Wednesday, August 26, 2015

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን - ክፍል አራት

Read in PDF

“መድሎተ ጽድቅ” በምዕራፍ አንድ፥ በ1.1 ላይ “የተሐድሶዎች መነሻዎችና መሠረቶች” በሚለው ርእስ ሥር የሚገኘውን ንኡስ ርእስ “1.1.1 በ ‘መሰለኝ’ ማመን” ብሎታል፡፡ በዚህ ንኡስ ርእስ ሥር የቀረበው ሐተታ፥ እኛ ሃይማኖትን ያኽል መሠረታዊና ጥልቅ ጕዳይ “ለእኛ የመሰለንን” እያልን እንደ ስብሰባ አስተያየት እምነታችን ለእኛ የመሰለን ሐሳብ ወይም ግምት እንደ ኾነ አድርገን እንደ ጻፍን በማስመሰል፥ በልል ግስ የተጻፉትንና ማስረጃ የሚላቸውን ከየ መጽሔቱና ከየ መጻሕፍቱ ጠቃቅሷል፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል ይህን ጕዳይ እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ የጠቀሰው የሚከተለውን ነው፡፡   
·        ለያንዳንዳችን የመሰለንንና ያመንበትን ከሊቃውንትም የተማርነውን ሐሳብ እውነት መኾኑንና ጠቃሚነቱን ከተቀበልነው ዘንድ ለሌሎች ማስገንዘብ ይገባል በማለት እነሆ ጮራ የተሰኘውን መንፈሳዊ መጽሔት ለማሳተም ተነሥተናል፡፡” (ጮራ ቊጥር 1 ገጽ 3)
በመሠረቱ እምነት በመሰለኝ የሚቆም ነገር አለ መኾኑ ለማንም ግልጥ ነው፡፡ ሰው ከወላጆቹ ከሚወርሰው ሃይማኖት ባሻገር በሃይማኖቱ ውስጥ ሲኖር በራሱ ያወቀውንና የተረዳውን እውነት ያምናል፡፡ ከተገለጠለትና በቃሉ መሠረት ማረጋገጫ ከቀረበለት እውነት ውጪ ያሉትንና ማረጋገጫ ያልተገኘላቸውን ጕዳዮች ለመመርመር ሲሞክር ግን በመሰለኝ ነው እንጂ “ነው” በሚል ርግጠኛነት አይደለም፡፡ ስለዚህ ገለጣው “እንዲህ ሊኾን ይችላል” “እንዲህ ይመስላል” ወዘተ. የሚል ይኾናል፡፡ ለምሳሌ “መድሎተ ጽድቅ” በገጽ 34 ላይ የጠቀሰውና ከጮራ ቊጥር 11 ገጽ 5 ላይ የወሰደውን እንመልከት፡፡ በዚህ ክፍል ስለ ሰብአ ሰገል መምጣትና ስለ ማንነታቸው ተጽፏል፡፡ የሰብአ ሰገል ወደ ቤተ ልሔም መምጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገበ እውነት በመኾኑ ርግጠኛ በኾነ ቃል “ጠቢባኑ (ሰብአ ሰገል) ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ” ተብሎ ነው የተገለጠው እንጂ፥ በመሰለኝ “መጥተው ሊኾን ይችላል” ወይም “ሳይመጡ አልቀረም” ወዘተ. ተብሎ በአስተያየት መልክ አይደለም የቀረበው፡፡ ስለ ማንነታቸው ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም” መምጣታቸውን ብቻ ነው እንጂ አገራቸው የት እንደ ኾነ፥ ከማን ወገን እንደ ኾኑ ወዘተ. ርግጠኛውን ነገር አይናገርም፡፡
ይህን በተመለከተ ልናደርግ የምንችለው የመጀመሪያው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ የገለጠውንና “ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ” የሚለውን ብቻ ተቀብሎ ማመንና መጽሐፉ ያልገለጠውን ነገር ለመግለጥ አለ መሞከር ነው፡፡ ኾኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ፍንጭ መነሻ በማድረግ ነገሩን ማጥናትና መላ ምታችንን ማስቀመጥ የምንችልበት ዕድል የተዘጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኹለተኛውን አማራጭ የምንከተል ከኾነ የደረስንበትን መላ ምት “ነው” በሚል ርግጠኛ ቃል ሳይኾን፥ “ሊኾን ይችላል” በሚል ልል ግስ ነው መግለጥ ያለብን፡፡ በጮራ የተደረገውም ይኸው ነው፡፡ ርግጡንና የታመነውን ነገር “ነው” እንላለን፤ ርግጠኛ ያልተኾነበትንና በእኛ መረዳት የደረስንበትን ጕዳይ ግን “ሊኾን ይችላል” እንላለን፡፡ ይህም እምነታችንን ርግጠኛ ባልኾነና በመሰለን ነገር ላይ እንዳሳረፍን ተደርጎ የሚወሰድና የሚያስወቅሠን ሊኾን አይገባም፡፡
ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ “የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት” የተሰኘውን መጽሐፍ ለመጻፍ ካነሣሡአቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የውጪ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች የጻፏቸውን ተርጕመው ያሳተሙና ያሠራጩ ኢትዮጵያውያን ጸሓፊዎች “ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን መኾናቸውንና የትንቢቱ ባለቤቶች መኾናቸውን ክደው የሌላ አገር ሰዎች በድንገት የተጠሩ አረመኔዎች እንደ ነበሩ” መናገራቸው መኾኑን ገልጠው ነበር (1953፣ 17፡ 111)፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን ሊኾኑ ይችላሉ ሳይኾን በርግጠኛነት ኢትዮጵያውያን “ናቸው”፡፡ ኢትዮጵያውያን ናቸው ለማለትም በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ከእነርሱ ጋር ተያይዘው ያልተጠቀሱና “ኢትዮጵያ” የሚል ስም ይዘው የተጻፉ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን አስደግፈው ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን መኾናቸውን ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ ይኹን እንጂ ሰብአ ሰገል ወደ ቤተ ልሔም የመጡት ከምሥራቅ መኾኑ ስለ ተገለጠ፥ ከኢየሩሳሌም ወደ ደቡብ 9 ኪሎ ሜትር ርቃ ለምትገኘው ቤተ ልሔም (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 1972፣ ገጽ 97) ኢትዮጵያ በምሥራቅ ልትገኝ አትችልምና ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚለውን መቀበል ያስቸግራል፡፡
በሊቀ ጠበብት አያሌውና ይህን ትውፊት ትረካ እንደ እምነት በተቀበሉቱ ዘንድ ኢትዮጵያውያን መኾናቸው ብቻም ሳይኾን ስማቸው ጭምር የታወቀ በመኾኑ በስም ጠቅሰዋቸዋል፡፡ ይህ በትውፊት ሲነገር የቈየና በአንድምታ ትርጓሜ የተገለጠ ከመኾኑ በቀር ምንጩን አልጠቀሱም፡፡ ምናልባት የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ይህን ትውፊታዊ ትረካ በ“ሊኾን ይችላል” ሳይኾን በ“ነው” ይኾናልና የሚያምነው እዚህ ላይ ልዩነት አለን፡፡ ልዩነታችንም መጽሐፍ ቅዱስ ያላረጋገጠውንና መነሻውን መጽሐፍ ቅዱስ አድርጎ ተጨማሪ ማብራሪያ የተሰጠበትን ጕዳይ እንደ አንድ አስተያየት ከመውሰድ በቀር “ነው” ብሎ በርግጠኛነት መቀበልና ማመን ስለማይቻል ነው፡፡ 

“መድሎተ ጽድቅ” ከጮራ ቊጥር 1 ገጽ 3 ላይ የወሰደውና በመሰለን እንደምናምን አድርጎ የጠቀሰውም በዚህ መንገድ የሚታይ ነው፡፡ “ለያንዳንዳችን የመሰለንንና ያመንበትን ከሊቃውንትም የተማርነውን ሐሳብ እውነት መኾኑንና ጠቃሚነቱን ከተቀበልነው ዘንድ ለሌሎች ማስገንዘብ ይገባል በማለት እነሆ ጮራ የተሰኘውን መንፈሳዊ መጽሔት ለማሳተም ተነሥተናል፡፡” (ጮራ ቊጥር 1 ገጽ 3) የተባለው፥ በመሰለን የምናምን ሰዎች ነን ለማለት እንዳልኾነና በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠውን እውነት የምናምንና መጽሐፍ ቅዱስ ያላረጋገጠውን ደግሞ የመጨረሻ ባይኾንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠን ሁሉን ፈትኖ መልካሙን የመያዝ መርሕ (1ተሰ. 5፥20፡21) ለመመርመር በመሞከር የተረዳነውን ያኽል ማመናችንን ለመግለጥ ነው፡፡ “መድሎተ ጽድቅ” ግን፥ “መናፍቃን ደግሞ የሕይወት መጽሐፍ ከኾነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ለእነርሱ አስተሳሰብና አካሄድ የሚመቹ የመሰሏቸውን ጥቂት ጥቅሶች ወይም ሐሳቦች ብቻ ዘግነው ወይም አጠቃላይ ሐሳቡን አዛብተው” እንደሚነጕዱና እግዚአብሔር ግን በትዕግሥት እንደሚመለከታቸው በመቅድሙ ላይ አስፍሯል (ገጽ 11)፡፡ ይኹን እንጂ ለመተቸት ያኽል ብቻ  ይህ የተሳሳተ መርሕ መኾኑን በመጽሐፉ ውስጥ ቢጠቅስም፥ ከእግዚአብሔር ቃል ብቻ ሳይኾን ከእኛም ጽሑፍ ውስጥ ለሚያራምደው አስተሳሰብና አካሄድ የሚመቹ ይመስላሉ ያላቸውን ጥቂት ጥቅሶች እየዘገነና አጠቃላይ ሐሳቡን እያዛባ የጻፈው የ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ መኾኑ ግልጽ ነው፡፡ አንዱ ከላይ የተጠቀሰውና ከጮራ የተወሰደው ጥቅስ ነው፡፡ ይህን ጥቅስ ከመካከል መዝዞ በማውጣት አጠቃላይ ሐሳቡን ለማዛባትና እኛን በመሰለን የምናምን ለማድረግ ሞከረ እንጂ፥ የጮራን ርእሰ አንቀጽ የመጀመሪያ አንቀጽ አያይዞ ቢያቀርበው ኖሮ አንባቢውን አያሳስትም ነበር፡፡
ጥቅሱ ተመዝዞ የወጣበት ርእሰ አንቀጽ የመጀመሪያ አንቀጽ እንዲህ ይላል፤ “አእምሯችንን ከድንቍርና አውጥተን፥ ከፍ ያሉትን ያገር ጕዳዮችንና መንፈሳዊውን፥ ጥበብንና ያስተዳድርንም ነገሮች ለመከታተልና ለመመርመር ኹል ጊዜ ዕውቀታችንን ማሳደግ የክርስቲያኖች ኹሉ ተግባር መኾኑን እናምናለን፡፡” እዚህ ላይ ሃይማኖታዊ ጕዳይ ብቻ ሳይኾን፥ ሌሎች ማኅበራውያን ጕዳዮችም ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህን ጕዳዮች በተረዳነውና በደረስንበት መጠን፥ ለእኛ ትክክል በመሰለንም መንገድ ተቀብለን ለሌሎች እናስተላልፋለን፡፡ እንዲህ ያለውን ጕዳይ በዚህ መንገድ ከማስተናገድ ውጪ ሌላ ምን አማራጭ ሊኖር ይችላል? ይኹን እንጂ “መድሎተ ጽድቅ” እነዚህን ጕዳዮች ሳይኾን እምነታችንን በመሰለን እንደ መሠረትን አድርጎ ማቅረቡ፥ ምን ያኽል ነገሮችን እያዛባ በመጻፍ እንደ ተካነ ማሳያ ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ በአብዛኛው የምናገኘው የተዛባ አቀራረብ ነው፡፡
ይህን መንገድ እኛ ብቻ ሳንኾን መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉ ቅዱሳን ሰዎች፥ እንዲሁም ቀደምት አበው፥ ራሱም የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ተጠቅመዉበት ይገኛል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት፤
·        ”ራእዩንም ካየ በኋላ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ልንወጣ ፈለግን፥ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራን መስሎናልና።” (ሐ.ሥ. 16፥10)
·        “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ኹሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።” (ዮሐ. 21፥25)
·        “እንግዲህ ስለ አኹኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ኾኖ ቢኖር መልካም ነው።” (1ቆሮ. 7፥26)
·        “እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።” (1ቆሮ. 7፥40)
·        “ነገር ግን ሰው፥ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል።” 1ቆሮ 15፥35
·        “ኹል ጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል።” (2ጴጥ. 1፥13)
ሐዋርያት በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ በ”መስሎናል” እና በ“ይመስለኛል” የጻፉት እምነታቸውን በመሰለኝ ላይ ስለ መሠረቱ ነውን? አይደለም፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ መግለጥ የፈለጉትን ነገር ሊገልጡ የሚችሉት በዚህ መንገድ በመኾኑ ነው ብለን ከመውሰድ በቀር ምን ማለት ይቻላል?
ከቀደምት አበው መካከል መድሎተ ጽድቅ መመዘኛው ያደረገው ዮሐንስ አፈ ወርቅ በይመስለኛል ያቀረባቸውን ሐሳቦች አሉ፤ ለምሳሌ፦
·        ወይመስለኒ ከመ ይኤምር በዝየ በእንተ ፍልጠት ወተራኅቆ - በዚህ ስለ መለያየትና መራራቅ የሚያመለክት ይመስለኛል” (ድርሳን 6 ቍጥር 121 ገጽ 149)፡፡
·        “ሊተሰ ይመስለኒ ከመ ውእቱ ኢያርመመ ፍጹመ ወኢተናገረሂ ፈቂዶ ከመ ያፍትዎሙ ለሰማዕያን - ለእኔ ሰሚዎቹን ያስመኛቸው ዘንድ ወድዶ ፈጽሞ ዝም እንዳላለና እንዳልተናገረ ይመስለኛል” (ድርሳን 8 ቍጥር 166 ገጽ 187)፡፡
·        ወይመስለኒሰ ከመ እሙንቱ ያንኰረኵሩ ኀበ ኵሉ ምግባር - እነርሱ ወደ በጎ ሥራ ሁሉ እንደሚሄዱ ይመስለኛል” (ድርሳን 8፣ ቍጥር 295፣ ገጽ 195)፡፡
ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እነዚህ አስተያየቶቹን በ“ይመስለኛል” ያቀረበው ለምንድነው? የእርሱ አስተያየት እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ አቋም ስላልኾነ አይደለምን? አስተያየቱን በርግጠኛነት “እንዲህ ነው” ብሎ ቢያቀርብ ግን ጥያቄ ሊነሣበት ይችላል፡፡ ምክንያቱም የዕብራውያንን መልእክት ሲተረጕም በራሱ መረዳትና ግንዛቤ፥ ዕውቀትም ላይ ተመሥርቶ ነውና፥ በሌላው ዘንድ ተቀባይነት እንዳያጣ ወይም ሌላው ተነሥቶ ልክ አይደለህም ቢለው ይህ የእኔ አስተያየት ነው ብሎ ለመመለስ ይችላል፤ ወይም አንባቢው በራሱ ይህ የዮሐንስ አፈ ወርቅ አስተያየት ነው ብሎ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ያደረገው ትክክል ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት “ነው” ብሎ ማመን፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጥ ኾኖ ያልሰፈረን ሐሳብ ደግሞ “ሊኾን ይችላል”፥ “ይመስለኛል” ብሎ ማቅረብ ትሕትና ነው፡፡ የራስን ሐሳብና አስተያየት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት “ነው” ብሎ ማቅረብ ግን ድፍረትና ትዕቢት ነው፡፡
“መድሎተ ጽድቅ” ስለ ዘርዐ ያዕቆብ በጠቀሰበት ክፍል ንጉሡ ሰው በመኾኑ ስሕተቶችን ሊፈጽም እንደሚችል ከጠቀሰ በኋላ፥ ንስሓ ስለ መግባቱ ርግጠኛ ያልኾነንና የራሱን መላምት እንዲህ በማለት አስቀምጧል፡፡ “ንስሓ ገብተው ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው ሊኾን የሚችሉ ያለፉ ሰዎችን ኀጢአት ማንሣት ቊስል ለቊስል የሚሄዱ ዝንቦችን መምሰል ነው፡፡” (2007፣ 36 አጽንዖት የግል)፡፡ ከጥቅሱ መረዳት እንደሚቻለው፥ መጽሐፉ ይህን መላምት በግልጥ መንገድ አላቀረበውም። ምክንያቱ ደግሞ እኛን በተሳሳተ መንገድ በመሰለኝ ነው የሚያምኑት ስላለ፥ አንተስ? የሚል ጥያቄ እንዳይነሣበት ለማድረግ ይመስላል (ይህን ሐሳብ በይመስላል ካልኾነ በምን ይገልጧል?)። በዘወርዋራ መንገድ ለማቅረብ ይሞክር እንጂ ዞሮ ዞሮ “ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ንስሓ ገብቶ ሊኾን ይችላል” ነው ያለው፡፡ ይህን ጕዳይ በርግጠኛነት ሳይኾን በ“ሊኾን ይችላል” በማቅረቡ አልተሳሳተም፡፡ ወይም እምነቱን በ“መሰለኝ” ላይ ነው የመሠረተው አያሰኘውም፤ ምክንያቱም ይህን ጕዳይ በመሰለው መንገድ ካልኾነ በቀር በርግጠኛነት ለመናገር የሚያበቃ ማስረጃ የለውም፡፡ ታዲያ እርሱ የእርሱን መላምት በመሰለኝ ማስቀመጥ ከቻለ፥ እኛንስ የሚከለክለን ማነው? የሚያሳዝነው ግን በዚህ መንገድ ሊታይ የሚገባውን ግልጥና ቀላል ጕዳይ፥ እምነትን ያኽል ነገር በመሰለኝ እንደ መሠረትን አድርጎ ማቅረቡ ያስተዛዝባል እንጂ ማንንም አያሳምንም፡፡ በእውነት ማሸነፍ ያልቻለ በሐሰት ማደናገሩ አይቀርም፡፡          
·        “... አቡነ ተክለ ሃይማኖትና አባ ኤዎጣቴዎስ በአስተምህሮ የነበራቸውን ልዩነት በዝርዝር ለመገንዘብና ለማስገንዘብ ለረጅም ጊዜ የታሪክ ጥናት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ … እነዚህን ከመሳሰሉት ጥቃቅን ልዩነቶች በስተ ጀርባ የተለያዩ የስብከተ ወንጌል ድርጅቶችን ወደ ማቋቋም ያደረሱ መጠነ ሰፊ ልዩነቶች ሳይኖሩ እንዳልቀሩ ይገመታል፡፡” (ጮራ ቊ. 16 ገጽ 29) ብሎ ስለ ጠቀሰው፡፡
·        እንደ እውነቱ ከሆነ አባ እስጢፋኖስ የተከሰሰባቸውን ነጥቦች ስንመረምር መሠረተ እምነቱ
የሙታንን ነፍሳት ከመማጸን (እም ተማኅፅኖተ ነፍሳተ ሙታን)
መናፍስትን ተስፋ ከማድረግ (እም ተሰፍዎተ መናፍስት)
ከቅርጻ ቅርጽ አምልኮ (እም አምልኮ ኪነት) የጸዳ እንደ ነበር ልንገምት እንችላለን (ጮራ ቊ. 18 ገጽ 22)
የመጀመሪያው ጥቅስ በሃይማኖት ታሪክ ውስጥ በሁለት መነኮሳት መካከል የተከሠተ የአስተምህሮ ልዩነትን የተመለከተ ጕዳይ ነው፡፡ በጥቅሉ ከሚባለው ውጪ ስለ ልዩነታቸው በዝርዝር የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የጮራ ትኵረት ጥልቅና ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ከመኾኑ አንጻር ልዩነቱን በዝርዝር ማቅረብ እንደማይቻል ማሳየት ነው፡፡ እስከዚያው ግን ጕዳዩን ማቅረብ የሚቻለው ከሚታዩት አንዳንድ ሁኔታዎች በመነሣት ግምታዊ አስተያየት በመስጠት ይሆናል፡፡ ከላይ እንደ ጠቀስነው “መድሎተ ጽድቅ”ም እኮ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ንስሓ ገብቶ ሊኾን እንደሚችል ግምታዊ አስተያየቱን ሰጥቷል (ገጽ 36)፤ ግምታዊ አስተያየቱን እንደ አስተያየት መውሰድ እንጂ ለምን በግምት ይናገራል ማለት ግን አይቻልም፡፡
መጽሐፉ አንባቢውን ለማደናገር እንዲህ ያሉትንና በሃይማኖት ውስጥ የተከሠቱ ታሪካውያን ጕዳዮችን ሃይማኖታውያን አድርጎ በማቅረብ፥ እኛ ሃይማኖትን ያኽል ነገር በይመስላል እንደ መሠረትን አድርጎ ማቅረቡ ራሱን ትዝብት ላይ ከሚጥለው በቀር እውነተኞች አንባብያንን ማሳሳት አይቻለውም፡፡ ምናልባት ይህ በኹለቱ መነኮሳት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በግምት ሊቀርብ አይገባም የሚል ከኾነና ርግጠኛውን ካወቀ፥ ከሌሎች ጽሑፎቻችን ላይ ቈንጽሎ የወሰዳቸውንና ለእርሱ በሚመቸው መንገድ የተቻቸውን ጥቅሶች በተቸበት መንገድ እነዚህንም መተቸትና ርግጠኛውን መናገር ነበረበት፤ ነገር ግን እንዲህ ማድረግ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ስለዚህ ጕዳይ ከግምት ያለፈ ርግጠኛውን ነገር ማቅረብ አይችልምና፡፡   
ስለ አባ እስጢፋኖስ የተገለጠውን በተመለከተ የቀረበው ትችት “ጕዳዮችን የራሳቸው ደጋፊ አስመስለው ለማቅረብ ካላቸው ጕጕት የተነሣ ብቻ በታሪክ ራሱን በቻለ ኹኔታ ሊጠና የሚገባውን ጕዳይ በመቈንጸል አንዳችም ማስረጃ ሳያቀርቡ እንዲሁ በግምት ብቻ” በድፍረት ተናግረዋል ይላል (ገጽ 33)፡፡ በቅድሚያ በአባ እስጢፋኖስ ጕዳይ ላይ ጸሓፊው የያዘው አቋም ብዙዎች እርሱን የመሰሉ ሰዎች የያዙት አቋም እንደ ኾነ ግልጥ ነው፡፡ ይህ አቋም በተለይ የደቂቀ እስጢፋኖስ ገድላት ተተርጕመው ለንባብ መብቃታቸውን ተከትሎ የተያዘ አቋም እንደ ኾነም ይታወቃል፡፡ ከዚህ በፊት እነርሱን “ፀረ ማርያም”፣ “ፀረ ዕፀ መስቀል”፣ “አይሁድ” ወዘተ. ማለት የተለመደ ነበር፡፡ ለዚህም በተኣምረ ማርያምና በእርሱ ላይ በተመሠረተውና “ማሕሌተ ጽጌ” በተሰኘው ድርሰት ከአባ እስጢፋኖስ ጋር በተገናኘ የተነገረውን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው (ተኣምረ ማርያም ማሕሌተ ጽጌ “ዘሰ ይብል አፈቅረኪ” የሚለውን ይመለከቷል)፡፡ ከዚህ የተነሣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መናፍቃን፥ ፀረ ማርያም ሲባሉ የኖሩት ደቂቀ እስጢፋኖስ፥ በአኹኑ ጊዜ ያ ስማቸው እየ ተለወጠና ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጋር የነበራቸው ውዝግብ የሃይማኖት ሳይኾን ሌላ እንደ ኾነ ሲነገር እየሰማን ነው፡፡ ጕዳዩ የሃይማኖት እንደ ነበረ ግን ማስተባበል አይቻልም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱም ይህን ታምናለች፡፡ “ደቂቀ እስጢፋ /የእስጢፋ ተከታዮች በአለቃቸውና በመምህራቸው በሠርጸ እስጢፋ መሪነት ይሰጡት የነበረው ትምህርት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ክርክር ተነሥቶ መለያየት ተፈጥሮ ነበር፡፡” (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻፥ 2000፣ ገጽ 22)፡፡
የደቂቀ እስጢፋኖስን ገድላት ስንመረምር እምነታቸው በዘመናቸው በደረሱበት የመረዳት ደረጃ፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተና ከእርሱ ዝንፍ ላለማለት የሚጠነቀቁ እንደ ኾኑ እናስተውላለን፡፡ ለዚህም በተደጋጋሚ ተጠይቀው የገለጡት የእምነት ዐቋማቸው፥ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው እምነትና ስግደትን (አምልኮትን) ለእርሱ ብቻ ለመስጠት እንጂ ለሌላ አካል ላለማጋራት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት የደረሰ ዋጋ መክፈላቸው፥ ለቅርጻ ቅርጽና ለሥዕላ ሥዕል የነበራቸው ዐቋም በጮራ እንደ ተገለጠው መኾኑ ለማንም ግልጥ ነው፡፡
“መድሎተ ጽድቅ” ግን በጮራ ቍጥር 18 ላይ የአባ እስጢፋኖስን ገድል መሠረት በማድረግ የቀረበውን ጽሑፍ ያኽል እንኳ ስለ እነርሱ ምንም ማለት ሳይችል፥ እንዲሁ በደፈናው “በታሪክ ራሱን በቻለ ኹኔታ ሊጠና የሚችለውን ጕዳይ በመቈንጸል አንዳችም ማስረጃ ሳያቀርቡ እንዲሁ በግምት ብቻ ‘ይገመታል ልንገምት እንችላለን ብለው’ ደፍረው መናገራቸውን ሲያዩት በአንድ በኩል በትምህርት በኩል ያለባቸውን መጐዳት፥ በሌላ በኩል ደግሞ በባዶው ደፋር መኾናቸውን ይመሰክርባቸዋል፡፡” ሲል ይተቻል፥ ይዘልፋልም፡፡
ጮራ ገድለ አቡነ እስጢፋኖስን መሠረት አድርጎ ስለ አባ እስጢፋኖስ የተረዳውን ጻፈ፡፡ የደረሰበትን ድምዳሜም “ነው” ብሎ በርግጠኛነት መደምደም አያስኬድም፤ ሌሎች ደግሞ ሌላ ሊሉ ይችላሉና፡፡ ከ“መድሎተ ጽድቅ” የሚጠበቀው ጮራ ያቀረበውን ሐሳብ ሊያስለውጥ የሚችል በማስረጃ የተደገፈ ሌላ ሐሳብን ማቅረብ ነበር፡፡ ነገር ግን ባዶ ትችት ከማቅረብ በቀር እንዲህ ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህ አንጻር በትምህርት በኩል የተጐዳውም ኾነ በባዶው ደፋር የኾነው ማን እንደ ኾነ ፍርዱን ለአንባቢ መተዉ ሳይሻል አይቀርም፡፡     
·         “መዝሙረ ዳዊት 1ዐ(11)፥1-7 ላይ ያለው ቃል ከሌዋውያን መካከል የሆነው የመዘምራኑ አለቃም ዝማሬውን የሚመራ ሲኾን ሌዋውያን መዘምራንና ምናልባትም ሕዝቡ ጭምር በተሰጥዎ መልክ ምላሹን እያዜሙ በማስተዛዘል አምልኮ የሚያቀርቡበት መዝሙር ሳይሆን አይቀርም” (ጮራ ቊ. 28 ገጽ 3)፡፡
ይህ ጽሑፍ የመዝሙሩን ቃላት ሳይኾን መዝሙሩ የቀረበበትን መንገድ በተመለከተ ነው ሐሳብ ለማቅረብ የሞከረው፡፡ ይህ የመዝሙር ክፍል የቀረበበትን መንገድ ሲመረምር እንዲህ ሳይኾን አይቀርም ብሎ ነው የጻፈው፡፡ እንዲህ ከማለት የሚከለክል አሠራር የለም፡፡ ርግጡ ይህ ነው ብሎ ቢያቀርብ ኖሮ ግን እርሱ አጠያያቂ ይኾን ነበር፡፡ ስለዚህ የቀረበውን ሐሳብ እንደ አስተያየት እንጂ እንደ እምነት ማንም ሊወስደው አይችልም፡፡ ወይም ደግሞ ጮራ በሚለው መንገድ ሳይኾን በሌላ መንገድ ነው የቀረበው ማለትም ከተቻለ ያን ማቅረብና ማሳየት ጥሩ ይኾን ነበር፡፡ ይህ ባልኾነበት ኹኔታ ባዶ መተቸት ግን ራስን ያስገምታል፡፡
·        “ወንጌላዊው ሉቃስ በስሙ የሚታወቀውን ወንጌል ለመጻፍ የተነሣሣበትን ምክንያት በመጀመሪያው ምዕራፍ ውስጥ መዝግቧቸዋል፡፡ ቃሉን እንዲያገለግሉ የተመረጡትና የዐይን ምስክሮች የኾኑት ደቀ መዛሙርት ያስተላለፉት ማስረጃ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ … በርግጥም ሉቃስ የቃሉ አገልጋዮች ሲል የኾኑት ምስክሮች ያስተላለፉት የጠቀሰው ማስረጃ እርሱው ራሱ የሐዋርያት ሥራ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ “የሐዋርያት ትምህርት” በማለት የዘገበው ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡” (ጮራ ቊ. 28 ገጽ 13)፡፡
በዚህም ጥቅስ በተጠቀሱት ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተገኘውን ፍንጭ መሠረት በማድረግ የተሰጠ አስተያየትን ነው የምናየው፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው “ከመጀመሪያው በዐይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የኾኑት” ያስተላለፉትን መሠረት በማድረግ መኾኑን ጠቅሷል (ሉቃ. 1፥1-4)፡፡ ይህ “ከመጀመሪያው በዐይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የኾኑት” ያስተላለፉት ምንድን ነው? ይህን ማንም በርግጠኛነት መናገር አይችልም፡፡ ኾኖም ይኸው ጸሓፊ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ “የሐዋርያት ትምህርት” ብሎ የጠቀሰው አለ (2፥42)፡፡ ስለዚህ ጮራ፥ “ሉቃስ የቃሉ አገልጋዮች ሲል የኾኑት ምስክሮች ያስተላለፉት ሲል የጠቀሰው ማስረጃ እርሱው ራሱ የሐዋርያት ሥራ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ‘የሐዋርያት ትምህርት’ በማለት የዘገበው ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡” ሲል በጕዳዩ ላይ ግምቱን አስፍሯል፡፡ ይህን ጕዳይ “ነው” ብሎ ያለ አንዳች ማስረጃ በድፍረት ከማቅረብ ይልቅ፥ በዚህ መንገድ ማቅረብ ትሑት የኾነ አቀራረብ ነው፡፡
አቀራረቡ በጊዜው የሐዋርያት ትምህርት የተባለ ትምህርት መኖሩን የሚያምን እንጂ በመኖሩ ላይ ርግጠኛነት የማይሰማው አቀራረብ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሉቃስ በወንጌሉ “ከመጀመሪያው በዐይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የኾኑት እንዳስተላለፉልን” ያለው፥ በሐዋርያት ሥራ ደግሞ “የሐዋርያት ትምህርት” ያለው ትምህርት የቱ እንደ ኾነ ግን ከመገመት በቀር ርግጠኛ ኾኖ መናገር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ጮራ ኹለቱ ተመሳሳይ ወይም አንድ ሊኾኑ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ሌላ ግምት ካለም አሳማኝ ማስረጃ አቅርቦ ያን ማስፈር ይቻላል፡፡ የተገለጠውን እውነት “ነው” ብሎ ማመን፥ ያልተገለጠውን ደግሞ የተቻለውን ያኽል መመርመርና ግምትን ማስቀመጥ በመሰለኝ እንደ ማመን ተደርጎ ሊወሰድ ግን አይገባም፡፡  
·        “… ፍጹም አምላክ የሆነ ቃል ፍጹም ሰው ሆነ ብላ ቤተ ክርስቲያን በሙሉ አንደበቷ የምትመሰክርለት ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤ በኋላ ፍጹም አምላክ እንጂ ፍጹም ሰው ሊባል አይገባም የሚል ሐሳብ ሲነገር ተሰምቷል፡፡” (ጮራ ቊ. 16 ገጽ 1)፡፡
በቅድሚያ ይህ ጥቅስ በመሰለኝ የቀረበ ሳይኾን በርግጠኛነት ሲነገር ከተሰማው የተጠቀሰ ነው፡፡ ይህን በአደባባይ የተናገረው ሰው የሰጠው ምስክርነት ስሕተት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱም ትምህርት አይደለም፡፡ ይኹን እንጂ ብዙ ጊዜ ይህን የመሰሉ ትምህርቶች ሲተላለፉ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ዛሬ በጕልሕ የሚሰበከው አምላክነቱ ነው እንጂ ሰብእነቱም አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነውና ያ ሳይሸራረፍ፥ ሳይቀነስለትና ሳይጨመርበት ሚዛኑን ጠብቆ መሰበክ አለበት፡፡
ሌላው “መድሎተ ጽድቅ” ሊተቸው የሞከረው ሐሳብ፥ ከአንድምታ ጋር በተያያዘ የተጻፈውን ነው፡፡ “… ለእነርሱ ኑፋቄ የማይመች ሲኾኑ[ን] ‘አንድም’ እየተባለ መተርጐም የለበትም ብለው ይቃወማሉ፡፡”  (ገጽ 33፡34) በማለት ከተቀበረ መክሊት መጽሐፍ ላይ የሚከተለውን ጠቅሷል፡፡
·        “... ስሕተቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገቡ ሰፊ በር የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ችግር ነው በቤተ ክርስቲያናችን የሚታወቀው አንድምታ የተሰኘው የትርጓሜ ስልት… እውነትን ዐፍኖ ስሕተትን በማራመድ ረገድ ብዙ ረድቷል፡፡ አንድምታ በአንድ የእግዚአብሔር ቃል ላይ የተለያዩና ፊተኛው ትርጉም በኋለኛው የሚፈርስበት ብዙ ትርጉሞችን ስለሚሰጥ ሰው አንድ ተጨባጭ የሆነ ቁም ነገር እንዲይዝ አያስችለውም፡፡ በዮሐ. 1፥49 ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለናትናኤል፥ “ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ” ብሎ የተናገረው ግልጽ የሆነ ቃል በባለ አንድምታዎች ዘንድ ሌላ ድብቅ ምስጢር እንዳለው ተቈጥሮ ስድስት ዐይነት አንድምታዊ ትርጓሜዎች መሰጠታቸውን በምሳሌነት እንመልከት፡- …. (ስድስቱም ተዘርዝረዋል) በዚህ መልክ የሌለውን ድበቅ ምስጢር ለማውጣት ሲባል የእግዚአብሔርን ቃል ማስጨነቅ ትርፉ የፈጠራ ድርሰትና ታሪክ መፈልሰፍ ሲሆን ኪሣራው ደግሞ ከእግዚአብሔር ዐሳብ ርቆ መሳሳት ነው...” (የተቀበረ መክሊት 1993፣ ገጽ 95-96)፡፡
እንደ ገናም፥ “… ኾኖም ለእነርሱ የሚስማማና የሚደግፋቸው መስሎ ሲታያቸው ግን ያንኑ የነቀፉትን የትርጓሜ ስልት ይጠቀሙበታል፡፡ ለምሳሌም ከመሠረቱ የተለዩ ስለ ኾኑ ከአበው ቀደምት የትርጓሜ ትምህርትና ሐሳብ ምንም ባልተገናኘ መንገድ በለመዱት የግምትና የ‘ሊኾን ይችላል’ አካሄድ እንዲህ ይላሉ፡፡” (መድሎተ ጽድቅ 2007፣ ገጽ 34) ይላል፡፡
በመሠረቱ አንድን ምንጭ ለጥናት ወይም ለጽሑፍ ሥራ የምንጠቀምበት ስለምንደግፈው ወይም ስለምንቃወመው ሳይኾን ከምናጠናው ጕዳይ ወይም ከምንጽፈው ጽሑፍ ጋር በአዎንታዊም ኾነ በአሉታዊ መንገድ ተያያዥነት ስላለው መኾን አለበት፡፡ ከዚያ ምንጭ ውስጥ የምንቀበለውና የማንቀበለው፥ የምንደግፈውና የምንቃወመው ትምህርት ሊኖር ይችላል፡፡ ‘ከዚያ መጽሐፍ ውስጥ የምትጠቅሱ ከኾነ መጽሐፉ የሚለውን በሙሉ መቀበል አለባችሁ፥ የማትቀበሉት ትምህርት ካለ ደግሞ መጽሐፉን መጥቀስ አትችሉም’ የሚል ተፈጥሯዊም ኾነ ሰው ሠራሽ ሕግ ግን ሊኖር አይችልም፤ አይገባምም፡፡ ቢኖር እንኳ የሚቀበለው አይኖርም፡፡
አንድምታ ትርጓሜ አንዱ የትርጓሜ ስልት ቢኾንም፥ ትክክለኛነቱም ኾነ ስሕተትነቱ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚመዘን እንደ ኾነ ግልጥ ሊኾን ይገባል እንጂ፥ ስሕተት አልባ የትርጓሜ ስልት ነው ማለት ከክርስትና ትምህርት ውጪ የኾነ አመለካከት ነው፡፡ ለምሳሌ በተቀበረ መክሊት ውስጥ ለዮሐንስ ወንጌል 1፥49 የተሰጠው አንድምታዊ ትርጓሜ ላይ የቀረበው ሐተታ ችግሩ ምንድነው? “መድሎተ ጽድቅ” ይህን ችግር በግልጥ አላስቀመጠም፡፡ በደፈናው፥ “… ለእነርሱ ኑፋቄ የማይመች ሲኾኑ[ን] ‘አንድም’ እየተባለ መተርጐም የለበትም ብለው ይቃወማሉ፡፡” ነው ያለው፡፡ አንባቢው እንዳያገናዝብ ግልጥ ለኾነውና ምንም አንድምታዊ ትርጓሜ ለማያሻው የዮሐንስ ወንጌል 1፥49 ቃል የተሰጡትን ስድስት ፍቺዎች በቅንፍ “ስድስቱም ተዘርዝረዋል” ብሎ ነው ያለፋቸው፡፡ ምናልባት ስድስቱም ለአንባቢው እንዳለ ቢቀርቡና በየተቀበረ መክሊት ላይ ከተሰጠው ሐተታ ጋር ቢገናዘቡ አንድምታ ያለበትን ችግር በግልጥ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በ2006 ዓ.ም. ተሻሽሎ ለ3ኛ ጊዜ በታተመው “የተቀበረ መክሊት” ላይ የቀረበው ሐተታ እንዲህ ይላል፡፡
‘የአንድም ትርጓሜ የሚባለው አንድ ጊዜ ከተተረጐመ በኋላ እንደ ገና አንድም እያለ እስከ ዐሥራ ዐምስት ጊዜ ድረስ የሚያወርዱት አወራረድ፥ የሚሰጡትም ሐተታ ነው።’ (ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም (አልቦ ዓ.ም.)፣ ገጽ 216-217)።አንድምታ የተለያዩ የመጻሕፍት መምህራን በአንድ ንባብ ላይ የሚሰጡት ልዩ ልዩ ትርጓሜ ስብስብ እንደ ኾነ በቃል የሚናገሩ የመጻሕፍት መምህራን አሉ። በአንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንባብ ላይ የተለያዩና ፊተኛው ትርጉም በኋለኛው የሚፈርስባቸው ልዩ ልዩ ትርጉሞችን ስለሚሰጥ፥ አንድ ተጨባጭ የኾነ ቁም ነገር እንዳንይዝ ያደርገናል። ለምሳሌ፦ በዮሐ. 1፥49 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለናትናኤል፥ “ፊልጶስ ሳይጠራኽ ከበለስ በታች ሳለኽ አየኹኽ” ብሎ የተናገረው ግልጥ የኾነና ምንም ትርጓሜ የማያሻው ንባብ አለ። በባለ አንደምታዎች ዘንድ ግን ከንባቡ ውስጥ “በለስ” የሚለው ቃል ሌሎች የተደበቁ ምስጢራት እንዳሉት ተቈጥሮ ስድስት ልዩ ልዩ አንድምታዊ ትርጓሜዎች ተሰጥተዉታል። እነርሱም፦
1.      ሄሮድስ ሕፃናትን በገደለ ጊዜ ወላጅ እናቱ [ናትናኤልን] በቀፎ አድርጋ ከበለስ ሥር ሰውራው ነበርና ያን ጊዜ ያዳንኹኽ እኔ ነኝ ሲል፤
2.     አንድም፥ [ናትናኤል] ሰው ገድሎ ከበለስ ሥር አስቀብሮ ነበርና ዐውቅብኻለኹ ሲለው፤
3.     አንድም፥ [ናትናኤል] የጕልማሳ ሚስት ቀምቶ ከበለሱ ሥር የማይረባ ሥራ ሲሠራ ነበርና ዐውቅብኻለኹ ሲለው፤
4.     አንድም፥ [ናትናኤል] ባለጠጋ ነው፤ ከበለስ ሥር ወይፈኑን ሲያስፈትን፥ ፈረስ በቅሎ ሲያስገራ ይውል ነበረና ያን ማወቁን ሲነግረው፤
5.     አንድም፥ [ናትናኤል] ምሁረ ኦሪት ነውና ከበለስ ሥር ኾኖ ትንቢት ደረሰ፥ ሱባኤ ሞላ እያለ ይውል ነበረና ዐውቅልኻለኹ ሲለው፤
6.    አንድም፥ በለስ ቅጠሉ ሰፊ ስለ ኾነ [ናትናኤልን] ኀጢአት ሰፍኖብኻል ሲለው ነው ይላል (ወንጌል ቅዱስ ንባብና ትርጓሜው 1988፣ ገጽ 458)።
በዚህ መልክ የሌለውን “ድብቅ ምስጢር” ለማውጣት ሲባል የእግዚአብሔርን ቃል ማስጨነቅ፥ ትርፉ የፈጠራ ድርሰትና ያልተፈጸመ የፈጠራ ታሪክ መጻፍ ይኾናል። ኪሳራው ደግሞ ከእግዚአብሔር ሐሳብ ርቆ መሳሳት ነው። እነዚህ ስድስት አንድምታዊ ትርጓሜዎች፥ ናትናኤል ክፉውንም ደጉንም ለመሥራት ከበለሱ ዛፍ ጋር የተማማለ አስመስለውታል። ከአንድምታዊ ትርጓሜዎቹ መካከል አንዳንዶቹም፥ ስለ ናትናኤል በቅዱስ ወንጌል ከተጻፈውና ከተገለጠው ሐሳብ ጋር ይጋጫሉ። ይህም ትርጓሜዎቹ ሐሰተኞች መኾናቸውን ያመለክታል። 
በተራ ቍጥር 2 እና 3 የተገለጡት፥ ጌታ ስለ ናትናኤል ከሰጠው ምስክርነት ጋር አይስማሙም፤ ይጋጫሉ። ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፥ ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ’ (ቍጥር 48)። በተጨማሪ፥ ናትናኤል፥ ‘ምሁረ ኦሪት ነው’ የተባለውና በ5ኛ ተራ ቍጥር ላይ የተቀመጠው፥ ናትናኤል ከሰጠው ምስክርነት ጋር አይስማማም። ፊልጶስ ለናትናኤል፥ ‘ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስን አግኝተነዋል’ ብሎ ሲነግረው፥ ናትናኤል በምሁረ ኦሪትነቱ፥ በነቢይ፥ ‘ናዝራዊ ይባላል’ ተብሎ የተነገረውን ሊያስተውል በተገባው ነበር። እርሱ ግን ከዚያ በተቃራኒ፥ ‘ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?’ ብሎ ምሁረ ኦሪት አለ መኾኑን ገልጧል (ዮሐ. 1፥46-47፤ ማቴ. 2፥23)።
‘ፊልጶስ ሳይጠራኽ ከበለስ በታች ሳለኽ አየኹኽ’ የሚለው ንባብ ያለው ግልጥና አንድ መልእክት ነው፤ ፊልጶስ ናትናኤልን ሳይጠራው በፊት፥ ናትናኤል ተቀምጦም ይኹን ቆሞ ብቻ ከበለሱ ዛፍ ሥር ይገኝ ነበር፤ ጌታም ይህን ኹኔታ በስፍራው ሳይገኝ አስቀድሞ ያወቀ መኾኑን ያመለክታል። ይህም ለናትናኤል ትልቅ ምልክት እንደ ኾነው፥ መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ’ (ቍጥር 50) በማለት እምነቱን እንዲገልጥና ክርስቶስን እንዲከተለው እንዳደረገው እንረዳለን (ዮሐ. 21፥2) (የተቀበረ መክሊት 2006፣ ገጽ 94፡95፡96)።
መድሎተ ጽድቅ በአንድ ወገን አንድምታን ተቃውመን ስናበቃ ለራሳችን የሚስማማና የሚደግፈን መስሎ ሲታየን ግን ያንኑ የነቀፍነውን የትርጓሜ ስልት እንደምንጠቀም ጠቅሶ፥ “ከአበው ቀደምት የትርጓሜ ትምህርትና ሐሳብ ምንም ባልተገናኘ መንገድ በለመዱት የግምትና የ‘ሊኾን ይችላል’ አካሄድ እንዲህ ይላሉ፡፡” በማለት የሚከተለውን ማስረጃ ከጮራ አቅርቧል፡፡
አንደኛ ትውፊት ራእይም የራእይ ግብም አይሆንም… ጠቢባኑ (ሰብአ ሰገል) ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ ማንነታቸው በግልጽ ባይነገርም የመሲሕን መገለጽ ሲጠባበቁና ሲናፍቁ ከቈዩት ወገኖች መካከል መኾናቸው አያጠያይቅም፡፡ ምናልባት ወደ ባቢሎን ተማርከው ከሄዱ በኋላ እስከ ሕንድ ድረስ ተበትነው ከነበሩትና ሳይመለሱ እዚያው ከቀሩት እስራኤላዊ የባቢሎናውያንን ጥበብ ከእነ ዳንኤል ጋር ከተማሩ በኋላ በዳንኤል ሥር የተመደቡት ጠቢባን ዝርያዎች ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ (ጮራ ቊ. 11 ገጽ 5)፡፡
ይህን በተመለከተ ከላይ የሰጠነው ሐተታ እንደ ተጠበቀ ኾኖ፥ በአንድምታና በዚህ አስተያየት መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት መግለጥ ያስፈልጋል፡፡ አንድምታ ለአንድ ቃል የሚሰጣቸውን የተለያዩ ትርጓሜዎች “ነው” ብሎ በርግጠኛነት ነው የሚያቀርበው፡፡ ላላ አድርጎ “ሊኾን ይችላል” ብሎ ቢያቀርብ ኖሮ እንደ አስተያየት ተወስዶለት ትችቱ ምናልባት በአስተያየቱ ላይ ያነጣጠረ በኾነ ነበር፡፡ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ መምጣታቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት በመኾኑ “መጡ” ተብሎ ተገለጠ፡፡ የመጡበት አቅጣጫም “ምሥራቅ” ተብሎ ተጠቍሟልና ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ከምትገኘው ከኢትዮጵያ እንዳልኾኑ ግልጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በኢየሩሰሌም ሰግዶ ሲመለስ የደቡብን አቅጣጫ ይዞ ነበር ወደ አገሩ የተመለሰው (ሐ.ሥ. 8፥26-28)፡፡ ስለዚህ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ ከተባለ በጮራ ከተጠቀሱት አገሮች ነው የሚለው አያስኬድም ማለት አይቻልም፡፡  

·        “… በዚሁ መሠረት ዐፄ ዐምደ ጽዮን ታላቋና ታናሽዋ በመባል በንግሥትነት የተሰየሙ ሁለት ሚስቶችና ቊጥራቸው የማይታወቁ ዕቁባቶች ነበሩት፡፡ በዚህም ሥራው ከቤተ ክህነት ተቃውሞ አልደረሰበትም፡፡ ምናልባትም ለሁለቱም ንግሥታት ሥርዓተ ንግሥ ፈጻሚዋ ቤተ ክህነት ልትሆን እንደምትችል ማሰብን የሚከለክል አንዳችም ነገር የለም፡፡” (ጮራ ቊ. 15 ገጽ 26)፡፡ (መድሎተ ጽድቅ ገጽ 31-35)፡፡

በዚህ ክፍል የቀረበው አስተያየት በጊዜው ሊኖር የሚችለውን እውነታ ባገናዘበ መልኩ የቀረበ ነው፡፡ ታሪክን ስንመረምር የተጻፈ ርግጠኛ ነገር ባናገኝ በታሪኩ ውስጥ ያጋጠመውን ክሥተት መሠረት በማድረግ፥ በታሪኩ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማንነት በጊዜው ከነበረው ነባራዊ ኹኔታ ጋር በማገናዘብ አኹንም አስተያየት መስጠትን የሚከለክል የለም፡፡

“መድሎተ ጽድቅ” እስካኹን ለመመልከት የሞከርነውን ትችቱን ሲያጠቃልል እንዲህ ብሏል፤
“ስለ እምነት እንቈረቈራለን ባዮቹ ተሐድሶዎች እምነትን የሚያስረዱበት መንገድና ኹኔታ እንዲህ ያለ ነው፡፡ ‘ይመስላል’ ‘ይኾን ይኾናል’ ‘መገመት ይቻላል’ ‘ያስኬዳል’ ወዘተ[.] በሚሉ ሐሳቦች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሃይማኖት ግን ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እመኒ እወ እወ ወእመኒ አልቦ አልቦ ወፈድፋደሰ እም እሉ እም እኩይ ውእቱ - ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይኹን፤ ከእነዚህም የወጣው ከክፉው ነው’ ባለው መሠረት ‘ይመስላል’ ‘ሊያስኬድ ይችላል’ ወዘተ[.] እያሉ መቀባጠር ምናልባት ለሰብኣዊ አስተሳሰቦችና ለምድራዊ ርእዮቶች ካልኾነ በስተቀር ለክርስትና ቦታም አግባብነትም የላቸውም፡፡” (ገጽ 35)፡፡
ይህ የ “መድሎተ ጽድቅ” ድምዳሜ ስሕተት መኾኑን እስካኹን ያቀረብነው ሐተታ ያስረዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እኛ የተገለጠውንና እምነትን ‘ይመስላል’ ‘ይኾን ይኾናል’ ‘መገመት ይቻላል’ ‘ያስኬዳል’ ብለን አልጻፍንም፤ ልንጽፍም አንችልም፡፡ ከእምነት ውጪ በኾኑት፣ ባልተገለጡትና ሊመረመሩ በሚችሉት ጕዳዮች ላይ እነዚህን ቃላትና ሐረጋት የተጠቀምነው ግን የተረዳነውን ያኽል መረዳታችንን ለመግለጥ መሞከራችንንና የእኛ አስተያየት መኾናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ መወቀሥ የነበረብን እነዚህን “ነው” በሚል ርግጠኛ ቃል ገልጠን ብንገኝ ነበር፡፡ “መድሎተ ጽድቅ” እንደነዚህ ያሉት “…ምናልባት ለሰብኣዊ አስተሳሰቦችና ለምድራዊ ርእዮቶች ካልኾነ በስተቀር ለክርስትና ቦታም አግባብነትም የላቸውም፡፡” ያለው ግን እምነት ያልኾነውን ጕዳይ ኹሉ እምነት አስመስሎ በማቅረብ እንደ ኾነ ልብ ይሏል፡፡ እነዚህን ልል ግሶች መጽሐፍ ቅዱስም ቀደምት አበውም ለተገቢው ኹኔታና በተገቢው ቦታ እንደ ተጠቀሙባቸው ደግሞ ከላይ ተመልክተናልና፥ እነርሱም በክርስትና ቦታ የላቸውም ማለት ነው?

እውነተኛ ሐሳብ ይዞ ያልተነሣውና ያቀረበው ሐተታና ማስረጃ ያልተስማሙለት “መድሎተ ጽድቅ”፥ በዚሁ ሐሳቡን መቋጨት ሲገባው፥ ፈራሽ ሐሳቡን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አስደግፋለሁ ብሎ፥ ስለ መሐላ የተነገረውን ስለ ሃይማኖት በመጥቀስ “ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይኹን፤ ከእነዚህም የወጣው ከክፉው ነው” ለማለት ዳድቶታል፡፡ በቅድሚያ ቃሉ የተነገረው መማል የማይገባ መኾኑን ለማስረዳት ነው እንጂ ሃይማኖትን “ነው” ወይም “አይደለም” ብለን እንድንገልጥ አለ መኾኑን ማቴ. 5 ከቍጥር 33 ጀምሮ በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ክፍሉ ስለ ሃይማኖት የተነገረ ቢኾን ምናልባት “አዎን አዎን” በማለት ፈንታ “ነው”፥ “አይደለም አይደለም” በማለት ፈንታም “አይደለም” ተብሎ መገለጥ ነበረበት ማለት እንችላለን - “ነው” ወይም “አይደለም” በሉ እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው የ “መድሎተ ጽድቅ” ጸሓፊ ዐውደ ምንባቡን ጠብቆ ሳይኾን ለሐሳቡ የሚደግፈው የመሰለውንና ለእኔ ይስማማል ያለውን ጥቅስ ከመኻል እየመዘዘ እንዳሻው የሚጠቀም መኾኑን ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ከእውነት መራቅና በራስ መንገድ መጓዝ እንጂ ወደ እውነት መድረስ አይቻልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን እግዚአብሔር በተናገረበት መንገድ ሳይኾን እኛ በምንፈልገው መንገድ የምናነብ ከኾነም ራሳችንን እንጂ እግዚአብሔርን እየሰማን አይደለም፡፡ ታዲያ በክፍል ሦስት ምላሻችን መጨረሻ ላይ የመድሎተ ጽድቅ ጸሓፊ፥ ይህን መርሕ መናገር እንጂ መጠበቅ እንደማይታይበት የገለጥነው እውን አልኾነምን?

ይቀጥላል

1 comment:

  1. እግዚአብሔር ዲያቆን ያረጋል አበጋዝን በመንፈሱ ይጠብቅኝ። ቀጣዩ የመጽሐፋን ክፍል በጉጉት እንጠብቃለን። እናንተም መጽሐፉን እንድናነበው እዚህ በመጻፋችሁ ስላደረጋችሁት ነገር አመሰግናለሁ። መጽሐፋ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እምነትና አስተምህሮት በግልፅ አማርኛ የሚያስተምር ስለሆነና የኑፋቄ አስተምህሮዎችን ሀሳበ ቀሊልነት ያሳየኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ክብር ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን። አሜን።

    ReplyDelete