Thursday, August 29, 2019

የዘመን ምስክር


አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ
መግቢያ
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በተለይ የነገረ ሃይማኖት፣ የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ፣ የባሕረ ሐሳብም (የዘመን ቍጥር) ጉዳይ ሲነሣ በጕልሕ ከሚጠቀሱት ሊቃውንት መካከል፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ግንባር ቀደም ናቸው። አንዳንዶች ስማቸውን በአኅጽሮት (ባጭሩ) ኪ.ወ.ክ. እያሉ ይጠራሉ። እኒህ የነገረ መለኮት፣ የሰዋስውና የመዝገበ ቃላት ሊቅ በዋናነት ነገረ ክርስቶስን አስመልክቶ በሚከተሉትና በኢትዮጵያ ቀዳሚው ኦርቶዶክሳዊ ባህለ ትምህርት በኾነውና ተቃዋሚዎቹ “ሦስት ልደት” (ጸጋ) እያሉ በሚጠሩት ባህለ ትምህርት ምክንያት በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን በአንዳንድ ሥራዎቻቸው እየተጠቀመ ስማቸውን ግን በተገቢው መንገድ ለማንሣትና ተገቢውን ስፍራ ለመስጠት ቢቸገርም፣ ሊቅነታቸውን ግን በምንም መንገድ ሊያስተባብል አይችልም።

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከነገረ ክርስቶስ በተጨማሪ በአንዳንድ አስተምህሮቶችና ታሪኮች ላይም ለየት ያሉና አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን በድፍረት ያቀርባሉ። ከዚህ የተነሣ እርሳቸውን ለማጣጣል የሚሞክሩ አንዳንድ ደፋሮች ባይጠፉም፣ እውነትን ደፍረው በመናገራቸውና እውነትን ይዘው ለብቻቸውም ቢኾን በመቆማቸው ተከታዮችና ደጋፊዎችን አላጡም። ስለ እርሳቸው ሊነገርና ሊጻፍ የሚገባው ብዙ ነገር ቢኖርም ጥቂቱንም እንኳ እንጻፍ ብንል ብዙ ይኾናል። በዚህ ጽሑፍ የገጠመንም ይኸው ነው። ለመኾኑ እኒህ ሊቅ ማናቸው? ሥራዎቻቸውስ የትኞቹ ናቸው? ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን መታደስ ምን አበረከቱ? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ቀጥሎ እንቃኛለን።

የሕይወት ታሪክ
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (ከዚህ በኋላ ኪ.ወ.ክ.) በሰሜን ሸዋ መንዝ ተጕለትና ይፋት ውስጥ ልዩ ስሙ እንቢጣጣ በሚባል ስፍራ በ1862 ዓ.ም. ተወለዱ።[1] አባታቸው ደብሩ የውነቴ ይባላሉ። ይኹን እንጂ በኋላ ላይ የተጠሩት ዝቅ ብለን እንደምንገልጠው በወላጅ አባታቸው ስም ሳይኾን፣ በመምህራቸው በክፍለ ጊዮርጊስ ከፊለ ስም - ክፍሌ ነው።

አያታቸው የውነቱ የተማሩ ሊቅ ነበሩ። ኪ.ወ.ክ.ንም በትውልድ ስፍራቸው ንባብ፣ የቃል ትምህርትና የቁም ጽሕፈት ያስተማሯቸው እርሳቸው እንደ ኾኑ ይነገራል። በኋላም ወደ ጎንደር ተጕዘው መጻሕፍተ ብሉያትንና መጻሕፍተ ሐዲሳትን ተምረዋል። በጊዜው የነበራቸው የትምህርት አቀባበል፣ የመመራመርና የመራቀቅ ችሎታ “የቀለም ቀንድ” የሚል ቅጽል አሰጥቷቸው ነበር።

20 ዓመት ሲኾናቸውም በ1882 ዓ.ም. በገዳማዊ ሕይወት ወይም በምንኩስና ለመኖር ወስነውና ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳቀኑ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ወደዚያ ከመድረሳቸው በፊትም በግብጽ አስቄጥስ ገዳም ለአንድ ዓመት ያኽል ቈይተዋል። ለኑሯቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት አያታቸው ባስተማሯቸው የቁም ጽሕፈት ሙያ፣ ብዙ የውጭ አገር ሊቃውንት እየጠየቋቸው የብራና ጽሑፎችን ይገለብጡላቸው ነበር። ይከፈላቸው የነበረው ገንዘብ ግን ከድካማቸው ጋር ተመጣጣኝ አልነበረም።

ኪ.ወ.ክ. በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የኢትዮጵያውያን ገዳም ይግቡ እንጂ ምንኩስናን አልተቀበሉም (አልመነኮሱም) ነበር። በኢየሩሳሌም ካሳለፏቸው 30 ዓመታት ውስጥ ዐሥሩን ዓመታት ከመምህራቸው ከክፍለ ጊዮርጊስ ጋር ነበር ያሳለፉት። የዚህን ጊዜ ይኾናል በወላጅ አባታቸው ስም መጠራቱን ትተው እጅግ በሚወዷቸውና በሚያከብሯቸው መምህራቸው ስም መጠራት የጀመሩት። በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ከእርሳቸው ብዙ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ቀሥመዋል። መጻሕፍተ ሊቃውንትን፣ መጽሐፈ አቡሻህርንና (“አቡሻህር የተባለ ዮሐንስ የጻፈው ታላቅ የቍጥር መጽሐፍ ነው።”[2]) የመሳሰሉትን በሚገባ ተምረዋል።

ኪ.ወ.ክ. ኢየሩሳሌም የነበሩት በ19ኛው ምእት ዓመት ኹለተኛ አጋማሽ ላይ ነበር። ይህም ዘመን የታወቀው ጀርመናዊው ሊቅ ኤኖ ሊትማን በኢየሩሳሌም የሚገኙትን የኢትዮጵያን ገዳማት ዴር ሡልጣንን የጐበኘበት ጊዜ ነበርና፣ በዚያ እርሳቸውን አግኝቶ በሰፊው አነጋግሯቸዋል። ከዚያ ሲመለስ “በኢየሩሳሌም የሐበሾቹ ገዳም” በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ አሳትሟል። በጽሑፉ ውስጥ እርሳቸው ከዐማርኛና ከግእዝ በተጨማሪ ዐረቢኛን እንደሚያውቁ ጠቅሷል። ይህን ኹኔታ የገለጡት ዶ/ር ሥርግው ሀብለ ሥላሴ “[ሊትማን] ባይረዳላቸው ነው እንጂ የቋንቋ ዕውቀታቸው ዕብራይስጥንና ላቲንንም ይጨምራል።” ብለዋል። “ላቲን ማወቃቸውን የምረዳው የግእዝ መዝገበ ቃላትን ሲያዘጋጁ ኦገስት ዲልማን ያዘጋጀውን የግእዝ ላቲን መዝገበ ቃላትን ተጠቅመዋል።” ሲሉም አክለዋል።

በኢየሩሳሌም ሲኖሩ፣ ዐረብኛን፣ ዕብራይስጥን፣ ጽርእን፣ ሱርስትን፣ ሮማይስጥን በማጥናትና በመጠንቀቅ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንም በየቋንቋው በማመሳከር እንዳሳለፉ ይታወቃል። አያሌ መጻሕፍትን አንብበዋል፤ በጥልቀት መርምረዋል፤ ምስጢርም አደላድለዋል። ለምሳሌ በመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ ለአስረጂነት ከ62 በላይ የታወቁ የብሉይ፣ የሐዲስ የሊቃውንትና አዋልድ መጻሕፍትን እንደ ተጠቀሙ ገልጠዋል።

ይህ የቋንቋና የመጻሕፍት ዕውቀት ችሎታቸው በግእዝ መዝገበ ቃላታቸው ላይ በሰፊው ተንጸባርቋል። አንድ የግእዝ ቃል በእነዚህ ቋንቋዎች ውስጥ ካሉ ቃላት ጋር ተመሳስሎ ሲኖረው በቅንፍ ውስጥ፦ የዕብራይስጥ፣ የጽርእ፣ የዐረብኛ፣ የሱርስትና የሮማይስጥ ተመሳሳዮችን ይጽፋሉ። እያንዳንዱ የግእዝ ቃል የሚገኝበት የግእዝ ንባብም በጥቅስነት ከየመጻሕፍቱ እየተጠቀሰ፣ በአንድ ንባብ ውስጥ የቃሉ አገባብ ምን እንደሚመስልና ምን ትርጉም እንዳለው ማሳየታቸውን በመዝገበ ቃላቱ የሚጠቀሙ ኹሉ ሊመሰክሩት የሚችሉት ሐቅ ነው። ይህም ቋንቋውን ማወቅ ብቻ ሳይኾን ከላይ የተጠቀሱትን መጻሕፍት በምን ያኽል ጥልቀትና ማስተዋል እንዳነበቧቸውና እንደ መረመሯቸው ያሳያል።
 
በኢየሩሳሌም በተለይ ዕብራይስጥን የተማሩበት ዘመን እጅግ አስቸጋሪ እንደ ነበርና ከኹለት አቅጣጫ የሚደርስባቸውን ጫና ተቋቍመው እንደ ተማሩ ሲመሰክሩ አለቃ ታየ እንዲህ ብለዋል፤ “እርሳቸው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ዕብራይስጥ በተማሩበት ዘመን የነበረውን ችግር ያስተዋለ ሰው ብቻ ድካማቸውን ሊመዝነውና ሞያቸው ትልቅ መኾኑን ሊረዳው ይችላል። … ከዚያ የነበረው የኢትዮጵያ መነኮሳት ማኅበር ከጸሎት በቀር ትምህርት መቀጠል የማያስፈልግ ሥራ ኾኖ ሲታየው፣ እስራኤላዊ ደግሞ በዓለም ያለ ሕዝብ ዐሥር ቢማር እንደማያፈቅረው ተረድቶት ቋንቋውን ሊማርለት የመጣውን ክርስቲያን መርዳት እባብን ከመቀለብ ይቈጥረው ነበር። ስለዚህም አለቃ ኪዳነ ወልድ ዕብራይስጥ የተማሩት በኹለት ፊት ሥቃያት እያዩ ነው።”
    
ኪ.ወ.ክ. ከ30 ዓመታት የኢየሩሳሌም ኑሮ በኋላ ወደ አገራቸው የተመለሱት ዐፄ ኀይለ ሥላሴ መጽሐፈ ሕዝቅኤልን እንዲተረጕሙ ደብዳቤ ጽፈው በጠየቋቸው መሠረት ሲኾን፣ ዘመኑም 1912 ዓ.ም. ነው። ወደ አገራቸው ገብተውም የታዘዙትን የመጽሐፈ ሕዝቅኤልን አንድምታ አዘጋጅተው ካስረከቡ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ወጥነውት የነበረውን የመዝገበ ቃላቱን ሥራ በድሬዳዋ ማዘጋጀት ጀመሩ።

ዶ/ር ሥርግው ሀብለ ሥላሴ እንደ ጻፉት “አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከኢየሩሳሌም በ1912 ዓ.ም. ከተመለሱ በኋላ ቀዋሚ ሥራ አልተሰጣቸውም። በድጎማ መልክ አንዳንድ የገንዘብ ጕርሻ ያገኙ ነበር። የቤተ ክርስቲያን ሰዎችም አላስጠጓቸውም ነበረ። ኑሮን የሚገፉት በግል በጎ አድራጊዎች እርዳታ ነበር። እርሳቸውን የመሰለ ባለሙያ ሊቅ የዕለት እንጀራውን ቧግቶ (ለምኖ) መብላት ተገቢ አልነበረም። ግን በዚህ አገር ይህ የቈየ ልማድ ነውና አያስገርምም። ኾኖም የነበረባቸው የኑሮ ችግር የአገራቸውን ፍቅር አልቀነሰባቸውም።”[3] የተማሩ ሊቃውንትን እንደሚገባ በመጠቀም ወደፊት መራመድ የሚገባቸው አገርና ቤተ ክርስቲያን፣ የተማሩትንና ከፍ ያለ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉትን ሊቃውንት፣ መማራቸውን እንደ ዕዳ በመቍጠር ብዙ እንግልት ማድረሳቸውና ተገቢውን ስፍራና ክብር አለመስጠታቸው አገርንም ቤተ ክርስቲያንንም በእጅጉ ጐድቷቸዋል እንጂ አልጠቀማቸውም።

በድሬዳዋ በአልዓዛር (ላዛሪስት) ማተሚያ ቤት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር የሚሉ ምንጮችም አሉ። ደስታ ተክለ ወልድ እንደ ጻፉት ደግሞ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ያዘዙላቸውን ቀለብና ድርጎ እያደራጁ በዕለት መፍቅድ ይረዷቸው የነበሩት የክቡር ብላታ አሽኔ ኪዳነ ማርያም ባለቤት ክብርት ወ/ሮ በላይነሽ ጐበና ነበሩ። በዚህም ተባለ በዚያ ሊቁ የሚገባቸውን ያኽል ክብር እንዳላገኙ መገመት አይከብድም። ይኹን እንጂ ተገቢው ስፍራና ክብር ባይሰጣቸውም የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ብርቱ እንደ ነበረ ሥራዎቻቸው ይመሰክራሉ።

ኪ.ወ.ክ.ን የመሰለ ሊቅ ስፍራ ሊያገኝና ለአገርና ለወገን ጥቅም ሊሰጥ ሲገባ ቸል መባሉ ያሳዝናል። ይኹን እንጂ እርሳቸው በዚያው ልክ ለአገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው ያላቸው ፍቅር አለመቀነሱ ደግሞ አስገራሚ ነው። ጣሊያን አገራችንን በወረረ ጊዜ ግልጥና ቀጥተኛ ጠባይ የነበራቸው ኪ.ወ.ክ. ወራሪውን ጠላት አጥብቀው ይቃወሙና ኢትዮጵያ በቶሎ ነጻ እንደምትወጣም በግልጥ ይናገሩ ነበር። በዚህም ምክንያት ፋሺስቶች በጨለማ ቤት አስረዋቸው የዐይናቸው ብርሃን ጠፋ።

ቤተ ክርስቲያንም እርሳቸውን የመሰለ ሊቅ አክብራ መያዝ፣ በዕውቀታቸው መጠቀምና አስፈላጊውን ተሐድሶ ማድረግ ሲገባት፣ ስፍራ አለመስጠቷ ቢያሳዝንም፣ እርሳቸው ግን የሚበጃትን እንድታደርግ በየጽሑፎቻቸው ይመክሩና ይዘክሩ ነበር።

ኪ.ወ.ክ. ግልጥና ቀጥተኛ ባሕርይ ያላቸው መኾኑ በጽሑፎቻቸው ውስጥ በስፋት ተንጸባርቋል። በተለይም በሃይማኖተ አበው ቀደምት ላይ በትምህርት ያልመሰሏቸውንና እርሳቸው ከሚያምኑት በተቃራኒው የቆሙትን፣ በእነርሱ ላይ ብዙ ግፍ የፈጸሙባቸውን ነገሥት፣ ጳጳሳትና በአጠቃላይም የካራና ቅባት ሰዎችን ጠንከር ባሉ ቃላት ጭምር ሲሸነቍጧቸው እናነባለን።

 ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን ካበረከቷቸው አስተዋፅኦዎች፦
ለግእዝና ለዐማርኛ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ እድገት ተግተዋል
አለቃ ታየ ገብረ ማርያም ስለ ደራስያን ባዘጋጁትና ባልታተመው ጽሑፋቸው ውስጥ፣ “የኢትዮጵያን የጥንቱን ትምርት ከሚያውቁት ሊቃውንት ዐማርኛንና ግእዝን ለማጣራት፣ ያለቃ ኪዳነ ወልድን ያኽል የሚደክም ብዙ አልተገኘም። ዐማርኛ ለግእዝ ልጁ በመኾኑ፣ ከግእዝ የተቀበላቸውን ቃላት ልክ እንደ ግእዝ አድርጎ መያዝ አለበት የሚል ዐሳብ ስላለባቸው፣ ይህንኑ ውሳኔ ለመግለጥ የታተመና ያልታተመ ብዙ መጽሐፍ ጽፈዋል። ዐሳባቸውን ተቀብሎም ለማስቀበል የሚጣጣር በያገሩ ብዙ ደቀ መዝሙር አውጥተዋል።” ሲሉ መስክረዋል።

የጥንቱ የፊደል ቅደም ተከተል “አበገደ” መኾኑንና የየትኛውም ቋንቋ ፊደል የአበገደን መንገድ እንደሚከተል በመግለጥና የ“ሀለሐመ” ሥርዐት ከእኛ በቀር በየትም የሌለ መኾኑን በማውሳት ይነቅፉታል። ከአበገደ ወደ ሀለሐመ የገባነው ከከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ ወዲህ መኾኑን የሚገልጡት ኪ.ወ.ክ “አበገደ የነበረውን ሀለሐመ ብለው ከላይ እስከ ታች ያፋለሱትም ከእርሱ [ከከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ] ጋር ዐብረው የነበሩ ጽርኣውያንና ቅብጣውያን ናቸው ይባላል።” ይላሉ። በመኾኑም መዝገበ ቃላታቸውን ያዘጋጁት በሀለሐመ ሳይኾን በጥንቱ በአበገደ መንገድ ነው። ይኹን እንጂ ይህ እንኳን የአገበደን የሀለሐመን ቅደም ተከተል በሙሉ በቃሉ መዝለቅ ለተሣነው ትውልድ ከባድ መኾኑ አልቀረም።
 
ኪ.ወ.ክ. የቋንቋና የሥነ ልሳን ሊቅ እንደ መኾናቸው፣ ለግእዝና ዐማርኛ የተለየ ትኵረት በመስጠት የሰዋስው ሥርዐታቸውና የፊደላት አጠቃቀማቸው ተጠብቆ እንዲቈይና እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ጽሕፈትን በተመለከተ ሆሄያት (ፊደላት) በቃላት ውስጥ ስፍራቸውን ጠብቀው መጻፍ አለባቸው ይላሉ። ይህም ለግእዙ ብቻ ሳይኾን ለዐማርኛም ጭምር ይሠራል፤ ምክንያቱም ዐማርኛ ከግእዝ የወሰዳቸው እጅግ በርካታ ቃላት ስላሉና እንደርሳቸው ባሉ ሊቃውንት ዘንድም ዐማርኛ ለግእዝ ልጁ ስለ ኾነ ፊደላትን እንደ መሰለንና እንደ ገጠመን ሳይኾን ሥርዐታቸው ተጠብቆ መጻፍ አለበት። አሊያ፦
       “ባንዱ የሚጣፈው በሌላው ሲጣፍ
       ቋንቋው ተበላሽቶ ይኾናል ጸያፍ” ይላሉ።
ይኹን እንጂ ጽሕፈትና ትምህርትን አስተባብረው የያዙ ሰዎች በመመናመናቸው ምክንያት፣ ፊደላት ተገቢ ቦታቸውን ይዘው፣ ጽሕፈትም ሥርዐቱን ጠብቆ መከናወን እንዳልቻለ ያስረዳሉ። “ጥፈትና ትምርት እየቅል ኹኖ ጥፈት ዐዋቆች ከሰዋስው ትምርት የራቁ፥ መጽሐፍ ዐዋቆችም ጥፈት የማያውቁ” መኾናቸው ወይም “ጥፈትና ትምርት ተባብረው በአንድ ሰው እጅ ስላልተገኙ ነው። ጥፈት የማያውቁ መምህራን የተጣፈውን ከመተርጐም በቀር የጸሐፍትን ስሕተትና ግድፈት ማረምና ማቅናት እንዳይችሉ፥ ሰዋስው የማያውቅ ጸሓፊም መልክአ ፊደሉን (የፊደሉን መልክ) ሐረጉን ቅጠሉን (የታጠፈውን ብራና/ወረቀት) አጣጣሉን ብቻ ከማሳመር በቀር ንባቡንና አገባቡን አጥርቶ ማወቅ ፊደሉን መጠንቀቅ አይችልም።” ይላሉ።

የኹለቱ “አዐ” እና የሦስቱ “ሀሐኀ” ግእዛቸው (የመጀመሪያው ፊደላቸው - አዐ፣ ሀሐኀ) ከራብዓቸው (ከአራተኛው ፊደላቸው - ኣዓ፣ ሃሓኃ) በመልክ ብቻ ተለይቶ እንደ ሌሎቹ ፊደላት በድምፅ ስላልተለየና ልዩነቱ ስላልታወቀ፣ በግእዙ (በመጀመሪያው ፊደል) መጻፍ ያለበት በራብዑ (በአራተኛው ፊደል)፣ በራብዑም መጻፍ ያለበት በግእዙ የሚጻፍበት ኹኔታ በስፋት ይስተዋላል። ለምሳሌ፦ ጐሥዐ፣ ሞአ፣ በልዐ፣ በርሀ ተብለው መጻፍ የነበረባቸው ቃላት፣ በራብዕ፣ እንዲሁም በሌላው ተመሳሳይ ድምፅ ባለው ፊደል (የተሰመረባቸውን ፊደላት ይመለከቷል)፣ ጐሥ፣ ሞ፣ በል፣ በር ተብለው የሚጻፉበት ጊዜ አለ። በሌላም በኩል፦ ጸሓፊ፣ ከሃሊ፣ ወሃቢ ተብለው በራብዑ መጻፍ የነበረባቸው ፊደላት በግእዙ - ጸፊ፣ ከሊ፣ ወቢ ተብለው ይጻፋሉ። የእነዚህ አጻጻፍ የመጀመሪያውን መከተል ያለበት መኾኑን ከእነዚህ ውጪ በኾኑ በሌሎች ፊደላት አጠቃቀም መገንዘብ ይቻላል። ለምሳሌ፦ ፈጣሪ፣ ገባሪ … ስንል “ጣ” እና “ባ” ራብዕ ናቸው እንጂ ግእዝ “ጠ” እና “ለ” መኾን አይችሉም። በ “አዐ” እና በ “ሀሐኀ” ላይም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም አለብን ማለት ነው።

ሞክሼ (ተመሳሳይ) ድምፅ ያላቸው ፊደላት ቢቀነሱ ይሻላል የሚሉ ሰዎች ተነሥተው፣ ይልቁንም “ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ” ጽፎ ስለ ነበር ኪ.ወ.ክ. መፍትሔው ፊደላትን መቀነስ ሳይኾን ትምህርቱን ማስፋትና የትምህርት አሰጣጡን ማዘመን መኾኑን በመግለጥ ፊደል ይቀነስ የሚለው ተቀባይነት የሌለውና በሴማውያን ዘንድ ቢሰማ እንኳ ሞኝ የሚያሰኝ መኾኑን በሚከተሉት ስንኞች ገልጠዋል፦

“ለቋንቋ በሽታ ለፊደል ሕማም
ከትምርት በቀር መድኀኒት የለም።
እንደ ምን ይቻላል በቀንጃ (አጣማጅ በሌለው) ፊደል
የቋንቋውን ሞክሼ ማወቅ መነጠል።
ጥንቱን ፊደላችን ሴማዊው በገና
ኹለት ኹለት ኾኖ ለምን ተሠራና።
ዐማርኛችንስ በፊደል ጐዳና
ካባቱ ከግእዝ መቼ ይለይና።
የትምርቱስ ችጋር የዕውቀቱ ቀጣና (ትንሽ ረኃብ)
ፊደል በማሳነስ መቼ ይለቅና።
በሴማውያን ዘንድ በያፌት ልጆች
ይህ ነገር ቢሰማ ያሰኛል ሞኞች”

የኪ.ወ.ክ. የጽሑፍ ችሎታ (በስድ ንባብም ኾነ በግጥም) እጅግ የተመሰከረለት ነው። ጽሑፎቻቸው በቃላት አመራረጥ የተዋጣላቸው፣ በዘይቤ አጠቃቀምም የተሳካላቸው ናቸው። እንዲያውም በዘይቤ የተሞሉና ለሚያነባቸው ሰው ምስል የመከሠት ዐቅማቸው ከፍ ያለ ነው። እጅግ የተመጠኑና ሐሳባቸውን ሊሸከሙ የሚችሉ የተመረጡ ቃላትን የሚጠቀመውና አላስፈላጊ ቃላትን የማያግበሰብሰው ጽሑፋቸው በዐረፍተ ነገር አሰካኩም ቢኾን እጅግ የሰመረ ነው። ኾኖም ብዙ ጊዜ ላቅ ያሉ ቃላትን ስለሚጠቀሙ ጽሑፎቻቸው ለማንኛውም አንባቢ ኹሉ ቀላል ላይኾኑ ይችላል።

ግእዝ እንዳይጠፋና እንዲስፋፋ መዝገበ ቃላቱን ከማዘጋጀት ባሻገር ትውልዱን በመምከርም ጭምር የበኩላቸውን የማስተማር ሚና በሚገባ ተወጥተዋል።

ዛሬ ላይ ኾነን ስናየው ብዙ ነገሮች መመለስና መስተካከል ከማይችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ በመኾናቸው፣ የሚሰጡ አስተያየቶች ቍጭትን ከመፍጠር በቀር የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሚረዱ ባይመስልም፣ እርሳቸው ግን ትምህርትና ጥፈት አስተባብሮ ያልያዘ መምህር ፊደል ማስተማር የለበትም፤ አሊያ ትውልድን ያበላሻል የሚል ስሜት ያለው መልእክታቸውን በስንኞች ገልጠው ነበር።
“ስማ ስማ መምር ከነተማሪኽ
የተማሪ ቤትም ከነትምርትኽ
ግእዝ የማይሰማ ጥፈት የማያውቅ
ፊደል ከማስተማር ፈጽሞ ይራቅ
ላስተዋዩ ሕፃን ላይናማው ተማሪ
አያሻውምና ያይነ ስዉር መሪ
ልጆችም ይማሩ ካይናማ መምር
ጥፈትና ቋንቋ ከሚያስተባብር
ዘር እንደ መኾኑ የሥንዴ ቅንጣት
ጥሩነት ያሻዋል በቃል በጥፈት”

“አበገደ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ፣ በኪናዊ መንገድ ተማሪዎችን[4] ከፊደል ጋር በጥያቄና መልስ እንዲወያዩ ባደረጉበትና 13 ክፍል ባለው ግጥም ውስጥ በርካታ ቀስቃሽ፣ ወቃሽ፣ መካሪ፣ ዘካሪ፣ አስተማሪና ተሐድሶኣዊ የኾኑ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። ጥቂቱን እንጥቀስ፦
“መጣፍ የሚበላ የመጣፍ ቀበኛ (መጽሐፍ አንባቢ/ዐዋቂ)
ዛሬ በኛ ዘመን አይገኝም ከኛ
የመጣፉን ማበር ሸንጎና ጕባይ
የውጭ አገር ቋንቋ ወርሶት የለሞይ”
ለሚለው የተማሮች ጥያቄ በፊደል በኩል ከተሰጠው ምላሽ ውስጥ እንዲህ የሚሉ ስንኖች ይገኛሉ።
የውጭውስ ቋንቋ መች ይነቀፍና
የሚነቀፈውስ የእናንተ ስንፍና
ሰው በፊደሉ ላይ ቢጨምር ፊደል
ዐይናማ ይኾናል እንደ ኪሩቤል
በቋንቋ ላይ ቋንቋ ብትጨምሩማ
ያድርባችሁ ነበር የሱራፌል ግርማ

ቀጥሎ በተማሮች በኩል የተነሣው ነጥብ እንዲህ የሚል ነው
ሃይማኖት ያስለውጥ እየመሰለን
እጅግ አንወደውም ቋንቋ መማሩን
ከሃይማኖት ኹሉ የኛ ሃይማኖት
ትበልጣለችና በውነተኛነት

(እንዲህ ያለው ዕሳቤ በዚያ ዘመን በስፋት ይንጸባረቅ ነበር። ለምሳሌ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የውጭ ቋንቋዎችን ለመማር ወደ ሚስዮናዊ ትምህርት ቤት ቢገቡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች “እንግሊዝኛ የሚማረው ‘ካቶሊክ’ ለመኾን ነው”፣ ዐረቢኛውንም ጀምረውት ሳለ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ቍርዓንን ያስቀድማል ብለው ስላስወሩባቸው ኹለቱንም ለማቋረጥ እንደ ተገደዱ የሕይወት ታሪካቸው ያወሳል (ጮራ ቍጥር 42፣ ገጽ 10)። ይኹንና ከላይ ለቀረበው የተማሪዎች ጥያቄ በፊደል በኩል የተሰጠው ምላሽ እንዲህ የሚል ነው።
የልጅ ነገር ወትሮ ኹለት ቅንጣት ፍሬ
አንዱ ፍጹም ብስል አንዱ ፍጹም ጥሬ
አባቴ ታናሽ ነው ሃይማኖቴ ክፉ
የሚል የለምና በዚህ አትስነፉ
ምንም ብዙ ቢኾን ስሙና ማኅበሩ
አንድ ክርስቶስ ነው የክርስቲያን በኵሩ
በክርስቶስ ክርስቲያን የተባለ ኹሉ
የክርስቶስ መንጋ እንደ ኾነ አስተውሉ
ኋላ በፍርድ ቀን እስኪለየው ፈርዶ
ኹሉ ዐብሮ ይግጣል የተስፋውን ሰርዶ
የሃይማኖት ወንፊት የምግባር ሰፌድ
በትእዛዙና በሕጉ መኼድ
ወንድምን እንደ ራስ አጥብቆ መውደድ
መች አንዱ በአንዱ ላይ መጓደድ መፍረድ
የወንጌል ሃይማኖት ፍቅርና ትሕትና
ኹሉን ታስኬዳለች በአንድ አምላክ ጐዳና
አንድ ወጣት (ትንሽ) ስልቻ በያገሩ ባህል
አቅማዳ ቀልቀሎ ለቆታ እንዲባል
የሃይማኖትም ስም ልዩ ልዩነቱ
ይህንን ይመስላል ቋንቋ ለሚያውቁቱ”

“ሆሄ ኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት” ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሸለማቸው የሥነ ጽሑፍና የኪነ ጥበብ ሰዎች መካከል ኪ.ወ.ክ. አንዱ ናቸው። “የሕይወት ዘመን የሥነ ጽሑፍ የላቀ ባለ ውለታ” ተብለው ነው የተሸለሙት። እርሳቸው ካንቀላፉ ከ73 ዓመታት በኋላ በተዘጋጀው በዚህ የሽልማት መርሐ ግብር ላይ ተገኝቶ እርሳቸውን በመወከል ሽልማቱን የተቀበለውና ስለ እርሳቸው ምስክርነት የሰጠው፣ ጋዜጠኛ ሔኖክ ያሬድ፣ የኋላ ታሪክን በማስታወስ ከ57 ዓመት (በ1952 ዓ.ም.) ሐምሌ ወር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለሰባተኛ ጊዜ ተማሪዎችን ባስመረቀበት ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቻንስለር የሥነ ጽሑፍ ሽልማት በሦስት ዘርፍ፦ በቅኔ፣ በግጥምና በድርሰት አዘጋጅቶ እንደ ነበርና እዚያ መድረክ ላይ ከአለቃ ዘነብና ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ጋር በክብር የተወሱትና ፋና ወጊ ተብለው የተጠቀሱት ኪ.ወ.ክ. መኾናቸውን ገልጧል። አክሎም “ከ1500 ዓመት የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ጕዞ በኋላ 19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ዐማርኛ ሲረከብ ፋና ወጊ የኾኑት አንዱ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ነበሩ። … የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ኹለተኛ ዲግሪ፣ ሦስተኛ ዲግሪ፣ ባሕር ማዶ ጭምሮ ያሉ ታላላቅ ፕሮፌሰሮች ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ማዕድ ያልተቋደሰ የለም።” በማለት ሊቁ ብዙዎችን በትምህርት የወለዱ ታላቅ አባት መኾናቸውን መስክሯል።
 
መጽሐፈ ሕዝቅኤል     
ኪ.ወ.ክ. ከኢየሩሳሌም ተጠርተው የመጡበት ዋናው ጉዳይ የትንቢተ ሕዝቅኤልን ትርጓሜ እንዲያዘጋጁ መኾኑን ከላይ ገልጠናል። ማንም አዘጋጅቶት በማያውቅ መንገድ የትንቢተ ሕዝቅኤልን አንድምታ ትርጓሜ አዘጋጅተው ረቂቁን ባ፲፱፻፲፮ ዓ.ም. ድሬዳዋ ላይ አሳትመው አስረከቡ፡፡ አለቃ ይህን ትንቢተ ሕዝቅኤል “ሐዲሱ መጽሐፈ ሕዝቅኤል”[5] እያሉ ጠርተውታል። በዚህ ሥራ በሰብዓ ሊቃናት የግሪኩ ብሉይ ኪዳንና በዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን መካከል ያለውን ልዩነት አሳይተው ነበር፤ በዚህም ምክንያት ከራስ ተፈሪ መኰንን፣ በኋላ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጭምር ተቃውሞ ያዘለ ደብዳቤ ደረሳቸው። ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነው፦
“የኢትዮጵያ መንግሥት ዐልጋ ወራሽና እንደ ራሴ ተፈሪ መኰንን
“ይድረስ ካቶ  ኪዳነ ወልድ
“እንደ ምን ሰንብተሃል እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነኝ፡፡ ስለ ሕዝቅኤል ትርጓሜ የላክኸውን መጽሐፉንም ደብዳቤውንም አይቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን ቃለ በረከትና ሙባአ ብለህ በራስህ ዐሳብ የጻፍከው ቃል ከኢትዮጵያ ታሪክና ከሊቃውንቱ ልማድ የተለየ ስለ ኾነ ወሬውን ለሚሰሙ ሊቃውንቶች የሚያሳዝን መጽሐፉንም ለሚያነቡ ሰዎች ኹሉ የነቀፋ ምክንያት የሚኾናቸው ይመስላልና ዐብሮ ለመጠረዝ አያስፈልግም፡፡ መቸም እኛ የፈለግነው ያንኑ ጠፍቷል የተባለውን የነቢዩን የሕዝቅኤልን ትርጓሜ ለየሰው ኹሉ ለመግለጽና ደስ ለማሰኘት እንጂ በዚህ በትርፍና በትንሹ ነገር መጽሐፉን ለማስነቀፍ ምክንያት የሚኾን ነገር ለመጻፍ አያስፈልግም፡፡

“የውጭ አገር ታሪክ ጸሓፊዎች እንኳ የብሉይ መጻሕፍት በኢትዮጵያ ቋንቋ እንደ ተገለበጡ ጽፈዋልና አኹን አንተ የብሉይ መጽሐፍት ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋ አልተገለበጡም ብለህ ብትጽፍ ለሀገራችን ክብር አይኾንም፡፡ ለማናቸውም ቢኾን የራስህ ሐሳብ ነው እንጂ የነቢዩ የሕዝቅኤል ቃል አይደለምና ቢቀር ይሻላል፡፡

“የሚቀረውም በቀይ ቀለም ተሠርዞ ተመልክቷልና እንደ ተሠረዘ ማድረግ ነው፡፡ ከመጽሐፉም ጋር ዐብሮ የሚታተመውን የኔን ፎቶግራፍ ልኬልሃለሁ፡፡

“ጥር 30 ቀን 1916 ዓመተ ምሕረት ዐዲስ አበባ፡፡”

ራስ ተፈሪ መኰንን በዋናነት ሊቃውንቱ ሌላ ተቃውሞ ያስነሣሉ ብለው በማሰብ በዚያ የተዋጣለት ሥራ ቅር ቢሰኙም፣ ኪ.ወ.ክ. የደከሙበት አንዳንዱ እንዲቀር፣ እንዲሰረዝና እርሳቸው ባረሙት መንገድ እንዲታተም ቢያደርጉም፣ ሥራው ግን ዮሴፍ ወልደ ኮርዮንን፣ ፊልዮን፣ ሰብዓ ሊቃናትን፣ የኢየሩሳሌምንና የዮናታንን ትርጕም፣ ሚድራሽን፣ ሊቃውንተ አይሁድን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትንና ዐውደ ጥበባትን፣ በዐረብኛና በሌሎችም ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሌሎች መጻሕፍትንም ያመሳከሩበትና ላቅ ያለ ምሁራዊ ትንተናም ያሳዩበት ነው።

መጽሐፉን ከመረመሩት ሊቃውንት መካከል አለቃ ታየ የሰጡት ምስክርነት እነሆ፦ “የሕዝቅኤልን ትንቢት ዕብራይስጡን ወደ ዐማርኛ ገልብጠው ባማርኛ የጨመሩበት መግለጫ ኹሉ ፊት ላገራቸው ሊቃውንት ከግሪክ ተተርጕሞ በግእዝ ተቀብለውት የሚኖሩትን የብሉያትን መጻሕፍት ዋናውን አብነት ዕብራይስጡን እያዩ ማቃናት እንዳለባቸው አነቃቅተዋቸዋል።

“ዳግመኛም ትምህርቱም መጠነኛ ቢኾን ዐማርኛ ያወቀ ኹሉ ሊያስተውለውና ሊያጣጥመው በሚችል ንግግር በመግለጣቸው ተራውን ሕዝብ ሳይቀር ከሊቃውንቱ ዕውቀት እንዲካፈል አድርገውታል። እግረ መንገዳቸውንም ልዩ ስለ ኾነው ከባድ ዕውቀት ልዩ የኾነና ያጌጠ ዐማርኛ ፈጥረውለታል።

“… ይህ ኹሉ ድካማቸው በክርስቲያን ሊቃውንት ጭምር ስለ ብሉያት መጻሕፍትና ታሪክ ያመጡትን ዐዲስ መግለጫ ለመከታተል ቢቸግራቸው፣ ዐማርኛው ከተሰናዳው መግለጫቸውም በክርስቲያንነታቸው የጸኑት ሊቃውንት ከደረሱበት የታሪክና የትርጕም ዐዲስ አካሄድ ለመድረስ ቢያቅታቸው አይፈረድባቸውም።”

ይህን የመጽሐፈ ሕዝቅኤል አንድምታ ትርጓሜ ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ ዛሬ ድረስ እየተጠቀመችበት ቢኾንም፣ በመጽሐፉ አንጻር እንኳ ለአዘጋጁ ለኪ.ወ.ክ. ተገቢውን ዋጋና ክብር ሰጥታለች ማለት አይቻልም። ለምሳሌ መጽሐፉን ያዘጋጁ እርሳቸው ኾነው ሳለ፣ መጽሐፉ ከታተመ ከ74 ዓመት በኋላ በ1990 ዓ.ም. በድጋሚ ሲታተም በመጽሐፉ ላይ ስማቸው እንኳ በአግባቡ አልተጠቀሰም። ለመጽሐፉ በተዘጋጀው የፓትርያርኩ መልእክት መጨረሻ አንቀጽ ላይ፣ “በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የተጻፈውን በ፲፱፻፲፮ ዓ.ም. የታተመውን” ተብሎ ከመጠቀስ ባለፈ በተገቢው መንገድ ስማቸው እንዲጠራበት የተፈለገ አይመስልም። ለምን?

ይቀጥላል

(በጮራ ቍጥር 50 ላይ የቀረበ)



[1] ደስታ ተክለ ወልድ ባሳተሙላቸው መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ መጽሐፋቸው ላይ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ከኢትዮጵያ ወጥተው በኢየሩሳሌም መኖር የጀመሩት በተወለዱ በ20 ዓመታቸው በ1882 ዓ.ም. መኾኑን ጠቍመዋልና፣ በዚህ መሠረት ከተሰላ የተወለዱበት ዘመን 1862 ዓ.ም. ይኾናል። ሌሎች ምንጮች ግን የተወለዱበት ዘመን 1864 ዓ.ም. ነው ይላሉ። በዚህ ጽሑፍ የመረጃ ምንጭ የኾኑት ደስታ ተክለ ወልድ የጻፉትን ዓ.ም. ነው የተከተልነው። 

[2] አለቃ ያሬድ 2004፣ ገጽ 154

[3] ሥርግው (ዶ/ር) 1981፣ ገጽ 24-27

[4] በዚያ ዘመን የአብነት (የቤተ ክህነት) ትምህርት ተማሪዎችን ነው።

[5] ኪዳነ ወልድ 1948፣ ገጽ 25።


No comments:

Post a Comment