Monday, September 23, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ


አለቃ ነቅዐ ጥበብና አገልግሎታቸው

አለቃ ነቅዐ ጥበብ በመካከል ካለችው ከአሮጌዋ አትሮንስ ፊት ለፊት ተቀምጠዋል፡፡ አለቃ ደምፀ ቃለ አብ በስተቀኛቸው የኔታ ማኅተመ ሥላሴም በስተግራ አጐዛና ሰሌን በተነጠፈበት መደብ ላይ ጕብ ብለዋል፡፡ ቀሳውስት፥ ዲያቆናትና ምእመናን የአለቃን እልፍኝ አጨናንቀዋታል፡፡ ከጥማት ለመርካት በምንጭ ዙሪያ የተሰለፉ ዋልያዎችን ሁኔታ የሚያስታውስ ትዕይነት ነበር (መዝ. 41/42፥1)፡፡

በጉባኤው የተገኙ ዐዳዲስ ታዋቂ ዕድምተኞችም ነበሩ - መሪ ጌታ ንዋይ ሲሞን፥ አጋፋሪ ዕንባቆም ኀይለ ልዑልና ተማሪ የማነ ብርሃን፡፡ የሁሉም ዐይኖች በመሪ ጌታ ንዋይ ሲሞንና በአለቃ ነቅዐ ጥበብ ላይ በየተራ ያርፉ ነበር፡፡

Saturday, September 14, 2013

ጋብቻ


የጋብቻ ትምህርት

የእግዚአብሔር ሥራ ምን ጊዜም መልካም ነው
የሰው ባሕርይ ከቤተ ሰቡ የተወረሱ ድክመቶችን የሚያንጸባርቀው በሁለት ተቃራኒ መንገዶች ሊሆን ይችላል፡፡ የአባቶች ድክመቶች ምናልባት ባለማወቅ የሚደጋገሙና የበለጠ እየተባባሱ የሚሄዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወይንም በራሳቸው ውሳኔ ወደ ሰፋ ልዩነት የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ በሚፈልጉ ተከታይ ትውልዶች ግልጽ ተቃውሞ ይገጥማቸው ይሆናል፡፡

አብርሃም ልጅ ስላልወለደ ተጨንቆ በአንድ ወቅት አባ ወራነቱን ትቶ የሣራን አስተሳሰብ በመከተል ድክመቱን ሲገልጥ፥ ልጁ ይሥሐቅ ከሚስቱ ከርብቃ ጋር ስለ ልጆቻቸው የሚጸናና የሚዘወተር አለመግባባትን ለመቈጣጠር ባለመቻሉ የባሰውን ድክመት አሳየ፡፡ የይሥሐቅ ታናሽ ልጅ ያዕቆብ ግን በወላጆቹ የተለመደ ድክመት እንዳይደገም በሌላ አቅጣጫ ሲሄድ በዚህ ጽሑፍ እንመለከታለን፡፡

Wednesday, September 4, 2013

የዘመን ምስክር


በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡


አለቃ ታየ ገብረ ማርያም (1853 - 1916 ዓ.ም.)
አይሁድ መሲሑን ይጠባበቁ የነበሩ ሕዝብ ናቸው፤ መሲሑ ሲመጣ ግን አልተቀበሉትም፡፡ የመሲሑን ደቀ መዛሙርትም አሳድደዋል፡፡ እነርሱን መስሎ የሚኖረውን ሰው እውነተኛ አይሁዳዊ ሲሉ፥ ዐዲስና እንግዳ ትምህርትን ሳያመጣ በመጽሐፋቸው የተገለጠውንና እነርሱ ያላስተዋሉትን እውነት የሚያምነውንና የሚኖረውን የመሲሑን ተከታይ ደግሞ መናፍቅ እያሉ ሲኰንኑ ኖረዋል፡፡

ሳውል፥ በጊዜው በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር በነበረው በገማልያል እግር ሥር ተቀምጦ የተማረ ሊቅ እንደ መሆኑ በዚያው ሥርዐት ሲኖር እጅግ የተከበረ ሰው ነበረ (ፊል. 3፥5-6)፡፡ ክርስቶስ ከተገለጠለትና በወንጌል አምኖ የእርሱው አገልጋይ ከሆነ በኋላ ግን፥ የቀድሞ ክብሩን ዐጥቶ አሳዳጁ ሲሰደድና ሲንገላታ፥ አለሥራውም ክፉ ስም ሲወጣለት ነበር፡፡ ቀድሞ ያከበሩት ወገኖች፥ “ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን ሆኖ አግኝተነዋልና፤ መቅደስንም ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው” (ሐ.ሥ. 24፥1-9) ሲሉ በሐሰት ከሰዉታል፡፡ እርሱም ለቀረበበት ክስ በሰጠው ምላሽ፥ “በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፡፡ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት ጻድቃንም ዐመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ ” (ቊጥር 10-21) ብሏል፡፡