በደቂቀ እስጢፋኖስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሽ ውስጥ በተዘጋጀው
የመዘምራን ጉባኤ ለሚታደሙ ዘማርያንና ዘማርያት፥ እንዲሁም ለሌሎች ታዳሚዎች በመዝሙር ላይ ትምህርት እንዲያቀርቡ በተቀጠረው ቀን
አለቃ ነቅዐ ጥበብ ወደ ስፍራው የደረሱት በሰዓቱ ነው። አዳራሹ በሰው ግጥም ብሎ ሞልቷል። አብዛኛው ታዳሚ ለመስማት ብቻ ሳይኾን
በመዝሙር ላይ አለኝ የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅ ተዘጋጅቶ የመጣ ነው የሚመሰለው። አለቃ ስለ መዝሙር ምንነት፥ ስለ ይዘቱ፥ መዝሙር
መቅረብ ያለበት ለማን እንደ ኾነና ስለ መሳሰለው ኹሉ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
ጉባኤው በጸሎት ከተከፈተና ሊቀ መዘምራን ያሬድ በጆሮ ሲንቈረቈር
ለነፍስ ትልቅ ርካታን በሚሰጠው መልካም ድምፃቸው ኹለት እግዚአብሔርን የሚወድሱና ምእመናንን ለአምልኮ የሚቀሰቀሱ ዝማሬዎችን ካቀረቡ
በኋላ፥ የመድረኩ መሪ አለቃን ወደ መድረክ ጋበዙ። አለቃም አትሮንሱ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳቸውንና የያዙትን ማስታወሻ ካሰቀመጡ በኋላ
ለጉባኤው ሰላምታ ሰጡ። በመቀጠልም ለዚህ ጉባኤ በመዝሙር ዙሪያ ትምህርት እንዲያቀርቡ ስለ ተሰጣቸው ዕድል የጉባኤውን አዘጋጆች
በማመስገን በቀጥታ ወደ ትምህርታቸው ዐለፉ።
“ለዚህ ጉባኤ ያዘጋጀሁትን ትምህርት የማቀርበው” አሉ አለቃ
በንግግራቸው መጀመሪያ ላይ፥ “ለዚህ ጉባኤ ያዘጋጀሁትን ትምህርት የማቀርበው በቅርቡ ዘመድ ለመጠየቅና በዚያ የሚገኙትን ወገኖች
ለማበረታታት በሄድሁኝ ጊዜ በተሳፈርሁበት አውቶቡስ ላይ የገጠመኝን ነገር ለእናንተ በማካፈል ነው። ይህን የማደርገው ገጠመኙ ከማቀርበው
ትምህርት ጋር ግንኙነት ስላለውና አብዛኛውን የትምህርቴን ክፍል ስለሚያብራራልኝ ጭምር ነው” አሉና ታዳሚው ኹሉ እየተከታተላቸው
መኾኑን ለማረጋገጥ በዐይናቸው ከግራ ወደ ቀኝ ከፊት ወደ ኋላ ጉባኤውን ቃኘት ቃኘት አደረጉት። የኹሉም ጆሮ ገጠመኛቸውን ለመስማት
ቆሟል። አለቃ ቀጠሉ፤
“ማልጄ ነበር ወደ አውቶቡስ ተራ የሄድሁት። የተሳፈርንበት አውቶቡስ
መናኸሪያውን ለቆ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን እንደ ተጓዘ ሾፌሩ ቴፑን ነካካና መዝሙር ከፈተ። እኔም ጕዟችን በመዝሙር መጀመሩ መልካም
ነው ብዬ ዐሰብሁ። በመጀመሪያ አንዲት ዘማሪት ለጌታችን ክብርን የሚሰጡና ውለታውን የሚያሳስቡ ዝማሬዎችን በተከታታይ ዘመረች። እኔም
በመረዋ ድምፅዋ የሚንቈረቈሩትን ዝማሬዎች ሳደምጥ በተመስጦ ወደ ሰማያዊቱ ቅድስተ ቅዱሳን ገባሁ። ከዚያ የመለሰኝ ከእርሷ ለጥቆ
የተሰማው የሌላው ዘማሪ መዝሙር ነው። የመዝሙሩን ጥቂት ስንኞች በቃሌ ይዣቸዋለሁ። … ቈይ እንዲያውም ከግጥሙ ጥቂት ስንኞችን ላንብብላችሁ”
አሉና ወደ ማስታወሻ ደብተራቸው ተመለከቱ። “አዎን፥ እንዲህ ይላል፥
“ደጅ ጠናሁ ቈይቼ ኪዳነ ምሕረትን
ተጽናናሁኝ ረሳሁ ሐዘኔን፤
የአምላክ እናት እመቤታችን
ሞገስ ኹኚኝ ቀሪ ዘመኔን።”
“በዚህ ዝማሬ መንፈሴ እጅግ ተበሳጨ። የተበሳጨሁት በኹለት ጕዳዮች
ምክንያት ነው። የመጀመሪያው፥ ዝማሬ መቅረብ ያለበት አምላክ፥ ፈጣሪ፥ ጌታ፥ አዳኝ ለኾነው አንድ አምላክ ለእግዚአብሔር ብቻ ሆኖ
ሳለ ለፍጡር ዝማሬ በመቅረቡ ነው። እንደሚታወቀው ፍጡር ለፈጣሪ መዝሙር አቅራቢ እንጂ በፈጣሪ ስፍራ ኾኖ መዝሙር ተቀባይ ሊኾን
በፍጹም አይችልም። ኹለተኛው ምክንያቴ ደግሞ በኪዳነ ምሕረት ስም የተዘመረው መዝሙር አስቀድሞ ለእግዚአብሔር
የተዘመረና በኋላ ግን የስም ለውጥ ተካሂዶበት ‘ኪዳነ ምሕረት’ ለተባለች ለማርያም የተሰጠ በመኾኑ ነው። መቼም የእግዚአብሔርን
ስፍራ ለፍጡር ብንሰጥ እኛ ይኹን ስላልን ስፍራው ለፍጡራን አይስማማም፤ አይኾንም” አሉና ማስረጃውን ለማቅረብ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን
ገልበጥ ገልበጥ አደረጉ። ከዚያም “በመዝሙር 39 በቅንፍ 40 ከቍጥር 1 ላይ፥ ‘ቆይቼ እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፥ እርሱም ዘንበል
አለልኝ፥ ጩኽቴንም ሰማኝ’ የሚል ቃል አለ። እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ኪዳነ ምሕረት በሚለው ስም እንደ ተተካ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
“በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞችና እኅቶች፥” አሉ አለቃ ተማጽኖ
ባጠላበት የድምፅ ቃና፥ “በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞችና እኅቶች፥ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የዘመረው የዳዊት ዝማሬ ምን ስሕተት
ተገኝቶበት ነው ስመ እግዚአብሔር ወደ ስመ ኪዳነ ምሕረት መዛወር ያስፈለገው? ምናለ ዘማሪዎች ከመዘመራቸው በፊት ከመምህራን እግር
ሥር ተቀምጠው መዝሙረ ዳዊትን እንኳ ቢያጠኑ? ያ ቢሆን ኖሮ መንፈስ ቅዱስን ለማረም ወይም እርሱ የተናገረውን ለመለወጥ ባልተነሣሡ
ነበር። ከቶ መንፈስ ቅዱስን ማረም ማን ይቻለዋል? ይህ በእውነቱ እጅግ ታላቅ ድፍረት ነው።
“ዘማሪው መች በዚህ ሊያበቃ! በዚህኛው መዝሙር ስገረም ከዚህ
የባሰ ሌላው መዝሙር ተከተለ፤ ከመዝሙሩ ስንኞች፥
“በእስራቴ አላፍርም እኔ የማርያም ነኝ፤
ሮማዊ አይደለሁ ፍጹም ክርስቲያን ነኝ፤
ከእመቤቴ ፍቅር የሚለየኝ ማነው?
መከራና ሥቃይ ወይስ መራቈት ነው?”
“ምነው ልጆቻችን እንዘምር ከማለታቸው በፊት ‘መጠየቅ ያደርጋል
ሊቅ` እንዲሉ፥ አበውን ስለ መዝሙር ጠይቀው ቢያውቁና ቢረዱ? እንስበክ ከማለታቸው በፊት ቀድመው ወንጌልን ቢሰበኩ? አካላቸው ከቤተ
ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ለአንድም ቀን ጠፍቶ አያውቅም፤ ልባቸው ግን አንድም ቀን በመድረኩ እንዳልተገኘ ይህ ስመ መዝሙር ያረጋግጣል።
ይህ ባይሆንማ ኖሮ በየዕለቱ ‘በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉድ የተሰኛችሁ’ እየተባለ ዘወትር በየስብከቱ መድረክ የሚነገረው
አይጠፋቸውም ነበር። ለመኾኑ ባለአእምሮ እና መጽሐፍ ቅዱስን ያነበበ ሰው በአንድ በኩል ክርስቲያን ነኝ እያለ፥ በሌላ በኩል ደግሞ
እንዴት የማርያም ነኝ ይላል? የክርስቶስ ብቻ ሳይኾኑ የሌላ ኾኖ ክርስቲያን ነኝ ማለትስ ከቶ እንዴት ይቻላል?
“ዘማሪው በዜማ ምሪት ‘ከእመቤቴ ፍቅር ማን ይለየኛል?’ ያለውን
ሐዋርያው ጳውሎስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ሲናገር፦ መከራ፥ ሥቃይ፥ ችግር፥ መራቈት ከክርስቶስ ፍቅር ሊለዩት እንዳማይችሉ መስክሮበታል።
ሌላው ቀርቶ ይህ ዘማሪ አላስተዋለውም እንጂ ሐዋርያው፥ ልዩ ፍጥረት እና መላእክትም ቢኾኑ በጌታችን በክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር
ፍቅር ሊለየው እንደማይችል አጽንዖት ሰጥቶ ተናግሯል። ታዲያ ይህ ዘማሪ ከክርስቶስ ፍቅር በማርያም ፍቅር ተለይቶ የአምላኩን ስፍራ
ለእርሷ ሰጥቶ አልሳተምን? አድማጮቹንስ ከቀናው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱስ ትምህርት እንዲወጡና እንዲስቱ አላደረገምን?” ብለው በመጠየቅ
ምላሽ ሳይሹ ወደ ቀጣዩ ገጠመኛቸው ለመሸጋገር ጥቂት ንግግራቸውን ገታ አደረጉ።
ቀጠሉና እንዲህ አሉ፤ “እንዲህ የተደበላለቁ
ዝማሬዎች፥ በአውቶቡሱ ሾፌር ግብዣ መስማታችን ሳያንስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ከተጓዝንና ፀሓይ ወጥታ በመንገዳችን ግራና ቀኝ ሳሩ
ያዘለው ጤዛ እየረገፈ፥ ቅዝቃዜውም እየለቀቀን ሲመጣ፥ ሾፌሩ የመዝሙሩን ካሴት አወጣና የዘፈን ካሴት ቴፑ ውስጥ ዶለበትና ድንገት
መዝሙሩ ወደ ዘፈን ተሸጋገረ። ይህ ሲኾን ባለሁበት ትክዝ አልሁኝ። መዝሙርና ዘፈን አንድ ላይ እንዴት ይሄዳሉ? የሚል ጥያቄ በውስጤ
ተጫረ። ጕዟችን ቀጥሏል። አንዱ ካሴት ሲያልቅ ሌላውን እየዶለ ቀሪ ጕዟችንን ዘፈን እየሰማን እንድንሄድ ተገደድን፡፡ በአውቶቡሱ
ውስጥ የተሳፈረው ሰው የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ በመኾኑ፥ ይህ ይከፈትልን ወይም ይህ ይዘጋ ማለት ባይችልም፥ ቢያንስ ግን ከሾፌሩ
ጋር የሃይማኖት ተመሳስሎ ያላቸው ወገኖች እንኳ ለምን እንዲህ ይኾናል? እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ? ለማለት የደፈረ አልነበረም።
በሾፌሩ ሃይማኖት ላይ ጥያቄ መነሣቱ ግን ግድ ሳይል አይቀርም። በርግጥ መዝሙሩን የከፈተ ጊዜ የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ እንደ
ኾነ ታውቋል። ግራ መጋባት የተፈጠረብኝ ግን መዝሙሩን ሲያሰማን ከቈየ በኋላ፥ ወደ ዘፈን መዞሩ ነው። በርግጥ ሃይማኖቱ ለዘፋኝነት
ሕጋዊ ዕውቅና አይሰጥም። ግለሰቦች ግን በሃይማኖቱ ውስጥ ሲኖሩ መዝሙርንም ዘፈንንም መሳ ለመሳ እየዘመሩና እየዘፈኑ መኖራቸው አይካድም፤
ያ ሾፌርም እንዲህ ከሚያደርጉቱ አንዱ ነው ማለት ይቻላል።
“ለመሆኑ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚለው ሕዝባችን ወዴት እየሄደ ነው?
ምንስ እየሆነ ነው? መዝሙርንና ዘፈንን እንዴት በአንድ ላይ ሊያስኬድ ቻለ? እንዴትስ ሄዱለት? ደግሞስ ጧት ጧት ቤተ ክርስቲያን
ውስጥ ዘማሪ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በየዳንኪራ ቤቱ ጨፋሪ ከኾነ፥ ከቶ ለሁለት ጌቶች መገዛት ይቻላልን? ጨለማ ከብርሃን፥ ጽድቅ ከኀጢአት፥
ዲያብሎስ ከክርስቶስ ጋር በአንድ ስፍራ ተስማምተው እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ? እንዲሁ ዓለማዊ ዘፈንና መንፈሳዊ መዝሙር በአንድ አማኝ
ልብ ውስጥ የጋራ ቦታ ይዘው እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ? ለመሆኑ ቤተ ክርቲያን በነዚህ ሁለት ተቃራኒ ጉዳዮች መካከል ድንበር የማታበጀውስ
እስከ መቼ ነው? እንዲህ ብለን ብንናገር ሕዝቡ ያኰርፍና ገቢያችን ይቀንሳል ተብሎ የተሠጋ ከሆነ፥ መባ ተብሎ ከሚገባው ገንዘብ
ይልቅ መንግሥተ ሰማያት መግባት ላለበት የምእመናን ነፍስ የማይገደን እስከ መቼ ይሆን? እንደ ምንደኛ ጠባቂ በጎቻችንን የተኵላ
ሲሳይ አድርገን ካስጨረስናቸው የእረኞች አለቃ ሲመጣ፥ ደማቸውን ከእጃችን ይፈልገዋል እኮ!” አሉና መንጋውን በትጋት አለመጠበቅ
ከባድ ተጠያቂነት ያለበት ዐደራ መኾኑን ከውስጣቸው በሚንቀለቀል የቍጭት ስሜት ጭምር አስገነዘቡ። እንደ ገናም የድምፃቸውን ቃና
ለስለስ አደረጉና፥ “የተወደዳችሁ ወንድሞችና እኅቶች መዝሙርና ዘፈን በአንድነት ተስማምተው መኖራቸው ገረመኝና ከገጠመኙ ማስተማሪያ
ቢኾኑ ብዬ እዚያው በጕዟችን ላይ ሳለሁ የሚከተሉትን ስንኞች ቋጠርሁ፤
ረጅሙን መንገድ ማልደን ለመገሥገሥ
ተሳፍርን ባውቶቡስ
መዝሙር ተከፈተ፥ ከዓለመ ሥጋ ገባን ወደ መንፈስ
ቀጠለ ሙዚቃ
የተኛው ሥጋችን አለ ነቃ ነቃ
ሰው ሥጋና መንፈስ
በመንፈስ ወጥኖ በሥጋ ‘ሚጨርስ
ለአለቃ በጥቂት ስንኞች ለታጀበው አስተማሪ ገጠመኛቸው በአዳራሹ
የተሰበሰበው ኹሉ በጭብጨባ አድናቆቱን ገለጸላቸው።
ጭብጨባው ጋብ እንዳለ፥ “ትምህርቱን በገጠመኜ
ላይ የመሠረትሁት በትምህርቱ አነሣቸዋለሁ ብዬ ያሰብኋቸውን ብዙዎቹን ነጥቦች ስለሚዳስስልኝ ነው። ስለዚህ ከትምህርቱ አንድ መሠረታዊ
ነገር ላንሣና ላብቃ። ከዚያ በጥያቄና መልስ ሌሎች ጕዳዮች ካሉ እንዳስሳቸዋለን።” አሉና አለቃ ወደ ትምህርታቸው ማጠቃለያ መቃረባቸውን
ጠቈሙ።
“በእናት ቤተ ክርስቲያን በየሳምንቱ እሑድ መንፈሳዊ አገልግሎት
የሚቀርብበት ‘መዝሙር’ የተባለ ያሬዳዊ ዜማ አለ። የዕለቱ ተረኛ መዝሙር የመጨረሻ ክፍል ‘ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ፥ ዘምሩ ለንጉሥነ
ዘምሩ። - ለአምላካችን ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ’ የሚልና ከመዝሙረ ዳዊት 46(47)፥6 ላይ የተወሰደ ነው።” ካሉ በኋላ አለቃ
ይህን ቃል አመላለስ በተባለው ወረብ መሰል ዜማ አንዴ ከዘለቁት በኋላ ቃሉን መሠረት ያደረገውን የማጠቃለያ ነጥባቸውን ወደ ማንሣት
ተሸጋገሩ።
“ይህ አስቀድሞ መዝሙረኛው ዳዊት የተናገረውና የዜማ ተሰጥዎ
ያለው ያሬድም በመዝሙር በዜማ ያቀረበው የምስጋና ዐይነት ሲኾን፥ እንደ ሌሎቹ ምስጋናዎች ሁሉ መዝሙር፥ አምላከ አማልክት፥ እግዚአ
አጋዕዝት፥ ንጉሠ ነገሥት ለሆነው ለእግዚአብሔር ብቻ ሊቀርብ እንደሚገባ ያስገነዝባል። ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረው ሌሎች ፍጥረታት
ይልቁንም ሰውና መላእክት የተፈጠሩት የእግዚአብሔርን ስም ለማመስገን፥ ክብሩንም ለመውረስ ነው እንጂ፥ እርስ በርስ ለመመሰጋገን
አይደለም። እርስ በርሳችሁ ተመሰጋገኑ ወይም አንዱ ሌላውን ፍጡር በመዝሙር ያመስግን የሚል ትእዛዝ የለም። እርስ በርሳችን በመዝሙር
ለእግዚአብሔር እንድንዘምርና ቅኔም እንድንቀኝ ግን ታዘናል (ኤፌ. 5፥19፤ ቈላ. 3፥16)።” ራሱ አምላካችንም “እኔ እግዚአብሔር
ነኝ፥ ስሜ ይህ ነው፥ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።” ብሎ ከእርሱ በቀር ሌላውን ፍጡር ወይም የጥበብ
እድ ውጤት የኾኑትን ምስሎችና ቅርጻ ቅርጾች እንዳናመስግን ከልክሎናል። ዛሬ እየኾነ ያለው ግን ይህን አምላካዊ ጥብቅ ትእዛዝ በአንድም
በሌላም መንገድ የሚጥስ ነው። ስለዚህ ክብሩንና ምስጋናውን ለሌሎች ፍጡራንና ምስሎች በመስጠት የበደልነውን አምላካችንን በንስሓ
ይቅርታ መጠየቅና ከዚህ በኋላ ምስጋናችንና ዝማሬያችን ብቻውን ስቡሕ ወውዱስ ለኾነው ለአምላካችን ማቅረብ ይገባናል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር”
ሲሉ ታዳሚው አሜን አለና በጭብጨባ መስማማቱን ገለጸ።
አለቃ ከገጠመኛቸው በመነሣት በሰጡት ትምህርት ላይ ጥያቄ የተፈጠረባቸው
ከጉባኤው ተሳታፊዎች ዘማርያን የኾኑቱ አንዳንዶቹ ጥያቄዎችን ሰንዝረው ነበር። ከቀረቡትና በአለቃ በኩል ምላሽ ከተሰጠባቸው ጥያቄዎች
መካከል የመጀመሪያው ጠያቂ ዘማሪ በልሁ እንዲህ ሲል ጠየቀ “የኔታ መዝሙር ለአምላክ ብቻ የሚቀርብ ምስጋና ስለ መኾኑና ሌሎቹ ፍጥረታትም
የተፈጠሩት እርሱን ብቻ ለማመስገን እንደ ኾነ ቅድም የሰጡት ትምህርት ሐሳቡ ግር ስላለኝ ትንሽ ቢያብራሩልኝ።”
አለቃ ሲመልሱ እንዲህ አሉ፤ “ልጄ ቅደም በትምህርቱ ለመግለጽ
እንደ ሞከርሁት መዝሙር በዜማ የሚቀርብና ከማመስገኛ መንገዶች ወይም ከምስጋና ዐይነቶች አንዱ ነው። የሚቀርበውም ለእግዚአብሔር
ብቻ ነው። ምክንያቱም ምስጋና ምእመናን የሚያቀርቡት የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕት ነው። መሥዋዕት ደግሞ ሊቀርብ የሚችለው ለእግዚአብሔር
ብቻ እንጂ ለሌላ አይደለም። በብሉይ ኪዳን ይቀርቡ የነበሩ ልዩ ልዩ መሥዋዕቶች ለአምላክ ብቻ ነበር የሚቀርቡት። በሐዲስ ኪዳን
መንፈሳዊ መሥዋዕት (1ጴጥ. 2፥5) ከተባሉቱ አንዱ ከውስጣዊ ማንነታችን የሚመነጨው የምስጋና መሥዋዕትማ
እንዴት ይልቁን ለእግዚአብሔር ብቻ
አይቀርብ! ይህን መሥዋዕት ሠዉ የተባልነው
ለእግዚአብሔር ብቻ ነው (መዝ. 49/50፥14፤ ኤር. 33፥11፤ ዕብ. 13፥15)” ብለው በዐጭሩ መለሱለት።
ሌላው ዘማሪ “ፍቅረ ማርያም እባላለሁ” በማለት ራሱን ካስተዋወቀ
በኋላ እንዲህ ሲል ጥያቄውን አቀረበ፤ “የኔታ ለእመቤታችንስ መዘመር አይገባም? እርሷ ራሷም እኮ ‘እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ
ያመሰግኑኛል’ ብላለች” አላቸው።
አለቃ፥ “ወደ ጥያቄህ ምላሽ በቀጥታ ከመሄዴ በፊት የእግዚአብሔር
ቃል በሰው ቋንቋ ስለሚደርስበት የትርጉም መዛባት ጥቂት ልበል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሐሳብ ነው። ኾኖም የተዘጋጀው ለሰው
በመኾኑ የተጻፈው በሰው ቋንቋ ነው። ከቋንቋ ወደ ቋንቋ ሲተረጐም ዐልፎ ዐልፎ የሐሳብ መሸራረፍ ሊገጥመው ስለሚችል የእግዚአብሔርን
ሐሳብ ለመገንዘብ የመንፈስ ቅዱስ አብርሆት በዋናነት አስፈላጊነቱ እንዳለ ኾኖ፥ መጽሐፉ በመጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች የሚለውን
መለስ ብሎ ማየቱ ጠቃሚ መኾኑን መናገር እሻለሁ። ወደ ጥያቄህ ምላሽ ሳመራ ቅድም ያነሣኸውና በተለይ “ያመሰግኑኛል” የሚል ፍቺ
የሰጠኸው ቃል ወደ ዕብራይስጡ ሳንሄድ እንኳ በግእዝ የሚለውን ብንመለከት ነገሩ ግልጽ ይኾንልናል፤ “ያመሰግኑኛል” ተብሎ በአንተም
በአንዳንዶችም እንደ ተፈለገ የተተረጐመውን ቃል ግእዙ “አስተብፅዐ” ነው የሚለው። ትርጉሙም፦ ‘አከበረ፥ አመሰገነ፥ አደነቀ፥ ደስ
አሰኘ’ የሚል ነው። ከፍቺዎቹ መካከል ‘አመሰገነ’ ሲል ለተደረገለት ወይም ለኾነው ነገር የሚገለጥለትን ደስታ ለማመልከት የሚቀርበውን
አድናቆት ያሳያል እንጂ ብፁዕ ወይም ብፅዕት የተባሉት ፍጡራን በመዝሙር ወይም በሌላ መንገድ ይመሰገናሉ ማለት አይደለም (የአለቃ
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ 281ን ይመለከቷል)።
“ከላይ በሉቃስ ወንጌል ቅድስት ድንግል ማርያም የተናገረችውን
ቃል መጽሐፍ ቅዱስ፥ የተባረኩ መኾንን እና ደስተኛነትን የሚገልጠውን ሐሳብ ግእዙ፦ ብፁዕ፥ ብፅዕት፥ ብፁዓን ብፁዓት ይለዋል (ሉቃ
1፥48፤ መዝ. 31(32)፥1፤ መዝ. 144፥15፤ ማቴ 5፥1-11፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 119ንም ይመለከቷል)።
ይህም ግልጽ እንዲኾንልን መልአኩ ገብርኤል ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ ያላትን ግእዙ “ቡርክት” ሲለው፥ ከዘመዶቿ መካከል
የሆነችው ኤልሳቤጥ ያለቻትን ተመሳሳይ ሀሳብ ደግሞ “ብፅዕት” ብሎታል። እርሷ ራሷም እግዚአብሔር የባሪያዪቱን ውርደት ተመልክቶ
እርሷን መምረጡን ስትገልጥ የተናገረችውን ቃል ግእዙ “ያስተበፅዑኒ” ብሎታል። ሐሳቡም መላኩና ኤልሳቤጥ ከገለጡት እና የተባረከች
(የተመረቀች) መኾኗን የሚገልጠውን ሐሰብ ያሳየናል እንጂ፥ እንደ እግዚአብሔር መመስገንን አያመለክትም፤ የክርስቶስ ከድንግል መወለድ
በጸጋ የመሞላትና የባርኮት ነጻ ስጦታ እንጂ የበጎ ሥራ ውጤት አይደለምና።
“ያም ኾኖ እርሷ በተናገረችው ንግግር ውስጥ ‘ይዘምሩልኛል’
የሚል ሐሳብ ፈጽሞ የለም። በመጻሕፍት ውስጥ ያለውን እውነት ለመገንዘብ የምዕራፉን ዐውደ ንባብ መከተል እንጂ ከመኻል አንድ ቍጥር
ገንጥለንና የሌለውን ፍቺ በራሳችን መንገድ ሰጥተን ለግል ሐሰባችን ማዳበሪያ ማድረግ የለብንም። ስለዚህ ‘አንብብዋ ለመልእክት እም
ጥንታ እስከ ተፍጻሜታ - መልእክቲቱን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ አንብቧት’ ያለውን የአንጾኪያውን ሊቀ ጳጳሳት የዮሐንስን መመሪያ
ብንከተል መልካም ነው (ሃይማኖተ አበው 1986፥ 457)።
ከዘማርያኑ መካከል ሌላው ዲያቆን ደግሞ
ፈራ ተባ እያለ እንዲህ ብሎ ጠየቀ። “የኔታ፥ ዳዊት ‘መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ - እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው’ (መዝ. 67/68፥35) እንዳለው እነርሱን ማመስገን እግዚአብሔርን
ማመስገን ሊኾን አይችልም?” አላቸው።
አለቃም በኹኔታው ተገርመው እንዲህ አሉ፤ “በቅድሚያ እነርሱን
ማመስገን እርሱን ማመስገን እንዴት ሊኾን ይችላል? ይህ ከቶም የሚታሰብ አይደለም። በጠቀስከው ቃል ውስጥ ያለው ሐሳብ እግዚአብሔር
በወዳጆቹ ላይ ዐድሮ ድንቅ ሥራን እንደሚሠራና በዚህም እርሱ እንደሚከብር የሚገልጥ ነው እንጂ ለቅዱሳን ከሚቀርብ ምስጋና የሚጣልለትን
የምስጋና ፍርፋሪ ጠበቂ መኾኑን የሚያሳይ አይደለም። ይልቁንም በዚህ በሐዲስ ኪዳን ዘመን በሌላ ፍጡር ሳይኾን በቃልም ኾነ በተግባር
የምናደርገውን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለእግዚአብሔር እንድናደርግ ሐዋርያው ጳውሎስ በማያሻማ ኹኔታ ነግሮናል (ቈላ.
3፥16)። እርሱም፥ ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመኾኑ፥ ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ - በሰውና
በእግዚአብሔር መካከል ያለ የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ ነውና፥ ሰውንና እግዚአብሔርን ያገናኘና ያስታረቀ ነው (1ጢሞ. 2፥5)” በማለት
መለሱላቸው።
ለዚህ ጠያቂ የተሰጠው ምላሽ በቂ ቢኾንም በቀላሉ እጅ ላለመስጠት
በሚመስል አኳኋን ሌላ ጥያቄ እንደ ገና አቀረበላቸው፤ “የኔታ ጥሩ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን ግን ለብዙ ዘመናት በተገለገለችባቸው
የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት ውስጥ ለሌሎች ቅዱሳን ሰዎች እና ለመላእክት የቀረቡ መዝሙራትን እናገኛለን። ታዲያ ቅዱስ ያሬድ ተሳሳተ
ማለት እንችላለን?” አላቸው።
አለቃም፥ “የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ከእርሱ ወደ እኛ በቀጥታ እንዳልተላላፈና
በዜማውም ኾነ በድርሰቱ ንባብ ላይ ብዙ ማሻሸያ እንደ ተደረገበት ለኹላችንም የተሰወረ ባለመኾኑ አኹን የጠቀስሃቸው ድርሰቶች በቅዱስ
ያሬድ ለመደረሳቸው በበኩሌ ርግጠኛ አይደለሁም። ኾኖም ‘እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል’ ተብሎ እንደ ተጻፈ
ተላላኪ በላኪው ሐሳብ ላይ አንዳች ሳይጨምርና ሳይቀንስ መልእከቱን ለሚመለከተው ክፍል ሊያደርስ እንደሚገባው ኹሉ፥ በእግዚአብሔር
መንፈስ የሚመሩ ዘማርያንም በቃሉ ላይ አንዳች ሳይጨምሩና ሳያጐድሉ ዝማሬዎቻቸውን የሚያቀርቡት ለአምላካቸው ብቻ መኾን አለበት።
መጽሐፍ ቅዱስ ዘምሩ ብሎ የሚያዘው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ የሚከተሉት መጽሐፍ ቅዱሳውያን ጥቅሶች የሚያስረዱትም ይህንኑ ነው።
እስኪ ለአብነት ያኽል ከብሉይ ኪዳን ኹለት ከሐዲስ ኪዳንም ኹለት ማስረጃዎችን እንጥቀስ።
“የምድር ነገሥታት፥ ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥
ለጌታም ዘምሩ። በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ የኀይል ቃል የኾነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል“ (መዝ.
67/68፥32-33)።
“እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፥
ለአሕዛብም ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ኹሉ ተናገሩ” (መዝ. 104/105፥1-2)።
“የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ።
በጥበብ ኹሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” (ቈላ.
3፥16)
“በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤
ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ኹል ጊዜ ስለ ኹሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ኹሉ አመስግኑ”
(ኤፌ. 5፥19-20)።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው ተመዝግቦ
የምናገኛቸው ቅዱሳንም በዜማ ያመሰገኑት ፈጣሪያቸውን እግዚአብሔርን ብቻ ነው እንጂ ሌላ ማንንም አልነበረም። ለምሳሌ፥ ጳውሎስና
ሲላስ ስለ ወንጌል በወኅኒ ታስረውና እግራቸው በግንድ ተጠርቆ በነበሩበት ኹኔታ፥ ‘በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ
እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር’ (ሐ.ሥ. 16፥25)። “ልብ በሉ በዜማ ያመሰግኑ የነበረው
እግዚአብሔርን ነው።” አሉና ለጠቀሱት ማስረጃ አጽንዖት ሰጡ። ቀጠሉና “እኛም እነርሱን አብነት ልናደርግ ይገባል። ለዚህ ነው ሐዋርያው
በወንጌል ከተገለጠውና መጀመሪያ ካስተማሩዋቸው እውነት ያፈነገጠ ሌላ ትምህርት፥ ራሳቸውን ሐዋርያትን ጨምሮ የሰማይ መልአክ እንኳ
ወርዶ ቢያስተምራቸው እንዳይቀበሉ የገላትያን ምእመናን ያስጠነቃቃቸው (ገላ. 1፥8)።
አለቃም በጥያቄና መልሱ መዘምራኑ ዐይናቸው ጥቂት የተከፈተ መስሎ
ስለ ተሰማቸው፤ “ሌላ ጥያቄ ከሌለ ሐሳቤን ላጠቃል” አሉ። “ልጆቼ በመዝሙር ጕዳይ ከናንተ በላይ የሚመለከተው ስለማይኖር ለጥያቄያችሁ
እንደ እግዚአብሔር ቃል የሆነ ምላሽ ለመስጠት ሞክሬአለሁ። በመጨረሻም የምመክራችሁ ምክር ቢኖር ዘማርያን እንደ መኾናችሁ መጠን፥
ከዓለም ዘፋኞች በሐሳብ ተለዩ። እነርሱ የሚዘፍኑት በአብዛኛው እንደ እነርሱ ፍጡራን ለሆኑና ለተቃራኒ ጾታዎቻቸው ነው። እናንተም
የአምልኮተ እግዚአብሔር መገለጫ ከሆኑት አንዱ የሆነውን መዝሙርን የምታቀርቡት ለተፈጠሩ ሰዎችና መላእክት ከሆነ ምኑን ከእነርሱ
ተለያችሁ? እንዴትስ ዘማርያን ልትባሉ ትችላላችሁ? እውነቱን ልንገራችሁና ልጆቼ ለእግዚአብሔር ስትዘምሩ ዘማርያን፤ ለፍጡራን ስትዘምሩ
ግን አዝማሪዎች ነው የምትኾኑት።” ሲሉ አዳራሹ በሣቅና በጭብጨባ ተናጋ።
አለቃ ቀጠሉ፤ “በሀገራችን ታሪክ ዘመነ መሳፍንት በመባል የሚታወቅ
አንድ ወቅት ነበር። በዚያ ዘመን መሳፍንቱ ሀገሪቱን በአካባቢ ከፋፍለው ለየግላቸው ተቀረማምተዋት ስለ ነበር፥ በዘመኑ ለሚነግሠው
ንጉሥ የተረፈው ስም ብቻ ነበር። ምክንያቱም ሕዝቡ ከስሙ ውጭ ለንጉሡ የሚገባውን ግብር የሚገብረው በየአካባቢው ለተሾመው ለራሱ
መስፍን ነበር። ዛሬም በቤተ ክርስቲያናችን የእግዚአብሔር የአምልኮቱ መገለጫ የሆኑ ዝማሬ፥ ቅኔ፥ ስግደት፥ ወዘተ. የሚቀርቡት ለእግዚአብሔር
ብቻ ሳይኾን በየአጥቢያው ለተሠየሙ ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ነው። ግፋ ቢል ለእርሱ የሚደርሰው ከእነርሱ ተካፍሎ የሚቀረው የምስጋና
ፍርፋሪ ነው። በጥቅሉ ለእርሱ የተረፈው እግዚአብሔር የሚለው ስም ብቻ ነው።” ሲሉ የብዙዎች ዐይን እንባ አቅርሮ ይታይ ነበር።
አለቃም ከዚህ በላይ መግፋት አልፈለጉም “እግዚአብሔር የተረፈው ስሙ ብቻ ነው እንጂ ምስጋናውማ ለሌሎች ተሰጥቶበታል” የሚለው የሚታይና የሚዳሰስ እውነት በታዳሚዎቹ ልብ ውስጥ እንዲታተም ፈልገዋልና ንግግራቸውን አቁመው ከመድረኩ ወረዱ። ታዳሚው ከመቀመጫው ብድግ ብሎ ለአለቃ ያለውን አክብሮት ገለጠ። ጉባኤውም በጸሎት ከተዘጋ በኋላ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ኾነ።
በጮራ ቍጥር 46 ላይ የቀረበ
No comments:
Post a Comment