንዶች ለሚያነሧቸው ክርክሮችም መልስ ለመስጠት ተሞክሯል።
የዚህን ትምህርት እውነተኛነት
ለማረጋገጥ ከራሱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በላይ ማንም ሊናገር አይችልም። ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይም ሌላ ምስክር አይኖርም። ይሁን
እንጂ ይህ ጌታችን ያስተማረው፣ ሐዋርያትም ከእርሱ ተቀብለው ያስተላለፉት እውነተኛ ትምህርት፥ ከእነርሱ በኋላ በተነሡ አበው ዘንድም
የታወቀ መሆኑን ማሳየት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ይህን የምናደርገው የእነዚህ አበው ምስክርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተመዘገበው የጌታችን
ትምህርት፣ ከእርሱ ተቀብለው ሐዋርያት ከሰጡትም ምስክርነት የሚበልጥ ምስክር ሆኖ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የዐዲስ ኪዳን ብቸኛ
መካከለኛ ነው የሚለው ትምህርት “እንደ ውሃ ፈሳሽ፣ እንደ እንግዳ ደራሽ” በድንገት ብቅ ያለ ዐዲስ ትምህርት ሳይሆን፣ ከጥንት
የነበረ፣ በአበውም ትምህርት ውስጥ በስፋት የተንጸባረቀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መሆኑን ለማሳየትም ጭምር ነው።