Wednesday, November 30, 2011

ርእሰ አንቀጽ(1)

Read PDF
              በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 1፣ ላይ  የቀረበ

አእምሮአችንን ከድንቊርና አውጥተን ከፍ ያሉትን ያገር ጕዳዮችንና መንፈሳዊውን፥ የጥበብንና የአስተዳደርንም ነገሮች ለመከታተልና ለመመርመር ሁል ጊዜ ዕውቀታችንን ማሳደግ የክርስቲያኖች ሁሉ ተግባር መሆኑን እናምናለን፡፡
ለእያንዳንዳችን የመሰለንንና ያመንበትን ከሊቃውንትም የተማርነውን ሐሳብ እውነት መሆኑን ጠቃሚነቱን ከተቀበልነው ዘንድ ለሌሎች ማስገንዘብ ይገባናል በማለት እነሆ “ጮራ” የተሰኘውን መንፈሳዊ መጽሔት ለማሳትም ተነሥተናል፡፡
ላለፉት ዐሥራ ሰባት ዓመታት ተዘግተው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ተከፍተው መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ሲሰጡ፥ ታሽገው የነበሩ ልሳኖች ተከፍተው ኢየሱስ ጌታ መሆኑን ሲያበሥሩና ምስጋና ሲያቀርቡ፥ ታስረው የነበሩ እጆችም ተፈትተው ብርዕ ይዘው ለመጻፍ ተነሥተዋል፡፡ 

Saturday, November 26, 2011

በደቂቀ እስጢፋኖስ የነገረ መለኮት ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና በማኅበረ ቀናዕያን አመራሮች መካከል የተደረገ ክርክር (2)

           READ PDF                                                
 ቅዳሜ ኅዳር 16 2004       
                                ክፍል ሁለት 

“ሌላው የነመምህር በቃሉ የማደናገሪያ ስልት ከአባቶች ትምህርት የሚስማማቸውን ብቻ ከፍሎ በመጥቀስና ሌላውን በመተው የእኛ ትምህርት የአባቶች ነው ለማለትና ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርት ወደ ፕሮቴስታንታዊ ትምህርት ለማንሸራተት መሞከራቸው ነው። እኛ እያልን ያለነው አንዱን ጠቅሶ ሌላውን መተው ትክክለኛ አያሰኝምና ከአባቶች ከጠቀሳችሁ ሁሉንም መጥቀስና ስለ ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን ስለ እመቤታችን፣ ስለ መላእክት፣ ስለ ቅዱሳን አስተምሩ፤ ትክክለኛውን አስተምህሮአችንን ወደ ፕሮቴስታንቶች አስተምህሮ አታንሸራቱ ነው። ይህ ደግሞ ወንጌል እንጂ ከወንጌል የሚቃረን አይደለም” አለና ንግግሩን አጠናቀቀ።

ቀጣዩ ተረኛ ተናጋሪ መምህር በቃሉ እንዲናገር ከመድረክ መሪው ሲጋበዝ ለመናገር ጕረሮውን በእህህህታ ሞርዶ ለጥቂት ሰኮንዶች በዐይኖቹ ታዳሚዎቹን ከቃኘ በኋላ ቀጠለ። “እኔ ለዲያቆን በለው ጽርፈት (ስድብ) የተሞላበት ንግግር ምላሽ ከመስጠቴ በፊት፥ በለውን ጨምሮ ሁላችንም በየልባችን ምላሽ የምንሰጥባቸውን ጥያቄዎች መጠየቅ እፈልጋለሁ። ለመሆኑ ማኅበረ ቀናዕያን የተቋቋመበት ዐላማ አሁን ዲያቆን በለው የዘረዘረውን ለማድረግ ነው ወይ? እንዲህ እንዲያደርግ ሥልጣን የሰጠው አካልስ ማነው? እንዲህ የማድረግስ ሕጋዊ መብት አለው ወይ? ማኅበሩ ራሱን የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ፖሊስና ጠበቃ በማድረግ፥ እኔ ከሌለሁ ቤተ ክርስቲያን አትኖርም ማለቱስ የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነውን የክርስቶስን ስፍራ መንጠቅ አይሆንም ወይ? … እነዚህን ጥያቄዎች ሁሉም ለራሱ እንዲመልስ በትሕትና አሳስባለሁ።

Tuesday, November 22, 2011

በደቂቀ እስጢፋኖስ የነገረ መለኮት ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና በማኅበረ ቀናዕያን አመራሮች መካከል የተደረገ ክርክር (1)

READ PDF
                                                                            ረቡዕ ኅዳር 13 2004
በደቂቀ እስጢፋኖስ የነገረ መለኮት ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና በማኅበረ ቀናዕያን አመራሮችና አባላት መካከል እየተካረረ የመጣውን ውዝግብ ተከትሎ የአጋዓዝያን ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትና ሊቃውንት ሁለቱን ወገኖች ፊት ለፊት ለማነጋገርና ችግሮችን ለመፍታት ጉባኤ ጠርተው ነበር። በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ይምርሐነ ክርስቶስና ብፁዕ አቡነ ፍሬምናጦስ፣ ከሊቃውንትም አለቃ ነቅዐ ጥበብና መጋቤ ወንጌል ኅሩይ እም አእላፍ፥ የኮሌጁ ደቀ መዛሙርትና የማኅበሩ አንዳንድ ተወካዮች፥ እንደዚሁም ጉዳዩ ይመለከተናል ያሉ ሁሉ የጉባኤው ታዳሚዎች ነበሩ። 

ብፁዕ አቡነ ፍሬምናጦስ ጉባኤውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ፥ የመድረክ መሪ ሆነው የተሠየሙት መጋቤ ወንጌል ኅሩይ እም አእላፍ ጉባኤው የሚካሄድበትን ቅደም ተከተል በደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተሰበሰበሰው ታዳሚ አብራሩ። በዚሁ መሠረት የሁለቱም ወገኖች ተወካዮች በየተመደበላቸው ስፍራ ላይ ሆነው ቅሬታቸውን በመደማመጥ ተራ በተራ እንዲያሰሙና በመጀመሪያው ዙር ሁለቱም ወገኖች ሐሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ፥ በሁለተኛው ዙር አንደኛው ወገን ለቀረበበት ጥያቄ ወይም ክስ፥ ወይም ለተሰነዘረበት ትችት በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ እንዲሰጥ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚኖርም አስረዱ። በመጨረሻም ከጉባኤው ታዳሚዎች አስተያየት ከተሰጠ በኋላ፥  ከሊቃውንት ደግሞ አለቃ ነቅዐ ጥበብ ሐሳብ ሰጥተው ጉባኤው ወደ መፍትሔ ሐሳብ እንደሚያመራ፥ በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ይምርሐነ ክርስቶስ ቃለ ምእዳን አሰምተውና ጸሎት አድርገው መርሐ ግብሩ እንደሚጠናቀቅ የጉባኤውን አካሄድ አስታወቁ። 

Thursday, November 17, 2011

መቅደሱ ሊሠራ የጠላት ፉከራ

Read pdf 
ኀሙስ፣ ኅዳር 7/ 2004
ከጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊ ጥር 41


የእግዚአብሔር ሕዝብ ውድቀት የሚጀምረው የእግዚአብሔርን ዐሳብ ከማገልገል ሲወጣ ነው። እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ የፈጠረን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነት ያዳነንም ለፈቃዱ እንድንገዛ ነው። ስለዚህ ክብራችንም ሆነ ውድቀታችን ለእርሱ በመገዛታችንና ባለመገዛታችን ይወሰናል።

የእግዚአብሔርን ሥራ መሥራት እንዲህ በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም። ሥራው የሚጠይቀው የራሱ መስፈርቶች አሉት፤ በራሱ በእግዚአብሔር መጠራት፣ የአገልግሎት ጸጋ እና የተሰጠ ማንነት ያስፈልጋሉ። ከነዚህ መስፈርቶች ውስጥ ሁለቱ ከእግዚአብሔር ሲሆኑ፥ ሦስተኛው ግን የተጠራው አካል ድርሻ ነው። እግዚአብሔርም በዘመናት የሚሠራው በዚህ መንገድ ነው። የሥራው ባለቤት፣ ሠራዒው እንዲሁም መከናወንን የሚሰጠው ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም፥ በሥራው ውስጥ እንድንሳተፍና የክብሩ ተካፋይ እንድንሆን ይፈልጋል።