Read in PDF
(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 4 ላይ የቀረበ)
“እኔ ምንኛ ጐስቋላ
ሰው ነኝ … ማን ያድነኛል? …” (ሮሜ 7፥24)
ካለፈው የቀጠለ
ባለፈው ዕትም የሰው አፈጣጠር እንከን አልባ እንደ ነበር
ከእግዚአብሔር ቃል ማንበባችንን እናስታውሳለን፡፡ ግሩምና ድንቅ ለተባለ የውስጥና የውጭ ውበት ባለቤት ሆኖ የተፈጠረው ሰው፥ “እኔ
ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ . . . ማን ያድነኛል?” እንዲል ያስገደደው ብልሹነት እንዴትና ከየት መጣበት የሚለው ጥያቄ በዛሬው
ዕትም ይመለሳል።
የሰው
ተፈጥሮ መበላሸት ከየት መጣ?
“ሕያው ነፍስ” ያሰኘውን የሕይወት እስትንፋስ ከሕያው አምላክ
በመቀበሉ እግዚአብሔርን መስሎና ከማንኛውም ፍጥረት በልጦ እንከን አልባ የሆነው ሰው አንድ ቀን በእባብ እንደ ተጐበኘ መጽሐፍ
ቅዱስ ይነግረናል።
እባብ ሆኖ ወይም በእባብ ተመስሎም ሆነ ዐድሮ ወደ ሰው
የመጣው፥ በዕብራይስጥ ሰይጣን በግሪክ ዲያብሎስ የተባለው ታላቁ ዘንዶ ነበር (ራእ. 12፥19-21)።
- ሰይጣን ማለት ስቶ የሚያስት ማለት ስለ
ሆነ ራሱን በራሱ ካሳተ በኋላ ሌሎችን የማሳት ግብሩ ያሰጠው ስም ነው (ዮሐ. 8፥44)።
- ዲያብሎስ ከሳሽ ባለጋራ፥ ደመኛ ማለትም
የመልካም ነገር ሁሉ ተቃዋሚነቱና የእግዚአብሔርን ሰዎች ጠልፎ ለመጣል ሌት ተቀን የሚያደርገው ጥረቱ ያስገኘለት ስሙ
ነው (ዘካ. 3፥1-5፤ ራእ. 12፥10)።
ሰይጣን ሌሎችን ለማሳት መጀመሪያ ራሱን ማሳት ነበረበት።
ስለ ሆነም ሰይጣን ራሱን ስሑት ከማድረጉ በፊት ምን ነበር? የሚለውን ጥያቄ የሚመልሱት የኢሳ. 14፥12-17 እና ሕዝ. 28፥11-19
ምንባባት እንደ ሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጒማን ያብራራሉ።
ቀድሞ ኪሩብ ያውም አኃዜ መንጦላዕት የነበረው መልአክ
በልዑል ለመመሰል ምኞትን ከልቡ አፈለቀ። ምኞቱን ሌሎች መላእክት እንዲቀበሉት ከልቡ አውጥቶ ተናገረው። ራሱን በራሱ አስቶ
ሌሎችን መላእክት ያሳተ ይህ መልአክ ሐሳቡን ከተቀበሉት መላእክት ጋር ወደቀ፤ ሁሉም ሥልጣናቸውንና ክብራቸውን ዐጡ፤ መላእክት
መሆናቸው ቀረና ሰይጣናት ተባሉ፥ ሆኑ። የእነርሱን ሐሳብ ያልተቀበሉት መላእክት ግን በሥራቸውና በስፍራቸው ጸኑ (ራእ. 12፥7-9)።
በነዳፊ መርዛምነቱ እባብ፥ ዘንዶ በአሳሳችነቱም ሰይጣን
የተባለው ይህ የወደቀ መልአክ ነበር እንግዲህ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አዳምንና ሔዋንን አንድ ቀን የጐበኛቸው። ሰይጣን ለእነዚህ
ወላጆቻችን በውሸት እግዚአብሔርን አማላቸው። ሰዎቹ ሐሜተኛውን መቃወምና ማሳፈር ይችሉ ነበር። ነገር ግን በችሎታቸው ሳይጠቀሙ፥
በውሸት የቀረበላቸውን ሐሜት እንደ እውነት ተቀበሉት። እግዚአብሔር ተናግሮአቸው የነበረውን ቃል ማስተባበልንና የራሱን ቃል
በእግዚአብሔር ቃል ምትክ ለሰዎች ማቅረብን ሰይጣን ችሎበት ነበር። ዕቅዱ ቢሳካ የእግዚአብሔርን ቃል ከሰው ልብ ማስወገድንና በምትኩ
የራሱን ቃል በሰው ልብ ውስጥ መትከል ቻለ ማለት እንደ ሆነ በሚገባ ዐስቦበታል። ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ከልባቸው አውጥተው
የሰይጣንን ቃል በልባቸው ለማስገባት ፈቃደኞች ሆኑ ማለት ደግሞ፥ በሚታዘዙለት ቃሉ አማካይነት ለሰይጣን ዐደሩ፤ ባሮች ሆኑ
ማለትን እንደሚያስከትል ማወቅ ነበረባቸው።
የእግዚአብሔር
ቃል
በገነት ካሉ ዛፎች ሁሉ ትበላለህ፤ በገነት መካከል ካለችው ክፉንና በጎውን
ከምታስታውቀው ዛፍ ግን አትብላ፤ ከእርሷ በበላህ ቀን ትሞታለህና (ዘፍ. 2፥16-17)።
የሰይጣን
ቃል
እግዚአብሔር እንደ እርሱ እንዳትሆኑ ብሎ ነው እንጂ
ሞትንስ አትሞቱም (ዘፍ. 3፥1-5)።
እርስ በርስ ተቃራኒ ከሆኑት ከእነዚህ ሁለት ቃሎች
አንደኛውን ብቻ መምረጥ፥ ማመን መቀበልና መታዘዝ ሰዎች የሚፈተኑበት ወሳኝ ጊዜና ሁኔታ ተደቀነ። ከሁለቱ አንዱን መምረጥና
መቀበል ብቻውን ችግር አልነበረም። የሚያስከትለው ውጤት ግን ከባድ ችግር ነበር። ያልተመረጠውንና ተቀባይነት ያጣውን ቃል
መናቅና በሚታዘዙለት ቃሉ አማካይነት እደ ልቡናቸውን በመስጠት ለሚማረኩለት ጌታ ተሸናፊና ባሪያ መሆንን ማስከተሉ የከፋና
የከበደ የምርጫ ውጤት ነበር (2ጴጥ. 2፥19፤ ዮሐ. 8፥34)።
አዳምና ሔዋን ግን በቀላሉ ምርጫቸውን ወሰኑ።
የእግዚአብሔርን ቃል ከልባቸው አውጥተው በምትኩ የሰይጣንን ቃል ወደ ልባቸው አስገቡ። ሰይጣንም ሰዎቹ ወደውና መርጠው
በተቀበሉት ቃሉ አማካይነት ወደ ልባቸው ገባና ዙፋኑን ተከለ፤ በሁለንተናቸውም ናኘ። ከዚሁ ቅጽበት ጀምሮ የሰው ግንኙነት
ከአምላኩ ጋር መሆኑ ቀረ፤ ግንኙነቱ በራሱ ምርጫ ጌታ ካደረገው ከሰይጣን ጋር ሆነ ምርጫው ነጻ በነበረ ፈቃዱ ላይ ያስከተለውን
ለውጥ እንመልከት፥
ሀ) “እግዚአብሔር
የከለከለውን ብበላ አሳዝነዋለሁ፥ አስቈጣዋለሁ፤ እኔም እሞታለሁ። ስለዚህ አልፈልገውም” እንዳይል የመከላከል ኀይሉ ተወሰደበት።
ሊበላው ተመኘ (የሥጋ ምኞት)
ለ) አስፈሪውንና
አስከፊውን የሞትን ዛፍ ሊጠላው ሲገባ፥ ይህን መቃወሚያ ፈቃዱን ስላጣ በጒጒት አየው፤ ሊበላው ጐመጀ (የዐይን አምሮት)
ሐ) ሊበላው
ከተመኘውና ካስጐመጀው የሞት ዛፍ በሚያገኘው ጥበብ እንደ አምላክ ሲሆን ታየው። (ከአምላክ ባልሆነ የራስ በሆነ በተፈጠረ ነገር
መመካት) (ዘፍ. 3፥6፤ 1ዮሐ. 2፥15-16፤ ያዕ. 4፥1)።
አዳምና ሔዋን እንግዲህ ነጻ የሆነ ፈቃዳቸውን ዐጡ።
ልባቸውን፥ እግራቸውን፥ ዐይናቸውን፥ እጃቸውን የሚያዝበት ሌላ ሆነ። የአዳምና የሔዋን ውድቀት እዚህ ላይ ተፈጸመ። ከእንግዲህ
ወዲያ ያለው ሁኔታቸው ጭቃ ውስጥ ከወደቁ በኋላ እንደ መገላበጥ
የሚቈጠር ነበር።
የሰው ተፈጥሮኣዊ ባሕርይ መበላሸት እንደዚህ ሆኖ
ተጀመረ፤ የሚከተሉትም የብልሹነት ፍሬዎች ተመዘገቡበት።
1.
እግዚአብሔር ሲናገር፥ “በበላህ ቀን ትሞታለህ” ብሎ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አዳምና ሔዋን
ከሞት ዛፍ በበሉበት ቀን ወዲያው ሞቱ። ሞቱ ሲባልም መንፈሳዊ ሞትን መሞት፥ ከኀጢአት ጋር ኅብረት ከሌለው አምላክ ግንኙነትን
ማቋረጥና መለየት ነው። የሕይወታቸው ምንጭ ከሆነው ቅዱስ እግዚአብሔር መለየት መንፈሳዊ ሞትን መሞት ነውና (ሕዝ. 18 ፥4፤
ኤፌ. 2፥1-5)።
2.
ከመንፈሳዊው ሞት በኋላ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” በተባለው ርግማን መሠረት፥
መንፈሳዊ ሞትን የሞተችው ነፍስ ማደሪያዋ ከሆነው ሥጋ በመለያየት፥ የሥጋ
ወደ መቃብር፥ የነፍስም ወደ ሲኦል መውረድ ቀጥሎ በሰዎች ላይ መጣ (ዘፍ. 3፥19)። አዳም ከሞት ዛፍ ከበላበት ዕለት ጀምሮ
መንፈሳዊ ሞትን ሞተ፤ መንፈሳዊ ምውት ሆኖም 930 ዓመት በሥጋ ከኖረ በኋላ የነፍስና የሥጋው መለያየት ተፈጸመ (ዘፍ 5፥5)።
3.
በመንፈስ የሞተው ሰው በኀጢአት ምክንያት ከቅዱስ አምላኩ ሲለይ በምትኩ የርኲሰት ምንጭ
ከሆነው ከሰይጣን ጋር ኅብረትን አደረገ ብለናል። ሰው በምርጫው በእግዚአብሔር ቦታ ሰይጣንን አስቀምጦ እንደ ታዘዘለትም አይተናል።
ታዲያ የፍጥረታት ገዥ የነበረው ሰው ለሰይጣን ሲያድር ለሰው
አገልግሎት የተፈጠረችው ምድር በላይዋ የሚገኙትና ከእርስዋ ተፈጥሮ ጋር የተያያዙት ፍጥረታት፥ ገዥአቸው
ከነበረው ከሰው ጋር በሰይጣን ባርነት ሥር ወደቁ። ከዚህም የተነሣ ሰይጣንን የዚህ አለም አምላክ፥ የዚህ ዓለም ገዥ ለመባል
አበቁት (ዮሐ. 12፥31፤ 2ቆሮ. 4፥4)።
4.
እግዚአብሔርን መስሎ የተፈጠረው ሰው በኀጢአት ከመውደቁ በፊት ልጅን ቢወልድ ኖሮ ያ ልጅ
እንደ አባቱ ጥንተ ተፈጥሮ እግዚአብሔርን የሚመስል በሆነ ነበር። ዳሩ ግን
እንዲህ ከመሆኑ በፊት አዳምና ሔዋን ስለ ወደቁ ከዚያ በኋላ የተወለደው ሴት በኀጢአት የወደቀውን አዳምን መሰለ እንጂ
እግዚአብሔርን አልመሰለም። መንፈሳዊ ምዉት ከሆነው አዳም መንፈሳዊ ምዉት ሴት ተወለደ (ዘፍ. 5፥1-3)። ከርኲሰት ቅድስናን
ማፍለቅ አይቻልምና (ኢዮ. 14፥4)።
በዚህ ምክንያት አጠቃላዩና ጅምላው ሰብኣዊ የተፈጥሮ
ባሕርይ ተበላሸ፤ የእግዚአብሔርም ቊጣ እንዲገለጥበት ተገቢ ሆነ (ሮሜ 1፥18)።
ኀጢአተኛው ሰው ከአምላክ ቊጣ ለማምለጥ የራሱን ዘዴ መፍጠር ይችል ነበርን?
የሰው ልጆች ሁሉ በሰይጣን ባርነት ሥር ከወደቁት
ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች (አዳምና ሔዋን) በመወለድ የተገኙ ናቸውና ከኀጢአት ነጻ የሆነ ሰብኣዊ ተፈጥሮ የላቸውም። በመወለድ
ባገኙት ባሕርየ ሰብእናቸው ከኀጢአተኞች ወላጆቻቸው ኀጢአተኞች ሆነው እንደ ተወለዱ ከላይ የተመለከትነውን እናስታውሳለን። ሰዎች
ኀጢአተኞች ሆነው በመወለዳቸውም የኀጢአት ደመ ወዝ የሆነውን ሞትን የመሞት ግዴታን ከኀጢአተኛ ባሕርይ ጋር በአንድነት እንደ
ወረሱ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል (ሮሜ 5፥12)።
ሰይጣን ወደ ሰው ልብ ባስተላለፈው ቃሉ አማካይነት ራሱን
የሰው ገዥ አድርጎ ለቃሉ ከታዘዘለት ከሰው ተፈጥሮ ጋር አዋሕዷል። በሚወለዱትም ልጆችና ቀጣይ ትውልድ ሁሉ ከሰይጣን የመጣው
የኀጢአት ዘር በሥጋና በደም እየተላለፈ ሰውን ሁሉ ከሰይጣን ጋር ስላቈራኘው፥ ሰውን የእባብ ወይም የሰይጣን ልጅ ለመባል
አበቃው (ማቴ. 3፥6፤ 12፥34፤ ሉቃ.3፥7)።
እያንዳንዱ ሰው የሚፀነስበት ዘር ከሰይጣን ወደ ሰው
በተላለፈው በኀጢአት ከተበከለ ሥጋና ደም የሚገኝ እንደ መሆኑ መጠን በኀጢአት መፀነሱና በኀጢአት መወለዱ ግዴታ ሆነ (መዝ. 50/51፥5)።
ሥጋዊ ፍላጎትን ለማሟላት የሚያቅድ የሚንቀሳቀስና ከፍተኛ
ጥረት የሚያደርግ፥ በባሕርዩ እንስሳን የመሰለ ቢሆንም (መዝ. 48/49፥12) የተከለከለውን ዛፍ ከበላባት ቀን ጀምሮ በመንፈሱ
የሞተ መንፈሳዊ በድን ሆኖአል።
ከምድራዊ ኑሮ ማብቂያው በኋላም አስፈሪውን ዘላለማዊ
ቅጣት የሚቀበልበት ገሃነመ እሳት ይጠብቀዋል (ዳን. 12፥2፤ ማቴ. 13፥39-42፡49፤ 25፥41፤ ራእ. 20፥7-10፤
21፥8)። ታዲያ እንደዚህ ካለው ማለት በአንድ በኩል፥
- ከሰይጣን በተቀበለው ኀጢአት ከተመረዘና
ከረከሰ፤ በዚህም ምክንያት መንፈሳዊ ሞትን ከሞተ፤ በሌላ መልኩም፥
- አስፈሪውና ዘላለማዊው ገሃነመ እሳት
እንደሚጠብቀው ዐውቆ ከሚርደው ሰው ለነፍስ ደኅንነት የሚበጅ መልካም ነገር እንዴት ሊገኝ ይችላል? በተበላሸ ባሕርዩ ዐልፎ ዐልፎ መልካም ነገር ብልጭ ቢልበትስ መልካሙን የሚሠራበትን ነጻነትና ንጹሕ
ባሕርይ ከየት ያገኛል? ምክንያቱም፥
- እግዚአብሔር
የሚወደውን ሊሠራ ይቅርና መንፈሳዊ ምውት የሆነው ሰው ራሱም ቢሆን በተዛባ አእምሮውና በተበረዘ ፈቃዱ ማለት በሚገኝበት
ደረጃው የማይወደውንና ክፉ እንደሆነ የሚያውቀውን ክፉ ነገር ሳይወድ እየጠላው ሳለ ይሠራቸዋልና (ሮሜ 7፥19)።
ሳይወድም ሆነ
እየወደደ ክፉ ማድረጉ ዐመፃን አስቈጥሮበታል (1ዮሐ. 3፥4)።
- በእግዚአብሔር
ዘንድ የሚወደደው መልካሙን ነገር ምን እንደ ሆነ በተዛባ አእምሮውና በተበረዘ ፈቃዱም ቢሆን አሳምሮ ያውቀዋል። ይህን
የሚያውቀውን መልካሙን ነገር የማድረግ ችሎታ ግን ለሰው የለውም (ሮሜ 7፥19)። የሚያውቀውን መልካም ነገር
አለማድረጉም ቢሆን ከኀጢአት ነጻ አያደርገውም (ያዕ. 4፥17)።
የማይወደውን ክፉውን የማድረጉና የሚወደውን መልካሙን
ያለማድረጉ ምክንያት ምንድር ነው? ቢባል ለጥያቄው የእግዚአብሔር ቃል መልስ ይሰጣል። ከአዳም ጀምሮ በውርስ እየተላለፈ
ከመጣው፥ በውስጡ ሆኖና ባሪያ አድርጎ ለሰይጣን ከሚያስገዛው፥ ራሱ ኀጢአት ሆኖ ኀጢአተኛ ካደረገው ከኀጢአተኛ ባሕርዩ
የማስገደድ ኀይል የተነሣ ሰው የሚወደውን መልካም ነገር መሥራት አይችልም፤ የሚጠላውን ክፉ ነገር ከማድረግም አይታቀብም (ማቴ.
12፥34፤ ሮሜ 7፥20-23)።
ለምሳሌ፥ የያዕቆብ ተወላጆች በግብጽ ጭቃ ይረግጡና ጡብ
ይጠፈጥፉ የነበረው ወደው፥ በጭቃ ለመጫወት ሲሉ አልነበረም፤ ባሮች ያደረጓቸው ግብጻውያን እያስገደዷቸው ነበር። ወደ ግብጽ
የገቡት አባቶቻቸው ሳይገደዱ በራሳቸው ምርጫ ቢሆን ልጆቻቸው ግን ከግብጽ ለመውጣትና በነጻነት ለመኖር አልቻሉም። ከሰይጣን
ባርነት ሥር የወደቀው የሰው ዘር ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን ይህን ይመስላል (ዘፀ. 2፥23፤ ዘፍ. 42፥1-2፤ 47፥1-6፤ ዘፀ.
1፥8-14)።
- በኀጢአት
የሞተች የሰው ነፍስ በሰው ሥጋ ውስጥ መንፈሳዊ በድን ስለ ሆነች ከዚህ መንፈሳዊ ሞት በኋላ የሰው መጠሪያ በአብዛኛው
በሚታወቅበት ስም “ሥጋ” ወይም “ሥጋና ደም”፥ ወይም “ፍጥረታዊ ሰው” ተባለ (ዘፍ. 6፥3፤ ዮሐ. 3፥6-7፤ 1ቆሮ.
2፥14፤ 1ቆሮ. 15፥50)።
- ሥጋ፥
ወይም ሥጋና ደም፥ ወይም “ፍጥረታዊ ሰው” የሆነው ሰው የተበላሸ ተፈጥሮው ካልታደሰና የመንፈስ ትንሣኤ ካላገኘ በቀር
እስከዚያው ድረስ ዐልፎ ዐልፎ ብልጭ የሚልለትን መልካም ሥራ ቢሠራም ወይም በሰው አስተያየት የሠራ መስሎ ቢታይም
መልካም የተባለ ሥራውን የሠራበት ባሕርይ ቅዱስ አይደለምና አምላኩን ሊያስደስትበት አይችልም። በመክፈያ (ፖፖ)
የቀረበውን ምግብ ማን ቀምሶት ነው? ጣፋጭነቱን የሚያደንቅለት? (ማቴ. 12፥33፤ ሮሜ 8፥8)።
- ሰው
መልካሙን ባለማድረጉና ክፉውን በመሥራቱ ኀጢአተኛ መሆኑን ዐውቋልና በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት መቆም ከቶ አይሆንለትም።
ይፈራል፥ ይርዳል፥ ይቅበዘበዛል፥ ይሸሻል። እንቡዘ ልብም (ልብ-የለሽ) ሆኖአልና የማያድኑትን ሣሩን፥ ቅጠሉን፥ ዛፉን፥
ተራራውን ከእግዚአብሔር ቊጣ መደበቂያ ለማድረግ ከንቱ ሙከራ ያደርጋል። ላያድኑት ላይደብቁት ፍጥረታትን ይማጸናል።
እንደ አዳምና ሔዋን (ዘፍ. 3፥7-10)።
የአዳምና
የሔዋንም ልጆች ያው እንደ ወላጆቻቸው ቢያደርጉ ምን ያስደንቃል?
ሰው ሌላውን ይቅርና
ለኀጢአት ወደዓለም መግባት ምክንያት የነበሩትን፥ ነፍሳቸውን ለማዳን ከእግዚአብሔር ረድኤትና ታዳጊነት በስተቀር በራሳቸው ተስፋ
የሌላቸውን፥ በአጠገቡ የሌሉትን በዐጸደ ነፍስ የሚገኙትን አዳምና ሔዋንን እንኳ “ሰአሉ ለነ፥ ለምኑልን፥ አማልዱን” ሲል
ይሰማል። ይህም ብቻ አይደለም፤ ሕይወትና አካል አልባዋን የ24 ሰዓታት ድምር (ውጤት) የሆነችውን ዕለት “ሰአሊ ለነ ሰንበተ
ክርስቲያን ለምኚልን፥ አማልጂን” እስከ ማለት ደርሷል። ይህም ድርጊት በእግዚአብሔር ላለመታየትና ከቊጣውም ለመደበቅ ሲል በቊጥቋጦ
ውስጥ እንደ መሸሸግ፥ ቅጠልንም እንደ መልበስ የሚቈጠር ነው።
ይህን ሁሉ እንዲያደርግ የሚያነሣሣው ከኀጢአቱ የተነሣ
በቅዱስ እግዚአብአሔር ፊት ለመቆም ስለሚያስፈራው ሲሆን፥ እንቡዘ ልብ ከመሆኑ የተነሣም በራሱ የሚያደርገው ሁሉ አሥቂኝ ከመሆን
የማያልፍ ራሱን ወደ ቀድሞ ትክክለኛ ተፈጥሮው ሊመልሰው የማይችል ነው።
ስለ ሆነም ሰው “ራሴን እንቃለሁ፤ በዐፈርና በዐመድ ላይ
ተቀምጬ እጸጸታሁ። ከዚህ ዐይነት ሕይወትስ ማን ያድነኝ?” ብሎ ከራሱ ውጪ የሆነ መለኮታዊውን አዳኝ ኀይል ለማግኘት ወደ
አምላኩ ብቻ መጮኽ የሚገባው ምስኪን ፍጡር ነው ማለቱ ተገቢ ይሆናል (ኢዮ. 42፥6፤ ሮሜ 7፥24)።
በባርነት ውስጥ የነበሩ የእስራኤል ልጆች ያደረጉት
ይህንኑ ዐይነት ሥራ ነበር። “የእስራኤል ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፤ ጮኹም። ጩኸታቸውም ወደ እግዚአብሔር ወጣ” (ዘፀ.
2፥23)።
በራሱ ራሱን ነጻ ማውጣት ያልቻለውን የሰው ዘር ለማዳን እግዚአብሔር ያወጣው
ዕቅድና የአፈጻጸሙ ተስፋ በሚቀጥለው ክፍል ይቀርባል።
No comments:
Post a Comment