Thursday, June 15, 2017

የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ፳፭ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዐት ተከበረ

በፈቃደ እግዚአብሔር በታላቁ ሊቅ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ አሰባሳቢነት በተመሠረተው ማኅበረ በኵር ከነሐሴ 1983 ዓ.ም. አንሥቶ ስትታተምና ስትሠራጭ ላለፉት ፳፭ ዓመታት የዘለቀችውና ለብዙዎች የወንጌል ብርሃንን ስትገልጥ የቈየችው የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ፳፭ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት አዳራሽ የአገልግሎቱ አባላትና ደጋፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸውም ወገኖች በተገኙበት ለልዑል እግዚአብሔር ክብርን በመስጠት ተከበረ።


በዚህ የመጽሔቷ የ፳፭ ዓመታት የአገልግሎት ጕዞ በተዘከረበት በዓል ላይ ልዩ ልዩ መንፈሳውያን መርሐ ግብሮች የቀረቡ ሲሆን፣ ማኅበሩን ለመሠረቱና እዚህ ላደረሱ አባቶች ዕውቅናም ተሰጥቷል። ጮራ መጽሔት ላይ ያተኰረ ዳሰሳም የቀረበ ሲሆን፣ ለዚህ በዓል የተዘጋጀውና በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ላይ በተከታታይ ሲወጣ የነበረው የመሠረተ እምነት ዐምድ ተከታታይ ጽሑፎች ስብስብ ቅጽ አንድ መጽሐፍም ታትሞ ተመርቋል። መጽሐፉ በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳውያን መጻሕፍት መሸጫ መደብሮች አማካይነት በመሠራጨት ላይ ይገኛል።



የመጽሔቷን አገልግሎት ለማጠናከርና ለማስፋት በተያዘው ዕቅድ መሠረትም የጮራ መጽሔት የአባልነት ቅጽና መታወቂያ ተዘጋጅቶ በዕለቱ የተዋወቀ ሲሆን፣ የጮራ አንባብያንና አገልግሎቱን መደገፍ የሚፈልጉ መሙላትና አባል መሆን ጀምረዋል። ወደፊትም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ የአገልግሎቱ ደጋፊዎች የመጽሔቱ አባል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል። በዕለቱ የቀረቡ ጥናታዊና ዳሰሳዊ ጽሑፎች፣ የአባልነቱም ቅጽ  እንደ አስፈላጊነቱ በቀጣዩ ጮራ ዕትም እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።     

No comments:

Post a Comment