Sunday, December 30, 2012

መሠረተ እምነት

Read in PDF
(በጮራ ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)
         ከናሁ አዳም
(ካለፈው የቀጠለ)

ባለፈው ዕትም (ጮራ ቍጥር 3 ገጽ 18-20) ይሆዋ በአካል ሦስት መሆኑን፥ እያንዳንዱም አካላዊ መንፈስ በራሱ “የሠራዊት ጌታ ይሆዋ” ተብሎ የመጠራትና የመመለክ ባለመብት እንደ ሆነ፥ የብሉይ ኪዳን አባቶች ተረድተው የነበረ መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል ማለት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አንብበን ከሐዲስ ኪዳንም ጋር አመሳክረን እንደ ነበረ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዕትምም ከዚያው በመቀጠል የሚከተሉት ነጥቦች በሐዲስ ኪዳን ትምህርት እንመርምራቸው፡፡

ነጥብ (ጭብጥ) ሦስት
ከሥላሴ እያንዳንዱ አካል የባሕርይ ምሉዕነትና የህላዌ (አኗኗር) ፍጹምነት አለው፤ ለሥራውም በባለቤትነት ይታወቃል፡፡

Wednesday, December 26, 2012

ክርስትና በኢትዮጵያ

Read in PDF
(በጮራ ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)

የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

 (ካለፈው የቀጠለ)

አምልኮት በኢትዮጵያ

ጥንታዊው የኢትዮጵያውያን አምልኮት በተመሳሳይ ጊዜ በሌላው የዓለም ክፍል ከነበረበት የአምልኮት ታሪክ መሠረታዊ ልዩነት የለውም፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም በሌላው የዓለም ክፍል እንደ ነበረው ሁሉ ዐይነቱ ብዙ ቢሆንም አያስደንቅም፡፡ የአምልኮቱ ዐይነት መብዛትና መለያየት ከነገዶቹ ዝርያ ጐሣዎች መብዛት፥ ከገቡበትም አቅጣጫና ጊዜ መለያየት የተነሣ ነው ቢባል ለእውነት የቀረበ ይሆናል፡፡

በቤት እንስሳት፥ በአራዊት፥ በአዕዋፍ፥ በኰረብታ፥ በሐይቅ በወራጅ ውሃ፥ በሚሳቡ ፍጥረታት (የእባብ ዐይነቶች)፥ በዛፎች፥ በድንጋዮች… የማምለክ ልምድ የነገደ ካም ዝርያዎች ትውፊት ነበር ይባላል፡፡ የነገደ ካም ዝርያዎች በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ያዩዋቸውን፥ ለኑሮአቸው ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸውንና እንደ ብርቅ ድንቅም የቈጠሯቸውን፥ ማለት ወይ በጠቃሚነታቸው፥ ወይ በእንቅስቃሴአቸው፥ ወይ በአቋማቸው ወዘተ. ስሜታቸውን የማረኳቸውን ተንቀሳቃሽና ኢተንቀሳቃሽ ፍጥረታትን ያመልኩ ነበረ የሚለውን ትረካ ከተቀበልን፥ በዚያን ጊዜ ሐሳባቸው ገና በአካባቢያቸው ውሱንና ትኲረታቸውም ካፍንጫቸው ሥር ብዙ ያልራቀ እንደ ነበረ የግምት ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል፡፡

Friday, December 21, 2012

ፍካሬ መጻሕፍት

Read IN PDF
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 44 ላይ የቀረበ)

“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ
በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአፅምኢ እዝነኪ”
“በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።
ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ” (መዝ. 44/45፥9-10)

ይህን የመዝሙረ ዳዊት ጥቅስ በሚያነብብ በአብዛኛው ሰው አእምሮ ውስጥ በቶሎ የምትከሠተው ድንግል ማርያም ናት። ይህ የሆነው ጥቅሱ ስለ እርሷ የተነገረ ስለ ሆነ ግን አይደለም። ስለ እርሷ የተነገረ ነው ተብሎ ስለ ተወሰደ፥ በተደጋጋሚ ከእርሷ ጋር ተያይዞ ስለ ተነገረ፥ በየወሩ በ21 ለበዓለ ማርያም የሚዜም ምስባክ ስለ ሆነ ነው ስለ እርሷ የተነገረ ያህል እየተሰማን የመጣው። ቅድስት ድንግል ማርያምን ንግሥተ ሰማይ ወምድር ብለው የሚያምኑ ክፍሎች፥ ሐሳባቸውን በዚህ ጥቅስ ለማስደገፍ ይሞክራሉ። እርሷን በንጉሥ እግዚአብሔር ቀኝ እንደ ተቀመጠች ንግሥትም ይቈጥሯታል።

ቃሉ ስለ ማን እንደ ተነገረ ከመጽሐፉ ተነሥተን እንመልክት። ጥቅሱ ለሚገኝበት ለዚህ የመዝሙረ ዳዊት ክፍል የዐማርኛው የ1953ቱ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስ “ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት፤ የፍቅር መዝሙር” የሚል ርእስ ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ባሳተመችው የ2 ሺሁ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስም “ለመዘምራን አለቃ በመለከቶች የቆሬ ልጆች ትምህርት የፍቅር መዝሙር” በማለት ይህንኑ ርእስ ነው ያስቀመጠው።

Tuesday, December 18, 2012

ማስታወቂያ

Read in PDF
ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 44 ለንባብ በቅቷል
*   መሠረተ እምነት
ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ በኋላ እርሱን ተክተው በክህነት እንዲያገለግሉ የሾማቸው ካህናት አሉን? በሚል ርእስ በተዘጋጀው ጽሑፍ አየሱስን ወክለው የተሾሙ ካህናት አሉ የሚሉ ወገኖችን በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይሞግታል፡፡
*   የዘመን ምስክር
የዚህ ዕትም የዘመን ምስክር ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ናቸው፡፡ ለአገርና ለወገን ያፈለቋቸው ተራማጅ ሐሳቦች ተዳስሰዋል፡፡ ስለ ሃይማኖት ነጻነት ከተናገሩት መካከል የሚከተለው ይገኛል፥ “… ባገራችን አንድ የድንቊርና ነገር አለ፡፡ ሃይማኖቱ ተዋሕዶ ያልሆነ ሰው ሁሉ እንደ ርኩስ ይቈጠራል፡፡ ይህም እጅግ ያሥቃል፡፡ አእምሮ የሌለው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳያውቅ የእግዚአብሔር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል፡፡”

*   ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
በዚህ ዐምድ ሥር ለሁለት ጥያቄዎች ምላሸ ተሰጥቷል፡፡ አንደኛው ጥያቄ መልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊ ነወይ? የሚል ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ “አንዳንድ አጋንንትን እናስወጣለን የሚሉ ሰዎች ግን በኢየሱስ ስም ብቻ ሳይሆን በጻድቃንና በሰማዕታት ስም እናስወጣለን ይላሉ። በተጨማሪ አጋንንቱ ካደሩበት ሰው ጋር ትግል መግጠም፥ ሰውዮውን በመቊጠሪያ፥ በጧፍ፥ በመስቀል ወዘተ. መደብደብና የመሳሰሉ ድርጊቶችን ይፈጸማሉ። እነዚህንም ድርጊቶች በሲዲ እያሠራጩ ከክርስትና ትምህርት ውጪ የሆኑ ልምምዶችን ያስፋፋሉ። እውን እነዚህ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸውን?”
*  ታላላቅ መንፈሳውያን ቃላት
ስለ ዐዲስ ልደት ምንነት ትምህርት ያገኛሉ፡፡
*  ፍካሬ መጻሕፍት
“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ” ለሚለው ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ሌሎችም ጽሑፎች ተካተዋልና ጮራን ያንብቡ፡፡ ሌሎችም እንዲያነቡ በማድረግ መንፈሳዊ አደራዎን ይወጡ፡፡

Sunday, December 9, 2012

ጋብቻ

የጋብቻ መሥዋዕትነት
በዝግጅት ክፍሉ
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)

መግቢያ

ጋብቻ እግዚአብሔር በባልና በሚስት መካከል የሚገኝበት ቅንጅት ሲሆን፥ በቅንጅቱም ባልና ሚስት ፊት ለፊት ተያይተው ልባዊ መግባባት እንደሚኖራቸው በመጀመሪያው ጹሑፋችን ገልጸናል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የጋብቻ ቅንጅት እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዲሆን፥ በጋብቻ ውስጥ ያለውን አባወራነትና የሁለቱንም የተለያየ ኀላፊነት እንዴት እንደሚያብራራ ተመልክተናል፡፡ ይኸውም “የሴት ራስ ወንድ እንደ ሆነ” በእግዚአብሔር አብና በክርስቶስ መካከል ባለው አባወራነት ላይ ማለትም “የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው” በሚለው የተመሠረተ መሆኑን አይተናል፡፡ ይህም ለባልና ለሚስት ምን ማለት እንደ ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ገልጸናል፡፡ በመጨረሻም ጋብቻችን እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዲሆንና በሕይወታችን እንዲገለጽ አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠይቀናል፡፡

በዚህ በሦስተኛው ጽሑፋችን ጋብቻን በተመለከተ ስለ ሌላ መሠረታዊ ሐቅ እግዚአብሔር ወደሚያስተምረን ወደ ዔደን ገነት እንመለስ፥ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡” በጋብቻ ውስጥ የእርስ በርስ መቈራኘት መኖሩ (ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ)፤ ጥቅሱም ቊርኝቱ መሥዋዕትነትን እንደሚጠይቅ (ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል) ያስተምረናል፡፡ ሁኔታው በሴት አፈጣጠር ይታያል፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከአዳም ጐን አንድ አጥንት ወስዶ ሴቲቱን ፈጠረ፤ ሴት የተገኘችው በአዳም “መሥዋዕትነት” ነበረ፡፡ ከዚህም በኋላ አዳም ሙሉ ሰው ሊሆን የሚችለው ከሚስቱ ጋር አንድ ሲሆን ብቻ ነበር፡፡ አዳምም “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት” በማለቱ በጋብቻ ውስጥ ያለውን የርክክብና የመሥዋዕትነት ሁኔታ እንደ ተረዳ እናስተውላለን፡፡ የጋብቻ ቅንጅት የተቀደሰ ነውና በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ቅዱስ ግንኙነት እንደሚያመለክት ሐዋርያው ጳውሎስ ያስረዳናል፡፡ ጋብቻ የትርፍ ወይም የፌዝ ነገር ሳይሆን መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ የርስ በርስ ርክክብ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡

Friday, November 9, 2012

የመዳን ትምህርት

Read in PDF

                                                            (በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)

“እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ … ማን ያድነኛል? …” (ሮሜ 7፥24)
ካለፈው የቀጠለ

ባለፈው ዕትም የሰው አፈጣጠር እንከን አልባ እንደ ነበር ከእግዚአብሔር ቃል ማንበባችንን እናስታውሳለን፡፡ ግሩምና ድንቅ ለተባለ የውስጥና የውጭ ውበት ባለቤት ሆኖ የተፈጠረው ሰው፥ “እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ . . . ማን ያድነኛል?” እንዲል ያስገደደው ብልሹነት እንዴትና ከየት መጣበት የሚለው ጥያቄ በዛሬው ዕትም ይመለሳል።

የሰው ተፈጥሮ መበላሸት ከየት መጣ?

          “ሕያው ነፍስ” ያሰኘውን የሕይወት እስትንፋስ ከሕያው አምላክ በመቀበሉ እግዚአብሔርን መስሎና ከማንኛውም ፍጥረት በልጦ እንከን አልባ የሆነው ሰው አንድ ቀን በእባብ እንደ ተጐበኘ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።

Monday, September 17, 2012

ርእሰ አንቀጽ

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 4 ላይ የቀረበ
ይቅር ባይነት እንማር

ሰዎች የምንባል ሁሉ በልዩ ልዩ አገርና ስፍራ የተወለድን ከልዩ ልዩ የሰው ዝርያ (ነገድ) የተገኘን እንደ መሆናችን መጠን በቋንቋ በአኗኗር፥ በአመጋገብ፥ በአለባበስ፥ በአስተሳሰብ በአጠቃላይ በባህል፥ በሙያና በመልክ ቀለም መለያየታችን የታወቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በመካከላችን ከሚታዩት ጥቃቅን ልዩነቶች ይልቅ ሁላችን አንድ የምንሆንበትና የምንመሳሰልበት ነገር ጒልህ ሆኖ የሚታይ መሆኑን ማስታወስ አለብን፡፡

በተለይ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አንድነታችንን ለመጠበቅ፥ የተጣለብንን አደራና ዓላማ ያለውን ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን በሚገባ ከግቡ ለማድረስ እንድንችል በብዙ ሜዳዊ ልዩነቶች መካከል የምንመሳሰልባቸውንና አንድ የሚያደርጉንን ቁም ነገሮች መገንዘብም ማሰላሰልም ያስፈልገናል፡፡

Saturday, August 18, 2012

ጸሎት


(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ)


“ጌታ ሆይ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን፡፡” (ሉቃ. 11፥1)

ከክርስትና ሕይወታችን አብዛኛው ክፍል የሚያዘው በጸሎት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ያለመታከት መጸለይ እንዲገባን የእግዚአብሔር ቃል ይመክረናል (ሉቃ. 18፥1-7)፡፡

ኑሮአችን በጥያቄና በችግር የተሞላ ስለሆነና ሁል ጊዜ የምንቀበለው ስለሚበዛ፥ ያለ ጸሎት ልንኖር አንችልም፡፡ ትንሽ ልጅ ሲርበው፤ ቊርሱን ምሳውን፥ እራቱን፤ ሲበርደው ልብሱን፥ መጠለያውን ይጠይቃል፡፡ ሲታመም ይቅበጠበጣል፥ ያለቅሳል፡፡ እንቅፋት ቢመታው፥ እሾኽ ቢወጋው፥ የጎረቤት ልጅ ቢያጠቃውና በእድገቱ ሂደት የሚያጋጥሙትን ዐዳዲስ ነገሮች ሁሉ የማወቅ ጥማቱን ለማርካት ጥያቄዎችን ይደረድራል፡፡ ትናንት ጠይቆ በተቀበለው ተጠቅሟል፥ አመስግኗልም፡፡ ሆኖም ትናንት ዐልፎአልና ዛሬ ለዐዲስ ጥያቄ ዐዲስ ምላሽ ይጠብቃል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቲያንም በዚህ ተመሳሳይ ምክንያት ጸሎትን ማቋረጥ አይችልም፤ አያስታጕልም፡፡

Monday, August 13, 2012

ግጥም

Read in PDF
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ)
                                        
                                        የትግል ምዕራፍ

በቀጭኑ መንገድ ሰዎች ባልበዙበት
መሰናክልና እንቅፋት ባለበት
ጀምረህ እንደ ሆን አቅንትህ መራመድ
ወደ ኋላ ሳትል ወደ ፊትህ ንጐድ፡፡

ጒዞህን ጀምረህ ጥቂት ዕልፍ ስትል
አለልህ እንቅፋት የሚጥር ለመጣል፡፡

አለልህ እርግጫ  አለልህ ኲርኲሙ
ሊጥልህ ይታገላል ሁሉም እንዳቅሙ፡፡

እርሱን ዐለፍ ብለህ በሥቃይ እንዳለህ
እምነት እሚፈታ ተራራ ታያለህ፡፡

ይህን ሁሉ ዐልፈህ መንገዱ ወለል ሲል
የመረረው ጒዞ ሲተካልህ በድል
ምዕራፉ ሲዘጋ ግፊውም ያከትማል፡፡

Sunday, August 5, 2012

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 43 ላይ የቀረበ
ትረካ፥ ከነቅዐ ጥበብ
በገጽ ጥበት ምክንያት በጮራ ቊጥር 42 ላይ የዚህ ዐምድ ጽሑፍ አልቀረበም ነበር። አንባቢ እንደሚያስታውሰው በቊጥር 41 ላይ ወጥቶ የነበረውንና በማኅበረ ቀናዕያንና በደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት የተደረገውን ጉባኤ የተመለከተውን ዘገባ የመጀመሪያ ክፍል፥ በጮራ ቊጥር 41 ላይ አውጥተን ነበር። የዚያን ጽሑፍ ተከታይ እነሆ!

በመርሐ ግብሩ መሠረት ማኅበረ ቀናዕያንን በመወከል ዲያቆን በለው፥ ደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅን ወክሎ ደግሞ ደቀ መዝሙር በቃሉ በየተራና በመደማመጥ ሐሳባቸውን ካስተላለፉ በኋላ፥ በቀረቡት ሁለት ተቃራኒ ሐሳቦች ዙሪያ ታዳሚው አስተያየት እንዲሰጥ የመድረክ መሪው መጋቤ ወንጌል ኅሩይ እምአእላፍ ታዳሚውን ጋበዙ። የመናገር ዕድሉን ለማግኘት በርካታ እጆች ወጡ። ሁሉም ዐጠር ዐጠር አድርገው ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ተደረገ። ሁለቱንም ወገኖች ደግፈውና ተቃውመው አስታያየቶች የሰጡ ነበሩ። ሁለቱን ከመደገፍም ከመቃወምም ርቀው ሚዛናዊ አስተያየት የሰጡም ነበሩ። እኛም ይጠቅማሉ ካልናቸው አስተያየቶች መካከል ጥቂቶቹን ከዚህ ቀጥሎ እናቀርባለን። በመጨረሻም አለቃ ነቅዐ ጥበብ የሰጡትን ሐሳብ በማካተት ዘገባችንን እናጠቃልላለን።

Monday, July 30, 2012

የጋብቻ አባወራነት

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
መግቢያ፡-
የጋብቻ ቅንጅት” በተባለው በአንደኛ ጽሑፋችን በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተገለጠው የጋብቻ ቅንጅት እግዚአብሔር በሁለት ባልና ሚስት መካከል የሚገኝበት ቅንጅት ነው፡፡ በቅንጅቱም ባልና ሚስት ፊት ለፊት ተያይተው የልብ መግባባት እንደሚኖራቸው ተመልክተናል፡፡ በአንድ በኩል የባልና ሚስት እኩልነት እግዚአብሔር እነርሱን በመፍጠሩና በመውደዱ ለክብሩ እንዲኖሩ በዓለም በማስቀመጡ ተገልጾአል፡፡ በሌላ በኩል ግን በጋብቻ ውስጥ የሁለቱንም ኀላፊነት ስንመለከት ጐላ ያለ ልዩነት ይታያል፡፡ በመካከላቸው ያለው የፍቅር ግንኙት እንደ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዲሠራ ባልና ሚስት በፈጣሪያቸው ከመጀመሪያ በጋብቻ ውስጥ የተፈጠረውን መሠረታዊ ልዩነት እንዲያስተውሉ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ በጋብቻ ውስጥ ያለው አባወራነት ይህን ልዩነት እንዴት እንደሚያብራራ አሁን ልንመለከት እንችላለን፡፡

የአባወራነት ሕግ
የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ይህ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃል ሊያስደነግጠን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ቃል የሚያመለክተን አባወራነት የተጀመረው በዔድን ገነት ውስጥ ሳይሆን ከዘላለም በሥላሴ ዘንድ ነው፡፡ እኛም ስለ ሥላሴ ስንናገር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን እንጂ ወልድ አብ መንፈስ ቅዱስ አንልም፡፡ በመለኮታዊ ባሕርይ አንድና እኩል ሲሆኑ በተግባራቸው የሚገለጥና በአባወራነት የተመሠረተ ቅደም ተከተል አላቸው፡፡ በምድራዊ አባትና ልጅ መካከል ያለውን ያንጸባርቃል፡፡  

Sunday, July 22, 2012

“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ … ማን ያድነኛል?” (ሮሜ 7፥24)

                 Read IN PDF                                                              (በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ)
ካለፈው የቀጠለ
እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሲመለከት ጻድቅ የሆነ አንድ ሰው ስንኳ ከመካከላችን እንዳልተገኘ፥ ኀጢአት ያልተመረተበት የሰውነት ክፍልም በእያንዳንዳችን እንደ ሌለ የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ባለፈው ዕትም ተመልክተናል (መዝ. 13፥1-3)። የዛሬው ዕትም ደግሞ ሰው መበላሸት ከመፈጠሩ ጀምሮ እንዳልሆነ ያስነብበናል።

የሰው አፈጣጠር እንዴት ነበር?

መቼም እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም እንደ ነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በቅድሚያ ያረጋግጥልናል (ዘፍ. 1፥4፡10፡12፡18፡21፡25፡31)።

እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነበረ ሲባል፥ መልካም ከነበረው ፍጥረት አንዱ ሰው እንደ ሆነ ግልጽ ነው። እንዲያውም “መልካም” የሚል ገደብ የተበጀለትን የየዕለቱን ፍጥረት መመዘኛ በማለፍ “እጅግ መልካም” የሚል እመርታን የሚያሳይ ዐዲስ የመመዘኛ ወሰን የተገኘው ሰው ከተፈጠረና የፍጥረት ገዥ ሆኖ ከተቀመጠ በኋላ ነበር (ዘፍ. 1፥31)።

Thursday, July 19, 2012

ልዩ ልዩ





በመሠረተ እምነት
ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሰጡትን ምስክርነት በመልክ በመልኩ በማቅረብ አንዳንዶች ዛሬ ቢያስተባብሉትም፥ የክርስቶስ መካከለኛነት ግን በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የታወቀ መሆኑን ያስረዳል፡፡


የዘመን ምስክር
የቀደሙ አባቶቻችን የሠሩትን መልካም ሥራና ያሳዩትን በጎ አርኣያነት የሚዘክረው ይህ ዐምድ፥ የአባ እስጢፋኖስንና የደቂቀ አስጢፋኖስን የተጋድሎ ታሪክ፥ በዚህ ዘመን እየተነሡ ካሉ አከራካሪ ጉዳዮች ጋር በማዋሐድ፥ ስለወንጌልና በምድራችን እንዲመጣ ይፈልጉት ስለነበረው ተሐድሶ ያለፉበትን መንገድ ያስቃኛል፡፡

Friday, June 1, 2012

ጋብቻ

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ

የጋብቻ ቅንጅት

መግቢያ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና ስለ ሰው ልጆች የቅርብ ግንኙነት ሰፋ ባለ ሁኔታ አብራርቶ ያሳየናል፡፡ በመጀመሪያ የነበረው ይህ ግንኙነት የሰው ልጅ ፈጣሪውን እስከ በደለበት ወቅት መልካም ነበር፡፡ ሆኖም ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፎ በኀጢአት በመውደቁ ግንኙነቱ ተበላሸ፡፡ ምንም እንኳ የሰው ልጅ በኀጢአት ቢወድቅም፥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የነበረውን ግንኙነት እንደ ገና ዐድሶታል፡፡ በተጨማሪም ይህ የእግዚአብሔር ቃል በወንድና በሴት መካከል የነበረውን የቅርብ ግንኙነት የሚያስረዳ ሲሆን፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ የጋብቻን ክቡርነትና የበላይነት በሰፊው ዘግቦ ይገኛል፡፡ ይህም ከዘላለም የነበረው የእግዚአብሔር አሠራርና ባሕርይ አሁንም ያልተለወጠ በመሆኑና ቀደም ሲልም በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ የሚገኘው የሰው ልጆች የሕይወት ታሪክ በአሁኑ ወቅት ላለነው ለእኛ ለየት ያለ ቢሆንም መልካም ትምህርት ይሰጠናል፡፡


የመጀመሪያ ጋብቻ
ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ሲገለጥ ለተከታዮቹ መመሪያና ትምህርት የያዘ ስለ ሆነ በይበልጥ ልብ ልናደርገው ይገባናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለመጀመሪያው የጋብቻ ሁኔታ ትኲረት ሰጥተን ሰፋ ባለ ሁኔታ እንመለከተዋለን፡፡ እግዚአብሔር በወንድና በሴት መካከል ስላለው የጋብቻ ሁኔታና ዓላማ እንዴት እንዲሚያስብ በእግዚአብሔር ቃል በግልጥ ይታያል፡፡

Wednesday, May 2, 2012

ልዩ ልዩ


Read in PDF 
በጮራ ቊጥር 3 ላይ የቀረበ

ለፈገግታ



ገበሬው ባለው አንድ በሬ ከሌሎችም አቀናጅቶ ማረሱ ከፍተኛ ችግር ይፈጥርበትና ያንን ሸጦ ሁለት መለስተኛ በሬዎችን መግዛት ይፈልጋል፡፡ በሬው ለዐይን ሞላ ብሎ ጥሩ ዋጋ እንዲያወጣለት በማሰብ ጭድ በገፍ ሲያበላው ይሰነብትና ለገበያ ያቀርበዋል፡፡ 

በሬውን ሊገዛ የመጣ ነጋዴም የበሬው አቋም ከሩቅ ይስበውና ጠጋ ብሎ ተዟዙሮ በደንብ ይመለከተዋል፤ በመጨረሻም ከወደ ሆዱ ጐሸም እያደረገ፤ «ባለ ጭድ ዋጋውስ?» ይለዋል በሽሙጥ፡፡ 

ነገሩ የገባው ገበሬም «ለጠንቋይ አይሸጥም» በማለት አጸፋውን መለሰለት ይባላል፡፡

Monday, April 23, 2012

በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

 Read PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበና ካለፈው የቀጠለ

የፊደልና ሥነ ጽሑፍ ልደትና እድገት

ቀደምት ነዋሪዎች የነበሩት የነገደ ኩሽ ዝርያዎች በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች ለረጅም ጊዜ የኖሩ መሆኑ ሲረጋገጥ፥ ለሰው ዝርያ መኖሪያ በመሆን ሀገሪቱን የቀዳሚነት ደረጃ እንድትይዝ ያደረጓት መሆኑም ሲታወቅ፥ ተመራማሪዎች የእነዚህን ነገዶች ነባር ሥልጣኔ ፈልፍሎ በማውጣት ወደ ብርሃን አላመጡትም፡፡ ስለ ሆነም ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሳባዊ ሥልጣኔ ይቀድማል ተብሎ የሚታመነው የነገደ ኩሽ ኢትዮጵያውያን ፊደልና ሥነ ጽሑፍ ተገኝቶ ለንባብ አለ መብቃቱ ያሳዝናል፡፡ ወደ ፊት ዋሻዎች የኰረብታዎችና ሸለቆዎች ከርሠ ምድር ሲመረመሩ የሚገኘውን ውጤት በተስፋ እንጠባበቃለን፡፡

አሁን ግን በኢትዮጵያ የሳባዊውን ፊደል ታሪክ እንመለከታለን፡፡ ከዚህም ተያይዞ ከሳባውያን ፊደል የተወረሰውንና የተሻሻለውን የግእዝን ፊደል ልደትን እድገት እናነባለን፡፡

Saturday, March 31, 2012

በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

                                                             በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
PDF:በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

በቊጥር 2 የጮራ ዕትም እንደ ተገለጸው፥ የዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን “ኩሽ” ሲል ከካም ልጆች አንዱ የሆነው የኩሽ ነገድ በባለቤትነት ለሰፈሩባት የመሬት ክልልና ለነዋሪዎችዋ ለራሳቸው የሰጠው ስም እንደ ሆነ አንብበናል። ብሉይ ኪዳንን ወደ ጽርእ የተረጐሙት ሊቃውንት ኩሽ የሚለውን ቃል “ጥቊር” የሚያሰኝ ትርጕም እንዲኖረው “ኢትዮጵያ” በሚለው ጽርኣዊ ቃል መተርጐማቸውን ተረድተናል። ሰባ (ሰብዓ) ሊቃውንት የነገደ ኩሽ ጥቊረት የመጣው በሚኖሩበት ምድረ በዳ ካለው የፀሓይ ሐሩር መሆኑን ለመግለጽ ሲሉ፥ ነዋሪዎቹን ብቻ ሳይሆን መኖሪያ አገራቸውን ጭምር ኢትዮጵያ ማለታቸው፥ እንዲሁም በዕብራይስጡ የምድረ በዳ ትርጕም ያለውን ቃል ኢትዮጵያ እያሉ ወደ ጽርእ መመለሳቸው ለቃሉ የነበራቸውን ፅንሰ ሐሳብ እንደሚያመለክት የተሰጠውን ግምገማ ተረድተናል።

ከዚህም በመነሣትና በማያያዝ ኢትዮጵያ፥ የዛሬዪቱ ሱዳን (የቀድሞዪቱ ኑብያ) እና ግብጽ እርስ-በርስ የተገዛዙበት ጊዜ መኖሩን ከግምት በማስገባት፥
አንደኛ ለስሙ በዋና ባለቤትነት የምትታወቀው የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ፥
ሁለተኛ በዐረብኛ ጥቊር የማለትን ትርጕም የያዘችው ሱዳን (የቀድሞ ኑብያ-ኢትዮጵያ)፥
ሦስተኛ የኩሽ ወንድም የሚጽራይም አገር የሆነችው ምስር (ግብጽ)፥

በወልም ሆነ በየግል ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ሲጠሩበት እንደ ነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ጥቅሶችን በየተስማሚ ክፍሉ ማንበባችንን እናስታውሳለን።

Tuesday, March 20, 2012

መሠረተ እምነት

በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
(ካለፈው የቀጠለ)

በአንድ ይሆዋ ከሁለት በላይ የሆኑ አካላት እንዳሉ የሚገልጹትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ያውም ከብሉይ ኪዳን የመጀመሪው መጽሐፍ አንድ ባንድ መመልከታችንን እናስታውሳለን፡፡ በዚሁ ሁኔታ ጥናታችንን በመቀጠል የብሉይ ኪዳን አባቶች ይሆዋ በአካል ከሦስት እንደማይበልጥና እንደማያንስ አረጋግጠው እንደ ነበረ የዛሬው ዕትም ያስነብበናል፡፡

ነጥብ (ጭብጥ) ሁለት

በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ አባቶች ይሆዋ በአካል ሦስት መሆኑን ተምረው አስተምረዋል፡፡


Monday, March 12, 2012

አለቃ ነቅዐ ጥበብና ቤተሰባቸው

 Read PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
ጭውውት
አለቃ ነቅዐ ጥበብና ቤተሰባቸው


ከቊርስ በኋላ፥ ጊዜው በግምት ሦስት ሰዓት ይሆናል፡፡
“እነዚህ ልጆች ዛሬም ወደ ዕርሻ ሄደው አይሠሩም ማለት ነው?” አሉ ወይዘሮ ትደነቂያለሽ ጦቢያው፡፡
“ነገ ይሰማራሉ፤ ዛሬ እኔ የትም ስለማልሄድ እነርሱም እቤት ውለው ቢያጠኑ ይሻላል፡፡” አሉ አለቃ ነቅዐ ጥበብ የምሩ፡፡ ወዲያውም በማከታተል ተጣሩ፡፡ “ግሩም፣ አንተነህ፣ ልዕልት!” አሉ፡፡

“አቤት፥ አቤት!” አሉ፥ ሁሉም በየተራ፡፡

“ኑ፥ ወንበራችሁን ዘርጉና ቀጽሉ፡፡ እስካሁን ምን እየሠራችሁ ነው?” በጥያቄ የተዘጋ፥ ግን መልስ የማይሻ ኮስታራ ትእዛዝ ነበረ፡፡
እነግሩም እየተቻኰሉ ወደ አባታቸው ሲሄዱ፥

“የወንዶቹስ ይሁን፥ መቼም አሁን የሴቷ ልጅ ትምህርት ምን ይባላል? ዳዊት ከደገመች መቼ አነሳትና ነው፤ አትቀድስ፥ አትሠልስ፤ መጣፍ፥ ቅኔ እያሉ ሥራ እሚያስፈቷት፡፡” አጒረመረሙ ወይዘሮ ትደነቂያለሽ፡፡ ልጆቻቸው እንጂ አለቃ የባለቤታቸውን ንግግር አልሰሙትም፤ ቢሰሙትም አይመልሱላቸው እንደ ነበረ ከልማድ የታወቀ ነው፡፡

ሦስቱም ልጆች መጣፍ መጣፋቸውን ይዘው ተቀመጡ፡፡ እግዚአብሔር ትምህርቱን እንዲባርክላቸው አለቃ ጸሎት
አደረሱ፡፡

Tuesday, March 6, 2012

የመዳን ትምህርት

Read PDF
ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ

የመዳን ትምህርት

“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ … ማን ያድነኛል? ሮሜ 7፥24 ካለፈው የቀጠለ፡፡

እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሲመለከት ጻድቅ የሆነ አንድ ሰው ስንኳ ከመካከላችን እንዳልተገኘ ኀጢአት፥ ያልተመረተበት የሰውነት ክፍልም በእያንዳንዳችን እንደ ሌለ የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ባለፈው ዕትም ተመልክተናል (መዝ. 13፥1-3)፡፡

የዛሬው ዕትም ደግሞ ሰው መበላሸት ከመፈጠሩ ጀምሮ እንዳልሆነ ያስነብበናል፡፡

Sunday, February 26, 2012

መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ

Read PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ
ካለፈው የቀጠለ
 በም. 1፥3-4 በሞሪያ ተራራ በጽዮን አምባ ላይ ንጉሥ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ “የእግዚአብሔር ሕግ ማደሪያ ታቦተ ጽዮን” በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ዘመን እንደ ነበረች ይናገራል፡፡ በአገላለጹ ከዜና መዋዕል ካልእ 35፥3 ጋር ይስማማል፡፡  ጊዜው የኢዮስያስ 18ኛ የግዛት ዓመት ስለ ሆነ (2ዜና. 35፥19) ሰሎሞን ከሞተ 359 ዓመት ዐልፎአል ማለት ነው፡፡

ም. 1፥54-55 ከለዳውያን የእግዚአብሔርን ማደሪያ ታቦት ማርከው ወደ ባቢሎን እንደ ወሰዱ ይናገራል፤ ትረካው ግን፡-
1.      ታቦተ ጽዮን በሰሎሞን ዘመን ተሰርቃ ተወስዳ ነበር ባዮችን የሚደግፍ ሆኖ አልተገኘም፡፡ መሰረቋን ማወቅ ያልቻለ እንደ ዕዝራ ሱቱኤል ያለ ሰው ነው ካልተባለ በቀር፤ ዕዝራ ሱቱኤል 9፥21-22፡፡
2.     የተረፈ ኤርምያስ ጸሓፊ ቤተ መቅደሱ በውስጡ ካለው ዕቃ ጋር ተሰወረ በሚለው ሐሳብ አልተስማማም፤ ተረፈ ኤር. 8፥13፡፡

Wednesday, February 22, 2012

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ዕውቀት

 Read PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ


ባንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ በብሉይ ኪዳን  መጨረሻ ከገጽ 721 እስከ 1037 በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች የማይገኙ መጻሕፍት በመጨመራቸው ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው ያውቃሉን? «ተጨማሪ (ዲዩትሮካኖኒካል) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት» በሚል የክፍል መጠሪያ የተጨመሩት መጻሕፍት ዐሥራ ስምንት ናቸው (በ1980 ዕትም)፡፡

በውሳኔ የተጨመሩት መጻሕፍት የሚገኙበት ጥራዝ ባንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲቈጠር፥ እነርሱ የሌሉበት ጥራዝ ግን ጐደሎ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ ሲጠራ ተሰምቷል፡፡

Wednesday, February 15, 2012

ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 42 ለንባብ በቅቷል፡፡


 REad PDF
ርእሰ አንቀጹ፡-
እውነት ምንድር ነው? በማለት የእውነትን ፍለጋ ተከትለን እውነት ወደሆነውና ወደሚያድነው እውነት ወደ ኢየሱስ ያድርሰናል፡፡
መሠረተ እምነት
ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት ራሱ ክርስቶስ ያስተማረውን እውነት ያብራራል፡፡ መካከለኛነቱን ለማስተባብል የሚሰነዘሩ ጕንጭ አልፋ ክርክሮችን ይሟገታል፤ ተከራክሮም በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይረታል፡፡


ክርስቲያናዊ ምግባር
በማቴ. 5÷10 ላይ ተመሥርቶ ስለጽድቅ የሚደርሰው ስደት ለክርስቲያኖች ያለውን ጥቅም እና በአሳዳጆች ላይ የሚያስከትለውን ጕዳት ይገልጣል፡፡
የዘመን ምስክር
የቀደሙ አባቶቻችን የሠሩትን መልካም ሥራና ያሳዩትን በጎ አርኣያነት የሚዘክረው ይህ ዐምድ ለውጥ ናፋቂውን ብላቴን ጌታ ኅሩይንና መልካም ሥራዎቻቸውን ያስተዋውቃል፡፡   
ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው
በቊጥር 94 በስያሜ 81 እየተባለ ስለሚጠራው፣ ከሒሳብ ስሌት ውጪና ግራ አጋቢ ስለሆነው  የመጽሐፍ ቅዱስ አቈጣጠር ለቀረበ ጥያቄ፣  ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ 
66 + 28 = 84 መጻሕፍት፡፡
ወቅታዊ ጕዳይ
ኦርቶዶክስ ማነው? በሚል ርእስ በተከታታይ በሚቀርበው በዚህ ርእስ ማኅበረ ቅዱሳን በአስተምህሮው ኦርቶዶክሳዊ መሆን አለመሆኑን ይፈትሻል፡፡ በዚህ ዕትም አንድ ቀሪ ነጥብ ቢኖርም፣ ማኅበረ ቅዱሳን ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት ተገምግሞ ኦርቶዶክሳዊ አለመሆኑ ተደርሶበታል፡፡ 
ሌሎችም ጽሑፎች ተካተዋል፡፡ በ“እውነት ምንድር ነው?” የጀመረው የዚህ መጽሔት መልእክት “እስከ ማእዜኑ” በተሰኘውና እውነትን በሚያቀነቅነው የዮናስ አድማሱ ግጥም ይደመድማል፡፡
መጽሔቱን በየመንፈሳዊ መዝሙር ቤቶች ያገኙታል፡፡

Wednesday, February 1, 2012

የሰይጣን ባቄላ

Read PDF
የሰይጣን ባቄላ
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 2 ላይ የቀረበ


የሳባ ታሪኮች ከሚለው መጽሐፍ የተገኘ (የአንድ ሰባኪ ትረካ)

አንድ ቀን እጅግ ብዙ የሆነ አሳማ አንዱን ሰው ተከትሎ ሲጥመለመል አየሁ፡፡ የአሳማ መንጋ ከወደ ኋላ ሆኖ ሲነዱት እንኳ ግራና ቀኝ እያለ ነጂውን ያስቸግራል:: በዚህ ጊዜ ግን ያለ አንዳች ችግር ተቀጣጥሎ ሰውየውን ይከተል ነበር፡፡ እኔም ሁኔታውን ለመረዳት ተከታትዬ ተመለከትሁ፡፡ ሰውየውም እየመራ ከብት ወደሚታረድበት ቄራ ሲደርስ በሩን ከፍቶ የተከተለውን የአሳማ መንጋ አስገብቶ መልሶ ዘጋ፡፡

እኔም ወደ ሰውየው ቀርቤ ያለአንዳች ችግር ይህን የሚያህል የአሳማ መንጋ ወደ ቄራው ውስጥ ልትመራው እንደ ምን ተቻለህ? ብዬ ብጠይቀው ከት ብሎ ስቆ “በብብቴ የያዝኩትን አንድ ከረጢት ባቄላ አላየህም ይሆናል፡፡ አሳማዎቹ ደስ የሚያሰኛቸውን ነገር ሳንጠባጥብላቸው ወደ መሞቻቸው እንደሚደርሱ ሳያስተውሉ ያንን እየለቃቀሙ ወደሚታረዱበት ቄራ ድንገት ገቡ እንዳይወጡም ዘጋሁባቸው” አለኝ፡፡

Monday, January 23, 2012

መሠረተ እምነት

Read PDF
ካለፈው የቀጠለ
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 2 ላይ የቀረበ
ማስረጃ 2

በኦሪት ዘፍጥረት 1፥26 “ኤሎሂም (አማልክት) በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ሰውን እንፍጠር አለ፤” ተብሏል፡፡ ተናጋሪው በአንድ አካል “ኤል” ራሱን አልገለጸም፡፡ የብዙ ቊጥር መግለጫ በሆነው ስም “ኤሎሂም (አማልክት)” ራሱን የገለጸው ይሆዋ ነው፡፡

“እንፍጠር” የሚለውም ውሳኔ ብዛትን ከሚያመለክተው የአረፍተ ነገሩ ባለቤት ከሆነው “ኤሎሂም” (አማልክት) ጋር ይስማማል፡፡ ሆኖም “ኤሎሂም” (አማልክት) እንፍጠር በማለት ያሳለፉትን ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስ ለኛ ሲያስተላልፍ በአንድ ይሆዋነት የሚታወቁ አካላት መኖራቸውን ለማስረዳት በመፈለጉ እንፍጠር አሉ ሳይል “እንፍጠር አለ” ይለናል፡፡ አገላለጹ ሚዛናዊ ልብ ላለው ሰው ብዛትንና አንድነትን ሊያስተምር ይችላል፡፡

Wednesday, January 18, 2012

መሠረተ እምነት

Read Pdf
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩ ምእምናን ሲጽፍ እንዲህ አለ፡- “ስለዚህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጎችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች ናችሁ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡ በሐዋርያትና በነቢያትም መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑም ራስ የሆነው ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሕንጻው በሙሉ በእርሱ ተገጣጥሞ የጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ያድጋል፡፡ እናንተም እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚያድርበት ሕንጻ ለመሆን በክርስቶስ ትታነጻላችሁ፤” (ኤፌ. 219-22)፡፡

ለአንድ ምእመን የማእዘኑ ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ በሆነበት፥ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ በሚያስተማምን ሁኔታ ጸንቶ መቆሙን ከሌሎች ምእመናን ጋር በመገጣጠም ለሕንጻው እድገትና ውበት አስተዋጽኦ ማድረጉን መርምሮ ከማረጋገጥና በዚህም እግዚአብሔርን ከማመስገን የሚበልጥበት ምንም ነገር እንደማይኖር የታመነ ነው፡፡

Sunday, January 15, 2012

በኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ

    Read PDF
በጮራ ቊጥር 2 ላይ የቀረበ

/ካለፈው የቀጠለ/

በዚህ ርእስ የሚቀርበው ታሪክ ከጥንት ጀምሮ እየተለዋወጠ እስከ እኛ ዘመን የደረሰውን የሀገራችንን የዳር ድንበር ክልል፥ የመንግሥቷን ዐይነትና አወቃቀር በየዘመኑ በመንግሥቷ የታቀፉትን ልዩ ልዩ ነገዶች ስማቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ አምልኮታቸውን ወዘተርፈ በመጠኑም ቢሆን መያዝ በተገባው ነበር፡፡ ዳሩ ግን በአንድ በኵል ከርእሱና ከዐላማው ላለመውጣት፥ በሌላው በኩልም በሙያው ብዙ የደከሙትን ተመራማሪዎች ድርሻ ላለመሻማት ሲባል በርእሱና በዐላማው መወሰን የሚሻል ሆኗል፡፡

          ሊቀር የማይገባው ነጥብ ቢኖር “ኢትዮጵያ” ስለሚለው ስያሜ ዐጭር መግለጫ የማቅረቡ ጕዳይ እንደ ሆነ ይታመናል፡፡
ለኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ የሚያገለግሉ ምንጮች ናቸው በመባል በባለታሪኮች ከሞላ ጐደል የሚታመንባቸው፡-

Thursday, January 5, 2012

“እኔ ጐስቋላ ሰው ነኝ . . . ማን ያድነኛል?” (ሮሜ 7፥24)፡፡

Read PDF
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 2 ላይ የቀረበ)

ካለፈው የቀጠለ

መዳንን አጥብቀው የሚሹ በሽተኞች መሆናቸውን የተረዱና የጤና ስንኩልነታቸው ያስከተለባቸው ጕዳትና ውርደት ከልብ የተሰማቸው ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ በብዙ ድካም ያገኙትን መድኀኒት በሚገባ ሊጠቀሙበት ሙሉ ፈቃደኞች  ይሆናሉ (ሉቃ. 5፥31፤ ሐ.ሥ. 16፥30)፡፡ በዚህ ትይዩ እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ያዘጋጀውን መድኀኒት በምስጋና እንቀበለው ዘንድ በቅድሚያ የበሽታችንን ምንነትና ያደረሰብንን ገናም የሚያደርስብንን አስከፊ ውጤት በጥልቀት ልናጠናው ይገባል፡፡

የእግዚብሔር ቊጣና ምክንያት

በኀጢአተኝነትና በዐመፃ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ እንደሚገለጥ በማስታወቅ ሐዋርያው ጳውሎስ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ለሰው ዘር ሁሉ ያስተላልፋል (ሮሜ 118-31)፡፡ ሐዋርያው “ኀጢአተኛነት” ሲል ኀጢአተኛ የሆነውን ሰብኣዊ ባሕርይ ያመለክታል፡፡ እንዲሁም “ዐመፃ” ሲል ኀጢአተኛ ሰው በኀጢአተኛ ባሕርዩ የሚያፈራውን የኀጢአት ፍሬ ይገልጻል፡፡ በዚህ አገላለጽ መሠረት ሰው በሁለት መንገድ ኀጢአት እንደ ተቈጠረበት መረዳት ተችሏል፡፡ ይህም ማለት ኀጢአተኛነትና ኀጢአት ነው፡፡ ሰውን ኀጢአተኛ ባሰኘው ኀጢአተኛ ባሕርዩና ከኀጢአተኛ ባሕርዩ የተነሣ ሰው በሠራው ኀጢአት ላይ መለኮታዊ ቊጣ ሊገለጽ ተገባ፡፡