Friday, May 10, 2013

አለቃ ነቅዐ ጥበብ


ጭውውት
አለቃ ነቅዐ ጥበብና ቤተሰባቸው

የተደበላለቀ የአነስተኛ ከበሮዎች ድምድምታና ዝየራ የሌሊቱን ጸጥታ ተዳፍሮታል፡፡ ዐልፎ ዐልፎ እልልታ የተቀላቀለበት ያላቋረጠ ጭብጨባ ከበሮውን አጅቦታል፡፡ በመደብ፣ በዕድሜ፣ በጾታ፣ በጐሣ፣ በሥራና በዕውቀት ደረጃም የተሰባቀለ ሕዝብ ወደ አዳራሹ ራስጌ ከመጋራጃው ውጪ የቆመ አስተናባሪ አደግድጎ ሥርዐተ ማሕሌቱን ይመራል፡፡ በቅልጥፍናቸውና ከሰው ጋር በሚያደርጉት ፈጣን ትውውቅ የሚደነቁ፣ ነገር ግን ገራገር ያገር ቤት ሰው የሚመስሉ ወጣቶች በየባለጕዳዩ መካከል ተቀምጠዋል፡፡ እነርሱም በዜማውና በጫጫታው መካከል በየአጠገባቸው ላለ ባለጉዳይ ለመምጣት ምክንያት የሆነውን ችግራቸውን እያስተዛዘኑ በለሆሳስ (በሹክሹክታ) ያወሩለትና በለውጡ የእርሱን ጕዳይ ያደምጣሉ፡፡

ከጉባኤው መካከል አንዳንዱ ሰው በዝየራው፣ በእልልታው፣ በከበሮውና በጭብጨባው ውስጥ በአጠገቡ ወደሚገኘው ሰው ጆሮ በመጠጋት የአቶ ምንተስኖትን ታሪክ ሹክ ይለዋል፡፡ ከሚወራው ታሪክ አብዛኛው መቼ? የት? ለማን? እንደ ተደረገ የማይታወቅ፣ እንዲያው በይለፍ ይለፍ እየተናፈሰና እየተጋነነ የሚወራ ነው፡፡ ማንም ሰው ልብ ያላለው የኪስ ያይደለ የልብ ዳበሳም እየተቀላጠፈ ነበር፡፡ እነዚያ ልብሰ አዳፋ ንግግረ ጐልዳፋ ያገር ቤት ሰው የሚመስሉት ወጣቶች አሁንም ስፍራቸውን እየለዋወጡ በየሰው መካከል ገብቶ መቀመጥን እንደ ተያያዙት ነበር፡፡ የራሳቸውን ጕዳይ በመጫወት የሌላውን ጠይቆ በማውጣጣት በዕሴት ያልተመጣጠነ ልውውጥ ያካሂዳሉ፡፡ በልዋጭ ከሚያጠናቅሩት ዘገባ ዋናው ያባለጕዳዩን ስምና የመጣበትን ችግር ማወቅን ነበር፡፡ የዝየራው፣ የእልልታው፣ የከበሮውና የጭብጨባው ድምፆች ተደበላልቀው በአየር ላይ እኔ-እበልጥ እኔ-እበልጥን ለማስወሰን ፍልሚያ እያካሄዱ የሚመስልበት ውድቀቱ ሌሊት የተደፈረውን መብቱን ለማስከበር አቤቱታውን እያቀረበ ነበር፡፡


በሚተነፍገው አዳራሽ ውስጥ አደግድጎ ከቆመው አጋፋሪ በስተ ጀርባ ለየት ያለ ድምፅ፣ የጅብ ጩኸት አይሉት ወይ የበሬ ግሣት፣ በውል ያልታወቀ የተደባላለቀውን ድምፅ ሁሉ እያቈራረጠና አየራትን እየሰነጣጠቀ የተሰማ ድምፅ በግቢውም በውጪውም የቆመውንና የተቀመጠውን የሚማለለውንና የሚያዜመውን፣ የሚሰግደውን፣ የሚያጨበጭበውን ሁሉ ጸጥ ረጭ አደረገው፡፡ አጋፋሪው ወደ ኋላ ተመለሰና ጀርባውን ለሕዝቡ ሰጥቶ እጅ ነሳ፡፡ ሕዝቡ ሁሉ እንደ ቅጠል ረገፈና መሬት ሳመ፡፡ ምን ተስኖት ደመቀ በመጋረጃው ውስጥ እንደ ሆነ ሥራ መጀመሩ ተበሠረ፡፡ ከዚያ ጫጫታና ጩኸት ይህ ዐይነቱ ጸጥታ መወለዱ አስደናቂ ነበረ፡፡ ሁሉም ሰው ጆሮዎቹን አቁሞ ትንፋሹን ውጦት ነበር፡፡

“ገበያነሽ ዱባለ! የሚል ጥሪ ከምን ተስኖት አፍ ሲወጣ ወዲያው አንዲት ሴት ከሕዝቡ መካከል ስትቆም ታየች፡፡ “አቤት፣ አቤት፣ አቤት፣ ጌታዬ” አለች፡፡

“ገበያ ቀዘቀዘብኝ ወረት ዐጣሁ አይደለም እምትዪው? ... መነሻው ምን እንደ ሆነ ዐውቀሽዋል?” ሲል ጠየቀ ምንተስኖት፡፡

“አዎን፣ ጌታዬ ገበያ ቀዝቅዞብኛል ምኽኛቱን አላውቀውም፡፡ እንዲያው መላ-እጡ ቢጠፋብኝ መጣኹኢ” አለች፡፡

ሕዝቡ እልልልልል ይላል፡፡ አንዳንዴም ያደንቃል፡፡ የሴትዬዋ ስምና ችግሯን እንዴት ዐወቁት? ብሎ፡፡

ምን ተስኖት ጐርነን ባለ ድምፅ “አቤትሽ ጣሪያ ላይ የተደበቀ በአንድ ደብተራ የተጻፈ መተት አለ፤ ምቀኛሽ ብዙ ነው፤ እኛ ማርከሻውን እንሰጥሻለን” ሲል ሴትየዋ በግምባርዋ መሬቱን በመንካት እልልታዋን አቀለጠችው፡፡ ሕዝቡም የእልልታ ምላሽ ሰጣት፡፡

“ተከተል ደመላሽ” አለ ምን ተስኖት፣ ተረኛውን ሰው መጥራቱ ነበር፡፡ ከሕዝብ መካከል አንድ ሰው ቆመና “አቤት ጌታዬ” አለ፡፡

“እኛ ዘንድ የመጣኸው የደረጃ እድገት ባለማግኘትህ ነው፤ አይደለም እንዴ?” ሲል ምን ተስኖት “ነው፤ ነው እንጂ ጌታዬ” ነበር የተከተል መልስ፡፡ ምን ተስኖት በተናገረና ባለጕዳዩ ምላሽ በሰጠ ቍጥር የሕዝቡ ማድነቅ፣ ማዳነቅ እልልልል ማለት አይቀሬ ነበር፡፡

“በመሥሪያ ቤት ጠላቶች አሉህ፤ አለቃህም ይቀናብሃል፤ መድፍነ ፀር፣ መስተፋቅርም እንሰጥሃልን” ለሚለው የምን ተስኖት የተስፋ ቃል ተከተል ከሰገደና እልል ካለ በኋላ ተቀመጠ፡፡ ለሌላ ተረኛ ጊዜውን መልቀቁ ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እየተበባለ የሌሊቱ ሰዓት ተገባደደ፡፡ ትዳር ያጡ፣ የትዳር ጓደኛ አልረጋ ያላቸው፣ ሥራ ፈላጊዎች፣ ከሥራ የተባረሩ፣ ትምህርት አልገባን አለ የሚሉ፣ ከሥራ የታገዱ፣ ሥልጣን ፈላጊዎች፣ ጤና ዐጣን ባዮች …. በስም በስማቸው እየተጠሩ የመጡበት ችግርና የመፍትሔው ተስፋ ከምን ተስኖት ተነገራቸው፡፡ በስተ መጨረሻው “ቄስ በሻህ ውረድ!” የሚል ድምፅ ከምን ተስኖት አንደበት ወጣ፡፡ ከወደ ጥግ በቂ ብርሃን ካልደረሰበት ስፍራ አንድ ሰው ብድግ ብሎ ሰገደና ቆመ፡፡ ቀጭን ነው የሰው ጥላ ይመስላል፡

“ሚስትህ እየኰበለለች አስቸገረችህ አይደል? ወደ ቤትህ እንመልሳታለን ባንተ እንድትረጋ እናስራታለን” አለ ምን ተስኖት፡፡ ቄሱ እልልታውን ሲያቀልጠውና መሬት ሲስም እንጂ እንዴት እንደ ተነሣና በየት በኩል እንደ ወጣ ማንም አላየው፡፡ የሕዝቡ እኩሌታ ቄሱን በእልልታ ሲያጅበው እኩሌታው ግን ተጐሻሸመ፡፡ “ቄሱም ከእኛ ጋ ጠንቋይ ቤት ተገኘ!!” በሚል ድምፅ የለሽ ንግግር እየተግባባ፡፡ ገና ከማታው ጀምሮ ባለጕዳዩን ሁሉ በስሙ በመጥራትና የመጣበትን ጕዳይና የመፍትሔውንም ተስፋ እየተናገረ አነጋ፡፡ ዐሥራ አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን ምን ተስኖት ከመጋረጃው ውስጥ እንደ ሆነ “ከቤተ ክርስቲያን መልስ ሁላችሁም የገብርኤልን ጠበል እንድትቀምሱ ተጋብዛችኋል፡፡ ዛሬ ከገባልኝ ስጦታ ከጧፉም፣ ከሻማውም፣ ከዕጣኑም፣ ከሱቲውም፣ ከዘቢቡም፣ ከጃንጥላውም፣ ከአበባ ምንጣፉም፣ በጠቅላላው ከሁሉም እኩሌታው እንደ ተለመደው ለገብርኤል ይሰጣል፡፡ ይህን የተከበረ ባህላችንንና ሃይማኖታችንን ሊያስለውጡን በመንደራችን እየዞሩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰብኩትን ብትቀበሉ ረግሜአችኋለሁ፡፡” በማለት ካዘዘና ከናዘዘ በኋላ ሕዝቡ እየተጋፋ ወጥቶ በየአቅጣጫው ተጓዘ፡፡ ሁሉም ሰው ግን በሌሊቱ ዐዳር የተገነዘበውንና የታዘበውን እያነሣ ከመሰል ከመሰሉ ጋር ይወያይበት ነበር፡፡

በአንደኛው አቅጣጫ ይጓዙ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ ንግግር ጀመረ “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ የሚለውን አምላካዊ ሕግ በመተላላፍ ለምን ተስኖት መስገዳችን፣ ከእርሱም ለችግራችን መፍትሔ እናገኛለን በሚል ተስፋ መታመናችን ኀጢአት ነውና ንስሓ ልንገባ ይገባል፡፡” በማለት በጸጸት ከተመላ ልቡ አወጥቶ ተናገረ፡፡

ስግደት በሦስት ይከፈላል፤ አንደኛው የአምልኮት ስግደት፣ ሁለተኛው የጸጋ ስግደት፣ ሦስተኛው የአክብሮት ስግደት እያሉ ቄስ በሻህ ውረድ የነገሩትን በመጥቀስ “ለምን ተስኖት የሰጠነው የአክብሮት ወይም የጸጋ ስግደት ነውና አያስኰንንም” ሲል ሁለተኛው ተከራከረ፡፡

ሦስተኛውም ሰው በተራው “ጕልበት ሁሉ ለኔ ይንበረከካል” ብሎ እግዚአብሔር የተናገረውንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ” ያለውን በመጥቀስ ከአምልኮ ባዕድ ሁሉ እንድንጠነቀቅ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ሲያስተምሩ ሰምቻለሁ፡፡ ስለ ሆነም የሠራነው ሁሉ ሕገ እግዚአብሔርን መተላለፍ እንደ ሆነ ልንክድ አይገባም አለ፡፡

ከዚህ በኋላም ሁሉም የየስሜቱን ለመናገር ባደረበት ፍላጎት መደማመጥ ቀረና ጫጫታ በረከተ፡፡ ከመካከላቸውም አንዱ ረጋና ኮስተር ባለ አነጋገር “እስኪ ቈዩ፣ እንደማመጥ፣ ካልተደማመጥን መነጋገራችን ምን ይፈይድልናል” ሲል ሁሉም ጸጥ አሉ፡፡ የማድመጥ ዝንባሌያቸውን ካረጋገጠ በኋላም ሰውዮው እንዲህ አለ፡-

“የጸጋ ስግደት ተፈቅዷል የምንለው አንዱ ሰው በራሱ ስሜት ማለት ከፍርሃት፣ ከድንጋጤ፣ ከአክብሮት፣ ይሁን ከፍቅር፣ ወይም ግልጽ ካልሆነ ውስጣዊ ግፊት የተነሣ እሌላው ፍጡር ፊት ወድቆ መስገዱን የሚገልጸውን ቃል እንደ አብነት በመጥቀስ የሚቀርብ ክርክር ነው እንጂ፣ ከእግዚአብሔር አንደበት ለፍጡራን የጸጋ ስግደትን እንድትሰጡ አዝዣለሁ ተብሎ አልተነገረም፡፡ ክልከላው ግን በግልጽ ተጽፎ ታውጇል፡፡

ከክልከላው አንዳንዱን አንቀጽ ማስታወስ ቢያስፈልግ ቅደም የተቀሳችሁት፣
“ከእኔ በቀር ሌላ አታምልክ” (ዘፍ. 20፥1-3)
“ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል” (ኢሳ. 45፥22-23)
“በፍጡር የሚታመን እንደ ርሱ ሥጋ ለባሽ የሆነውንም ተስፋ የሚያደርግ የተረገመ ነው” (ኤር. 17፥5-8)
“ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ብቻ ስገድ” (ሉቃ. 4፥8) እየተባለ ሕግና ትእዛዝ ሆኖ በማያሻማ ሁኔታ ለሌላ መስገድና ሌላን ተስፋ ማድረግ እንደማይገባ ታውጇል፡፡

“ወኢትግስሱ መሲሓንየ ወኢታሕሥሙ ዲበ ነቢያትየ - የቀባኋቸውን አትዳስሱ፤ በነቢያትም ላይ ክፉ አታድርጉ …” ማለት ስገዱላቸው እንደ ማለት አይወሰድም፡፡

ለፍጡራን የጸጋ ስገደት እንዲሰጥ ተፈቅዷል የሚባል ከሆነ በዚሁ በክልከላው አዋጅ ትይዩ የተፈቀደበት ግልጽ አዋጅ መገኘት ነበረበት፡፡ በራሳቸው ድንገተኛ ስሜት የተገፋፉ ሰዎች ለሌላው እንደነሱ ፍጡር ለሆነው መስገዳቸውን፣ እግዚአብሔር በዐሠርቱ ትእዛዛት ውስጥ የደነገገው አስመስለን በመናገራችን ራሳችንን አታለልን እንጂ በሕግ አፍራሽነት ከመጠየቅ አያድነንም፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ያደረጉትን ተአምር አይተው የተደነቁ አረማውያን መሥዋዕት ሊያቀርቡላቸው ሲዘጋጁ ጳውሎስና በርናባስ እኛ እንደናንተ ሰዎች ነንና ይህን ከንቱ ሥራ በመተው ሁሉን ወደ ፈጠረ ሕያው እግዚአብሔር ልትመለሱ ይገባል ሲሉ ከለከሏቸው እንጂ በጸጋ ሊሰገድልን፣ በጸጋም መሥዋዕት ሊቀርብልን ይገባል ብለው አልተቀበሉትም፡፡

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእግዚአብሔር ወደ ርሱ በተላከውና ምስጢር በገለጸለት መልአክ እግር ሥር ወድቆ ሲሰግድለት መልአኩ የጸጋ ስግደትን መቀበል ቢፈቀድለት ኖሮ አበጀህ ብሎ በመረቀው ነበር፡፡ ዳሩ ግን፣ “ዕወቅ ተጠንቀቅ ሁለተኛ እንዳታደርገው እኔም እንዳንተ አገልጋይ ነኝ፡፡ ሁለታችንም ለእግዚአብሔር ልንሰግድ ይገባናል፡፡” እያለ እንደ ከለከለው ተጽፎአል፡፡ አሁን የሚሰገድላቸው ሁሉ በሥጋ ሕይወት ያሉ ቢሆኑ ኖሮ ስግደታችንን አይቀበሉትም ነበር፤ ወደ እኛ የተላኩ የእግዚአብሔር መላእክት ቢኖሩም ኖሮ አትስገዱልን ባሉን ነበር፡፡ ወድቅህ ስገድልኝ የሚል ፍጡር ከዲያብሎስ በቀር አስካሁን አላየንም፡፡ (ማቴ. 4፥8-9)

ስለዚህ ወደድንም ጠላንም ከምን ተስኖት ረድኤት ለማግኘት ተስፋ ማድረጋችን፣ ለእርሱ ክብር ስንዘምር ማደራችን መስገዳችን፣ ከቤተ ክርስቲያን መልስም የጋበዘንን ምዉት መሥዋዕት ለመብላት ብንሄድ፣ ሁሉም ንስሓ ልንገባበት የሚገባ ኀጢአት ነው፡፡ ፈቃደኞች ከሆናችሁ አለቃ ነቅዐ ጥበብን እንጠይቅና እንረዳ አለና ንግግሩን ደመደመ፡፡ ሐሳቡን የተቀበሉትም የተቃወሙትም በአንድ ነገር ተስማሙ፡፡ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ከእግዚአብሔር ቃል እየጠቀሱና እየተረጐሙላቸው የሚያስተምሩአቸውን ለመቀበል፡፡

በጮራ ቍጥር 6 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment