Read in PDF
“መድሎተ ጽድቅ” በምዕራፍ
አንድ፥ በ1.1 ላይ “የተሐድሶዎች መነሻዎችና መሠረቶች”
በሚለው ርእስ ሥር የሚገኘውን ንኡስ ርእስ “1.1.1 በ
‘መሰለኝ’ ማመን” ብሎታል፡፡ በዚህ ንኡስ ርእስ ሥር የቀረበው ሐተታ፥ እኛ ሃይማኖትን ያኽል መሠረታዊና ጥልቅ ጕዳይ
“ለእኛ የመሰለንን” እያልን እንደ ስብሰባ አስተያየት እምነታችን ለእኛ የመሰለን ሐሳብ ወይም ግምት እንደ ኾነ አድርገን እንደ
ጻፍን በማስመሰል፥ በልል ግስ የተጻፉትንና ማስረጃ የሚላቸውን ከየ መጽሔቱና ከየ መጻሕፍቱ ጠቃቅሷል፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል
ይህን ጕዳይ እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ የጠቀሰው የሚከተለውን ነው፡፡
·
“ለያንዳንዳችን የመሰለንንና
ያመንበትን ከሊቃውንትም የተማርነውን ሐሳብ እውነት መኾኑንና ጠቃሚነቱን ከተቀበልነው ዘንድ ለሌሎች ማስገንዘብ
ይገባል በማለት እነሆ ‘ ጮራ’ የተሰኘውን መንፈሳዊ መጽሔት ለማሳተም ተነሥተናል፡፡” (ጮራ ቊጥር 1 ገጽ
3)
በመሠረቱ እምነት በመሰለኝ
የሚቆም ነገር አለ መኾኑ ለማንም ግልጥ ነው፡፡ ሰው ከወላጆቹ ከሚወርሰው ሃይማኖት ባሻገር በሃይማኖቱ ውስጥ ሲኖር በራሱ
ያወቀውንና የተረዳውን እውነት ያምናል፡፡ ከተገለጠለትና በቃሉ መሠረት ማረጋገጫ ከቀረበለት እውነት ውጪ ያሉትንና ማረጋገጫ
ያልተገኘላቸውን ጕዳዮች ለመመርመር ሲሞክር ግን በመሰለኝ ነው እንጂ “ነው” በሚል ርግጠኛነት አይደለም፡፡ ስለዚህ ገለጣው
“እንዲህ ሊኾን ይችላል” “እንዲህ ይመስላል” ወዘተ. የሚል ይኾናል፡፡ ለምሳሌ “መድሎተ ጽድቅ” በገጽ 34 ላይ የጠቀሰውና
ከጮራ ቊጥር 11 ገጽ 5 ላይ የወሰደውን እንመልከት፡፡ በዚህ ክፍል ስለ ሰብአ ሰገል መምጣትና ስለ ማንነታቸው ተጽፏል፡፡
የሰብአ ሰገል ወደ ቤተ ልሔም መምጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገበ እውነት በመኾኑ ርግጠኛ በኾነ ቃል “ጠቢባኑ (ሰብአ
ሰገል) ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ” ተብሎ ነው የተገለጠው እንጂ፥ በመሰለኝ “መጥተው ሊኾን ይችላል” ወይም “ሳይመጡ
አልቀረም” ወዘተ. ተብሎ በአስተያየት መልክ አይደለም የቀረበው፡፡ ስለ ማንነታቸው ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ከምሥራቅ ወደ
ኢየሩሳሌም” መምጣታቸውን ብቻ ነው እንጂ አገራቸው የት እንደ ኾነ፥ ከማን ወገን እንደ ኾኑ ወዘተ. ርግጠኛውን ነገር
አይናገርም፡፡
ይህን በተመለከተ ልናደርግ
የምንችለው የመጀመሪያው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ የገለጠውንና “ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ” የሚለውን ብቻ ተቀብሎ ማመንና
መጽሐፉ ያልገለጠውን ነገር ለመግለጥ አለ መሞከር ነው፡፡ ኾኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ፍንጭ መነሻ በማድረግ ነገሩን
ማጥናትና መላ ምታችንን ማስቀመጥ የምንችልበት ዕድል የተዘጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኹለተኛውን አማራጭ የምንከተል ከኾነ
የደረስንበትን መላ ምት “ነው” በሚል ርግጠኛ ቃል ሳይኾን፥ “ሊኾን ይችላል” በሚል ልል ግስ ነው መግለጥ ያለብን፡፡ በጮራ
የተደረገውም ይኸው ነው፡፡ ርግጡንና የታመነውን ነገር “ነው” እንላለን፤ ርግጠኛ ያልተኾነበትንና በእኛ መረዳት የደረስንበትን
ጕዳይ ግን “ሊኾን ይችላል” እንላለን፡፡ ይህም እምነታችንን ርግጠኛ ባልኾነና በመሰለን ነገር ላይ እንዳሳረፍን ተደርጎ
የሚወሰድና የሚያስወቅሠን ሊኾን አይገባም፡፡
ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ
“የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት” የተሰኘውን መጽሐፍ ለመጻፍ ካነሣሡአቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የውጪ አገር ታሪክ
ጸሐፊዎች የጻፏቸውን ተርጕመው ያሳተሙና ያሠራጩ ኢትዮጵያውያን ጸሓፊዎች “ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን መኾናቸውንና የትንቢቱ
ባለቤቶች መኾናቸውን ክደው የሌላ አገር ሰዎች በድንገት የተጠሩ አረመኔዎች እንደ ነበሩ” መናገራቸው መኾኑን ገልጠው ነበር
(1953፣ 17፡ 111)፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን ሊኾኑ ይችላሉ ሳይኾን በርግጠኛነት
ኢትዮጵያውያን “ናቸው”፡፡ ኢትዮጵያውያን ናቸው ለማለትም በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ከእነርሱ ጋር ተያይዘው ያልተጠቀሱና
“ኢትዮጵያ” የሚል ስም ይዘው የተጻፉ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን አስደግፈው ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን መኾናቸውን ለማሳመን
ይሞክራሉ፡፡ ይኹን እንጂ ሰብአ ሰገል ወደ ቤተ ልሔም የመጡት ከምሥራቅ መኾኑ ስለ ተገለጠ፥ ከኢየሩሳሌም ወደ ደቡብ 9 ኪሎ
ሜትር ርቃ ለምትገኘው ቤተ ልሔም (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 1972፣ ገጽ 97) ኢትዮጵያ በምሥራቅ ልትገኝ አትችልምና
ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚለውን መቀበል ያስቸግራል፡፡
በሊቀ ጠበብት አያሌውና ይህን
ትውፊት ትረካ እንደ እምነት በተቀበሉቱ ዘንድ ኢትዮጵያውያን መኾናቸው ብቻም ሳይኾን ስማቸው ጭምር የታወቀ በመኾኑ በስም
ጠቅሰዋቸዋል፡፡ ይህ በትውፊት ሲነገር የቈየና በአንድምታ ትርጓሜ የተገለጠ ከመኾኑ በቀር ምንጩን አልጠቀሱም፡፡ ምናልባት
የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ይህን ትውፊታዊ ትረካ በ“ሊኾን ይችላል” ሳይኾን በ“ነው” ይኾናልና የሚያምነው እዚህ ላይ ልዩነት
አለን፡፡ ልዩነታችንም መጽሐፍ ቅዱስ ያላረጋገጠውንና መነሻውን መጽሐፍ ቅዱስ አድርጎ ተጨማሪ ማብራሪያ የተሰጠበትን ጕዳይ እንደ
አንድ አስተያየት ከመውሰድ በቀር “ነው” ብሎ በርግጠኛነት መቀበልና ማመን ስለማይቻል ነው፡፡