Tuesday, April 2, 2019

ምስባክ

“ዓሣ ከውሃ ከወጣ ነፍሱ ወጣ”
አንዳንድ ሰዎች ለወንጌል መሰል ስብከታቸው መንግሥተ ሰማያት ለማስገባት አንድ እርምጃ የሚቀር እስኪመስል ድረስ ለስብከታቸው የሚገርም ርእስ ይሰጣሉ። ወደ ስብከቱ ፍሬ ነገር ሲገባ ግን ውጤቱ አብዛኛውን ጊዜ የመኪናን ፍሬቻ መብራት ወደ ግራ አሳይቶ ወደ ቀኝ እንደ መታጠፍ ያኽል ነው፤ ወይም ወደ ቀኝ አሳይቶ ወደ ግራ እንደ መሄድ ይኾናል።

እኔና ክርስቲያን ወንድሜ (አሁን በሕይወተ ሥጋ የለም) በመንገድ ስናልፍ የምንሄድበትን ጉዳይ ትተን ይህን ስብከትማ ሳንስማ መሄድ የለብንም እንድንል ያደረገንን የስብከት ርእስ አንድ ቤተ ክርስቲያን የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በትልቁ ተለጥፎ አየን። ርእሱ “ዓሣ ከውሃ ከወጣ ነፍሱ ወጣ” የሚል ነበር። ከዚያ ና እባክህ ይህን የወንጌል ቃል ተካፍለን እንሂድ፤ የሚገርም ርእስ ነው ተባብለን መልእክቱን ለመስማት ጎራ አልን። በጕጕት ስንጠብቅ የወንጌሉ ድምዳሜ “የዚህች ቤተ ክርስቲያን አባል ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም” የሚል ኾኖ አገኘነው። እኛም ሰባኪውን በመጨረሻ አግኝተን ማነጋገር አለብን ብለን ቈየንና አገኘነው፤ አነጋገርነውም። በተለይ ወንድሜ በሰል ያለ ሰው ነበርና እግዚአብሔርን፣ ሕዝቡንም ይቅርታ እንዲጠይቅና ከስሕተቱ እንዲመለስ አበክሮ መክሮት በሰላም ተለያየን። በእውነት ርእሱና የስብከቱ ሐተታና ድምዳሜ እንደ ወንጌሉ ቃል የተገናኙ አልነበሩም።

Monday, January 14, 2019

ዕቅበተ እምነት


"መድሎተ ጽደቅ" በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን

ክፍል አራት

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዕትሞችመድሎተ ጽድቅለተሰኘው መጽሐፍ ምላሽ ስንሰጥ መቈየታችን ይታወሳል። በዚህ ዕትምም ካለፈው ለቀጠለውና በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ጽሑፍ ላይ ለተሰነዘረው መሠረተ ቢስ ትችት ምላሽ መስጠታችንን እንቀጥላለን።

በዚህ ዕትም መድሎተ ጽድቅገጽ 42 ላይ የሚገኘውና በተራ ቍጥር 1.3.3. ላይ፣ከእምነት ይልቅ በስሜት ሕዋሳት (በማየት፣ በመስማት፣ …) ላይ መመሥረትበሚለው ንኡስ ርእስ ሥር ለተጠቀሱት እንዲሁም “1.1.4 ተገቢ ያልኾኑ አባባሎችንና ጸያፍ አገላለጾችን መጠቀምበሚለው ንኡስ ርእስ ሥር ለቀረበው ሐሳብ ከዚህ እንደሚከተለው ምላሽ እንሰጣለን፦

በመጀመሪያው ንኡስ ርእስ ሥር መድሎተ ጽድቅጸሓፊ ለመተቸት የተጣጣረው፣አብርሃም በዐጸደ ነፍስ ባለበት ኹኔታ በምድር የሚደረገውን ኹሉ ያውቃል ማለት የሚታመን ቀርቶ የማይመስል ነው።” (ጮራ . 38 ገጽ 17) የሚለውን ሐሳብ ነው። 

Tuesday, January 1, 2019

ርእሰ አንቀጽወሰላም በምድር - በምድር ሰላም

በኢየሩሳሌም የነገሠው የነቢዩ የዳዊት ልጅ ጠቢቡ ሰሎምን በመጽሐፈ መክብብ ውስጥ ለኹሉም ነገር ጊዜ እንዳለው በርካታ ክሥተቶችን በመጥቀስ ይናገራል። ለመወለድ፣ ለመትከል የተተከለውን ለመንቀል፣ ለመግደል ለመፈወስ፣ ለማፍረስ ለመሥራት፣ ለማልቀስ ለመሣቅ፣ ዋይ ለማለት ለመዝፈን፣ ድንጋይን ለመጣል ድንጋይን ለመሰብሰብ፣ ለመተቃቀፍ ከመተቃቀፍ ለመራቅ፣ ለመፈለግ ለማጥፋት፣ ለመጠበቅ ለመጣል፣ ለመቅደድ ለመስፋት፣ ዝም ለማለት ለመናገር፣ ለመውደድ ለመጥላት፣ ለጦርነት ለሰላም ጊዜ አለው በማለት ጠቢቡ ጊዜ በምሕዋሩ ውስጥ ልዩ ልዩ የሚቃረኑ ነገሮችን እንደሚያመላልስ ያስረዳል። በዚህ ሂደት ውስጥ የኹኔታዎች መለዋወጥ በጊዜ ቀመር የታቀበ ነው። ከዚህ ልውውጥ በስተ ጀርባም ነገሮችን የሚቈጣጠረው መጋቤ ኵሉ ወመሴስየ ኵሉ (ኹሉን የሚመግብና ደስ የሚያሰኝ)፣ ጊዜያትን የሚያመላልስና የሚያለዋውጥ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ ክብር ለእርሱ ይሁን!

ለኹሉ ጊዜ አለው እንደ ተባለው፣ በለውጥ ኺደት ላይ የምትገኘው አገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ያልተጠበቁና ያልታሰቡ ለውጦች ጊዜያቸውን ጠብቀው እየተከሠቱባት ትገኛለች። ስለዚህ ወቅቱ አገራችን ለውጡን ተከትሎ በተከሠቱ ኹኔታዎች ለለውጥ ተስፋ የተሰነቀችበት ብቻ ሳይኾን በለውጡ ሂደት ሰላሟ የደፈረሰበትም ጊዜ ነው። እየመጣ ያለውን ለውጥ ተከትሎ በብዙ ቦታዎች የሰላም መደፍረስና ሥጋት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ በተወለዱበት፣ ባደጉበትና ንብረት ባፈሩበት ስፍራ አገሬ ብሎ የመኖር ዋስትና ማጣት፣ በሕግ ሳይኾን በመንጋ ኢፍትሓዊ ፍትሕ የሚሰጥበትና በርካታ አሳዛኝና አስከፊ ኹኔታዎች እየታዩ ነው። ከዚህ ቀደም የኾነውን ኹሉ ወደ ቦታው መመለስ አይቻልም፤ ወደ ፊት የባሰ ችግር እንዳይከሠትና እየታየ ያለው የተስፋ ጭላንጭል እንዳይጨልም ለመሥራት ግን ዕድሉ አለ።