Monday, January 20, 2014

የመዳን ትምህርት

ካለፈው የቀጠለ
የእማሆይ ኤልሳቤጥ ስብከት

አንዳንድ ሰዎች፥ ኢየሱስን ተቀበሉና ለተቀበሉት ሁሉ ያዘጋጀው የእግዚአብሔር ልጅነት መብት ይኑራችሁ ሲባሉ፥ ስቀድስ፥ ስወድስ የኖርኩ ክርስቲያን ነኝ፤ ወላጆቼ፥ አያቶቼ … ከክርስቲያን ቤተሰብና ዘር የተወለዱ ናቸው፤ እንዴት እንደ አረመኔ ቈጥረህ ኢየሱስን ተቀበል ትለኛለህ? ይላሉ፡፡

ከእነዚህ ጋር የወገንክ ወዳጄ ስማኝ ልንገርህ! ኢየሱስ ክርስቶስን ወላጆችህ ሲጠሩት መጽሐፍ ሲነበብ፥ ስሙን ሰምተህ፥ ታሪኩንም ዐውቀህ ይሆናል፡፡ ይህ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም በዓለም ታሪክም የተመዘገበ ታሪካዊ እውነት ስለሆነ ታሪኩን በማንኛውም መንገድ ልታገኘው ትችላለህ፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሪካዊነት በላይ ተፈላጊው ጉዳይ ለአንተ የሆነልህንና ያደረገልህን ዐውቀህና አምነህ መቀበልህና በተቀበልኸውም መጠቀምህ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም መወለዱንና በዓለም ውስጥ ሲያስተምር ቆይቶ መሞቱን የዓለም ሕዝብ ሁሉ ማለት ወዳጆቹ፥ በጠላትነት የተሰለፉበት፥ ገለልተኞች የሆኑት ሁሉ ከመጽሐፉ ይረዱታል፤ ሊክዱትም አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከኀላፊ ታሪክ ሁሉ የሚለየው ጠቃሚ ቁም ነገር ለምን መጣ? በነቢያት ትንቢት መሠረት መጣ፡፡ በሰጠው ተስፋና በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መጣ፡፡ ከዚህ የኔ ድርሻና ጥቅም ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው ልባዊና እውነታዊ መልስ ነው፡፡ 

ትንቢቱ፥ ቃል ኪዳኑ፥ ተስፋው ምን ነበረ? “ይሆዋ ጽድቃችን” የሚል ሕዝብ ከሚያድነውና ከሚያጸድቀው አምላኩ የተነሣ “ምን አለብኝ! እፎይ” በማለት ዕረፍትንና ሰላምን የሚቀዳጅበት፤ ጽድቅን በመጐናጸፍም በኀጢአት ዕዳ ከመጠየቅ ነጻ የሚወጣበት ድርጊት ይፈጸም ዘንድ እንዳለው የተተነበየ፥ ቃል የተገባበት፥ ተስፋ የተነገረበት የምሥራች ነበር (ኢሳ. 45፥25፤ ኤር. 23፥5-6)፡፡

“ይሆዋ ጽድቃችን” ለሚል ሕዝብ መፈጠር ምክንያት የሆነው በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት፥ ያለሕግ የተገለጸው የሚታመኑበትን ሁሉ ማዳን የቻለው “ጽድቅ” ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሮሜ 3፥21-23፤ 1ኛ ቆሮ. 1፥31)፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ “ይሆዋ ጽድቃችን” ሆኖ በመገለጹ የተቀበልነውን ሁሉ ከኀጢአት፥ ከሕግ ክስና ከፍርድ ነጻ ሊያወጣን የቻለው እንደ ሕግ ፍርድ መቀበል የሚገባንን ቅጣት፥ ቤዛችን ሆኖ ራሱ ስለተቀበለልንና በፍርድ ነጻ ስለወጣን ነው (ኢሳ. 1፥27፤ ሮሜ 3፥24)፡፡ የዚህንም የምሥራች ቃል መሰበክ አስፈላጊነት ሰው በእምነት እንዲቀበለውና፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛ ነው፤ በሞቱም የሞት ዕዳዬን ከፍሎልኛል፡፡ በኀጢአቴ ከመጠየቅ ነጻ ወጥቻለሁ፤ እግዚአብሔር ይመስገን” በማለት እንዲታመንበትና እንዲድን ነው (ኢሳ. 53፥4-12፤ ሮሜ 3፥25-26፤ 4፥22-25፤ 5፥21፤ ገላ. 3፥13፤ 1ጴጥ. 2፥22-24)፡፡

ስማኝ ወዳጄ! አንተም ይህን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በእምነት ብትቀበል ኖሮ ልትድንና የእግዚአብሔር ልጅ ልትሆን መብት ተሰጥቶህ ነበር፡፡ ይህን ወንጌል እንዳልተቀበልክ ግን ሕይወትህ ይመሰክራል፡፡ ለመዳን ከአንዱ የታሪክ ቦታ ወደ ሌላው፥ ከደብር ወደ ደብር (ከተራራ ወደ ተራራ) ከገዳም ወደ ገዳም (ከዱር ወደ ዱር) በመንከራተት ደኅንነትን፥ ጽድቅን፥ ስለምን ትፈልጋልህ? መዳን በዚህ በኩል ለመገኘቱ ርግጠኛ ከሆንክ ዕድሜ ልክ መንከራተት ሳያስፈልግህ የአንዱ የታሪክ ቦታ፥ የአንዱ ደብር፥ የአንዱ ገዳም ጉብኝት አይበቃህም ነበርን?

በደብረ ፋይድ ገብርኤል ስም መጠራት ማለት ወልደ ገብርኤል፥ እኅተ ገብርኤል … ፣ መባል ለዐሥር ትውልድ የሚበቃ የኀጢአት ስርየት ያስገኛል ብለህ ታምናለህ? በዚህ ለመዳን ትችል ዘንድ ስምህ ክንፈ ገብርኤል ሆኗል፡፡ በደብረ ፋይድ ገብርኤል ስም የዘከረ እንኳን ለራሱ ለአንድ እልፍ ዝርያው ገነት የሚያስገባ ይለፍ ያገኛል በሚለው ተስፋ ለመሸፈን በየወሩ የደብረ ፋይድ ገብርኤልን ትዘክራለህ፡፡ ተስፋው በመንፈስ ቅዱስ የታተመ እውነት ከሆነ በሕይወትህ አሁንም አለመርካት መቅበዝበዝና ተስፋ ቢስነት ለምን ይታያል?

አባ ዱካዎስ፥ እማሆይ ተክሪዛ፥ ቅድስት ሰማሪት፥ መላኩ ተርፍኤል፥ ቅዱስ ተክለ ሰንበት…  በየሳምንቱ ሲኦልን እየመዘበሩ እልፍ፥ እልፍ ነፍሳትን (ያልተጠመቁትን እንኳ እያጠመቁ) ወደ ገነት ያስገባሉ እያልክ በቃልም በመጻፍም ትሰብካለህ፡፡ በዚህ ሁኔታ አንድም ነፍስ በሲኦል ባልተገኘ ነበር፡፡ የምትሰብከው እውነት ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ለመንፈስህ ቢመሰክርልህ ኖሮ ከእነዚህ አለኝታዎች ሁሉ አንዱ በበቃህ ነበር!!

ኧረ ለነፍስህ አንድ እውነት ብታስጨብጣት ይበጅሃል! ጽድቅን የተራበችና የተጠማች ነፍስህ የምትፈልገው “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ ወደ እኔ የሚመጣ አይራብም፤ የሚያምንብኝም አይጠማም፡፡” በማለት የተረጋገጠ ተስፋ ሲጪውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ሆኖ ሳለ (ዮሐ. 6፥35) አንተ ያቀረብክላት ድንጋይን ነው እንዴት ትቈርጥምልህ? ነፍስህ በኢየሱስ ክርስቶስ ከተባረኩት ሁለት ዓሣዎች (ብሉይና ዐዲስ?) ስጠኝ ስትልህ ነዳፊዎችን እባብንና ጊንጥን ሌሎችንም ተልከስካሽ ፍጥረታትን ሰጠሃት፡፡ አንዴት ትመገባቸው? ለነፍስህ ይህን ያህል ክፉ ከሆንክ ለሌላውማ ምን ያህል ትከፋ ይሆን? ኧረ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ለተቅበዝባዥ ነፍስህ ዕዘንላት!!

ቀኖች ዕረፍትን ይሰጡኛል ብለህ ስንቱን ቀኖች “ሰንበት” በማለት ሰየምካቸው? አከበርካቸው? ሰንበት ማለት ዕረፍትን እንዲሰጥ በሰው የሚሰየም ቀን ማለት እኮ አይደለም፡፡ በራሱ ዕረፍት ማለት እንደ ሆነ አልተገነዘብክም፡፡ ሰንበታትህ እንዲሆኑ በሰየምካቸው በዓላት (ቀኖች) ነፍስህ የምትፈልገውን ዕረፍት መቼ አግኝታ ታውቃለች? ምሳሌ ልንገርህ ከጉድጓድ ውስጥ የገባው በሬ በጕድጓድ ውስጥ ሆኖ ሰንበትን ያክብር ተባለ፥ በሰንበት ከጕድጓድ ማውጣት አይቻልም በሚል ባህላዊ እምነት በሬው በጕድጓድ ውስጥ እንደ ተሰበረ፥ እንደ ቈሰለ ሆኖ እየተጨነቀ፥ እየታመመ፥ እየተሠቃየ፥ በረኃብ፥ በጥማት የሚያሳልፈው ቀን እውን ሰንበት (ዕረፍት) ይሆንለታልን? ጌታ ግን ድርጊቱን አውግዞታል (ማቴ. 12፥9-14፤ ማር. 3፥1-6፤ ሉቃ. 6፥6-11)፡፡

ሰንበት ዕረፍት ማለት ነውና እግዚአብሔር እንዳረፈው ዐይነት ወደ ሆነው ዘላለማዊ ዕረፍት መግባት ነው (ዕብ. 4፥10)፡፡ ከጕድጓድ ውስጥ ወደ ገባው ወደ በሬው ምሳሌ ስንመለስ ከገባበት ጕድጓድ ቢወጣ ቊስሉን ቢታከም፤ ስብራቱን ቢጠገን፤ ቢጠግብ፥ ቢረካ ለእርሱ ሰንበቱ ይህ በሆነ ነበር!! አንተም ከበሬው በከፋ ሁኔታ ውስጥ እያለህ ስንትና ስንት ሰንበቶችን አሳለፍክ ዘላለማዊ ዕረፍት ሰጭውን፥ ራሱ ዕረፍት (ሰንበት) የሰንበትም ጌታ የሆነውን ኢየሱስን ብትቀበልና ብትኖርበት ነፍስህ ከመቅበዝበዝ ትድን፥ ከእስራትም ሁሉ ትፈታ ነበር (ማቴ. 11፥28-29፤ 12፥8፤ ቈላ. 2፥16-17)፡፡

በጎረቤትህ፥ በሥራህ ቦታ፥ በቤተሰብህ መኻል ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበሉ ክርስቲያኖች እንዳሉ እስኪ ልብ ብለህ አጥናቸው፡፡ ምድር ብትናወጥ እንኳ አይታወኩም (መዝ. (46)፥1-2)፡፡  በሆነው ቅጽበት ውስጥ ከዚህ ዓለም የመለየት ጥሪ ቢመጣ የሚናፍቁትን እንዳገኙ ይቈጥሩታል እንጂ አይሸበሩም፡፡ ሰዎች ምን ዐይነት ዋስትና የተገባላቸው ቢሆኑ ነው እስኪሉ ድረስ ሊደነቁባቸው ይችሉ ይሆናል (1ቆሮ. 5፥8፤ ፊል. 1፥20-24፤ 2ጢሞ. 1፥12፤ 4፥6-8)፡፡

እነዚህ ክርስቲያኖች ወደኔ ኑ እያለ ከጠራቸው፥ ሸክማቸውንና ድካማቸውን ከወሰደላቸው ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ የነፍስ ዕረፍት የልብ ሰላም፥ የመንፈስ ደስታና የሕይወት ዋስትና ርግጠኛነት ተትረፍርፎ ስለታደላቸው አይደለምን? አንተ ግን የራሳቸው ሸክም ከብዷቸው የሚፍገመገሙት፥ በድካምም የዛሉት ያንተ ቢጤ ሰዎች፤ እንዲሁም ሰይጣን ከሰው አእምሮ ጋር በመተባበር የፈጠራቸው መናፍስት ሸክምህንና ድካምህን የሚወስዱልህ መስሎህ በመታለልህ ብዙ በረከት ቀረብህ! እስኪ አንተው ራስህ አስበው! ና ብሎ የጠራህ ጌታ ኢየሱስ፤ አንተ የሄድከው ወዳልተጠራህበት ቦታ፡፡ ታዲያ ረድኤት ከየት ይምጣልህ? (መዝ. 121፥1-2)፡፡

በሥጋ ወንድም የሆንክ፥ አንተ የስም ክርስቲያን! እንደ እውነተኛ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹምና ሙሉ ደኅንነት አለ ብለህ ትናገራለህ፡፡ በልብህ ያለው እምነት በአፍህ ከሚነገረው ጋር አይመሳሰልም፡፡ “ፍጹምና ሙሉ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ዐስበህበት ታውቃለህ? ሙሉ በሆነ የእህል ወይም የውሃ ወይም የሌላ ነገር ስፍር ላይ ምንም ነገር ልትጨምር አትችልም፡፡ ብትጨምር ግን መስፈሪያው ቁናውና እንስራው ጭማሪውን ትርፍ አይቀበሉትም፤ በትርፍ የሚጨመረው ወደ ውጪ ይፈስሳል እንጂ፡፡ ፍጹም መዳንን መስጠት የማይችል ኢየሱስ ተሰብኮልህ እንደ ሆነ ብትመረምር ይበጅሃል፡፡

እነዚህ የታመንክባቸው ሰውና ሰይጣን-ሠራሽ የሆኑት የመዳኛ መንገዶች ሁሉ ሊያረኩህ አለመቻላቸው አያስደንቅም፡፡ የመዳኔን አጋማሽ በምግባር አሟላለሁ ትላለህ፡፡ እድንበታለሁ፥ ያጸድቀኛል ብለህ በምትመካበት ሥራም ቢሆን እንኳ በእግዚአብሔር ዐይን ቀርቶ በሰውም ፊት ጻድቅ ሆነህ አታውቅም፡፡ ማንን ታታልላለህ? ዳሩ ግን በሥራቸው የተፈረደባቸው ምስኪኖች መሆናቸውን የተረዱት በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ አዳኝነት ብቻ በመታመናቸው ነፍሳቸው ዕረፍትን የተጐናጸፈችላቸው ክርስቲያኖች መዳናቸውን ባረጋገጠላቸው መንፈስ ቅዱስ ተኣምር ሠሪነት፥ እምነታቸው የማይመኩባቸውን የመንፈስ ፍሬዎች እያፈራላቸው እንደሆነ አይተሃልን? (ሉቃ. 18፥9-17)፡፡

የደብረ ፋይድ መምህር አንድ ቀን እንዲህ አሉ፤ “የኛ ካህናት በምግባረ ብልሹነት እየተከሰሱ ነው፤ ለተቃዋሚዎቻችንም መሣለቂያና መሣቂያ አድርገውናል፡፡ እናንተ ካህናት እባካችሁ ተጠንቀቁ” አሉ፡፡ ንግግራቸውን የሰማው አንዱ ካህን ግን አጕረመረመ፡፡ “ባምር ጠላሁ እንዴ! አለች ዝንጀሮ፡፡ አድርግ፤ አታድርግ የሚለን ሰው አያስፈልገንም፡፡ እንደ እኛ የነበሩትን ሰዎች (ጌታን የተቀበሉትን ማለቱ ነው) የለወጠና ዐዲስ ፍጥረት ያደረጋቸውን ተኣምር ሠሪ ኀይል የሚሰጠን ያስፈልገን ነበር፡፡ ደግሞስ ምግባረ ብልሹነት የሚወገደው እግዚአብሔርን በመፍራት መሆኑን አለቆቻችን አልተገነዘቡትም” አለ፡፡ እውነቱ ይህ ነው፡፡

ነፍሱ በኀጢአት ለሞተችበት ሰው (በድን) አድርግ፤ አታድርግ መቼ ያስፈልገዋል፡፡ መጀመሪያ “አልዓዛር ና ውጣ” የሚል የኢየሱስ ድምፅ ብቻ ያስፈልገዋል፡፡ በእውነትም “ለሙታን ወንጌል ይሰበካል በመቃብር ያሉትም (ኢየሱስን) የሚሰሙበት ሰዓት አሁን ነው፡፡ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ፡፡” የተባለው ተስፋ ሲፈጸም በቅድሚያ ሊታይ ይገባዋል፡፡ በድኑ ሕይወት ከዘራና ከመቃብር ከወጣ በኋላ እንቅስቃሴ ይታይበት ዘንድ፥ “ፍቱት፥ ተዉት ይሂድ” የሚለው ቃል ይከተላል (ዮሐ. 5፥25፤ 11፥43-44፤ ኤፌ. 2፥1-10፤ 1ጴጥ. 4፥6)፡፡

በሥጋ የሞቱ ሰዎች እግዚአብሔር እንዲከብርበት፥ ምእመናን እንዲታነጹበት ፈቃዱ ሲሆን፥ በአገልጋዮቹ የሥጋ ትንሣኤን ያገኛሉ (ሐ.ሥ 9፥36-41፤ 20፥7-12)፡፡ በሥጋ እየተንቀሳቀሱ በመንፈስ ምዉታን ለሆኑት ግን የመንፈስ ትንሣኤን ኢየሱስ ክርስቶስ ካልሆነ በቀር ሌላ ማንም ሊሰጣቸው አይችልም (ዮሐ. 11፥25) አሉና እማሆይ፥ ስለ መዳን የተሰጠው ትምህርት ጠልቆ የተዋሐዳቸው አይመስላችሁምን?

የእግዚብሔር ጸጋ
ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ሲወሳ የጸጋን ትርጉም በትክክል የማይረዱ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ የጸጋን ብሂል ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እንዲህ ተብሎ ቢብራራ ይሻላል፡፡ ጸጋ ማለት የይገባኛል መብት ጥያቄ የማይቀርብበት፥ ተቀባዩ የማይገባው፥ አገኘዋለሁ ብሎ የማይጠብቀው ሆኖ ሳለ፥ ከሰጪው በጐ ፈቃድ የተነሣ እንዲያው በነጻ የተገኘ ስጦታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ የተገለጠባቸውን አራት መንገዶች ወይዘሪት ልዕልት ነቅዐ ጥበብ እንደሚከተለው በአለቃ ነቅዐ ጥበብ ጉባኤ ላይ ገልጻዋለች፡፡

አንደኛ፥ በመፍጠር የተገለጸ ጸጋ
እግዚአብሔር ሰውንም ሆነ ሌሎች ፍጥረታትን ሲፈጥር እንዲሁ ከጸጋው የተነሣ ነው እንጂ ፍጥረታት የመፈጠር መብት ስለ ነበራቸው እንዳልሆነ ስውር አይደለም፡፡ በተለይ ሰውን በመልኩ እንደ ምሳሌው ሲፈጥረው፤ ለእርሱ ጥቅምና አገልግሎት ቀደም ብሎ በተፈጠሩት ፍጥረታት ላይም ሲያሠለጥነው፤ የጸጋውን ሥራ ልናስተውል እንችላለን፡፡ ሰውን በዚህ ደረጃ ከሚያስፈልጉትና ከሚገለገልባቸው ፍጥረታትና ከተሟላ የተፈጥሮ ሥርዐት ጋር ፈጠረው ሲባልም ሰው በዚህ ደረጃ መፈጠር ይገባኛል የምፈጠርም ከሆነ እነዚህና እነዚያ ሁሉ በቅድሚያ ሊሟሉልኝ ይገባል የሚለው ጥያቄ ይነሣል ተብሎ አልነበረም፡፡

ይልቁንም ሰው እንደ ተፈጠረ የተዘጋጀለትን ክብር ቢያጣውም በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገና (ዳግም) በመፈጠር የመለኮታዊ ክብር ተካፋይ መደረጉ ከፍጡሩ የመብት ጥያቄ የማይቀርብበትን የጸጋውን ብዛት፥ ምሉእነትና ታላቅነት አጐልቶ ያሳየናል፤ በምሳሌ ሲገለጽም፡-

ጸጋ + 0 = መፈጠር የተገባው ሰው ሆነ፡፡

ሁለተኛ፥ በመውደድ የተገለጸ ጸጋ
ለክብር በክብር የተፈጠረው ሰው በእግዚአብሔርና በመንግሥቱ ላይ ካመፀው ሰይጣን ጋር በማበሩ በጸጋ ከተሰጠው ክብር ወደቀ፡፡ ይህም ዐመፀኛ ሰው መቀበል ከሚገባው ፍርድ በታች ራሱን ከመተው በቀር የሚጠብቀው ሌላ ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም በቅድስና ደረጃ ያልተገኘውን፥ በኀጢአት የረከሰውን፥ አጸያፊውን ሰው ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር ወደደው፡፡ እንዴት ተብሎ! የሚያሰኝ አስገራሚ ታሪክ ነው፡፡ በቅድስናው ትይዩ ያለው ፍቅሩ ያረፈበት የረከሰው ሰው ነውኮ!! የጸጋው ሽፋን በሰው ላይ ያረፈውን የእግዚአብሔርን ፍቅር መወደድ  በሚገባው ባለውለታ ላይ እንዳረፈ ይቈጥር ዘንድ አስቻለ፡፡ እንደ ኅሊናው እንደ ፈቃዱ እንደ ዕቅዱና ሥራው መወደድ ተገቢው ባልሆነው ፍጡር ላይ ያረፈው መለኮታዊ ፍቅር ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ነው እንጂ የመብት ጥያቄ የማይቀርብበት ዕድል ነበረ፡፡  
ጸጋ + ኀጢአተኛ ሰው = በእግዚአብሔር የተወደደ ኀጢአተኛ ሰው፡፡

ሦስተኛ፥ ወልድን ቤዛ በመስጠት የተገለጸ ጸጋ
ለቅዱስ ባሕርዩ ተመጣጣኝ ያልሆነውንና በኀጢአት የረከሰውን ሰው እግዚአብሔር የወደደው ከጸጋው የተነሣ እንደ ሆነ ከላይ ተመለከትን፡፡ ኀጢአተኛው ሰው በእግዚአብሔር ቢወደድስ ቤዛዬ ነው የሚለውን በማቅረብ የኀጢአት ዕዳውን ክፍሎ ከመታረቅ በቀር ሌላ ምን እንዲሆንለት ወይም እንዲደረግለት መጠበቅ ነበረበት? ቤዛዬን ልስጥ ቢልስ ቤዛው ማንና ምን ሊሆኑ ይችሉ ነበር? እጅግ አስገራሚ የሆነው ሌላው የጸጋው ምስጢር እዚህ ይከሠታል፡፡

የበደለው ሰው እያለ የተበደለው እግዚአብሔር በበደለኛው በሰው በኩል ሆኖ ቤዛ መስጠት ወደደና ያለውን አንድዬውን፥ የአካሉ ምሳሌ፥ የባሕርዩ ነጸብራቅ የመብራትነቱ ብርሃን የሆነውን በቃል ከዊኖቱ (ቃሉ በመሆኑ) ዓለማትን የፈጠረበትን ውድ ልጁን ሰጠን፡፡ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረውን ልጁን ለተፈጠረው ሰው ተለዋጭ (ቤዛ እንዲሆን አሳልፎ ሲሰጠው፥ የሰውና የልጁ ዋጋ እንዴት ተመጣጠነ ቢባል፥ ፍቅር ኪሳራን አይቈጥርምና በዕሴት መመጣጠን ረገድ ስሌት ከግምት ውስጥ እንዳይገባ ጸጋው ሚዛኑን አስተካከለው ወይም ሸፈነው፡፡ ጸጋው ይህን ባያደርግማ ኖሮ በጥቅም ላይ የማይውል ቈሻሻን በዕንቊ የሚለውጥ የትኛው ሞኝ ነው? ወይስ የተፈጠረው በዚያውም ላይ ኀጢአተኛ የሆነው ሰው በአንድዬ ልጅህ ልትቤዠኝ ይገባሃል የሚል የመብት ጥያቄ ለፈጣሪው ማቅረብ ይችል ነበርን?

ጸጋ + የተወደደ ኀጢአተኛ ሰው = ቤዛው (ልዋጩ) ኢየሱስ የሆነ ኀጢአተኛ ሰው፡፡

አራተኛ፥ ለወልድ የቤዛነት ዐዋጅ የሰውን ልብ በማስገዛት የተገለጸ ጸጋ
የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ቤዛ ሆኖ የተገለጸበት ዐዋጅ በመላው ዓለም ለሰው ሁሉ ቢሰበክም፥ በኀጢአት ተፀንሶ በኀጢአት የተወለደ ሰው በኀጢአት ምክንያት ሰይጣን የተቈራኘው ስለ ሆነ፥ ለዐዋጁ የሚታዘዝበት ነጻ ፈቃድ እንደሌለው የታወቀ ነው፡፡ እንደዚህም ሆኖ የነጻነቱ ዐዋጅ በስብከት ሞኝነት እየተቀበሉ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪያ መሰባሰብ የሚገባቸው ናቸው የምንላቸው፥ በሥነ ምግባር በሃይማኖታዊነትና በአእምሮ ንቃት የተሻሉ የሚመስሉ ብዙዎች እያሉ፥ ለእነዚህ ሁኔታዎች ተቃራኒዎች ናቸው የሚባሉና አይገባቸውም የተባሉ ሰዎች በስብከቱ ሞኝነት በኩል ለነጻነቱ ዐዋጅ ልባቸውን ሲያስገዙ መታየታቸው፥ ለተመራማሪዎች እንቈቅልሽ የሚመስል የእግዚአብሔር የጸጋ ሥራው ውጤት ነው፡፡

የሰዎች ሁሉ ቤዛ ሆኖ በሞተውና ሊያጸድቃቸውም በተነሣው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚሰበከውን የወንጌሉን የስብከት ሞኝነት የሰሙ፡-
ሀ. ብዙዎች ዐዋቂዎች የዕውቀትንና የጥበብን መስፈርት አያሟላም፤ ስንፍና ነው እያሉ ሲንቁት፥ ጥቂቶች ይህስ የዕውቀትና የጥበብ ራስ ነው በማለት በአድናቆትና በምስጋና ይቀበሉታል፡፡
ለ. ብዙዎች ሃይማኖተኞችና የሥነ ምግባር ሰዎች ነን ባዮች እንደኛ ላሉ በሥነ ምግባር ለተለበጡ፥ በሰዎች ዘንድ በመዓርገ ማዕርጋት ላይ ለተቀመጡ የሚሆን አይደለም፤ ተስፋ ቢስ ለሆኑ ምስኪኖች እንጂ እያሉ ያጥላሉታል፡፡ ዳሩ ግን ከመካከላቸው ጥቂቶቹ በሰው ዘንድ ረብ የሚያስገኘውን ፈሪሳዊነታቸውን በቀራንዮ መስቀል ላይ በተቸነከረው በኢየሱስ ክርስቶስ ሚዛን ሲመዝኑት እንደ ነበረ እንኳ የማይቈጠር ነፋስን እንደ መዝገን ያለ መሆኑን ይረዱና በመስቀሉ እግርጌ ራሳቸውን በመጣል ክብራቸውንና እኔነታቸውን ይቀብራሉ፡፡ በለውጡም በትንሣኤው ኀይል ታድሰው ይነሣሉ፡፡

ዳዊት፥ “ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፤ ርስቴም ተዋበችልኝ” (መዝ. (16)፥5-6) በማለት እንደ ተቀኘው ስለ ሆነላቸው በምስጋና ይሞላሉ፡፡ “ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ዘገብረ ዐቢየ ወመንክረ ባሕቲቱ፥ ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ ይባረክ” እያሉ በውዳሴ፥ በሽብሸባ፥ በእልልታ፥ በሃሌታ ያመሰግናሉ፤ አምላካቸውን ይባርካሉ፤ የተዘጋውን ማኅተም የፈታላቸውን ባለፈው ዘመናቸው ሳያዩት ቀርተው ሲያለቅሱ የነበሩበትን፥ አሁን ግን በዙፋኑ መካከል ያለውን ማኅተሙን የፈታውን የታረደውን በግ ሲወድሱ፥ ከተኣምራት ሁሉ የላቀ ተኣምር፥ ከመንክራት ሁሉ የበለጠ መንክር የሆነውን የነፍሳቸውን መዳን እያሰቡ፥ ከመላእክት ጋር ዝማሬያቸውን በማስማማት ድምፃቸውን በማስተካከልና ሽብሸባቸውን በማዋሐድ ለታረደው በግ በረከት፥ ክብር፥ ምስጋናም፥ ኀይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን ይላሉ (ራእ 5፥13-14)፡፡

በዕውቀትና ባሃይማኖታዊነት ጥረት ለረጅም ጊዜ በተሞከረ ልምምድ ያልተገኘ የሕይወት ለውጥ፥ በእነዚህ አመስጋኝ ክርስቲያኖች መታየቱ እንቈቅልሹን እንደ ገና አያ ድቡልቡሌ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም የጸጋው ሥራ ውጤት ብቻ መሆኑን ሰዎች ሳያስተውሉ ቢያልፉት ስንፍና ነው፡፡ በምሳሌ ቢገለጽ፦

ጸጋ + ቤዛው ኢየሱስ የሆነ ሰው = አምኖ የዳነ ሰው
የሰው መዳን ከመነሻው ጀምሮ አስከ መጨረሻው ድረስ ለትምክሕት የሚያበቃ የነጥብ ቍርጥራጭ ያህል እንኳ ሰብኣዊ ፈቃድ፥ ችሎታና ጥረት ያልታከለበት መቶ በመቶ (100%) የእግዚአብሔር የጸጋ ሥራ ውጤት ስለ ሆነ፥ ስለ ሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን ከማለት በቀር ሌላ ምን ይባላል!!

ምሉአ ጸጋ ወጽድቅ (ጸጋንና እውነትን የተሞላውን) ኢየሱስ ክርስቶስን ከተቀበልን በኋላማ ጸጋን በጸጋ ላይ ደርቦና ደራርቦ አፈሰሰልን (ዮሐ. 1፥16) የጌታ ስም ብሩክ ይሁን አለችና ልዕልት ደመደመች፡፡

አንባብያን እናንተስ እስካሁን ከተሰጠው የመዳን ትምህርት ምን እንደ ተገነዘባችሁ ራሳችሁ ራሳችሁን ገምግሙ፡፡ እንደ እማሆይ ኤልሳቤጥና ወይዘሪት ልዕልት ጻፉልን ማለታችን ግን አይደለም፡፡

ጸጋ ሲደመር ዜሮ (ጸጋ + 0 ) ይሆናል መፈጠር የተገባው ሰው፡፡
ጸጋ ሲደመር ኀጢአተኛ ሰው ይሆናል በእግዚአብሔር የተወደደ ኀጢአተኛ ሰው፡፡
ጸጋ ሲደመር በእግዚአብሔር የተወደደ ኀጢአተኛ ሰው ይሆናል ኢየሱስ ቤዛ የሆነለት ኀጢአተኛ ሰው፡፡
ጸጋ ሲደመር ኢየሱስ ቤዛ የሆነለት ኀጢአተኛ ሰው ይሆናል በኢየሱስ አምኖ የዳነ ሰው፡፡


በጮራ ቍጥር 8 ላይ የቀረበ

2 comments:

  1. 1 welde gebirael tebiye bitera ye geta melak tasebe enji yetemekut yetsega lijinent yagegnhut be fetari sim new.2.geta bedemu silegezagn waga siletkefelelign bewirs hatyat aliteyekim.3.sew silehoku be hatyat biwedik benisiha emelesalehu .be siga wedemu etatemalehu. 4 debir ledebir bizor bereket agegnibetalehu hulum yesu maderya nachewna.5eletati bekidusanina be senibet biseyemuna metasebiya bideregu bereket agegnibetalehu be eyeletu ke hayimanot guadegnoche gar lemgenagntina sile egizabeher kal endininegager mikiniyat yihonegnal.yetsadik metasebiya le bereket new yilalina .atimetsadek yekomik kemeseleh litiewdik tichilaleh . yenakachew be nisha litatebu yichilalu.kidusan bota mehed tibarkibetalh

    ReplyDelete
  2. menafik atawetawim neber asiteyayeten

    ReplyDelete