Tuesday, April 2, 2019

ምስባክ

“ዓሣ ከውሃ ከወጣ ነፍሱ ወጣ”
አንዳንድ ሰዎች ለወንጌል መሰል ስብከታቸው መንግሥተ ሰማያት ለማስገባት አንድ እርምጃ የሚቀር እስኪመስል ድረስ ለስብከታቸው የሚገርም ርእስ ይሰጣሉ። ወደ ስብከቱ ፍሬ ነገር ሲገባ ግን ውጤቱ አብዛኛውን ጊዜ የመኪናን ፍሬቻ መብራት ወደ ግራ አሳይቶ ወደ ቀኝ እንደ መታጠፍ ያኽል ነው፤ ወይም ወደ ቀኝ አሳይቶ ወደ ግራ እንደ መሄድ ይኾናል።

እኔና ክርስቲያን ወንድሜ (አሁን በሕይወተ ሥጋ የለም) በመንገድ ስናልፍ የምንሄድበትን ጉዳይ ትተን ይህን ስብከትማ ሳንስማ መሄድ የለብንም እንድንል ያደረገንን የስብከት ርእስ አንድ ቤተ ክርስቲያን የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በትልቁ ተለጥፎ አየን። ርእሱ “ዓሣ ከውሃ ከወጣ ነፍሱ ወጣ” የሚል ነበር። ከዚያ ና እባክህ ይህን የወንጌል ቃል ተካፍለን እንሂድ፤ የሚገርም ርእስ ነው ተባብለን መልእክቱን ለመስማት ጎራ አልን። በጕጕት ስንጠብቅ የወንጌሉ ድምዳሜ “የዚህች ቤተ ክርስቲያን አባል ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም” የሚል ኾኖ አገኘነው። እኛም ሰባኪውን በመጨረሻ አግኝተን ማነጋገር አለብን ብለን ቈየንና አገኘነው፤ አነጋገርነውም። በተለይ ወንድሜ በሰል ያለ ሰው ነበርና እግዚአብሔርን፣ ሕዝቡንም ይቅርታ እንዲጠይቅና ከስሕተቱ እንዲመለስ አበክሮ መክሮት በሰላም ተለያየን። በእውነት ርእሱና የስብከቱ ሐተታና ድምዳሜ እንደ ወንጌሉ ቃል የተገናኙ አልነበሩም።
ጌታችን ቤተ ክርስቲያኑን የተመሠረተው ኢየሱስን ክርስቶስ እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጅ በሚለው እምነት ላይ ነው እንጂ በምድራዊ ድርጅት በኩል አይደለም። የቤተ ክርስቲያን መሠረትም ራሱ ጌታ እንጂ ሌላ ፍጡር አይደለም። ጌታ ኢየሱስ ለጴጥሮስ እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።” ብሎ የተናገረውም ይህንኑ ያሳያል። አንዳንዶች ግን ይህን ንባብ ዐለቱ ጴጥሮስ ነው ብለው ይተረጕሟሉ። ነገር ግን ዐለቱ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” የሚለው እምነት እንጂ ጴጥሮስ አይደለም (ማቴ. 16፥16፡18)። አለቃ ኪዳነ ወልድ ይህን አስመልክቶ በግጥም እንዲህ ብለዋል፦
“የቤተ ክርስቲያን መሠረት ኰኵሕ (ዐለት) - ማነው ይላሉ አለመሲሕ
ጴጥሮስም ማለት ኖራና ኆጻ (አሸዋ) - መሠረት ያለው ኰኵሓዊ (ዐለታዊ) ሕንጻ
ወዲበ ዛቲ ኰኵሕም (በዚህች ዐለት ላይ) ያለው - ዐጥፎ መልሶ ራሱን ነው።
ከግዜር ተወልደን በሃይማኖት (በእምነት) - ያባታችን ቤት የምንላት
ቤተ ክርስቲያን ሰላ ድንጋይ - አልታነጸችም በፍጡር ላይ
መሠረቷማ ጴጥሮስ ቢኾን - ገፍተው በጣሏት እነኔሮን
ሥር መሠረቷስ በመጻሕፍት - ወልድ ዋሕድ ወበኵር የሙሴ ዐለት
ዐርብ ተነጥፎ በሞት በረሓ - ያፈሰሰልን የሕይወት ውሃ
ካጠጣን በቀር ውሃና ደም - ሌላ መሠረት አለ አንልም” (ሃይማኖተ አበው ቀደምት ገጽ 244)

ቃሉም እንዲህ ይላል፦ “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” ይላል (1ቆሮ. 3፥11)። ስለዚህ በወንጌል ብሥራት ሰዎችን መጥራት ያለብን ወደ አዳኙ ኢየሱስ እንጂ ወደ ድርጅት ወይም ወደ ራሳችን መኾን የለበትም። እንዲህ ስንል ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል የሚማሩበት ስፍራ ኅብረት የሚያደርጉበት መንፈሳዊ ጉባኤ አያስፈልጋቸውም እያልን አይደለም። እነዚህ ግን ሰዎችን ወደ ኢየሡስ የሚመሩ እንጂ ወደራሳቸው የሚስቡ መኾን የለባቸውም።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፣ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር፤ ከአሁን ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁትማል” (ዮሐ. 14፥6-7) በማለት እንደ ተናገረው፣ ኢየሱስን ያየ አብን አይቶአል፤ ኢየሱስንም ያወቀ አብንም ዐውቋል፣ ምክንያቱም ወደ አብ የሚወስደን እውነተኛው የሕይወት መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ነው። ወደ ዐዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ ወደ ሰማያዊቱ ጽዮን፣ ወደ እውነት ከተማ መድረሻው ብቸኛ መንገድ መግቢያ ደጇም እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ነው። ሌላ አማራጭ ወይም መንታ መንገድ የለም።

ከእውነተኛውና ከቀጥተኛው ብቸኛ የበጎች በር ከጌታችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ የጓሮ ወይም የስርቆሽ በር የለም፤ ከተማዋ የእውነት ከተማ ናትና። የእግዚአብሔር ቃልም እንዲህ ብሎ ያረጋግጥልናል፤ “ኢየሱስም ደግሞ አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ። … በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል።” (ዮሐ. 10፥7፡9) እንዲሁም “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖረው፣ በደጆቿም ወደ ከተማዪቱ እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሻዎችና አስማተኞች፣ ሴሰኛዎችም፣ ነፍስ ገዳዮችም፣ ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ በውጭ አሉ።” (ራእ. 22፥14-15)።

ወደዚህች ወደ ዐዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ ጽዮን ሰማያዊት፣ ወደ እውነት ከተማ ለመድረስና ለመግባት የልጅነት ሥልጣንም ጭምር ሊኖረን ይገባል። ሥልጣን ስንልም ልብሳቸውን በበጉ ደም ላጠቡ ኹሉና፣ በእግዚአብሔር እንድያ ልጁ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ ኹሉ የተሰጠ ነው። “ለተቀበሉት ኹሉ ግን በስሙም ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይኾኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” ተብሏልና በሕያው ቃሉ (ዮሐ. 1፥12)።

በዚህ መልእክት ርእስ “ዓሣ ከውሃ ከወጣ ነፍሱ ወጣ“ ተብሎ እንደ ተጠቀሰው፣ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌለው ሕይወት የለውም፤ ብቻውን ለሰይጣንና ለመላእክቱ በተመደበው ዘላለማዊ ገሃነመ እሳት ለዘለዓለም እየተሠቃየ ይኖራል። በእግዚአብሔር ልጅ ያላመነች ነፍስ ሁለተኛውን ሞት ትሞታለች። ሁለተኛው ሞት ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር መለየትና በሥቃይ መኖር ነው። ቃሉ እንዲህ ይላልና። “ልጁ (ወልድ) ያለው ሕይወት አለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት ለውም” (1ዮሐ. 5፥12) በክርስቶስ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አሁን አለው (ዮሐ. 3፥16፡36፤ 1ዮሐ. 5፥11-12)። “በእርሱ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አኹን ተፈርዶበታል።”

“ዓሣ ከውሃ ከወጣ ነፍሱ ወጣ” እንዲሉ፣ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ መዳንን ዛሬ (አኹን) ካልተቀበለና ከክርስቶስ ጋር መኖር ካልጀመረ ከእርሱ ተለይቶ ይጠፋል። ለሰው ኹሉ አንድ ጊዜ መሞት ከዚያም በኋላ ፍርድ ተመድቦበታል (ዕብ. 9፥27)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን አዳኝና መድኀኒት አድርገን ስናምነውና ስንቀበለው በመንፈስ ቅዱስ ደግሞ የተወለድን የጸጋ ልጆቹ እንኾናለን።

እያለቀ ባለው በዚህ የጸጋ፣ የምሕረትና የወንጌል ዘመን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እናንተ ደካሞች ወደ እኔ “ኑ” ሸክማችሁን ልውሰድ ላሳርፋችሁም እያለ እያንዳንዳችንን እጁን ዘርግቶ ሲጠራን፣ ወንድሜ ሆይ ይህን የምሕረት ጥሪ አትለፈው፣ እኅቴ ሆይ ይህን የምሕረት ጥሪ አትለፊው። ነገን አናውቀውምና፣ የመዳን ቀን አሁን ነውና።

እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ በመስቀል ተሠቃይቶ የሞተውና የተነሣው ለእኛ ለኀጢአተኞች ኹሉ እንጂ “ለጻድቃን” አይደለም። ከእርሱ በቀር መድኀኒት እንደሌለ እየታወቀ መድኀኒቱን እርሱን የማንቀበልና የምንገፋ ከኾነ በእርሱ ሞት የተዘጋጀልንን የዘላለም ሕይወት እንዳንቀበል በራሳችን ላይ ፈርደናል ማለት ነው። ዛሬ የእግዚአብሐየር ትእዛዝ በልጁ እንድናምን ስለኾነ (ዮሐ. 629፤ 1ዮሐ. 323) እግዚአብሔርን እጅግ የሚያሳዝነው ኀጢአትም በልጁ አለማመን ነው (ዮሐ. 168-9)። ምክንያቱም “በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።” (1ዮሐ. 510-12)።  

ስለዚህ ሕይወትን ምረጥ/ጪ፣ “የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ እውነተኛም የኾነውን እናውቅ ዘንድ ልቦናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በኾነው በእርሱ አለን፤ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።“ (1ዮሐ. 5፥20)። ለጻድቅ የመታዘዝ ልጅ እንጂ ወደ ዘለዓለም ሞት ለሚወስደው የኀጢአት ባሪያ አትኹን። ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ላይ ከዛሬ 2000 ዓመት በፊት ስለ እኔና ስላንተ/ስላንቺ ስለ ሰዎች ልጆች ኹሉ ክቡር ደሙን አፈሰሰልን፣ በደሙም የኀጢአታችንን ስርየት ተቀበልን። ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞታችንን ሞተልን። ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ እርሱ ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እርሱ ስለ እኛ ተጨነቀ፤ ተሣቀየም፤ አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፤ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፣ ስሕዝብ ኀጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? (ኢሳ. 53፥4-9)።

ይህ ኢየሱስ በመጀመሪያው የነበረው፣ ሥጋም የኾነው ቃል ነው (ዮሐ. 1÷1፡14)። ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ተወለደ፤ ተጠመቀ፤ ከዲያብሎሰ ዘንድ ተፈተነ፤ ኢየሩሳሌምን ተመልክቶ አለቀሰ፤ እርሱ በጌቴሴማኔ ተጨነቀ፤ ተያዘ፣ እንደ ወንጀለኛም ተፈረደበት፤ ተገረፈ፤ ለሞት ዐልፎ ተሰጠ፤ ተሰቀለ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ደም በመስቀል ላይ ፈሰሰ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ በጦር ተወጋ፣ እርሱ ማስተስረያችንና ቤዛችን ነው። ሞተ፤ ተቀበረም፤ እርሱ ከሙታን በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ወደ ሰማይም ዐረገ፤ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛም ይመጣል፤ ሕያዋንንና ሙታንን ለይቶ እንደየሥራቸው ይሰጣቸዋል። እርሱ እግዚአብሔርን የሚገልጥ የእግዚአብሔር አስተርእዮ ነው፣ እርሱ አዳኛችንና መድኀኒታችን ነው። በእርሱ እግዚአብሔር ስለ መዳናችን ተናገረ፤ የምንድንበትን ሥራ ሠራ፣ መከራን ተቀበለ፣ በእርሱ እግዚአብሔር ያዘዘው ቤዛ እንዲቀርብ አደረገ። በእርሱ መሥዋዕታዊ ሞት እግዚአብሔር የኀጢአታችንን ይቅርታ አስገኘልን። በእርሱ ኹሉ ተፈጸመ።

ታዲያ አሁን ምን ላደርግ ይገባኛል ለሚል ጠያቂ መልሱ ዐጭርና ግልጽ ነው፤ ንስሓ መግባትና አንድያ በኾነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን፣ ከእርሱ በእርሱ የሚገኘውን መዳን መውረስና የዘለዓለም ሕይወት ማግኘት ነው። “እግዚአብሔርም የዘለዓለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው፤ ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም (1ዮሐ. 5፥11-12)።
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

(ከጮራ ቍጥር 50 ምስባክ ዐምድ ላይ የተወሰደ)  

No comments:

Post a Comment