Tuesday, November 10, 2015

ከተማረ አይሳደብም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተማረ ሰው ይወዱ ነበር። ስለሆነም በርካታ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለክፍተኛ ትምህርት ወደ ውጪ አገር እየሄዱ እንዲማሩ አድርገዋል። አንድ ጊዜ ተማሪዎች የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ውጪ ሲላኩ እሳቸውን የማይወድ፣ እየዞረ ስማቸውን የሚያጠፋና የሚሳደብ አንድ ተማሪም ዕድሉን አግኝቶ ወደ ውጪ አገር ለመሄድ ተፍ ተፍ ይላል። ይህ ተማሪ ለአቡነ ቴዎፍሎስ በጎ ነገር የማያስብ መሆኑን የሚያውቁ ተቆርቋሪ ሰዎች ይቀርቧቸውና የተማሪውን ስም እየጠቀሱ፡-
“እንዴት እሱን ወደ ውጪ አገር ልከው ያስተምሩታል?” ይሏቸዋል።
“እኮ እንዴት ለምንድን ነው የማይሄደው?” በማለት ይጠይቃሉ።
“እርሱ እኮ ለእርስዎ የማይተኛ እየዞረ ስምዎን የሚያጠፋ፣ የሚሳደብ ነው” ይሏቸዋል።
“የሚሳደበው እኮ ስላልተማረ ነው፡፡ ይሂድና ይማር፤ ከተማረ አይሳደብም” አሉ ይባላል።

በጮራ ቊጥር 41 ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment