ካለፈው የቀጠለ
የእማሆይ ኤልሳቤጥ ስብከት
አንዳንድ ሰዎች፥ ኢየሱስን ተቀበሉና ለተቀበሉት ሁሉ ያዘጋጀው የእግዚአብሔር ልጅነት መብት
ይኑራችሁ ሲባሉ፥ ስቀድስ፥ ስወድስ የኖርኩ ክርስቲያን ነኝ፤ ወላጆቼ፥ አያቶቼ … ከክርስቲያን ቤተሰብና ዘር የተወለዱ ናቸው፤ እንዴት
እንደ አረመኔ ቈጥረህ ኢየሱስን ተቀበል ትለኛለህ? ይላሉ፡፡
ከእነዚህ ጋር የወገንክ ወዳጄ ስማኝ ልንገርህ! ኢየሱስ ክርስቶስን ወላጆችህ ሲጠሩት መጽሐፍ
ሲነበብ፥ ስሙን ሰምተህ፥ ታሪኩንም ዐውቀህ ይሆናል፡፡ ይህ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም በዓለም ታሪክም የተመዘገበ ታሪካዊ እውነት
ስለሆነ ታሪኩን በማንኛውም መንገድ ልታገኘው ትችላለህ፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሪካዊነት በላይ ተፈላጊው ጉዳይ ለአንተ የሆነልህንና
ያደረገልህን ዐውቀህና አምነህ መቀበልህና በተቀበልኸውም መጠቀምህ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም መወለዱንና
በዓለም ውስጥ ሲያስተምር ቆይቶ መሞቱን የዓለም ሕዝብ ሁሉ ማለት ወዳጆቹ፥ በጠላትነት የተሰለፉበት፥ ገለልተኞች የሆኑት ሁሉ ከመጽሐፉ
ይረዱታል፤ ሊክዱትም አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከኀላፊ ታሪክ ሁሉ የሚለየው ጠቃሚ ቁም ነገር ለምን መጣ? በነቢያት ትንቢት መሠረት
መጣ፡፡ በሰጠው ተስፋና በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መጣ፡፡ ከዚህ የኔ ድርሻና ጥቅም ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው ልባዊና
እውነታዊ መልስ ነው፡፡