Monday, June 20, 2016

ምላሽ የሚያሻው የክርስቶስ ጥያቄ - ትወደኛለህን? (ዮሐንስ 21)

ይህን ጥያቄ ስናነብ ወደ አእምሮአችን በቶሎ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት ምን ዐይነት ጥያቄ ነው? ብለን እናስብ ይሆናል፤ ወይም ጥያቄው የአፍቃሪ ጥያቄ አንደሚሆን ልንገምት እንችላለን። አሊያ እንደዚህ ተብሎ ይጠየቃል ወይ? ብለን ልንጠይቅም እንችላለን። ጥያቄው ረጅም ጊዜ ዐብሮን ከኖረ ሰው፥ በጣም ከሚያውቀንና ከምናውቀው ሰው፥ ለምሳሌ፥ ከባለቤታችን ወይም ከጓደኛችን ቢመጣስ ምን ይሰማናል? ያለ ጥርጥር ምን አይቶብኝ ይሆን? ወይም ምን አይታብኝ ይሆን? ምን ሰምቶብኝ/ምን ሰምታብኝ ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያጭርብን ይችላል።
ጥያቄው “አዎን እወድሃለሁ” የሚል ምላሽን ለማግኘት ወይም መወደድን ለማወቅ የተጠየቀ ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው ከፍቅረኛ፥ ከትዳር አጋር ወይም ከጓደኛ የመጣ ሳይሆን ከጌታችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በተለይም ለጴጥሮስ የቀረበ ጥያቄ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ በ21ኛው ምዕራፍ አንደ ዘገበልን፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ያህል “ትወደኛለህን?” ሲል ጠይቆታል።

እወድሃለሁ
“ትወደኛለህን?” የሚለው ጥያቄ ፍቅርን ለማወቅ ወይም ለማረጋገጥ የሚጠየቅ ጥያቄ ቢሆንም፥ ዮሐንስ እንደ ጻፈው ጥያቄው ከዚያ የሚያልፍ መልእክት አለው። በርግጥ ትወደኛለህን? ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ አልወድህም የሚል አይሆንም። በክርስቶስና በጴጥሮስ መካከል የነበረውን ግንኙነት መለስ ብለን ስናስታውስ፥ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን በሥጋ ልለያችሁ ነው፤ ልሄድ ነው ብሎ በነገራቸው ጊዜ፥ ጴጥሮስ ‘ተለይተኸን ወዴት ትሄዳለህ? የትም ብትሄድ ዐብሬህ እሄዳለሁ፤ ሞት እንኳ ቢመጣ ከአንተ አልለይም’ ያለው ሰው ነበር (ዮሐ. 13፥36-38)። ጌታ ለጴጥሮስ ንግግር የሰጠው ምላሽ፥ ‘እንኳ ነፍስህን ልትስጠኝ፥ ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ’ የሚል ነበር።

ፍቅር እንዴት ይገለጣል?
እንደሚታወቀው በዓለም ላይ የፍቅር መገለጫ አንድ ዐይነት አይደለም፤ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ፥ ከባህል ባህል ይለያያል። የፍቅር መግለጫ ቋንቋ፥ የጋለ ጭብጨባ፥ እንባ፥ የቃል ንግግር፥ አበባ ማበርከት፥ መተቃቀፍ፥ መጨባበጥ፥ መሳሳም ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ በአንዱ ወይም በሌሎች መንገዶች ፍቅር ይገለጣል። ጌታ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ መላልሶ ሲጠይቀው፥ ጴጥሮስም ሦሰት ጊዜ መላልሶ እወድሃለሁ ብሎታል። እንዲሁም በኋላ ላይ ግራ የገባው በሚመስል መልክ፥ በማዘንም ጭምር እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ ብሎታል።

ፍቅርና ተግባር
በአጠቃላይ በወንጌል በተለይም በጌታችን ትምህርትና ሕይወት ውስጥ እንደምንመለከተው፥ የፍቅር ዋና መገለጫ ቃላት ሳይሆኑ ተግባር ነው። ጴጥሮስ “እወድሃለሁ” ቢልም በተግባር ግን ይህን ፍቅር ማሳየት አልቻለም፤ እወድሃለሁ ያለውን ጌታውን ክዶታል። ጌታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል 15፥13 ላይ ነፍሱን ለወዳጆቹ ከመስጠት የበለጠ ፍቅር እንደሌለና ነፍስን መስጠት የፍቅር ጣሪያ መሆኑን እንዳስተማረ፥ በተግባርም ነፍሱን በመስጠት ፍቅሩን አሳይቷል። ከዚህ በኋላ ነው ጌታ ጴጥሮስን “ትወደኛለህን?” ሲል መላልሶ የጠየቀው። ጴጥሮስም እንደ ቀድሞው፥ “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም” (ማቴ. 26፥35) አላለም። የራሱን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ “እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” ነበር ያለው። ጴጥሮስ ፍቅሩን በተግባር መግለጽ ባይችልም፥ ኢየሱስ ፍቅሩን በተግባር ከገለጠና፥ የካደውን ጴጥሮስን በዚህ ፍቅር እንደ ገና ከመለሰው በኋላ አልከሰሰውም። ይልቁንም ሲመልሰውና ወይም እንደ ገና ሲያድሰው፥ ኀላፊነትንም ሲሰጠው እንመለከታለን።

መልእክቱ

“ትወደኛለህን?” የሚለው የጌታ ጥያቄ “አዎን እወድሃለሁ” ከሚል ምላሽ ያለፈ ቀጥተኛ መልእክት አለው። መልእክቱም  የምትወደኝ ከሆነ አደራዬን ተወጣ የሚል ነው።  ጌታ ሦስት ጊዜ፥ “ትወደኛለህን?” ሲል ከጠየቀው በኋላ ጴጥሮስ “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” የሚል ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ፥ ግልግሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤  በጎቼን አሰማራ የሚል ግልጽ አደራ ሰጥቶታል (ዮሐ 21፥15-17)። ይህ ኀላፊነት ወይም አደራ የሕይወት መሥዋዕትነትን የሚጨምር እንደሚሆን ቀጥሎ በተጻፈው ቃል ውስጥ እናነባለን። “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጒልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው። በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ።” የዚህ ክፍል መልእክት በእኛም ሕይወት ሊተገበር የሚገባው ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ በዕለታዊ ሕይወታችን ተግባራዊ ምላሽን ይጠብቃል። ትወደኛለህን? ለሚለው ጥያቄ በቃል “እወድሃለሁ!!” የሚለውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፥ ራሳችንን መልሰን መጠየቅ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም። በርግጥ ጌታን እንወደዋለን ወይ? 

በጮራ ቍጥር 44 ላይ የቀረበ

1 comment:

 1. ወገኖቼ ለመጨረሻ ጊዜ ይህን ልበላችሁ ስሙ!ጌታ ኢየሱስ ከማርያም ተወልዶ ለ3 ዓመት ሲያስተምር ጴንጤ ወይም ኦርቶዶክክስ ወይም ካቶሊክ .... ካልሆናችሁ መንሥተ ሰማይ አትገቡም ብሎ ስለሃይማኖት አሰተምሯል እንዴ?ኧረ እናስተውል?እሱ ያስተማረው ይህን ብታውቁና ብታደርጉ /ዮሐንስ 13፡17/ በማለት፡
  1/ አዳም በኃጢአት ምክንያት ከገነት ወጣ = ከእግዜር ተለየ = ሰው ሁሉ /አንተም አንችም እኔም አባም ፓስተርም / ኃጢአትን ሠርተዋልና /ሮሜ 3፡23/ ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን /1ኛ ዮሐንስ 1፡10/
  2/ የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው /ሮሜ 6፡23/ = ከገነት መውጣት ነው /ዘፍጥረት 3፡24/ = ራቁትነትና በፍርሃት መደበቅ ነው /ዘፍ 3፡10/ = በመርገም ውስጥ መሆን ነው /ዘፍ 3፡15_17
  3/ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም /ዕብራውያን 9፡22/ በብሉ ኪዳን ዘመን የእንሳሳት ደም ይፈስ የነበረው ለዚህ ነበር፤ ግን በጥላነት አገለገለ እንጂ ዘለቄታ መፍትሄ አላመጣም።
  ስለዚህ የሁላችን ዋና ጥያቄ መሆን ያለበት ከዚህ ኃጢአት ካመጣብን የሞት በሽታ እንዴት መዳንና ከእግዜር ጋር እንታረቅ?መልሱን ከቃሉ አብረን እንይ:
  ሀ/ ወንድም ወንድሙን አያድንም፣ ሰውም አያድንም /መዝ 49፡7/
  ለ/ እግዚአብሔር ሰውም እንደሌለ አየ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት/ኢሳ 59፡15-17/
  ሐ/ ልጅም ትወልዳለች እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ /ማቴ 1፡21/ የተመረጠች እናቱ ማርያምም ይህን ተረድታ መድሐኒቴ /ሉቃ 1፡47/አለችው!
  መ/ መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና! የለምና! የለምና! የለምና! የለምና! /ሐዋ ሥራ 4፡12/።
  ሠ/ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል /ዮሐ 3፡14 እና 15/ ፍቅሩ የገለጠበት መንገድ /3፡6/
  ረ/ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም ስላለ /ዕብ 9፡22/ በደሙ ከኃጢያታችን ሊያነጻን /1ኛ ዮሐ 1፡7-9 / ቃል ሥጋ ሆነ /ዮሐ 1፡14/
  ስለዚህ ክርስትና በልጁ የመስቀል ሥራ ከሞት መዳን /1ቆሮ 1፡18/ እና የህይዎት ጉዳይ ነው እንጂ /ዮሐ 10፡10/ እና 1ኛ ዮሐ 5፡12/ ሰው ሠራሽ የሆነ የድርጅት ወይም የሃይማኖት ጉዳይ አይደለምና ቆም ብለን ክርስቶስ ኢየሱስ ከሰማይ የመጣበትንና በመስቀል ላይ ለሁላችን የከፈለውን የህይወት ዋጋ እናስተውል?
  ክርስትና በክርስቶስ የደም ዋጋ የተገኘ ሕይወት እንጂ በፍጹም ሃይማኖት አይደለም!!!
  በሰማይ ፍቅር የተሸነፍኩና
  በጸጋው ቃል ሁለንተና ማንነቴ የተማረኩ
  ብቸኛ አዳኝ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ብቻ ብቻ /ሌላ መጨመር በመስቀሉ ሥራ ላይ ብቃት የለኸም ማለት ስለሚሆን / መሆኑ በመጠኑ የገባኝ!ግን ቃሉን በመብላት ወደ ሙላቱ በመገስገስ ላይ ያለሁና ጨለማየ በብርሃኑ የተገፈፈልኝ!!!
  ለሁላችንም ማስተዋልን ይስጠን!
  ያለወንጌል /ሮሜ 1፡1-4/ ክርስቲያን ያስባለንንና
  በመርገም ውስጥ እንድንሆን ያደረገን /ገላት 1፡6-9 /
  እና እንደ ሳውል/ጳውሎስ /ሐዋ ሥራ 9፡1-9 /
  ፎካሪና ገዳይ ሃይማኖተኛ ብቻ ያደረገን ክፉ
  የደበተራ መንፈስ በቃሉ ሰይፍ ከሕዝባች ላይ የተሰየፈ ይሁን! አሜን።
  የቀደመችው ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታማኝ ልጆች አንዱ!
  እ ው ነ ቱ ይ ነ ገ ር !!!

  ReplyDelete