Monday, October 28, 2013

ንግባዕኬ ኀበ ጥንተ ነገር



ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ በተሰኘው በዚህ ዐምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት የበረዙና የከለሱ የስሕተት ትምህርቶችን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ጋር አንባቢው እንዲያነጻጽር ይቀርባሉ፡፡ 
         
         ማኅሌተ ጽጌ                                     መጽሐፍ ቅዱስ                                                      
በከመ ይቤ መጽሐፍ ማእከለ ፈጣሪ ወፍጡራን፡፡                አሐዱ እግዚአብሔር ወአሐዱ ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ
ለዕረፍት ዘኮንኪ ትእምርተ ኪዳን፡፡                              ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኮነ ሰብአ፡፡ ዘመጠወ ርእሶ ቤዛ ኵሉ፡፡
ሰንበተ ሰንበታት ማርያም ዕለተ ብርሃን፡፡          
ብኪ ይትፌሥሑ ዘገነተ ጽጌ ጻድቃን፡፡                              ትርጕም፡-
ወብኪ ይወፅኡ ኃጥኣን እምደይን፡፡                               አንድ እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል
                                                                      ያለው መካከለኛው ደግም አንድ አለ፡፡
ትርጕም፡-                                                           እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፡፡
መጽሐፍ እንዳለ በፈጣሪና በፍጡራን መካከል                                                               (1ጢሞ. 2$5-6)፡፡
ለዕረፍት የምልክት ኪዳን የሆንሽ
የሰንበታት ሰንበት ማርያም ሆይ!
አንቺ የብርሃን ዕለት ነሽ፡፡
አበባ በሞላበት ገነት ውስጥ ያሉ ጻድቃን በአንቺ ደስ ይላቸዋል፡፡
በአንቺም ኃጥኣን ከሥቃይ ስፍራ (ከሲኦል) ይወጣሉ




     
(ዘአለቃ ታየ ገብረ ማርያም)
አልቦ ካልዕ ስም ወአልቦ ካልዕ ፍኖት
እንበለ ስሙ ለክርስቶስ ዘይወስድ ኀበ ሕይወት
ወኢበመኑሂ እምፍጡራን ኢይትረኃው አንቀጸ ገነት
ኢበቅዱሳን አበው ወኢበመላእክት
እስመ ሎቱ ለባሕቲቱ ዘሰማይ መንግሥት
(ከመዝሙረ ክርስቶስ  ገጽ 71 የተወሰደ)

ትርጕም
ሌላ ስምና ሌላ መንገድ የለም፤
ወደ ሕይወት የሚወስድ ያለ ክርስቶስ ስም፡፡
ከፍጡራን በማንም የገነት በር አይከፈትም
በቅዱሳን አበው ወይም በመላእክት
የእርሱ ብቻ ነውና ሰማያዊው መንግሥት፡፡

(በጮራ ቍጥር 39 ላይ የቀረበ)

Monday, October 14, 2013

መሠረተ እምነት


ክርስቶስ ኢየሱስ የዐዲስ ኪዳን መካከለኛ

መንደርደሪያ
በሕክምናው ዓለም በሰው ውስጥ ያሉና የተለያዩ በሽታዎችን የሚያመጡ ተሐዋስያን ለምሳሌ፡- ባክቴሪያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከሚገድላቸው መድኀኒት ጋር የሚላመዱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከመድኀኒቱ ጋር ከተላመዱ ደግሞ የመድኀኒቱን የፈዋሽነት ዐቅም ያዳክማሉ፡፡ ሊያጠፉትም ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የበሽተኛው ጤና ይቃወሳል፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ጠቢባኑ$ ተሐዋስያኑ ከመድኀኒቱ ጋር የተላመዱበትን ምክንያት በመለየት መፍትሔ ይፈልጋሉ፡፡ ከመፍትሔዎቹ አንዱ ከቀድሞው የተሻለ ፈዋሽነት ያለውና ተሐዋስያኑን ሊያጠፋ የሚችል መድኀኒት መቀመም ወይም ማዘጋጀት ነው፡፡

ስለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽና በማያሻማ መንገድ ያስተምራል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን እውነት ለማስተሐቀር (ለማቃለል) የሚሞክሩ ከሓድያንና መናፍቃን ትናንት ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ለወደ ፊቱም ይኖራሉ፡፡ በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት በተለያዩ ዕትሞች ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት በልዩ ልዩ መንገድ ትምህርት ሲቀርብ መቈየቱን አንባብያን ያስታውሳሉ ብለን እናምናለን፡፡ ይሁን እንጂ ከመድኀኒቱ ጋር እንደሚላመዱ ተሐዋስያን$ በርእሰ ጕዳዩ ላይ ዛሬም መልካቸውን የቀየሩና የሚያደናግሩ የሚመስሉ ኢመጽሐፍ ቅዱሳውያን ትምህርቶች እንዳዲስ እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ መንገዶች እየተስተባበለ ያለውን የክርስቶስን መካከለኛነት$ በአሁኑ ጊዜ እየቀረበ ካለበት ስልት አንጻር፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረውና የቤተ ክርስቲያን አበውም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው በሚሰጡት ምስክርነት ላይ የተመሠረተ ትምህርት ማቅረብ አስፈልጓል፡፡

Friday, October 4, 2013

ርእሰ አንቀጽ


እስከ መቼ?

የሰው ልጅ በኑሮው ውስጥ እውነተኛ ፍርድን ይፈልጋል፡፡ የክፉዎች ተራ ሲያበቃና እውነት ስፍራዋን ስትይዝ ማየት ይናፍቃል፡፡ እውነትን ሁሉም ጥቁር ካባ ሲያለብሳት፥ እውነተኞች ጥላሸት ሲቀቡ ማየት ለእውነተኞች ሕመም አለው፡፡ እውነት በሌለበት ፍርድ የለምና እውነትና ፍርድ በጠፋበት ዓለም ላይ እውነተኞች ፍርድን ከሰማይ ይናፍቃሉ፡፡ የሰማዩ ፍርድ የዘገየ ሲመስልም እስከ መቼ? ይላሉ፡፡ ዐልፎ ዐልፎ የእውነት ጊዜ ብልጭ ይልና ብዙ ሳያጣጥሙት ቶሎ ድርግም ይልባቸዋል፡፡ የሐሰት ዘመን ሲረዝምባቸውም በሐዘን ድምፅ እስከ መቼ? ይላሉ፡፡

ሰው ስለ እውነት ከእግዚአብሔር ካልተማረ÷ ኑሮው የሚያስተምረው ጥቂቱን ነው፡፡ የእድሜ ርዝማኔም በራሱ የእውነትን ዕውቀት ለመግለጽ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ብዙ አይደለም፡፡ የታሪክ ክምርም ወደ እውነት አያደርስም፡፡ ወደ እውነት ለመድረስ እግዚአብሔር የዘመን ደወል ያደረጋቸውን እውነተኞቹን መምህራን ማድመጥ ይጠይቃል፡፡

Tuesday, October 1, 2013

መጽሐፍ ቅዱስ


የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት

ከሁሉን መርምር

በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ በብሉይ ኪዳን መጨረሻ ከገጽ 721-1037 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች የማይገኙ መጻሕፍት በመጨመራቸው ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ያውቃሉን? “ተጨማሪ (ዲዮትሮካኖኒካል) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት” በሚል የክፍል መጠሪያ የተጨመሩት መጻሕፍት ዐሥራ ዐምስት ናቸው፡፡

በውሳኔ የተጨመሩት መጻሕፍት የሚገኙበት ጥራዝ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲቈጠር እነርሱ የሌሉበት ጥራዝ ግን “ጐዶሎ መጽሐፍ ቅዱስ” ተብሎ ሲጠራ ተሰምቷል፡፡