Monday, November 24, 2014

አለቃ ነቅዐ ጥበብ

በደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሽ ውስጥ በተዘጋጀው የመዘምራን ጉባኤ ለሚታደሙ ዘማርያንና ዘማርያት፥ እንዲሁም ለሌሎች ታዳሚዎች በመዝሙር ላይ ትምህርት እንዲያቀርቡ በተቀጠረው ቀን አለቃ ነቅዐ ጥበብ ወደ ስፍራው የደረሱት በሰዓቱ ነው። አዳራሹ በሰው ግጥም ብሎ ሞልቷል። አብዛኛው ታዳሚ ለመስማት ብቻ ሳይኾን በመዝሙር ላይ አለኝ የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅ ተዘጋጅቶ የመጣ ነው የሚመሰለው። አለቃ ስለ መዝሙር ምንነት፥ ስለ ይዘቱ፥ መዝሙር መቅረብ ያለበት ለማን እንደ ኾነና ስለ መሳሰለው ኹሉ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

ጉባኤው በጸሎት ከተከፈተና ሊቀ መዘምራን ያሬድ በጆሮ ሲንቈረቈር ለነፍስ ትልቅ ርካታን በሚሰጠው መልካም ድምፃቸው ኹለት እግዚአብሔርን የሚወድሱና ምእመናንን ለአምልኮ የሚቀሰቀሱ ዝማሬዎችን ካቀረቡ በኋላ፥ የመድረኩ መሪ አለቃን ወደ መድረክ ጋበዙ። አለቃም አትሮንሱ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳቸውንና የያዙትን ማስታወሻ ካሰቀመጡ በኋላ ለጉባኤው ሰላምታ ሰጡ። በመቀጠልም ለዚህ ጉባኤ በመዝሙር ዙሪያ ትምህርት እንዲያቀርቡ ስለ ተሰጣቸው ዕድል የጉባኤውን አዘጋጆች በማመስገን በቀጥታ ወደ ትምህርታቸው ዐለፉ።

Thursday, November 6, 2014

ርእሰ አንቀጽ

“ንፈቅድ ንርአዮ ለእግዚእ ኢየሱስ - ጌታ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን” (ዮሐ. 12፥21)
ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም ለፋሲካ በዓል መጥተው የነበሩ የግሪክ ሰዎች ለሐዋርያው ፊልጶስ ያቀረቡት ሐሳብ ነው። ፊልጶስም ለእንድርያስ ነግሮት ኹለቱም ለኢየሱስ መጥተው የሰዎቹን መሻት አወሩለት። ጌታም፥ “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” አለ። በዚህ መስተጋብር ውስጥ በተለይ ኢየሱስን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችንና ለእነርሱ ኢየሱስን ማሳየት የቻሉ አገልጋዮችን መመልከት እንችላለን።

ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስን የሚፈልጉና ኢየሱስን ከፈላጊዎቹ ጋር የሚያገናኙ ምን ያኽል ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት ይኖርብናል። በዚህ ዘመን በቤተ ክርስቲያን እየታየ ያለው አንዱ ችግር፥ ጌታ ኢየሱስን የሚፈልግ ምእመንና እርሱን የሚያሳይ አገልጋይ ቍጥር እየተመናመነ መምጣቱ ነው። ርግጥ የምእመናን የልባቸው መሻትና የነፍሳቸው ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ብዙዎቹ አገልጋዮች ግን ዕረፍተ ነፍስ ወደ ኾነው ጌታ ምእመናኑን ማድረስ ሲገባቸው ወደ ራሳቸው ይስቧቸዋል። በዚህ ምክንያት ምእመናን የክርስቶስ ተከታዮች ሳይኾኑ የእነርሱ ተከታይና አድናቂ እንዲኾኑ፥ ክርስቶስን ሳይኾን እነርሱን እንዲመለከቱ፥ የሕይወታቸው ዋና ምሳሌም ክርስቶስ ሳይኾን አገልጋዮቹ እንዲኾኑ በማድረግ፥ ኢየሱስን ፈልገው የመጡትን ምእመናን ወደ ኢየሱስ ሳያደርሷቸው እነርሱ ዘንድ በማስቀረት የእነርሱ ሎሌ ያደረጓቸው አገልጋዮች ጥቂቶች አይደሉም።