Monday, February 22, 2016

ፍካሬ መጻሕፍት

ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን ዐውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይኾን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ኹሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” (2 ጢሞ. 3፥15-17)፡፡
አንዳንዶች ይህን ጥቅስ ሲያነቡ ወይም ሲነበብ ሲሰሙ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ወይም ዛሬ ላይ ኾነው ከአጠቃላዩ መጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ በአእምሮአቸው ውስጥ በቶሎ የሚከሠቱት አዋልድ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ይህም የኾነው ጥቅሱ ስለ አዋልድ መጻሕፍት የተጻፈ ስለ ኾነ አይደለም፤ አንዳንድ ሰዎች ጥቅሱን ደግመው ደጋግመው ስለ አዋልድ መጻሕፍት እንደ ተነገረ አስመስለው በአፍም በመጣፍም ስለሚጠቅሱት ነው እንጂ፡፡ “ዓምደ ሃይማኖት” የተሰኘ መጽሐፍ ይህን ጥቅስ ይጠቅስና፥ “እንግዲህ ድርሳናትም ኾኑ ገድላት ስለ እግዚአብሔር አዳኝነት፣ ታላቅነት የሚገልጹ ስለ ኾነ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መኾናቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ ጳውሎስ ስል[ድ]ሳ ስድስቱን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ተጠቀም አላለም፡፡ ገደብ ሳያደርግ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው በቅዱሳን አባቶችም ኾነ በሌሎችም ክርስቲያኖች የተጻፉትንም መንፈሳዊ መጻሕፍት አለ እንጂ፡፡” ይላል (ብርሃኑ ጎበና 1995፤ ገጽ 37)፡፡
ምንም እንኳ መጽሐፉ የጳውሎስን መልእክት በማብራራት ስም ጳውሎስ ያላለውንና ሊል ያልፈለገውን ሐሳብ፣ እንዳለ አስመስሎ ቢያቀርብም፣ በዚህ ጽሑፍ የምናብራራው የጳውሎስ መልእክት ይህን ሐሳብ የሚቃረን እንጂ የሚደግፍ አይደለም፡፡ እርሱ እየ ተናገረ ያለው፦ “ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ” ስለሚሰጡት ቅዱሳት መጻሕፍት ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ብቻ ሳይኾን ድኅነትን የተቀበለ የእግዚአብሔር ሰው “ፍጹምና ለበጎ ሥራ ኹሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ … ለትምህርትና ለተግሣጽ፥ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” የሚጠቅሙ ናቸው፡፡

የቅዱሳት መጻሕፍት ማእከላዊ መልእክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ጌታችን ለአይሁድ ሲናገር፣ እነርሱ በቅዱሳት መጻሕፍት የዘላለም ሕይወትን እንደሚያገኙ በማሰብ መጸሕፍቱን የሚመረምሩ ቢኾንም፥ መጻሕፍቱ ስለ እርሱ የሚመሰክሩ መኾናቸውን ግልጽ አድርጓል (ዮሐ. 5፥39)፡፡ ስለዚህ ሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን (መጽሐፍ ቅዱስን) እንደ እግዚአብሔር ቃል  ካነበበ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን የሚድንበትን ዕውቀት ያገኛል፡፡ ቀጥሎም ለክርስቲያናዊ ኑሮው የሚያስፈልገውን ምክርና መመሪያ ያገኛል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀር መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጥ የሚችል ሌላ መጽሐፍ የለም፡፡ አለ ቢባል እንኳ ይህን ጥበብ የወሰደው ከመጽሐፍ ቅዱስ መኾን አለበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው የመዳን ትምህርት የማያሳስትና ‘ይህም ያድናል፤ ያም ለመዳን ይጠቅማል’ በሚል የማያምታታና ግልጽ ነው፡፡ የኀጢአተኛውንም ልብ ያሳርፋል፡፡ የበጎ ሥራን ምንነት ከማስተማሩም በላይ፥ ለበጎ ሥራም ኹሉ ያዘጋጃል፡፡ ልብን ያቀናል፤ በጽድቅም ላለው ምክር ይጠቅማል፡፡
ጥቅሱን ከመልእክቱና ከዐውዱ ውጪ ማናገር
መነሻችን የሆነው 2 ጢሞ. 3፥15-17 የሚናገረው ስለ ብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ኾነን ስንናገር ደግሞ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍትን ብቻ ሳይኾን፥ የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ጭምር ነው “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ” የምንለው፡፡ በመነሻው ላይ የተጠቀሰው “ዐምደ ሃይማኖት” የተሰኘው መጽሐፍ ግን ይህን ክፍል ይጠቅስና አዋልድ መጻሕፍትን ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ደረጃ ከፍ ያደርግበታል፡፡
ይህን ጥቅስ ለማብራራት “ዐምደ ሃይማኖት” ባሰፈረው ጽሑፍ ውስጥ አንድም እውነት የለም፡፡ ድርሳናትም ሆኑ ገድላት ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ የሚስማማቸውን ንባብ ቢጠቅሱም፣ ማእከላዊ ሐሳባቸው ግን የእግዚአብሔርን አዳኝነትና ታላቅነት መግለጽ ሳይኾን፣ ድርሳኑ ወይም ገድሉ በስማቸው የተጻፈላቸውን መላእክት ወይም ጻድቃንና ሰማዕታትን ማንነት እጅግ አጋንኖ አምላክ-አከል አድርጎ በማቅረብ፣ አንባቢውን ወደ እነርሱ የሚስብና በአዳኝነታቸውና በተራዳኢነታቸው እንዲማጸን የሚያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ድርሳነ ሚካኤል በያንዳንዱ ክፍል በዋናነት የሚካኤልን ታላቅነትና አዳኝነት የሚናገር ነው፡፡ በኅዳር ድርሳን ላይ ሰው ሊድን የሚችልበትና አማራጭ የሌለው ያለውን ሌላ መንገድ ያሳያል፤ እንዲህ በማለት፦ “ኦ አኀውየ አልቦኬ ዘይረክብ ሰብእ ግሙራ ተስፋ ድኂን ወመዊእ ወረድኤት እንበለ ትንብልናሆሙ ወአስተብቍዖቶሙ ለትጉሃነ ሰማይ መላእክት፡፡ - ወንድሞቼ ሆይ በሰማይ ተግተው በሚኖሩ በመላእክት ምልጃና ልመና ካልኾነ በቀር የመዳን ተስፋ፣ ድል ማድረግና ረድኤት የሚያገኝ ሰው ፈጽሞ የለም” (ድርሳነ ሚካኤል 1964፣ ገጽ 6)፡፡ ይህ ንባብ በተሐድሶኣዊ ጽሑፎች ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑ በተደጋጋሚ ስለ ተተቸ ግን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚታተመው ድርሳን ውስጥ፣ “ኦ አኀውየ ኵሉ ሰብእ ዘይረክብ ተስፋ ድኂን ወመዊእ ወረድኤት በትንብልናሆሙ ወበአስተብቍዖቶሙ ለትጉሃነ ሰማይ መላእክት፡፡ - ወንድሞቼ ሆይ በሰማይ ተግተው በሚኖሩ በመላእክት ምልጃና ልመና ረድኤትን፣ ድል ማድረግን የድኅነት ተስፋን ያገኛል” (ድርሳነ ሚካኤል 1989፣ ገጽ 4) በሚለው ንባብ እንዲለዝብ ተደርጓል፡፡ ይህም ቢኾን የስሕተቱ ጠንካራነት እንዲለዝብ ተደረገ እንጂ ስሕተትነቱ አልተለወጠም፡፡ ይህን ያነበበ ሰው ታዲያ ለድርሳነ ሚካኤል ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መኾኑ የተረጋገጠ ነው’ የሚለው እንደማይስማማው በቀላሉ አይገነዘብምን?
“… ጳውሎስ ስል[ድ]ሳ ስድስቱን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ተጠቀም አላለም፡፡ ገደብ ሳያደርግ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው በቅዱሳን አባቶችም ሆነ በሌሎችም ክርስቲያኖች የተጻፉትንም መንፈሳዊ መጻሕፍት አለ እንጂ፡፡”  የሚለው የዐምደ ሃይማኖት ድምዳሜም ቅዱስ ቃሉን ለራስ ሐሳብ ማመቻቸት ካልኾነ በቀር፣ ማንም ተነሥቶ የሚጽፈውን መጽሐፍ ኹሉ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ” ለማለት ፈቃድ መስጫ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቍጥር መቀነን (መወሰን) ያስፈለገበት አንዱ ምክንያትም በነቢያትና በሐዋርያት ስም አያሌ መጻሕፍተ ሐሰት እየ ተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት መስለው ወደ ቤተ ክርስቲያን በሥርዋጽ እንዳይገቡ ለመከላከል መኾኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት እንደሚመሰክሩት፣ ቤተ ክርስቲያን እንድትቀበላቸው የታዘዙት መጻሕፍት ብቻ አልነበሩም “ቅዱሳት አምላካውያት” ወዘተ. እየ ተባሉ ይጠሩ የነበሩት፤ ነገር ግን እነዚህን ቅጽሎች ይዘው የተሠራጩ፣ ነገር ግን “ቅዱሳት መጻሕፍት” ያልነበሩ፣ ዛሬም ያይደሉ፣ ብዙ መጻሕፍተ ሐሰት ነበሩ፡፡ “የአንድ ቅዱስ መጽሐፍ እውነተኛ አምላካዊነት … አምላካዊ ሆኖ መገኘት የሚረጋገጥበት ቅድመ መመዘኛ ‘ቅዱስ’ የሚለውን ቅጽል” መያዙ ሳይኾን፣ “ይዘቱና መንፈሱ አምላካዊ - የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት /የተቃኘበት መጽሐፍ ኾኖ መገኘቱ ነው፡፡ (2ጢሞ. 3፥16-17)” (ዲበኩሉ ዘውዴ፣ 81 ቅዱሳት መጻሕፍትና ምንጮች-ቀኖናት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ 1987፣ ገጽ 25፡25)፡፡
ፍትሐ ነገሥትም ከቅዱሳት መጻሕፍት ውጪ የኾኑ መጻሕፍት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ ለመከላከል “ቅዱሳት” የተባሉትን መጻሕፍት ዝርዝር ካቀረበ በኋላ (አንዳንድ የብሉይ አዋልድን ጨምሯል)፣ “እንድትጸኑባቸው ያዘዝናችሁ መጻሕፍት እሊህ ናቸው፡፡ ከሓድያን ከአስቀመጧቸው የሐሰት መጻሕፍት የወሰደና ንጽሕት የኾነች የእግዚአብሔር መጽሐፍ እንደ ኾነች አድርጎ ሕዝብን ለማሳሳት ወደ ቅዱስ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ያገባ ሰው ቢኖር ይለይ” ይላል (አንቀጽ 2 ቍጥር 19)፡፡ በዚህ መመዘኛ መሠረት ገድላትና ድርሳናት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገቡ ዘንድ የሚፈቀድላቸው አልነበረም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ሊቃውንት እንደነዚህ ያሉትን መጻሕፍት “በበር በኩል ያልገቡ አንዳንድ ጕሕልያዎች (ቀጣፊዎች) የሰነቀሩአቸው ናቸው” ብለው እንደሚሠርዟቸውና አሜን ብለው እንደማይቀበሏቸው ይናገራሉ (መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት 1988፥ ገጽ 156)፡፡
ጥቅሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያሉትን መጻሕፍት የማይሸፍነው ለምንድን ነው?
1.    የሚሰብኩት የመዳን መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ነው
በ2ጢሞ. 3፥15 መሠረት አዋልድ መጻሕፍት “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው” መጻሕፍት ተብለው ለመጠራት ብቃት አላቸው ወይ? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ከሐሰተኞቹ መጻሕፍት ተለይተው በቀኖና ከተወሰኑ በኋላ የተደረሱ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በይዘታቸውና በሚያስተላልፉት ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክትም ጭምር “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው” መጻሕፍት ለመባል ብቁ አለ መኾናቸው ይታወቃል፡፡ አዋልድ መጻሕፍት የሚሰብኩት ሐዋርያው ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት በገለጸው መሠረት፣ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን የሚገኘውን መዳን ሳይኾን፣ ድርሳኑ ወይም ገድሉ በተጻፈለት መልአክ ወይም ጻድቅና ሰማዕት በመማጸንና በስማቸው ልዩ ልዩ ነገሮችን በማድረግ ስለሚገኘው “ጽድቅ” ነው የሚሰብኩት፡፡ ይህ ደግሞ መንፈሳዊ መስሎ ይቅረብ እንጂ ሐዋርያት ከሰበኩት ወንጌል የሚለይ በመኾኑ የተወገዘ “ልዩ ወንጌል” ነው (ገላ. 1፥6-9)፡፡
ለምሳሌ፦ ተአምረ ማርያም የተባለው መጽሐፍ ክርስቶስን በመስበክ እውነተኛውን የመዳን መንገድ የሚጠቁም ሳይኾን፣ ከዚያ የሚያወጣና በማርያም በኩል መዳን እንደሚገኝ የሚሰብክ ነው፡፡ አንዱን ለማስረጃነት እንመልከት፤ “እንደኔ ያላችሁ ኃጥኣን ወንድሞቼ እንግዲህስ ወዲህ ዐሥራ ስድስቱን ሕግጋት ለመፈጸም የእግዚአብሔር ባሮች መሆንን አንሻ … የእመቤታችን የእናታችን የማርያም ባሮች ለመኾን ፈጽመን እንሽቀዳደም ብዬ እነግራችኋለሁ” (ተኣምረ ማርያም 1985፤ ገጽ /ተኣምር 12 ቊጥር 52 እና 53)፡፡
ይህን በመተቸት ለተጻፈ መጽሐፍ ምላሽ ሲሰጥ የኢኦተቤክ የሊቃውንት ጉባኤ እንዲህ ብሎ ነበር፤ “በጥንታዊው ታምረ ማርያም የብራና መጽሐፍ፣ እንዲህ ያለ ዘር የለም፣ የቤተ ክርስቲያናችንም ትምህርት አይደለም፡፡ ምናልባት አንዳንዶች የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሳይመረምሩት ጽፈዉት ቢገኝም የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት አለ መኾኑን ልትገነዘበው ይገባል፡፡” (ዑቁ ኢያስሕቱክሙ 1996፣ ገጽ 39)፡፡ ይኹን እንጂ፣ በቅርቡ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ለአራተኛ ጊዜ በታተመ ተአምረ ማርያም ላይ፣ “እንደኔ ያላችሁ ኃጥኣን ወንድሞቼ እንግዲህስ ወዲህ ዐሥራ ስድስቱን ሕገጋት ለመፈጸም የእግዚአብሔርን ባሮች መኾንን እንሻ፤ እሱ በቀትር ጊዜ በመስቀል ላይ እመቤታችሁ እናታችሁ እነሆ እያለ የቃል ኪዳን እመቤት እሷን ሰጥቶናልና፡፡ ስለዚህ ነገር የእመቤታችን የእናታችን የማርያም ባሮች ለመኾን ፈጽመን እንሽቀዳደም ብዬ እነግራችኋለሁ”፡፡ በሚል ከንባቡ መንፈስ ጋር የማይሄድ “ማስተካከያ” ተሰጥቶበታል (ተኣምረ ማርያም 2007፣ ገጽ 187)፡፡
“ማስተካከያው” ግእዙ “ኢንኅሥሥ” ዐማርኛው “አንሻ” የሚለውን ቃል፣ “ንኅሥሥ” - “እንሻ” በሚል የተካ ነው፡፡ ይህ “ማስተካከያ” ለእግዚአብሔር በተነገረው ላይ ተገቢ ማስተካከያ ነው፤ ምክንያቱም የቀደመው ንባብ ለእግዚአብሔር ጌትነት እንዳንገዛና የእግዚአብሔር ባሮች እንዳንኾን የሚናገር ነበርና፡፡ ቀጥሎ ለማርያም ከተነገረው ጋር በተያያዘ ግን ሐሳቡ እንዳለ መቀመጡ፣ አኹንም በማዕርግ የሚበላለጡ ኹለት ጌቶች (አንድ ጌታና አንዲት እመቤት) ያሉ ከማስመሰሉም በላይ፣ ለኹለቱ ጌቶች እንደየ ማዕርጋቸው ተገዙ የሚል መልእክት ነው ያለው፡፡ (“ለእኛስ ነገር ኹሉ ከእርሱ የኾነ እኛም ለእርሱ የኾንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ኹሉም በእርሱ በኩል የኾነ እኛም በእርሱ በኩል የኾንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።” (1ቆሮ. 8፥6)፡፡) በአንድ በኩል ለእግዚአብሔር ባሮች መኾንን እንሻ ሲል፣ የማርያም ባሮች ለመኾን ደግሞ እንሽቀዳደም ነው የሚለው፡፡ የትኛው ነው በማዕርግ ከፍ ያለው? ብንል፣ የእርሱ ባሮች መኾንን እንድንሻ ከተነገረለት ከእግዚአብሔር ይልቅ፣ የእርሷ ባሮች ለመኾን እንድንሽቀዳደም የተነገረላት ማርያም ከፍ ያለ ስፍራ እንዳገኘች ማስተዋል እንችላለን፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን፣ አንድ ባሪያ ለኹለት ጌቶች መገዛት አይችልም ብሎ፣ ራሱን ለእግዚአብአብሔር ያስገዛ ሰው ከእግዚአብሔር ውጪ ለሌላ ለማንም መገዛት እንደማይገባው አስታውቋል (ማቴ. 6፥24፤ ሉቃ. 16፥13)፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም አስቀድሞ እርሱና ወገኖቹ፣ ከእግዚአብሔር በቀር ሌሎች ጌቶች እንደ ገዟቸውና አኹን ግን በእርሱ (በእግዚአብሔር) ስሙን እንደሚያስቡ ተናግሯል (ኢሳ. 26፥13)፡፡ ከዚህ አንጻር የተደረገው ማስተካከያ አኹንም ከትችት የሚያመልጥ አልኾነም፡፡
ከትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ይልቅ ቀደም ብሎ በ1983 ዓ.ም. በተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት የታተመው ተኣምረ ማርያም በተጠቀሰው ምንባብ ላይ ከስሕተት ያልወጣ ቢኾንም ማሻሻያ አድርጎ ነበር፡፡ እንዲህ በማለት፣ “እንደኔ ያላችሁ ኃጥኣን ወንድሞቼ እንግዲህስ ወዲህ ዐሥራ ስድስቱን ሕግጋት ከመፈጸም ጋር የእመቤታችን የእናታችን የማርያም ባሮች ለመኾን ፈጽመን እንሽቀዳደም ብዬ እነግራችኋለሁ” (ተኣምረ ማርያም 1983፣ ገጽ 274)፡፡ ይህ ማስተካከያ አምኖ ለዳነ ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ ከመፈጸም ወዲያ ምን ያስፈልገዋል? እግዚአብሔር ያላሸከመው ሌላ ሸክምስ ከሕገ እግዚአብሔር ጋር ተካክሎ ለምን ይጫንበታል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች ይነሡበታል፡፡
በሁለቱም ማተሚያ ቤቶች በታተሙት ተአምረ ማርያም ላይ የተሰጡት ማስተካከያዎች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው የተሰጡ ባለ መኾናቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር መጋጨታቸው አልቀረም፡፡ ማስተካከያው በተደረገበት መጽሐፍ ላይ፣ ስሕተት ስለ ነበረው የቀደመው ንባብና ለስሕተቱ ስለ ተሰጠው ማስተካከያ፣ በመግቢያው ወይም እዚያው ላይ በእግርጌ ማስታወሻው ላይ የተባለ ነገር አለ መኖሩ፣ የተሰጠው ማስተካከያ፣ ስሕተትን ከማረም አንጻር ታስቦበት፣ ሰው ኹሉ እንዲገነዘበውና ዐቋሙን እንዲያስተካከል ተደርጎ የተሰጠ አለ መኾኑን ያመለክታል፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለው መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረን መጽሐፍ እንዴት ኾኖ ነው ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወለደ የሚባለው?
የተአምረ ማርያም ውላጅ (ደስታ ተክለ ወልድ፣ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣ 1962፣ ገጽ 524) የሆነውና ደባትራኑ በወርኀ ጽጌ ማሕሌት የሚቆሙበት ማሕሌተ ጽጌው ግን ምንም አልተሻሻለምና ይኸው ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ድርሰት በዜማ ይባላል፡፡ እንዲህ የሚለው፦
እመ ተሰቅለ ቍልቍሊተ ወተተክለ በርእሱ
እንበለ ርድኤትኪ መኑ ዘይክል አድኅኖ ነፍሱ
አኮ ድንግል በፈጽሞ ቃላት ስሱ
ለተአምርኪ ድንግል ከመ ይትነከር ሞገሱ
በገነተ ጽጌ ሢምኒ ምስሌኪ አንሶሱ

ቍልቍሊት ቢሰቀል በራሱ ቢተከል
ያለ ረድኤትሽ ነፍሱን ማን ማዳን ይችላል
በመፈጸም አይደል ስድስቱን ቃላተ ወንጌል
የተአምርሽ ሞገሱ ይደነቅ ዘንድ ድንግል
በአበባ ገነት ሹሚኝ ካንቺ ጋር ልንጐማለል
ተኣምረ ማርያም ይህን የመሰለ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረኑ በርካታ እንግዳ ትምህርቶች አሉበትና ከመጽሐፍ ቅዱስ መወለዱ ቀርቶ የቀረበ ዝምድናም የለውም (አግዛቸው ተፈራ (ዲ/ን) የተቀበረ መክሊት 2006፣ ገጽ 180)፡፡
2.   የሚሰብኩት በጎ ሥራ በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም
መጽሐፍ ቅዱስ አምነን ስለምንጸድቅበት እምነት ብቻ ሳይሆን ጸድቀን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለምንሠራው በጎ ሥራ ምንነትም ያስተምራል፡፡ በክርስትና ትምህርት መሠረት መልካም ሥራ ምን እንደ ኾነ የምንማረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልኾነ “በጎ ሥራ” ቢኖር እንኳ ምንጩ ሌላ ነው እንጂ የሚያድነው እምነት መገለጫ ሊኾን አይችልም፡፡ አምኖ የዳነ ሰው መዳኑ የሚታወቅበት በጎ ሥራ ግን ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
በዚሁ በ2ጢሞ. 3፥16-17 ላይ፣ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ኹሉ የተዘጋጀ ይኾን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ኹሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል፡፡” ተብሏል፡፡ ይህም በቀጥታ የሚመለከተው መጽሐፍ ቅዱስን ነው፡፡ አዋልድ መጻሕፍት ይህን መስፈርት ሊያሟሉ ይችላሉ ወይ? ለዚህ መልሳችን አይችሉም የሚል መኾኑን ቀጥሎ እናስረዳለን፡፡
አዋልድ መጻሕፍት የሚሰብኩት “በጎ” የሚሉት ሥራ አለ፡፡ ያ “በጎ ሥራ” ግን በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት የሌለው ነው፡፡ በአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ዋና ዋና በጎ ሥራዎች ገድሉ ወይም ድርሳኑ በተጻፈላቸው መላእክት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ስም ዝክር መዘከር፣ ገድላቸውን ወይም ድርሳናቸውን በበዓላቸው ቀን ማንበብ፣ ቤተ ክርስቲያናቸውን ወይም ገዳማቸውን መሳለም ወዘተ. ናቸው፡፡ እነዚህ “በጎ ሥራዎች” ከሰው ውስጣዊ ማንነት ጋር የማይገናኙና በአፍኣ (በውጪ) ሊፈጽማቸው የሚችላቸው ናቸውና፣ ለትምህርት፣ ለተግሣጽ፣ ልብን ለማቅናትና በጽድቅ ላለው ምክር የሚጠቅም ነገር አናገኝባቸውም፡፡ እንዲያውም አቀራረባቸው ሰው እንዳሻው ኾኖ እንዲኖር መረን የሚለቅቁ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሰው የቱንም ያኽል ኃጢአተኛ ቢኾን፣ በአንዱ መልአክ ወይም ጻድቅና ሰማዕት ከተማጸነና በገድሉ ወይም በድርሳኑ እንደ ተጻፈው ካደረገ ይድናል የሚል ተስፋ ይዘዋልና፤ በዚህ መንገድ ዳኑ የተባሉ ሰዎችን ትረካም ይተርካሉና፡፡
ደቂቀ እስጢፋኖስ አንዱ የተከሰሱበት ነጥብ፣ ተኣምረ ማርያምን ወደ ገዳማችን አናስገባም በማለታቸው ነው፡፡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የተኣምረ ማርያምን ቅጂ ወደ ደቂቀ እስጢፋኖስ ገዳም ልኮ የነበረ ቢኾንም፣ ወደ ገዳማቸው እንዳላስገቡት ምንጮቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ ይህም በዚያ ዘመን ብዙዎች እንደ ሠጉት ተኣምረ ማርያም ታላላቅ ኀጢአቶችን የሠሩትን ብዙዎችን ኀጢአተኞች ማርያም እንዳዳነቻቸው ስለሚተርክ፣ ይህን የሚሰሙ መነኮሳት ጻማቸውንና ገድላቸውን ትተው ንዝሕላል ይኾናሉ በሚል እምነት ነው፡፡ ይህ በተለይ ሰባ ስምንት ሰው የበላውና በዚሁ እኩይ ግብሩ በላዔ ሰብእ (ሰው በላ) የሚል ስም የተሰጠው ሰው፣ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ክዶ በማርያም ስም ለአንድ ሰው ዕፍኝ ውሃ ስለ ሰጠ ብቻ ወደ መንግሥተ ሰማያት ገባ ከሚለው ታሪክ ጋር የሚገናኝ ነው (ጌታቸው ኀይሌ፣ ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ፣ 1996፣ ገጽ 26)፡፡
እንደ ተኣምረ ማርያም ሁሉ ሌሎቹም ገድላትና ድርሳናት እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ በጎ ሥራን የሚያስጥሉና ጽድቅ “በአቋራጭ” የሚሸመትበትን ቀላል፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ያልሆነ መንገድን የሚያሳዩ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ የተነሣ ሊቃውንት በፍና ተሣልቆ (በመሣለቅ ዐይነት) “እንደ ወንጌል ማን ጸድቆ¡ እንደ ገድልስ ማን ተኰንኖ¡” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

በአጠቃላይ አዋልድ መጻሕፍት በ2 ጢሞቴዎስ 3፥15-17 ባለው ቃል ሲፈተሹ የሚያስተምሩት የመዳን መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ውጪና ተቃራኒ በመኾኑ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የኾነን፣ በእግዚአብሔር ያልታዘዘንና ከእግዚአብሔር ዘንድ ብድራት የሌለውን “በጎ ሥራ” ስለሚያስተምሩ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት ናቸው ማለት ፈጽሞ አይቻልምና 2 ጢሞቴዎስ 3፥15-17ን ለእነርሱ መጥቀስ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” እንደሚባለው መሆን ነው፡፡

1 comment:

  1. do u have any data which tell me bible is 66. and can u tell me when and how the 66 bible is collected. can u tell me about the book of enok (henok)which found in the cave in Israel????????? i think u are ignorant and u hate the truth. plea came with the truth.

    ReplyDelete