የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ
ከነቅዐ ጥበብ
ካለፈው የቀጠለ
በፍሬምናጦስ ትጋት፥
በኢትዮጵያ በተቋቋመችው የእግዚአብሔር መንግሥት ወይም ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ውስጥ በዘመኑ ከተፈጸሙት ድንቅ ሥራዎች መካከል ሳይመዘገቡ
የታለፉ፥ ተመዝግበው ከነበሩትም በቅብብሎሽ (በትውፊት) እንኳ ዘመናትን አቋርጠው ከእኛ ዘንድ ሳይደርሱ ከጊዜ ርዝመትም ከሁኔታዎች
መለዋወጥም የተነሣ በዘመናት እርከናት ላይ እየወደቁ የተረሱና እንዳልነበሩ የሚቈጠሩ እጅግ ጠቃሚ የሥራ ውጤቶች በብዛት ሊኖሩ እንደሚችሉ
ይታሰባል፡፡ የሚታወሱት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት እንደ ሆኑ ይታመናል፡፡
1.
መካሪ፥ አበ ነፍስ፥
ወይም አበ ንስሓ መመደብ
በኢትዮጵያ ክርስትናን
የተቀበለው ሕዝብ እንደ ማንኛውም ሌላ ሕዝብ ኑሮው የተመሠረተበትን የዕለት ተዕለት ሥራ የእደ ጥበብ፥ የግብርናና የንግድ ሥራን
ለመከታተል ያመቸው ዘንድ ቦታ እየመረጠ ተበታትኖ የሰፈረ በመሆኑ፥ በቅዱሳት መጻሕፍት ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንደ ነበራቸው እንደዚያ
ጊዜ ዲያቆናት፥ ቀሳውስት፥ ጸሐፍት… ትምህርተ እምነታቸውን ለማሳደግ ሁኔታው ያላመቻቸው ክርስቲያኖች፥ ብዙኃን እንደ ነበሩ በእግረ
ልቡና ወደ ኋላ ተመልሶ ግምት መውሰድ ይቻላል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም እንደ አኹኑ በየሰው እጅ የሚገቡበት ዕድል አልነበረም፡፡ የማንበብና
የመጻፍም ችሎታ የጥቂት ሰዎች መታደል ብቻ ሆኖ ይቈጠር ነበር፡፡ በእነዚህና በመሳሰሉ ምክንያቶች የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድ
ከምሁራኑ መካከል በየመንደሩና በየቀበሌው መካሪና አስተማሪ አድርጎ መመደብ ጊዜያዊ መፍትሔ ሆኖ ተገኘ፡፡