Saturday, August 18, 2012

ጸሎት


(በጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቊጥር 3 ላይ የቀረበ)


“ጌታ ሆይ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን፡፡” (ሉቃ. 11፥1)

ከክርስትና ሕይወታችን አብዛኛው ክፍል የሚያዘው በጸሎት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ያለመታከት መጸለይ እንዲገባን የእግዚአብሔር ቃል ይመክረናል (ሉቃ. 18፥1-7)፡፡

ኑሮአችን በጥያቄና በችግር የተሞላ ስለሆነና ሁል ጊዜ የምንቀበለው ስለሚበዛ፥ ያለ ጸሎት ልንኖር አንችልም፡፡ ትንሽ ልጅ ሲርበው፤ ቊርሱን ምሳውን፥ እራቱን፤ ሲበርደው ልብሱን፥ መጠለያውን ይጠይቃል፡፡ ሲታመም ይቅበጠበጣል፥ ያለቅሳል፡፡ እንቅፋት ቢመታው፥ እሾኽ ቢወጋው፥ የጎረቤት ልጅ ቢያጠቃውና በእድገቱ ሂደት የሚያጋጥሙትን ዐዳዲስ ነገሮች ሁሉ የማወቅ ጥማቱን ለማርካት ጥያቄዎችን ይደረድራል፡፡ ትናንት ጠይቆ በተቀበለው ተጠቅሟል፥ አመስግኗልም፡፡ ሆኖም ትናንት ዐልፎአልና ዛሬ ለዐዲስ ጥያቄ ዐዲስ ምላሽ ይጠብቃል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቲያንም በዚህ ተመሳሳይ ምክንያት ጸሎትን ማቋረጥ አይችልም፤ አያስታጕልም፡፡

እግዚአብሔር አባታችን እንዲሁ ከበጎ ፈቃዱ የተነሣ የሚያሻንን እንደሚሰጠን አጣራጣሪ አይደለም፡፡ የጸለይንበትን አብዝቶ፤ ያልለመነውንም አትረፍርፎ የሚሰጠን ከበጐ ፈቃደኛነቱና ለመስጠት ካለው ዝንባሌው የተነሣ ነው (ማቴ. 6፥8፤ 25-32)፡፡ ልጆቹም የሚያሻቸውን ሁሉ እንዲጠይቁ ሰፊ የጸሎትን በር ከፍቶላቸዋል (ማቴ. 7፥7-11፤ ሮሜ 8፥11)፡፡

ጸሎት በተለያዩ ወቅቶችና ስፍራዎች፥ በተለያዩ  ምክንያቶች እንደ ሁኔታው የሚቀርብ፥ ወይም በአባትና በልጅ መካከል የሚካሄድ ነጻ ውይይት ቢሆንም፥ ስለ ውይይቱ በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

1.    መቅድመ ጸሎት

ጸሎት የድርሳን ዐይነት መቅድም የለውም፡፡ ጸሎተኛው በቅድሚያ የሚያሟላቸውን ዝግጅቶች እንደ መቅድመ ጸሎት በመቊጠር ከሚያስፈልጉት ዝግጅቶች ዋና ዋናዎቹን በዚህ አቅርበናል፡፡

1.1.    ጸሎት የሚቀርብለትን ባለሥልጣን ማወቅ

ትክክለኛ አድራሻ ያልተጻፈበት ደብዳቤ ተቀባይ አያገኝም፡፡ የተሻለ ዕድል ከገጠመው ዞሮ፥ ዞሮ ወዳ ላኪው ከነጒድለቱ ይመለሳል፡፡ ክርስቲያን የሚጸልየውን ጸሎት ከደረሰበት ይድረስ በማለት ወዳልተረጋገጠ አድራሻ ሊወረውረው አይገባም፡፡ ለዐላማ በዐለማ የሚጸልይ ከሆነ ለታወቀ ሁነኛ ባለሥልጣን ጸሎቱ ቢደርስለት የደከመለት ዕቅዱ ይሠምርለታል፡፡ ታዲያ ጸሎትን የመቀበልና የመፈጸም ችሎታ ያለው ባለሥልጣን ማን ነው?

1.1-ሀ. ክርስቲያን ወደ ሞቱ ሰዎች ነፍሳትና ወደ ልዩ፥ ልዩ መናፍስት ሊጸልይ ይገባዋልን?
የጸሎትን ትክክለኛ አድራሻ የማያውቁ አረማውያን ሆድ ሲብሳቸው ወደ ወላጆቻቸው፥ ወደ ዘር ግንዶቻቸው መቃብር እየሄዱ በማልቀስ ችግራቸውን ያመለክታሉ፡፡ አንዳንዶቹም ሲጨንቃቸው በተለምዶ የሰሟቸውን የመናፍስት ስሞች በመጥራት ይማጠናሉ፡፡ ብልጣ ብልጥ ሥራ ፈቶች ለጥቅማቸው የጻፏቸው ግጥሞችና ስድ ንባቦች፥ በቃልም የሚተርቷቸው ወጋ ወጎች ወደ ሞቱ ሰዎች ነፍሳትና ወደ መናፍስት ለሚቀርብ ጸሎት መንሥኢ  ናቸው፤ በትውልድም አእምሮ ዘላቂ ተጽእኖ አላቸው፡፡

እንደዚህ የሚያደርጉ አረማውያን ብቻ አይደሉም፡፡ በሩቅም ሆነ በቅርብ ጊዜ ከአረማውያን ቤተ ሰብ የሞቱ ክርስቲያኖችም የባዕድ አምልኮ ዘርፍ የሆነውን ወደ ሙታን ነፍሳትና ወደ መናፍስት የመጸለይን ልምድ የወረሱ ስለ ሆነ ልምዱ በክርስትናቸውም ቢሆን ጣልቃ እየገባ ያስቸግራቸዋል፡፡ ሆኖም ለእግዚአብሔር በወገንነት የተለዩትን ሁሉ “ወደ መናፍስትም ሆነ ወደ ሙታን ነፍሳት” እንዳይጸልዩ መለኮታዊ ቃል ከልክሎአቸዋል፡፡ እንዲህ ሲል፡-

“ሟርተኛ፥ መናፍስትን የሚጠራ፥ ጠንቋይ፥ ሙታንን የሚስብ በአንተ ዘንድ አይገኝ፡፡ ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው፡፡” (ዘዳ. 18፥9-12፤ በተጨማሪ ኢሳ. 8፥19-20)፡፡

1.1-ለ የሞቱ ዘመዶቻችንን ነፍሳት ብንጠራቸው ይሰሙናል የምንጠይቃቸውንስ የመፈጸም ችሎታ አላቸውን?

ምድራዊ ተልኮአቸውን ጨርሰው ያንቀላፉትን (የሞቱትን) ሰዎች ነፍሳት በሥጋ ሕይወት ያለነው እኛ ብንጠራቸው አይሰሙም፤ የምንጠይቃቸውንም ለመፈጸም አይችሉም፡፡ ሞትን ተሻግረው ወደ ጸደ ነፍስ የተዛወሩ ሰዎች በዐጸደ ሥጋ ያሉ ተወላጆቻቸው ቢከብሩ ወይም ቢዋረዱ የማወቅ ወይም የማየት ችሎታ የላቸውም ይላል ቃሉ (ኢዮ. 7፥9-10፤ 14፥1-22)፡፡
የሞቱ ሰዎች ከፀሓይ በታች ማለት በምድር በሚሠራው ነገር ዕድል ፈንታ የላቸውም፡፡ ሲሞቱ በዐጸደ ሥጋ ያለውን ሰው የማፍቀርና የመጥቀም፤ ወይም የመጥላትና የመጕዳት ችሎታን ዐጥተዋል (መክ. 9፥4-6)፡፡

1.1-ሐ. መናፍስትንም እንዳንጠራ ከተከለከልን መናፍስት በምን ሁኔታ ወደ ሰው ይመጣሉ?

በመናፍስትነት የምናውቃቸው መላእክት ናቸው (ዕብ. 1፥7፡13-14)፡፡ ዐመፅን የሠራ ሰይጣንና ተከታዮቹ ከማኅበረ መላእክት እንዲለዩና ክብራቸውን እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ ሆኖም መናፍስት ናቸው (ራእ. 13፥9፤ ይሁ. 6)፡፡

የወደቁትንም ሆነ ያልወደቁትን መናፍስት (መላእክት) እንድንጠራ አለመፈቀዱን ከኦሪት ዘዳግም 18፥9-12 አንብበናል፡፡ ሰው በጸሎት አምላኩን ብቻ እንዲጠራ መታዘዙ እንደ ሆነ ከቃሉ እንረዳለን፡፡ ጸሎትን የማድመጥ ችሎታ ያለው እግዚአብሔርም በተለያዩ አገልግሎት ከመደባቸው ታማኝ መላእክት (ኪሩቤል፥ ሱራፌል፥ እልፍ አእላፋት) መካከል አንዱን መልአክ ሲልከው ወደ ተላከበት ሰውና ስፍራ ይመጣል፡፡ የተላከበትንም ግዳጅ ይፈጽምና ይመለሳል (መዝ. (91)፥11-12፤ ሐ.ሥ. 10፥1-33፤ 12፥5-11)፡፡

1.1-መ. መናፍስትንና የሞቱ ሰዎችን ነፍሳት መጥራት ማሟረት ነው፡፡

መናፍስትንና የሞቱ ዘመዶቻችንን ነፍሳት ብንጠራ ወይም ብንማጸን የባዕድ አምልኮ ዘርፍ የሆነውን ሟርት መፈጸማችን ነው፡፡ የምንጠራቸውን መናፍስት ወይም ነፍሳት በመምሰል ራሳቸውን የለወጡ ውዱቃን መላእክት እንደሚቀርቡንና እንደሚያታልሉን የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል፡፡ ሳኦል ወደ ሟርተኛ ሴት ዘንድ ሄደና የሞተውን ሳሙኤልን እንድትጠራለት ጠየቃት፤ ጠራችለትም፡፡ ሳሙኤል በሰው ጥሪ አይመጣም፤ የመጣው ግን ራሱን በሳሙኤል መልክ ያቀረበ መንፈስ ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር ብቻ ሊቀርብ የሚገባውን ሁሉ ለራሱ ማድረግ የሚወደው ሰይጣን አጋጣሚውን ይጠቀምበታል፡፡ ልብ እናድርግ በሟርተኛዋ ጥሪ  የተገለጸው መንፈስ ሳሙኤል ነኝ በማለት ራሱን ሲያስተዋውቅ ሳኦል ሰገደለት (1ሳሙ. 28፥3-19፤ 2ቆሮ. 11፥14-15)፡፡

1.1-ሠ. ለመሆኑ የሞቱ ዘመዶቻችን ነፍሳት የት ይኖራሉ?

ከዐጸደ ሥጋ ወደ ዐጸደ ነፍስ የተዛወሩ (የሞቱ) ሰዎች ነፍሳት በገነት ወይም በሲኦል ይቀመጣሉ፤ ይጠበቃሉም፡፡ ፍርድ እስኪሰጥ ድረስ የጻድቃን ነፍሳት በገነት ሲያርፉ፥ የኀጥኣን ነፍሳት ግን በሲኦል ይጋዛሉ እንጂ እንደ አልዓዛር (የእነ ማርታ ወንድም) በተኣምር ካልተነሡ በቀር ከሁለቱም ስፍራዎች ቢሆን አምልጠው በመውጣት በሕይወተ ሥጋ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ጋር ግንኙት መፍጠር የሚችሉ የሉም፡፡ በሕይወተ ሥጋ በነበሩበት ጊዜ ይፈጽሙት የነበረውን አስነዋሪ ተግባር ያልሞቱ ዘመዶቻቸው እንዳይሠሩ ለመምከር እንኳ አይችሉም (ሉቃ. 23፥42-43፤ ራእ. 6፥9-11፤ ሉቃ. 16፥22-30)፡፡

1.1-ረ እንግዲያስ ጸሎት ወደ ማን?

ክርስቲያን እንደ መሰለው ጸሎትን በማቅርብ ለፍቶ መና እንዳይሆን፤ በመሳሳትም ወደ መናፍስትና ወደ ሙታን ዘመዶቹ ነፍሳት በመጸለይ ከሰይጣን ጋር እንዳይቈራኝ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛውን የጸሎት አድራሻ አሳውቆናል፡፡ “እናንተስ ስትጸልዩ እንደዚህ በሉ፡፡ አባታችን ሆይ!” ትክክለኛው ጸሎት የሚቀርብለት ባለሥልጣን እግዚአብሔር አባታችን ነው (ማቴ. 6፥9፤ ሉቃ. 11፥12፤ መዝ. (65)፥1-2 (66)፥1-4)፡፡

1.2.   የጸሎትን መላኪያ መንገድ (ምዕራገ ጸሎትን) ማወቅና መጠቀም፡፡

እግዚአብሔርና ሰው በሁለታቸው መካከል ባለው፥ መካከለኛቸው በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ተገናኝተዋል ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርና ሰው በአንድ አካል የተገናኙበትና የተዋሐዱበት “አማኑኤል” ነውና፡፡ (ማቴ. 1፥23)፡፡ እርሱ እግዚአብሔር በመሆኑ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ከኀጢአትም በቀር ሁለንተናችንን ገንዘብ አድርጓልና ፍጹም ሰው ነው (1ጢሞ. 2፥3-5)፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና ሰው መሆን በቅዱስ እግዚአብሔርና በኀጢአተኛው የሰው ዘር መካከል የማይፈርስ ዝምድናን አስገኝቶልናል፡፡ አዎን! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር በተገናኘበት ሥጋና ደሙ ስለ ኀጢአታችን ተሠዋ፡፡ ለኀጢአት ሥርየት የፈሰሰውን የአንድያ ልጁን ንጹሕ ደም የተመለከተው እግዚአብሔር አምላካችን በልጁ በኩል ለሚቀርቡት ሁሉ ኀጢአታቸውን ላለመቊጠር የዘላለም ቃል ኪዳን አቆመ (ዕብ. 9፥11-12፤ 10፥11-16፤ 7፥23-28)፡፡
ስለዚህ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ የሁለታችንን ዝምድና ያስገኘውን የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም እንጠራለን፡፡ “በአሐዱ ወልድከ” በማለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብሎ ጸሎታችንን እንዲቀበልልን በዚህ ታላቅና ቅዱስ ስም አምላካችንን እናማጸናለን (ዮሐ. 14፥6፡13፡14፤ 15፥16፤ 16፥23፡24፤ ኤፌ. 5፥19-20፤ ቈላ. 3፥17)፡፡

1.3.   ከጸሎት አካባቢ መወገድ ያለባቸውን ማስወገድ

ጸሎት ከፍጡር ለፈጣሪ፥ ከልጅ ለአባት፥ ከበታች ለበላይ የሚቀርብ ምስጋና፥ ልመና፥ ምልጃ … መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ጸሎትን የመቀበል ሁነኛ ባለሥልጣን እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ማወቅና ጸሎትን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም (በኩል) ማቅረብ የግንኙነት መሥመሩን የተስተካከለ፣ የጠራና የሠመረ ያደርገዋል፡፡ የሚያስፈልገው ተጨማሪ ነገር ከአካባቢው መሰናክሎችን በማስወገድ ለመሥመሩ ጥበቃና ጥንቃቄ ማድረግ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሰናክሎቹን በመጠቈም ስለ ማስወገጃ ዘዴዎች አጠቃቀም መመሪያ ይሰጠናል፡፡ 

1.3.1 ጸሎትን ለታይታ ማድረግ፤ አንደኛ መሰናክል

ፈሪሳውያን ሲወቀሡ፥ ሲገሠጹ፥  በወንጌላት ውስጥ ደጋግመን እናነባለን፡፡ ለሚወቀሡበት ጒድለት ሁሉ ምንጩ ግብዝነታቸው ነበር፡፡ ግብዝነት ማለት የሆኑትን መደበቅና ባልሆኑት መልክ መታየት፤ ያደረጉትን ትንሽ መልካም ሥራ ከመጠን በላይ ጐልቶ እንዲታይ መሞከር፤ የተደረገውን ጕልሕ ክፋት እንዳይታወቅ ወይም አንሶ እንዲታይ ማለባበስ፤ ወዘተርፈ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል፡፡

መንገደኞች በብዛት በሚተላለፉባቸው አውራ መንገዶችና አደባባዮች፥ በምኵራቦችም ከፍተኛ ስፍራዎች በመቆም መጸለይ የፈሪሳውያን ወግ ነበር፡፡ ዐላማቸው በሰዎች ለመታየት፥ እንዴት ያሉ ጸሎተኞች ናቸው ለመባልና ለመከበር ሲሆን፥ በጸሎታችሁ ዐስቡን ከሚሉ ሰዎችም ጥቅምን (የአትርሱኝ ስጦታን) መፈለግ ሌላው የጸሎታቸው ዐላማ ነበር (ማቴ. 23፥14)፡፡

የፈሪሳውያን ጸሎት ዕውቅ አድራሻ አምላክ አልነበረም፤ ሰው እንጂ፡፡ ሥርዐትና ወግ እንጂ እንዳለሙት እንደ መሻታቸው ከሰዎች ከበሬታን ተደናቂነትንና ጥቅምን ከመቀበል በቀር ከአምላክ የሚሰጣቸው ምንም የለም፡፡ “እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡” (ማቴ. 6፥5)

የእንቅፋቱ ማስወገጃ ዘዴ “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ፥ መዝጊያህንም ዝጋና በስውር ለሚያይ አባትህ ጸልይ፡፡ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጽ ይሰጥሃል፡፡” (የጸሎትህን መልስ) (ማቴ. 6፥6)፡፡

1.3.2እንደ አረማውያን ነገር ማብዛት

ሁለተኛው መሰናክል አረማውያን እንደ ፈሪሳውያን እግዚአብሔርን ብቻ አያመልኩም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትንም አያውቁም፡፡ ለአረማውያን የእውነተኛ አምላክ መኖር በኅሊናቸው ርግጠኛ ሆኖ ይሰማቸዋል፡፡ ዳሩ ግን በፍጥረቱ የሚታወቀውን በኅሊናቸውም የተረጋገጠላቸውን ፈጣሪ ብቻ ማምለክ ሲገባቸው፥ የፈጣሪን ፍጥረትና የራሳቸውንም የፈጠራ ውጤቶች (ምርቶች) የፈጣሪ ተጨማሪ በማድረግ ያመልካሉ (መዝ. (115)፥4-9)፡፡
እንዲህ ያለውን ልማድ ከአረማውያን የወረሱትን ሕዝበ እስራኤል አንድ ጊዜ ኤልያስ እንዲህ አላቸው እግዚአብሔርንና በኣልን በአንድነት በማምለክ እስከ መቼ ድረስ ትበድላላችሁ? ወይ እግዚአብሔርን ብቻ፤ ወይ በኣልን ብቻ አምልኩ (1ነገ. 18፥20-21)፡፡

አረማውያን አማልክቶቻቸው በቃላት ብዛት የሚሰሟቸው እየመሰላቸው በሚጣፍጡ ተደጋጋሚ ቃላት የጸሎት ድርሳኖችን ከምሁራኖቻቸው ያጠናሉ፡፡ የሚያሳዝን፥ የሚማርክ፥ ልብን የሚያራራ የሚመስል ቃል በጸሎቱ ውስጥ ሲኖር ተደጋግሞ (3፣ 7፣ 12፣ 49፣ 72፣ 150… ጊዜ) ይጸለያል፡፡ ድግምቱም ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ አባባሉን በይበልጥ ለመረዳት 1ነገ. 18፥18-35ን ማንበብ ይቻላል፡፡ የበኣል ነቢያት ከነግህ እስከ ሠርክ ጣዖታቸውን በሚያባብል ቃልና ውዝዋዜ ሲጸልዩ እንደ ዋሉና መልስ ግን እንዳላገኙ ምንባቡ ያስረዳል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአረማውያንን ሥርዐተ ጸሎት ሲነቅፈው የመናገርን ብዛት “ከንቱ ድግምት” ብሎታል (ማቴ. 6፥7)፡፡
የመሰናክሉ ማስወገጃ ዘዴ፥ ሰማያዊ አባትህ የሚያስፈልግህን ያውቃልና፥ ነገር አታብዛ፤ ከንቱ ድግምት አታነብንብ (ማቴ. 6፥8)፡፡ ሳይታክቱ መጸለይ ሁል ጊዜ በየቀኑ መጸለይን እንጂ ነገር ማብዛት ወይም መዘብዘብ ማለት አይደለምና (ሉቃ. 18፥1-8)፡፡
ድግምት ማለት የራስን ጒዳይ ለመግለጽ ከልብ ያልወጣ፥ ነገር ግን የተጠና የጸሎት ድርሰትን ማነብነብ፤ እንዲያው በልማድ ከናፍርንና ምላስን ማንቀሳቀስ (ጅምናስቲክ ማሠራት)ነው፡፡ እስኪ የበኣልን ነቢያትና የእግዚአብሔርን ነቢይ የኤልያስን ሁኔታ እናስታውስ፡፡ የበኣል ነቢያት ከነግህ እስከ ሠርክ በከንቱ ሲደግሙ ከዋሉ በኋላ ኤልያስ ቦታውን ተረከበና በተራው ጸለየ፡፡ ጸሎቱ ከሁለትና ሦስት ዐረፍተ ነገሮች የበለጠ አልያዘም፡፡ ነገር ግን በከንቱ የተደገመ ንባብ አልነበረም፤ ለእግዚአብሔር እውነተኛ ፍቅር ካለው ልብ ተጨምቀው በወጡ ቃላት የተገነባ ጸሎት ነበር፡፡ ስለ ሆነም ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር መልስ ተሰጠው (1ነገ. 18፥36-39)፡፡

1.4.   በጸሎት መክፈቻዎች መጠቀም

የጸሎት እልፍኝ ልጅ ከአባቱ ጋር ለውይይት የሚገባበት ምስጢራዊ መገናኛ ነው፡፡ ወደዚህ እልፍኝ በመንፈስ መግባት ያስፈልጋል፡፡ የጸሎት ማድረስ ሥርዐት የሚከናወነው በመንፈስ ነውና (ኤፌ. 6፥18፤ ይሁ. 20-21)፡፡ በመንፈስ ወደ ጸሎት እልፍኝ ለመግባት ሁለት የቊልፍ መክፈቻዎችን መጠቀም ግዴታ ነው፡፡

1.4.1 አንደኛው መክፈቻ እምነት ነው
ጸሎታችንን የሚያዳምጥ መልስም የሚሰጠን አምላክ እንዳለን ልናምን ይገባል፡፡ ስለ ሆነም ገና ከጸሎት እልፍኛችን ስንወጣ የጸለይንበትን ሁሉ እንደ ተቀበልን ርግጠኞች መሆን አለብን (ዕብ. 11፥6፤ ማር. 11፥22-24፤ ያዕ. 1፥7፡8)፡፡
1.4.2. የሁለተኛ መክፈቻ ይቅርታ ነው፡፡
የምስጋና መሥዋዕት፥ ወይም የኀጢአት ኑዛዜ፥ ወይም ምልጃ የማቅረብ ፍላጎት ቢኖረን፥ ይህን ከመፈጸማችን በፊት ከበደልነው ሰው ጋር መታረቅን አንርሳ፡፡ በደለን በማለት የተቀየምነው ቢኖርም ይቅርታ ልናደርግለት ይገባል፡፡ በዝንጋታ ይህን ሳናደርግ ቈይተን ከሆነና ጸሎት ለማድረስ ስንዘጋጅ፥ ወይም በማድረስ ላይ እያለን ይቅር ያልተባልንበትም ሆነ ይቅር ያላልንበት በደል መኖሩ ትዝ ካለን፥ ጸሎቱን ማቋረጥና ሁኔታዎችን ማስተካከል፥ ከዚያ በኋላ ጸሎቱን መቀጠል እንደሚገባን ጌታችን አስተምሮናል (ማቴ. 5፥23-24፤ ማር. 11፥25-26)፡፡
በእነዚህ በሁለት መክፈቻዎች የጸሎት እልፍኛችንን በር ሳንከፍት፥ እኛና እግዚአብሔር በአንድ መንፈስ ወደምንገናኝበት መገናኛ ለመግባት መሞከር ግምብ በመግፋት በከንቱ እንደ መድከም ይቈጠራል፡፡

1.5.   የቀድሞ ሰዎችን ጸሎት መድገም እንደ ጸሎት ይቈጠራልን?

ሞገስና ተካልኝ በአንድ መሥሪያ ቤት አብረው ይሠሩ ነበር፡፡ ሞገስ የአካባቢው አየር ስላልተስማማው በሐኪም ወደ ተመረጠለት ክፍለ ሀገር ተዛውሮ እዚያ በነበረው የመሥሪያ ቤቱ ቅርንጫፍ ውስጥ ለመሥራት እንዲፈቀድለት አመለከተ፡፡ ጥያቄው በማስረጃ የተደገፈ ሆኖ ተገኘና፥ በቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱም ለሞገስ ችሎታና ደረጃ የሚመጥን ክፍት የሥራ መደብ መኖሩ ተረጋገጠና ዝውውሩ ተፈቀደለት፡፡

ተካልኝም ከሞገስ ቀጥሎ በሚገኝ የሥራ ደረጃ ላይ ነበረ፡፡ የተለቀቀው ሥራ መደብ ይሰጠው ዘንድ እንዲጠይቅ ሞገስ ተካልኝን መከረው፡፡ ተካልኝም እንደ ተመከረው ለመፈጸም ወሰነ፡፡
በቃላት አመራረጥና አገባብ በሐረጎችና በዐረፍተ ነገሮች አሰካክ የተዋጣለትን የሞገስን ማመልከቻ ደጋግሞ አነበበው፤ ንባቡ ለጆሮውም ለአንደበቱም ጣፈጠው፡፡ አንድ ቀን ጧት የዋሁ ተካልኝ ወደ መሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣን ቀረበና ገልብጦ የያዘውንና ደጋግሞ በማንበብ በቃል ያጠናውን የሞገስን ማመልከቻ አነበበላቸው፡፡ ምን ተብሎ ይሆን?

የሰዎች መሻት የተለያየ ነው፤ እንደየችግራቸውና እንደየመሻታቸው መጸለይ ይገባቸዋል፡፡
“ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” (1ነገ. 3፥5)
“የልቡን መሻት ሰጠኸው” (መዝ. (21)፥2)
“አንዳች ብንለምን ይሰማናል” (1ዮሐ. 5፥14)

ሆኖም የአባቶች ጸሎትና የጸሎት ታሪክ ለጸሎት አካላት አወቃቀር ከፍተኛ ልምምድንና ጥንካሬን እንደሚሰጠን አይጠረጠርም፡፡

1.6.   ለጸሎት የተለየ ስፍራንና ጊዜን መወሰን ይገባልን?

እግዚአብሔር መንፈስ ስለ ሆነ ምንጊዜም በየትም ሥፍራ ወደ እርሱ የሚጮኹትን ሁሉ ለማዳመጥ ዝግጁ በመሆኑ ለጸሎት ጊዜንና ሥፍራን መለየት አያስፈልግም (ዮሐ. 4፥20-24፤ መዝ. (24)፥1፤ ኤር. 23፥23-24)፡፡ እንዲህም የምንለው ስለ እስራኤል ዘመንፈስ (ስለ ክርስቲያን) ነው፡፡ ስለ እስራኤል ዘሥጋ ከሆነማ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ፥ በዚያ መናዘዝ፥ በዚያ የኀጢአትና የምስጋና መሥዋዕት ማቅረብ እንዲገባቸው ተጽፎ የለምን? (ዘዳ. 12፥1-18)፡፡

ለአንዳንዶች ሰዎች የእስራኤል ቤተ መቅደስና ቤተ ክርስቲያን ልዩነት የሌላቸው ይመስላቸዋል፤ አንድ የሚያደርጋቸው መሠረታዊ ነጥብ ግን ፈጽሞ የለም፡፡ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሁለትና ከዚያም በላይ የሆኑ ክርስቲያኖች በተሰበሰቡበት ስፍራ ቤተ ክርስቲያን ሊኖር ይችላል፡፡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያን ኅብረት ወይም ጉባኤ ነው ሲባል ቦታንና ሕንጻን አያመለክትም፡፡

በዚሁ መሠረት የመጀመሪዎቹ ክርስቲያኖች ለጸሎት ለአምልኮትና ቃሉን ለማጥናት ይሰበሰቡ የነበረው ቦታን ሳይመርጡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኤጲስ ቆጶሳትና ዲያቆናት የነበሯት የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በወንዝ ዳር አምልኮአቸውን ይፈጽሙ ነበር (ፊል. 1፥1፤ ሐ.ሥ. 16፥11-13)፡፡ ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናት በሰዎች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተቋቁመው ነበር (ሮሜ 16፥5፤ 1ቆሮ. 16፥19፤ ፊልሞና 2)፡፡ የእስራአል ቤተ መቅደስ በነበረበት በኢየሩሳሌም እንኳ ቤተ ክርስቲያን ተቋቁሞ ነበር (ሐ.ሥ. 15፥4)፡፡

ጌታ ሆይ! ስንጠፋ አይገድህምን? እስከ ማለት ድረስ የጸሎት መብት ስለ ሰጠኸን ተመስገን!! አንዳች ለሌለን ምስኪኖች፥ አንዳች መልካም ነገር መሥራት ለተሳነን ደካሞች፥ ባሰብነው፥ በተናገርነው፥ በሠራነውም በደል ለተቈጠረብን ኀጢአተኞች እንድንጸልይ ባታስተምረን ኖሮ በተስፋ መቊረጥ ረግረግ ውስጥ የተጣልንና የተረሳን በሆንን ነበር፡፡

ይቀጥላል፡፡

3 comments:

  1. ጥሩ ስለሆነ እግዚአብሔር አምላክ ይባረክች ጸጋውን ያብዛለችው

    ReplyDelete