Monday, September 17, 2012

ርእሰ አንቀጽ

Read in PDF
በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 4 ላይ የቀረበ
ይቅር ባይነት እንማር

ሰዎች የምንባል ሁሉ በልዩ ልዩ አገርና ስፍራ የተወለድን ከልዩ ልዩ የሰው ዝርያ (ነገድ) የተገኘን እንደ መሆናችን መጠን በቋንቋ በአኗኗር፥ በአመጋገብ፥ በአለባበስ፥ በአስተሳሰብ በአጠቃላይ በባህል፥ በሙያና በመልክ ቀለም መለያየታችን የታወቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በመካከላችን ከሚታዩት ጥቃቅን ልዩነቶች ይልቅ ሁላችን አንድ የምንሆንበትና የምንመሳሰልበት ነገር ጒልህ ሆኖ የሚታይ መሆኑን ማስታወስ አለብን፡፡

በተለይ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አንድነታችንን ለመጠበቅ፥ የተጣለብንን አደራና ዓላማ ያለውን ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን በሚገባ ከግቡ ለማድረስ እንድንችል በብዙ ሜዳዊ ልዩነቶች መካከል የምንመሳሰልባቸውንና አንድ የሚያደርጉንን ቁም ነገሮች መገንዘብም ማሰላሰልም ያስፈልገናል፡፡


በእኛ በኩል በቊጥር የማያንሱ፥ የማይጨምሩም የምንመሳሰልባቸውና አንድ የምንሆንባቸው ሁለት ግልጽ ነጥቦች መኖራቸውን አረጋግጠን እናውቃለን፤

አንደኛ፥ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ምእመናን በጻፈው መልእክቱ ምእራፍ 3 ላይ ስለ ሰው ጠባይዓዊ ተፈጥሮ እንዲህ ሲል ጽፎአል፤ “ልዩነት የለምና ሁሉ ኀጢአት ሠርተዋልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል፡፡” ቀደም አድርጐም “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ” ብሏል፡፡ ይህ መመዘኛ ሁላችንንም ከልብ እንደሚነካን የታወቀ ነው፡፡ ስለ ሆነም እኩልነታችንና አንድነታችን ተረጋገጠ ማለት ነው ከአዳምና ከሔዋን ዘር በመወለድና በሠራነው ኀጢአት ሁላችንም እኩል በአንድነት በአንድ መዝገብና አንቀጽ ተከሰናልና፡፡

ሁለተኛ፥ መጽሐፍ ቅዱስን የምናነብ ሁሉ እግዚአብሔር ስለ ይቅርታ በሰፊው መናገሩን እንገነዘባለን፡፡ በሪት ዘሌዋውያን ምእራፍ 19 “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ሲል ያወጀው አምላካችን ልጁን ወደዚህ ዓለም እንዲልክ ያደረገው ኀጢአታችን እንጂ ቅድስናችን እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ስለ ጠፋው ልጅም የተነገረው ምሳሌ የያንዳንዳችን ታሪክ ነው፡፡ የጠፋው ልጅ ወደ አባቱ ከመመለስ በቀር የተበላሸውን እንዳልተበላሸ ለማድረግም ሆነ ለማሻሻል ባይችልም እንኳ አባቱ በፍቅር ተቀበለው፡፡ ለምን? ይቅር አለዋ! ምሕረት አደረገለት! ራራለት! ያጠፋውንም ሁሉ ተወለት!

ይህን በጥልቀት የተረዳው ሌላው ሐዋርያም “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፤ በኀጢአታችን ብንናዘዝ … ይቅር ሊለን ከመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡” ይለናል (1ዮሐ. 1፥8-9)፡፡

 እንግዲህ በኀጢአት በመከሰስ አኩል እንደ ሆንን ሁሉ እንዲያው በጸጋው በእምነት በመጽደቅና ይቅር በመባል አንበላለጥም፤ አንተናነስምም፡፡ ሁሉም፥ ሕዝብም አሕዛብም ክርስቶስ ኢየሱስ የሞተለትና በሞቱ የዋጀው መንጋ ሆኖአል፡፡  የዚህ የአንዱ መንጋ እረኛም አንድ ነው፡፡

እንዲህ ከሆነ በአንድ እረኛ የሚጠበቀውን ይህን አንድ መንጋ ለመበተን የሚጥር በጥባጭ ጠላት ከየት መጣ? ከመንጋው ውጪ? አይደለም እርስ በርስ መጠላላቱ፥ መተማማቱ፥ መጋጨቱ፥ ለውጭ ጠላት መግቢያ ቀዳዳ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “እርስ በርስ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ” ያለው፡፡ ገላ. 5፥15 እንዲህ ባለ ፈተና እንዳንወድቅና ጠላት እንዳይሳለቅብን፤ በይቅርታ የተቀበለን አምላካችንም እንዳያዝንብን የእግዚአብሔር ቃል በሚመራን ቀና ጐዳና እንጓዝ፤ ያም የይቅርታ መንገድ ነው፡፡

ይቅርታን የማያውቅ ዓለም እንኳ በመቻቻልና ልዩነትን በማጥበብ በአንድነት ለመኖር ይሞክር የለም?

No comments:

Post a Comment