Monday, December 18, 2017

ማስታወቂያ

ጮራ ቍጥር 49 በቅርብ ቀን ለንባብ ትበቃለች


Sunday, June 25, 2017

የሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበርን የአገልግሎት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ተመረቀ

ከሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ሚስዮናውያት አንዷ በነበሩት ዶሪስ ቤንሰን፣ “The Most Valuable Thing: The Word at Work in Ethiopia” ተብሎ በእንግሊዝኛ የተጻፈውና ወደ ዐማርኛ “ከሁሉ የበለጠ ዋጋ ያለው:- የእግዚአብሔር ቃል በሥራ ላይ በኢትዮጵያ” ተብሎ የተተረጐመው መጽሐፍ በርካታ የአገልግሎቱ የቀድሞ አባላትና ተሳታፊዎች በተገኙበት ሠኔ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት አዳራሽ ተመረቀ።

            በጸሎተ ወንጌል የተከፈተው የምረቃው ሥነ ሥርዐት ዝማሬዎችም የቀረቡበት ሲሆን፣ ቃለ ወንጌልም ተሰብኮበታል። የማኅበሩን አገልግሎት በተለይ ከመጽሐፉ ደራሲት ጋር በተገናኘ ቅኝት ያደረገ ጽሑፍም የመርሐ ግብሩ አካል የነበረ ሲሆን፣ በመጽሐፉ ላይ የተዘጋጀ ዳሰሳዊ ጽሑፍም ቀርቧል። በመጽሐፉ ላይ የታተመው ቀዳሚ ቃልም በንባብ ተሰምቷል። ቀዳሚ ቃሉ አንድ ታሪክ ሳይዛባና እውነተኛነቱ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በተለይ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባትና በሚታወቀው ታሪክ ላይ ሌሎች ሲዋሹ እውነተኛ ምስክር ሆና አለመቅረብ ትልቅ ትዝብት ላይ እንደሚጥላት አስረድቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ታሪክ ላይ የተፈጸመውን ታሪክን አዛብቶ የማቅረብ ክፉ ሥራ ይህ ከእንግሊዝኛ ወደ ዐማርኛ የተመለሰውና ለምረቃ የበቃው መጽሐፍ እንደሚያስተካክለው ተስፋ አድርጓል። አክሎም መጽሐፉን ማስተርጐምና ማሳተም ያስፈለገበትን ምክንያቶች ሲያብራራ፥

Thursday, June 15, 2017

የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ፳፭ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዐት ተከበረ

በፈቃደ እግዚአብሔር በታላቁ ሊቅ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ አሰባሳቢነት በተመሠረተው ማኅበረ በኵር ከነሐሴ 1983 ዓ.ም. አንሥቶ ስትታተምና ስትሠራጭ ላለፉት ፳፭ ዓመታት የዘለቀችውና ለብዙዎች የወንጌል ብርሃንን ስትገልጥ የቈየችው የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ፳፭ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት አዳራሽ የአገልግሎቱ አባላትና ደጋፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸውም ወገኖች በተገኙበት ለልዑል እግዚአብሔር ክብርን በመስጠት ተከበረ።


በዚህ የመጽሔቷ የ፳፭ ዓመታት የአገልግሎት ጕዞ በተዘከረበት በዓል ላይ ልዩ ልዩ መንፈሳውያን መርሐ ግብሮች የቀረቡ ሲሆን፣ ማኅበሩን ለመሠረቱና እዚህ ላደረሱ አባቶች ዕውቅናም ተሰጥቷል። ጮራ መጽሔት ላይ ያተኰረ ዳሰሳም የቀረበ ሲሆን፣ ለዚህ በዓል የተዘጋጀውና በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ላይ በተከታታይ ሲወጣ የነበረው የመሠረተ እምነት ዐምድ ተከታታይ ጽሑፎች ስብስብ ቅጽ አንድ መጽሐፍም ታትሞ ተመርቋል። መጽሐፉ በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳውያን መጻሕፍት መሸጫ መደብሮች አማካይነት በመሠራጨት ላይ ይገኛል።የመጽሔቷን አገልግሎት ለማጠናከርና ለማስፋት በተያዘው ዕቅድ መሠረትም የጮራ መጽሔት የአባልነት ቅጽና መታወቂያ ተዘጋጅቶ በዕለቱ የተዋወቀ ሲሆን፣ የጮራ አንባብያንና አገልግሎቱን መደገፍ የሚፈልጉ መሙላትና አባል መሆን ጀምረዋል። ወደፊትም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ የአገልግሎቱ ደጋፊዎች የመጽሔቱ አባል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል። በዕለቱ የቀረቡ ጥናታዊና ዳሰሳዊ ጽሑፎች፣ የአባልነቱም ቅጽ  እንደ አስፈላጊነቱ በቀጣዩ ጮራ ዕትም እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።     

Monday, May 22, 2017

የዘመን ምስክር READ PDF
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዘኵሎን አድያማተ ትግራይ (1887 - 1983 ..)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተከሥተውና በርካታ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተው ካለፉ ታላላቅና ስመ ጥር አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ተጠቃሽ ናቸው። እኒህ አባት በእምነታቸው የጸኑ፣ በመልካም ሥራቸው የተመሰከረላቸው፣ በትምህርታቸው ብሉያትንና ሐዲሳትን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን በሚገባ የተረዱ፣ በስብከታቸው፣ በተደማጭነታቸው የሚታወቁ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ላመኑበት እውነት ብቻቸውንም ቢኾን የሚቆሙ፣ በፈሊጥና በጥበበ ቃል የማይረሳና ጠንካራ መልእክት ማስተላለፍ የቻሉ፣ ማንንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ የተረዱትን እውነት በሚገባ በመስበክ የኖሩ መምህር ወመገሥጽ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልትሻሻልና ትውልዱን ልትታደግ የምትችለው በትምህርት ብቻ መኾኑን ያመኑ፣ አምነውም በትምህርት ላይ ብዙ የሠሩ ታላቅ አባት ነበሩ። የሕይወት ታሪካቸውና ሕያው ሥራዎቻቸው እነሆ፣  


ልደት እድገት እና ትምህርት
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ከቄስ ገብረ ኢየሱስ ፈቃዱና ከወ/ሮ (በኋላ እማሆይ) ወለተ ኢየሱስ ምሕረተ አብ ሐምሌ 12 ቀን 1887 ዓ.ም. ኤርትራ ውስጥ በአካለ ጕዛይ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ኩርባርያ በተባለ አጥቢያ ተወለዱ። በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሲጠመቁም ገብረ መስቀል ተባሉ። በዚህ ስመ ክርስትና ጳጳስ እስከ ሆኑ ድረስ ተጠርተዉበታል። ወላጆቻቸው የወለዷቸው በስእለት ስለ ነበር፣ በተወለዱ በሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜያቸው በአካባቢያቸው ወደሚገኝ የአቡነ ብፁዕ አምላክ ሥላሴ ገዳም ወስደው ለማኅበረ መነኮሳቱ ሰጧቸው። ማኅበረ መነኮሳቱም ወላጆቻቸው በእምነታቸው መሠረት የገቡትን ቃል መፈጸማቸውን በማድነቅና በማመስገን፣ እስከ ስድስት ዓመት ድረስ እዚያው በቤታቸው እንዲያሳድጓቸው በመምከር አሰናበቷቸው። ስድስት ዓመት ሲሞላቸውም አምጥተው አስረከቧቸውና ከንባብ ትምህርት እስከ ግብረ ዲቁና ያለውን ተምረው በዘጠኝ ዓመታቸው የዲቁና ማዕርግ ተቀበሉ።

Monday, January 16, 2017

“ዘቦቱ መርዓት መርዓዊ ውእቱ - ሙሽራዪቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” (ዮሐ. 3፥29)

መጥምቁ ዮሐንስ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት መንገድ ጠራጊ፣ ዐዋጅ ነጋሪ እንደ መኾኑ፣ ሕዝቡ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ እንዲመለሱና ለንስሓ የሚገባ ፍሬ እንዲያፈሩ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” በማለት በበረሓ እያወጀ ነበር የመጣው። 

የሰሙትም ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር። ዮሐንስ እኔ ጐንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ነኝ፤ ከእኔ የሚበልጠው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል አለ። ሕዝቡን ከጌታው ጋር ካገናኘ በኋላም ሕዝቡ የጌታ፣ ጌታም የሕዝቡ ብቻ መኾናቸውን ለመግለጽ “ሙሽራዪቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” ሲል ተናገረ። በዚሁ ዐውድ እርሱ እንደ ሚዜ የሚቈጠርና አገልግሎቱም እዚሁ ድረስ ብቻ መኾኑንና መፈጸሙን ገለጸ። 

ከመጥምቁ ዮሐንስ በኋላ የተነሡት የቃሉ አገልጋዮች ሐዋርያትም፣ በዮሐንስ መንገድ ጠራጊነት የመጣውንና ስለ በጎቹ ራሱን አሳልፎ የሰጠውን ጌታ እርሱ ለሞተላቸው ኹሉ በማስተዋወቅ ሙሽራውንና ሙሽራዪቱን የማገናኘት ተግባር ነው የፈጸሙት። ቅዱስ ጳውሎስ “እስመ ፈኃርኩክሙ ለአሐዱ ምት ድንግል ወንጹሕ ክርስቶስ ከመ አቅርብክሙ ኀቤሁ - እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ ዐጭቻችኋለሁ” (2ቆሮ. 11፥2) ሲል የሰጠው ምስክርነትም ይህንኑ እውነት ያስረዳል። 

Monday, January 2, 2017

 መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 48 ለንባብ በቅታለች

በዚህ ዕትም፦
·        በዘመን ምስክር ዐምድ፦ የብፁዕ አቡነ ዮሐንስን ታሪክ ያስቃኛል።
·        በዕቅበተ እምነት ዐምድ፦ ለመድሎተ ጽድቅ የተሰጠውን ምላሽ ቀጣይ ክፍል ይዟል።
·        በአለቃ ነቅዐ ጥበብ ዐምድ፦ ስግደትን የተመለከተ ትረካዊ ጽሑፍ ቀርቧል።
·       በፍካሬ መጻሕፍት ዐምድ፦ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ፥ የካሌብን የታናሽ ወንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው” (መሳፍንት 39) የሚለውን እየተጠቀሰ፥ ቅዱሳን በነገረ ድኅነት ውስጥ ሱታፌ /ተሳትፎ/ አላቸው በማለት ለሚነዛው ኑፋቄ ዐውዳዊ ፍቺ በመስጠት ጥቀሱን ያብራራል።
·        በመንፈሳውያን ቃላት ዐምድ፦ “ሕግ” የተሰኘው ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር የተብራራበትን ጽሑፍ ይዟል።
·        በምስባክ ዐምድ፦  “ተስፋ አለ” በሚል ርእስ ስብከተ ወንጌል ቀርቧል። እና ሌሎችም

አገልግሎቱን ለመደገፍ ቢያስቡ፡- በሚከተለው አድራሻ ሊያገኙን ይችላሉ
ማኅበረ በኵር ስ.ቊ. 0118950459/0911971167
የፖ.ሳ.ቊ. 23956 ኮድ 1000
የባንክ ሒሳብ ቊጥር ማኅበረ በኵር፡-
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልደታ ቅርንጫፍ
ሒሳብ ቊጥር 1000002276848

ዳሸን ባንክ መገናኛ ቅርንጫፍ
ሒሳብ ቊጥር 0025663937001

አቢሲኒያ ባንክ 6 ኪሎ ቅርንጫፍ
ሒሳብ ቊጥር 1118382

ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ
ሒሳብ ቊጥር 1600160009836