Monday, January 23, 2012

መሠረተ እምነት

Read PDF
ካለፈው የቀጠለ
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 2 ላይ የቀረበ
ማስረጃ 2

በኦሪት ዘፍጥረት 1፥26 “ኤሎሂም (አማልክት) በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ሰውን እንፍጠር አለ፤” ተብሏል፡፡ ተናጋሪው በአንድ አካል “ኤል” ራሱን አልገለጸም፡፡ የብዙ ቊጥር መግለጫ በሆነው ስም “ኤሎሂም (አማልክት)” ራሱን የገለጸው ይሆዋ ነው፡፡

“እንፍጠር” የሚለውም ውሳኔ ብዛትን ከሚያመለክተው የአረፍተ ነገሩ ባለቤት ከሆነው “ኤሎሂም” (አማልክት) ጋር ይስማማል፡፡ ሆኖም “ኤሎሂም” (አማልክት) እንፍጠር በማለት ያሳለፉትን ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስ ለኛ ሲያስተላልፍ በአንድ ይሆዋነት የሚታወቁ አካላት መኖራቸውን ለማስረዳት በመፈለጉ እንፍጠር አሉ ሳይል “እንፍጠር አለ” ይለናል፡፡ አገላለጹ ሚዛናዊ ልብ ላለው ሰው ብዛትንና አንድነትን ሊያስተምር ይችላል፡፡አርዮሳውያን ግን እንፍጠር አለ ብሎ መናገሩ ምድራውያን አስተዳዳሪዎች እኛ በማለት እንደሚናገሩ ዐይነት ይሆዋም በዙፋኑ ከሚታቀፉት ፍጥረታት ጋር እንፍጠር ሲል ምክክር ማድረጉን ያስተምሩናል፡፡ አባባላቸውን ላለመቀበል ከዚህ በታች የተጻፈው ምክንያታዊ ግድግዳ ይከለክለናል፡፡

ሀ. በዙፋኑ የሚተዳደሩትን እንደ መላእክት ያሉትን እንፍጠር ብሎ ማማከርና ፈቃደኛነታቸውን ማግኘት ለይሆዋ ቢያስፈልገውና መላእክትም በመፍጠር ተግባር ተሳትፈው ቢሆን ኖሮ መላእክት ለፈጣሪ ብቻ የሚገባውን አምልኮት እንዳይጋሩ ባልተከለከሉ ነበር፤ (ቈላ. 2፥18፤ ራእ. 19፥9፡10፤ 22፥8፡9)፡፡ (በሰማይ ያሉ በምድር ያሉና ከምድርም በታች ያሉ ፍጥረታት ሁሉ በአምልኮት ለይሆዋ እንዲገዙ እንጂ ራሳቸው አምልኮት እንዳይቀበሉ ተከልክሎአልና) ዘዳ. 5፥8 ከፊል. 2፥10 እና ራእ. 5፥3፤ 13፥14 ጋር ይመሳከር፡፡
ለ. ኤሎሂም /አማልክት/ የሆነው ይሆዋ ሰውን ለመፍጠር ባሳለፈው ውሳኔ ውስጥ፡-
1ኛ. እንደ መልካችን
2ኛ. እንደ ምሳሌያችን (በምሳሌያችን)
ተብሎ በተነደፈው ዕቅዱ መሠረት ሰውን በመልኩና በምሳሌው ፈጠረው፡፡ በመልካችን የሚለውን ቃል ብቻ የይሆዋ መልክ እውነትና ቅድስና እውቀት … ነውና በዚህ ራሱን አስመስሎ ፈጠረው በማለት አርዮሳዊ ለመወሰን ይገደዳል፡፡ እንደ ምሳሌችን የሚለውን ሐረግ ሳይተረጉመው ማለፍ ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ያለ ምክንያት አይደለም፤ በብዙ ጥር ኤሎሂም ለተባለው አንዱ ይሆዋ መግለጫ የሆኑት ምሳሌዎቹ ምንድር ናቸው? በእነርሱስ ሰው ኤሎሂምን ሊመስል እንዴት በቃ ማለትን ስለሚያስከትልበት አይደለምን? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለአርዮሳዊ ትምህርት አይበጀውም፡፡ ጒዳዩ እንዲህ ነው፡-

ወንጌላዊ ዮሐንስ ቃል አስቀድሞ ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ … ሁሉ በእርሱ ሆነ … ቃልም ሥጋ ሆነ ይለናል፤ ዮሐ. 1፥1-14፡፡

በእግዚአብሔር ዘንድ ከዘለዓለም እግዚአብሔር ሆኖ የኖረውን ወልድን ወንጌላዊው “ቃል” ብሎታል፡፡ ቃል የተባለው ወልድም ከአብ ነው የወጣሁት ሲል ራሱን ያስተዋውቀናል (ዮሐ. 3፥1-3፤ 8፥42፤ 16፥28)፡፡

እንግዲህ ወልድ በቃል ከዊን (ቃል በመሆን) ከተገለጸ፥ የነበረው በአብ ዘንድ ሆኖ የወጣውም ከአብ መሆኑ ከተረጋገጠ፥ አብም ወልድን በቃልነቱ ከዊን ካወጣው፥ ቃልን ሊያወጣው የቻለ አብ ራሱ በምን ከዊን ሊገልጽ ቢችል ነው? የሚለውን ጥያቄ ያፈልቃል፡፡ ለጥያቄውም ከእግዚአብሔር ቃል መልስ መገኘት አለበት፡፡ ለጥያቄውም መልስ ይሆነን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ከልብ እንደሚወጣ ያስተማረንን እናስታውሳለን (ማቴ. 12፥34፤ 15፥18)፡፡ ቃልን ያወጣ የአብ መግለጫ ከዊን “ልብ” መሆኑን ነግሮናል ማለት ነው፡፡

በቃል ከዊን የተገለጸውን ወልድን የአብ ልጅ ያሰኘው፥ ሰው በሚያውቀው የልደት ሥርዐት አብ ስለ ወለደው እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ቃል ከልብ በሚወጣበት አወጣጥ /ፀአት/ ዐይነት በልብ ከዊን ከሚታወቀው አብ ከዘለዓለም በመውጣቱ ወልድ ተሰኝቶአልና (ሚክ. 5፥2) “አወጣጡ ከጥንት ለዘለዓለም ነው፡፡” ቃል ከልብ እንደሚወጣ /እንደሚወለድ/ ወልድ ከአብ ወጣ የተባለበት አወጣጥ ልደት ተሰኝቶ ቃልን ወልድ አሰኘው ማለት ነው፡፡

ልብ ቃልን እንደሚያወጣ አየን፡፡ ሌላ የሚያወጣው አለን? ቢባል፥ አዎን፥ ሕይወትን (እስትንፋስን ወይም መንፈስን) ያወጣል የሚል መልስ ሊኖር ይገባል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ልብ የሕይወት መውጫ ነው ተብሏልና (ምሳ. 4፥23)፡፡

በዚህ ትይዩ የይሆዋ ሕይወት የሆነው መንፈስ ቅዱስ የወጣው /የሠረጸው/ በልብ ከዊን ከሚታወቀው ከአብ እንደ ሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ “ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ” ይላል (ዮሐ. 15፥26)፡፡

እንግዲህ አብ በልብ ከዊን (ልብ በመሆን) በመታወቁ በቃል ከዊን የሚታወቀውን ወልድን አወጣ፡፡ በሕይወት ከዊን /ሕይወት በመሆን/ የሚታወቀውን መንፈስ ቅዱስን አወጣ (አሠረጸ)፡፡

ከዚህ ገለጻ እንደምንረዳው ኤሎሂም (አማልክት) የተባለው አንዱ ይሆዋ፡-
1.      አብ፥ ቃልንና ሕይወትን አወጣ (እና አሠረጸ) በተባለበት ከዊን መግለጫው  ልብ
2.     ወልድ፥ ቃል ከልብ እንደሚወለድ (እንደሚወጣ) ከአብ ወጣ በተባለበት የከዊን መግለጫው  ቃል
3.     መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ከልብ እንደሚወጣ ከአብ ወጣ በተባለበት የከዊን መግለጫው ሕይወት ነው ማለቱ ግልጽ ይሆናል፡፡
ይህ የመሆን (የኩነት) ሦስትነት አንድነትን የሚያስከትል ስለሆነ በኤሎሂምነት ራሱን የገለጸው ይሆዋ አንድ ነው ሊባል ተገባ፡፡
የጨበጥነውን ግንዛቤ እንደ ያዝን ወደ ኦሪት ዘፍጥረት 1፥26 ስንመለስ፥ ሰው ከዚህ በላይ ዘርዘር ተደርጎ እንደ ተገለጸው የኤሎሂምን መልኩን ብቻ ሳይሆን ምሳሌውንም ጭምር ይዞ እንደ ተፈጠረ የሚያስተምረውን ቁም ነገር ልናስተውል እንችላለን ሰው፡-
-   እንደ አብ ልብ ከዊን ለባዊ፥
-   እንደ ወልድ ቃል ከዊን ነባቢ፥
-   እንደ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ከዊን ሕያው፥
በመሆኑ፥ በለባዊነቱ፡- አብን፥
በነባቢነቱ፡- ወልድን
በሕያውነቱ፡- መንፈስ ቅዱስን
መስሎአል፡፡ አንድነትን ባላፈለሰ ሦስትነት ኤሎሂም (አማልክት) ይሆዋ መልኩንና ምሳሌውን ያያዘ ፍጡር ሆኖአል (ዘፍ. 5፥1-2)፡፡


ማስረጃ 3
በኦሪት ዘፍጥረት 3፥22 አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ በማለት የተናገረ ይሆዋ አንድ አካል ነው ለማለት አይቻልም፡፡ እንዲህ በማለት የመወያየት መብት የሚኖራቸው ሁለትና ከዚያ በላይ ብዛት ያላቸው ሕያዋን አካላት ብቻ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚህ በቀር “እኛ” በሚል ራስ ማስተዋወቂያ ውስጥ ሊገለጽ የሚችል ሌላ እንዳልነበረ የሚያስገነዝበን ዐቢይ ኀይለ ቃል በውይይቱ ተናጋሪ “ኤሎሂም  ይሆዋ” መባሉ ነው፡፡ ይሆዋ ኤሎሂም ሲሆን ኤሎሂምም ይሆዋ ነው፥ ሌላ የለም፡፡

ማስራጃ 4
ሰይጣን አላስተዋለም እንጂ በኦሪት ዘፍጥረት 11፥6፡7 “… ኑ እንውረድ … ቋንቋቸውን እንለዋውጥባቸው …” የሚል ጥቅስ የብሉይ ኪዳን አማኞች “ይሆዋ አንድ አካል ነው” በማለት አለማመናቸውን ባስረዳ ነበር “ኑ እንውረድ” ሲል የተናገረው እንደ ተናገረውም ወርዶ ቋንቋቸውን የደባለቀና የአዳምን ልጆች የበተነ አንዱ ይሆዋ ነው፡፡ ሌላ ማንም በምክሩም በሥራውም የተካፈለ አልነበረምና (ዘፍ. 8፥9፤ ዘዳ. 32፥7፡8)፡፡

እንግዲህ ከተራ ቊጥር 1 እስከ 3 የተመለከትናቸው ጥቅሶች ይሆዋ አንድ አካል አለመሆኑን የሚያስገነዝቡ ቢሆንም ከሁለት አካላት በላይ መሆኑን በግልጽ አያስረዱም ነበር፡፡ በዚህ በአራተኛ ተራ ቊጥር በቀረበው ጥቅስ ግን ከሁለት በላይ የሆኑ አካላት በአንዱ ይሆዋ እንዳሉ ገሃድ አውጥቶታል፡፡ አንዱ አካል ሌሎቹን “ኑ እንውረድ” ሲላቸው ተሰምቷልና፥ ሁለት አካላት ብቻ ቢሆኑማ ኖሮ “ና እንውረድ” ሊል በተገባው ነበርና፡፡

አርዮሳውያን ሲጨንቃቸው በይሆዋ ኤሎሂምነት ውስጥ አብና ወልድን ለመቀበል ይገደዱና ታዲያ ሁለት ብቻ ናቸው እንጂ መቼ ሦስት ናቸው እያሉ /6/ መንፈስ ቅዱስን ከኤሎሄምነትና ከይሆዋነት ለማውጣት ይሞክራሉ፡፡ ይህ የብሉይ ኪዳን መጀመሪያ መጽሐፍ በዐሥራ አንደኛው ምዕራፍ የሰጠን ትምህርት ግን ይሆዋ በሁለት አካላት ያልተወሰነ መሆኑን አበክሮ ያስገነዝበናል፡፡ “ና እንውረድ” የሚለውን የሁለት አካላት ንግግር ሳይጠቀም ከሁለት በላይ የሆኑ ሕያዋን ሊያደርጉት በሚገባ ውይይት በመጠቀም አንዱ ሌሎችን (እኩዮቹን) “ኑ እንውረድ” እንዳላቸው መዝግቦ አቈይቶልና፡፡
በመናፍቃን ወጥመድ እንዳንወድቅ አስቀድሞ ያሰበልን ኤሎሂም የሆነው ይሆዋ ይመስገን!!!

ማጠቃለያ
ከዚህ በላይ ከ1 እስከ 4 ተራ ቊጥር ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱት ጥቅሶች የሚከተሉትን ፍሬ ሐሳቦች ያስጨብጡናል፡፡
ሀ. የብሉይ ኪዳን አማኞች ይሆዋ አንድ አካል ነው ብለው አለማመናቸውን፥
ለ. በአንዱ ይሆዋ ከሁለት በላይ የሆኑ ሕያዋን አካላት እንዳሉ መረዳታቸውን፥
ሐ. የብዙ አካላት መግለጫ የሆነውን “ኤሎሂምን” (አማልክትን) አያይዘው እንዲነበብ ያደረጉት ከይሆዋ ጋር ስለ ሆነ “ኤሎሂም” (አማልክት) ያሉት አንዱ ይሆዋ ጋር በመደመር አለመሆኑን ይገልጹልናል፡፡ የእምነታችን መሠረት ጥልቀትና ጽናት እንዳለውም ያረጋግጣሉ፡፡
“እስራኤል ሆይ ስማ፤ የኛ ኤሎሂም የሆነው ይሆዋ አንዱ ይሆዋ ነው” (ዘዳ. 4፥6)፡፡

የማስረጃ ምንጮች
  1. ሰባልዮስ አንዱ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን እንደ አብ ታወቀ፡፡ በኋላም ሰው ሆኖ እንደ ወልድ፥ በበዓለ ኃምሳም እንደ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ታወቀ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ራሱን በሦስት ስሞችና የግብር ባለቤቶች የገለጸው ያው አንዱ መለኮታዊ አካል ነው ሲል በ3ኛው ክፍለ ዘመን ያስተማረ መናፍቅ ነበረ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ከአባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ 1978 ዓ.ም. አዲስ አበባ የታተመ ገጽ 72 አንቀጽ 3፡፡
  2. አርዮስ ወልድ በአብ የተፈጠረ ነው በማለቱ በ4ኛው ክፍለ ዘመን ከቤተ ክርስቲያን እንዲለይ የተወሰነበት መናፍቅ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ከአባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ 1978 ዓ.ም. አዲስ አበባ የታተመ ገጽ 105-116፡፡
  3. ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራው እውነት በዩ.ኤስ.ኤ. የታተመ ምዕራፍ 13 ቊጥር 12 እና 13
  4. መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ከኪዳነ ወልድ ክፍሌ 1948 ዓ.ም. አዲስ አበባ በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት የታተመ ገጽ 222
  5. ዘ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል ለንደን፥ ዌስት ሚኒስተር 18 ጁን 1985 የታተመ የዘፍ. 1፥26 የግርጌ ማብራሪያ
  6. ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራው እውነት በዩ.ኤስ.ኤ. የታተመ ምዕራፍ 6 ቊጥር 13፡፡

No comments:

Post a Comment