Friday, May 17, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

ካለፈው የቀጠለ

በምን ተስኖት ቤት ዐድረው ከወጡት ሰዎች መካከል በሌላ አቅጣጫ የሄዱትም እንደዚሁ በተመሳሳይና በሌሎች የወቅቱ ሁኔታ በፈጠራቸው ነጥቦች ላይ ይከራከሩ ነበር፡፡ ሐሳባቸውን በውይይት እያጠነከሩና እየተስማሙ መጥተው በመጨረሻ በአንዳንድ ነጥብ ላይ ለመግባባት አልቻሉም፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላ ያስቸገሯቸውንና አልታረቅ ያሏቸውን ነጥቦች በሚከተለው ሁኔታ አጠቃለሏቸው፡፡

 1. ምን ተስኖት በሰይጣን መንፈስ እንደሚሠራ እናውቃን፤ ከጥንቈላ፣ ከሟርት፣ ከአስማተኛነት ጋር የእግዚአብሔር መንፈስ ግንኙነት የለውምና፥ ለእግዚአብሔር ብቻ ሊቀርብ የሚገባውን ክብር፣ አምልኮት፣ ስግደትና ዝማሬ የሚቀበለው በምን ተስኖት ያደረ ራሱን የእግዚአብሔር ተገዳዳሪ ያደረገው ሰይጣን ነው፡፡ ታዲያ ሰይጣን በምን ተስኖት ቤት ሲመለክ የሚያድርበትን ዕለት በየወሩ ለሚካኤልና ለገብርኤል መታሰቢያ በሚከበሩ በዓላት ለምን አደረገው?

Friday, May 10, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ


ጭውውት
አለቃ ነቅዐ ጥበብና ቤተሰባቸው

የተደበላለቀ የአነስተኛ ከበሮዎች ድምድምታና ዝየራ የሌሊቱን ጸጥታ ተዳፍሮታል፡፡ ዐልፎ ዐልፎ እልልታ የተቀላቀለበት ያላቋረጠ ጭብጨባ ከበሮውን አጅቦታል፡፡ በመደብ፣ በዕድሜ፣ በጾታ፣ በጐሣ፣ በሥራና በዕውቀት ደረጃም የተሰባቀለ ሕዝብ ወደ አዳራሹ ራስጌ ከመጋራጃው ውጪ የቆመ አስተናባሪ አደግድጎ ሥርዐተ ማሕሌቱን ይመራል፡፡ በቅልጥፍናቸውና ከሰው ጋር በሚያደርጉት ፈጣን ትውውቅ የሚደነቁ፣ ነገር ግን ገራገር ያገር ቤት ሰው የሚመስሉ ወጣቶች በየባለጕዳዩ መካከል ተቀምጠዋል፡፡ እነርሱም በዜማውና በጫጫታው መካከል በየአጠገባቸው ላለ ባለጉዳይ ለመምጣት ምክንያት የሆነውን ችግራቸውን እያስተዛዘኑ በለሆሳስ (በሹክሹክታ) ያወሩለትና በለውጡ የእርሱን ጕዳይ ያደምጣሉ፡፡

ከጉባኤው መካከል አንዳንዱ ሰው በዝየራው፣ በእልልታው፣ በከበሮውና በጭብጨባው ውስጥ በአጠገቡ ወደሚገኘው ሰው ጆሮ በመጠጋት የአቶ ምንተስኖትን ታሪክ ሹክ ይለዋል፡፡ ከሚወራው ታሪክ አብዛኛው መቼ? የት? ለማን? እንደ ተደረገ የማይታወቅ፣ እንዲያው በይለፍ ይለፍ እየተናፈሰና እየተጋነነ የሚወራ ነው፡፡ ማንም ሰው ልብ ያላለው የኪስ ያይደለ የልብ ዳበሳም እየተቀላጠፈ ነበር፡፡ እነዚያ ልብሰ አዳፋ ንግግረ ጐልዳፋ ያገር ቤት ሰው የሚመስሉት ወጣቶች አሁንም ስፍራቸውን እየለዋወጡ በየሰው መካከል ገብቶ መቀመጥን እንደ ተያያዙት ነበር፡፡ የራሳቸውን ጕዳይ በመጫወት የሌላውን ጠይቆ በማውጣጣት በዕሴት ያልተመጣጠነ ልውውጥ ያካሂዳሉ፡፡ በልዋጭ ከሚያጠናቅሩት ዘገባ ዋናው ያባለጕዳዩን ስምና የመጣበትን ችግር ማወቅን ነበር፡፡ የዝየራው፣ የእልልታው፣ የከበሮውና የጭብጨባው ድምፆች ተደበላልቀው በአየር ላይ እኔ-እበልጥ እኔ-እበልጥን ለማስወሰን ፍልሚያ እያካሄዱ የሚመስልበት ውድቀቱ ሌሊት የተደፈረውን መብቱን ለማስከበር አቤቱታውን እያቀረበ ነበር፡፡