Read PDF
ካለፈው የቀጠለ
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 2 ላይ የቀረበ
ማስረጃ 2
በኦሪት ዘፍጥረት 1፥26 “ኤሎሂም (አማልክት) በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ሰውን እንፍጠር አለ፤” ተብሏል፡፡ ተናጋሪው በአንድ አካል “ኤል” ራሱን አልገለጸም፡፡ የብዙ ቊጥር መግለጫ በሆነው ስም “ኤሎሂም (አማልክት)” ራሱን የገለጸው ይሆዋ ነው፡፡
“እንፍጠር” የሚለውም ውሳኔ ብዛትን ከሚያመለክተው የአረፍተ ነገሩ ባለቤት ከሆነው “ኤሎሂም” (አማልክት) ጋር ይስማማል፡፡ ሆኖም “ኤሎሂም” (አማልክት) እንፍጠር በማለት ያሳለፉትን ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስ ለኛ ሲያስተላልፍ በአንድ ይሆዋነት የሚታወቁ አካላት መኖራቸውን ለማስረዳት በመፈለጉ እንፍጠር አሉ ሳይል “እንፍጠር አለ” ይለናል፡፡ አገላለጹ ሚዛናዊ ልብ ላለው ሰው ብዛትንና አንድነትን ሊያስተምር ይችላል፡፡