“ከሕፃንነትህም
ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን ዐውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይኾን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ኹሉ
ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” (2 ጢሞ. 3፥15-17)፡፡
አንዳንዶች
ይህን ጥቅስ ሲያነቡ ወይም ሲነበብ ሲሰሙ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ወይም ዛሬ ላይ ኾነው ከአጠቃላዩ መጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ በአእምሮአቸው
ውስጥ በቶሎ የሚከሠቱት አዋልድ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ይህም የኾነው ጥቅሱ ስለ አዋልድ መጻሕፍት የተጻፈ ስለ ኾነ አይደለም፤
አንዳንድ ሰዎች ጥቅሱን ደግመው ደጋግመው ስለ አዋልድ መጻሕፍት እንደ ተነገረ አስመስለው በአፍም በመጣፍም ስለሚጠቅሱት ነው
እንጂ፡፡ “ዓምደ ሃይማኖት” የተሰኘ መጽሐፍ ይህን ጥቅስ ይጠቅስና፥ “እንግዲህ ድርሳናትም ኾኑ ገድላት ስለ እግዚአብሔር
አዳኝነት፣ ታላቅነት የሚገልጹ ስለ ኾነ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መኾናቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ ጳውሎስ ስል[ድ]ሳ
ስድስቱን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ተጠቀም አላለም፡፡ ገደብ ሳያደርግ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው በቅዱሳን አባቶችም ኾነ
በሌሎችም ክርስቲያኖች የተጻፉትንም መንፈሳዊ መጻሕፍት አለ እንጂ፡፡” ይላል (ብርሃኑ ጎበና 1995፤ ገጽ 37)፡፡
ምንም እንኳ
መጽሐፉ የጳውሎስን መልእክት በማብራራት ስም ጳውሎስ ያላለውንና ሊል ያልፈለገውን ሐሳብ፣ እንዳለ አስመስሎ ቢያቀርብም፣ በዚህ
ጽሑፍ የምናብራራው የጳውሎስ መልእክት ይህን ሐሳብ የሚቃረን እንጂ የሚደግፍ አይደለም፡፡ እርሱ እየ ተናገረ ያለው፦ “ክርስቶስ
ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ” ስለሚሰጡት ቅዱሳት መጻሕፍት ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት መዳን የሚገኝበትን
ጥበብ ብቻ ሳይኾን ድኅነትን የተቀበለ የእግዚአብሔር ሰው “ፍጹምና ለበጎ ሥራ ኹሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ … ለትምህርትና ለተግሣጽ፥
ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” የሚጠቅሙ ናቸው፡፡