Tuesday, November 10, 2015

ከተማረ አይሳደብም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተማረ ሰው ይወዱ ነበር። ስለሆነም በርካታ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለክፍተኛ ትምህርት ወደ ውጪ አገር እየሄዱ እንዲማሩ አድርገዋል። አንድ ጊዜ ተማሪዎች የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ውጪ ሲላኩ እሳቸውን የማይወድ፣ እየዞረ ስማቸውን የሚያጠፋና የሚሳደብ አንድ ተማሪም ዕድሉን አግኝቶ ወደ ውጪ አገር ለመሄድ ተፍ ተፍ ይላል። ይህ ተማሪ ለአቡነ ቴዎፍሎስ በጎ ነገር የማያስብ መሆኑን የሚያውቁ ተቆርቋሪ ሰዎች ይቀርቧቸውና የተማሪውን ስም እየጠቀሱ፡-
“እንዴት እሱን ወደ ውጪ አገር ልከው ያስተምሩታል?” ይሏቸዋል።
“እኮ እንዴት ለምንድን ነው የማይሄደው?” በማለት ይጠይቃሉ።
“እርሱ እኮ ለእርስዎ የማይተኛ እየዞረ ስምዎን የሚያጠፋ፣ የሚሳደብ ነው” ይሏቸዋል።
“የሚሳደበው እኮ ስላልተማረ ነው፡፡ ይሂድና ይማር፤ ከተማረ አይሳደብም” አሉ ይባላል።

በጮራ ቊጥር 41 ላይ የቀረበ

Monday, November 2, 2015

ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

በዚህ ዓምድ ለአንባብያን ጥያቄዎች ምላሾች ይሰጣሉ
ጥያቄ፡- ከቀሲስ ወልዱ አስተርአየ
1ኛ. ጮራዎች ሐመር የተባለው የማኅበረ ቅዱሳን ልሳን የሆነው መጽሔት በጥርና በየካቲት 2003 ዓ.ም. ዕትሞቹ ላይ፥ “ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅና የተሐድሶዎች ቅሰጣ” በሚል ርእስ ተከታታይ ጽሑፎችን አስነብቧል። በጽሑፎቹም እናንተ የዮሐንስ አፈ ወርቅን ትምህርት መጥቀሳችሁን ኰንኖ፥ እናንተና እርሱ በትምህርት አለመመሳሰላችሁን፥ እርሱን አባታችን እያላችሁ የምትጠቅሱትም ለማደናገር እንጂ በትክክል ልጆቹ አለመሆናችሁን በስፋት ዐትቷል። ለዚህም ያሳይልኛል ያለውን ማሰረጃ ከድርሳኑ ጠቅሶ ትንታኔ ሰጥቷል። በዚህ ጕዳይ ላይ ምን ምላሽ አላችሁ?
2ኛ. ይኸው ማኅበር “የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ” በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፍ ገጽ 67 ላይ ታላቁንና በብዙ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ዘንድ አንቱ የተባሉትን ስመ ጥር ሊቅ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብን “አንተ” እያለ በማንኳሰስ ጽፏል። በዚህ ላይ አንድ ነገር ብትሉ መልካም ነው። 

1ኛ መልስ፡- በመምህርት ሲያዴ
በቅድሚያ ቀሲስ ወልዱን ስለ ጥያቄዎ ከልብ እናመሰግናለን። እርስዎ የጠቀሷቸውን መጽሔቶች ተመልክተናቸዋል። ከጥንት ጀምሮ ሐሰተኞች እውነተኞች ነን በሚል፥ የእውነተኞችን ጩኸት እየቀሙ እውነተኞችን ሐሰተኞች ሲሉና ሲያሰኙ ኖረዋል፤ ዛሬም ይኸው አካሄድ እንደ ቀጠለ ነው።