Sunday, March 9, 2014

ክርስትና በኢትዮጵያ


የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ
ከነቅዐ ጥበብ
ካለፈው የቀጠለ

Read In PDF

ፍሬምናጦስ  በሐዋርያዊ ስብከቱ ለመሠረታት ለማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ካከናወናቸው ዐበይት ሥራዎች ጥቂቱን ባለፉት ዕትሞች ተመልክተናል፡፡ በረጅም ዓመታት ጕዞ ውስጥ የሚታዩና የማይታዩ መሰናክሎችን ዐልፋ ከእኛ ዘንድ በደረሰችው የእግዚአብሔር መንግሥት ምክንያት ባለውለታችን የሆነው ሐዋርያ በአሁኑ ጊዜ ስንት የሥራው መታሰቢያዎች በስሙ ተመዝግበው እንደሚገኙ በተጠየቅን ጊዜ እኛም ጠይቀን የተሰጠንን መልስ ለጠያቂዎቻችን ነግረናል፡፡ ሆኖም አላረካቸውም፡፡ ጠያቂዎቹ ከትምህርት ተቋማት፥ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፥ ከመሰብሰቢያዎች (አደባባዮች) ከሐውልቶች፥ ከመንገዶች… ጥቂቱ ስሙ የሚጠራባቸውና ሥራው የሚታሰብባቸው ቢሆኑ አይበዛበትም ባዮች ናቸው፡፡ አሁን ግን የዚህኑ የደገኛውን ሐዋርያ ሥራ መግለጹን እንቀጥላለን፡፡

ስምንተኛ - ኤጲስ ቆጶስ መሾም

የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነቱንና ጌትነቱን ለአይሁድም ለአረማውያንም ከሰበከ በኋላ፥ አማኞችን አሰባስቦ “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” በሚል መጠሪያ ክርስቲያናዊ ድርጅቱን እንዳቋቋመ፥ በኋላም ከምእመናን መካከል በቅዱስ መጽሐፍ ላይ በመሠረተው ትምህርተ ሃይማኖት የላቀ ዕውቀት ያላቸውን እንደየጸጋ ስጦታቸው ዲያቆናት፥ ጸሐፍት፥ ቀሳውስት በሚል የሥራ ደረጃ እንደ መደበ ተመልክተን  ነበር፡፡